ህወሓት በድርጅቱ ውስጥ ተዘረጋብኝ ያለውን፣ የኔትዎርክ ሰርቨሩን አግኝቶት ይሆን?

Wednesday, 24 January 2018 14:54

 

በሳምሶን ደሣለኝ

 

ከጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመቐለ ከተማ ሲካሄድ የነበረው 7ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ መጠናቀቁን ተከትሎ ድርጅቱ እርምጃዎች እየወሰደ ይመስላል። በተለይ የኤፈርት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አዜብ መስፍንን በቦርድ ውሳኔ መነሳታቸው ለአደባባይ በቅቷል።


እንደሚታወሰው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ “ስብሰባ ረግጠው” መውጣታቸው ተነግሮ፤ መታገዳቸው ታውቋል። ሆኖም ለማዕከላዊ ኮሚቴው ከስብሰባው ለምን እንደወጡ ተናግረው፣ በውይይቱ ተሳታፊ ነበሩ።


ሌላው አቶ ብርሃነ ኪ/ማሪያም (ብርሃነ ማረት) እና ወ/ሮ አረጋሽ በየነ ከማዕከላዊ ኮሚቴ መነሳታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ለመነሳታቸው በዋናነት በድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደተነገረው፣ በኔትዎርክ የተያያዙ ናቸው የሚል ነው። ሆኖም ሰዎቹ ከየትኛው የድርጅቱ ሰርቨር ጋር እንደተያያዙ የተነገረ ነገር አልነበረም። ኔትዎርኩም በተጨባጭ ያደረሳቸው ችግሮች እና አደጋዎች በግልፅነት አልተቀመጡም። ተጨማሪ ግምገማዎችም በኔትዎርክ በተወነጀሉ ሰዎች ላይ መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል።


በተያያዘም በትግራይ ክልል ምክር ቤት እና በሕዝባዊ ኮንፈረንሶች የህብረተሰቡ ተወካዮች ከኃላፊነት ስለሚነሱት ሰዎች ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቧል። አሁንም በተለያዩ ወገኖች ይህ ጥያቄ ምላሽ እንዲሠጠው እየተጠየቀ ይገኛል። ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ እና አሁን በሀገር ውስጥ ካለው ተጨባጭ ችግሮች አንፃር ከኃላፊነት የሚነሱት ሰዎች ለችግሮቹ መፈጠር የነበራቸውን ድርሻ በግልፅ እንዲቀመጥ የሚፈልጉ ባለድርሻ አካላት በርካታ ናቸው።


በሌሎች ወገኖች የሚቀርበው ቅሬታ ደግሞ የአጀንዳዎች ቅደም ተከተል ናቸው። ይህም ሲባል፣ በ“ኔትዎርክ” እና በ“በከፍተኛ ሙስና” ውስጥ በመዘፈቅ በሚጠረጠሩት መካከል የትኛው አጀንዳ መቅደም ነበረበት፤ በሌላ ወገን “አጀንዳ መቀያየር የሚያመጣው የተለየ ትርጉም የለውም” የሚሉም አሉ።


ከጥቂት ወራት በፊት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በዛሚ ሬዲዮ ላይ ቀርበው በአደባባይ፣ “በእኔም፣ በቤተሰቤም የተመዘገበ ወይም የተመዘበረ ሃብት የለም በማለት” ማንኛውም ወገን ድርጅታቸውን (ህወሓት) ጨምሮ ካለ በይፋ እንዲያጣራ ጋብዘዋል። አያይዘውም፣ ሆን ተብሎ ቤተሰባቸውን “በሙስና” ስም የሚያጠለሹ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ወደ እሳቸው ጣታቸውን የሚቀስሩ ሰዎች፣ የሙስና ጥያቄዎች ወደ እራሳቸው እንዳይመጣ የሚከላከሉ ይሆናሉ ሲሉ ሸንቆጥ ማድረጋቸውም የሚጠቀስ ነው።


ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአደባባይ ቀርበው ለመናገር የወሰዱትን ድፍረት እና ቁርጠኝነት፣ በሌሎች በኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮችም በአደባባይ ቀርበው “እኔ” ከኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውጪ ነኝ ብለው ቢያረጋግጡ ብዙ ነገሮችን ያቀሉ ነበር። ማረጋገጥ የማይችለውን፣ በሕግ የበላይነት ሥር ማዋል ይቻል ነበር። ቢያንስ በአደባባይ የተነገረን ጉዳይ፣ ለማረጋገጥ ፍላጎት የሌለው ወገን መመልከት ግን በጣም አስገራሚ ነው።


በአደባባይ ፍርድን የተጠየቁትን ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከድርጅቱ ከፍተኛ ተቋም ከኤፈርት ማንሳት እና በ“ማዕከላዊው ኮሚቴ የውስጥ ደንብ” ከጉባኤው ማገድ ግልጽነት የጎደለው እርምጃ አድርጎ ቢወሰድ ችግሩ ማን ላይ ነው? ምክንያቱም ለአደባባይ በቀረበ ጉዳይ “እውነት” ወይም “ሃሰት” የማለት የማስረዳት ሸክሙ የወደቀው በድርጅቱና ያገባኛል በሚለው ባለድርሻ አካል ላይ ነው። ከዚህ በላይ ግን ድርጅቱ ወ/ሮ አዜብ መስፍን የገመገመበትን መነሻና ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ሲገባው፤ ሾላ በድፍኑ ዓይነት አድርጐ ማለፉ የእርምጃውን ግልጽነት ጥያቄ ውስጥ ጥሏል፡፡
የሕወሓት ጉባኤም በቀጣይ ሲካሄድ ቢያንስ ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሄዱበትን ያህል ርቀት ከፍተኛ የድርጅቱ አባሎች እንዲራመዱት መጠየቅ አለበት? ጉባኤው፤ የሚሰጠው ውሳኔም ቢያንስ ከአዲስ ኔትዎርክ ተፅዕኖ ነፃ መሆኑ ማረጋገጥ እና ለተሰውቱ ሰማዕታት ታማኝ መሆን ይጠበቅበታል። ጉባኤው፤ አስጊ ናቸው ከተባሉት ኔትዎርኮች የድርጅቱ ሰርቨር ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ ታሪካዊ ተልዕኮ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ድርጅቱ፤ የትግራይን ሕዝብ ከሻዕቢያ ፕሮፓጋንዳ መጠበቅ ይችል ይሆን?


ሀገሪቷ አሁን ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በየትኛውም የቀውስ ተግባር ለመግለፅ ሁለት ሀረጎች በማሰሪያነት ይቀመጣሉ። አንደኛው፣ የፀጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ ተጠያቂው ሲቀመጥ “የአጋዚ ጦር” ሲባል፤ ሁለተኛው ከፖለቲካ ኢኮኖሚ ጋር የሚነሱ የልሂቃን ጥያቄዎች መገለጫቸው “የትግራይ ሕዝብ የበላይነት” በሚል የሚገለጹ ናቸው። እነዚህ ሁለት ሀረጎች ጥልቅ ትንተናዎች (root cause analysis) አላቸው። እንደው ለማለት ብቻ የተሰነጉ ሳይሆኑ፣ በተጠና ሁኔታ በትንተናዎች መካከል እየተወተፉ ትንተናው እና አመለካከቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው የተደረጉ፤ እያስከፈሉት ያለው ዋጋም በቁስ የቆመ ሳይሆን ሰብዓዊ ሕይወትንም የቀጠፈ ነው።


የሕወሓት አንዳንድ አመራሮች እና በድርጅቱ ሥም፣ በሕዝቡ ሥም እያስፈራሩ፣ ለዘረፋ የተሰለፉ ኃይሎች ከላይ ለሰፈሩት ሁለት ሀረጎች ተቀባይነት እንዲኖራቸው የተጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አሁንም በተቻለ ፍጥነት መታረም ያለበት ጉዳይ ነው።


ዋናው “የአጋዚ ጦር” እና “የትግራይ ሕዝብ የበላይነት” የሚለውን ትንተናና አመለካከት አስራጊው ኃይል፣ የሻዕቢያ አገዛዝ መሆኑ ይህ ጸሃፊ ያምናል። ሻዕቢያ በተለይ በውጭ በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን “የአጋዚ ጦር” እና “የትግራይ ሕዝብ የበላይነት” በሚሉ ሀረጎች የኢትዮጵያን ማንኛውንም ችግር እንዲተነተን፣ እንዲገለጽ ከፍተኛ ዶላር በመበተን ይሰራል። ለሚዲያ ተቋሞች ከፍተኛ ክፍያ ይፈጽማል።


