የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታትን ልዩነቶች፤ በሁለቱ ሕዝቦች ለመፍታትና ለመዳኘት ያለመው መድረክ

Wednesday, 20 December 2017 13:29

 

በሳምሶን ደሳለኝ

 

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስታት መካከል የሰላም አማራጭ ለማምጣት የተሄደበት መንገድ እስካሁን ድረስ ውጤት አልባ በመሆኑ፤ ጉዳዮን ወደ ሁለቱ ሕዝቦች በማውረድ ያሉትን አማራጮች ለመፈተሽ በሐርመኒ ሆቴል በሰለብሪቲ ኤቨንት ኃ/የተ/የግ/ማ ጠንሳሽነት ውይይት ተደርጓል።


ከመድረኩ አስተባባሪዎች የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ግቦች መቀመጣቸው ተገልፃል። የአጭር (የቅርብ ጊዜ) ግቦች ተብለው የተለዩት፣ የምክክር ሂደቱን በመጀመር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የጋራ መድረክ ይፋ ማድረግ፤ በምሁራንና በሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች መካከል የምክክር አውደጥናት መፍጠር፤ የጋራ ዓላማና ቁርጠኝነትን መገንባትና ማንጸባርቅ እና ምክክሩን ወደፊት ለማራመድ የሚረዳ መዋቅር መዘርጋት ናቸው።


የመካከለኛ ጊዜ ግብ፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ግንኙነት እመርታዊ ለዉጥ ለማምጣት የሚረዳ የዉይይት መድረክ መፍጠር። የሚፈጠሩት መድረኮች አስፈላጊነት በወፍ በረረር ሲቀመጡ፤ የሁለቱም አገሮች ምሁራንና የሲቪል ማህበረሰብ አባላት - በዉጪ የሚኖሩትን (Diaspora) ጨምሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላለዉ ግጭት ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ መፍትሄዎችን እንዲጠቁሙ መልካም ዕድልን ይፈጥራል፤ የአገራቱ የአሁንና የድሮ ባለስልጣናትንና የሲቪል መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሁለቱንም ወገኖች የሚያግባቡ የጋራ አጀንዳዎችን ለመለየት ዕድል ይሰጣል፤ በየመን ያለዉ ጦርነትና የዉጪ ኃይሎች ወታደራዊ ግስጋሴ የመሳሰሉ ከፊት ለፊታችን የተደቀኑ ዓበይት የሰላምና የደህንነት ተግዳሮቶች በተመለከተ ዉይይት ለማካሄድ ይጠቅማል፤ መሬትና ሰላም፣ ምጣኔ ሃብታዊ ማነቆዎችና አገራዊ ሉአላዊነት፣ ግጭቶችን በመፍታት ወይም በማባባስ ረገድ ዴሞክራታይዜሽን ያለዉ ሚና፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መረጋጋትን በማምጣት ረገድ ሊኖረዉ የሚችለዉ አስተዋፅኦ በተመለከተ ያሉት አጨቃጫቂ ነጥቦች ለመዳሰስ ይረዳል፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ የአገራዊ ደህንነት ፍላጎቶች የት የት ላይ እንዳሉ ለማሳየትና ለማጉላት ይጠቅማል፤ መደበኛ ያልሆነዉ የድርድር ሂደት ሊኖረዉ የሚችለዉን ሚናና የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲዉን የማጠናከር አስፈላጊነት ለማጤን አስፈላጊ ነዉ፤ የሁለቱም አገሮች እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ መፃኢ እድል የሚያሳስባቸዉ አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ቡድኖችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሁለቱም ወገኖች ያሉት አገራዊ አስተሳሰቦችና ትንታኔዎች እንዲያዳምጡና ወደ ዉይይት መስተጋብሩ እንዲያመጡት ያስችላል፤ የሲቪል ማህበረሰብ አባላት በተለይም በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዱት ወጣቶች አሁን በሁለቱ አገሮች መካከል ባለዉ ግንኙነት ዙሪያ ሃሳባቸዉን እንዲያበረክቱ ያነቃቃል፤ የምክክር መድረኩ ዉጤት የሚሆነዉ ሪፖርትና በመድረኩ የሚቀርቡት ጥናታዊ ጹሁፎችን ማሳተምና ማሰራጨት የስራዉ አካል ይሆናል፤ የተያዙት ግቦች ወደፊት ለማራመድ ይረዳ ዘንድ የሚታዩ ለዉጦችን ለመከታተል የሚረዳ ንድፍ ለማዘጋጀት ይረዳል።


