እርቁ ራሱ ይታረቅ!

Wednesday, 13 December 2017 12:36

በአንድነት ቶኩማ

 

በቅርቡ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦችን አንድነት ለመመለስ ወይም በአገራቱ መንግስታት መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ ይሁን ውሉ ባልታወቀ መልኩ አዲስ አበባ ላይ የሁለቱን አገራት ቀጣይ ግንኙነት በተመለከተ አንድ የውይይት ፕሮግራም ተካሂዶ ነበር።


በውይይቱ ላይም በርካታ ምሁራን ቀርበው አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ከውይይቱ ማግስት ደግሞ ለንባብ የበቃ አንድ ጋዜጣ (ህዳር 16 ቀን 2010 ዓ/ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ) የፊት ገፅ ላይ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ተስፋና ስጋት?” በሚል ርዕስ አምስት ሰዎች ቃለመጠይቅ አድርገዋል። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ታዋቂ ሰዎችም አሉ። ሁለት ታዋቂ ልሂቃንንም ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። አንደኛው ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ናቸው። “ሁለቱ ህዝቦች የተለያዩት በመሪዎች ራዕይ ማጣት ነው” ይላል የተሰጠው ሃይለ ቃሉ። ራዕይ ያሉት ርዕይ ለማለት ነው። ሌላኛው ልሂቅ ደግሞ ፕሮፌሴር መድሀኔ ታደሠ ናቸው። እንደ ጋዜጣው ኃይለ ቃል አዘጋገብ ከሆነ “ኤርትራውያን ይጠሉናል የሚባለው በጥናት አልተረጋገጠም” ይሉናል።


አቶ ሀብቶም ገብረ ሊባኖስ ደግሞ ከሌሎች ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው አስተያየት ሰጪዎች አንዱ ሲሆኑ እሳቸውም “መንግስታት ያልፋሉ ሕዝብ ይቀጥላል።” በሚል ኃይል ቃል የታጀበ ነበር ቃለ መጠይቃቸው። ኤርትራዊው ጋዜጠኛ የተባሉት ግለሰብ “የሁለቱ አገራት ህዝቦች ጠብና ጥላቻ የላቸውም።” ይላሉ። ሌላው ኤርትራዊ ስደተኛ የተባሉት ደግሞ “የሁለቱ መንግስታት ችግር ሰለባው ህዝቡ ነው።” ይሉናል። በመግቢያው ገፅ ላይ ከተቀመጠው ሀሳብ ሳንወጣ ብናየው ስጋት የለውም ተስፋ እንጂ። ወደ ውስጥ ገብተን ጽሁፉን በፈተሸን ጊዜ ግን የሚገጥሙን ብዙ ፈታኝ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ጥያቄዎችና ቃለመጠይቆች በግርድፉ ማየት የሚገባ አይመስለኝም። በውጉ ወግ አስይዞ ማየት እና መፈተሸ ይገባናል።


ኢትዮጵያና ኤርትራ አብረው ሰላሙንም መከራውንም ተጋርተው ኖረዋል። ይህ ሃቅ ነው። ያም ሆኖ ከብዙ ዘመን የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ተለያይተዋል። ይህም ሌላ ሃቅ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይፈልግ ኤርትራውያን ፈልገው ጥለውን ሄደዋል። ይህም ሃቅ ነው። ሲሄዱ የፍች ድንበር፣ ወግና ማዕረግ ያልተደረገበት ነበር። ይህ ደግሞ ሌላ ሃቅ። ህዝቡ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትግራይና ከሄዱት የኤርትራ ሕዝብ በስተቀር በቅሬታ ሳይመርቅ ልኳቸዋል። ተገዶ ነው። ወዶ አይምሰላችሁ። አንድ ጥልቅ ምልክታ የነበራቸው ልሂቅ መሄድ የለባቸውም ከሄዱ ግን አካሄዳቸው ድንበር ይሠራለት ብለው ነበር። ይህን በማለታቸው እኒህ ግለሰብ ‹‹የነፍጠኛው ሥርዓት ርዝራዥ›› ተባሉ። ‹‹እኛና እነሱ የሚባል የለንም። እኛ አንጣላም የጦርነት ናፋቂዎች ወሬ ነው›› ተብሎ ተነገረ። ይሁን እንጂ የማይቀረው ጦርነት መጣ። ሁለቱም አገሮች እንደገና ተዋጉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኤርትራውያን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርሱት ጣልቃ ገብነት አስቸግሮን ነበር። አሁን ግን ቆመ ተባለ። ብዙዎቻችን ኤርትራውያን ጣልቃ መግባታቸውን እንኳ አናውቅም ነበር። ከዚያ ወዲያ ጦርነትም ሆነ ሰላም የለም።


