ሦስቱ መሪዎች በርግጥ ተስማምተዋል?

Wednesday, 31 January 2018 13:11

 

30ኛ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን ተከትሎ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በሸራተን አዲስ ባደረጉት የጎንዮሽ ስብሰባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአካባቢ ጥበቃ ተፅዕኖ ጋር በተያያዘ ጥናት እንዲደረግ ቀደም ብለው የተስማሙ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ግብፅ በጥናቱ አካሄድ ላይ አለመተማመንና አለመስማማት በተደጋጋሚ ጊዜ በማቅረቧ ውጥረት ነግሶ የነበረ ቢሆንም፣ ባልተጠበቀ መልኩ በጃንዋሪ 29 ቀን 2018 የገጠሙቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ተስማምተናል የሚል ሰበር መግለጫ አውጥተዋል።


ሰበር ዜና ተብሎ የተነገረው፣ በሶስቱ ሀገሮች መካከል ያለው ወንድማማችነትና ትብብር አንድነታቸውንና ለጋራ ጥቅም መቆማቸውን ማረጋገጫ ነው። በዚህ መንፈስ ሶስቱ ሀገሮች እንደአንድ ሆነው ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ፤ እንዲሁም በካርቱም ለተፈረመው የመርሆች ስምምነት (Declaration of Principles)ተገዢ መሆናቸውን ዳግም አረጋግጠዋል።


ሶስቱን ሀገሮች የበለጠ ግንኙነታቸውን ለማስተሳሰር የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በጋር ለማልማት እና የእኩሌታ መዋጮ ለማቅረብ ተስማምተዋል። መሪዎችም በዓመት አንድ ጊዜ በመገናኘት ለመስራት ተስማምተዋል።


በተጨማሪም መሪዎቹ ኮሚቴ በማወቀር እና ውይይቶች በማድረግ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያሉ በጣም አስፈላጊ መረጃዎችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመመልከት ተስማምተዋል። እንዲሁም በቴክኒካል ኮሚቴው ላይ በተመሳሳይ መንፈስ እና ሕብረት ለመመልከት ተስማምተዋል።


የስምምነቱ አጠቃላይ ይዘት ጉዳዩን በሚከታተሉ ባለድርሻ አካላት የተለየ ተደርጎ አልተወሰደም። አዲስ የተባለው ጉዳይ ግብፅ ዳግም ለመለሳለስ መሞከሯ ብቻ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ቢሮ አነጋግረናል።


የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሶስቱ ሀገሮች ስምምነትን አስመልክተው በሰጡን ማብራሪያ፣ “የሶስቱ ሀገሮች የስምምነት መግለጫው ፍሬ ነገር፣ በሶስቱ ሀገሮች መካከል የሚደረገው ውይይትና ትብብር ከኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ታጥሮ መቀመጥ የለበትም። በተለያዩ ዘርፎች ሁሉን አቀፍ ውይይትና ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ነው የተስማሙት” ብለዋል።


አያይዘው በሀገሮቹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውሃ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ ንዑስ ኮሚቴ አዋቅረው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ያልተፈቱ ጉዳዮችን ለይተው በአንድ ወር ውስጥ እንዲያቀርቡ መሪዎቹ መመሪያ ሰጥተዋል። ለመሰረተልማት ግንባታ የሚሆን ፈንድ በእኩል ድርሻ በማዋጣት ለማቋቋም ተስማምተዋል። ከኢትዮጵያ እስከ ግብፅ የሚደርስ ባቡር ይዘረጋል፤ መንገዶች ይገነባሉ፤ ግንኙነቱና ትብብሩም ተያይዞ ይጠናከራል ብለዋል።


“ግብፅ የዓለም ባንክ ያደራድረን ያለችውን ጥያቄ አንስታለች ወይ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቃል-አቀባዩ የሰጡት ምላሽ “ግብፅ ስለዓለም ባንክ ያደራዳሪነት ጉዳይ ስለማንሳቷ አላውቅም። መሪዎቹ ዝግ ስብሰባ አድርገው በሰጡት መግለጫ ዓለም ባንክን በተመለከተ አጀንዳቸው አልነበረም። አጀንዳው ቀደም ብዬ ገለፃ ባደረኩባቸው ጭብጦች ዙሪያ ነበር” ብለዋል።


“አሁን ተደረገ የተባለው ስምምነት ለግብፅ ፕሬዝደንት አብዱልፈታ አል-ሲሲ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውድድር የፖለቲካ ድጋፍ ከመስጠቱ ውጪ ፋይዳ የለውም የሚሉ አሉ። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በግብፅ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውድድር አንዱ ምንአልባትም ዋናው አጀንዳ በመሆኑ፣ ሶስቱ ሀገሮች የገጠማቸውን ችግር በጋራ ለመፍታት መስማማታቸውን መግለፃቸው ለፕሬዝደንት አልሲሲ ፖለቲካዊ ትርጉምና ድጋፍ መስሏል፤ እሳቸውም እንኳን ደስአላችሁ” የሚል መልክት አስተላልፈዋል። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?”


