“አገዛዙ፤ በአውሮፓ ከአንድ ግለሰብ ጋር አብረህ ተቀምጠህ ታይተሃል ብሎ የፖለቲካ ፓርቲ መሪን የሚያስር ይሉኝታ ቢስ ነው”

Wednesday, 27 December 2017 12:30

“አገዛዙ፤ በአውሮፓ ከአንድ ግለሰብ ጋር አብረህ ተቀምጠህ ታይተሃል ብሎ

የፖለቲካ ፓርቲ መሪን የሚያስር ይሉኝታ ቢስ ነው”

 

አቶ ጌታነህ ባልቻ የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር

 

በይርጋ አበበ

 

ሰማያዊ ፓርቲ ለተከታታይ ሶስት ሳምንታት በአምባሳደር ቴአትር አዳራሽ ከምሁራን፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፓርቲው ደጋፊዎች እንዲሁም የአገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል። ከተመሰረተ ገና ስድስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘውና በአመራሮች ውዝግብ የተነሳ የራሱ ጽ/ቤት የሌለው ሰማያዊ ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያካሂድ የአሁኑ በዚህ ዓመት ያካሄዳቸውን ውይይቶች ሁለት አድርሶለታል። ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽ ተመሳሳይ ውይይት መድረክ አካሂዶ ነበር።


ሰማያዊ ፓርቲ “ኢትዮጵያ ትጣራለች” በሚል መሪ ቃል ያካሄደውን ውይይት “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?” ሲል በመጠይቅ ይጀምራል። ለሶስት ሳምንታት የቆየው ይህ የውይይት መድረክ ምናልባትም ከዚህ በኋላ ተይዞ የነበረው የአራተኛው ሳምንት መርሃ ግብር እንደማይካሄድ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተገለጸላቸው መሆኑን የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በተላለፈ ውሳኔ እንደሆነ ተገልጿል። ፓርቲው ለሶስት ሳምንታት ያካሄደውን ውይይት አስመልክቶ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር እና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ የሰጡትን ምላሽ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ሰንደቅ፡- ፓርቲያችሁ “ኢትዮጵያ ትጣራለች” በሚል መሪ ቃል ለተከታታ ሶስት ሳምንታት ያካሄደውን የውይይት መድረክ በአጭሩ ያስታውሱን?


አቶ ጌታነህ፡- ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ስጋት እና ቀውስ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ይህንን ቀውስ ለመታደግ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት በሚል መነሻ ሃሳብ ለተከታታይ አራት ሳምንታት የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ተነሳን።


በመጀመሪያው ሳምንት “የአገር ሽማግሌዎች የአገርን ስጋት ከመቅረፍና ቀውሱን ከማረጋጋት አኳያ የሚኖራቸው ሚና” በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እና ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም መነሻ ሃሳብ አቀረቡ። በውይይት አዳራሹ የተገኙት ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ግለሰቦችም አስተያየት ሰጡበት። ከዚያ ተነስተን የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራንም የነበራቸው አስተዋጽኦ ምን ይመስል እንደነበር እና የተፈጠረውን ቀውስ መረጋጋት ለመፍጠር ምን አይነት ሃሳብ ነው ማቅረብ የሚኖርባቸው የሚለውን እንደ መነሻ ከቤቱ ውይይት ተነስቶበታል። ከዚያም ባለፈ በአዳራሹ ለተገኙት በርካታ ታዳሚያን ሁሉም በየቤቱ የምሁራን እና የአገር ሽማግሌዎች ሚና አገርን በማረጋጋት በሚለው ላይ እንዲወያዩ አድርገናል።


በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ ቋንቋን መሰረት አድርጎ የተመሰረተው የፌዴራል አወቃቀር ነው አሁን ለተፈጠረው ቀውስ እና ስጋት መነሻ የሆነው የሚል ግንዛቤ በብዙዎች ስነበረ በዚያ ላይ የሚያተኩር የመነሻ ሃሳብ እንዲያቀርቡ የተደረገው የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ እና የህግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ ነበሩ። በመነሻ ሃሳቡ ላይ የፌዴራል መንግሥቱ አመሰራረቱ የችግሩ ምክንያት ነው ወይስ አይደለም በሚለው ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።


