እኛና ግብጽ

Wednesday, 06 December 2017 13:16


ዳደ ደስታ

 

1) ግብጽ ምናችን ናት?


በአገር ደረጃ እምንፈራው ጠላት ምን ዓይነት ነው? መጀመርያ ‘ማነው?’ ወደሚለው እንሂድ። “ጠላት” እሚባለው ነገር “ሁኔታ” ሊሆን አይችልም፣ በምክንያትና ውጤት የሚገለጽ “ኃይል” እንጂ። ትልቁ ጉዳይህን ወይም ዓላማህን ከማደናቀፍ እስከ ማኮላሸት፣ ህልውናህንም ከመፈታተን እስከማክተም የሚሄድ ውጥኑን ለማሳካት አቅዶ እሚንቀሳቀስ ኃይል ነው። ድህነት “ሁኔታ” ነው። ስትራተጂ ነድፎ፣ ለያንዳንዱ እንቅስቃሴ መልስ እየሰጠ፣ ለማሸነፍና ላለማሸነፍ የሞት ሽረቱን እሚፍጨረጨር ኃይል አይደለም። ስለዚህ ድህነት የሁኔታዎች ውጤት እንጂ ጠላት አይደለም።


ታዲያ ለምን ‘ቀንደኛ ጠላታችን ድህነት ነው’ እንላለን? ለጠላት ተጋላጭ ስለሚያደርገን ነው፣ ሲባል ሰምቻለሁ። ይህ ግን አሳማኝ አይሆንም። እንዲያውም የተሳከረ ቅደም ተከተል ነው፣ ምክንያቱም ከድህነቱ በፊትም ቢሆን ጠላት እሚባል ነገር ነበረና ነው። ጠላት ለመባል እሚበቃው እንደ ድህነት ያለ ዓይነት ግኡዝ ነገር ሳይሆን ተጋፊ አጀንዳ ይዞ እሚንቀሳቀስ ህያው አካል (active organism) መሆን አለበት።


በሌላ በኩል ጠላትነት መጀመርያና መጨረሻ ያለው የእንቅስቃሴዎች ፍሰት ነው። ይህ ማለት ታድያ፣ ልክ እንደ ወዳጅነት፣ ጠላትነትም ነጠላ ክስተት አለያም ዘላለማዊ እርግምት አይደለም። የአንድ ወቅት ጠላትነት ወደ ወዳጅነት ሊቀየር ይችላል። ይህ ሽግግር እውን ይሆን ዘንድ እንደ ዓላማ መያዝም አለበት። ወዳጅነት ወደ ጠላትነት ቢንሸራተት ግን አንድም ክፉ ዕድል፣ አለያም ከዚህ ሁኔታ ሊጠቀም አቅዶ የሰራ ኃይል ስላለ ብቻ ነው። ለአቶ ድህነት፣ ወዳጅነትም ጠላትነትም ጉዳዩ አይደለም።


ወደ ምድረ ግብጽ ቁልቁል ከሚፈሰው የናይል ወራጅ ውሃ 85%ቱ ከኢትዮጵያ ነው ይባላል። ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ሽቅብ ከሚፈሱት ክፋቶች 85%ቱ ከግብጽ ሳይሆኑ አይቀሩም። ብዙዎቹ ውጭ-ወለድ የኢትዮጵያ ችግሮች ምንጫቸው ቢጠና ግብጽ ከመሆን አይዘልም። ለምሳሌ የአፍሪካ ቀንድ ለብዙ ዘመናት እርጋታና ሰላም የራቀው ቀጠና ሆኖ መዝለቁ። የኢትዮጵያ በዓላትና የማይሰራባቸው ቀናት መብዛታቸው ራሱ የግብጽ ተንኮል ነው በማለት አስረጅ ጠቅሰው እሚከራከሩ ምሁራን አሉ። በግብጾችም ቢሆን አይፈረድም። እርግጥ ዘላቂ አገራዊ ጥቅም ዋስትና እሚያገኘው ከወዳጅነትና ከፍትህ ነው። ‹ልክ ናቸው አይደሉም›ን ትተን ግን ኢትዮጵያን አቆርቁዞና ቀስፎ መያዝ ዋነኛ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው ስለቆጠሩት በዚያ አቅጣጫ በሙሉ አቅማቸው ቢረባረቡ እሚገርም አይሆንም። የግብጽ ጥፍሮችን ከአንገታችን ማላቀቅ ደግሞ ለኛ የህልውናና የሞት ሽረት ጉዳይ ይሆናል።

 