የረዥም ጊዜ ግብ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ አስተማማኝ የደህንነት ቀጣና ማስፈን ናቸው።


አጠቃላይ የመድረኮቹ የምክክር የውይይት ቅርጽ በአምስት ምዕራፎች የተደራጀ ነው። በእያንዳንዱ ምዕራፍ ለሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ጥቅል ሃሳቦች ይዘጋጃሉ። እንደአስፈላጊነቱም ቀደም ብለዉ ለተሰብሳቢዎች ይሰራጫሉ። ምክክሩ ከታች በተዘረዘሩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በሴሚናር መልክ በሚቀርቡት ፅሁፎች ላይ ዉይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።


ለምክክሩ የሚቀርቡ አጀንዳዎች በአምስት ዋና ዋና ርዕሶች የተደራጁ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ይኸውም፣ 1.ባህል፣ ታሪክና ጂኦግራፊ (በኢትዮጵያና በኤርትራ ማዕከል ያደረገ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ታሪክ)፤ 2.የቅኝ አገዛዝንና ኢፍትሃዊነትን በመቃወም የተደረጉት የጋራ ተጋድሎዎች፤ 3.በቅርቡ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገዉ ጦርነትና የድህረ-አልጄርስ ምህዳር (ግጭቱ ያስከተለዉ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ፣ የፖለቲካና የፀጥታ አንድምታዎች) 4.በግጭቱ ዙሪያ ያሉ አስተሳሰቦች (የኤርትራ ህዝብ ሃሳባዊና ተጨባጭ ስጋቶች፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳባዊና ተጨባጭ ስጋቶች) 5.የሰላምና የደህንነት ተግዳሮቶች (የጋራ የሆኑ ስትራቴጂያዊና የህላዌ ስጋቶች፣ አዳዲስ ስጋቶች) 6. በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም የማስፈን ቅድመ ሁኔታዎች (የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚኖረዉ ሚና፣ ትዉፊታዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ትስስር) ናቸው።


በሐርመኒ ሆቴል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ግንኙነት በይነ ትውልዳዊ ውይይት መድረክ ላይ ከፍተኛ ሊሂቃኖች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ባለሃብቶች፣ በኤርትራ ወገን የቀረቡ ተሳታፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ለመድረኩ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ሲሆኑ፤ በዚህ የፖለቲካ አምድ ሥር ምሁራዊ እይታቸውን እንድናካፍላችሁ ስለወደድን አቀረብነው። መልካም ንባብ።


በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ግንኙነት በይነ ትውልዳዊ ውይይት (Intergenerational Dialogue on Ethiopia-Eritrea) መድረክ ላይ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር መድረክ ለማካሄድ የተቀመጠውን ትልም ሲያስረዱ፣ “ኢትዮጵያና ኤርትራ አሁን በሚገኙበት ወሳኝ የታሪካቸዉ ምዕራፍ ከፊት ለፊታቸዉ የተደቀኑት ፈተናዎች በተመለከተ ብሩህነት ያለዉ አረዳድ እንዲኖር ማስቻል” እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው አስረድተዋል።


