“በሕግ የበላይነት የሚመጣ እርቅ ለሁሉም ወገን አዋጪ ነው”

Wednesday, 27 December 2017 12:37

“በሕግ የበላይነት የሚመጣ እርቅ ለሁሉም ወገን አዋጪ ነው”

አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር
የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት

 

 

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ “በክልላችን ያለውን የልማትና የዴሞክራሲ እውነታ በአጠቃላይ እና በቅርብ ጊዜ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ የሶማሌ እና የኦሮሞ ተወላጆች ወገኖችን ከመመለስና ከማቋቋም አንፃር ያለውን ሁኔታ” ለማስጎብኘት ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ታህሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ጅግጅጋ ከተማ ደርሰን ተመልክተናል።


በጅግጅጋ ከነበሩት ፕሮግራሞች መካከል ከክልሉ ፕሬዝደንት ከአቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ጋር የተደረገ ቃለምልልስ አንዱ ነው። ከጋዜጠኞችም በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው ፕሬዝደንቱ ምላሽ ሰጥተዋል።


በዚህ ፖለቲካ ዓምድ ሥር ከሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለቀረበው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ አትኩሮት በመስጠት እና የተወሰኑ በሌሎች ጋዜጠኞች የቀረቡ ጥያቄዎች ምላሾችን አካትተን አቅርበናል።

*** *** ***

 

ሰንደቅ፡- በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስና ለጠፋው ህይወት መነሻ ተደርገው የሚቀመጡት ሦስት ምክንያቶች አሉ። አንደኛው፣ በ1997 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች በተደረገው የማካለል ሥራ ደስተኛ ባልነበሩ ወገኖች ግጭቱ መነሳቱ ይነገራል። ሁለተኛ፣ በኦሮሚያ ክልል አመራሮችና በአብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ለግጭቱ መነሻ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ መሣሪያ ባልታጠቁ ንጽሃን የኦሮሞ ልጆች ላይ ግድያ በመፈጸሙ እንደሆነ ይገራል። ሶስተኛው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሚመሩት መንግስት በበኩሉ ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው ለግጭቱ ተጠያቂዎች ሲል ይከሳሉ። በእነዚህ ነጥቦች ላይ ክቡር ፕሬዝደንት የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?


አቶ አብዲ፡- በመጀመሪያ ኮንትሮባንድ ምን ማለት ነው? ኮንትሮባንድ፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ አሠራር በሕገወጥ መንገድ የወጣ ወይም የገባ ዕቃ ማለት ነው። ዕቃው ብቻውን ኮንትሮባንድ አያስብለውም። በሕገወጥ መንገድ ከወጣ ወይም ከገባ ኮንትሮባንድ ዕቃ ይባላል። ስለዚህ ኮንትሮባዲስቶች ከማን ጋር ነው የሚጣሉት? ከሕዝብ ጋር አይጣሉም። የሚጣሉት ከፀረ-ኮንትሮባንዲስቶች ጋር ነው። ነገር ግን በንግድ ሽያጭ እኔ ነኝ.. እሱ ነው የምነግደው በሚል የሚጣሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ይህ የሚጣራ ነው የሚሆነው። በዚህ ሒደት ኪራይ ሰብሳቢዎች ሊጣሉ ይችላሉ።


ብዙ አይነት ኮንትሮባንድ አለ። ኢምፖርት-ኤክስፖርት አለ። ለምሳሌ የዶላር ኮንትሮባንድ አለ። በታሪክ ከጅግጅጋ ወይም ከቶጎ ውጫሌ ተነስቶ ወደ መሐል ሀገር የሚሄድ የዶላር ኮንትሮባንድ የለም። ብዙ ጊዜ የዶላር ኮንትሮባንድ የሚያዘው ከአዲስ አበባ ወደ ቶጎ ውጫሌ ወይም ወደ ጅግጅጋ ሲላክ ነው።