2) የሆነው ይህ ነው፤ ሁሌም የግብጽ አሸናፊነት - ሁሌም የኢትዮጵያ ተሸናፊነት


ከግብጾች ጋር የቆየ ታሪክ አለን። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለት የሚታወቁ ጦርነቶች ገጥመናል። ሁለቱንም ጊዜ ድል አድርገናል። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከህልፈታቸው አንድ ዓመት ገደማ ቀደም ብለው ለአንድ የውጭ ሚድያ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ “ግብጾች ድርድርን ትተው ጦርነት የመረጡ እንደሆነ ውጤቱ የነሱ ሽንፈት ሆኖ ያበቃል” የሚል አስተያየት ሰንዝረው ነበር። አክለውም፣ “ግብጾች የጦርነቱን አማራጭ ከዚህ በፊት ደጋግመው ሞክረውታል። በህይወት ተርፎ የጦርነት ዉሎው ለመተረክ የበቃ ወሬ ነጋሪ ግን አልነበረም” ሲሉ ተናገሩ። ይህ ምናልባት ወታደርና ትጥቅ በማሰለፍ የተደረጉትን ፍልሚያዎች ብቻ ስንቆጥርና ስናስታውስ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሁለቱ አገሮች መካከል በአባይ ጉዳይ ላይ በይፋ ያልተነገረና መታኮስን ያልጨመረ ስውር ጦርነት ሁለቴ ብቻ ሳይሆን ሁሌ እንደተካሄደ ነው። አባርቶም አያውቅም።


በዚያ ስውርና ያላቋረጠ ጦርነት ግን ሙሉ ለሙሉ አሸናፊዋ ግብጽ ናት። አሸናፊነቷም በግልጽ እሚታይ ነው። እሰከ ቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ከአባይ/ናይል ውሃ አንዲት ጭልፋ ስንኳ እንዳትነካ አድርጋት ቆይታለች። ግብጽ ይህን ማድረግ የቻለችበት ዘዴና አካሄድ ኢትዮጵያ ዉስጥ ችግሮች እንዲበዙና የኢትዮጵያ መንግስታትና ህዝቦች በውስጥ ችግሮች ተተብትበው ፋታ እንዲያጡ የሚያደርጓቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር ፍጥጫና ዉጥረት ዉስጥ እንድትገባ በማድረግ፣ ኢትዮጵያን የማይመለከቱ ፍርደገምድል ዉሎችና መብቶች እንደመሟገቻ ባንዲራዎች ከፍ አድርጋ በማውለብለብ፣ ዓለም አቀፍ ኃይሎችና የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እንዲለግሙ በማግባባት፣ የድርድር መዓዶች የግብጽ ጥቅሞች ማስጠበቂያ ይሆኑ ዘንድ ሙዝዝ ያሉ አሰልቺ ንትርኮች በማካሄድ፣ አስቀያሚ የኢንፎግራንዳ (ኢንፎርሜሽን+ፕሮፖጋንዳ) ዘመቻዎች በመክፈትና አስፈላጊ በመሰላት ጊዜ ደግሞ ኃይልን ጨምሮ “ማንኛውንም ዘዴ እጠቀማለሁ” እያለች በማስፈራራት ነው። መቼም አይሳካላትም እያልን ራሳችንን አናሞኝም።

 

3) የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ዳርቻዎችና ማዕከሎች


ይህ ጽሁፍ “ምስለ ኢትዮጵያን ከናይል ተፋሰስ አንጻር ስለመገንባት” ያወሳል። ይህም “የኢትዮጵያን ምስል እንደ አንዲት የተፋሰሱ ቀጠና ኃያል አገር” እንዲታይ ወይም እንዲቀረጽ ማድረግ ያስፈልጋል ከሚል ነጥብ ይነሳል። “ኃያል” እሚለው ቃል ከጡንቻ ጥንካሬ ይልቅ የበጎ አሳቢነት፣ የትብብር ፈላጊነት፣ የመርህ አጥባቂነትና የፍትህ ጠበቃነት ጥንካሬን ያመለክታል። የራስ አገራዊ ጥቅም ማስከበርም ሁሌ የጡንቻ ኃይል ጉዳይ አይደለም የፍትህ እንጂ። የኢትዮጵያን ምስል በዚህ መልክ እንዲቀረጽ የማድረጉ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም። አሁን ጥያቄው የዚህ ዓይነት ምልከታና ቅኝት የሚጠይቀው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የትኩረት ስበት ቀዳሚ ማእከሎች እሚመሰረቱት “በየትኞቹ ጉዳዮችና አካባቢዎች ላይ መሆን አለበት” እሚለው ይሆናል። ይህም ቢሆን እንዲሁ በአግባቡ ለመንደርደር ይረዳ ያህል አነሳነው እንጂ ለአሻሚ ሙግት እሚዳርግ ነጥብ ሆኖ አይደለም።


ከኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዋነኞቹና ቀዳሚዎቹ፡ 1) የናይል ወንዝ፣ የናይል ተፋሰስና ተያያዥ ጉዳዮች፥ 2) የአፍሪካ ቀንድና የቀይባህር አካባቢ፣ 3) አፍሪካና የአፍሪካ ህብረት፣ 4) ልዕለ ኃያላን፣ ዓለም አቀፍ ኃይሎችና ተቋሞቻቸው ወዘተ እያለ በተዋረድ እሚፈረጁ ናቸው። ከተጨባጭ አገራዊ ጥቅምና ወደፊት ከሚኖረው የውጭ ግንኙነት ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ከታሪክም አንጻር ሲታይ ይህ አፈራረጅ ዝንፈት የለውም።


