በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው ስርገት መነሻው ከየት ነው?

Wednesday, 13 December 2017 12:47


በሳምሶን ደሣለኝ

 

ማጣቀሻዎች እንደሚያሳዩት፤ ፖለቲካ፤ የኅብረተሰብ አደረጃጀት፣ የመንግስት ይዘትን፣ ዓይነትን፣ ቅርፅንና ተግባርን፣ መደቦችና የኅብረተሰብቡ ክፍሎች መሰረተዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ትግል እና በመንግስትታት መካከል የሚፈጠሩትን ግንኙነቶች ማለትም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በሚመለከት የተወሰነ መደብ የሚኖረው ንድፈ ሐሳባዊ ግንዛቤና ከዚህ የሚመነጨውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያጠቃልላል።


ፖለቲካ ከመንግስት ሕልውና ጋር የሚገናኝ ነው። ፖለቲካ ከፍተኛው የኢኮኖሚ መሰረት መገለጫ ነው፤ ይህ ማለት ግን ፖለቲካው በኢኮኖሚው ላይ ምንም ተፅዕኖ የማያደርግና፣ የኢኮኖሚው ነጸብራቅ ብቻ የሆነ ማለት አይደለም።


ከላይ ከሰፈሩት ፍሬ ነገሮች አንፃር፣ ገዢው ፓርቲ የተጨቆንኑ ሕዝቦችን በማስተባበር የበላይነታቸውን የሚያረጋግጡበት ርዕዮት በመያዝ፣ ርዕዮቱን የሚያስቀጥሉበት ማሕበራዊ መሰረቶችን በማመቻቸት እና መሰረታዊ ለውጦችን በመዘርጋት የፖለቲካ ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩ ማስቻሉን በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው የአደባባይ ሚስጥር ነው። በአንፃሩ ሌሎች ወገኖች “አዲስ ገዢ እንጂ ለውጥ አልመጣም” ሲሉ ይሞግታሉ።


በተለይ ገዢው ፓርቲ የተጨቆኑ ሕዝቦችን አስተባብሮ ፖለቲካ ኢኮኖሚውን እንዲጨብጡ ማድረጉን ቢያንጸባርቅም፣ ፖለቲካው ኢኮኖሚውን መጫኑን ግን ያስተዋለ አይመስልም። ምክንያቱም ፖለቲካ ታላቅ የኅብረተሰብ ለውጥ መሣሪያ የመሆኑን ያህል፣ መልሶ በኢኮኖሚው መሠረታዊ ባሕሪይ ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳርፋል። ገዢው ፓርቲ ይህንን እውነታ አጣጥሞ መጓዝ ባለመቻሉ፣ የሕዝቡን ጥያቄ በማያቋርጥ ነውጥ ውስጥ እንዲገባ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ በእሳት ማጥፋት ሥራዎች እንዲጠመድ ሆኗል።


በማሕራዊ መሰረቶች መካከል የሚፈጠሩ የፖለቲካ ግንኙነቶች የሚመነጩት በሕብረተሰቡ ሕይውት ውስጥ መደቦች ካላቸው የኢኮኖሚ አቋምና ከዚህም የተነሳ በኅብረተሰቡ ውስጥ በሚጫወቱት ሚና ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እና ተቋማት የማሕበራዊ መሰረቶች የኢኮኖሚ ነፃብራቅ የሆነው፣ የላዕላይ መዋቅሩ አካል ናቸው።


የላዕላይ መዋቅሩ አካል የሆነው የመንግስት ሥልጣን ጥያቄ፣ የአንድ ማሕበራዊ አብዮት የሚያካሂድ አካል ጥያቄ ነው። የላዕላይ መዋቅሩ የተገነባበት ኢኮኖሚያዊ መሰረት ሲለወጥ የነበረው የላዕላይ መዋቅር እየከሰመ መምጣቱ አይቀርም። ምክንያቱም፣ ላዕላይ መዋቅር በሕብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ የኢኮኖሚ ግንኙነቶች ነፀብራቅ የሆኑት ሐሳቦች፣ ድርጅቶችና ተቀዋሞች የሚያመለክት ጽንሰ ሐሳብ በመሆኑ ነው።


