የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምሁራን እና በፖለቲከኞች እይታ

Wednesday, 21 February 2018 12:13

 

በይርጋ አበበ

 

 

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ካሸነፈ በኋላ በአገሪቱ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ከመስከረም 28 ቀን እስከ ሐማሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ለአስር ወራት በአገሪቱ ላይ ተጥሎ የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተነሳ በወራት ልዩነት አገሪቱ እንደገና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንድትመራ የሚያስችለውን ውሳኔ መንግስት ያሳለፈው ባሳለፍነው ቅዳሜ ረፋዱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።


እንደ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ መግለጫም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውሳኔ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተፈጻሚ ይሆናል። በስድስት ወራት ውስጥ የሚፈለገው ለውጥ ካልተገኘ ደግሞ እንደገና ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ይደረጋል።


“በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በተለመደው የህግ አሰራር መምራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ” መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ መገደዱን አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ አያይዘውም ውሳኔው አሁን ተግባራዊ እንዲሆን ተደረገ እንጂ ኢሕአዴግ ለ17 ቀናት ባካሄደው የስራ አስፈጻሚ ስብሰባው ወቅት የተፈጠረው ችግር በ15 ቀናት ውስጥ እልባት ካላገኘ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ውሳኔ ላይ ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን በአገሪቱ ላይ የተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳለፈው ዓመት ዝርዝር መመሪያ የወጣለት ባይሆንም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሊከለክል የሚችላቸውና ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን በዝርዝር አስቀምጠዋል።


ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደውን ውሳኔ “አልስማማም” አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል አቋሙን ገልጿል። ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚህኛው ሃሳብ የሚስማሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የሰጧቸውን መግለጫዎች ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አጣምረን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊነት


በ1987 ዓ.ም የጸደቀው የአገሪቱ ህገ መንግስት በአንቀጽ 93 ቁጥር 1(ሀ) ‹‹የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝቡን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፤ የፌዴራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው›› ሲል ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ የሚዳርጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል።


በአሁኑ ወቅት የታወጀውንም ሆነ ቀደም ሰል በአገሪቱ ላይ ለአስር ወራት ታውጆ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት ሆኖ የቀረበው ‹‹ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን›› የሚለው ምክንያት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።


የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሰጠው የፕሬስ መግለጫ (ፕሬስ ሪሊዝ) ላይ ደግሞ ‹‹ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የተከሰተው አለመረጋጋት በህዝቦቻችን ደህንነትና በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል። ችግሩን ለመከላከልና ለመቀልበስም በተለመደው አሰራር እና አካሄድ ለመፍታት ጥረት ተደርጎ ባለመሳካቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ሁኔታዎች የመሻሻል አዝማሚያ አሳይተው የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ስርዓት አልበኝነት ተፈጥሮ የዜጎች ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ እየጠፋ እና ዜጎች ለዘመናት ያፈሩት ሀብት እና ንብረት በቀላሉ እየወደመ ይገኛል። ይህ አጠቃላይ ሁኔታ ህዝባችንና መንግስት ከሚሸከሙት እና ከሚታገሱት በላይ እየሆነ መጥቷል›› ሲል የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጣለበትን ምክንያት ያስታውቃል።


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዚህ ምክንያት ከሆነ የታወጀው አገሪቱ ውስጥ ያለው የጸጥታ እና የዜጎች ህይወት ምን ይመስላል? የሚለውን ጥያቄ ለምሁራን አቅርበን ነበር። በአምቦ ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት መምህር የሆነው አቶ ስዩም ተሾመ ‹‹በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 በተቀመጠው መሰረት ካየነው በዚህ ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም›› ሲል ተናግሯል። በአብዛኞቹ የአገራችን ክፍሎች የተነሱ ግጭቶችና ብጥብጦችም ቢሆኑ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈልጋቸው አይደለም ይላል። ‹‹በአገራችን የተከሰተው ችግርም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ድምር ውጤት ነው›› ያለው መምህር ስዩም፤ በ2007 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ደግሞ ለችግሩ የመጨረሻው ምክንያት መሆኑን ተናግሯል።


