አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ እርቅ መምጣት ብቸኛ መፍትሄ ነው

Wednesday, 21 March 2018 13:22

አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ እርቅ መምጣት 

ብቸኛ መፍትሄ ነው

አቶ ነጋሽ ገሰሰ
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

 

በይርጋ አበበ

 

አቶ ነጋሽ ገሰሰ ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጅኦግራፊ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በህዝብ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተምረው ተመርቀዋል። ከሰባት አስርት በላይ ዓመታትን ያሳለፉት አንጋፋው ምሁር ቀደም ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን፣ ግብርና ሚኒስቴር እና የህዝብ አስተዳደር ኢንቲትዩት (አሁን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሚባለው) የመሳሰሉትን የመንግስት ተቋማት በሙያቸው አገልግለዋል። ከመንግስት ስራ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ደግሞ በUNDP ለተወሰኑ ዓመታት ሰርተዋል።


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሲመሰረት ከመጀመሪያው መስራቾች አንዱ የነበሩት አቶ ነጋሽ ገሰሰ ተቋሙን በቦርድ አባልነትና በዋና ፀሀፊነት አገልግለዋል። በአሁኑ ሰዓት ከግልም ከመንግስት ስራም ውጭ ሆነው በጡረታ ላይ የሚገኙት እኒህ አንጋፋ ምሁር ‹‹በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ዝም ከማለት መናገር ይሻላል›› ብለው ያምናሉ። በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ ስለ ሰመጉ ወቅታዊና ታሪካዊ ዳራ፣ ስለ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ተስፋ እና ፈተና እንዲሁም ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለሰንደቅ ጋዜጣ ሰጥተዋል። የቃለ ምልልሱ ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ተሰናድቶ ቀርቧል።


ሰንደቅ፡- ውይይታችንን በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ እናድርግ፤ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል?


አቶ ነጋሽ፡- ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንዳትወድቅ ኢሰመጉ (አሁን ሰመጉ) ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ኢሰመጉ ሲመሰረት ሶስት ዓላማዎችን አንግቦ ነበር፤ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ጥረት እንዲደረግ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚል አቋም ይዞ ነው የተቋቋመው። መንግስት እነዚህን ሶስት ዓላማዎች ይዞ ከተራመደ ህዝብ መልካም አስተዳደር ያገኛል ማለት ነው። ህዝብ መልካም አስተዳደር አገኘ ማለት ደግሞ ሰላም ይኖራል። ልማት የሚመጣው ሰላም ሲኖር ብቻ ስለሆነ። ይህን መሰረት በማድረግም በየቦታውና በየጊዜው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ምርመራ እየተካሄደ የሰብአዊ መብት ጥሰት መካሄዱን እየተረጋገጠ ጥፋት ያደረሱትን የመንግስት አካላት እንዲጋለጡ ጥረት ተደርጓል። መንግስት እነዚህን አጥፊዎች እየቀጣ ሲሄድ በህዝብ ተቀባይነት ይኖረዋል ከሚል እሳቤ ነበር። ነገር ግን ይህ ጥረታችን ከመንግስት ጋር አለመግባባት ውስጥ እንድንገባ አድርጓል።


እንደነገርኩህ በተቻለ መጠን መንግስት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እየተከታተለ የሚፈጠሩ ስህተቶች ካሉ እንዲታረሙ የማሳሰብ ስራ ስንሰራ ቆይተናል። በእኔ ግምት መንግስት እነዚህን ነገሮች በትክክል ተመልክቶ አስፈላጊውን እርምጃ በወቅቱ ቢወስድ ኖሮ እንዲህ አይነቱ ቅጥ የሌለው ረብሻ እና ችግር አይፈጠርም ነበር። አሁን በየቦታው መብታችን ተጣሰ ብለው የሚጮኹ ብዙ ናቸው። ይህ ችግር ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ ሁላችንም መለየት አልቻልንም።


ሰንደቅ፡- አገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋት እና ችግር መኖሩን ገልጸዋል፤ ብዙዎችም በዚህ ጉዳ ስማማሉ መንግስትን ጨምሮ። ይህ የኢትዮጵያ ውስጣዊ አለመረጋጋት በምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እንዳለ የሚናገሩም አሉ። እርሰዎ በዚህ ላይ ያለዎት እይታ ምንድን ነው?


