“ኢህአዴግ የችግር ምንጭ እንጂ መፍትሔ አምጭ ሊሆን አይችልም”

Wednesday, 17 January 2018 13:30

“ኢህአዴግ የችግር ምንጭ እንጂ መፍትሔ አምጭ 

ሊሆን አይችልም”

አቶ ተማም አባቡልጉ የህግ ባለሙያ

በይርጋ አበበ

አቶ ተማም አባቡልጉ የህግ ባለሙያ ናቸው። በ1987 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪያቸውን የተቀበሉት አቶ ተማም ለአምስት ዓመታት በአቃቤ ሕግ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህግ አማካሪነት አገልግለዋል። ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ግን በጠበቃነት ሙያ ተሰማርተው ይገኛሉ። በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሙያዊና ፖለቲካዊ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቁት የህግ ባለሙያው፤ ሰሞኑን ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር እፈታለሁ ማለቱን ተከትሎ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የቃለ መጠይቁን ሙሉ ሃሳብ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ሰንደቅ፡- የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ 528 እስረኞች ከፌዴራል መንግሥት እና ከደቡብ ክልል እስር ቤቶች እንደሚፈቱ ሰሞኑን ተናግረዋል። ይህም የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የአባል ፓርቲዎች ሊቀመንበሮች የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የተካሄደ ሲሆን በቅድመ ሁኔታ ተገድቦ የተደረገ ምህረት ነው። ይህ ደግሞ እንደተባለው ብሔራዊ መግባባትን ሊያመጣ አይችልም የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?


አቶ ተማም፡- የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች (መስፈርቶች) ስንመለከት (ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ያልተሳተፉ፣ በከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ ያልተሳተፉና ያልመሩ፣ የሰው ህይወት ያላጠፉና ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሱ እና በስርዓቱ ተጠቃሚ ሆነው በሌሎች ገፋፊነት ወደ ሁከትና ብጥብጥ ያልገቡ) በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ ምህዳሩ ሊሰፋ እና ብሄራዊ መግባባት ሊፈጠር አይችልም። ምክንያቱም ይህን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ ሰው እኮ ከመጀመሪያውም መታሰር የለበትም ወይም ወንጀል ሳይፈፅም ነው የታሰረው ማለት ነው። የአሁኑ የጠቅላይ አቃቤ ሕጉ መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብለው የተናገሩትንና ህዝቡ ተስፋ የተጣለበትን ንግግር ነው ተግባራዊ እንዳይሆን ያደረጉት። እኔ ባለኝ መረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በአሮሚያ ክልል ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች ታስረዋል፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ክልልም እንዲሁ በኮንሶ እንዲሁም በወልቃይት ጉዳይ ላይ የታሰሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። እኛ የጠበቅነው እነዚህ ሰዎች ይፈታሉ ብለን ነበር። አሁን በተነገረው መሠረት ግን እነዚህ ሰዎች የማይፈቱ ከሆነ ምንም የሚፈታ የለም ማለት ነው። ስለዚህ በእኔ እይታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በዚህ የአቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጫ ተሽሯል ብዬ ነው የማምነው።


ሰንደቅ፡- ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባሎች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም አክቲቪስቶች የታሰሩት እና ክስ የተመሰረተባቸው በሽብርተኝነት ወንጀል እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ በሚል ክስ ነው። የአሁኑ ምህረት ደግሞ ይህን ስለማያካትት እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ አንዷለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞች ከእስር ላይፈቱ ይችላሉ የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አረዳድ ምንድን ነው?