አንድ አዲስ ባንክ የመጀመሪያው ቅርንጫፍ አዲስ አበባ ሲከፈት፣ ሁለተኛው ቅርንጫፍ ቶጎ ውጫሌ ነው የሚከፈተው። ለምንድን ነው የሚከፈተው? ኮንትሮባንድ የዶላር እንቅስቃሴ ለማግኘት ተብሎ ይመስለኛል።


ሌላው ከ1997 ዓ.ም. የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ሕግ ሆኖ ነው የተረከብነው። ልንጥሰው አንችልም። ከእኛ በፊት የነበረው ጉዳይ ፍትሃዊ ነው፣ አይደለም የሚለው ጥያቄ ነው የሚሆነው። እኛ የተረከብነው ሕጋዊ የሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝበ ውሳኔ የተሰጠባቸው ቀበሌዎች ወደ ኦሮሚያ የተካለለውን በኦሮሚያ፣ ወደ ሶማሌ የተካለለውን በሶማሌ ግዛት ውስጥ ሆነው ነው። እኛ እምቢ የምንለው አይደለም። ቅሬታ ኖረ፣ አልኖረ ሕግ ሆኖ ነው፤ የተቀበልነው። ከእኛ በፊት የተወሰነ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነ ሕግ ሆኖ ቀርቦ ነው የተረከብነው። አፈፃፀም እኛን የጠበቀን የለም። ስለዚህ ከግጭቱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።


ነገር ግን ሕዝበ ውሳኔውን ወደታች የማውረድ ሥራዎች ቀርቶ ነበር። ለምሳሌ ትንሽ ቀበሌ የነበረው አድጎ ሰፍቷል። ብዙ ጂኦግራፊካል ለውጦች አሉ። ሕዝበ ውሳኔውን በተመለከተ የትኛውም አመራር ቅሬታ ቢኖረው ሕግ ሆኖ ስለተቀበልነው፣ አጀንዳ አይደለም። አጀንዳው ሕዝበ ውሳኔውን መሬት ማስነካት ነው። በሁለታችንም ከስምምነት ተደርሷል፣ አሁን በተፈጠረው ጉዳይ ነው እንጂ ወደ መሬት እንደምናደርሰው ቃል እገባለው።


ሌላው፣ በሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች መካከል መወነጃጀል አለ። በሶማሌ በኩል፣ የኦሮሚያ የፀጥታ አካል ነው በሶማሌ ግዛት ገብቶ እንደዚህ ያደረገው ሲሉ እንሰማለን። በኦሮሚያ በኩል፣ የሶማሌ ልዩ ፖሊስ በግጭቱ ድንበር አካባቢ ተካፍሏል ነው የሚሉት። ስለዚህ ይህንን ማጣራት ያስፈልጋል። የትም ቦታ ግን፣ መወነጃጀል አለ። ለሚዲያ የማይቀርቡ ነገሮችን ለመናገር አልፈልግም። ሕዝብን የሚያስተሳስር እንጂ ሕዝብን የሚያራርቅ ክልሎችን የሚያራርቅ ነገሮች ከመናገር መቆጠብን እመርጣለሁ። እውነቱ ተጣርቶ እርምጃ መወሰድ ግን አለበት። የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፤ ብዬ አምናለሁ።


ልዩ ፖሊስን በተመለከተ ግን ለክልሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ፀጥታን ለማስከበር አስተዋጽኦ ያበረከተ እና መስዋዕትነትም የከፈለ ነው። እነሱን ለማገዝ ብቻ ተብሎ አካላቸው ጎድሎ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በአካል ሄዳችሁ መመልከት ትችላላችሁ። ለዚህች ሀገር የተሰው፣ ውድ አካላቸውን ያጡ ናቸው።


