“ገዥዎቻችን በተናገሩት ቃል ላይ እንደማይቆሙ የተረጋገጠ ነው”

Wednesday, 14 February 2018 12:17

 

“ገዥዎቻችን በተናገሩት ቃል ላይ እንደማይቆሙ
የተረጋገጠ ነው”


አቶ ሙሉጌታ አበበ የመኢአድ ም/ሊቀመንበር

በይርጋ አበበ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ላለፉት አስር ዓመታት እና ከዚያ በላይ ተዘግቶ የቆየውን የሰሜን ሸዋ ዞን ጽ/ቤቱን ባሳለፍነው እሁድ ከፍቷል። በኢትዮጵያ ስለሚታየው ወቅታዊ ሁኔታ እና አመላካች መፍትሔዎች እንዲሁም የፓርቲውን አቋም በተመለከተ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገዋል። አቶ ሙሉጌታ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ ምልልስ እነሆ።


ሰንደቅ፡- ፓርቲያችሁ ሰሞኑን በደብረ ብርሃን ከተማ ጽ/ቤት ከፍቷል። ከዚህ በፊት የነበረውን ጽ/ቤት ነው የከፈታችሁት ወይስ አዲስ ቢሮ ነው?


አቶ ሙሉጌታ፡- የሰሜን ሸዋ ጽ/ቤት ሲከፈት የአሁኑ የመጀመሪያው ሳይሆን ገና በ1984 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብሔር እና አማርኛ ተናጋሪ ዜጎቻችን ላይ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ጅምላ ግድያ እና ሌሎች ጭቆናዎች በሚደርሱበት ጊዜ ፓርቲያችን መአሕድ ትግል ሲጀምር ጀምሮ የተከፈተ ጽ/ቤት ነው። ከዚያ በኋላም መአሕድ ከብሔር ወደ ህብረ ብሔር ፓርቲነት ሲሸጋገር በደብረ ብርሃን ከተማ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ የሰሜን ሸዋ ወረዳዎችም ቢሮዎችን ከፍተን ስንሰራ ቆይተናል።


ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ቢሮዎች ቢዘጉም መኢአድ በዞኑ 22 ወረዳዎች መሰረቱን ጥሎ ተስፋፍቶ የሚሰራ ፓርቲ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው ህዝብ ለነጻነቱና መብቱን ለማስከበር ወደኋላ የማይል እና በሰፊው እየታገለ የሚገኝ ህዝብ ሲሆን ምንም እንኳን በመሪዎች፣ በአባላትና በደጋፊዎቻችን ላይ ጫና እና እስር ቢበረታባቸውም በ22ቱም የዞኑ ወረዳዎች መኢአድ ሰፊ መሰረት ኖሮት ትግሉን እያካሄደ ይገኛል። ሰሞኑንም ጽ/ቤቱን እንደገና ስንከፍት ሁለት የሰማያዊ እና ሁለት የመኢአድ ፓርቲ አመራሮች ሆነን በመኢአድ ስም ጽ/ቤቱ እንዲከፈት አድርገናል። በቅርቡም በዚያው በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና በደብረ ብርሃን ከተማ በሰማያዊ ፓርቲ ስም ተጨማሪ ጽ/ቤቶችን እንከፍታለን።


ሰንደቅ፡- ሰማያዊ እና መኢአድ የቅድመ ውህደት ጥናት እያካሄዳችሁ መሆናችሁን ገልጻችኋል። ሆኖም በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ጽ/ቤቶችን በተናጠል ነው እየከፈታችሁ የምትገኙት። በተናጠል ቢሮ መክፈት ለምን አስፈለገ? የቅድመ ውህደት ድርድሩስ የት ደረሰ?


አቶ ሙሉጌታ፡- ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተናጠል መክፈቱ ጥፋት የለውም፤ እንዲያውም ወሳኝነት አለው። ምክንያቱም ህዝቡ ሃሳቡን የሚገልጽበትና ትግሉን የሚቀላቀልበት ቢሮ መክፈቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ሁለቱ ፓርቲዎች ለውህደት የሚያደርጉት ድርድርና ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ውህደት እስክንደርስ ድረስ ሁለታችንም በተናጠል በርካታ ቢሮዎችን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ መክፈታችን ይቀጥላል። ምክንያቱም የሁለታችን ውህደት ሊሳካ የሚችለው በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አባላት በሚያደርጓቸው እና በምናደርጋቸው የጋራ ውይይቶች መስማማት ላይ ሲደረስ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በሁለታችንም ስም ጽ/ቤቶችን መክፈቱ የውህደት ጉዞውን የተሳካ ያደርገዋል።


ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን መፍታት ጀምሯል። የእስረኞችን አፈታት ተከትሎ የሚሰጡ አስተያየቶች አሉ። መንግስት በምህረት እለቃለሁ ብሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የይቅርታ ፎርም ሞልተው እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል። ይህም በቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ስለሆነ ውስንነት ይታይበታል ሲሉ የሚናገሩ አሉ። በአጠቃላይ የእስረኞቹን መፈታት በተመለከተ የመኢአድ አረዳድ እንዴት ነው?


