በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ የኢራፓ እና ሰማያዊ ፓቲዎች አቋም

Wednesday, 28 February 2018 12:59

 

 

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን መንግስትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ፖለተካ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ምሁራን እና ፖለቲከኞች ደጋግመው አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ያጤነው የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጀ ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ‹‹ለችግሩ መፍትሔ አካል ለመሆን›› ራሳቸውን ከስልጣን ማውረዳቸውን ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የአመራር ለውጥ ሲያደርጉ (ኦህዴድ አቶ ለማን በዶክተር አብይ ሲቀይር የአቶ ኃይለማሪያም እናት ፓርቲ ደኢህዴን ደግሞ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ከምክትልነት ወደ ሊቀመንበርነት ከፍ እንዲሉ ማድረጉን ልብ ይሏል)፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራዊያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በበኩሉ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉትን አቶ ደመቀ መኮንን በፖርቲው ሊቀመንበርነታቸው እንዲቀጥሉ ወስኗል። አህአዴግ በቅርቡም የፓርቲውን ሊቀመንበር እና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።


ይህን የኢህአዴግ ውስጣዊ ለውጥ ተከትሎ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ዋና ፀሀፊ አቶ መላኩ መሠለ ‹‹ለአገሪቱ ወቅታዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ አይደለም›› ሲሉ አስታውቀዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታሁን ባልቻ በበኩላቸው “የአቶ ኃይለማሪያም መልቀቅም ሆነ በቦታው ላይ መቆየት ለውጥ የለውም” ሲሉ ተናግረዋል። የሁለቱ ፓርቲዎች ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ያደረጓቸውን ቃለ ምልልሶችና የኢራፓን መግለጫ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የወቅቱ ጥያቄ እና የፓርቲዎቹ ሃሳብ

 

ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ላይ የተነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ቁጣዎች ቶሎ መፍትሔ አግኝተው አገሪቱ ወደ ነበረችበት ሂደት እንድትመለስ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በውስጣዊ ለውጥ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኩል መረጋጋትን እፈጥራለሁ በማለት ሙከራ እያደረገ ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላም የመሻሻል ምልክቶች እየታዩ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ይፋ አድርጓል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀደም ብሎም እስር ላይ የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን በምህረት እና በይቅርታ መፍታቱ የሚታወስ ሲሆን ይህን ያደረገውም ለዘላቂ ሰላም፣ ለብሔራዊ መግባባት እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እንደሆነ ነበር ያስታወቀው።


በአገሪቱ የተፈጠረው ቀውስ መፍትሔ እንዲያገኝ በሚለው ጉዳይ ላይ ከመንግስት ጋር ልዩነት የሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በበኩላቸው ‹‹ሰላም እንዲሰፍን የሚደረግበት መንገድ›› ላይ ነው ልዩነት የሚያነሱት። ለዚህ ደግሞ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሲያስቀምጡ ሁሉን አሳታፊ ውይይት እና ብሔራዊ እርቅ መካሄድ እንዳለበት ይገልጻሉ። በዚህ ሃሳብ ላይ ቀደም ባሉት ሳምንታት ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን በሙሉ በአንድ አቋም የገለጹት ሲሆን ለዚህ ዝግጅት ከጋዜጣችን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ጌታነህ ባልቻ እና አቶ መላኩ መሰለ ‹‹መንግስት ሁሉንም አካላት ለድርድር እና ለውይይት ይጋብዝ፤ ለብሔራዊ እርቅ በሮችን ይከፈቱ መድረኮችም ይዘጋጁ›› ሲሉ ተናግረዋል።


ኢራፓ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን እየታዩ ያሉት የማህራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ምስቅልቅሎች በቀላሉ በማይገመት ፍጥነት እየነጎዱ አገራዊ እና ህዝባዊ ህልውናችንን በተጨባጭ እስከመናድ እየደረሱ በመምጣታቸው ዛሬውኑ እገሌ ከእገሊት ሳንባባል ሁላችንም ባለድርሻ አካላት ወደ ብሔራዊ መግባባት መድረክ እንድንመጣ የሚያስገድድ ተጨባጭ ሁኔታ ተፈጥሯል›› ሲል በአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተናል ለሚሉ ሀይላት ሁሉ ጥሪ አቅርቧል።


