እርቁ ራሱ ይታረቅ!

Wednesday, 20 December 2017 13:24

በአንድነት ቶኩማ

 

ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ ርዕስ የተዘጋጀውን ጽሁፍ የመጀመሪያ ክፍል አቅርበን ነበር። የዛሬው ፅሁፍ ካለፈው የቀጠለ መሆኑን እንገልፃለን።

 

7ኛ. የጎሳ ትምክህተኝነት (chauvinism)


የጎሳ ትምክህተኝነት የሚከሰትባቸው ሳይንሳዊ ምክንያቶች አሉ። ከነዚህም መካከል በስልጣን ወይም በገንዘብ አልያም “በስልጣኔ” እኔ እበልጣለሁ፣ እኔ እበልጣለሁ ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። በኢትዮጵያ ትምክህተኛ እና ጠባብ የተሰኙ ቃላትም ሆኑ ብሔረሰቦች በብዛት ሲጠቀሱ እንሰማለን።


ብዙዎች አማራን ትምክህተኛ ኦሮሞን ጠባብ ለማለት የሚጠቀሙበት መሆኑን ይታወቃል።


የትግራይ፣ የኤርትራ እና የኦሮሞ ነፃ አውጪዎች የጋራ ጠላታችን ትምክህተኛው ነው ያሉትንም እናታውሳለን። ይህ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዳከም ነው። በተለይ ህወሀትና ሻዕቢያ ጣምራ ሆነው “የትምክህተኛውን ሀይል መስበር አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል። በአንድነት ሆነውም ጦርነት አውጀው ነበር። ተሳክቶላቸዋል። ድሉን ጊዚያዊ ነው የሚሉ አሉ። ይህን በሂደት የምናየው ይሆናል።


የጎሳ ትምክህተኝነት ግን ከዚህ ጠለቅ ያለ በጎጥ የተደራጀ አካሄድ ነው። ከጎሳው ውጭ ላለ ማህበረሰብ ንቀት ማሳየት ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። የራስን ከፍ አድርጎ የሌላውን ማንኳሰስ። የሌላውን አሳንሶ የራስ ክብርን ማዳነቅ። በዚህ ቃለ መጠይቅ ውስጥ የጎሳ ትምክህተኝነት ምልክቶች አይቻለሁ። የታጋይ ትምክህተኝነት የወለደው ሊሆንም ይችላል።


ከአየኋቸው የጎሳ ትምክህት ውስጥ የሚከተሉት ናቸው። የመጀመሪያው የእርቁ አሰባሳቢ እና የመቀራረቡ ዋልታ ወደ ህወሀት መንደር ዘልቆ መግባቱ ነው። አንድ በትግራይ ልጆች ተዋናይነት (ዋና መሪነት) መሆኑ ሌላው የመንግስት ተዋናይነት ሁኔታውን በጥርጣሬ እንድንመለከተው በመንግስት ውስጥ የህወሀት እጅ ምን ያህል የጎላ መሆኑን እናውቃለን። ያደርገናል። የክልል አንድ ሰዎች መኖራቸው ችግር የለውም። እነሱ ብቻ ከሆኑ ግን ትክክል አይደለም።


የማናውቅም እንጠረጥራለን። የልሂቃኑ ጉባዔ መሪ የህወሀት መፍለቂያ የደም ንክኪ ያላቸው ሰው መሆናቸው ሌላው ነው። ልብ አድርጉ ይህ የኤርትራ መገንጠል ላይ ጣልቃ የገባው ጎሳ ጦርነቱ ላይ ወሳኝ ነበር። አሁንም ድርድሩን እኔ ልምራ ያለ ይመስላል። “ልጓሙን ያዝ አድርገው” የሚል ያሻል።


የሁለተኛው የጎሳ ትምክህተኝነት በቃለ መጠይቁ እንዳየሁት ከሆነ የአጋዚያን ማህበር ማለትም የኤርትራና የትግራይ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ህብረት አለ የሚባለው ነው። በርግጥ ሰሞኑን የተደረገው ውይይት የአጋዚያን ማህበር ከሚባለው የተለየሁ ነኝ ብሏል። ይህ ነው ሁለቱን ህዝቦች የሚያቀራርብ ነው የተባለለት። ልብ በሉ አጋዚያን የተባለው ማህበር የሌላውን ሕዝብ አይጨምርም።