አንድ የፀጥታ ኃይል በዲሲፕሊን ካልተመራ፣ ግምገማ ካልተገመገመ፣ ተጠያቂነት ከሌለው በግለሰብ ደረጃ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እንደ መዋቅር ግን፣ ልዩ ፖሊስ ያገሩን ፀጥታ በተለይ በክልሉ ውስጥ የነበሩ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ደምስሰዋል። በዚህ ሥራቸው ብዙዎች ስለሚጠሏቸው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ያደርጉባቸዋል።


ሰንደቅ፡- ቀውሱ በልዩ ፖሊስ ተከሰተ ከተባለም በኋላ ለጠፋው ሕይወት የተጠየቀ አካል የለም፤ አወዳይ ላይ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው በሶማሌ ዜጎች ላይ ግድያ ተፈጽሟል፣ የተጠየቀም አካል የለም፤ የአወዳይን ቀውስ ተከትሎ በጅግጅጋ በተነሳው ቁጣ ከ600 ሺ ዜጎች በላይ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለዋል ተብሏል፤ የተጠየቀ አካልም የለም። ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በሶማሌ ዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ብለዋል፤ የተጠየቀ አካል የለም። የግጭቱ ሒደት በሕግ የበላይነት ባለመያዙ የከፈላችሁት ዋጋ አይደለም? አሁንስ በሁለቱ ክልሎች እርቅ ይደረግ ሲባል “አንተም ተው” “አንተም ተው” በሚል መልኩ ወንጀል የሰሩ ሰዎች የሚያመልጡበትን መንገድ ወይንስ እያንዳንዱ ሰው በተሳተፈበት የወንጀል ድርሻ ተጠያቂ በማድረግ የሚመጣ የእርቅ መንገድ ትከተላላችሁ?


አቶ አብዲ፡- እንዳልከው፣ አንተም ተው አንተም ተው የሚለው እርቅ መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ። የሕግ የበላይነት ይከበር የሚለው አማራጭ ነው የሚያዋጣን። ለምሳሌ በምዕራብ ሐረርጌ የተፈጠረውን ግጭት ለኦሮሚያና ለፌደራል መንግሥት ትተን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የማይታወቅ ጅምላ ጭፍጨፋ የፈጸሙትን አካሎች ወይም ጸረ-ሕዝብ ኃይሎችን የገቡበት ቦታ ገብቶ ተፈልገው የሕግ የበላይነት መስፈን አለበት።


በአወዳይ ላይ የተመጸመው ድርጊትም በሕግ የበላይነት መዳኘት አለበት። እንዲሁም በኦሮሞ ልጆች ላይ ችግር ያደረሰው ሶማሌም ታስሮ ለሕግ መቅረብ አለበት፤ የሚል አመለካከት ነው ያለን። በሁለቱ ሕዝቦች ላይ ወንጀል የፈጸሙት በጥፋታቸው ልክ ተመጣጣኝ ቅጣት ማግኘት አለባቸው የሚል አመለካከት እና አማራጭ ነው የምንወስደው። የሕግ የበላይነት መከበር አለበት።


ሰንደቅ፡- ጅግጅጋ ተዘዋውሬ አይቻለሁ፤ በኦሮሚያ ልጆች ይዞታ የነበሩ ሆቴሎችና ሱቆች ተዘግተው ተመልክቻለሁ። እንደሚታወሰው እርስዎ የሚመሩት የሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተፈጸመው ነገር ስህተት እንደነበር አምኖ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ መስማማታችሁን ገልፃቹሁ ነበር። ዜጎችን የመመለሱ ሒደት በሚፈለገው ደረጃ አይደለም። በጣም የዘገየ ነው። ከዚህ መነሻ፣ እርስዎ የሚመሩት የፖለቲካ አመራር እና በኦሕዴድ የፖለቲካ አመራር መካከል ያለው ግንኙነት ምንያህል ጤናማ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል? የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ አይቀድምም ነበር ወይ?