በሶስተኛው ሳምንት ያካሄድነው ደግሞ አሁን በአገራችን ላይ ላለው ቀውስ እና አለመረጋጋት መፍትሔ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሀይማኖት ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት ሚና ምን መሆን አለበት በሚል ነበር የውይይት መነሻ ያደረግነው። ሆኖም ከሀይማኖት አባቶች ጥሪውን ተቀብለው መጥተው ውይይቱን ሊመሩልን አልቻሉም። ከሲቪክ ማህበራቱም ጥሪ ያቀረብንላቸው ‹‹የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ተቋም›› ጥሪውን ተቀብሎ ውይይቱን ሊመራ አልቻለም። በመሆኑም የቪኢኮድ ዋና ጸሀፊ አቶ ታደለ ደርሰህ እና የህግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ የመነሻ ሃሳብ አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።


እስካሁን የተካሄዱት ውይይቶች አሳታፊ እና ወቅታዊ ሀሳቦች የተነሱባቸው ናቸው። እኛም የምንፈልገው እንደዚህ አይነት ውይይቶች እንዲካሄዱ ነው። ውይይቶቹም እንዲቀጥሉ ነው የምንፈልገው። ምክንያቱም የውይይቱ ዋናው ዓላማው በዚህች አገር መረጋጋት እና ሰላም እንዲሰፍን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተቋም ውስጥም ሆነ በግሉ ወይም በአካባቢው ተመሳሳይ የውይይት ሃሳቦችን አንስቶ መወያየት አለበት።


ሰንደቅ፡- የውይይት መድረኩ የተዘጋጀበት ዓላማ የነገሩን ከሆነ ከዓላማው አኳያ ውጤቱን እንዴት ገመገማችሁት?


አቶ ጌታነህ፡- ፓርቲያችን በራሱ መንገድ ይህን ውይይት ያየበት የራሱ ግንዛቤ አለ። ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳነሳነው ይህች አገር አሁን ባለችበት ሁኔታ ኢህአዴግ ማስተዳደር አልቻለም። ስለዚህ ኢህአዴግ ማስተዳደር ካልቻለ አገር እንዳይፈርስ ምንም እንኳን የሰላማዊ የፖለቲካን እንቅስቃሴ እና የመገናኛ ብዙሃንን እንቅስቃሴ ቢያፍነውም የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ጉልህ ሚና ስላለው አገራችንን ከጥፋት ማዳን አለብን ብለን እናምናለን። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በግልጽ ጥሪ አቅርባለች። ይህች አገር ደግሞ የሁላችንም እንደሆነችው ሁሉ እያንዳንዱ ዜጋም የአገርን ጥሪ ተቀብሎ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት።


ነገር ግን ምሁራን ለምንድን ነው አደባባይ ወጥተው ሀሳባቸውን የማይገልጹት? የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምን ተዳከሙ? የሲቪክ ማህበራትስ ለምንድነው ድምጻቸው የጠፋው? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናይ፤ በተደጋጋሚ እንደምንለው ኢህአዴግ ለስልጣኑ ዋስትና ያሳጡኛል ብሎ በሚፈራቸው ላይ ያወጣቸው የመገናኛ ብዙሃን፣ የጸረ ሽብርተኝት፣ የበጎ አድራጎት ህጎች የጠቀስኳቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ አደባባይ ወጥተው የሚጠበቅባቸውን እንዳያበረክቱ አድርጓቸዋል።


በዚህ ውይይት ላይም ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራንና ተቋማት ያልተገኙት የአገራቸው ጉዳይ ስለማያሳስባቸው ሳይሆን ከኢህአዴግ የሚደርስባቸውን ጥቃት ከመፍራት አኳያ እንደሆነ እናምናለን። ይህ ደግሞ ስርዓቱ የጣለብን ችግር ነው።


ሰንደቅ፡- በአገራቸው ጉዳይ ኃላፊነት ይሰማቸዋል ያልናቸውን ምሁራን፣ ተቋማት እና ዜጎች ጥሪ አቅርበንላቸዋል ብለዋል። ጥሪውን ተቀብለው የቀሩ ድርጅቶች የትኞቹ ናቸው?


