148 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ የምትመዘበረውን አፍሪካን ሰሞነኛው የመሪዎች ዘመቻ ይታደጋት ይሆን?

Wednesday, 31 January 2018 13:05

 

በይርጋ አበበ

 

አምባገነን ገዥዎች (መሪዎች) አዛዥ እና ናዛዥ በሆኑበት የአፍሪካ ምድር በአምባገነን ገዥዎቹ እና የአምባገነን ገዥዎች ጥቅመኞች በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር ያጣል። በዚህ የተነሳም በርካታ ወጣቶች አዱኛ ፍለጋ ውቅያኖስ እና ጫካ አቋርጠው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው እንጀራ ፍለጋ ይሰደዳሉ። ከስደት የተረፉት ደግሞ በአገራቸው ምድር ለከፋ ድህነት ተዳርገው አንገታቸውን ደፍተው ይኖራሉ ወይም ለልመና ይዳረጋሉ። ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ ገዥዎቹ ፈላጭ ቆራጭነት የተጠናወተው አገዛዛቸው ምክንያት ነው። አምባገነን መንግስታት በባህሪያቸው ተጠያቂነት የማይሰማቸው መሆናቸውን ተከትሎ ሙስና መለያቸው ነው።


ይህ ያለፉት ረጅም ዓመታት የአፍሪካ እጣ ፈንታ እስኪመስል ድረስ ምድሪቱን ሲቦጠቡጥ የቆየ ድርጊት ነው። ይህ አካሄድ ግን ከዚህ በኋላ ይብቃ ሲሉ አንዳንድ መሪዎቿ መናገር ጀምረዋል። በተለይ በቅርቡ ከኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ስልጣኑን የተረከበው የቀድሞው እግር ኳሰኛ ጆርጅ ዊሃ ‹‹ሙስና በአገሩ እንዲጠፋ›› እንደሚሰራ ተናግሯል። ከ37 ዓመታት የሙጋቤ ቀንበር የተላቀቀችው የዝምባብዌ አዲሱ ሊቀመንበር ኤመርሰን ምናንጋጋዋም ቢሆኑ በሙስና ላይ እንደሚዘምቱ ዝተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀው 30ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የመድረኩ ዋና ሃሳብ ሆኖ የቀረበው ‹‹ሙስናን መዋጋት ለዘላቂ የአፍሪካ ህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል ነው። ሙስናን ከአፍሪካ ለማጥፋት በአንድ ጀምበር ዘመቻ ይሳካል ወይ? በሙስና አህጉሪቱ እና ዜጎቿ የከፈሉትን ዋጋ ሙሰኞቹ በምን መልኩ ያወራርዱታል? የመሪዎቹ ወቅታዊ አቋምስ ዘላቂነቱና ቁርጠኝነታቸው ምን ያህል ነው? በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ምሁራን የሰጡትን አስተያየት ይዘን ቀርበናል።


አፍሪካ እና ሙስና


በአፍሪካ ያለውን የሙስና ደረጃ ይፋ ያደረገው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በአህጉሪቱ መጠነ ሰፊ የገንዘብ ምዝበራ መኖሩን አስታውቋል። በአገራቸው በሙስና ወንጀል ክስ የቀረበባቸው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው አህጉሪቱ ውስጥ ሙስና መኖሩን አምነው ሆኖም የሚወራውን ያህል የከፋ አይደለም ሲሉ በ30ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ተናግረዋል። የ2014 የአልጄዚራ ዘገባ ደግሞ አህጉሪቱ ላይ ሙስና በስፋት መኖሩን ይዘግብና በተለይ የአህጉሪቱ ባለስልጣናት ከአገራቸው ገንዘብ የማሸሽ ተግባር ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን ይገልጻል። በዚህ ዘገባ ላይ ተመስርቶ ሪፖርት ያቀረበው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር ከአፍሪካ እንደሚመዘበር ይፋ አድርጓል። ከዚህ አሃዝ ውስጥ ደግሞ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት የበለጠ ተጠቂ ናቸው ሲል ሲ ኤን ኤን በዲሴምበር 2017 አስነብቧል። ጃኮብ ዙማ ‹‹እንደሚባለው የተጋነነ አይደለም›› የሚሉት የአህጉሪቱ ሙስና ደረጃ ይህ ነው።


የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ጸሀፊ ፕሮፌሰር ኢማኑኤል ናዶዜ በበኩላቸው የችግሩን ግዝፈት እና አሳሳቢነት ይጋሩታል። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች በህዝባቸውና በዓለም አቀፍ ማህረሰብ ተዓማኒነታቸውን ለማሳየት ሲሉ ቁርጠኛ ውሳኔ ሊያሳልፉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። ፕሮፌሰሩ በአዲስ አበባው ጉባኤ ለተገኙት ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ለአፍሪካ መሪዎች የምለግሰው ምክር ቢኖር መሪዎች ከሌሎች ጉዳዮቻቸው ሁሉ በፊት ለጸረ ሙስናው ትግል ቅድሚያ እንዲሰጡ ነው። ምክንያቱም የችግሩ ጥልቀት ከፍተኛ ነውና›› ሲሉ ሙስና በአፍሪካ ያለውን ደረጃ አስታውቀዋል።

 

የሙስና በር እና መስኮቶች


በኢንዱስትሪ ያልበለጸገ፣ በኢኮኖሚ የደኸየ ህዝብ፣ የትምህርት እና የጤና አቅርቦት ችግር ያለበት፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ ያልሆነ እና የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምበት ህዝብ የሚገኝባት አፍሪካ መሪዎች ከነቤተሰቦቻቸውና በዙሪያቸው ካሉት የበታች ሹሞቻቸው ጋር ሆነው የአዱኛ ማማ ላይ የሚወጡባት ምድርም ነች። ለዜጎቿ የሰቆቃ ለአለቆቿ የፍስሃ ምድር የሆነችው አፍሪካ ለዚህ የሙስና ደረጃ ምን ዳረጋት? የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው የሙስና ምንጩ የመሪዎቹ ዴሞክራሲያዊነት አለመላበስ እና የነጻ ተቋማት አለመገንባት እንደሆነ ይናገራሉ።


የህግ ባለሙያው ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያ በበኩላቸው ከአቶ ልደቱ አያሌው ሃሳብ ጋር ይስማሙና ሊተገበር የሚችል ህግ አለመኖሩን እንደ መንስኤነት ያቀርባሉ።


የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሀፊ ፕሮፌሰር ኢማኑኤል ናዶዜም ሆኑ ኢትዮጵያዊያኑ ምሁራን ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪም እና አቶ ልደቱ አያሌው በአፍሪካ ለሰፈነው መጠነ ሰፊ ሙስና መግቢያ በሩ ዴሞክራሲና ተጠያቂነት አለመኖር ነው ሲሉ ይገልጻሉ። በህዝብ እና በአሰራር (ሲስተም) ተጠያቂነትን ያላሰፈነ የአገር መሪ ሙስናን እታገላለሁ ብሎ ቢናገር ውጤቱ ‹‹ጉንጭ አልፋ›› እንደሆነ ይናገራሉ።

 

ሙስናን ለመከላከል የሚዘጉ ደጆች


ምንም እንኳን በሁሉም የአፍሪካ አገራት በሚያብል ደረጃ መሪዎቹ በሙስና እና ምዝበራ የሚጠረጠሩ ቢሆንም ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ መጠነ ሰፊ ሙስና የሚንቀሳቀስባቸው አገራት እንደሆኑ ይነገራል። የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት የቀድሞው የዓለም፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ‹‹በላይቤሪያ ልሳነ ምድር የሙስና ደጆች ሊዘጉ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን የመረጠኝ ህዝብ በድህነት የመኖር እድሉ የሰፋ ይሆናል›› ሲል በበዓለ ሲመቱ ላይ ተናግሯል።


የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃሞዱ ቡሃሪ ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ከ50 በላይ ለሆኑት ጓዶቻቸው በአዲስ አበባው ጉባኤ ሲናገሩ ‹‹ሙስናን መታገል የአህጉሪቱ ህልውና ጉዳይ ነው›› ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የህግ ማዕቀፍ ማውጣት እና ለህጉ ተፈጻሚነት የመሪዎች ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል። የደቡብ አፍሪካ አቻቸው ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው በአፍሪካ አለ የሚባው ሙስና የተባለውን ያህል የተጋነነ እንዳልሆነ መናገራቸው ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች በሙስና ላይ ተመሳሳይ አቋም አለመያዛቸውን ያመለክታል ሲሉ የሚናገሩ አሉ።


አቶ ልደቱ አያሌው በዚህ ጉዳይ ላይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ሲናገሩ ‹‹የአፍሪካ መንግስታት በሙስና ላይ ቁርጠኝነቱ እንደሌላቸው ብዙ ጊዜ የታየ ነው። ግን ደግሞ ተስፋ ተቆርጦ የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ ጉዳዩ ተነስቶ በአጀንዳ መታየቱ ተገቢ ነው›› በማለት የአዲስ አበባው 30ኛው ጉባኤ በሙስና ላይ መወያየቱን ያደንቃሉ። እንደ ፖለቲከኛው እምነት አጀንዳው መነሳቱ በራሱ መልካም ቢሆንም ወደ ትግበራ ለመግባት ግን የሚያስፈልጉ ቅድመ ሂደቶች እንዳሉ ይናገራሉ። ‹‹ሙስናን ለመፍታት ግን የመሪዎቹ ቁርጠኛ መሆን ወይም ጉዳዩ በአጀንዳነት መታየት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እና ለህዝብና ለህግ ተጠያቂነት ያላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ነው። ሰዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀያየር ግልጽ እና ገለልተኛ የሆኑ ድርጅቶችን መገንባት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው›› ሲሉ ሙስናን ለመግታት ሊዘጉ የሚገባቸው በሮች እንደሆኑ ገልጸዋል። አቶ ልደቱ አያይዘውም ‹‹በአፍሪካ መሪዎች ለረጅም ዓመታት ስልጣን ላይ የሚቆዩትም ሆነ ስልጣናቸውን ተገን አድርገው በአገራቸው ላይ ምዝበራ የሚፈጽሙት እንዚህ ተቋማት ስለሌሉ ነው›› ብለዋል።


‹‹እኔ እንደሚገባኝ ሙስና በአዋጅ ብቻ የሚጠፋ አይደለም›› የሚሉት የህግ ባለሙያው ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም በበኩላቸው፤ ‹‹ሙስና ከፖለቲካ ስርዓቱ ጋር የተያያዘ ነው። በአምባገነን ስርዓት ከሚተዳደሩ አገራት ይልቅ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚመሩ አገራት ላይ ሙስናው የቀነሰ ነው። ይህ የሚሳየው ሙስና ከስርዓት ጋር ጠንካራ ቁርኝት እንዳለው ነው። ስለዚህ በአፍሪካም መሪዎቹ ሙስናን ለማጥፋት ከልባቸው የተነሱ ከሆነ መከተል ያለባቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት፣ ነጻ ፕሬስን ማቋቋም፣ ነጻ ፍርድ ቤት መመስረቱ ነው›› ብለዋል።

 

የአፍሪካ መሪዎች እና ባህሪያት


የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሀፊ ፕሮፌሰር ኢማኑኤል ማዶዜ አዲስ አበባ ለተገኙ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲናገሩ ‹‹የአፍሪካ መሪዎች ሙስናን መዋጋት የራሳቸው የቤት ስራ ነው›› ሲሉ ሙስና ለስልጣናቸውም ቢሆን አስጊ እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ራሳቸው መሪዎቹ የሚመሩት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሊቋቋም እንደሚገባ ተናግረዋል።


ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም ደግሞ ሙስናን ለመታገል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በመጀመሪያ የመሪዎቹ ግላዊ ባህሪ ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል። ለአብነት ያህልም እንደ ጃኮብ ዙማ ያሉ መሪዎችን ይዞ በአፍሪካ ሙስናን ማጥፋት አይቻልም ይላሉ። ዶክተር ያዕቆብ ሲናገሩ ‹‹ከአፍሪካ እንደ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት በአንጻራዊነት ዴሞክራሲ እና ነጻ ፕሬስን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻነታቸው ጥሩ የሚባል ቢሆንም የደቡብ አፍሪካው መሪ ጃኮብ ዙማ ግን በግል ባህሪያቸው ሙስናን መታገል የሚችሉ መስለው አይታዩኝም›› ብለዋል። ዶክተር ያዕቆብ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹ሁሉንም መሪዎች ባህሪ በአንድ ላይ መደመር አይቻልም። በተወሰነ ደረጃ የሚሻሉ መሪዎች ጥሩ የሚባል ባህሪ አላቸው። ሙስናን ለመታገል ጥሩ የሚባሉ ህጎች ቢወጡም መሪዎቹ እስካልተገበሩት ድረስ ህጉ ከተጻፈበት ወረቀት የዘለለ ጠቀሜታ አይኖረውም። ስለዚህ መሪዎቹ ሙስና ላይ የጸና አቋም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል›› ሲሉ የአፍሪካ መሪዎች ግላዊ ባህሪ ለፀረ ሙስና ትግል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።


በመሪዎች ግላዊ ባህሪ ላይ ከዶክተር ያዕቆብ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው አቶ ልደቱ አያሌው ከመሪዎቹ ባህሪ በላይ ግን የስርዓቱ መዋቅር ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባ እምነታቸውን አስቀምጠዋል።


በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር በምታጣው አፍሪካ መሪዎቿ የወሰዱት እርምጃ ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም ለጊዜው ጉዳዩን በአሳሳቢነት መመልከታቸው በራሱ መልካም ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን እና ግብጽን በመሳሰሉ አገራት መሪዎቹ አጀንዳውን ፈልገውት ሳይሆን ህዝብ በመሪዎች ላይ ያነሳባቸውን ተቃውሞ ለማስተንፈስ ወይም አቅጣጫ ለማስቀየር የተጠቀሙበት ነው ሲሉ የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ።


ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በአፍሪካ በየዓመቱ የሚመዘበረውን ህልቆ መሳፍርት ገንዘብ ማስቆም የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ መሪዎች ቁርጠኛ ከሆኑ አጀንዳውን የሚደግፉት ወገኖች በርካቶች ናቸው። ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ግን ወደፊት የምናየው ይሆናል።


የውጭ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ግዙፍ የመዋለ ንዋይ አንቀሳቃሽ ተቋማት በአፍሪካ ምድር በነጻነት መስራት የሚስችላቸው ዴሞክራሲን ባህሉ ያደረገ እና ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ የሆነ መንግስት ሲኖር ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የአህጉሪቱ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እና ትልቅ አቅም ያለው የህዝብ ጉልበት ተቀናጅቶ ለአህጉሪቱ ህዳሴ እውን መሆን በር ይከፍታል። ለዚህ ግን በቅድሚያ ከላይ የተቀመጡት ነጥቦች በተገቢው መልኩ ሲመለሱ ነው። ያ ካልሆነ ግን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሌለው ህዝብ በመንግስትና በአገር ላይ የሚነሳው ተቃውሞ የከፋ ስለሚሆን አህጉሪቱን እንደገና ወደ ከፋ ጉዞ መምራቱ አያጠያይቅም። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
179 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1161 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us