ፕሮፌሰር መድሃኔ አያይዘውም፣ “ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን በታሪክና በባህል እጅግ የተሳሰሩ መሆናቸዉ ጊዜ የማይሽረዉ ሃቅ ነዉ። እነዚህ ድንቅ የጋራ ዉርሶች ወደ ጎን የምንተዋቸዉ ሳይሆኑ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሌሎች አዎንታዊ እሴቶች ለመገንባት የሚረዱ በእጃችን ያሉ መሣሪያዎች ናቸዉ። በተለይም አሁን ካለዉ ዓለምአቀፍ የፀጥታ መስተጋብርና የቀጠናችን የደህንነት ስጋቶች አንፃር የኢትዮጵያውያንና የኤርትራዉያን ደህንነትና ብልፅግና ፍፁም የማይነጣጠሉና እርስ በርስ የሚመጋገቡ ናቸዉ።” ብለዋል።


ፕሮፌሰር መድሃኔ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ታሪካዊ ዳራ መለስ ብለው እንደገለጽት፣ “እ.አ.አ. ከ1998-2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደዉ ጦርነት ለስሙ ያህል ቆሟል ቢባልም፣ የሁለቱንም አገሮች መንግስታት እርስ በርስ የሚጠራጠሩ ከመሆናቸዉም በተጨማሪ ወደ መካረርና መፋለም ለመግባት ሁሌም አፋፍ ላይ ያሉ ናቸዉ። ሁለቱም አገሮች አንዱ ሌላዉን ለማናጋት አሊያም በቀጥተኛ ግጭት ለመግጠም ሙሉ አቅማቸዉን ያዘጋጁ ናቸዉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ የሁለቱንም አገራት ዜጎች ጭንቅ ዉስጥ ከቷቸዋል። ሁኔታዉ የሚያስከትለዉ ቀጥተኛ የፀጥታ ሰጋት፣ እሱን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለዉ ሰብዓዊ ቀዉስ፣ የሚከሰተዉ የመንግስታቱ ዉስጣዊ አለመረጋጋትና በቀጠናዉ ሊስፋፉ የሚችሉ እንደ ወንጀል፣ የስደተኞች ፍልሰት፣ ደም መፋሰስና ሽብር ሊጠቀሱ የሚችሉ ስጋቶቻቸዉ ናቸዉ።”


ከላይ የሰፈሩት ችግሮች ከቀንዱ ሀገሮች ጋር ደህንነት ጋር ተያያዥ መሆናቸውን አስቀምጠው፤ “ያለንበት ንዑስ ቀጠና በዓለማችን ካሉት እጅግ ያልተረጋጉ አካባቢዎች በዋነኛነት ከሚጠቀሱት አንዱ ሲሆን፣ አስተማማኝ የፀጥታ መደላድል ያልፈጠረና ይህንን ዓይነት የደህንነት ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታም የሌሉበት ነዉ። የሁለቱም አገራት መንግስታትና ዜጎች እርስ በርስ የሚኖራቸዉን ግንኙነት ሊመራ የሚችል አቅጣጫ በተመለከተ መግባባት ላይ አልደረሱም።” ብለዋል።


“ባለፉት 15 ዓመታት ግጭቱን በመፍታት ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካለት የነበረው ትኩረት መንግስታቱ ላይ ነበር። ውጤት አልባ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ ሊፈጠር ይችል የነበረዉን የዉስጥ አቅምና ከአከባቢዉ ሊገኝ ይችል የነበረዉን ፖለቲካዊ ድጋፍ እጅጉን አቀጭጮታል።” ይህም በመሆኑ፣ “ገና ያልተሄደባቸዉ መንገዶችና አገር በቀል የሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ማፈላለግ የግድ” የሚልበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንደምንገኘ ፕሬፌሰሩ አስታውቀዋል።


በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስታት መካከል ሰላም ባለመውረዱ ምክንያት በርካታ ምላሽ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች መኖራቸውን ፕሮፌሰር መድሃኔ ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፣ “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያሉት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ግጭቶች የሰዉ ህይትን በመቅጠፍ፣ የኢኮኖሚ እድገታቸዉን በማጓተት፣ የተራዘመ አለመረጋጋት በመፍጠርና ለንዑስ ቀጠናዉ የተረፈ ትርምስ በማስከተል በሁለቱም አገሮች ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ይህ አልበቃ ብሎ የሁለቱ እህትማማች አገራት ህልዉናና ደህንነት ላይ አዉዳሚና የረዥም ጊዜ ተፅዕኖ ያላቸዉ አዳዲስ ስጋቶች ጉልበት እያገኙ በመሄድ ላይ ናቸዉ። እነዚህ ክስተቶች ሊፈተሹ የሚገባቸዉ በርካታ ጥያቄዎች እንድናነሳ ያስገድዱናል።” ብለዋል።


“የተደቀኑትን ችግሮች በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች አለመኖራቸው ሁለቱን ሕዝቦች ለተጨማሪ አደጋዎች አጋልጧል” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ሃሳባቸውን በዚህ መልክ አስቀምጠዋል፣ “ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን ሊከተሉ የሚችሉ የረዥም ጊዜ ተፅዕኖ ያላቸዉ መዘዞች በተመለከተ እየወሰዱት ያሉ እርምጃዎች ቅንጅት የሌላቸዉ ናቸዉ። ይህ ደግሞ የተደቀኑባቸዉ የሰላምና የደህንነት ፈተናዎች ለመመከት ያላቸዉን አቅም በሚገባ እንዳይጠቀሙ ያግዳቸዋል ብቻ ሳይሆን አኮላሽቶ ለባሰ ስቃይ ይዳርጋቸዋል። ስለዚህም ከዚህ አዙሪት የሚያወጣቸዉ የተቀናጀና ምልአተ ቀጠናዉን ያቀፈ ስልት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን መካከል ዘላቂነት ያለዉ ገንቢ ግንኙነት እንዲያንሰራራ የሚረዳ ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል ስራ ነዉ።” ሲሉ አስምረውበታል።


በሁለቱም አገሮች መካከል የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት እንዲኖር መወሰድ ያለባቸዉ የመጀመርያ እርምጃዎች ምን ምን ናቸዉ? ለሚለውም ጥያቄ በጥያቄ ምላሽ አቅርበዋል፣ “ሁለቱም እህትማማች አገሮች በጥላቻ አዙሪት ዉስጥ ዘፍቀዉ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ አሳማኝ ምክንያቶች አሉን? በዚህ ረገድ የታሪክና የባህል ሚና ምንድን ነዉ? ታሪክና ባህልን በተመለከተ ቀናነት ያለዉ ዉይይት ሳይደረግ አሁን ያለዉን የተካረረ ግንኙነት ለማስተካከል የሚረዳ የጋራ መደላድል ማግኘትስ ይቻላል? እርቅ ለማዉረድና መልካም ዝምድናዉን ለመመለስ ያለዉ እድል ምን ያህል ነው? ዴሞክራሲና ልማት በሁለቱም አገራት ለማረጋገጥ ያለዉ እድልስ ምን ያህል ነዉ? ግንኙነታቸዉን ለማሻሻል፣ ቀዉሱን ለመግታትና ግጭቱን ለመፍታት የሚረዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችስ በምን መንገድ ስራ ላይ ሊዉሉ ይችላሉ? ለምንድን ነዉ ሁለቱ አገሮች እርስ በርስ ለመፋለምና ለመጠፋፋት የተሰለፉት? ይህ እንዴት ነዉ በየአገራቱ ካለዉ የፖለቲካ ሁኔታና የስርዓቶቹ ባህርያት የሚያያዘዉ? ይህ ክስተት ስትራቴጂያዊ ጥቅምን ወይም ታሪክን በሚገባ አለመተንተን እንዲሁም የጋራ እጣፈንታ በትክክል አለመረዳት ያስከተለዉ ሊሆን ይችላል? ስትራቴጂያዊ አቋሞቻቸዉ ወይም የዉጪ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት የወለደዉ ቢሆንስ? በአካባቢዉ ልዕለ ኃያል ሀገር ካለመኖሩ ጋር ተያይዞና የግብፅ በአጓዳኝነት መኖር ሲታይ ለግጭት ተጋላጭነቱ በንዑስ ቀጠናዉ ካለዉ የስልጣን መዋቅራዊ አደረጃጀት ጋር የተሳሰረ ይሆን? እንዲያ ከሆነ ይህንን መዋቅራዊ ችግር ለማረም ምን ማድረግ ይቻላል?” ሲሉ ብዙ ገጽ የሚወጣው የውይይት ጥያቄዎችን ፕሮፌሰሩ አስቀምጠዋል።


