ለኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ድርጅታዊ መግለጫ ጊዜ መስጠት፤ እንዴት ይታያል?

Wednesday, 14 February 2018 12:28

 

በሳምሶን ደሣለኝ

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥር 29 ቀን 2010 ዓ.ም ለ10 ቀናት ዝርዝር ግምገማ በማድረግ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ሶስት ዓመታት ወጣ ገባ የሚሉ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች በክልሉ ተስተናግደዋል። ከፍተኛ የአመራር ለውጦችም ተደርገዋል። ከእሕት ድርጅቶችም ጋር ጥልቅ ውይይት ተከናውኖ፣ አራቱም ፓርቲዎች ለሕዝብ የደረሱበትን ውጤት በእራሳቸው መንገድ አንጸባርቀዋል።


የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ እና ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ሥራዎች መግባት ቢጀምርም በኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ተቃውሞዎች እንደቀጠሉ ናቸው። በተለየ የመግለጫውን ይዘት ወደ መሬት ለማውረድ በተራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ብቻ የሚሞከር አይደለም። ጠንካራ የፖለቲካ አመራር እና ቁርጠኛ አስፈፃሚ አካል ይሻል። ከሁሉም በላይ በቂ ጊዜ ያስፈልጋል፤ ለምን?


የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ የፌደራል ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ የሚከት የተዛባ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መኖሩ አስቀምጧል። በአንድ ሀገር ውስጥ ተዛብቷል የተባለውን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ማስተካከል በአንድ ጀምበር የሚሆን ጉዳይ አይደለም። በአንድ ትውልድም ለመቀየር በጣም ከፍተኛ ሥራዎች ያስፈልጋሉ።


ማዕከላዊ ኮሚቴው ቅድሚያ በመስጠት እሰራዋለሁ ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል፣ “የወጣቶችን የስራ አጥነትን በመቀነስ የኑሮ ሁኔታቸውን ማሻሻል” አንዱ ነው። በአሁን ሰዓት በኦሮሚያ ውስጥ ከ6 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ይገኛሉ። ለእነዚህ ሁሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እውቀት፣ የአመራር ጥበብ፣ ቁርጠኝነት እና ጊዜ ያስፈልጋል። በክልሉ ውስጥ የሚገኘውን እውቀት በማሰስና በማቀናጀት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት፣ አመራሩ በቂ ጊዜ ማግኘት አለበት። የሲቪልና የፖለቲካ አመራሮችን ለማብቃት፣ ጊዜ ያስፈልጋል። ለሕዝብ የተሰጠ እና አድርባዩን ለመለየት ጊዜ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አዲሱ አመራር የሰዎች ስብስብ እንጂ የአስማተኞች ስብስብ ባለመሆኑ ነው።


ማዕከላዊ ኮሚቴውም እንዳስቀመጠው፣ “ቀንደኛ የሕልውናችን ጠላት ድህነት ከዚህ ጋር በተያያዙ መሆኑ ቢታወቅም፤ ይህንን ጠላት ለመዋጋት በመንግስት፣ ድርጅትና ሕዝብ ትስስር ሊሰራ እንደሚገባውና አዳዲስ ሃሳቦችን እያፈለቀ አመራር የመስጠት ጉዳይ ከድርጅታችን እንደሚጠበቅ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።” ብሏል። ስለዚህም ጊዜ ቁልፍ ጉዳይ ነው።


ሌላው፤ የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ካስቀመጣቸው ሥራዎችና ጥሪዎች መካከል አንዱ፣ “በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራችንና በሕዝባችን የጋራ ጥቅም ላይ ከድርጅታችን ኦህዴድ ጋር አብራችሁን እንድትሰሩ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።” ይህ ጥሪ የቀረበው ለተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ነው።


እንደሚታወቀው ኦሮሚያ ክልል ካለው የሕዝብ ብዛት እና ከተፈጠረው ጠያቂ ትውልድ ፍላጎት አንፃር በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ሊሟላ አይችልም የሚል መሰረታዊ መነሻ ያለው ይመስላል። ወይም በኦሮሚያ ፖለቲካ ውስጥ ያገባኛል የሚል ሁሉ የድርሻውን እንዲወጣ የሚጋብዝ ጥሪ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፤ ተገቢም ነው።


ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ውህደት አንድነት የሚባሉት ለበርካታ ጊዜ የተሞከሩና፤ ያልሰሩ መንገዶች ናቸው። የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አብረን እንስራ የሚለውን ጥሪ፣ ተቀናቃኝ የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች እንዴት ይመለከቱታል? ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? መተማመን ላይ ለመድረስ ምን ቅድመ ሁኔታዎች ሊያስቀምጡ ይችላሉ? እና ሌሎች ጥያቄዎችም ይኖራሉ። ሁሉንም ለመፈተሽ በቂ ጊዜ ማግኘት ወሳኝ ነው።


ሌላው፤ “የፌዴራላዊ ስርዓታችንን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምጽ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፤ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን” አንዱ ነው ይላል፤ የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ።


“ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች” ማስተካከል የአንድ ጊዜ ሥራዎች አይደሉም። እንደውም የሕይወት ዘመን ሥራዎች ናቸው። በሰለጠነው ዓለም ሙስናን መቀነስ እንጂ ማጥፋት አልተቻለም። ይህንንም ማድረግ የቻሉት ሙስናን የሚጠየፍ ማሕበረሰብ ገንብተው ነው። እንዲሁም የአሰራር እና የገንዘብ ቁጥጥራውን በዘመናዊ መሣሪያዎች በማገዝ ነው፣ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የቻሉት። ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም እንደሚባለው፤ ኦሮሚያም በአንድ ቀን ልትገነባ አትችልም፤ በትውልዶች ቅብብል ሥረዎች እንጂ በአንድ ጀንበር ወይም በአንድ ዓመት የሚመጣ ነገር የለም። ስለዚህም፣ አመራሩ በቂ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል።