ይህ ሁለተኛው መለያየት አቶ ገብሩ አስራት በመጽሓፋቸው እንደሚሉት የመጣው የኤርትራውያን የበላይ ለመሆን ካላቸው ፍላጎት ነው። ሁሉን የመቆጣጠር አባዜ ውጤት ነበር ሲሉም ጽፈዋል። የፓሊቲካል ኢኮኖሚ ውድድር እና ከኢትዮጵያ ለመጠቀም የመፈለግ አዝማሚያ ነው ችግር የፈጠረው ሲሉ ይሞግታሉ። በተለይም ከትግራይ ክልል ጋር የነበራቸው ጊዜያዊ ፍቅር፣ ውለታ እና ዝምድና ያመጣው የተጠቃሚነት መንፈስ የወለደው ችግር ነው። ደራሲው ዋናውን የወቀሳ ድርሻ ሻዕቢያና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው መውሰድ ያለባቸው ይላሉ። ይህን በስፋት ያራምዱ የነበሩት ከሕወሓት የወጡ አንጃዎች ነበሩ።


ይሁን እንጂ ሰሞኑን እየስማን ያለነው ሁሉንም ነገር ረስቶ አዲስ ነገር የተፈለገ ይመስላል። የተጀመረው ስለ ሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ውይይት ወይም እንቅስቃሴ አንድ ነገር ያጭራል። በመጀመሪያ ውይይቱ ይበል የሚያስብል ነው። ለምን ዛሬ? ለምን ዘንድሮ? እነማን ናቸው የውይይቱን መነሻ ያፈለቁት? የሚለውን ማጤን ተገቢ ቢሆንም በመጀመሪያ ሁለቱን ልሂቃን እጅግ የማከብራቸው መሆኔ ይሰመርበት። ኤርትራውያን ወንድሞቼንም ሳላሞጋግስ አላልፍም። ጥሩ ሃሳብ ይዘው መጥተዋልና። የመጣውን ሃሳብ መፈተሸ ስለሚገባን ብቻ ነው ይህን የምፅፈው። በግሌ ጠብም፣ ግጭትም፣ ትውውቅም የለኝም። አለቀ።


በመሆኑም ሃሳብን በሃሳብ ለመሞገት ብቻ ነው ይህን ሃሳብ የሰነዘርኩት። የታሪክ ባለሙያ አይደለሁም። ፖለቲካም የእኔ ሙያ አይደለም። ዜጋ ነኝ። የዜግነት ዐይኔ፣ ጆሮዬ እና ልቦናዬ ነው ይህን የሚያፅፈኝ። ሳንፈታተሸ ዝም ብሎ ሰላም ሰለተባለ ብቻ እንግባባለን ማለት አይደለም። ከዚህ በሚከተሉት ነጥቦች ቃለ መጥይቁን አሄሳለሁ።

1ኛ ሁሉ ለእኔነት (Pan-selfism)
ሁሉ ለእኔነት (Pan-selfism) የሚባል ነገር ሰምቼ አላውቅም። እኔው ከአዕምሮዬ አፍልቂያት ነው። ከዚህ በፊት ተብሎ እንደሆን አላውቅምና ይቅርታ አድርጉልኝ። ሁሉ የሚለውን (Pan) ከሚለው ተዋስኩ። ፓንአፍሪካኒዚም ስንል (አንድ አፍሪካ) ለማለት ነው። ፓንቲዚም ማለት ደግሞ ሁሉ አምላክነት ማለት ነው። ፓን (Pan) ሁሉ ማለትም ሳይሆን አይቀርምና። ፓንሰልፊዝም (ሁሉ ለእኔነት) የሚለውን የፈለሰፍኩት በዚህ መንገድ ነው። ትርጉሙ ሁሉ ነገር ለእኔ ጥቅም ይዋል ከማለት ተነስቶ የሚደረግ እርምጃ፣ ድርድር ወይም መቀራረብን ነው በዚህ የሰየምኩት። የግል ጉምጀታ ልትሉትም ትችላላችሁ። “ተማልሎ ራስ” (Quest for self) ማለትም ይቻላል።


