“ህዝብን እያጠቃ የሚንቀሳቀስ አካል፤ የእኔ የሚለው ህዝብ ሊኖረው አይችልም”

Wednesday, 07 February 2018 13:37

“ህዝብን እያጠቃ የሚንቀሳቀስ አካል፤ 

የእኔ የሚለው ህዝብ ሊኖረው አይችልም”

 

አቶ ጌታቸው ረዳ
የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል

 

በማህበራዊ ሚዲያ “ትግራይ" መገንጠል እንደአንድ አማራጭ በሚል የውይይት አጀንዳ ለማስቀመጥ እየተሰራ እንደሚገኝ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ የአጀንዳው ዋነኛ ባለቤት በርግጠኝነት ማስቀመጥ ባይቻልም፣ በርግጠኝነት በትግራይ ክልል እየተጠየቁ ካሉት የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የልማት እና የፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጉዳዮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው በውስጣዊ እምቅ ፍላጎቶች በተሞሉ ኃይሎች የቀረበ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡


በሌላ መልኩ ከተመለከትነው፣ ሆን ተብሎ በተዘጋጁ የክልሉን ሕዝብ በአንድ ከረጢት ውስጥ ከተው “የሕወሓት የበላይነት”፣ “የትግራይ ሕዝብ የበላይነት”፣ “የአጋዚ ጦር” እና ሌሎች ቅጥያዎችን በመጨመር በዘመቻ መልክ የክልሉን ሕዝብ በጅምላ ለማሸማቀቅ በተጠና የፕሮፖጋንዳ ቅጥቀጣ የተሰላቹ የክልሉ ሰዎች ያቀረቡት ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል፡፡


ሌላው፣ በሻዕቢያ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳ አውቀው ወይም ሳያውቁ ተጠልፈው ጥያቄውን ያቀረቡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፕሬዚደንት ኢሳያስ የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 39 መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል ይህ አንቀጽ በሕግ-መንግስቱ እንዳይካተት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ከአንድ ወር በፊት ለመገናኛ ብዙሃን መግለፃቸው ይታወቃል፡፡


በአንድ ክልል ሕዝብ ላይ አንድ አይነት ይዘት ያላቸው፣ በተለያየ አቀራረብ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ውጤታቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር መለካት አለባቸው፡፡ የአንድ ክልል ሕዝብን እንደሕዝብ ጥግ አሲዞ የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወት የተሰለፉ ኃይሎችን ፍላጎት፣ በጥንቃቄ መመልከቱ ተገቢነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሁሉም ወገን የዚህን አይነት የፖለቲካ ጨዋታ ትርፍና ኪሳራውን ማስላት አለበት፡፡


በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በየክልሎች እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በትግራይ፣ በሶማሌ እና በሌሎች ልጆች ላይ ተፈጽሟል፡፡ የወንጀሉ ተደጋጋሚነት እየቀጠለ እየበረታም ይገኛል፡፡ እንደሕዝብ ይህንን መሰል ወንጀል ወዴት ያደርሰናል? እንደሕዝብ አንድ አድርጎ ሊያስቀጥለን ይችላል ወይ? ሁሉም ዜጋ ቆም ብሎ ምላሹን መስጠት አለበት፡፡ የሚበጀውን መምረጥና ወደፊት መጓዝ ሀገርና መንግስትን የማስቀጠል ጥያቄ ነው፡፡


ወደተነሳንብት ነጥብ ስንመለስ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ከማንነት ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል ልጆች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ከሚል መነሻ፣ “ትግራይ ብትገነጠልስ” የአማራጭ አጀንዳ ለውይይት በማሕበራዊ ሚዲያ ተጥዷል፡፡ ሃሳብ ማቅረብ ሕገመንግስታዊ መብት መሆኑ አሻሚ አይደለም፡፡ የቀረበው ሃሳብ “እራስን” የሕዝብ ጠበቃና አዳኝ አድርጎ፣ ሌላውን ለክልሉ ሕዝብ ደንታ የሌለው ዳተኛ አካል አድርጎ የማቅረቡ ፍላጎት ዓላማው ምንድን ነው? የሚለውን መፈተሽ ተገቢ በመሆኑ ነው፡፡ በሌሎች ክልል ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ የማንነት ጥቃቶች ተፈጽመዋል፤ የመገንጠል ወይም ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ አልቀረበም፡፡ አሁን ላይ ለምን የተለየ ጥያቄ ማቅረብ አስፈለገ? የማንነት ጥቃት የደረሰበትን ወገን የሚዳኝ ሕገመንግስታዊ ሥርዓት የለም ብሎስ መውሰድ ይቻል ይሆን? በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የማንነት ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚጠብቃቸው ማንነው?