አቶ ተማም፡- ይህ እኮ ትልቅ ስህተት ነው። አንዷለም አራጌ፣ ውብሸት ታዬ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ፣ በወልቃይት ጉዳይ የተከሰሱት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና የመሳሰሉት ግለሰቦች ካልተፈቱ ማነው የሚፈታው? ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ ኖረም አልኖረ አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ማንነት ያላቸው ሰዎች ናቸው የታሰሩት። እነዚህ ሁሉ ካልተፈቱ የተፈታ የለም እኮ። (ቃለ ምልልሱ ከተካሄደ ከደቂቃዎች በኋላ የኦፌኮው ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ክሳቸው መቋረጡን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል)


ሌላው ህገ-መንግታዊ ስርዓቱን በሃይል መናድ የሚለውን ነጥብ በተመለከተ ከአሁን በፊት ደጋግመን ተናግረናል። ይህን ማድረግ የሚችለው ኢህአዴግ ብቻ ነው። ምክንያቱም የታጠቀ ሃይል ያለው እሱ ብቻ ነው። በህግ ቋንቋ በሃይል መናድ የሚችለው የታጠቀ ሃይል ያለው አካል ብቻ ነው። ሌሎቹ አገር ውስጥ ያሉ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚታገሉ የፖለቲካ ሰዎች እኮ ብዕር እና ወረቀት እንጂ ምንም የታጠቀ ሃይል የላቸውም። እስክንድር ነጋ እኮ ብዕር እንጂ ታንክ የለውም። ስለዚህ ይህ የክስ ነጥብ (ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን በሃይል መናድ ማለት እኮ ከህገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ውስጥ አንዱን አንቀጽ መጣስ ነው። ይህን በማድረግ ህገ መንግሥቱን የናደው ደግሞ ኢህአዴግ ራሱ ነው። የፀረ ሽብር አዋጁ በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ ብዙ አንቀጾችን ነው የጣሰው። ህገ መንግስቱን የሚጥስ ህግ ማውጣት ደግሞ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በሃይል መናድ ነው።


ከዚህ አንፃር የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ስንመለከተው የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች ላለመፍታት የተፈለገ ነው የሚመስለው። ለዚህ ነው ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ሰዎች እና የሙስሊም ህዝብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ካልተፈቱ የሚፈታ የለም የምለው።


ሰንደቅ፡- የፖለቲካ አመራሮችን ክሳቸው እንዲቋረጥም ሆነ የተፈረደባቸው እስረኞች እንዲፈቱ የወሰነው የመንግስት መዋቅሩ ማለትም የሚኒስትሮቸ ም/ቤት ሳይሆን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ነው። ይህን ስንመለከተው አንድ ፓርቲ መንግስት ስለመሰረተ ብቻ እስረኛ መፍታት እችላለሁ ብሎ መግለጫ መስጠት ይችላል?


አቶ ተማም፡- ይህ እኮ በአገሪቱ ውስጥ የህግ የበላይነት አለመኖሩን የሚያሳየው አንዱ መገለጫ ነው። የመንግስት እና የፖለቲካ ፓርቲ ድንበር ያልተለየበት ስርዓት ነው። ከህግ አኳያ ስናየውም እንደዚህ አይነት ውሳኔዎችን ማድረግ የሚችለው መንግስት እንጂ ፓርቲ አይደለም። በየትኛውም አምባገነን ሥርዓት ባለበት አገር መሪዎች ትንሽም ቢሆን ስርዓት ለማክበር ይሞክራሉ። በእኛ አገር ግን ያለው አሰራር በየትኛውም አገር የሌለ ነው። ለዚህ ነው መንግስት እና ፓርቲ ድንበራቸው ተጥሷል፤ ድንበሩ ሊጣስ አይገባውም የምለው። ቢያንስ ቢያንስ ለህዝብ ክብር ያለው መንግስት በፓርቲ ደረጃ መግለጫ አይሰጥም።


ሰንደቅ፡- በመንግስት እና በፓርቲ መካከል ያለው ድንበር (boundary) ሊሰመር ይገባል ብለዋል። መንግስት የመሠረተው ፓርቲ ኢህአዴግ ባህሪው እርስዎ እንዳሉት ይህን ለማድረግ ያስችለዋል?