አቶ ነጋሽ፡- አለመረጋጋቱ በአገር ውስጥ እያስከተለ ያለውን ውጤት የምናየው ነው። ብዙ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ እያደረገ ሲሆን ሌሎችም ችግሮች እያስከተለ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ንዑስ ቀጠና ኢትዮጵያ መሪ የሆነችበት ቀጠና እንደመሆኑ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ሌሎቹ ላይ ተጽኖ የኖረዋል የሚል ግምት አለኝ። ይህ ችግር እንዳይቀጥል መንግስት የተቻለውን ያህል ጥረት ማድረግ አለበት። ይህ ሲባል መብቶችን ከማፈን ይልቅ ሰፋ አድርጎ በመስጠት ህዝቡ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች ሁሉም አካላት ተወያይተው ለችግሩ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥረት ሲያደርግ የተሻለ ነው። ይህ ካልሆነ ግን እያየነው ያለው ነገር አቅጣጫው ደስ አይልም።


ሰንደቅ፡- በምስራቅ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታዩ ያሉት ለውጦች እንደ አገር ኢትዮጵያን የሚያሰጋ እንደሆነ የሚገልጹ ምሁራን አሉ። በተለይ በሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ያሉ አገራት የቀደሙ የኢትዮጵያ ጠላት የሚባሉ አገራት ወታደራዊ ሰፈር እስከመገንባት ደርሰዋል ሽብርተኝነትም ሳይዘነጋ ማለት ነው። አካባቢው በጠላቶች የተከበበ መሆኑ እና ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው ሽብርተኝነት በቀጠናው መኖሩ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ የሚያሳድረው ነገር ምንድን ነው?


አቶ ነጋሽ፡- በእውነቱ እኔም በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ወስጄ አስቤበት ነበር። የኢትዮጵያን ደህንነት የማይፈልጉ ሀይሎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚከታተሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ሀይሎች ይህንን ሁኔታ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ወይም እንደሚፈልጉ የሚያጠራጥር ነገር አይደለም። ለዚህ ነው ቀደም ብዬም መንግስት ይህንን ተረድቶ ነገሮችን እንዲስተካከሉ ማድረግ አለበት ያልኩህ። ኃላፊነትም አለበት። ምክንያም ጠላቶቻችን አጋጣሚውን ተጠቅመው አገራችን ወደባሰ ቀውስ እንድትገባ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። ስለዚህ መንግስትም በተቻለ መጠን ያለው ችግር እንዲፈታ በድፍረት ወደ ውይይት በመግባት አዲስ መንገድ መፈለግ አለበት። ማንኛውም ኃላፊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ከዚህ የተለየ ሃሳብ ያለው አይመስለኝም። ካስፈለገም እኮ አዲስ መንግስት የሚቋቋምበት መንገድንም ማየት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚሆነው ደግኖ አገርን ለማዳን ሲባል ነው። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ጥቂቶቹ ነጮች በብዙሃኑ ጥቁሮች ላይ በጣም ብዙ ወንጀሎችን ሰርተው የነበረ ቢሆንም አገርን ለማዳን ሲባል ደቡብ አፍሪካን እንደ አገር ለማስቀጠል ሲባል ሁላችንም የምናውቀውን መፍትሔ (እርቅና ብሔራዊ መግባባት) ወሰዱ። አሁን ደቡብ አፍሪካዊያን ሁሉም ችግሮቻቸው ባይፈታም እንደ አገር ለመቀጠል ግን የሚቸገሩበት ነገር የለም። እኛ ግን አሁን የምናየው ነገር እንደ አገር ለመቀጠል ስጋት የሚያሳድር ሆኖ ነው የምናየው።


ሰንደቅ፡- እርስዎን ጨምሮ በርካታ ምሁራን እና ፖለቲከኞች አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አሳታፊ ውይይትና እርቅ ቢካሄድ መፍትሔ እንደሚመጣ ትገልጻላችሁ። ኢህአዴግ ለዚህ አይነት የመፍትሔ ሃሳብ ጥያቄ በሩን ይከፍታል ብለው ያስባሉ?


