ማረፊያ አልባው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ መግለጫ፤ የሕግ በላይነትን ለማስከበር ዋስትና አለማቅረቡ እንዴት ይታያል?

Wednesday, 03 January 2018 16:42

 

ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለአስራ ስምንት ቀናት ሲያደርግ የነበረውን ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ ይፋዊ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው። 

 

ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት ፈተና በገጠመው ወቅት በርካታ መግለጫዎች ማውጣቱ የአደባባይ እውነት ነው። መግለጫዎችን ለማስታወስ በ1993 ዓ.ም. “በድርጅቱ ውስጥ አጋጥሞ በነበረው የጥገኛ ዝቅጠት፣ የትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰቦች ለአጭር ጊዜ እንደ ሰደድ እሳት የመቀጣጠል ምልክት አሳይተዋል” የሚል ይዘት ያለው መግለጫና ትንታኔ አቅርቧል። በሕዳር 2004 “የሕዳሴው መድረክና የአመራር ጥያቄ” በሚለው ትንታኔው፣ “የሕዝብ ጥያቄዎች ወይም ፍላጎቶችን በመለየት ለመፍታት የተዘጋጀ አመራር ሕብረተሰቡን በተሻለ ደረጃ ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ የለውጥ ሃሳቦችን የማመንጨት ሰፊ እድል አለው” የሚል ይዘት ያለው ሰፊ ጽሁፍ በመጽሄት ጠርዞ አስነብቧል። ከየካቲት እስከ መጋቢት 2009 ዓ.ም. በድርጅቱ ልሳን መጽሔት በአዲስ ራዕይ “በጥልቅ የመታደስ ጉዞዖችን” የሚል ግምገማዊ ጹሁፍ እና በምልሰት ወደ 1993 ዓ.ም. በመመለስ፣ “ከስር-መሰረታቸው ይነቀላሉ ያልናቸው ጠባብነትና ትምክህተኝነት አሁን የት ደረሱ?” በሚል ጠያቂ ጹሁፍ ድርጅቱ ዝርዝር ነገሮች አቅርቦ፤ አስነብቧል።


እንደተጨማሪ፣ በባሕርዳር እና በመቀሌ የድርጅቱ ጉባኤ ሲካሄድ፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓቱን እንደደፈቀውና ተጨባጭ አደጋዎች እንደተጋረጡበት፤ የድርጅቱ አባሎች እውቅና የሰጡበት ሁኔታዎች ነበሩ። በዝርዝር መመልከት የሚፈልግ አንባቢ የድርጅቱን የሁለቱ ጉባኤዎችን የተጠረዘ ሰነድ መመልከት ይችላል። ከላይ የወጡትን መግለጫዎችና ትንታኔዎች ደምሮ መመልከት የሚችል ሰው፤ ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚው በተሰጠው የመግለጫ ይዘት ላይ አዲስ ነገር አያገኝም። መፍትሄ አልባ ተደማሪ ችግሮች ከመሆናቸው ውጪ፤ መግለጫው ጠብ የሚል ነገር የለውም። ለችግሮቹ መፍትሔ የላቸውም የሚል አጠቃላይ ድምዳሜ ውስጥ መድረስ ግን አስቸጋሪ ነው።


በዚህ ጸሐፊ እምነት እስከዛሬ ድረስ ኢሕአዴግ መንግስት ሆኖ ካወጣቸው መግለጫዎች መካከል፣ በ1993 ዓ.ም. የወጣው መግለጫ ብቻ በሰዎች ተጠያቂነት ላይ ማረፍ የቻለው። የተሰጠው ውሳኔ ትክክል ወይም ሰህተት ነበር የሚለው ለጊዜው የጸሐፊው የትኩረት ነጥብ አይደለም። ከአሰራር አንፃር ሲታይ ግን፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ግምገማ ሲያደርግ፤ ችግሮችን ይለያል፤ ለችግሮቹ መፈጠር ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦችን ለይቶ ያስቀምጣል፤ ወደፊት ችግሮቹን በማስተካከል የቀጣይ ጉዞ መንገዶችን ያመላክታል፣ ለተግባራዊነቱ የማያወላዳ ውሳኔዎችን ያሳልፋል፣ ያስፈጽማል። ከእነዚህ መመዘኛዎች አንፃር በ1993 ዓ.ም. የወጣው መግለጫ በአንፃራዊነት ሚዛን ይደፋል። በሀገሪቷም ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች በተቀመጠው አቅጣጫ መመልከት ተችሎም ነበር።