ከላይ ካሰፈርናቸው ነጥቦች መነሻ የሕወሓት ሥራአስፈፃሚ ለሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን ጥያቄ አቅርበን ምላሽ ሠጥተውናል፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም መምህርና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ አቶ ናሁሠናይ በላይ አነጋግረናቸው ለአንባቢ እንዲመች በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

 

“ከማንነት ጥቃት ጋር በተያያዘ “ትግራይን” የመገንጠል ሃሳብ በተወሰኑ ግለሰቦች ቀስቃሽነት በማሕበራዊ ሚዲያው በስፋት ለውይይት ቀርቧል፡፡ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች በክልሉ ሕዝብ ዘንድ ምን አይነት መሰረት አላቸው? ወይም የተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት አድርጎ የሚወሰድ ነው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጌታቸው የሰጡት ምለሽ፣ “እንገንጠል የሚል አመለካከት ያለው ሰው ቢኖር ብዙም አይገርመኝም፤ በየቦታው አለ፤ በትግራይ ህዝብ ደረጃ ግን ቁምነገር ተደርጎ የሚወሰድ ጉዳይ አይደለም። የትግራይ ህዝብ የታገለዉም የሚያስደስተዉም የሚመኘውም ጥቅሙ የሚከበረዉም ዴሞክራስያዊትና ብዝሃነት በምታከብር ጠንካራ ኢትዮጵያ ነው ብሎ፤ የሚያምን ህዝብ ነው። ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ የታገለው። አንድ ሁለት ሰው በሞቅታ ወይም በስሜት የተናገሩት ሊሆን ይችላል እንጂ ትርጉም የለዉም። ተቀባይነት ያለው ነገርም አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡


አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ችግሮች ዋና ዓላማቸው ስርዓት ማፍረስ ነው፣ ዋና ትኩረታቸው የትግራይ ህዝብ አይደለም። ሥርዓቱን ለማፍረስ የተንቀሳቀሱ በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል፤ እንደ ሕዝብ ጥቃት አልተሰነዘረም። በዚህ ላይ ተመስርቶ ልገንጠል የሚል ካለ፣ ትግራይንም ኢትዮጵያንም አያዉቃትም ማለት ነው። ማንኛዉም ኃይል ህዝብን ማዕከል አድርጎ ለማጥቃት ከተንቀሳቀሰ ዓላማው ሃገር ማፍረስ ነው። ይህ አፍራሽ እንቅስቃሴ ሁላችንም ነው ልንመክተው የሚገባን። አንዳንድ ቦታዎች ላይ የትግራይ ተወላጆች ማዕከል ተደርጎ ጥቃት ይፈፀማል፣ አላማው ግን ስርዓትን ማፍረስ ነው። በየመንደሩ በምትፈጠር ችግር ተመስርቶ አገር ልገንጥል የሚል ካለ ተበትኖ መፍትሔ አይገኝም። ሁላችንም በጋር ልንታገለው የሚገባ ችግር ነው ያለው” ብለዋል፡፡


አቶ ጌታቸው አስምረው እንደተናገሩት፣ “ለአንዱ ህዝብ ያልሆነ ሰው፣ ለሌላው ህዝብ ሊሆን አይችልም፡፡ ህዝብን እያጠቃ የሚንቀሳቀስ አካል የእኔ የሚለው ህዝብ ሊኖረው አይችልም። ስርዓት የማፍረስ ዓላማ ያላቸው ሰዎች አሉ፣ በምን ብንጀምር ብለው አስልተው ይሰራሉ ያንን እምንከተል ከሆነ አብረናቸው ነው የምንነጉደው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡


“የህወሓት አዲሱ አመራር በየመንደሩ የሚካሄደዉን ስርዓትን የማፍረስ እንቅስቃሴ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በጋራ እንታገላለን ብሎ ነው፣ ስራውን የጀመረው። የህወሓት አመራር በየመንደሩ የሚያሰማራው ሚሊሻ የለዉም፤ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እርምጃዎች በጋራ እየወሰደ ስርዓቱ እንደ ስርዓት በማጠንከር ነው፣ የሁሉም ህዝቦች መብት የሚከበረው ብሎ ነው የሚያምነው። ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማስጠበቅ በዘለለ አዲሱ አመራር በምን መልኩ ጥቃት ማስቆም እንዳለበት ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚናገሩ ልጆች ይንገሩን። ዋስትናችን ሕገ መንግስቱ ብቻ ነው።” ሲሉ አማራጭ ሃሳብ አለኝ የሚል አካል ካለ ለመስማት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡


እንዲሁም “ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ሊሰጠው የሚችል ነገር ራሱን በማፅዳት፣ በማስተካከል ህዝቡ ለሚያነሳው የመልካም አስተዳደር፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በክልልም በፌዴራልም ድርሻዉን መወጣት ነው። ስለመገንጠል ማስብ ግን ትግራይንም ኢትዮጵያንም አለማወቅ ነው። ምንድን ነው መደረግ ያለበት? የሚል ላይ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ካሉ ለመስማት ዝግጁ ነኝ። ጠላት የትግራይ ህዝብ የበላይነት አለ ይላል፤ የሚልበት ምክንያት የበላይነት አለ ብሎ ስላመነ አይደለም። ስርዓት ለማፍረስ መነሻ እናድርገው ብሎ ስለተንቀሳቀሰ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ በትግራይ ህዝብ ስም የሚፎክሩት ይህንን የበላይነት የሚለው ነገር ከምር የወሰዱት ይመስላል። ሁሉም ዋስትና የሚያገኘው ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ሲከበር ነው። እያንዳንዱ ክልል ተወላጆቹ ባሉበት ቦታ ሚሊሻ እያሰማራ ሊሰራ አይችልም። ብሔር ተኮር ጥቃት ተጋሩ ላይ ሲፈፅሙ ያስቆመው ህዝቡ ነው። ህዝቡን ተክቼ ይህንን ስራ እኔ ልስራ የሚል የፌስቡክ አርበኛ ካለ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት” ሲሉ አቋማቸውን አሻሚ ባልሆነ መልኩ ገልጸዋል፡፡


በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም መምህር አቶ ናሁሰናይ በላይ በበኩላቸው “ትግራይን እንገነጥላለን የሚሉ ሰዎች መነሻቸው ምንድን ነው?" ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አራት ነጥቦች አስፍረዋል፡፡ “አንደኛ፣ በየቦታው ችግር ሲፈጠር "የትግራይ የበላይነት፣ ትግራይ፣ ተጋሩ" የሚል አሰልቺ ነገር ትግራዋዩን ስላስከፋ ይህ ጤነኛ ያልሆነ ትግራይን ሲከስ የሚዉል የተቃዉሞ ፖለቲካ ዉሸት መሆኑ በሰዓቱ የሚያብራራ አካል ስላልነበረ፤ ይህ መጥፎ አካሄድ ለመጥፎ ፖለቲካ እርሾ ሊሆን ይችላል። በመጥፎ የተቃዉሞ ፖለቲካ ቅኝት የከፋው ሰው አለ ለማለት ነው:: ብሔር ተኮር ጥቃት ሲፈፀም ደግሞ በስሙ ጠርተው ሊኮንኑት ይገባ ነበር፡፡


ሁለተኛው፣ ህወሓት ተሃድሶ አድርግያለሁ ካለ በኃላ የዘረዘራቸው ችግሮች እንዴት አድርጎ ሊፈታቸው እንዳሰበ የሚያሳይ ዝርዝር የመፍትሔ አጀንዳዎች (Transformational Agenda)፣ ከችግር የሚያሻግሩን መንገዶች ቶሎ ስላላቀረበ የተወሰነ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ፈጥሯል። የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ችግሮች እንዴት እንደሚፈታ ዘርዝሮ ካላስቀመጠ የህዝብ ተስፋ ማግኘት ከባድ በመሆኑ።


ሶስተኛ፣ ይህንን ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም የሚፈልግ አመራሩን ማሸማቀቅና ማሳጣት የሚፈልግ ፖለቲካዊ ግብ ያለው አካል ሊያራምደው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። አመራሩን መመዘን በማይቻልበት ነጥብ መዝኖ ለመጣል የሚደረግ ሙከራም ይኖራል። ህጋዊ እዉቅና ያለው እንቅስቃሴም አይደለም፣ ፖለቲካዊ መሰረትም ያለው ነገር አይደለም። አመራሩ ምን አዲስ ነገር አመጣህ፣ ምን ሰራህ፣ ተሃድሶ ማለት ምንድን ነው፣ ምንስ እቅድ ይዘሃል ብሎ መጠየቅ ሲቻል ቀጥተኛ ቁጥጥር በሌለው ነገር መዝኖ መጣልም የተፈለገ ይመስለኛል።
አራተኛ፥ በሁኔታዎች ተከፍቶ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን ምስቅልቅል ሊፈታ አይችልም ከሚል አረዳድ ተነስቶ ሃሳቡን የሚያቀነቅን እንደሚኖር መገመት ይቻላል። ይህ ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተፈጠረዉን ነገር በቅጡ ተረድቶ ፀጋዎቹንና ተግዳሮቶቹን መዝኖ ካለማየት ሊመነጭ የሚችል ነው። የግጭቱ ባህሪ ወይም አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያለው ቅራኔ በቅጡ ባለመረዳት ወይም ሆን ብሎ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንደተጋጨ አስመስለው የሚያቀርቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።”


አቶ ናሁሠናይ በመጨረሻም፣ “የመገንጠል ጥያቄ የትግራይ ህዝብ አጀንዳ እንዳልሆነ፤ የትግራይ ህዝብ እንደ ማንኛዉም ህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ የሰላም ፍላጎት ያለው ህዝብ መሆኑ፤ ለጋራ ችግሮቹ የጋራ መፍትሔ እንደሚፈልግ በከፈለው መስዋዕትነት ያረጋገጠ ህዝብ ነው፡፡ ከታሪኩም ከባህሉም ከዓላማዉም ኮሽ ባለ ቁጥር የሚደነግጥና የሚበረግግ ህዝብ አይደለም” ብለዋል። 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
701 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1022 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us