አቶ ነጋሽ፡- ለበርካታ ዓመታት የሄደበትን አቅጣጫ ስናየው ይህ መንግስት ለተለየ ሃሳብ በሩን ከፍቶ ይቀበላል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ግን ይህ ጉዳይ ዝም ብሎ ጉዳይ ሳይሆን በአንድ በኩል የአገር የህልውና ጉዳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የእነሱም የህልውና ጉዳይ ስለሆነ እነዚህን ሁሉ ግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል። በመካከላቸው ችግር ሊኖር ይችላል ሆኖም ግን መጨረሻ ላይ ሁሉም ወደ አእምሮው መመለስ ይኖርበታል። ወደ አእምሮው ከተመለሰ ብቻ ነው መፍትሔ የምናገኘው። ከዚህ አንጻር ስታየው ነገሩ ተስፋ አስቆራጭ መስሎ ይታያል። ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስቡ ከሆነ እና የዚህች አገር ህልውና ካሳሰባቸው ወይም ተጠያቂነት ከታያቸው የባህሪ ለውጥ አድርገው በዚህኛው ሃሳብ ይስማማሉ ብዬ ነው የማስበው። ለዚህ ደግሞ ቀደም ብዬ የነገርኩህ የደቡብ አፍሪካ ታሪክ ምሳሌ ነው። በአገራችንም እኮ ‹‹ውሾን ያነሳ ውሾ›› ይባል የለ? የአገራን ህዝብ በእውነት መሃሪ ስለሆነ ወደ እርቅ መምጣት ብቸኛ መፍትሔ ሆኖ ነው የሚታየኝ።


ሰንደቅ፡- ኢህአዴግን ላለፉት 27 ዓመታት በቅርብም በሩቅም እንደሚያውቅ ምሁር ይህን ሃሳብ ለመቀበል የሚያስችል የባህሪ ለውጥ አይተውበታል?


አቶ ነጋሽ፡- አጠቃላይ ሁኔታውንና ፓርቲውን እንደ አጠቃላይ ስታየው ለውጥ ያለ አይመስልም። ግን አሁን በቅርብ የታዩት አንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ የግንባሩ ፓርቲ አካል የሆኑ አንዳንድ ፓርቲዎች አቅጣጫው ትክክል እንዳልሆነ ሲናገሩ ታያለህ። በተለይ አሁን የኦህዴድ አባላት የተባሉት በፓርላማ ምርጫ ላይ ለየት ብለው መገኘታቸው የሚያሳየው ከእነሱ መካከል አንዳንዶች ወይም በርከት ያሉት መንገዱ ትክክል አለመሆኑን የመረዳት ነገር ይታያል። ፓርቲው ራሱ (ኢህአዴግ) ስህተት ሰርተናል ብሎ ማመኑ ቀላል ነገር አይደለም እኮ። ይህንን እስካመኑ ድረስ ሊቀየሩ ይችላሉ የሚል ግምት ነው ያለኝ። ይህን ስል ግን ነገሩ ቀላል አይደለም አሳሳቢ ነው።


እኔም እነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ ቀይረው አገራችን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሄድ ያደርጋ ወይ የሚል ጥያቄ ነበረኝ። እንግዲህ በግንባሩ ዋና መሪ ህወሓት የሚባለው የአስተዳደር ለውጥ አድርጓል፤ አንዳንዶቹንም የማስወገድ ነገር አድርጓል፤ በኦህዴድ በኩልም ትን…ሽ ለውጥ ነገር አለ። እነዚህ ነገሮች ናቸው ተስፋ የሚሠጡት እንጂ ይህን ጥያቄ ለመመለስ እርግጠኛ ሆኖ በፓርቲው ተማምኖ መናገር ከባድ ነው።


ሰንደቅ፡- የጥያቄያችንን ይዘት ከወቅታዊ ጉዳይ ወጣ እናድርግና ስለ መሰረቱት ኢሰመጉ ታሪካዊ ዳራ እና አሁን ስላለበት ደረጃ አጠር አድርገው ይንገሩን?


አቶ ነጋሽ፡- ድርጅቱ እስካሁን ድረስ እንዲቆይ ያደረገው ከልባቸው ለድርጅቱ ያስቡ የነበረ ግለሰቦች ናቸው ማለት እችላለሁ። ኢሰመጉ ከምስረታው ጀምሮ መስራቾቹ ለምሳሌ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከድርጅቱ ጥቅም ፈልገው አይደለም። የሚገርመው ፕሮፌሰር መስፍን ለድርጅቱ መፈጠር ምክንያት ከመሆናቸውም ሌላ ለአገሪቱ የሚበጀውን ነገር ከመናገር ወደኋላ ብለው አያውቁም። የግል ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ ከመንግስት ጋር የሚያጋጫቸውን እውነታ በአደባባይ መናገር አይፈልጉም ነበር። ምክንያቱም ጥቅም ፈላጊ የሆነ ሰው በአደባባይ እንደዛ አይናገርም። ከእሳቸው በተጨማሪ ሌሎቻችንም የድርጅቱ አባል የሆንን ሰዎች ከድርጅቱ ጥቅም ለማግኘት የመጣን አይደለን። ለምሳሌ እኔን ብትወስደኝ በግል ህይወቴ ባለቤቴ በህይወት ስለሌለች ብቻዬን የምኖር ሰው ብሆንም አንድ ቀን ችግር ቢደርስብኝ ማንም የሚሟገትልኝ እንደሌለ እያወኩኝ ነው እስካሁን ድረስ ስሟገት የነበረው።