በሁለቱ መንግስታ መካከል ሰላም መስፈኑ ፋይዳው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄም ሰፋ አድርገው ተመልክተው ጫሪ ጥያቄዎችን አያይዘው ፕሮፌሰሩ ይህንን ብለዋል፣ “አከራካሪ ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ሰፈነ ማለት ለሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለመላዉ የቀጠናዉ አካባቢ ትልቅ የምስራች ነዉ። ግጭቱ ለአገራዊ ደህንነት ጠባብ አተረጓጎም ከመስጠትና መንግስታዊ ስልጣንን ለማስቀጠል ከሚወሰዱ እርምጃዎች የመነጩ ናቸዉን? ይህ ከሆነ እንዴት ማስተካከል ይቻላል? ወይስ ግጭቱ ዉስጣዊ የሃይማኖት፣ የጎሳና የባህል መከፋፈሎች የወለዷቸዉ ናቸዉ? መንግስታቱ ያለባቸዉ መዋቅራዊ አደረጃጀት ወይም የዴሞክራሲያዊ ዉክልና ክፍተት የፈጠራቸዉስ ቢሆን? ወይስ የግጭቱና አለመረጋጋቱ መንስኤ የፖለቲካ ኢኮኖሚዉ ነዉ? ከዚህ ጋር የተያያዘና እጅግ ጠቃሚ ነጥብ ደግሞ የድንበር ሁኔታና የታሪካዊ የባህር ወደብ ጥያቄን ይመለከታል።” ብለዋል።


በሁለቱ መንግስታት መካከል ሰላም ባይሰፍንስ በሚል ሌላ የውይይት ጋባዥ ነጥቦችም ፕሮፌሰሩ አስቀምጠዋል፣ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ትብብር ማዕቀፍ ካልገቡ በመካከላቸዉም ሆነ በአካባቢያቸዉ መረጋጋት ይኖራል ብለዉ ሊጠብቁ ይችላሉ? ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት እርስ በርስ እየተናቆሩ ቢቀጥሉ ለአካባቢዉ ሰላምና መረጋጋት የሚኖረዉ አንድምታስ ምን ሊሆን ይችላል? በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለዉ ግጭት በሌሎች የዓለም ክፍሎች ካሉ የጋራ ታሪክና ጥቅም ኖሯቸዉ በግጭት ዉስጥ ካለፉ አገሮች እንዴት ሊነፃፀር ይችላል?”


ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች በመነሳት ከሌሎች አካባቢዎች በማነፃጸር፣ “እስካሁን ሰላም ለማስፈን ከተደረጉት ሙከራዎች ምን ትምህርት መዉሰድ ይችላል? በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከታዩትና አገሮች ከግጭት ወጥተዉ ወደ ጋራ ደህንነትና ልማት እንዲሸጋገሩ ካስቻሉ ጥረቶችስ ምን ተመክሮ መቅሰም ይችላል? ሰላማዊ ዝምድናን የሚያበስሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች በማካሄድ ቀጣይነቶቻቸዉን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ቢደረግስ? ለጅማሬ ያህል የሁለቱ አገሮች ምሁራንና የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች መደበኛ ዉይይት እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቅድሚያ ቢሰጠዉ ፋይዳ ይኖረዉ ይሆን? ለእንደዚህ አይነት ዉይይት የፖለቲካ አመራሮች ተሳትፎ እንደ ቅድመ ሁኔታ መዉሰድ ያስፈልጋል? ወይስ ጎጂ ነዉ? ወይስ መቅደም ያለበት የጋራ ታሪክና አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ትስስር ነዉ? የሁለቱ አገሮች ምሁራን፣ ሃሳብ አፍላቂዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የሚያደርጓቸዉ ዉይይቶችና የሚደርሱባቸዉ ስምምነቶች በዋና ዋና እሴቶችና የወል ጥቅሞች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የአዲስ የትብብር ዘመን መሰረት ለመጣል ምን ያህል ይረዳሉ?” ሲሉ ቀጣይ ውይይቶችን በጉጉት እንዲጠበቁ መሰረታዊ ምላሽ የሚፈልጉ ምሁራዊ አተያየታቸውን አካፍለዋል።