አንደኛው ቃለ መጠይቅ የሰጡት ሰው ስለ ኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ድርድር ሲያስረዱ “አጋዝያን የሚባል ትግረኛ ተናጋሪዎች ብቻ አቅፎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በጣም እንለያያለን።” ይሉናል። በውጭው ዓለም “የኤርትራ ሶላዲሪቲ ግሩፕ” የሚባል እንቅስቃሴ እንዳለ ሌላው ቃለ መጠይቅ የሰጡት ልሂቅ ተናግረዋል።


ተመልክቱ! የትግሪኛ ተናጋሪዎች ቡድንን። በኤርትራ ከስምንት በላይ የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች አሉ። ትግርኛ መናገራቸውን አላውቅም። ሁሉም ግን አጋዝያን አይደሉም። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማኒያ በላይ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች አሉ። ሁሉም ግን ትግሪኛ አይናገሩም። በመሆኑም “አጋዝያን” ማኅበር ውስጥ አይገቡም። ወይም አይደሉም። በመሆኑም “የአጋዝያን” ማህበር አግላይና የጎሳ ትምክህት ሰለባ ይመስላል። በአገር ውስጥ ባለፈው የተጀመረው ውይይትም “ትግራዊያን ትግራዊያንን ይሸታል” የሚሉ አሉ። ኢትዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦች በተዋናይነት እንጂ በመሪ ተዋናይነት መኖራቸውን አላየሁም ይላሉ አንዳንዶች። ቃለ መጠይቁም ይህን ያሳብቃል። ሦስት በቃለ መጠይቁ ብሔር ተዋጽኦ ለአንድ እየመሩ ነው የታዩት። የሌሎች ብሔሮች አባለት ሊኖሩ ቢችሉም ሂደቱ ከጎሳ ትምክህት መላቀቅ ይኖርበታል። የ˝ታግያለሁ" ትምክህትም ሊጠፋ ይገባል። ግልጽነት ማለት ይሄ ነው።
በሌላ በኩል በኤርትራውያን በኩል “ኢትዮጵያን ይጠላሉ” የሚባለውን ማናፈስ አይገባም እንላለን። ነገሩን መፈተሽ ግን ጥሩ ፍተሻ ነው። ከዚሁ ጋር ኤርትራውያን ያላቸውን ተገቢ ያልሆነ የጎሳ ትምክህት ጥለዋል ወይ? ማለትም ያስፈልጋል። ይህን ጉዳይ በደንብ መፈተሽ ይገባል። አለበለዚያ ነገሩ ሁሉ “እንዘንጭ እንቦጮ” ይሆናል። “እኛ ልዩነን፣ ከሌላው እንበልጣለን” የሚለው በሁለቱም ህዝቦች በኩል እስካልተራገፈ ድረስ ግንኙነቱ ውጤታማ ለመሆን ያስቸግረዋል። መከባበርን ማክበር አለብን።


የመገንጠል ዋና ተዋናይ የነበረው ድርጅት የህብረት፣ የመተባበር ወይም የአንድነት አቀንቃኝ ሲሆን መጠራጠር ይገባል። ተምሮ ወይም መንኩሶ ከሆነ ተግባር ይፈትነው። የአድር ባይነት ካባ ወይም የመጠጊያነት (ጥገኝነት) ንድፍ ከሆነም ይጣራ። በዚህ ሂደት የሚታመኑ ልሂቃንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካይ አድርጎ መላክ አለበት። የትግራይ ልጆች ውክልና ብቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና አይደለም። ግልፅነት ያስፈልጋል። ህወሀቶች በኢትዮ ኤርትራ አያያዝ ብቃትና እውቀት ያላቸው አይመስልም። ትግርኛ ቋንቋ መናገር ብቻ ወይም ከኤርትራውያን ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ መናገር ብቻ ብቃት አይሰጥም። አቶ ገብሩ አስራት እንደመሰከሩት ቋንቋውን እንጂ ስልጣንንና አያያዙን ያወቁበት አልመሰለኝም።

8ኛ. የተዛባ ምንጨታዊ ሥነ አመክንዮ መታየቱ (Deductive logic)