ቅድም እንደነገርኩህ ሰመጉ እስካሁን ሊቀጥል ያስቻሉት የህዝብ መብት ከተከበረ ብቻ ነው። አገሪቱ ሰላም አግኝታ የምትኖረው የሚለውን አስተምህሮ አንግበው የሚንቀሳሱ ሰዎች ናቸው። ከምስረታው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከኪሳቸው እያወጡ ነበር ድርጅቱ እንዲቆም ያደረጉት። እኛ የበኩላችንን በማድረግ እንዲቀጥል አደረግነው እንጂ ፈንድ የተገኘው በኋላ ነው። አሁን ያሉትን አመራሮች ብትመለከት አቶ ቁምላቸውም ሆነ አቶ አመሃ መኮንን ጠበቆች ሲሆኑ ከኪሳቸው በማውጣት ጭምር ድርጅቱ እንዲቀጥል ያደረጉት ዓላማውን ስለሚያምኑበት ነው። ሌሎችም አሉ፤ የድርጅቱን ህልውና ሊያስቀጥሉ የሚደክሙ። ይህ ባይሆን ኖሮ እንደ መንግስት አዋጅ ቢሆን ሊቀጥልም አይችልም ነበር። ምንም እንኳን የመንግስት ተጽእኖው ቢኖርም እንደነዚህ አይነት ሰዎች ለዓላማው የታመኑ ሰዎች እስካሉ ድረስ ድርጅቱ ህልውናው ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ።


ሰንደቅ፡- መንግስት ሰመጉን ጫና እያሳደረበት መቆየቱን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ድርጅቱን እንደማይፈልገው የሚገልጽበት ምክንያቶች አሉ። መንግስትን ጠልፎ ለመጣል የፖለቲካ ተሳትፎ አለው የሚል ክስ ይቀርባል። ለማስረጃነትም የድርጅቱ መስራች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በ1997 ዓ.ም ምርጫ ከቅንጅት ጋር ተሰልፈው ኢህአዴግን እየተቃወሙ መገኘታቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ሆን ተብለው መንግስትን የሚያጋልጡ ናቸው ይባላል። በዚህ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?


አቶ ነጋሽ፡- ሰመጉ አባሎቼ ፖለቲካ ውስጥ አይግቡ አይልም። ነገር ግን አባሎቹ የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኛ መሆናቸውን ሲያረጋግጥ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል። ፕሮፌሰር መስፍንም የድርጅቱን አቋም ያውቁ ስለነበረ በምርጫው ወቅት ከሰመጉ ወጥተው ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ለምን እዚያ ውስጥ ገቡ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለባቸው ራሳቸው ናቸው። ነገር ግን ፕሮፌሰር መስፍን አስተማሪዬም ስለነበሩ በቅርብ አውቃቸዋለሁ። የሚመስለኝ ወደ ፖለቲካው የገቡት የፖለቲካው መስመር ጥሩ እንዲሆን ለማደፋፈር ይሆናል እንጂ እሳቸው ስልጣን ለመያዝ ፈልገው አይደለም። መንግስት በወቅቱ የነበሩትን ፓርቲዎች ያዳክማቸው ስለነበር ቁጭት ይዟቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ተጠናክረው እንዲወጡ በሩን ለማሳየት በድፍረት ገቡበት እንጂ ስልጣን ፈልገው አይደለም። የስልጣን ፍላጎት ያላቸው ሰውም አይደሉም፤ እኔ እስከማውቃቸው ድረስ። በነገራችን ላይ በደርግ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን እንዲወስዱም ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ሰምቻለሁ። ለዚህ ነው በ1997 ምርጫ ወደ ፖለቲካው ተሳትፎ የገቡት ስልጣን ፈልገው ወይም ስልጣል ላይ ያለውን መንግስት ጠልፎ ለመጣል አስተሳሰብ ኖሯቸው አይደለም የምለው። በምርጫውም አልተወዳደሩም። ፕሮፌሰር በፖለቲካ ድርጅቱ ውስጥ ባይገቡ ጥሩ ነበር ከገቡ በኋላ ደግሞ ከእኛ ጋር ግንኙነት የላቸውም።