አቶ ጌታነህ፡- ለምሳሌ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት ደብዳቤ ጽፈንላቸው ነበር። ለማህበረ ቅዱሳን፣ የሀይማት ልሂቃን ለሆኑ ግለሰቦች እና ለምሁራንም ጥሪ አቅርበንላቸው ነበር። ነገር ግን ተገኝተው ውይይቱን አልተሳተፉም፤ የመነሻ ሃሳብም አላቀረቡም። አለመገኘታቸው ደግሞ ምናልባት የተለያየ ግንዛቤ ይዘው ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የፓርቲ ጥሪ ላይ ቢገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባል እንደሆኑ ተደርገው እንዳይታዩ። ነገር ግን የውይይት መድረኩ ነጻ ውይይት እንጂ የሰማያዊ ፓርቲ ብቻ እና የሰማያዊ ፓርቲን አመለካከት ብቻ የሚንጸባረቅበት አይደለም። በውይይት መድረኮቹ ላይ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ሁሉም ምሁራን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም፣ አቶ ስዩም ተሾመ፣ አቶ ተማም አባቡልጉ እና አቶ ታደለ ደርሰህ) የፓርቲያችን አባላት አይደሉም። ምሁራኑ በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን የሰጡትና የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት አገሪቱ ችግር ላይ ስለወደቀች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው። አገሪቱ ችግር ላይ እንደሆነች ደግሞ ኢህአዴግም ያምናል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልም በግልጽ የተናገሩበት ጉዳይ ነው።


ኢትዮጵያ ችግር ላይ መሆኗን ሁሉም የሚስማማ ከሆነ ከችግሩ ለመውጣት መፍትሔው ምንድን ነው? በሚለው ላይ መወያየቱ ነው አስፈላጊው እና ወቅታዊው ጉዳይ። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ባለቤቶች ናቸው አገራቸውን ከችግሯ ሊታደጓት የሚችሉት። ያንን ለማድረግ ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በነጻነት መነጋገር መቻል አለብን። ከዚህ በፊትም በተለይ ኢህአዴግ “ከእኛ በላይ አዳኝ ማንም የለም” የሚል ግትር አቋም ስላለው ነው ወደዚህ ችግር የገባነው። በ2007 ዓ.ም ምርጫ ተካሂዶ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ባለ በማግስት አገሪቱን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የሚጥል ቀውስ ተፈጠረ። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ወደ ቀውስ የገባነው የችግሩ መፍትሔ እኔ ብቻ ነኝ ከሚል አቋም የተነሳ ሌሎቹን አግልሎ በራሱ መንገድ የወሰደው የችግር አፈታት ውጤት ነው።


ሰንደቅ፡- የውይይት መድረኩን ለሶስት ተከታታይ ሳምንታት በሰላም ስታካሂዱ ብትቆዩም አራተኛውን ሳምንት ማካሄድ እንደማትችሉ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ትዕዛዝ ተሰጥቷችኋል። መረጃው ምን ያህል ትክክል ነው?


አቶ ጌታነህ፡- አሁን ከአንተ ጋር የማደርገውን ቃለ ምልልስ እንዳጠናቀኩኝ የምሄደው ወደ ማዘጋጃ ቤት ነው። ደብዳቤ አስገብተናል እሱን እየተከታተልኩ ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ስናደርግ ቆይተናል። ባለፉት ስድስት ዓመታት ሰማያዊ ምን ያበረከተው ነገር አለ? ወደፊትስ ተስፋችን ምንድን ነው? የኢትዮጵያን ችግርስ እንዴት አድርጎ ነው መታደግ የሚችለው? በሚሉት ነጥቦች ላይ ታህሳስ 22 የምስረታ በዓላችንን ምክንያት በማድረግ ውይይት እናካሂዳለን። ይደናቀፋል ብዬ አላስብም። ያስገባነውን የፈቃድ ደብዳቤም በበጎ ይመልሱልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ምክንያቱም አይታችሁት ከሆነ ውይይቱ ሲካሄድ ፖሊስ እንኳን የማይጠብቀው ፍፁም ሰላማዊ ስብሰባና ውይይት ነበር ስናካሂድ የቆየነው። በእርግጥ የመጀመሪያ ስብሰባችንን ስናካሂድ ቅስቀሳ በምናደርግበት ጊዜ አባሎቻችንን በማሰርና ንብረቶቻችንን በመያዝ እና በመሳሰሉት ማዘጋጃ ቤት እንቅፋት ሆኖብን ነበር። እንደዛም ሆኖ ግን ያሰብነውን የውይይት መድረክ ከማካሄድ አላገደንም። አራተኛውም ይካሄዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።


ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆኗን ገዥው ፓርቲ ሳይቀር ተናግረዋል። እናንተም ተመሳሳዩን አስተያየት ሰጥታችኋል። በፓርቲያችሁ እምነት አገሪቱ ከዚህ ችግር የምትወጣው በምን መልኩ ነው ብላችሁ ነው የምትገልጹት?