በዚህ ውይይት ላይ የተሳተፉም ሆነ መድረኩን ያዘጋጁ ሰዎች ከንግግራቸው የሚነቀሱ ነገሮች ብዙ ናቸው። በንግግራቸው “ሁሉ ለእኔነት አይቻለሁ።” ፓንሴልፊዝም። በነገራችን ላይ እኔ ምን እጠቀማለሁ ሌላውስ ምን ያገኛል? የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው። ፓን ሰልፊዝም ግን ይህን ሰናይ ነገር የሚያጣጥል ነው። ከዚህ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምን እንጠቀማለን? ሳይሆን ምን አገኛለሁ? ብቻ ከሆነ ችግር ነው። ለምሳሌ ኤርትራውያን “ኮንፌዴርሽንን” ለመቀበል ዝግጁ ይመስላሉ። ይህን አቋም ከያዙ ቆይተዋል። ጥያቄው በኮንፌዴሬሽን ብንቀላቀል ማን ይጠቀማል? ሳይሆን ኢትዮጵያስ ምን ትጠቀማለች? ማለት ተገቢ ነው። ሀብቶም ገብረ ሊባኖስ እንዳሰቀመጡት እዛ ያለው ሕዝብ “በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያውያን ወገኑ ጋር ሰላምና አንድነት መፍጠር እንደሚፈልግ በደንብ እናውቃለን” ይላሉ። ምክንያቱን ሲያስቀምጡ ደግሞ “ሲሰደዱ መጠለያ እያደረጉት ያሉት ኢትዮጵያን ነው” ይሉናል። ይህ ሁሉ ለእኔነት ነው። ፓንሰልፊዝም። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የተፈለገው መጠለያ የሆነች አገር ሰለሆነች ከሆነ ጥያቄ አለ።


ይህ ሃሳብ ግን የእሳቸው ብቻ አይደለም። የመንግስታችንም ነው። ‹‹እኛ አንዲያውም የምንፈልገው ጉዳይ ነው። ይህ ከሕዝብ ከመጣ ደግ ነው አሉን›› ይሉናል ተናጋሪው። ሌላው ሁሌ ለእኔነት ማለት ይህ ነው።


ተመልከቱ የመገንጠሉን ጥያቄ ያቀረበው ይኼ መንግስት ነው። ጦርነት ውስጥ የገባው እሱው ነው። የአሁኑን እንቅስቃሴ ድጋፍ ሰጭው እሱ ነው። የዜጎች የመሰብሰብ መብት “ተጠርንፎ” እንዴት ለዚህ እንቅስቃሴ በቀላሉ የመሰብሰብ መብት ተሰጠ? ፓን ሰልፊዝም በውስጡ ስላለ ነው። የመንግስት እርዳታው የመጣው ፖለቲከኞች የሚጠቀሙትን ነገር አድብተው መስሎኝ ነው። እኒህ ተናጋሪ “ሉዓላዊት ኤርትራና ሉዓላዊት ኢትዮጵያ” የምትልም ሃረግ ጨምረዋል። በዚህ ንግግር የኛውም መንግስት ሆነ ያኛው መንግስት ሃሳቡን እንዲደግፉት የተሰራ ቋንቋዊ የፖለቲካ ጨዋታ ይመስላል።


አንደኛው ተናጋሪ ደግሞ ˝ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃድና ወንድምነት ካሳዩ ነገሮች ይለወጣሉ" ብለዋል። በእሳቸውም ንግግር የኤርትራውያን ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል የሚል እንደምታ ይመስላል። ለምንድን ነው ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃድ እንዲያሳዩ የተጠበቀው “ብዙ ኤርትራውያን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ….” ይሉናል እኒህ ምሁር። ታድያ? So what? ይላሉ ፈረንጆች። ምን ይሁን ለማለት ነው። ብዙ ኢትዮጵያዊያን በስደት ሌላ አገር ይኖራሉ። ኢትዮጵያዊ ያሉበት አገር ጋር አንድ እንሁን ተብሎ ይሰበካልን? ኤርትራዊያን ምርጫ አጥተውስ ቢሆን የመጡት? መሸጋገሪያ ቀጠና ሆነንስ ቢሆን? ምን የተጠና መልስ አላቸው? አሁንም የኤርትራውያንን ጥቅም ማስጠበቅ ነው ፍላጎቱ? ለምን ኢትዮጵያውያን በጎ ፍቃድ ያሳዩ ዘንድ ተፈለገ?