ዜናውን እንደግብ መውሰድ ከጥናቱ ቀድሟል ወይም ከሚገባው በላይ ተጨብጭቦለታል። ነገር አለ ማለት ነው። የድርድሩ “የትምጣ” የተጠና ወይም የታወቀ አልመሰለኝም። ምንጨታዊ የሚለው መነጨ ከሚለው የመጣ ነው። ፈለቀ ለማለት ነው። ቃሉ ወጣ ማለትም ሲሆን ስረ ነገሩ ተብሎም ሊወስድ ይችላል። “የማርክሳዊ ሌኒናዊ መዝገበ ቃላት ምንጨታዊ ሥነ- አመክንዮ የሚባለውን ሲተነትን በገፅ 100 ላይ እንዲህ አስቀምጦታል። ˝ምንጨታዊ ስነአመንክዩ ከአንድ ወይም ከአንድ ከሚበልጡ አጠቃላይ መንደርደሪያ ሀሳቦች በመነሳትና በእነሱም ላይ በመመርኮዝ ዝርዝር መደምደሚያ ሀሳብን በማፍለቅ የዚህን ሀሳብ ትክክለኛነት አመንክዮአዊ ስርዓትና ትንታኔ መሰረት በማረጋገጥ ወይም የማሳየት “ስልጣን” ነው።" ይላል። ጥሩ ትንታኔ ነው። አንድ ወይም ከዚያ በላይ ያሉ ነገሮችን ተመርኩዞ መወሰን እንደ ማለት ነው።


ይሁን እንጂ እነዚህን ነገሮች ብቻ ይዞ የተገለጡትን አዳዲስ እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ሳይጨምር ይህን ድምዳሜ ማብቀል ልክ አይደለም። የሁለቱ ህዝቦች ምንነቱ (Essence) እና ገፅታ (appearance) በጥልቀት መታየት አለበት። የዚህን ዘመን ማለቴ ነው። አለበለዚያ የተሳሳተ ነገር ውስጥ እንገባለን። ለምሳሌ የኤርትራ ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪክ አንድ ነበር ይባላል። ልክ ነው። ምንነቱና ገፅታው ሰላልተጠና ግን አስከፊ ጦርነት ውስጥ ገባን። ለምን ተዋጋን? ለምን ጠሉን? ወይም ተጣላን? ወይም ሸሹን? መጠናት አለበት።


ሌላው ተናጋሪ ሲናገሩ “እኛ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖትና በመልክ እንመሳሰላለን” ይሉናል። ይህ ለአንድነት መሰረት አይሆንም። የሱማሊያ ክልል ሕዝብ ከሱማሊያ ሕዝብ ጋር በቋንቋ፣ በመልክ እና በሃይማኖት መመሳሰሉ አንድ አያደርገውም። በዚህ ስሌት ሶማሊያ ክልል ወደ ሶማሊያ ትሂዳ? ወይም ትግርኛ ተናጋሪዎች ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ ይሂዷ? ይህ ምክንያት አይሆንም። የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች በብዛት የክርስትናን፣ እስልምናን ወይም ሁሉአምላክነትን የሚባሉ እምነቶችን የሚከተሉ ናቸው። ከዚያ ውጭስ ምን እምነት አለና ነው? በሃይማኖት እንመሳሰላለን እና አንድ እንሁን የሚባለው። መመሳሰል የአንድነት መሰረቱ አይደለም። ከዚሁ ሌላም ምክንያት ሊኖር ይገበል። ግልብ መደምደሚያ መታረም አለበት። ህብረታችን በጥቅማችን ውስጥ ሊሆን ይገባል። በሥነ ልቦና መተሳሰር ጭምር ሊሆን ይገባል። ታሪካዊ መተሳሰራችን መሠረት ሊሆን ይገባል።


አንዱ ቃለ መጠይቅ ተደራጊ “የሁለቱ ህዝቦች አንድነት መጠናከር ያለበት ኤርትራውያን ሲከፋቸው ወደ ኢትዮጵያ ነው የሚመጡት ወይም ሰለሚመጡ ነው” ብለዋል። ይህም ለአንድነት ምክንያት የሚሆን አይመስለኝም። የመልክአ ምድር አቀማመጥ ያመጣው ሰበብ ነው። ደቡብ ሱዳኖች ሲከፋቸው ወደ ኢትዮጵያ ስደተኞች ጣቢያ ይመጣሉ። ሱማሌዎችም እንዲሁ። ይህ ለአንድነት አያበቃም ስል የደረደርኩት ነው። አንድ ብንሆንማ በምን እድላችን! በጥልቀት ተነጋግረን ነው ውይይቱን መጀመር ያለብን። መጀመሪያ ኢትዮጵያውያን ለብቻችን፣ ኤርትራውያን ለብቻቸው እንምከር። ከዚያ የሚቀጥለው ይሆናል።