‹‹እናንተ ለዚህ ጉዳይ ፓርቲዎችንና ምሁራንን ስትጋብዙ የፓርቲያችሁ ቁመና ለዚህ ብቁ ነወይ? ጥሪ ካቀረባችሁላቸው ፓርቲዎች እና ምሁራንስ ምን ምላሽ አገኛችሁ?›› የሚል ጥያቄ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለአቶ መላኩ ቀርቦላቸው ነበር። አቶ መላኩ ሲመልሱም ‹‹እኛ በራሳችን ተነሳሽነት ለብሔራዊ መግባባት መነሻ አስኳል መድረክ በጥምረት መፍጠር ስለሚቻልበት መድረክ መንገዶችን የማመቻት ስራ እንጂ እኛ እንምራው የሚል ፍላትም ሆነ እቅድ የለንም›› ያሉ ሲሆን ከተወሰኑ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን መቀበላቸውን የሚገልጽ ምላሽ እንደተሰጣቸው ጨምረው ተናግረዋል። ውይይቱ እንዲካሄድ የኢህአዴግ በጎ ፈቃድ እና ተነሳሽነት አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት የኢራፓ ዋና ጸሀፊ፤ ያለ ኢህአዴግ ተሳትፎ ድርድር ማድረግም አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲያውም ኢህአዴግ ለድርድሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት። ‹‹ሆኖም እስካሁን በኢህአዴግ በኩል ላቀረብንለት ጥያቄ ተነሳሽነት አላሳየም›› ብለዋል።


የሰማያዊ ፓርቲው አቶ ጌታነህ በበኩላቸው ‹‹ለአገራችን ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆነን የሚችለው ውይይት ማድረግ ነው›› በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

 

ከሹምሹሩ የሚጠበቅ

 

የኢህአዴግ አመራሮች መቀያየርን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት አቶ ጌታነህ ባልቻ ‹‹አቶ ኃይለማሪም ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የሰሩት ስራ የለም›› በማለት አስተያየታቸውን መስጠት ይጀምራሉ። ፖለቲከኛው አያይዘውም ‹‹አቶ ኃይለማሪያም ባለፉት ለስድስት ዓመታት አካባቢ በነበራቸው ስልጣን በዚህች አገር ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላመጡም። እንዲያውም ከዚህ በፊት ታይቶ ከሚታወቀው በባሰ መልኩ ቀውሱ በርትቶ እና በርክቶ ነበር የተገኘው። ይህም ማለት አቶ ኃይለማሪያም በነበራቸው ስልጣን ለህዝቡ ጥያቄ ሁነኛ የሆነ መልስ መስጠት እንዳልቻሉ የሚያሳይ ሲሆን ለሁለት ጊዜያትም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። ችግሮች ግን ከዚህም ከዚያም በተደጋጋሚ ተነስተዋል። ስለዚህ ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸው ምናልባትም ተገቢ እንደሆነ ነው የሚገባኝ›› ብለዋል።


አቶ ጌታነህ አክለውም ‹‹የሚመጣው የእሳቸው ተተኪ ጠንካራ እና ደፋር መሆን አለበት›› ይላሉ። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም ‹‹የህዝብ ጥያቄ ምን እንደሆነ ተረድቶ መልስ መስጠት ካልቻለ እና ህዝብን የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ካላደረገ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ የባለስልጣናቱ መቀያየር ለውጥ ያመጣል ብለን አናምንም›› ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የድርጅት እና የአገር ኃላፊነትን ለይቶ ማወቅ ይገባዋል›› ያሉት አቶ ጌታነህ የፓርቲ ስራን ከመንግስት ኃላፊነት ጋር ቀላቅሎ የሚሰራ ከሆነ ለውጥ የለውም ይላሉ።


በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በበኩሉ ‹‹የዚህች አገር ችግር መፍትሔ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ብቻ ነው›› ያለ ሲሆን፤ ‹‹አሁን አገራችን ያለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ወደ ባሰ እና የከፋ ደረጃ የሚወስዳት ነው። ለዚህ ደግሞ አሁን ኢህአዴግ እየሄደበት ያለው መንገድ መፍትሔ አይደለም›› ብሏል። የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አያይዘውም ኢህአዴግ በአመራሮቹ ላይ የሚያደርገውን ሹምሽር ውጤት ያመጣል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል። አቶ መላኩ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹አሁን በአገራችን ያለው ከፍተኛ ችግር ዋና ባለቤት በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በመሆኑ የአመራር ለውጥ ቢያደርግ ውጤት ያመጣል ብለን አናምንም። አቶ ኃይለማሪያም ከስልጣን መውረዳቸውን የምንመለከተው በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ስልጣን እየተገበሩት እንዳልነበረ ነው። በዚህ ላይም ቀደም ሲል መግለጫ አውጥተንበታል። አሁንም እየተካሄደ ያለው በአንድ የተወሰነ ቡድንተኞች የሚመራ ሀይል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን እየሰጡ ሰዎችን በመለዋወጥ የፓርቲውን መስመር መለወጥ ይቻላል ብለን አናምንም። ኢህአዴግ አቋሙን፣ ፕሮግራሙን እና ፖሊሲዎቹን መቀየር ይችላል ብለን አናምንም›› ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹምሽር ፓርቲያቸው የሚጠብቀውን ተናግረዋል።


አቶ መላኩ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግን እየጠየቀ ያለው ፖሊሲዎቹን እንዲያሻሽል፣ ፕሮግራሙን እንዲቀይር እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን አስፍቶ አሳታፊ መድረግ እንዲፈጥር ነው›› ብለዋል።


የኢህአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ የፓርቲውን ሊቀመንበር እና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2382 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 851 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us