የጋራ የውይይት መድረኩን ማዘጋጀት ለምን ያስፈልጋል?

 

የምክክር መድረኩ አስፈላጊነት ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን በአገሮቻቸዉ መካከል ሰላም ለማስፈን መደረግ ስላለበት ነገር ያሏቸዉን አስተሳሰቦች ወደ አንድ መአድ በማቅረብ ከላይ የሰፈሩትን ጥልቅ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና የጂ-ፖለቲካ ደህንነት ጥያቄዎችን እና ከሥር የሰፈሩ ጥያቄዎች ለማንሳት እና ለመጠየቅ አመቺ ሁኔታዎች ይፈጥራሉ ከሚል አስቻይ ሁኔታዎች በመነሳት ነው።


የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት በተመለከተ ያለዉ ልዩ ሁኔታ ምንድን ነዉ? ግንኙነታቸዉን በተመለከተ ሊኖሩ ይገባል የሚሏቸዉ ገዢ መርሆዎች ምንድን ናቸዉ? ይህንን ለማሳካት መቋቋም ያለባቸዉ ተቋማትስ ምን ዓይነት ናቸዉ? ስብሰባዎቹ ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን ከፊት ለፊታቸዉ የተጋረጡ ስጋቶች ምንነትና ዉስብስብነታቸዉ ላይ መግባባት እንዲፈጥሩ ይረዷቸዋል። ከምሁራንና ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት ግብአቶችን ለማግኘትም ይጠቅማሉ። ይህንን ፋይዳ ያለዉ ሂደት በጎ አቅጣጫ ሊያሲዝ በሚችል መርህ ከተመራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በተመለከተ የመጀመርያዉ ሁሉን አሳታፊ ቅኝት ሊሆን ይችላል። ሌሎች የመድረኩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይህንን መግባባት በቀጣይነት ሊያጠናክሩና ሊገነቡ ይችላሉ። ለዚህ መሳካት ደግሞ ከምንግዜም በላቀ መልኩ ለጋራ ተግዳሮቶች የጋራ አቀራረብ መገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል። ለኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና የደህንነት መስተጋብር መነሻ የሚሆንና መጪዉን ግንኙነታቸዉን በሚገዙ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ማዕቀፍ የዚህ ሂደት ዉጤት ሆኖ ብቅ ሊል ይችላል።


እየተከሰቱ ያሉት ማህበረሰባዊ መመሳቀሎች ሁለቱ አገሮች የተጋረጡባቸዉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አደጋዎች እና የአካባቢዉ ቀዉሶች በዜጎች ላይ የፈጠሩት ጭንቀት ተደምረዉበት አሁን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላለዉ ቀዉስ ጥራት ያለዉ ትንታኔ ማካሄድና ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ ተስማሚ ስትራቴጂዎችን መንደፍ ብሎም ለአዲስ የትብብር ዘመን መሰረት መጣል የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ረገድ መሻሻል ለማምጣት የረዥም ጊዜ ጥረትን ይጠይቃል። የመጀመሪያዉ ስብሰባ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ለሁለቱ ሀገሮች ዘላቂ የሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝበትን ሁኔታ ለመዳሰስ ጠቃሚ ይሆናል። የመጨረሻውን መጀመሪያ እርምጃ ለመራመድ ያለመ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
294 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 880 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us