አቶ ተማም፡- አያስችለውም። ኢህአዴግ እኮ አምባገነን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ቅኝ ግዛታዊ ፓርቲም ነው ብዬ ነው የማምነው። ህወሓት ኢትዮጵያ ላይ ለመሰረተው የቅኝ ግዛት ሥርዓት በኦህዴድ፣ ደኢህዴን እና ብአዴን በሚባሉ ድርጅቶች በኩል የዘረጋው ስርዓት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ እኮ መፍረስ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢህአዴግ ያለ ፓርቲ ማቋቋም ራሱ ህገ-ወጥ ነው በህግ ቋንቋ ስትገልጸው። በመጀመሪያ ደረጃ ኢህአዴግ እኮ ፓርቲ አይደለም ግንባር እንጂ። ይህ ደግሞ ወቅት ጠብቆ ምርጫ ተወዳድሮ ለህወሓት ቦታ የሚይዝለት ድርጅት ነው። ይህ አይነት አካሄድ ደግሞ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም መመዘኛ (standard) ፓርቲ ተብሎ የሚያስጠራውን ደረጃ አያገኝም። ይህን የምለው ደግሞ ዝም ብዬ ሳይሆን ታዋቂው የፖለቲካ ምሁር መሀመድ ባዲ ያደረጉትን ጥናት በማየት ነው። ለዚህ ነው ኢህአዴግ በመንግስትና በፓርቲ መካከል ድንበር ለማበጀት የሚያስችለው ባህሪ የለውም የምለው። በጨዋ ቋንቋ እንነጋገር ከተባለ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ የሚሆን ፓርቲም አይደለም። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ህዝብ የመብት ጥያቄ መመለስ እችላለሁ ካለ እና ያንን ማድረግ ከጀመረ ህልውናው ያን ጊዜ ያበቃል።


ሰንደቅ፡- እኔና እርስዎ የምንነጋገረው የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የፖለቲካ አመራሮችን እንደሚፈቱ ከገለፁ 13ኛ ቀኑ ላይ ቆመን ነው። እስረኞቹ ይፈታሉ ተብለው ከተገለፀላቸው በኋላ እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉን ስናየው መዘግየት ይታይበታልና ይህን መዘግየት እንዴት ያዩታል?


አቶ ተማም፡- አንድ መንግሥት በዚህ አይነት ጉዳይ ላይ መግለጫ ከመስጠቱ በፊት ሊደረጉ የሚገባቸውን ጉዳዮች ካጣራ በኋላ በዚህ ጉዳይ የታሰሩት እነ እንትና ይፈታሉ ብሎ ነው መግለጫ መስጠት ያለበት። ኢህአዴግ ግን ከህዝብ ከባድ ተቃውሞ ገጠመው። ይህን ተቃውሞ ለማብረድ አንድ ነገር ማድረግ ስላለበት ብቻ እስረኞች ይፈታሉ ብሎ ተናገረ እንጂ አስቦበት ያደረገውም አይደለም። ይህ ደግሞ ተጠያቂነት የሌለው መንግስት ባህሪ ነው። የጊዜው መርዘምም የሚያሳየው የተጠያቂነት አለመኖርን ነው።


ሰንደቅ፡- በኢህአዴግ እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል አለመተማመን ተፈጥሮ መቆየቱን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በምሳሌ ጭምር ተናግረዋል። ነገር ግን የአሁኑ ስብሰባችን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሁነኛ ውይይት ያደረግንበት ስለሆነ የአገራችን ህዝብ በስብሰባችን እምነት ይኑረው” ሲሉ ጠይቀዋል። በቀጣይ በህዝቡና በፓርቲው መካከል መተማመን እንዲፈጠር የሚያስችል ነገር ይኖራል ብለው ያምናሉ?