ሌላው፣ “በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብት” ማረጋገጥ ማዕከላዊ ኮሚቴው ከያዛቸው ሥራዎቹ መካከል አንዱ ነው። መግለጫውም እንዳስቀመጠው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከቀያቸው ተሰደው ከሥራ ገበታቸው ተነስተው፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቅስም በሰበረ መልኩ በተወሰኑ ቦታዎች ሰፍረው ይገኛሉ። የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቦታቸው እስካሁን መመለስ አለመቻላችን፣ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ በአሳፋሪነት ከሚጠቀሱ ትውልዶች መሆናችንን መቀበል አለብን። ሁሉም ነገር ዜጎቻችን ወደ ቀዬአያቸው ተመልሰው የሚታይ መሆን አለበት።
በርግጥ ማዕከላዊ ኮሚቴው፣ “ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት በመመለስ እንደ ወንድማማች ሕዝቦች የባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እንዲመራ ጊዜያዊ ችግሮችን ፈተን ለዘላቂ የጋራ ጥቅሞቻችን በወንድማማችነት መንፈስ እንድንረባረብ የሶማሌም ይሁን ሌሎች ብሔረ ብሄረሰቦች በኦሮሞ ባህልና የገዳ ስርዓተ ባስተማረን መልኩ በፍቅርና በአብሮነት እንዲኖሩ ለማስቻል ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።” ይበል የሚያሰኝ ነው። መፈጸም ያለበት ግን፤ አሁን ነው።


ማዕከላዊ ኮሚቴው ከፍ ያላ ደረጃ ላይ መሆኑ ያሳየበትን ትንታኔውን ስንመለከተው ለወቅታዊ ጉዳዮች መሠረታዊ ምላሽ አስቀምጧል። ይኸውም፤ “ዛሬ አድገው የሀገራቸውን ህዝብ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻሉ ሀገራት ታሪክ ሲመረመር በአገራዊ ጉዟቸው ውስጥ ሕዝባዊ አመጽን ያስተናገዱ፣ የወጣቶች ቁጣ የደረሰባቸውና መሰል አጋጣሚዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መቀልበስ የቻሉት፤ የዘላቂ ልማት ባለቤት እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል።” የዚህ ትንተና ቁልፍ ፍሬ ነገሩ፤ ዘላቂ ልማት ማምጣት የሁሉም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑን ያሳያል። ዘላቂ ልማት የሚመጣው በአምስት፣ በአስር፣ በአስራ አምስት፣ በሃያ ዓመታት የሚከናወኑ የልማት የዴሞክራሲ የማሕራዊ ፍትህ ስትራቴጂ ሰነዶች በመንደፍ ነው።


ዘላቂ ልማት ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ የከተተው የማዕከላዊ ኮሚቴው ማሳሰቢያ አብሮ አስቀምጧል። “በመሆኑም በወጣቶች ላይ የሚታየውን ፍትህ የመሻት ቁጣ ሀገርን በማያፈርስ መልኩ ከሃይል በፀዳ ሁኔታ ሰላማዊ የትግል ስልት እንዲከተሉ በማስተማር የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው ያምናል። ዋነኛ ሚናውም የተሻለች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር በመሆኑ የተሻለች ሀገር ብቻ ሳይሆን ብቁ ተረካቢ ወጣቶችን ማፍራት እንደሆነም ይገነዘባል።” ብሏል።


ማዕከላዊ ኮሚቴው “ሀገር በማያፈርስ መልኩ” የሚል ሀረግ ማስቀመጡ ትኩረት የሚወሰድ ነው። ምክንያቱም “ሥርዓት-መንግስት ማፍረስ” እና “ሀገር ማፍረስ” በጣም መሰረታዊ ልዩነት ስላላቸው ነው። ሀገር መገለጫው መንግስት “State” ሲሆን፣ ሥርዓት-መንግስት “Govrnment” ነው። ይህም ሲባል፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከ3ሺ ዘመን በላይ በፈጀ ጊዜ የተመሰረተ ነው። አሁን ያለው ሥርዓተ-መንግስት ከተመሰረተ ደግሞ በሃያዎች እድሜ የሚቆጠር ነው። ስለዚህም ተቋውሞ ማሰማት የኢትዮጵያ መንግስትን ከማፍረስ መለስ መሆን አለበት። ሥርዓተ-መንግስቱንም ለመቀየር የፈለገ ኃይል፣ በቀጣይ ምርጫ ተደራጅቶ በሕግ አግባብ ቢያደርገው የሠለጠነ መንገድ ይሆናል።


በአጠቃላይ የኦህዴድ መግለጫ በጊዜ ሒደት የተሻለ ልማትና አሳታፊ ዴሞክራሲ በኦሮሚያ ክልል ሊያመጣ ይችላል። የኦሮሚያ ሕዝብ ለድርጅቱ የሰጠውት ጊዜ በቂ ነው ብሎ ባመነበት እና ምንም ለውጥ ማምጣት ካልቻለ፤ የመቀየር መብቱ የተጠበቀ ነው። ስለዚህም ጊዜ ፈቅዶ መመዘኑ ይመከራል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1013 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1146 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us