አልፈልግም ያሉት እነሱ ናቸው። ሃቁ ይህ ነው። ከኛ ጋር ሳሉ ተበድለው ይሆናል። እርቅ መደረግ ያለበት በትክክል ነው። የኢትዮጵያውያን ስሜትስ ተጠንቷል? አንድ የማደንቃቸው ልሂቅ ‹‹ኢትዮጵያ የጋለሞታ አገር አይደለችም›› ብለዋል። በመሆኑም ነው የበሩ አከፋፈት ወሳኝ የሆነው። በሩ ተንኳኩቶ ነው መከፈት ያለበት። ተበርግዶ መሆን የለበትም።


በረከት አብርሃም የተባሉትም ግለሰብ “እኔ እዚህ ብሆንም ሌሎች ኤርትራውያን እህት ወንድሞቼ እዚያው በችግር ላይ ይገኛሉ።” ብለዋል። ምን ማለት ነው? ይህ ሕዝብ ከሕዝብ ግንኙነት ጋር ምን አገናኘው? ተናጋሪው የሸሹት “የመከራ ግፍ” ስለደረሰባቸው መስለኝ። በመንግስታቸው ላይ ያለው ቅሬታ የሚፈታው በራሰቸው በኤርትራውያን ነው። መንግስትን መቀየር ካስፈለገ ታግለው መቀየር ያስፈልግ እንደሆን እንጂ ይህ ከእርቁ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ይህ አስተሳሰብ ‹‹የሁሉ ለእኔነት›› ነው። ሌላኛው ተናጋሪ “በችግር ጊዜ ተሰደን የመጣነው እንግዲህ ወደ ኢትዮጵያ ነው” ይሉናል። ሌላኛው ተናጋሪ ደግሞ በኤርትራም በኢትዮጵያም ውስጥ ያለው የእርስ በርስ ችግር የሁለቱ መንግስታት ነፀብራቅ ነው ይላሉ። የኢትዮጵያ ጉዳይ የኤርትራ የውስጥ ጉዳይ ነው ይሉናል። አክለውም የኤርትራም ጉዳይ እንደዚያው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የሁለት መንግስታት አለመግባባት ችግር ነው እያሉን ነው። የውስጥ ችግርን ለማጥፋት ወይም ለማፈን ከኤርትራ ጋር እንታረቅ ነው የአንደምታው ትርጓሜ። የውስጡን ለመያዝ፣ የእርስ በርሱን ችግር ለመቆጣጠር ሲባል ሁለቱ ህዝቦች ይታረቁ የሚል ይመስላል። ሁሉ ለእኔነት ነው የምለው ለዚያ ነው። “ሁሉ ለእኔነት” ሳይሆን ወደ ‹‹ሁሉ ለእኛነት›› ይለወጥ።

 

2ኛ ሐሳዊ ሥብከተ ኑባሬ ይቅር!
በዚህ በሁለተኛው ክፍል አራት ቃላት አሉ። ሐሳዊ የሚለው የመጀመሪያው ቃል ነው። ትርጉሙ ውሸት፣ ክህደት፣ ቅጥፈት እና የመሣሰሉትን የሚያካትት ማለት ነው። ሁለተኛው ሥብከት ማለት ሲሆን ንግግር፣ ትንታኔ፣ ሰበካ፣ ቅስቀሳ፣ በንግግር አዕምሮን ማቅናት ማለት ነው። ኑባሬ ማለት ደግሞ ያለው የጊዜው ሁኔታ ማለት ነው። በተጨባጭ ያለው ነገር ለማለትም ነው።


በቃለ ምልልሱ ላይ ያየሁት ነገር ቢኖር “ዋሽቶ ማስታረቅ” የሚል ይመስላል። ለምሳሌ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ጥላቻ የለም ተብሏል። ዝቅ ብሎ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ፈቃደኝነት ይስተካከላል ይባላል። ምን ማለት ነው? በሌላ በኩል ጥላቻ የለም። በጥናትም አልተረጋገጠም ይባላል። አትርሱ ሁለቱ ህዝቦች 30 ዓመት እኮ ተዋግተዋል። የአዲሱ ትውልድ አካል የሆኑት እኮ በቃለ መጠይቃቸው ደርግና የአጼ ኃይለስላሴን መንግስት በደል አድርሶብናል የሚል አንድምታ አላቸው። ጠብ አለ ማለት ነው። ይህ አይካድም። ቁርሾውን መካድ ነውር ነው። ጥላቻ አለ። ኢትዮጵያውያንም ተስድበዋል። ከኢትዮጵያም አንድ የገዢ መደብ ነው የተባለ ብሔር ተዋርዷል። ኤርትራውያን ከኢትዮጵያዊያን ጋር መኖር ባርነት ነው ብለው መርጠዋል እኮ! ዝም ብለን ገዢዎችን ብቻ መንቀፍ አይገባም። የሻቢያ ጦር ከየት የመጣ ነው? ወጣቱ ከየት የተወለደ ነው? ከ‹‹ማርስ›› አይደለም። እርቁን ማካሔድ ከተፈለገ የሐሳዊ መሲህ (Demagoge) ሥነ ሥብከት ይቁም! እውነታውን መቀበል ያሻል። ወይም አምኖ እርቁን ማካሄድ ተገቢ ነው።