በቅርቡ ከእስር የተፈታው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በበኩሉ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለኢህአዴግ ጊዜያዊ እፎይታ ሊያስገኝለት ይችል ይሆናል እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ግን ሊያመጣ አይችልም። ምክንያቱም ያለው ብጥብጥና ግጭት የጸጥታ ችግር ሳይሆን በኢህአዴግ ፊት ተጋርጦ ያለው የፖለቲካ ጥያቄ ነው። የፖለቲካ ችግር ደግሞ መፍትሔውም ፖለቲካዊ ነው›› በማለት ተናግሯል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አያይዞም በኢትዮጵያ የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአሜሪካ መንግስት እንደማይደግፈው የገለጸበትን መግለጫ በተመለከተ ‹‹የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚጠቅማትን ትክክለኛና ወቅታዊ መግለጫ ስላወጣ በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ›› ብሏል።


በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት ሌላው ምሁር ደግሞ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም ናቸው። የህግ ባለሙያው በጉዳዩ ዙሪያ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹በእውነት ይህ ለችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ይሰጣል ብዬ አላምንም። ህዝቡ ችግሩን ከእነ መፍትሄው ነው የገለጸው። መንግስትም ይህን የህዝብ ጥያቄና ድምጽ ሰምቶ ወደ መፍትሔ መሄድ እንጂ በዚህ መልኩ ችግሩን እፈታለሁ ብሎ መነሳቱ አዋጭ ሊሆነው አይችልም›› ብለዋል። ዶክተር ያዕቆብ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ጦርነት ለመክፈት፤ እና ህዝቡን አደጋ ላይ የሚጥል የተፈጥሮ አደጋ (የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ ወረርሽኝ እና ቃጠሎን ጨምሮ የተለያዩ አደጋ አምጭ ምክንያቶች) ሲደርሱ ለመከላከል ሲባል የተወሰኑ ሰብአዊ መብቶች ሊጣሱ ይችላሉ። አሁን በእኛ አገር ባለው ሁኔታ ግን መፍትሔም አይሆንም አስፈላጊም አልነበረም። እንዲያውም በህዝብ እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሉ መካከል ልዩነትን የሚያሰፋ ስለሆነ ለሰላም የበለጠ ጠንቀ ይሆናል›› በማለት ተናግረዋል።

 

በኮማንድ ፖስት የሚወሰዱ እርምጃዎችና የተሰጡ አስተያየቶች


አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ የሚከተለውን ተናግረዋል።
1. የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር እና ከአደጋ ለመጠበቅ የህዝብና የዜጎችን ሰላም ጸጥታ ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፤ ማንኛውም ሁከት ብጥብጥና በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊ ሆነ የድብቅ ቀስቀሳ ማድረግን፣ ጽሁፍ ማዘጋጀትን፣ ማተምና መሰራጨትን፣ ትዕይንት ማሳየትን፣ በምልክት መግለጽን ወይም መልእክትን በማንኛውም ሌላ መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግን ይከለክላል።
2. ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም ደግሞ እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል።
3. የህዝብና የዜጎች ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የአደባባይ ሰልፍ እና ሰልፍ ማድረግን፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስ ይከለክላል (ዝርዝሩ በመመሪያ ይወጣል)
4. በህገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጄሎችን የጠነሰሰ፣ የመራ፣ ያስተባበረ፣ የጣሰ ወይም ደግሞ በማንኛውም መንገድ በወንጄል ድርጊቱ የተሳተፈ ወይም በወንጄል ድርጊቱ ተሳትፏል ተብሎ የሚጠረጠርን ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር ያደርጋል፤ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በመደበኛው ህግ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጋል።
5. ወንጄል የተፈጸመባቸው ወይም ሊፈጸምባቸው የሚችሉ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ማናቸውንም ቤት፣ ቦታ እና መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማናቸውንም ሰው በማስቆም ማንነቱን መጠየቅና መፈተሸ ይቻላል።
6. በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ እቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ተጣርቶ ለባለመብቱ ይመለሳል።
7. የሰዓት እላፊ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል።
8. ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይቡ ወይም ደግሞ ከተወሰነ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ይደረጋል።
9. የተቋማትን የመሰረተ ልማት ጥበቃ ሁኔታ ወስናል።
10. የህዝብ እና የዜጎችን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን ቦታዎች ለይቶ ይወስናል።
11. በሰላም መደፍረስ ምክንያት የፈረሱ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን ከክልል እና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ እንዲቋቋሙ ያደርጋል።
12. ብሔር ተኮር በሆኑ ወይም በሌሎች ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ከክልል መንግስታትና ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር ወደ ቀድሞ መኖሪያ ሰፈራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ድጋፍ ያደርጋል።
13. የሚገለገልባቸው አገልግሎት ተቋማት የንግድ ስራዎች ወይም የመንግስት ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ተገቢውን ጥበቃ ያደርጋል። ይህን ተላልፎ አገልግሎትን ያቋረጠ ማንኛውም ሰው በህግ ተጠያቂ ይሆናል።
14. የመሰረታዊ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን አቅርቦት የዝውውርና የስርጭት ደህንነት ያረጋግጣል። የትራንስፖርትን ፍሰት ደህንነት ያረጋግጣል።
15. በትምህርት ተቋማት በመማርና ማስተማር ሂደትን ከሚያውኩ ተግባራት የጸዳ እንዲሆኑ እንዲሁም መደበኛ የሆኑ ስራን የሚያስተጓጉሉ እንከኖች እንዳይፈጠሩ ይሰራል።
16. ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስተርዓቱን ለማስከበር፣ ከአደጋ ለመጠበቅ፣ የህዝብንና የዜጎችን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች ይወስዳል። እነዚህ እርምጃዎች ቀጣይ በሚወጡ በአፈጻጸም መመሪያዎች የሚዘረዘሩ እንደሚሆኑ አቶ ሲራጅ ተናግረዋል።