አቶ ሙሉጌታ፡- ገዥዎቻችን በተናገሩት ቃል ላይ እንደማይቆሙ የተረጋገጠ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የተነገረው በምህረት እለቃለሁ የሚል ቢሆንም እየቆየ ግን በይቅርታ ተብሎ መቀየሩም ከእሱ ባህሪ አኳያ የሚጠበቅ ነበር። ‹‹እኔ ጥፋተኛ ነኝ፤ ለደረሰው ችግር ኃላፊነት መውሰድ ያለብኝም እኔ ነኝ›› ብሎ በአደባባይ በዓለም ህዝብ ፊት የተናገረ መንግስት ኃላፊነት የሚሰማው ቢሆን ኖሮ የፖለቲካ እስረኞችን ለመልቀቅ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ሊያስቀምጥ አይገባውም ነበር። ነገር ግን በዚህ አይነት ቅድመ ሁኔታ የተገደበ እርምጃ መውሰዳቸው ራሳቸውንም ሳይቀር እርዳታ እና ድጋፍ በሚያደርጉላቸው ወዳጆቻቸው ዘንድም ትዝብት ላይ ነው የጣላቸው። እኛም በፓርቲያችን የተመለከትነው ጥፋቱን አምኖ ከስህተቱ ለመማር እስረኛ እፈታለሁ ያለ መንግስት ቅድመ ሁኔታ ሊያስቀምጥ አይገባውም ነበር ብለን ነው። ከዚህ የባሰው ደግሞ እስረኛ እፈታለሁ ጥፋተኛ ነኝ ባለ ማግስት በየቦታው ሰዎችን እየገደለ እና እያሰረ ነው ያለው። በተለይ በወልድያ የሆነው እኮ ወጣቶችን በጅምላ ስታዲየም ወስዶ ነው ያጎራቸው። ይህን የሚያደርግ መንግስት ነው ያለን።


ሰንደቅ፡- መኢአድ በተደጋጋሚ ጊዜ አባሎቼ እና አመራሮቼ ታሰሩብኝ ሲል ቆይቷል። በዚህ ሰሞን በተደረገው እስረኞችን የመፍታት እርምጃ ስንት አባሎቹ ተፈቱለት?


አቶ ሙሉጌታ፡- እንደእውነቱ ከሆነ ከተፈቱት ይልቅ ሰሞኑን የታሰሩት ይበዛሉ። በእርግጥ በምስራቅ ጎጃም የመርጦ ለማሪያም አመራርና የፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ጨምሮ ሶስት አባሎች የተፈቱ ሲሆን በወልድያው ግጭት ብቻ አምስት አመራሮች ታስረዋል።


ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት እያላችሁ ደጋግማችሁ ስትናገሩ ቆይታችኋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ መንግስት አገሪቱ ችግር ላይ መሆኗን የሚያመለክት መግለጫ ሰጥቷል። በእናንተ እይታ ለዚህ ችግር መፍትሔ ብላችሁ የያዛችሁት አቋም ኢህአዴግ በሩን ለድርድር ክፍት ያድርግ የሚል ነበር። ከኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ኦህዴድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያቀረበውን ጥያቄ እንዴት ገመገማችሁት?


አቶ ሙሉጌታ፡- በመጀመሪያ ደረጃ መግለጫውን ስንመለከተው በጣም ጥሩ ጅማሮ ነው ብለናል። ፓርቲው (ኦህዴድ) መግለጫውን የሰጠው በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ከሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሬ እሰራለሁ በማለት ነው። እኛም በመግለጫው መሰረት አንድ በሚያደርጉን ነጥቦች ላይ በተለይም በኢትዮጵያዊነት፣ በብሔራዊ መግባባትና ብሔራዊ እርቅ ላይ አብረን ለመስራት ፈቃደኞች ነን። እስካሁን ግን ከመግለጫ በዘለለ ጥሪ አላቀረቡልንም። ወደፊት ጥሪውን ያቀርቡልናል ብለን እንገምታለን። በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ ባህሪ ተጋብቶባቸው መግለጫው የሚዲያ ፍጆታ ሆኖ ሊቀርም ይችል ይሆናል። ስጋቱ እንዳለ ሆኖ ግን አሁን ለተሰጠው መግለጫ አክብሮት አለን፤ ለመሪዎቹም ጭምር። በተለይ ለክልሉ ፕሬዝዳንት። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ በክልል ደረጃ ሳይወሰን በአገር አቀፍ ደረጃ ጥሪው ቢደረግና ወደ መግባባት የሚወስደን ነጥብ ቢፈጠር ደግሞ የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችላል ብለን እናምናለን።


ሰንደቅ፡- መኢአድ የአማራ ድርጅት እየተባለ ነው በስፋት የሚነገረው። ኦህዴድ ጥሪ ያደርጋል መባሉን ተከትሎ ጥሪውን እየተጠባበቃችሁ ነው። ለመሆኑ መኢአድ በኦሮሚያ ክልል ያለው መሰረት ምን ያህል ነው?