 

3ኛ ሕሡም አካሔድ (ugly strategy)
የማርክሳዊ ሌኒናዊ መዝገበ ቃላት ‹‹ሕሡም›› የሚለውን እንዲህ ያብራራዋል። “በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ሕሡም የሚያመለክተው የሰው ነፃ እንቅስቃሴ መቀጨቱን ወይም በሚያጣምሙና በሚያዛቡ ማህበራዊ ሀይሎች ሥርዓት ስር መውድቁን ነው። በዚህም ፍችው መሠረት ሕሡም የመደብ ትግል ስሜታዊ ክስተት ነው። በአንፃሩም በስነውበት ውስጥ የሕሡም መታየትና መገለጽ በሰዎች ዘንድ የውበትን ፍላጎት ይፈጥራል፤ ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉትንም ትግል ያጠናክራል።”


ከዚህ በመነሳት ነው ሕሡም አካሔድ የሚለውን ሀሳብ ለማቅረብ የሞከርኩት። አስቀያሚ አካሔድ ማለት ነው። ወይም ትክክልነቱን የሳተ ሀሳብ ወይም አቀራረብ ነው። በዚህ በአራቱም ቃለ መጠይቅ አድራጊዎች ውስጥ የተመለከትኳቸው ወሳኝ ቃላት “ሰላም” እና “መተባበር” የሚል አደናጋሪ እና ትርጉም የሚሹ ጉዳዮች ተገልፀዋል። “ሰላም” ሲባል ምን ማለት ነው? መተባበርስ እስከ ምን ድረስ ነው? ባንተባበር የምናጣው ምንድን ነው? ብንተባበርስ የምናገኘው ምንድን ነው? መንግስት እርቁን ለማድረግ ለምን ፈለገ? ምን ሊጠቀም ፈልጎ ነው? በሌላ በኩል የኤርትራው መንግስት ምን ችግር ገጥሞት ነው ከአቋሙ ውጭ ለመደራደር የፈለገው? ወይም መንግስትን ምን አለሳለሰው?


የድርድሩ መንፈስ “ንጽህናን” በምን እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ከህዝቡ በስተጀርባ ሊሰራ የታሰበው ነገር ምንድን ነው? የመገንጠል ጥያቄን ተግባራዊ ሊያድርግ ምርጫ የተሰጠው ለኤርትራዊያን እንጂ ለኢትጵያዊያን አልነበርም? ለምን? ፕሮፌሰሩስ ለምን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከሁለቱ መንግስታት አገዛዝ መረጋጋት ጋር ሊያገናኙት ፈለጉ? ሕሡም አካሔድ ቢኖርስ? ደጋግሞ ማጥናት ይጠይቃል።


አንደኛው ቃለ መጠይቅ ተደራጊ ሲናገሩ “ኦፊሴላዊ ደብዳቤ ከኢትዮጵያ መንግስት ወደ ኤርትራ ይላካል" ይሉናል። አስተውሉ እኒህ ሰው የትግራይ ወጣቶች መሪ ነበርኩ እንዳሉ። ይቀጥሉና “ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ ትልቅ የሰላምና የፀጥታ ካውንስል ይቋቋምና የካውንስሉ መሪ ፕሮፌሰር መድሀኔ ታደሰ ይሆናል” ይሉናል። ማን ሾማቸው? ቀድመው ለምን ሹመቱን አከናነቧቸው? ዲሞክራሲያዊ አካሄድ አይደለም። ለምን ምርጫ አይደረግም? ደግሞስ ለምን ተደራዳሪዎቹ የአንድ ክልል ሰዎች ብቻ እንዲሆኑ ተፍለገ? የቆየው ደባ ተቀጥላ አለመሆኑን በምን እናረጋግጣለን?