አቶ ተማም፡- አይኖርም። ኢህአዴግ እኮ መለወጥ የሚችል ፓርቲ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ያጣው አገር ነው። ይህን ህዝብ የአገሩ ባለቤት ማድረግ የሚችል ውሳኔ እና እርምጃ መውሰድ ነው ለውጥ ማለት። ለዚህ ደግሞ ተቋማቱን ነፃ እና ገለልተኛ ታደርጋላችሁ ወይ? የህዝብን እኩልነት ትፈጥራላችሁ ወይ? ችግራችን ይህ ስለሆነ ይህን አድርጋችሁ ታሳዩናላችሁ ወይ? ነው ጥያቄው። ኢህአዴግም ተለውጫለሁ ካለ የኢትዮጵያን ህዝብ የአገሩ ባለቤት አድርጎ ማሳየት ይኖርበታል። አቶ ኃይለማርያም ስለተናገሩ ሳይሆን በተግባር ተፈፅሞ ማየት ይኖርብናል። ለምሳሌ ጦር ሰራዊቱ በህገ-መንግሥቱ መሠረት እንደገና ከተዋቀረ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ የፀጥታ እና የደህንነት መዋቅሩ ሁሉ ፈርሶ ገለልተኛ ሆኖ ከተዋቀረ ነው፤ ኢህአዴግ ተለወጠ የሚባለውና በህዝቡ እምነት እንዲጣልበት የሚያስችለውን መሰረት የሚያገኘው።


ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ተሳትፎ (በውጭም በውስጥም ያሉት) የሚያደርግበት የህገ-መንግስት ውይይት ተካሂዶ አዲስ ህገ-መንግሥት ሲፀድቅ ያኔ ኢህአዴግን እናምነዋለን። ኢህአዴግ ደግሞ ይህን ማድረግ የሚያስችል ስብዕና የለውም። ለዚህም ነው ኢህአዴግ በህዝብ እንዲታመን የሚያስችለው ድርጅት አይደለም ያልኩት። በተግባር የታየውም ይህ ነው።


ሰንደቅ፡- አሁን ከእስር ይፈታሉ የተባሉት ፖለቲከኞች በመጀመሪያው ዙር የሚፈቱ መሆናቸው ተገልጿል። ይህ ጅማሮ በራሱ ለብሔራዊ መግባባት በር የሚከፍት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። በእርስዎ እይታ ይህ ጅማሮ እንዴት ይታያል?


አቶ ተማም፡- በመጀመሪያ ደረጃ ብሄራዊ መግባባት ምንድን ነው? ብሔራዊ መግባባት ማለት እኮ ኢትዮጵያ በተግባር የማናት? ነው ጥያቄው። ብሄራዊ መግባባት ተፈጠረ ወይም መፍጠር የሚባለው እኮ ኢትዮጵያን ለዜጎቿ መስጠት ነው እንጂ አራቱ የግንባሩ ብሔራዊ ፓርቲዎች ስለተነጋገሩ የሚፈጠር አይደለም። የዴሞክራሲ ተቋማትን ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሆኑ ማቋቋም ነው። ተቋማቱ ለህዝብ ወገንተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ያ ደግሞ የህዝቡ የሆነ ህገ መንግስት ይፈጥራል ማለት ነው። ለዚያ ደግሞ ህዝብ በመጀመሪያ ከሥነ-ልቦና አፈና እና ከካድሬ አፈና ሚዲያውም ከጫና ነፃ መሆን ያስፈልጋል። እነዚህ ካልተፈጠሩ ብሔራዊ መግባባት ይፈጠራል ማለት አይቻልም።


ሃሳብን በነፃነት መግለጽ በማትችልበት አገር ውስጥ እንዴት ነው ብሔራዊ መግባባት ሊኖር የሚችለው? በተለይ የሃይል ተቋማት ማለትም ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያ ሰራዊትና ሚሊሻን ጨምሮ ሁሉም የታጠቁ ሀይሎች ህዝባዊነታቸው መጠበቅ አለበት እንጂ አሁን እንደሚታየው የህወሓት ስልጣን ጠባቂ ሆነው ብሔራዊ መግባባት ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።


