የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ፤

Wednesday, 24 January 2018 14:36

“ወደ ብሔር ፓርቲዎች መግባት ጥሩ ሆኖ አላገኘነውም

አቶ ተክሌ በቀለ


“ሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ፓርቲ ነው”

አቶ ተመስገን ዘውዴ


በይርጋ አበበ

 

ከዓመታት በፊት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) “ሊዋሃዱ ነው” የሚል መረጃ ወጣ። የሁለቱ ፓርቲዎችን ውህደት በተመለከተ በአቶ ሀብታሙ አያሌው የሚመራው የሚያጠና ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱም ተነገረ። ትንሽ ቆየት ብሎ ግን ውህደቱ ተቋረጠ የሚል ዜና ተሰማ። ለውህደቱ መደናቀፍም “ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በስለላ መዋቅሩ ገብቶ” እንዳንግባባ አድረገን ተባለ።


ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመታት በኋላ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በውስጡ መከፋፈል ተፈጥሮ አመራሮቹ እና በርካታ አባሎቹ ከፓርቲው ወጡ። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮም ከአንድነት የወጡ አመራሮችና አባላት ፓርቲ ሳያደራጁ ቆዩ። ሆኖም በ2009 ዓ.ም “ተራማጅ የዜጎች ንቅናቄ” የሚባል ፓርቲ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀመረ። በቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ እና በቀድሞው የአንድነት ተ/ም/ሊቀመንበር አቶ ተክሌ በቀለ የተመራ የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ በአራት ክልሎች ከ3ሺህ 900 በላይ የድጋፍ ፊርማ ሲያሰባስብ ቢቆይም የፓርቲው ምሥረታ እውን ሳይሆን ቀረ።


በመጨረሻም “ኢህአዴግ ፓርቲያችንን በጠራራ ፀሐይ ቀማን” ሲሉ የሚናገሩት እነዚሁ የአንድነት የቀድሞ አመራሮች፤ በሰማያዊ ፓርቲ ስር ሆነው ሰላማዊ ትግሉን ለመቀጠል መሥማማታቸውን ገለፁ። ከትናንት በስቲያም በይፋ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆነው ተመዘገቡ። በዚህ ዙሪያ የተጠናቀረው ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ወደ ሰማያዊ ለመግባት የነበረ ዝግጅት


ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ፕሮግራም፣ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም፣ ተመሳሳይ የትግል ስልት እና ልዩነት የሌለው አደረጃጀት አላቸው። ሆኖም ከአንድነት ይልቅ ልዩነት የነገሰባቸው በመሆኑ ብዛታቸው ለ70 የቀረበ ነው። ይህ በመሆኑም መራጩን ህዝብ ጨምሮ የአገሪቱን ዜጋ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ግራ እንዳጋቡ ነው። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ህዝቡ “ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” የሚል መልዕክት ቀደም ባሉት ዓመታት ማሰማት የጀመረው።


የሰማያዊ ፓርቲም ሆነ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላትም በፓርቲዎቻቸው ፕሮግራም፣ ርዕዮተ ዓለም እና የትግል ስልት ልዩነት የሌላቸው ቢሆንም ከአንድነት ይልቅ ሁለት ሆነው ቆይተዋል። የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራሮችም ከፓርቲያቸው ውጭ ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት በፓርቲ ተደራጅተው ለመታገል የነበራቸው ምርጫ ሁለት ነበር፤ በአዲስ መልክ ተደራጅተው ፓርቲ መመስረት ወይም በአደረጃጀት ከሚመስሏቸው ፓርቲዎች ጋር በአንድነት መሥራት የሚሉት ነበሩ አማራጮቹ። የአንድነት የቀድሞ አመራሮች ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ያደረጉትን ጉዞ በተመለከተ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ፤ “ወደዚህ ውሳኔ ከመግባታችን በፊት እኛ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ምን አይነት የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገናል? ብለን ጠየቅን። በዚህ መልኩ ባደረግነው ጥናት በተለይ ከ2009 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ አንድ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ያስፈልጋል ብለን አመንን። በዚህ የተነሳም ከመኢአድ ጋር ቅድመ ውህደት ሥምምነት ተፈራረመን እየሰራን ስንሆን የቀድሞ አንድነትም የፓርቲ እውቅና ባይኖረውም የፓርቲ ያህል መዋቅር፣ አባላት እና አመራሮች ያሉት ድርጅት ስለሆነ እነሱም በአዲስ መልክ ከመደራጀትና አንዱን መርጦ ወደዛ ሄደው ማጠናከር የሚሉ ሃሳቦች ነበራቸው። እኛም ሁለተኛውን እንፈልገው ስለነበረ ወደእኛ ብትመጡ ፕሮግራማችን፣ ደንባችን እና ዓላማችን አንድ አይነት ስለሆነ ማሻሻል የሚገባቸው ቢኖሩም አብረን እናሻሽላለን የሚል ግብዣ ስናቀርብላቸው የተወሰነ ጊዜ ወስደው አጠኑ። በመጨረሻም አብሮ ለመስራት ፍላጎታቸውን ገለፁ። ከጥቅምት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮም የፓርቲው አባል መሆናቸውን በይፋ አሳወቁ” ሲሉ የነበረውን ሂደት በዝርዝር ተናግረዋል።


በ1997 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ቅንጅት የተባለውን ፓርቲ ወክለው ፓርላማ የገቡት አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው “ሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ፓርቲ መሆኑን በተደጋጋሚ ያረጋገጠ ፓርቲ ስለሆነ ከፓርቲው ጋር ሆኜ ትግሉን ለመቀጠል ስለፈለኩ የፓርቲው አባል ሆኜ ተመዝቤያለሁ” በማለት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ያቀኑበትን ምክንያት ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።


የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተክሌ በቀለ ደግሞ “ፓርቲያችን በኢህአዴግ ጽ/ቤት፣ በደህንነት መዋቅሩ፣ በምርጫ ቦርድ እና የህወሓት ልሳን በሆኑ መገናኛ ብዙሃን ጫና ተደርጎበት በጠራራ ፀሐይ ከተቀማን በኋላ ሰላማዊ ትግሉ መቆም የለበትም የሚል አመለካከት ነበረን። ሰላማዊ ትግል ፓርቲ በመመሥረት ብቻ የሚገልፅ አይደለም። ህገ-መንግሥቱ በሚፈቅድልን መሠረት በተለያዬ መልኩ ሰላማዊ ትግሉን ጠበቅ አድርገን መያዝ አለብን የሚል አቋም ነበረን። በዚህ ሂደት ውስጥም በርካታ ክስተቶች ያለፉ ሲሆን አመራሩ ለሁለትና ለሶስት ዓመታት ከፍተኛ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቶ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሷል” ብለዋል።


እንደአቶ ተክሌ ገለፃ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ መሪዎች 10 አባላት ያሉት ኮሚቴ “ተራማጅ የዜጎች ንቅናቄ” የሚል ፓርቲ ለመመስረት እንቅስቃሴ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ሆኖም አዲስ ፓርቲ ከማዋቀር ይልቅ ያሉትን ማጠናከር እንደሚሻል ስለታመነበት ሰማያዊ ፓርቲን እንደመረጡ ገልጸዋል።


ከሰማያዊ በፊት የነበረ ጥረት


አቶ ተመስገን ዘውዴን ጨምሮ አብዛኞቹ የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች እና አባላት አሁን ከደረሱበት ውሳኔ በፊት ሌሎች አማራጮችን ማየታቸውን ይናገራሉ። ስለጉዳዩ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ተክሌ “ከዚህ ውሳኔ ከመድረሳችን በፊት የተለያዩ አባላትን ማነጋገር ነበረብን። ለዚህም ከላይኛው አመራር እስከ ወረዳ ስራ አስፈፃሚዎች ያሉ አመራሮችን ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ ፓርቲ መርጠን መቀላቀል እንዳለብን ተወሰነ። በተወሰነው መሰረትም አሁን ባለው የፖለቲካው አየር ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፣ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው ብለን ድምዳሜ የደረስንባቸው መድረክ፣ መኢአድና ሰማያዊ ነበሩ። መድረክን በአባልነት መቀላቀል አንችልም ፓርቲ አቋቁመን እንደፓርቲ መግባት ነው የምንችለው። ወይም ደግሞ በመድረኩ አባል ፓርቲዎች በተናጠል በአባልነት መመዝገብ ያስፈልግ ነበር መድረክን ለመቀላቀል። እኛ ደግሞ ወደ ብሔር ፓርቲዎች መግባቱ ጥሩ ሆኖ ስላላገኘነው ከመድረክ ጋር መግባት አልቻልንም። ስለዚህ ከመኢአድና ከሰማያዊ አንዱን መርጠን በአባልነት ለመቀላቀል ምርጫ ስናደርግ ከሰማያዊ ፓርቲ የቀረበልን ግብዣ እና ሌሎች አማካሪዎችን ስናማክር በመጀመሪያ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቅላችሁ የመኢአድ /ሰማያዊ ውህደትን ብትገፉበት ይሻላል የሚል ሃሳብ ስለቀረበ ነው ሰማያዊ ፓርቲን በአባልነት ለመቀላቀል የወሰን ነው” በማለት ተናግረዋል።


የሰማያዊ ፓርቲ ቀጣይ ጉዞ


“ከ2009 ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ አንድ የተጠናከረ የፖለቲካ ኃይል እንዲኖር ጥረት ስናደርግ ቆይተናል” የሚሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ ሰሞኑን የተካሄደው ክንውንም ከፓርቲው የሩቅ ጊዜ እቅዶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ፓርቲውን የተቀላቀሉትን የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ወደ ኃላፊነት መጥተው እንዲሰሩ ታደርጋላችው ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ የሺዋስ፤ “አመራርነት አገልጋይነት ነው። እነዚህ ሰዎች ፓርቲ ሲመሩ የነበሩ እና ብቃት ያላቸው ሰዎች ስለሆኑ ከእኔ ጀምሮ ሁሉም የፓርቲያችን አመራሮች እነዚህን ሰዎች በኃላፊነት ቦታ እንዲሰሩ ፈቃደኞች ነን” ብለዋል።


አቶ ተክሌ በቀለ በበኩላቸው በቀጣይ ሊካሄድ ይገባል ያሉትን ሲናገሩም በተወሰነ መልኩ የደንብ እና የፕሮግራም ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ተናግረዋል። “ይህም የሚሆነው ከነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ነው” ብለዋል።


“ጫናን ለመሸከም የሚፈቅድ ትውልድ አያስፈልግም” የሚሉት አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው “የጭቆናን ቀንበር አሻፈረኝ የሚል ትውልድ ለመፍጠር እየታገልን ነው። ወደፊት እዛ ላይ እንደርሳን። ሰላማዊ ትግልን በሚገባ አጠናክረን በመሄድ አንገታችንን ቀና አድርገን በራስ መተማመን በሞላበት መልኩ መብታችንን የምናውቅ ዜጎች መሆን እንችላለን። ጦር ይዞ ጫካ ስለተገባ ሳይሆን በሰላማዊ ትግል የህዝብን መብትና ክብር ማስጠበቅ፣ የህግ የበላይነት እንዲኖር ማድረግ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ መፍጠር እንችላለን” በማለት ሰማያዊ ፓርቲ ለዚህ ተልዕኮ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
142 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1009 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us