በሀርመኒ ሆቴል የተደረገው ጉባዔ በክልል አንድ ሰዎች ተዋናይነት ዳግመኛ መጀመሩ ችግር አለበት የሚሉ ቢኖሩስ? የኤርትራን መገንጠል ሲዋዋሉ ህወሀቶች እንጂ ሌሎች ህዝቦች አልነበሩም። አሰብንም ሰደራደሩ ማን ምን ያውቅ ነበር? ዛሬስ ምን ማረጋገጫ አለን? ሕሡም አካሄድ ይታየኛል። እርቁ ከኢትዮጵያ ጋር ወይሰ ከትግራይ ክልል ሕዝብ ጋር? ፍርጥርጥ ብሎ ይውጣ ወይም ይነገር። ለምን ዛሬ ተፈለገ? ጥድፊያው ምንድን ነው? በኋላ ማጣፊያው እንዳይጠፋ። በሕሡም መንገድ ውስጥ ምንአልባት እውነተኛውን ነገር መፈለግ ይመጣ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።

 

4ኛ ድብድብስ ምናባዊ ግብ (open-ended imaginative goal)
ምናብ ማለት በሀሳብ የተወጠነ ወይም የተቃዠ ነገር ማለት ነው። የዚህ እንቅስቃሴ ምናባዊ ሆነ ተግባራዊ ግብ “ሰላምና መተባበር” ነው የሚመስለው። ልብ አድርጉ ‹‹መሰለኝ›› ነው። በእርግጥ ሰላምና መተባበር ትልቅ ግብ ነው። ቢሆንም እነዚህ ቃላት መተርጎም ይገባቸዋል። ከሁሉም ቃለ መጠይቅ እንደተመለከትኩት ምናባዊ ግቡ ምንድን ቢባል የሁሉም ተመሳሳይ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ሲደግፍ ግቡ ምንድን ነው? ግማሽ መንገድ መሄድና መደራደር ነው ይሉናል።


ድርድሩ እንግዲህ በምን በምን ጉዳይ እንደሆነ አይታወቅም። ባድሜን ለመስጠት መደራደር ሊሆን ይችላል? ግልፅ አይደለም። ይህ ነገር ሳይጀምር የኢትዮጵያ መንግስት መደራደር መፈለጋቸውን የኤርትራውያን ስደተኛ ሲናገሩ ‹‹ኤርትራ እምቢ ብላ ነው ድርድሩ የቀረው›› ይሉናል። የፕሮፌሰሩም ምናባዊ ግብ ጥላቻን መቀነስ ወይስ የአገርን መንግስታት አገዛዝ ማረጋጋት ይሁን አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ ድርድሩ ይሳካል ይሉናል አደራዳሪዎቹ። መልካም ዜና ነው።


የዶ/ር ያዕቆብም ምናባዊ ግባቸው “ሰላምና መተባበር” ይመስላል። ደስ ቢልም ተድበስብሷል። የበለጠ ትብብር የተባለውም ይብራራ። በርግጥ ዶ/ር ያዕቆብ ሁለቱ አገሮች አንድ ቢሆኑ የሚል እውቀታዊ ቁጭት አለባቸው። ኮንፌዴሬሽን፣ ፌዴሬሽን እና አንድነት ሊመጣ ይችላል የሚለውም ንግግራቸው ጠቋሚ ነገር አለው።


ሰላምና መተባበር የሚለው ቃል ሰፊ ነው። ለምሳሌ ሰላምና መተባበር ከጅቡቲ ጋር እያደረግን መሰለኝ። ከኬኒያም ጭምር። የግድ ከኤርትራ ጋር ሰላምና መተባበር ከሌለን ችግር ላይ ነን ማለት ነው ያለው ማነው የሚል ቢመጣ ምን መልስ አለ? በርግጥ ጦርነት የሚያመጣው መጥፎ ነገር እንዳለ ሆኖ። ልማቱ እና ዲሞክራሲው የተስተጓጎለው በዚህ ምክንያት ነው የሚል ያለው አንድምታ አንዱ ተናጋሪ ተናግረዋል። ‹‹የኤርትራ መንግስት መሪ እስከ ዛሬ ከጎረቤት አገር ጋር የሄድንበት መንገድ ትክክል አይደለም ስላሉ እርቁ የሚቀል ይመስለኛል›› ብለዋል ሌላኛው። በአቶ ኢሳያስ በኩልም የተድበሰበሰ ምናባዊ ግብ ይታያል። እንደ ተናጋሪው ንግግር ከሆነ ፕሬዜዳንት ኢሳያስ ከጎረቤት አገር ሰላም መጀመር አለብን ብለዋል። በመንገድም መያያዝ አለብን እሱንም መጀመር ያለብን ከኢትዮጵያ ነው ብለዋል ይላሉ። የኢኮኖሚ ትብብር ነው። እሳቸው ብቻ ስለፈለጉ መሆን ያለበት አይመስለኝም። ፕሮፌሰሩም ቢሆኑ ‹‹የዚህ እንቅስቃሴ ዋና ግቡ በታሪክ እና በእውቀት የተደገፈ ግንዛቤ መፍጠር ነው›› ይሉናል። ከዚያስ? የምናየው ይሆናል እንደማይባል ተስፋ አለኝ። አገሪቱ እና ፖሊሲዋ የሙከራ አይደሉም። የሙከራም የመከራም እንዳይሆን ቁጭ ብሎ ማሰብ ይገባል። ተድበስብሶ እና ተዘናግቶ መጀመር ልክ አይደለም።