ከ1993 ዓ.ም. ውጪ የተሰጡት መግለጫዎች ትንታኔዎች እንዲሁም ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለአስራ ስምንት ቀናት ሲያደርግ የነበረውን ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ የተሰጠው መግለጫን ጨምሮ፤ ማረፊያ አልባ መግለጫዎች ናቸው። ከመጠየቅም ከማስጠየቅም የጸዱ፤ የሕዝብ ወገንተኝነት የሌላቸው ባዶ መግለጫዎች ናቸው።


የሕክምና ባለሙያዎች ለእንደዚህ አይነት መግለጫዎች ተመሳሳይ የሆኑ ማሳያዎች አሏቸው። አንዱ፣ Placebo effect - the tendency of any medication or treatment even an inert or ineffective one, to exhibit results simply because the recipient believes that it will work. መግለጫዎቹን ከላይ ከሰፈረው የሕክምና አገላለጽ ስንመለከታቸው፤ መግለጫው በራሱ ምንም ፋይዳ የሌለው፣ ሆኖም መግለጫው ችግሮቹን ይቀርፋል ብሎ የፓርቲው አባል ወይም ሕዝቡ ከተቀበለው ለተወሰነ ጊዜ መግለጫው ማስታገሻ ሊሆን ይችላል።


ሌላው፤ Band-aid - an adhesive bandage, a small piece of fabric or plastic that may be stuck to the skin in order to temporarily cover a small wound. በዚህኛው የሕክምና ባለሙያዎቹ አቀራረብ መግለጫውን ስንፈትሸው፣ ቢያንስ የታህሳስ 21 ቀን 2010 መግለጫ እንዳስቀመጠው “…የሚያስጎመዥ እውነታ ከቅርብ አመታት ወዲህ በመታየት ላይ ባሉ ጊዜያዊ ችግሮች የተነሳ ለአደጋ እየተጋለጥንና ለሁሉም ማሕበረሰቦቻችን የስጋት ምንጭ መሆን በጀመረ አዲስ ክስተት መልክ የሚገለጽበት አዝማሚያ ሰፋ ብሎ ታይቷል” ይላል። መግለጫው “ጊዜያዊ” እና “አዲስ ክስተት” በሚል የችግሮቹን ክብደትና ሥረ-መሰረታቸውን እውቅና በነፈገ መልኩ ለመሸፈንን መሞከሩን ያሳያል።


በአጠቃላይ ከ1993 ዓ.ም. መግለጫ ውጪ ያሉት፤ መግለጫዎች ዋና መገለጫቸው ማረፊያ አልባ መሆናቸው ነው። “ድርጅት”፣ “ፓርቲው” እና “ሥራ አስፈፃሚው” በሚሉ ግዑዝና የወል ተጠያቂነት በሚሰጡ ሐረጎች የሕግ የበላይነት በግለሰቦች ላይ እንዳያርፍ ሽፋን የሚሰጡ አሰራሮችን የሚገልጽ ባዶ መግለጫዎችን መስማት የተለመደ ነገር እየሆነ መምጣቱ፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተጠያቂዎች እስከወዲያኛው ከመጠይቅ ያመልጣሉ ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል።

የታህሳስ 21 መግለጫ፣ ምን ችግሮችን ለየ?