ከፍተኛ እና ጥብቅ የሆነ ቅድመ ሁኔታ በተቀመጠበት መልኩ ይፈታሉ የሚባሉ የፖለቲካ እስረኞች መፈታትና የማዕከላዊ መዘጋት ብቻውን ለብሄራዊ መግባባት በር ይከፍታል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ከዚህ ውሳኔ በፊት ቀደም ብዬ የነገርኩህ ሌሎች የዴሞክራሲ ምህዳሩን ሊያሰፋ የሚችሉ ጉዳዮችን ማየትና እልባት መስጠት ይገባል።


ሰንደቅ፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተነሱ ግጭቶችና ህዝባዊ ተቃውሞዎች ምክንያቱ ራሱ መሆኑን መንግስት እና ገዢው ፓርቲ ደጋግሞ ይናገራል። ወደ እርምጃ ሲገባ ግን የሚታየው ከመዋቅሩ ውጭ ያሉ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ነው። ችግር አለብኝ ያለ መንግስት ሊወስደው የሚገባው ራሱን ተሀድሶ ውስጥ በማስገባት ነው መሆን ያለበት ወይስ ሌላ እርምጃ ያስፈልገዋል?


አቶ ተማም፡- የኢህአዴግ አላማ እኮ በየትኛውም መንገድ ጊዜ እየገዛ የአገዛዝ ዘመኑን ማስፋት ነው። “ህዝቡ የሚለው እስካሁን አየውህ፣ ነገር ግን ያመጣህልኝ ነገር የለም ስለዚህ በቃህ ውረድና ራስህን ተመልክተህ እንደገና ተመለስ” ነው። ኢህአዴግ ደግሞ “አዎ ችግር አለብኝ ግን ችግሬን እያረምኩ ተሃድሶ እያደረኩ ልቀጥል” ነው የሚለው። ጥፋተኛ ነኝ ካልክ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለብህ እንጂ ልታደስ፣ ልታረም፣ ታገሱኝ፣ እመኑኝ እና የመሳሰሉትን አደናጋሪ ሃሳቦች ይዞ በመምጣት አገዛዙን ማስቀጠል አይደለም። ማን ታደስልን አለው? መታደስ ከፈለገም ስልጣን ለቆ ይታደስ እንጂ ስልጣን ላይ ተቀምጦና ችግር አለብኝ ታገሱኝ እያለ አይደለም።


ሰንደቅ፡- እንደ አንድ የአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል የተማረ ሰው ለአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ የሚሉት ምንድን ነው?


አቶ ተማም፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ ችግር ምክንያቱ የሥርዓት መሆኑን አይተናል። ኢህአዴግ የችግር ምንጭ እንጂ መፍትሄ አምጭ ሊሆን አይችልም፣ እንደማይችልም አሳይቷል። ስለዚህ ኢህአዴግ አገር ሳትረበሽ እንድትቀጥል ከፈለገ እሱ የማይመራው ውይይት መድረክ በምሁራን አዘጋጅቶ ውይይት እንዲደረግና ህዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚመክርበት የራሱ የሚለው ህገ መንግስት አፅድቆ ህዝብ የሚመርጠው መንግስት እንዲመሠረት ራሱን ያዘጋጅ። ያኔ ህዝብ በነፃነት ኢህአዴግ ይሻለኛል ብሎ ከመረጠው በሥልጣን ይቆያል። ካልሆነ ግን ራሱን ለለውጥ እንዲያዘጋጅ ይረዳዋል። ነገር ግን ኢህአዴግ ካለው ባህሪ ተነስተን ስናየው ይህን ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። እንደ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ኢህአዴግን የምመክረውም ሆነ የመፍትሄ መንገድ ነው የምለው ይህንን ነው።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
185 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1021 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us