“ኢትዮጵያዊያንን ኤርትራዊያን አይወዷቸውም” ይባላል የሚለው ጥያቄ ለምን እንዲጎላ ተፈለገ? ኤርትራውያን እንዲወዱን ማድረግ ነው እንዴ ምናባዊ ግቡ? የተቋጠረን ቂም መፍታት። ወይስ አገዛዞችን ማሰንበት? ወይስ ፌዴሬሽን? ወይስ ኮንፌዴሬሽን? ወይስ አንድነት? የአሰብን ባለቤትነትን ወይም ተጠቃሚነትን ማረጋገጥስ ምን ስፍራ አለው? ምንድን ነው ምናባዊ ግቡ? ተድበስብሷል።


ያስገርማል። አብረን ስንኖር ተድበሰብሶ፣ የአቡነ አረጋዊ ማህበር ጠበል አብረን ስንጠጣ ተድበስብሶ፣ ወንድሞቻችን ከእኛ ሲገነጠሉ ተደስበስብሶ፣ አጋር ስንፈልግ ተድበስብሶ፣ በሽምቅ ውጊያው ጊዜ ስንተባበር ተድበስብሶ። በአንድ ሕዝብ ላይ ስንዘምት ተድበስብሶ! አሁን ደግሞ ውይይቱ ተደበስብሶ ለምን ይሆናል። ካውንስሉ የሚቋቋመው በኢትዮጵያ ስም ከሆነ ግልፁ ነገር የትግራይ ልጆችን ብቻ መሪ አድርጎ በመወከል መደራደር ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው አይፈልጉም። አሰብን ያስወሰደውን የክልሉን ፓርቲ ማመን ይከብዳል። ለማመን ይከብደናል የተባለውም ፕሮፌሰሩንም ጨምሮ ነው። ለምሳሌ ውክልናው ትክክል አይደለም የሚሉ ቢመጡ ምን ይሆን መልሳችሁ? ይታሰብበት።


እርቁ በኢትዮጵያ ስም የሚደረግ የኤርትራና የትግራይ እርቅ ነው? ወይስ ሌላ? ይሄን ለይተን የምናውቀው ምናባዊ ግቡ በግልፅ ሲቀመጥ ነው። በእርግጥ ተጋባዥ እንግዶች ግቡ አንድነት ነው ሊሉን ይችላሉ። ዋና አንቀሳቃሽ አባላት ግን “…የእኛ የሉዓላዊት ኢትዮጵያ እና የሉዓላዊት ኤርትራ ህዝቦችን አንድነትና ሰላም ለማምጣት ሲሆን…” ይላሉ። አንድነት የሚለው ቃል እዚህ ጋር ለምን ተሰነቀረ? ምን ማለት ነው? ሉዓላዊት የሚለው ቃልን ምን አመጣው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሆነ ወሳኙ ፕሮፌሰሩን የካውንስሉ መሪ አድርጎ መቼ መረጣቸው። ሌላ ‹‹አስፈላጊ ምርጫ አድራጊ ወይም ባላባት የሆነ ሕዝብ›› ካለ አላውቅም። ግቡን አጥሩት። መንገዱን ንፁህ አድርጉት። በብርሃን መንገድ ውስጥ መደነቃቀፍ የለም። የጨለማ መንገድ ብቻ ነው ብዙ እንቅፋት ያለበት።

5ኛ ዳግማዊ መድሎ ፡-“ኢትዮጵያ” የመሸፈኛ ካባ…!