ረጅም አመታት በሰላም በኖረችው አገር ውስጥ የስጋት መንፈስና ጭንቀት ተፈጥሯል፣ ከበየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሰው ሞትና ከንብረት ውድመት በዘለለ የሃገራዊ ሕልውናችን ለአደጋና ሕዝባችንን ለጥፋት ቋፍ ያደረሱበት ሁኔታ ከመኖሩ በላይ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትለዋል።


በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱና ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ አልተቻለም፣ ዜገች በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸው የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መሆን በሚገባው ደረጃ ሳይፈፀም ቆይቷል፣ መንግስት የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጀክቶት ዙሪያ የሚታዩ የአፈፃፀምና የስነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነመንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት ታይቷል።


በአንድ ወይም በሌላ ብሔር ህዝብና ድርጅት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን አሉ፤ የውሳኔዎችን በታማኝነትና በቁርጠኝነት የመፈፀም ዲሲፒሊን የላላ ነው፣ ችግሮችና ልዩነቶች በግጭት መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ ታይቷል።


በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር የሰደደ ነው፣ በአመራሩ ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነትና ጥራት የለም፣ በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ስልት ወደመሆን ተሸጋግሯል፣ ጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርህ አልባ ግንኙነት ነግሷል።


የሃገራችን ሚዲያና ፕሬስ በሚገባው ደረጃ ነፃነታቸው ተጠብቆ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም፣ ህብረተሰብ በመገንባትና በህገመንግስታዊ ስርዓታችን ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እየተገባው የህዝብ የተደራጀ ሲቪል እንቅስቃሴ እንዳልተጠናከረ አረጋግጧል።


መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴያችን በአመራር ድክመት ምክንያት ለበርካታ ችግሮች ተጋልጧል፣ በየደረጃው የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በቅን ልቦናና መንግስታዊ ሕግና መመሪያዎችን በተከተለ አካኋን ህዝቡን የሚያገለግሉና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡበት እድል ቀንሷል።

 

ችግሮቹን የፈጠረው ማን ነው?


የተፈጠሩት ችግሮች በዋነኛነት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ድክመቶች መሆናቸውን ኢህአዴግ በሰሞኑ መግለጫው ያምናል።


ስራአስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱና የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተናጠልና በጋራ፣ስትራተጅያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር ነው።


የኢህአዴግ ሥራአስፈፃሚ ኮሚቴና የመንግስት የበላይ አመራሮች ወቅቱ የሚጠይቀውን ስትራቴጂያዊ አመራር የመስጠት ጉድለታቸው ሰፊ በመሆኑ የተፈጠረ ነው።


ከፍተኛ አመራሩ ችግርን አስቀድሞ የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሠረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ይዟል።


በመሆኑም ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል ይላሉ።


ኢሕአዴግ እና መግለጫው ተቀባይነት የሚያሳጣቸው የችግሮቹን ፈጣሪዎች በስማቸው መጥራት የሕግም የሞራልም አቅም ስለሚያጡ ነው። ሰይጣንን ሰይጣን ማለት አይችሉም ወይም አይፈልጉም። ሾላ በድፍኑ እንደሚባለው፣ ሥራ አስፈፃሚው ኃላፊነት ይወስዳል ይላሉ። በግለሰብ ደረጃ በዚህ መሰል ሀገራዊ ቀውስና ውድመት ላይ ተሳታፊ የነበሩትን ግለሰቦችን አሳልፈው የመስጠት አቅም የላቸውም። ለዚህም ነው፣ መግለጫው ማረፊያ አልባ መግለጫ የሚሆነው።


በአንጻሩ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ለጠፋው ጥፋት በቡድን ኃላፊነት ሲወስድ በሕግ ተጠያቂነቱንም አብሮ እንደሚወስድ የገባው አይመስልም። በቡድን ተጠያቂ ነኝ የሚለው አካል ከሀገሪቷ ሕግ አንፃር እንዴት በሥልጣን ላይ ሊቆይ እንደሚችል አሁንም ከኢህአዴግ ተጨማሪ ማብራሪያን የሚፈልግ ጉዳይ ነው።