አቶ አብዲ፡- በግጭቱ ምክንያት አንዳንዴ የመወነጃጃል ነገር አለ። ፌደራል መንግስት የተፈጠሩትን ችግሮች እያጣራ ነው የሚገኘው። በግለሰብ ደረጃ በመካከላችን ቅሬታ የለም። የተዘጉ ቤቶች እንዳሉ ነግርኽኛል፤ ለምን የተከፈቱ ቤቶችንስ አላየህም?


ሰንደቅ፡- ሥራ የጀመሩ አሉ። ሆኖም ከነበረው ጊዜ አንፃር ክፍተቱ ትልቅ መሆኑን ለማንሳት ነው?


አቶ አብዲ፡- እነሱንም ከተመለከትክ አመሰግናለሁ፤ መመልከትህን ስላልሰማሁኝ ነው። የተከፈቱም ያልተከፈቱም አሉ። ያቀረብነውን ጥሪ ተቀብለው የመጡ አሉ። ጥሪያችንንም ሳይቀበሉ የቀሩ አሉ። ሆቴሎች፣ ጋራዦች የነበሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተከፍተዋል። ሌሎቹም ደረጃ በደረጃ በሚፈጠር መተማመን ይመጣሉ ብዬ፤ እገምታለሁ።

 

በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አባላት የቀረቡ ጥያቄዎች


ጥያቄ፡- ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ክልሉ ቢመለሱ ዋስትና እንሰጣለን ብላችኋል። እርስዎም በግልዎ ኋላፊነት እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ለተመላሾች የምትሰጡት ዋስትና ምንድን ነው?


አቶ አብዲ፡- ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች በሶማሌ ክልል ውስጥ ይኖራሉ። የተፈናቀሉት ከጅግጅጋ አካባቢ ብቻ ነው። ከሌላ ወረዳ አልተፈናቀሉም። ከጅግጅጋ ቀጥሎ ከቶጎ ውጫሌ ነው የተፈናቀሉት። ይህንን እውነታ ፌደራል መንግስት፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ሕዝቡም ያውቃሉ።


እንደ ክልል አመራር ከጅግጅጋ ሲፈናቀሉ ካራማራ ድረስ ሄደን አለመለመናችን ይቆጨኛል። እንኳን በድጋሚ እንዲፈናቀሉ፣ የተፈጸመውም ይቆጨናል። አሁንም ያሉበት ቦታ ሔደን ጥሪያችን ደግመን ደጋግመን ወደቤታቸው ወደቄያቸው እንዲመለሱ እንለምናለን፤ እንጠይቃለን። መደረግም ያለበት ይህ ነው። በዚህ ጉዳይ ከፌደራልም ሆነ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅርበት እንሰራለን።


ዋስትና እንሰጣለን ለሚለው በፊት እንደነበረ አብረን እንኖራለን። በወቅቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ትኩሳት አሁን ወርዷል። በኦሮሞነቱ የሚያጠቃው ኃይል እንደሌለ ነው ዋስትና የምንሰጠው። ኦሮሞ ስለሆኑ አይፈናቀሉም። ችግር አይተህ ነው፣ መፍትሄ የምታመጣው። ኦሮሞን በሱማሌ ክልል እንዳይኖር መከልከል አንችልም፤ ሕገ መንግስታዊ መብቱ ነው። ብንፈልግም አንችልም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ቦታ የመኖር መብት አለው። በወቅቱ በብሔረሰቦች መካከል የተደረገ ግጭት ስለሆነ እንጂ በሕገ መንግስታችን እና በሕግ - ሕገወጥ ተግባር ነው።


ለምሳሌ ኦሮሞ ብቻ ስለሆነ ምንም ጥፋት ሳያጠፋ መፈናቀሉ ስህተት ነው ብዬ ነው የምወስደው። በአወዳይ ስለተደረገው ነገር አያውቅም። በሌላ በሶማሌ አካባቢ ስለተደረገውም አያውቅም፣ በእሱም ውሳኔ የተደረገ አይደለም። በዚህም መልክ መፈናቀሉ ይቆጨናል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
244 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 146 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us