ሪፖርቶቹን በተመለከተ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገን ነው የምናወጣው። አንድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጸመ ተብሎ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ መጀመሪያ የሚደረገው ቦታው ላይ ጥናት ሲካሄድ የአካባቢው ሰው እንዲገኝ በማድረግ ነው ጥናቱ የሚጀመረው። በጥናቱ ሪፖርት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተካሂዶበት ከተጠና እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከተመለከተው በኋላ የህግ ሰዎች እንዲያዩት ይደረጋል። በዚህ ምክንያት ነው ድርጅቱ ህልውናውን ጠብቆ ሊቆይ የቻለው። ምክንያቱም በምናወጣቸው ሪፖርቶች መንግስት አንድም ቀን በስህተት ስሜን አጥፍቷል ብሎ አይወቅስም ስህተትም ተገኝቶብን አያውቅም። እሱ ከሰመጉ ጋር ያለው ችግር አለመፈለግ ነው፤ ሰመጉን አይፈልገውም። ለዚህ ደግሞ ችግሩ ሰመጉ ጠንካራ እና ሀይለኛ ስለሆነ ጥንቃቄ እና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ያጠናውን ሪፖርት ይዞ ሲጮኸ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰሚ ስለሚያገኝ መንግስትን ያሳጣዋል።


ሰንደቅ፡- ሰመጉ አሁንም ሆነ ቀደም ሲል የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በመንግስት መዋቅር ተፈጸሙ የሚባሉ የመብት ጥሰቶችን ብቻ እንጂ በግለሰብ እና በግል ድርጅት ደረጃ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን አያጣራም። ይህ ደግሞ ድርጅቱ ዓላማው የፖለቲካ ወገንተኝነትን ይዞ በመንግስት ላይ ጫና ማሳደር ነው የሚሉ አሉና ይህንስ እንዴት ያዩታል?


አቶ ነጋሽ፡- አባባሉ በአብዛኛው ትክክል ነው። ነገር ግን ይህ ለምን ሆነ ያልን እንደሆነ በቂ የሰው ሀይል ስለሌለን ጥናት የምናካሂደውና መረጃ የምንሰበስበው ጥያቄውን መጀመሪያ ከሚመጣው በደል ደረሰብን ከሚሉ ወገኖች ነው። ከዚያ በኋላ ነው መርማሪዎቻችንን ወደ ስፍራው በመላክ ወደ ጥናት የሚገባው። ብዙ ጊዜ አቤት የሚባልባቸው ጥያቄዎችም መንግስትን የሚመለከቱ ስለሆኑ እንጂ የግል ድርጅት ይህን ያህል በደል አደረሰብኝ ብሎ ጥያቄ የሚቀርብ የለም። ያ ቢቀርብልን ግን በደል ያደረሰውን ድርጅት በደሉን አጣርቶ ጥናት ሰርቶ ሪፖርት ለማቅረብ ሰመጉ ችግር የለበትም።


በአሰራራችን ላይ በአንድ ወቅት ጥያቄ አንስተን ለውይይት አቅርበነው ነበር። ምን ማለት ነው ሁል ጊዜ የሚቀርብልንን ጥያቄ ብቻ ተከትለን ጥናት ከማካሄድ እኛስ ቀድመን ችግር ያለበትን አካባቢ ለይተን ለምንወደው ጥናት አንገባም የሚል ነበር። ሃሳቡን ሁላችንም ብንቀበለውም ትልቁ ችግር የነበረው የአቅም ጉዳይ በመሆኑ በቀደመው አሰራር መቀጠልን በብቸኛ አማራጭነት ወሰድነው። ለዚህ ደግሞ በተለይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሚመለከተው አዋጅ 561/2001 እኛ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በእውነቱ በጣም ከፍተኛ ነው። የበጀት ችግር ስለገጠመንም ከነበሩን 12 ጽ/ቤቶች ዘጠኙን ዘግተን በሶስት ክልሎች ብቻ እንድንወሰን አድርጎናል። ሌላው ቀርቶ ካለን የቆየ ገንዘብ ላይ ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ከባንክ እንዳናንቀሳቅስ ታግዶብናል። እስካሁን የቆየነውም አንድ አነስተኛ ህንጻ አለችን ያችን በማከራየት ከኪራይ በሚገኝ ገቢ ነው።