ሌላው የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ የሚጠየቀው፣ በፓርቲው በተሰጠው የሥራ ድርሻ መሰረት መነሻ ሲሆን ጠያቂዎቹም አባላቱ ብቻ ናቸው። በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስትን ለማስተዳደር ኃላፊነት የወሰደው እና ሥርዓተ መንግስት የዘረጋው ገዢው ፓርቲ፣ የመንግስት ስልጣንን የያዙ የፓርቲው ተሿሚዎችና ሲቪል ተሿሚዎች የሚጠየቁት በኢትዮጵያ ሕግ መሆኑን መሰመር አለበት።


በመንግስት ስልጣን ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች እንደፓርቲ ወይም እንደፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አይደለም የሚጠየቁት፣ በተሰጣቸው የመንግስት ኃላፊነት ነው የሚጠየቁት። ለምሳሌ በመሰረተ ልማት ወይም በስኳር ልማት ወይም በኃይል አቅርቦት ላይ የተሾመ ኃላፊ፣ የሚያስተዳድረው የመንግስት ንብረት በመሆኑ ካጠፋ የሚጠየቀው በኢትዮጵያ ሕግ እንጂ በፓርቲው የውሰጠ ደንብ አይደለም። ገዢው ፓርቲ በየትኛውም መመዘኛ ከሀገሪቷ ሕግ በታች መሆኑ ሊሰመር ይገባል። ተጠያቂ አባላቱም በስመ-ግምገማ ከሕግ ተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም፣ አይገባምም።


ስለዚህም በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብት፣ በልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፍ በተፈጸሙ ጥፋቶች ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች መንግስት ማቅረብ እስካልቻለ ድረስ፣ መግለጫው ማረፊያ አልባ ከመሆኑም በላይ ባዶ ነው። የተፈጠረውንም ችግር ከሥር መሰረቱ አይፈታም። እንደሀገር ውድቀትን ከመጋበዝ ውጪ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ምክንያቱም የሕግ የበላይነት ካለተጠያቂነት ዋጋ የለውም፣ ውጤቱም አናርኪ የሆነ ሥርዓት መፍጠር ብቻ ነው።

 

የመግለጫው መደምደሚያ ምን ይላል?


የሕዝባችንን ሰላማዊ ኑሮ የሚያውኩ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች ከህዝብ ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ለማዋል መንግሥት ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ እንዲያስፈፅም ተወስኗል። የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ላፍታም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደማይገባውና በዚህ ረገድ የሚታዩ የህግ ጥሰቶችን በመቆጣጠር ህግና ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ማስፈን እንዳለበት ተወስኗል።


በየአካባቢው በሕገወጥ መንገድ የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት፣ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ መብት የማወክ እንዲሁም የሕዝቡን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ የቡድንም የተናጠልም እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ይደረጋል።


በወሰንም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የሚያጋጥመውን ሞትና መፈናቀል ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ወስኗል። በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ የተፈጠረው የዜጎች ሞትና እንግልት እንዲሁም የመቶሺዎች መፈናቀል በአስቸኳይ ተገቶ ተፈናቃዮች መደበኛ ህይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ የሚመሩበት ሁኔታ ባስቸኳይ ለማመቻቸት ወስኗል።


ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ከህዝብና ከመንግሥት ጋር በመሆን ማከናወን እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።


ሕዝብ የሚደመጥበትና ወሳኝነቱ በሚገባ የሚረጋገጥበት እድል እንዲሰፋ አፅንኦት ሰጥቶታል። በተለይ ደግሞ ወጣቶቻችን የሚያነሱዋቸውን ጥያቄዎች በሚገባ ለመመለስና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በልማት ሊኖራቸው የሚገባውን ተሣትፎ በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተከታታይ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።


ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ወስኗል።


የህዝብን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአስተማማኝ ደረጃ ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ተጨማሪ ርምጃዎች እንዲወሰዱም አቅጣጫ አስቀምጧል።


በልማትና በሃገራዊ አንድነት ዙሪያ መትጋት ሲኖርባቸው ሕዝብን ከህዝብ ጋር በሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት አካሄዳቸውን የሚያስተካክሉበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ወስኗል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
280 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 152 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us