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተከትሎ ተቃውሞን በማሰማት የአሜሪካን መንግስት የቀደመው አልተገኘም። አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የመንግስታቸውን አቋም በሚገልፅ መግለጫ ላይ ‹‹የመናገርና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ይጋፋል፣ የሰዎችን መሰረታዊ መብቶች የሚጥስ ነው። በመሆኑንም አልስማማም›› ሲል አስታውቋል።

 

የተሻለ አገራዊ መፍትሔ


አገሪቱ ውስጥ መጠነ ሰፊ ግጭቶች መኖራቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት የተነሱ ግጭቶችን ለማብረድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንደ መፍትሔ ወስዶታል። ለዚህም ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሁለም የአገሪቱ ክፍሎች ለስድስት ወራት (እስከ ነሃሴ 9 ቀን 2010 ዓ.ም) ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ይህ አዋጅ በስድስት ወራት ውስጥ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ካልቻለም ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ይደረጋል ሲል አስታውቋል።


ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡ ፖለቲከኞችና ምሁራን ደግሞ ከኢህአዴግ የተለየ አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል። የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ያካሄደውን የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ እንደጨረሰ የወሰደውን አቋም እንደተመለከተው የገለጸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹‹ኦህዴድ በአገር ውስጥም በውጭ አገር ከሚኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንደራደራለሁ ማለቱን ስመለከት በኢህአዴግ ውስጥ መሻሻል እየታየ እንደሆነ አመላክቶኛል። አሁንም ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ከሁሉም ሀይሎች ጋር ድርድር እና ውይይት ማካሄድ ነው›› ሲል ይበጃል ያለውን አገራዊ መፍትሔ ተናግሯል።


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ‹‹በሄዱበት መንገድ መመለስ ነው›› ያለው መምህር ስዩም ተሾመ በበኩሉ ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህዝባዊ ተቃውሞ ማካሄድ እና ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድን ይከለክላል። ከዚህ ቀደምም የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባስቀመጠው መመሪያ ማንኛውንም አይነት የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ ክልክል ነው ብሎ ነበር። ያ ክልከላ ባለበት ሁኔታ ነው አገሪቱ ውስጥ እንደዚህ አይነት ሰፋፊ የተቃውሞ ሰልፍ እያየን ያለነው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ የተነሳውን ተቃውሞ ክልከላ እንደማያቆመው ነው። አሁን የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የተነሳውን የህዝብ ለውጥን የመሻት ጥያቄ ከማፈን ውጭ መፍትሔ ሊሆን አይችልም›› ብሏል። መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሲያስቀምጥም ‹‹ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት የችግሩ ብቸኛ መፍትሔ ነው›› ሲል አስቀምጧል።


ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም በበኩላቸው ‹‹ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አባሎችና የሲቪክ ማህበራትን ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል። ይህን ለማድረግ ግን ኳሱ በኢህአዴግ እጅ ላይ ነው ያለው። አገርን መውደድ እና ህዝብን ማክበር ይጠይቃል። ከዚህ በተረፈ ግን ሀይል መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ችግሩን ያባብሰዋል›› በማለት አሳስበዋል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1141 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1032 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us