አቶ ሙሉጌታ፡- የአማራ ፓርቲ ነው የሚባውን በሁለት መልኩ ነው የምናየው። አንደኛ በመግቢያችን ላይ እንደተነጋገርነው ፓርቲው ሲመሰረት በአማራው ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍ የሰሜን ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ጎጃም ህዝብ ግፊት ተቋቁሞ እየቆየ ወደ ህብረ ብሔር ፓርቲ ያደገ መሆኑን በማንሳት የተሰጠው ስያሜ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከአማራ ብሔር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ፓርቲውን እንዳይቀላቀሉ የአማራው ገዥ መደብን ለመመለስ የተነሳ ፓርቲ ነው እያሉ ደጋግመው ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል፤ ባይሳካላቸውም ቅሉ። ይህን የሚያሳየው ደግሞ በዞንና በወረዳ ተደራጅተው የሚታገሉ አባላት በአፋር ክልል አሉት። ደቡብ ክልል ደግሞ ጭራሽ ከአማራ ክልል በበለጠና ስፋት ባለው መልኩ ይንቀሳቀሳል። ለምሳሌ ሲዳማ ዞን ላይ በ22 ወረዳዎች ነው የሚንቀሳቀሰው። በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በሁለቱም ወለጋ ዞኖች፣ ምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ወሊሶ ቡራዩ፣ ፍቼ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይትን ጨምሮ በበርካታ ዞኖች እና ወረዳዎች ፓርቲያችን እየተንቀሳቀሰ ነው።


ስለዚህ መኢአድ አገር አቀፍ ፓርቲ እና ድጋፍ ያለው ፓርቲ እንደመሆኑ ከኦህዴድ የሚቀርብለትን ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ ነው።


ሰንደቅ፡- በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ መነሳታቸውን ተከትሎ አገሪቱ ስጋት አንዣቦባታል የሚሉ ወገኖች አሉ። በመኢአድ ምልከታ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ትገልጹታላችሁ?


አቶ ሙሉጌታ፡- ይህች አገር አደጋ ላይ መሆኗን ከአስር ዓመት በፊት ጀምሮ ነው። በተለይ እኛ ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ (የአሁኑ የፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላትን) ለጠቅላ ሚኒስትሩ እና ፕሬዝዳንቱ ደጋግመን ሃሳባችንን በጽሁፍ እስከማሳወቅ ደርሰናል። ነገር ግን ኢህአዴግ ሊሰማ አልቻለም ወይም አልፈለገምና ከእነ ችግሩ ቀጥሎ አገሪቱ ወደ ከፋ ችግር እንድትገባ አድርጓታል። ብዙ ሰዎች የአገሪቱ ቁልፍ በኢህአዴግ እጅ ላይ ነው ሲሉ እሰማለሁ። ነገር ግን ኢህአዴግ ቁልፉ በእጁ ላይ ይሁን እንጂ ቁልፉን ተሰርቋል ወይም ጥሎታል።


የአገር ቁልፍ ደግሞ እንደተከራየኸው ቤት በቀላሉ ሰብረህ የምትገባበት ሳይሆን ከሚመለከታቸው የቤቱ ባቤቶች ጋር የምትመክርበትና ቁልፉን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ዕድል ሊፈጠርላቸው ይገባል። አሁን የተነሳው ማንነትን ማዕከል ያደረገ ግጭት ከመከሰቱ በፊት ገና ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ አሰቃቂ ግድያ እና ማፈናቀል ሲደረግባቸው ጀምሮ ነው ማሳሰብ የጀመርነው። ማንም ሰው ፈልጎ እና ፈቅዶ ብሔሩን መርጦ አልተወለደም፤ ነፍስ ብሔር የላትም፤ ስለዚህ አሁን የተፈጠረው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በጊዜ እልባት እንዲበጅላቸው ነው ፓርቲያችን ደጋግሞ ሲገልጽ የቆየው፤ እየገለጸ ያለውም። ይህን የችግር መፍቻ ቁልፍ ደግሞ በኢህአዴግ ብቻ ተፈልጎ የሚገኝ አይደለም። ይህ የብሔር ግጭት ደግሞ ችግሩ የከፋ ከመሆኑ በፊት ሁላችንም የማንነትን ጉዳይ ትተን ስለአገራችን ብቻ በጋራ ልናስብ ይገባል። ይህንን አስከፊ ስርዓት በሰላማዊ መንገድና ሰላማዊ ትግል መቀየር የምንችለው ሁሉም በማንነቱ ላይ ተከባብሮ ሲኖር ብቻ ነው። ህዝቡም ይህንን ተገንዝቦ ወዳላስፈላጊ እልቂትና ደም መፋሰስ እንዳይገባ ፓርቲያችን አጥብቆ ያሳስባል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
958 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1009 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us