በዚህ ጽሁፍ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የሰረገው ኃይልን ፍላጎት ማወቅ ባይቻልም፤ ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን ግን አጠቃላይ የሀገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ በማየት መናገር ይቻላል። ስርገቱ የተደረገበትን ቦታ ለማወቅ አመላካች ናቸው ያልናቸውን አንዳንድ ነጥቦች ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል። ከፖለቲካ መስመር፣ ከፖለቲካ ሥልጣን እና ከፖሊት ቢሮ አባለት አንፃር ለማየት ሞክረናል።

በፖለቲካ መሥመሩ፣ ይሆን?


የፖለቲካ መሥመር፣ አንድ ዓይነት ርዕዮተዓለም ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አንግበው የተነሱትን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ የሚከተሉት የትግል ፈር ወይም የሚወስዱት አቋም ነው።
ፖለቲካዊ መሥመር በንድፈ ሃሳብ፣ በፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ሥራ ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ተግባራዊ እንቅስቃሴም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለሚያደርግ በበጋራ በሚያራምዱት አብዮቱ ወይም የለውጥ ሒደት ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።


ከዚህም የተነሳ አንድ ርዕዮተዓለም (ለምሳሌ ገዢው ግንባር) በሚከተሉና ለአንድ ዓላማ በተሰለፉ ኃይሎች መካከል በስትራቴጂና በታክቲክ ልዩነት ምክንያት የሚፈጠሩ የተለያዩ የትግል አቅጣጫዎች የግንባሩን ሕልውና ወይም የጀመሩትን አብዮት ዕድል የሚወስኑ በመሆናቸው በአንድ ላይ ለብዙ ጊዜ ሊጓዙ አይችሉም። በመሆኑም ለመስመሩ ታማኝ የሆኑ ወይም ለጀመሩት አብዮት ሃቀኛ ታጋዮች መስመራቸው አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ከፍተኛ ድርሻውን ይወስዳሉ። እንዲሁም መስመራቸውን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚወስደውን የፖለቲካ ማዕበል ወደ ትክክለኛ መስመር ለመመለስ በጽኑ ይታገሉታል።


ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ በተለይ የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ከፖለቲካ መሥመራቸው አንፃር ምን ያህል ታማኞች ናቸው? የተቀመጠው መስመር ያረጀ ያፈጀ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ፣ በግልፅ በፓርቲው መድረክ ላይ አዲስ የሰነቁትን መስመር ይዘው መሞገትና መስመሩን ለማስተካከል በግልፅነት ለመታገል ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? በመስመሩ ዙሪያ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ እና ታክቲካል ልዩነቶችን ለማስቀመጥ ምን ያህል ታማኝ ናቸው?

በፖሊት ቢሮ ተመራጮች በኩል ይሆን?


የፖሊት ቢሮ ተመራጮች፣ በማዕከላዊ ኮሚቴው መደበኛ ስብሰባዎች መካከል ባለው ጊዜ የፓርቲውን ተግባር የሚመሩ፣ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን የሚያስፈጽሙ በተለይም የፓርቲውን የዕለት ተዕለት ተግባሮች የሚያከናውኑ የአራቱ ፓርቲዎች አካሎች ናቸው።


ፖሊት ቢሮው፣ በተለይ የሚያተኩረው በዋና ዋና ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ነው። አባላቱም በፓርቲው መዋቅር ውስጥ በቋሚነት የሚሠሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ የፓርቲ አባላትም ሊሆኑ ይችላሉ። የፖሊት ቢሮዎቹ ተጠሪነታቸው ለማዕከላዊ ኮሚቴው ሲሆን፤ በጋራ ደግሞ የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚዎች ናቸው።


ገዢው ፓርቲ ላስቀመጠው የፖለቲካ መሥመር የፖለቲት ቢሮ ተመራጮች ምን ያህል ታማኞች ናቸው? በማዕከላዊ ኮሚቴው በተለይ በኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተወሰኑ ውሳኔዎችን ለመተግበር ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? ከጠባብነት እና ከትምክህት በፀዳ መልኩ ለፓርቲው ውሳኔ በታመን ለመፈጸም ምን ያህል ታማኝ ናቸው?