የውይይቱ ምክንያታዊነት መጠናት ይገባዋል። ውይይቱ ከህጋዊ መድረክነት ወደ ሰሜት አጫፋሪነት እንዳይለወጥ መጠንቀቅ ይገባል። በኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ መድረክ ስንል ተወካዮቹ የኢትዮጵያን ጥቅም በስሜት የሚያስረክቡ ተዋንያን እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይገባል። ህጋዊ ውክልና ያሻል። የኢትዮጵያዊያንን ሙሉ ድምፅ በአንድ ክልል ልጆች እጅ ማስቀመጥ አይቻልም። የሁሉም ሕዝብ ተወካዮች ውይይቱን መሳተፍ አለባቸው። አንዳንዶች ብዙ ኤርትራዊ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉና አንድነቱን ያፋጥናሉ ይሉናል። ልከኛ አተያይ አይመስለኝም።


ህዝቡ አሁን ያለበትን አቋም እንዴት ያዘ? የህዝቡን ልባዊ (Perception) አቋም በምን ተረዳነው? የመንግስታቱስ መለሳለስ ከምን ምንጨታዊ አመክንዮ የተነሳ ነው? ለምሳሌ በእርቁ በሁለቱም አገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት ነው? ይህ ከሆነ የስልጣን ማማ ማረጋጊያ እየተፈለገ ነው ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ህዝቡን ተዋናይ ማድረግ አይገባም። ሁለቱንም አገሮች ማቀራረብ ጥሩ ነው። ነገር ግን በደንብ ይፈተሽ!


በተጨማሪ ከዚህ በላይ ለምን የአገር ውስጡ የእርስ በርስ ጥላቻ አንድ በአንድ እንዲቀንስ ስራ አይሰራም? እንዴት የአሁኑ ውይይት የድንገቴ ውይይት መሰለ? ይህ የአቋም ከላሽነት የመጣው የስልጣን ማማ የውለደውስ ቢሆን? “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል” ይሏልና። አስፈለጊ ሆኖ ከተገኘ አራጋቢዎችም ሰከን በሉ መባልም አለበት። ወገኖች ሁኔታውን በደንብ አጥኑ! አስተውሉ! የሚሆነው ይሆናል። ጥንቃቄው የኢትዮጵያን እንዲሁም የኤርትራን ሕዝብ ይጠቅማል።

9. የጥንቃቄው መጠቁሞች!


መቼም ከዚህ በላይ ቃለ መጠይቅ በተደረገላቸው ሰዎች ችሎታ ላይ ጥያቄ የለኝም? የእኔ ችግር እውቀታቸው አይደለም። ቅን ልቦናቸውም ችግሬ አይደለም። ለዚህ ውይይት እውን መሆን መድከማቸውም ላይ ጥያቄ የለኝም። የእኔ ጥያቄ የውክልና ጥያቄ ነው። የእኔ ችግር ከታሪክ መማሬ ነው። ተደናግረው ያደናገሩን ሰዎች አሁንም አሉ። የእኔ ችግር ትናንት “ሁሉን በልክ አድርጉት” ሲባሉ በንቀት ልክ የሌለው ጋብቻና ፍች ምክንያት የሆኑት ዛሬ ጋብቻ መፈለጋቸው ነው። የእኔ ችግር ያለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና፣ ያለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ ኤርትራዊያን ብቻ ምርጫ አድርገው እንዲለዩ ያደረጉ ሰዎች በእጅ አዙር የአዲሱ የድርድሩ ተዋናይ መሆናቸው ነው።


ችግር አለብኝ። የእኔ ችግር የመጥፎው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ቆስቋሽ እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ አስተሳሰብ ወጥተው የራሳቸውን ግልብ ውሳኔ የወሰኑ ሰዎች በእጅ አዙር አርቲስቱን አስጨፍረው ችግር እንዳይፈጥሩ ስጋት ስላለኝ ነው። የእኔ ችግር ትናንት በዘፈን፣ በጭፈራና በፈንድሻ የመለየታቸውን ዜና ያበሰሩን ሰዎች መልክ መቀየር ነው። ትናንት “ጠላታችሁን አርቀን ቀርብረንላችኋል” ያሉት፣ ከዚያም በተጨባጭ ጠላትነትን ያስፋፉት መንኩሰው የእርቁ ተዋናይ መሆናቸው ነው። ከተለወጡማ እሰየው!!! ለማንኛውም የእንቅስቃሴውን አባላት ከአክብሮት ጋር በጥንቃቄ ይመለከቱት ዘንድ የሚከተሉትን ሀሳብ ጠቁሜ አልፋለሁ።