አቶ ጌታነህ፡- መፍትሄው በጣም ቀላልና ግልጽ ነው። የመጀመሪያው ቀላል መፍትሄ ስርዓቱ የመፍትሄ አካል ለመሆን ዝግጅቱን ማሳየት ነው። የአገሪቱን ትልቁን ስልጣን የያዘው እሱ (ኢህአዴግ) ስለሆነ። በተለመደው የችግር አፈታት መንገድ ማለትም ሰውን እያሰረ፣ እየገደለ እና እያፈናቀለ በጉልበትና በሀይል እየተጠቀመ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት እንቅፋት የሆነው እሱ ነው። ስለዚህ ለእውነተኛ መፍትሄ ቁርጠኛ መሆንና ይህንንም በተግባር ማሳየት አለበት።


ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ በቅርቡ ባካሄደው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የደረሰበትን ውሳኔ በመግለጫ አስታውቋል። በመግለጫው ላይም ለችግሮቹ መፈጠር ራሱን ተጠያቂ አድርጎ ለመፍትሄውም ራሱን እንዳዘጋጀ ተናግሯል። ለመሆኑ መግለጫውን አይተውታል ወይስ…?


አቶ ጌታነህ፡- እሱን እማ በፊትም ይሉት ነበር እኮ። ከአንድ ዓመት በፊት ተመሳሳይ ችግር በተፈጠረበት ወቅት “አሁን ያለንበትን ሁኔታ አይተን አገሪቱን ለማረጋጋት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀናል” ብለው ነበር። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአገሪቱ ችግሮች ተፈትተው ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈጠር አስታውቀው ነበር እኮ። አሁን የምናየው ነገር ግን ያ የኢህአዴግ የመፍትሄ መንገድ እና ችግር ፈች አለመሆኑን ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ነች። ኢህአዴግ አሁንም ደጋግሞ የሚገልጸውና የሚያስበው እሱ ብቻ የኢትዮጵያን ችግር እንደሚፈታ አድርጎ ነው። ነገር ግን ትክክለኛው የመፍትሄ መንገድ ኢትዮጵያ የሁሉም አገር ስለሆነች ችግሩ ትልቅና መጠነ ሰፊ እንደመሆኑ የመፍትሄው አካልም መሆን ያለብን ሁላችንም ነን።


ኢህአዴግ የሚለው ችግሩ የራሱ ባለሥልጣናት ግጭት የፈጠረው ስለሆነ የባለሥልጣናቱ ግጭት ሲበርድ የአገሪቱ ችግርም አብሮ ይጠፋል ነው። ይህ ፍፁም ስህተት ነው። የችግሩ ትክክለኛ መንስኤ ለ26 ዓመታት ሲጠራቀም የቆየ የጭቆና ቀንበር ጽዋው ሞልቶ ስለፈሰሰ ነው። ከዚህ ውጭ ግን “አይ እኔ አልገደልኩም፣ አላሰርኩም፣ ግፍ አልፈፀምኩም” የሚል ከሆነ መብቱ ነው፤ ግን አያዋጣውም። ምክንያቱም ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያዊያንን መብት እያፈነና እየነጠቀ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲሞክር ነው የታየው። ስለዚህ ለአገሪቱ ችግር መፍትሄ አመጣለሁ ብሎ ከልቡ ከተነሳ በመጀመሪያ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ያሰራቸውን የፖለቲካ መሪዎች ሊፈታ ይገባል። እነ በቀለ ገርባ፣ እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ ውብሸት ታዬ፣ እና እስክንድር ነጋን ሁሉ ይፍታ። ያንን ማድረግ ከቻለ ቢያንስ ሌሎቻችን መተማመኛ ይሆነንና ሳንፈራ ልንንቀሳቀስ እንችላለን። ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ሌሎች ምሁራንና የሀይማኖት ልሂቃን ወደ ውይይት መድረኩ መጥተው ያለመናገራቸወ ምክንያት የእነ ዶ/ር መረራ እጣ ፈንታ ይደርስብናል ብለው በመስጋት ነው። ስጋታቸው ደግሞ መሠረታዊ ነው። ምክንያቱም እንኳን አገር ውስጥ በግልፅ አቋምን ገልፆ ለሚናገር ምሁር ቀርቶ አውሮፓ ሄዶ ከአንድ ግለሰብ ጋር አብረህ ተቀምጠህ ታይተሃል ብሎ የፖለቲካ ፓርቲ መሪን የሚያስር ይሉኝታ ቢስ አገዛዝነው። ስለዚህ አገር ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ ችግር ላይ ናት ብለው ቢናገሩ የሚጠብቃቸውን ያውቃሉ።


ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ ለመፍትሄ ቁርጠኛ ከሆነ እኛ የመፍትሄ አካል ሆነን ለችግሩ መፍትሄ እናመጣለን እያሉን ነው። ለመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ይህን የመሰለ ለትልቅ አገራዊ ጉዳይ እምነት የሚጣልበት የፖለቲካ ቁመና አለው?


አቶ ጌታነህ፡- በተደጋጋሚ ሲነገር የምንሰማው አንድ አስተያየት አለ። ኢህአዴግ ከሌለ ማን አለ ይህችን አገር ሊረከብ የሚችል? ይባላል። ነገር ግን ይህ ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት የሆነው ነጥብ ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ የሚያደርገው አንዱ ኢህአዴግ ነው። ስብስቦ ያስራል፣ እንዳንወያይ መድረክ ይከለክላል፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳናካሂድ ይከለክላል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት በተለይ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ድርጅት ጠንክሮ የሚወጣው የሰላማዊ ትግል የሚጠይቀውን መሠረታዊ ጥያቄ ስትመልስ ነው።


መታወቅ ያለበት ነገር ኢህአዴግ የቱንም ያህል አፈና እና በእስር መፈናፈኛ ቢያሳጣንም ሀሳባችንን ግን በግልፅ እያስታወቅንና ለህዝብ እየገለፅን ነው። ያንን ባናደርግ ኖሮ እንደተባለው “ፓርቲ የለም” ቢባል ትክክል ይሆናል። ሁሉም ፓርቲዎች ሲዳከሙና ሲከስሙ ከሁሉም ላይ የኢህአዴግ እጅ አለበት።


ወደሰማያዊ ስንመጣ ገና ስንቋቋም የዛሬ ስድስት ዓመት ታህሳስ 22 ቀን መስርተን እውቅና ሳይሰጠን ስምንት ወር ነው የቆየነው። አዋጁ የሚለው አንድ ፓርቲ ከምስረታ በኋላ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እውቅና ይሰጠዋል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሰማያዊ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዶ ያሳለፈውን ውሳኔ እውቅና ለመስጠት 11 ወር ወስዶበታል። በፓርቲያችን ውስጥ በተፈጠረው አለመግባባት ድንገተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ የተላለፈውን ውሳኔም እውቅና ለመስጠት ስድስት ወር ፈጅቶበታል። ኢህአዴግ በምርጫ ቦርድ በኩል ይህን የመሰለ ውሳኔ የሚያስተላልፈው ህዝቡ በፓርቲዎች ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ የሴራ ፖለቲካ ነው። እንደዚህ እየተደረገብንም ግን እኛ መታገላችንን አላቆምንም።


ሁላችንም የፓርቲ አባል ሆነህ ወደ ተቃውሞው መስመር ስንመጣ በግል ህይወታችንና ስራ ቦታችን እንዲሁም በቤተሰቦቻችን ላይ የማይደርስብን በደል የለም። በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ሆነን የምትታገል ከሆነ ይህ እንደሚደርስብህ የታወቀ ነው። ወደጥያቄህ ስመጣ ሰማያዊ ፓርቲም የህዝብን አደራ ለመቀበል ብቁ ፖለቲካዊ ቁመና አለው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
221 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 145 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us