ፖለቲካዊ ትግል፣ ከመስመሩ አንፃር


የፖለቲካ ትግል፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ከርዕዮተዓለማዊ ትግል ሂደት የሚመነጭና አይቀሬ የሆነ የፓርቲ ወይም የሕዝቦች (የብሔሮች) ከፍተኛው የትግል ደረጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።


በዚህ ትግል ውስጥ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሚታገለው ሥርዓቱን ለማስተካከል ነው? በተናጠል ለፓርቲው ልዕልና ነው? ወይንስ ለግል ጥቅሙ ነው? እነዚህ የትግል ምርጫዎች እንደሀገር ለመቀጠል፣ እንደገዢ ፓርቲ ለመቀጠል፣ እንደ አንድ ተራ ዜጋ ለመቀጠል ወሳኝና መሠረታዊ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል። አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የሚፈልግ ኃይል፤ የፖለቲካ መስመሩን፣ ትክክለኛ መደባዊ ንቃተ ህሊና እና የመደብ ጥቅሙን ለይቶ በመታገል የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ ጥቅሙን ማስከበር ይችላል።


የፖለቲካ ትግል የሚያደርገው ኃይል፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቅራኔዎች በተመለከተ የመጨረሻውን መሠረታዊ መፍትሄ መስጠት የሚችል መሆን አለበት። ከዚህ ያነሰ ምላሽ የሚሰጥ የፖለቲካ ትግል፣ ውርዴ መሆኑ አይቀሬ ነው። ውጤቱም ሀገርን መበተን እና ሕዝቦችን ለእልቂትና ለስደት መዳረግ ነው።

 

በገዢው ፓርቲ ውስጥ፣ ፖለቲካዊ አብዮት እየተካሄደ ይሆን?


ፖለቲካዊ አብዮት የመንግሥት ሥልጣን “ከአንድ ገዥ መደብ” ወደ ሌላ “ተራማጅ መደብ” የሚሸጋገርበት ነው። ይህ ፖለቲካዊ ሥልጣን ተራማጁ መደብ በኅብረተሰብ ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሕይወት ዘርፎች ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣበት ወይም ለማምጣት የሚታገልበት ነው። በገዢው ፓርቲ አጠራር ‘ከጥገኛ አመራር ወደ ተራማጅ አመራር’ ማሸጋገር እንደማለት ነው።
ቁምነገሩ፣ ፖለቲካዊ አብዮት የመንግሥት ሥልጣን ከአንድ መደብ ወደ ሌላው መደብ የሚሸጋገርበት ቢሆንም፤ ማንኛውም ፖለቲካዊ ሥልጣን ከአንድ መደብ ወደ ሌላው መሸጋገሩ ግን ፖለቲካዊ አብዮት አያሰኘውም። ምክንያቱም የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን የማያረጋግጥ ሽግግር፣ ተለዋጭ ጥገኛን ከመፍጠሩ ውጪ ፋይዳ አይኖረውም።


ተራማጅ ኃይሎች በፖለቲካዊ አብዮት አማካይነት ሥልጣን መጨበጥ የመጨረሻ ግቡ ሳይሆን፤ ቀጣይ ሥራቸውን ለመስራት የሚያዘጋጅበት መሣሪያ ነው። ከዚህ አንፃር የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች በተናጠል የሰጧቸው መግለጫዎች ይህንን ቢያመላክቱም፤ እንደኢሕአዴግ ግን የሚታወቅ ነገር የለም። ቀጣይ ጉባኤውን የሚሰጠው ምላሽ ነው የሚሆነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
319 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 355 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us