አቶ መለስ ዓለም የሰጡት ምላሽ፣ “የግብፅ ሀገራዊ ምርጫ የግብፆች ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም፤ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችንም ጣልቃ ገብነትን የሚደግፍ አይደለም፤ የፖሊሲውም የማዕዘን ድንጋይ ይኸው ነው” ብለዋል።


በተያያዘም የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ጉባኤ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዘ አስጊ ነገር አለመኖሩ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው። እንዲሁም ከግብፅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ወታደራዊ እንቅስቃሴ መሠረተ ቢስነው ብለዋል።


ፕሬዝደንት ኢሳያስ ሰሞኑን በኤርትራ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት የአንድ ሰዓት ተኩል መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ከመግለፃቸው በተጨማሪ፣ በትልቅ ችግርነት ያነሱት በኢትዮጵያ ሕገመንግስት ላይ የሰፈረው አንቀጽ 39 እስከመገንጠል የሚፈቅደው አንቀጽ መሆኑን አትተዋል። ከፕሬዝደንቱ መግለጫ ጋር በተያያዘ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሰጡት ምላሽ “የፕሬዝደንቱ መግለጫ ሰሞኑን በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄዱ ባሉ እንቅስቃሴዎች ተገፍቶ የተሰጠ ነው፤ በእኛ በከል ፋይዳ ቢስ መግለጫ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።


ከላይ ከሰፈረው የሶስቱ ሀገሮች የስምምነት ቃል፤ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እየሰጠ ያለው መግለጫ እና ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብፅን ጎብኝተው ሲመለሱ በኤርትራ ቴሌቪዥን ቀርበው በግብፅ ስለለነበራቸው ጉብኝት የሰጡት መግለጫን ደምረን ስንመለከተው በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ያለው ተለዋዋጭ የፖለቲካ ቀውስና ቀውሱን ተከትሎ በሀገሮቹ መካከል የሚያዘው አቋም ለመገንዘብ አስቸጋሪ ነው።


በተለይ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ከግብፅ ጋር፤ ሱዳን እና ግብፅ፤ ኤርትራና ሱዳን፤ ኤርትራና ግብፅ ሲያንጸባርቁት የነበረው ፖለቲካዊ ዲስኩርና ትብብር በጣም አስገራሚ ነበር። አሰላለፋቸው አሁን የተቀየረ መስሎ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል የሚል አቋም አንጸባርቀዋል። ኤርትራና ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን ተደረገ የተባለውን ስምምነት እንዴት እንደሚመለከቱ ማወቅ ቢቻል ምነኛ መልካም ነበር። ኢሳያስ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንደሚባለው ይመለከቱት ይሆን?


ምክንያቱም ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከግብፅ ጉብኝታቸው መልስ የኢትዮጵያ መንግስትን እስከመቀየር የሚያደርስ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል። ፕሬዝደንት ኢሳያስ ሀገሮችን ከማተራመስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ወደ መንግስት የመቀየር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያደረጉት ሽግግር መነሻው ምንድን ነው? በርግጥስ የኢሳያስ አገዛዝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ወታደራዊ አቋም መዋቅራዊ በሆነ ደረጃ የተዘጋጀና አንድ መንግስት መገልበጥ በሚያስችለው ቁመና ላይ ይገኛል ብሎ መውሰድ ይቻላል?