1. ውዥብርን ማጥራት


ግልፅ አቋም ይዞ መራመድ ያሻል። ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በታሪክ እና በማህበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ የተፈጠረውን ውዥንብር ማጥራት ይገባል። ግባችንም ምን መሆን አለበት የሚለውን ማጥናት ያሻል። የመጨረሻው ግብ ህዝቡ ወሳኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ። ለማንኛውም መንገዱ በውዥንብር መሞላት የለበትም።

2. ድርድሩን "የእኛ ድርድር ማድረግ”


ድርድሩ የሕዝብ መሆን አለበት። ይህ የሚሆነው በግልፅነቱ፣ በተወካዩ አይነት እና በዓላማው ነው። አላማው እኛን እና እነሱን መጥቀም አለበት። ውክልናው ከእኛ የወጡ ኢትጵያዊያን የሚወዱት ሊሆን ይገባል። ዓላማው ግልጽና የፀዳ ሊሆን ይገባል። ተወካዮቹ የምናውቃቸው ሊሆኑ ይገባል። በአገር ወዳድነት፣ በብሔር ተዋፅኦ፣ በፖለቲካ አቋማቸው ተዋፅኦ እና በመሣሠሉት ይሁን።

 

3. ጅምላ ወቀሳን ማስቀረት (መፋቅ)


የአገዛዙን፣ የጦርነቱን እና የሌላውን ታሪክ ጅምላ ወቀሳ ማፅዳት ይገባል። ደርግን፣ አጼ ኃይለስላሴን እና ሌሎችን የሚወቅስ ግለሰብ በቃለ መጠይቁ አይቻለሁ። እነዚህ ስርዓቶች እንዲህ አደረጉን የሚለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መስማት የሚፈልግ አይመስለኝም። በዚህ ጉዳይ አባቶችን ለሚያናንቅ ወይም የሚያንቋሽሽ ወይም ለማንቋሸሽ የሚፈልግ በቂ ትውልድ አለን። ሌላ አንፈልግም። እንዲያውም በዝተዋል። ኤርትራውያንም “ይህን ሰርተውን” ማለት ማቆም አለብን።


ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ይልቅ ጣሊያንን፣ እንግሊዝን ወይም ሌሎችን ሲወቅሱ አይታዩም የሚሉ አሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ትውልድ ለወቀሳ የተዘጋጀ አይደለም። አሁን በአያቶቹ አይደራደርም። ያ ድሮ ቀረ። መጥፎም ሆነ ጥሩም ታሪክ የራሳችን ነው የሚል ሀሳብ ብቻ ነው መንሸራሸር ያለበት። “ወያኔ ይህን ሰርቶ ሻብያ ይህን አድርጎ” የሚለውም የሚያስፈልግ አይመስለኝም። መጠራጠር እንጂ ወቀሳ የለም። አበቃ! እውነቱን መነጋገር ወይም ጥሎ ማለፍ እንጂ ቁጭ ብሎ አያቶቹ ላይ ሊሳለቅ ማየት የሚፈልግን ማህበረሰብ ለመሸከም የሚችል የድሮው ትከሻ ኢትዮጵያዊያን የላቸውም። አውቃችሁ ግቡ። ያኛው አክትሟል። አናቋሪዎችን አርቀን አንድ በአንድ እየቀበርናቸው ነው። አናቋሪዎች ከማናቆር ወደ ፍቅር ቢመጡ ይሻላቸዋል።

 

4. ከግብታዊነት መጽዳት


ስሜታዊነት ወይም ግብታዊነት ጥሩ አካሄድ አይደለም። ግብን ተምኖ፣ መርምሮ እና መንገዱን አፅድቶ መሔድ ያስፈልጋል። ግብታዊ ውሳኔ ሁልጊዜ ችግር ይፈጥራል። ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ይገናኙ ዘንድ የሚሰሩት ሁሉ ግብታዊነትን ማንፀባረቅ አይገባቸውም። የሚወክለውም ሆነ የተያዘው አጀንዳ አገራዊ ነው። በስፋቱም፣ በጥልቀቱም፣ በዓላማውም ቢሆን ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ስክነት ይጠይቃል። አስቦ መራመድ!!!