ዳግማዊ መድሎ ሲባል ምን ማለት ነው? ዳግማዊ መድሎ አለ ሲባል የመጀመሪያ መድሎ ቀደም ሲል ነበር ማለት ነው። የመጀመሪያው መድሎ ምናልባትም አሜሪካ፣ ህወሀት፣ ሻዕቢያ እና ኦነግ ሰፊውን ሕዝብ አግልለው የወሰኑት ውሳኔን የሚያመለክት ነው። በዚህ በመጀመሪያው መድሎ (Seggregation) ጊዜ አብዛኞቹ የአሁኖቹ ወጣት ገዥዎች ዋና ተዋናይ አልነበሩም ለማለት ነው። ማስታወስ ግን ግድ ይላቸዋል። ያን ጊዜ በእውቀትም በእድሜም ‹‹ጨቅላ›› ሊሆኑ ይችላሉ። ቢሆንም ግን ድርጅታቸው ዋና ተዋናይ ነበር። ዛሬ ግን ዳግማዊ መድሎውን “ኢትዮጵያ”ን የመሸፈኛ ካባ ማላበስ የሚፈልጉ ሀይሎች ካሉ መቃወም ይገባቸዋል። የአገር ጉዳይ ነውና።


ተመልከቱ “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት” ይሉናል ተደራዳሪዎች። በአንድ በኩል “መንግስት መርቆ ልኮናል ሞራልም ሆኖናል” ሲሉ ያክላሉ። የትግራይ ወጣቶች መሪ የነበሩ ሰው መንግስት የሚልከውን ደብዳቤ እና አደራዳሪ ያቀርቡልናል። የሚቋቋመው ካውንስልም የካውንስሉን መሪ መርጦ ነው የጀመረው። ይህ መጠርጠር ይኖርበታል። ዶሮን ሲያታልሏት እንዲሉ “ኢትዮጵያ” ካባ ሆናስ ቢሆን? የመገንጠል ዋና ተዋናይ የነበረ ድርጅት እንዴት ደስ ብሎት የአንድነት ሰባኪ ሊሆን ይችላል? “ሕዝብ ከሕዝብ ሲታረቅ መንግስት ይታረቃሉ” ይላሉ አንደኛው ተናጋሪ። ይህ ሃሳብ ደግሞ ሌላ ነው። ሕዝብ ከሕዝብ አስታርቆ አገዛዞችን ማስታረቅ ነው እንዴ ግቡ? የኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ያላት ፖሊሲ ሰላም ወይም መተባበር የሆነበት ምን ተፈልጎ ነው? ዛሬ ከኢትዮጵያዊያን ጋር መታረቅ የሚገባቸው የስንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያውም ኢትዮጵያዊያን እያሉ ልሂቃኑ ለምን እዚያ ሄደው መዳከር ፈለጉ? ዳግማዊ መድሎ እንዳይሆን ይጠና። ደጋግመው ያጠኑት ዘንድ ያሻል።

 

6ኛ ኢትዮጵያ የሂደቱ አሻንጉሊት (Puppet)
ኢትዮጵያ አሻንጉሊት ሆና አታውቅም። በልጆቿ ግን ብዙ ጊዜ አሻንጉሊት ተደርጋለች። አሰብ የማናት? የሚለው መጽሓፍ ቢያንስ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የህወሀት አሻንጉሊት እንደነበረች ያረጋግጥልናል። አሁንም የሒደቱ አሻንጉሊት እንድትሆን እየተፈለገ ይመስላል። ለምሳሌ የመንግስት ይሉኝታ እና ድጋፍ ‹‹ኢትዮጵያ›› የገዥው ፓርቲ አሻንጉሊት እንድትሆን የታቀደች ይመስላል። የስደተኞችም አሻንጉሊት ልትሆን ትችላለች። የህወሀት አሻንጉሊት ልትሆን ትችላለች። ጥርጣሬ አይደለም። በቃለ መጠይቁም ውስጥ የተንፀባረቀው ሀሳብ ይኼ ነው። ቃለ መጠይቁ ይህን ነው የሚያሳየው። እርቁ ፕሮግራም ነው። ግቡ ምንድን ነው? ድብስብሱን ዓላማ ማወቅ ያስፈልጋል የሚባለው ለዚህ ነው። የተከደነው ይገለጥ። የተሸፈነው ራቁቱን ይውጣ። ከሌለም ‹‹ምንም ድብቅ ነገር የለም›› ይባል። የኤርትራ መንግስት ከውስጥ ምን ችግር ገጥሞት ነው ድርድር የሚፈልገው? ይጠና። ሰላም ከሆነ ሻሎም ይባል።


ይቀጥላል!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
130 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1042 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us