ሌላው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የፕሬዝደንት ኢሳያስ ሰሞነኛ መግለጫ በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄዱ ባሉ እንቅስቃሴዎች ተገፍቶ የተሰጠ ነው፤ በእኛ በከል ፋይዳ ቢስ መግለጫ ነው ማለታቸው፤ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያለው ገፊ ምክንያት ምንድን ነው የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ይጋብዛል። በዋናነት ከመካከለኛ ምስራቅ የፖለቲካ ሰልፍና አጀንዳ ከማሸከም አንፃር ከወሰድነው፤ አሰላፊውን እና የተሰጠው አጀንዳ ለማወቅ የሮኬት ሳይንስ አይጠይቅም።


ፕሬዝደንት ኢሳያስም የተሰጣቸውን አጀንዳ አስፈላጊ ከሆነ ለመፈጸም ሐሜት ፈርተው ወደኋላ እንደማይሉ በአንደበታቸው ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ በሰጡት መግለጫ “ከግብፅ ጋር ባለን ሁሉን አቀፍ ትብብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ ወደኋላ አንልም። በየትኛውም ሁኔታ ወታደራዊና የፀጥታ ትብብር ለማድረግ ብንፈልግ ወሬና ሐሜት ፈርተን የምንተወው ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።


ፕሬዝደንት ኢሳያስ፣ ከግብፅ ጋር “በየትኛውም ሁኔታ ወታደራዊና የፀጥታ ትብብር” ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል። በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለግብፅና ለኤርትራ የጋራ ስጋት የሚሆንባቸው ጉዳይና ሀገር ማነው? ግብፅ እና ወዳጆቿ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ለብዙ ዓመታት መስራታቸው የአደባባይ እውነት ነው። ግብፅ ኤርትራን የፈጠረችው ማስፈጸም ለምትፈልገው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተልዕኮ መሆኑን፤ እንኳን የኢትዮጵያ ሥርዓተ-መንግስት ቀርቶ፣ ኢሳያስም አይጠፋቸውም።


የግብፅና የኢሳያስ ጋብቻን የሚያጠናክረው ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትን የመሰረተው ገዢው ፓርቲ ወይም ሥርዓተ-መንግስቱ ነው። ሁለቱም የጋራ ጠላታቸው አድርገው የሚወስዱበት ምክንያት አላቸው። ግብፅ ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እጇን ከታ ከማተራመስ እስከ ኤርትራን እስከማስገንጠል ሁሉን አቀፍ ትብብር አድርጋለች፤ ለተወሰነ ጊዜም አሸናፊ ለመሆን በቅታ ነበር። ይህንን የግብፅ አቅም የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስተሳሰር ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት በሥራም በታሪክም የታደለው አሁን ያለው ገዢ ፓርቲ ነው። ስለሆነም ይህንን ገዢ ፓርቲ በማንኛውም ዋጋ ግብፅ ከማጥፋት አትመለስም። በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረገች ያለው የነውጥ ፖሊሲዋ እንደተጠበቀ ሆኖ ለማለት ነው።


ፕሬዝደነት ኢሳያስ እና አገዛዛቸው በበኩሉ፤ ኤርትራ ላይ ለተጋረጠው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና በተለይ የሕዝብ ፍልሰት በዋነኛነት ተጠያቂ የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ሥርዓተ-መንግስት የመሰረተውን ገዢውን ፓርቲ ነው። ከፍተኛ ክህደት እንደተፈጸመባቸውም ይናገራሉ። በተለይ ሕወሓት በታሪካዊ ጠላትንት በኤርትራ አገዛዝ ይወሰዳል። ስለዚህም አሁን ያለውን ገዢ ፓርቲ እንደግብፅ በማንኛውም ዋጋ ለማፈራረስ ይሰራሉ።


የግብፅና የኤርትራ መንግስት የጋራ ግባቸው ተደርጎ መውሰድ የሚቻለው፣ በአንድም በሌላ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመሰረተው መንግስት በእነሱ ፈቃድ ዝለል ሲባል የሚዘል መንግስት መፍጠር ነው። ይህ የተሳሳተ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንተናው የሚጀምረው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ በቅጡ ካለማወቅ እና ለማወቅ ካለመፈለግ መሆኑ አሻሚ አይደለም። ውጤቱም የሚሆነው ባስቀመጡት ትንታኔ ልክ እንደሚሆን አጠያያቂ አይደለም።


ስለዚህም “ሰበር ዜና” ተብሎ ለአደባባይ የበቃው የሶስቱ ሀገሮች ስምምነት፤ ለፕሬዝደነት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ፖለቲካዊ ድጋፍ ከመስጠት በዘለለ፤ የግብፅን ተፈጥሮያዊ ማንነት የሚቀይር ስምምነት አይደለም። አበው እንደሚሉት አሳን መብላት በብልሃት፤ ግብፅንም እንደዚሁ መሆኑ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
704 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1095 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us