ለናይል ተፋሰስ ከዉጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያችን አንጻር እምንሰጠው ትርጉም በኢትዮጵያ ዕይታ ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚወሰን አይደለም። የናይል ዉሃ የህልውናቸው መሰረት አድረገው እሚነሱት አገሮችና ህዝቦች እሚያደርጉትና እሚያስቡትንም ታሳቢ ያደርጋል። ለምሳሌ የግብጽ እንቅስቃሴ “ናይል ህልውናችን ነው” ከሚል አጠቃላይ መአዝን ይቃኛል። ዲፕሎማሲ የአገሮችና መንግስታት እንዲሁም ከመልቲላተራል ድርጅቶች ጋር የሚኖረውን ግንኙነታዊ ክዋኔ ወይም መስተጋብር መሳርያ ነው ካልን፣ ይህ የግብጽ አስተሳሰብ እንዳለና በቀጥታ ጉዳዩ የኢትዮጵያም የህልውና ጉዳይ እንዲሆን ግድ ይላል። በናይል ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ እምትሰጠው ትኩረት ከራስዋ እሚመነጭ ብቻ ሳይሆን ግብጽ የምትሰጠው ትኩረት ነጸብራቅ ጭምርም ሊሆን የግድ ነው።


የናይል ተፋሰስ አገሮች እሚባሉት አሁን በቁጥር አስራ አንድ ናቸው። ስለዚህ ሜዳው 11 ተጨዋቾች አሉት። የተመልካቾቹ ቁጥርና የመመልከቻው ሜዳ ግን ከተጨዋቾቹና ከመጫዎቻው ሜዳ ይልቃል። ተመልካቾቹም፣ ማለትም ኳስ ከሚነጥርበት ሜዳ ዉጭ ያለው ምህዳርም ግን ችላ እሚባል አይደለም። ያም ሆኖ ጨዋታው ላይ እሚከሰተው ሁነኛ ቁምነገር ወይም ተጽዕኖ ከሜዳው የሚመነጭ ነው። የሜዳውንም ጨዋታ ቢሆን ሁሉም ተጨዋቾች በእኩል መዋጮ እሚያመርቱት አይደለም። የጎላና ወሳኝ ሚና ከጥቂቶች ነው። እያጠበብን ስንሄድ የአንበሳ ድርሻ ይዞ ጨዋታውን በበላይነት እሚቆጣጠረውን አውራ ኃይል ለይተን እናገኘዋለን። ስለዚህም ነው ለአገራችን፣ አጠቃላይ ሁኔታዎችን በምልአት፣ ልዩ ሁኔታዎችን በትኩረት እና ወሳኝ ማእከሎች ደግሞ በሙሉ ቁጥጥር መከታተል ዋነኛው የድልና የውጤት መንገድ እሚሆነው።


የናይል ተፈሰስ ህዝቦችን በተመለከተ፣ ለሁሉም እሚጠቅም፣ ነገውን የተሻለ እሚያደርግ ቁምነገር እሚሰራው ሜዳውን በምልአተ ስፋት፣ ተጨዋቾችንም በምልአተ ቁጥር ያካተተ፣ ሁሉንም ፍላጎቶችና ስጋቶች የሚመልስ ቀመርና መግባባት የመንደፍ አስፈላጊነት አያጠያይቅም። ከህግና ከሞራላዊ መነሻ አንጻር የተፋሰሱ መሬት እያንዳንዷን አባል አገር መሬት በእኩል እሚያስብ፣ አገሮቹ ራሳቸውንም በእኩልነት እሚያይ አመለካከት መያዝ ተገቢ ነው። ከተግባራዊ አሰራርና ተጨባጭ ሚና አንጻር ሲታይ ግን ሁሉም ተጨዋችና ሁሉም የሜዳው መሬት ተመሳሳይ ፋይዳ አለው ማለት አይደለም።


የተፋሰሱ ዋና ማእከል ውሃው እሚፈስበት መስመር ወይም ባንክ ነው። አውራውን ፋይዳ የተሸከሙት አገሮች ለመለየትና እነሱ ላይ ትኩረት ለማድረግም ብዙ ውሃ እሚመነጭበትና ብዙ ውሃ እሚያልፍበት በሚል ማጥበብ ይቻላል። በዚህ ቀመር ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ዋነኞቹ ባለድርሻና የስበቱ ማእከሎች ሆነው እናገኛቸዋለን። ዋናውን የጥቅም ግጭትና ፍጥጫ እሚኖረው የራስጌ መነሻ በሆነችው ኢትዮጵያና የግርጌው መጨረሻ (መዳረሻ) በሆነችው ግብጽ መካከል መሆኑ ስለሚታወቅ የጡዘቱ ዋልታዎች ኢትዮጵያና ግብጽ ናቸው። ሆኖም፣ ሱዳን መሃል ሆና የጉተታውን ሚዛን ወዲህ ወይም ወዲያ እንዲያጋድል የማድረግ ተፈጥሯዊ ስፍራ በመያዟ እንደ አንዲት ወሳኝ ተጨዋች የዚህ ትንታኔ ትኩረት አካል ትሆናለች።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
166 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 827 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us