ሰንደቅ፡- ቀደም ባሉት የውይይታችን ክፍሎች ላይ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የሚጥል አለመረጋጋት መፈጠሩን ገልጸውልናል። የተፈጠረው ቀውስ ደግሞ ማንነት ላይ ያተኮረ እየሆነ መጥቷል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ደረጃ በማንነት ላይ መሰረት አድርገን ከመጋጨታችን ይልቅ በአንድ ላይ እንድንኖር የሚደርግ የታሪክ ተሞክሮ አገሪቱ የላትም?


አቶ ነጋሽ፡- የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ስናይ የአስተዳደር አካሄዳችን በእውነቱ አዲስ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ተዋህዳ ያለቀች አገር አይደለችም። ውህደቷን አጼ ቴዎድሮስ ጀምረው አጼ ዮሃንስም ሞክረው ነበር። በተለይ አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያን አዲስ አስተዳደር ስርዓት በመመስረት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። አጼ ምኒልክ የመሰረቱት አዲስ የአስተዳደር ስርዓት አሁን ፌዴራል አስተዳደር እንደሚባለው አይነት ነበር። በኢትዮጵያ ምድር የሚኖር አገረ ገዥ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ ለማዕከላዊ መንግስት ግብር እስከከፈለ ድረስ በውስጥ አስተዳደሩ ላይ ጣልቃ አይገቡበትም ነበር። ይህን ተቀብሎ በሰላም መገበር አልፈልግም ያለውን ደግሞ በየትኛውም አገር እንደሚደረገው እሳቸውም በሀይል ለማስገበር ሞክረዋል ተሳክቶላቸዋልም።


ይህ ሂደት ኢትጵያዊነትን እያዳበረ ነበር ሄደው። ምክንያቱም ከመሃል አገር ወታደር፣ ነጋዎች፣ አስተዳዳሪዎች እና የተለያዩ የመንግስት መዋቅር ያሉ ሰዎች ወደ ሁሉም አካባቢ ይሄዳሉ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን እንዲዳብር አንድ ምክንያት ሆነ። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ ባህሪ፣ ባህል፣ አስተሳሰብ እና በኢትጵያዊነት ላይ የጸና አስተሳሰብ አላቸው። በቅርቡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የጻፉትን መጽሃፍ አይተኸው ከሆነ ስለ ኦሮሞ እና አማራ አንድነት ጥሩ አድርገው ነው የገለጹት።


የኢትዮጵያ ህዝብ በእርግጥ በአንድ ቋንቋ ይናገር አይባልም። በአንድ ቋንቋ መናገርም ግጭት እንዳይፈጠር ዋስትና ይሆናል ማለት እንዳልሆነ በሶማሊያ የተፈጠረውን አይተናል። በቋንቋ ብንለያይም እኛ ኢትዮጵያዊያን በደም እና በባህል አንድ የሚያደርጉን የኢትዮጵያዊነት ስሜት አለን። ቀደም ባሉት ዘመናት የነበረው ኢትጵያዊነት ስሜትም ጠንካራ ነበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ፖለቲከኞች ነገሩ መልኩን እንዲቀይር ያደረጉት። እነዚህ ሰዎች ስልጣን ሲይዙም ያንን የሚለያይ ነገር እያጠናከሩ መጡ። ያ ደግሞ ልዩነትን እያሰፋ መጣ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነት ስሜቱና ታሪኩ ዘመናትን የተሻገረ ነው። አሁን የተፈጠረው ማንነትን መሰረት ያደረገ ልዩነት ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ልዩነት ለአገር እንደማይጠቅም አዝማሚያው ጥሩ እንዳልሆነ ቀደም ብዬ ደጋግሜ ተናግሬ ነበር። ግን የፈራሁት ደረሰ።


አሁንም ቢሆን መሪው ድርጅት በጎ ፈቃደኝነቱ ከታከለበት ይህን የልዩነት ችግር ተቀርፎ ወደነበረበት የአገር አንድነት ስሜት መመለስ የሚቻልበት ጊዜ የረፈደ አይመስለኝም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1276 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1158 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us