5. እውነቱን በጥልቀት መረዳት


እንደ እውነቱ ከሆነ ገና ጥልቅ ጥረት መደረግ ያለበት ይመስለኛል። በክፍለ ከተማ ደረጃ ወርደው “ስለሁለቱ ህዝቦች እየተነጋገርን ነው” ይላሉ ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ አንደኛው ተናጋሪ። አንደኛው ተናጋሪ ደግሞ “እውነተኛውን ትምህርት እናስተምራለን” ብለዋል። ይህ ጥሩ ነው። ደስም ያሰኛል። እኔ ግን ከዚህ ያለፈ መሆን አለበት እላለሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የኤርትራ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነበሩ እውነት ነው። አሁን ግን አይደሉም። ኤርትራውያን አንድነቱን አንፈልግም ብለው ተለዩ። ፓሪቲው ወይም የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ብቻ አይደለም ህዝቡ ተባብሯል። መርጧል። ምርጫ አልነበረውም ተገደው ነው ከተባለ ይህን ተቃውመው መታገል ነበረባቸው። ወይም ከነፃነቱ በኋላ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ፍንጭ ማሳየት ነበረባቸው። ግን አላሳዩንም። ሃቁ ይህ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ግልብ እውነት (Naive Truth) ላይ ተመሥርቶ እንዳይቀጥል ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ሁለቱ ሕዝቦች መቀራረብ የሚፈልጉበት ምክንያት መጠናት አለበት ያልሁት ለሁለቱ ሕዝቦች ነው።


ለምሳሌ:- በኢትዮጵያ በኩል ትተውን ለምን ይኼዳሉ የሚል ቁጭት “የፍቅር ቁጭት” ነበር። ኤርትራውያን ወንድሞች ግን የኢትዮጵያን ፍቅር የወደብ ናፍቆት ብለው ተሳለቁበት። ለምን እንዲህ ሊሉ ቻሉ ወይም ምን አይተውብን ነው? ከዚህ የተነሳ አሁን የኤርትራዊያን ትዝታ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እየጠፋ ነው። የተቆረሰችውን ካርታ አምኖ ወደ መቀበል እየደረሰ ነው። የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ደሙን ያፈሰሰበት እና አጥንቱን የከሰከሰበትን ምድር አሁን ያለ ሕዝብ ብዙ የትዝታ ማህደሩ ውስጥ ያስቀመጠው አይመስለኝም።


የሌላውን ባላውቅም በኢትዮጵያ በኩል ጥርጣሬ አለ። ከመጠራጠሩም የተነሳ በዚህ ሀሳብ ወይም እንቅስቃሴ ላይ ፍንገጣ (Deviation) ይታያል። አሁን ‹‹ሁለቱ ህዝቦች›› ተብለው ስለቆዩ “አንድ ነን” የሚለው ጠፍቶብናል። ወራሪ፣ ቅኝ ገዢ፣ ፊውዳል የተባለችው ኢትዮጵያ ዝምታ ውስጥ ናት። ደፈጣም ሊሆን ይችላል። የግንኙነቱን ፋይዳ ኢትዮጵያውያን ማወቅ ይፈልጋሉ። ኤርትራውያንም ቢያውቁት ጥሩ ነው። ስደተኛ መቀበል ለኢትዮጵያዊያን ዋና ነገር አይደለም። ባህላቸው ነው። የሱማሌ ስደተኞችን ተቀብላለች። የእስልምና ተከታዮችን ተቀብላ አስተናግዳለች። ሌሎችንም እንደዛው። እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ነው ተብሎ ተፅፎልናል። ይህ ለአንድነት ያለው ፍላጎት መለኪያው አይደለም። እንግዳ መቀበል ለኢትዮጵያዊያን ሕዝብ የኑሮ ዘይቤ ነው። ይህ ባህል የኤርትራውያንም ጭምር ነው።


የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አቀራራቢዎች ሊያጤኑት የሚገባው ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያዊያን ጋር በነበሩ ጊዜ አለብን የሚሉትን ቁርሾ ያክል ከኢትዮጵየዊያን ሕዝብ ጋር አብሬ አልኖርም ባሉ ጊዜም የሰሩትን የጥፋት ቁርሾ እንዳለባቸው ነው። አደራዳሪዎች መዘንጋትም መዘናጋትም የለባቸውም። በመሆኑም የነገሮችን፣ የጊዜውን ሁኔታ፣ ያስተሳሰቡን ምንነትና ገፅታ አጥንቶ እና ለይቶ በጥሩ ነገሩ ላይ በመጨመር መጥፎውን አረም በመንቀል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል።

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
188 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1004 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us