በተጨማሪም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ኃይል ላነሱ በይፋ ግዛቱን በመፍቀድ ከገንዘብ እስከ ወታደራዊ ቁሳቁስ ድረስ እገዛ ያደርጋል። ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ይደራደራል፤ ድጋፍ ያመጣል።


ሻዕቢያ፣ ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚሰራው ዋነኛ ምክንያት ኢትዮጵያ በሻዕቢያ አገዛዝ ላይ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው። በተለይ የሻዕቢያ መንግስት ከዓለም ከአቀፉ ሕብረተሰብ እንዲገለል እና አሸባሪዎች በመደገፍ በጥቁር መዝገብ እንዲገባ በኢትዮጵያ መንግስት የሚደረገውን እንቅስቃሴ፤ “የህወሓት ተግባር ነው” የሚል ከፍተኛ እምነት ያለው አገዛዝ መሆኑን ለማወቅ የፕሬዝደነት ኢሳያስ አፈወርቂን ቃለ ምልልሶች ማዳመጥና መረዳት በቂ ነው።


ሻዕቢያ በኤርትራ ሕዝብ የደረሰበትን የቅቡልነት ጥያቄ፣ በሕወሓት የመጣ ነው ብሎ ይወስዳል። በተለይ በኤርትራ ሕዝብ የደረሰውን የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ቀውሶች ሕወሓትን ተጠያቂ በማድረግ፣ የትግራይ ሕዝብ ተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ ለመጣል ሳይታክት የሚሰራ ቡድን ነው። በተወሰነ ደረጃ የተሳኩ ሥራዎችን ሰርቷል ብሎ መውሰድም ይቻላል።


የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕቢያን ያገለለ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሲከተል ውጤቱን ተከትሎ፤ ሻዕቢያ ምን አይነት አሉታዊ የፕሮፖጋዳ ስልቶችን መጠቀም እንደሚችል የተነተነው ነገር የለም። አለ ከተባለም፣ ውጤታማ ትንተና አይደለም። “የምንም ሰላም፤ የምንም ጦርነት” የሚለው ፖሊሲ የኤርትራን ሕዝብ ለችግር እና ለብተና ከማጋለጥ ውጪ፣ የሻዕቢያ አገዛዝ ትርጉም ባለው መልኩ ማዳከም አልቻለም። በጣም አስገራሚ ውጤት ደግሞ፣ በኤርትራ እና በትግራይ ድንበር ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውጪ ሲወጡ፤ የሻዕቢያ አገዛዝ ግን በአዲስ መልኩ የመካከለኛው ምስራቅ ፔትሮ ዶላር ተጠቃሚ በመሆን ወደ ጨዋታው ሜዳ መመለሱ ነው።


ስዚህም “የምንም ሰላም፤ የምንም ጦርነት” በሚል የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የትግራይ ሕዝብ ሁለት አደጋዎች ተጋርጠውበታል። አንደኛው፣ በድንበር ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቀሴ ውጪ ተደርገዋል። ሁለተኛው፣ የትግራይ ሕዝብ እንደሕዝብ በተቀናጀ የሚዲያ ፕሮፖጋዳ ተጠቂ ሰለባ ሆኗል። እነዚህን መሬት የረገጡ እውነታዎችን፣ የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ እና ጉባኤው ምላሽ መስጠት ይችሉ ይሆን? ድርጅቱ እንደሚለው በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግዱ ሃይሎችን በመዋጋት ብቻ፣ እንደ ሕዝብ የፕሮፖጋንዳ ቀለበት ውስጥ የገባውን የትግራይ ሕዝብ ንፅህናን መመለስ ይችል ይሆን? ወይንስ እንደአንድ የመንግስት አካል ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመወያየትና በመተማመን በሻዕቢያ ላይ አዲስ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ ድርጅቱ ይሰራ ይሆን? 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
411 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1001 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us