ከበርበራ ወደብ በስተጀርባ፤ ግብፅ እና ኳታር ምን እያሴሩ ነው?

Wednesday, 21 March 2018 13:35

 

 

 

የኢትዮጵያ መንግስት በበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ መያዙን ለመገናኛ ብዙሃን ጆሮ ከበቃ በኋላ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች እንቅልፍ አጥተዋል። የ19 በመቶውን ድርሻ ለማስከበር ለአንድ ዓመት የዘለቀ ድርድር ማድረጓንና ድርድሩ በመሳካቱም ወጪና ገቢ ንግዷን የምታስናግድበት ተጨማሪ ወደብ ማግኘቷን ኢትዮጵያ አስታውቃለች። በስምምነቱም መሰረት የዲፒ ወርልድ የቀድሞ ድርሻ 65 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ተቀንሶ ለኢትዮጵያ መሸጡን፣ የሶማሊያላንድ መንግሥት በበኩሉ የ30 በመቶ ከወደቡ ድርሻ መያዙ ይፋ ተደርጓል።


ወደቡን ዲፒ ወርልድ የሚያስተዳድረው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከባለድርሻነትና የወደብ ተጠቃሚነት በተጨማሪ፣ በበርበራ ኮሪዶር የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ያከናውናል። ይህም የአገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያቀላጥፈው ሦስቱ አካላት በስምምነታቸው ወቅት አስታውቀዋል። ዲፒ ወርልድ ከወዲሁ ተጨማሪ የመርከብ መልህቅ መጣያ ግንባታ ሥራ መጀመሩም በስምምነቱ ወቅት ይፋ ተደርጓል።


የሶስትዮሹን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ መንግስት፣ የግዛቴ አካል ከሆነውና ራሱን ነፃ መንግሥት ብሎ ከሚጠራ አካል ጋር የተደረገ ስምምነት ሉዐላዊነቴን ተጋፍቷል ሲል ቅሬታ አቅርቧል። በዚህም ሳይገታ፣ የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ ከዱባዩ ዲፒ ወርልድ ኩባንያ እና ከሶማሊያላንድ ጋር ያደረገችው የበርበራ ወደብ የባለድርሻነት ስምምነት ውድቅ እንዲደረግ ለዓረብ ሊግ ጥሪ ማቅረቡ ተሰምቷል።


በኢትዮጵያ በኩል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊነትን የሚዳፈርም ሆነ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ስምምነት ሳይሆን፣ ሙሉ በሙሉ በኢኮኖሚና በንግድ ላይ ያተኮረ የወደብ ልማትና ተጠቃሚነት ስምምነት ማድረጉን ደጋግሞ ሲገልፅ እንደነበረ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የሞቃዲሾ መንግሥት ግን በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን ማብራርያም ሆነ ማስተባበያ ካለመቀበሉም በላይ፣ የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማቅረብ ስምምነቱን ውድቅ መደረጉን ይፋ አድርጓል።


በሶማሊያ መንግሥት የቀረበበትን ተቃውሞ በማስመልከት የኢትዮጵያ መንግሥት በትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሰሞኑን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የመንግስታቸውን አቋም ሲያስቀምጡ፣ “የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ፖለቲካዊ አጀንዳ ውስጥ የመግባት አካሄድ አልተከተልም” ብለዋል። አያይዘውም፣ ‹‹የሶማሊያ መንግስትና ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው። ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መስዋዕትነት በመክፈል፣ ደሙን በማፍሰስ አብሮ የታገለ ነው፤›› በማለት መንግስታቸው በሶማሊያ ሕዝብና መንግስት ጀርባ ሊንቀሳቀስ እንደማይችል ሚኒስትሩ አሻሚ ባልሆነ መልኩ ገልጸዋል።


የሶማሊያ መንግስት የተቃውሞ ድምጹን ማሰማቱ መብቱ መሆኑን የሚያከራክር አይደለም። ሆኖም በሶስቱ ሀገሮች መካከል የተደረገው ስምምነት ተከትሎ ጉዳዩን ለመቀልበስ የተንቀሳቀሰበት መንገድ ግን ከበስተጀርባ ያሉ ኃይሎች ፍላጎት መሆኑን ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ይኸውም፣ የበርበራ ወደብ የዓረብ ሊግ እንዲገባበት ጥሪ ከማቅረቡ በላይ፤ በሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ) የተመራ ልዑክ ወደ ኳታር በዚህ ጉዳይ ለመወያየት ማቅናቱም ተዘግቧል።


በዚህ ጽሁፍ የግብፅ ያልተሳካ ፍላጎቶች እና የኳታር ፍላጎቶች ምንድን ናቸው የሚለውን በወፍ በረር ለማየት ይሞክራል።

 

ከላይ ከሰፈረው ሃተታ መነሻ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ለሰንደቅ እንደገለጹት፣ “በኢትዮጵያ መንግስት፣ በዲፒ ወርልድ እና በሶማሊያላንድ መንግሥት መካከል የበርበራ ወደብን ለመጠቀም የተፈረመው ስምምነት በተለየ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የተደረሰ አይደለም። በኢትዮጵያ በኩል በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንድ እና ሁለት ላይ በግልፅ የሶማሊያላንድ የበርበራ ወደብን በመጠቀም የወጪና የገቢ ንግዳችን ለመጨመር እንደምንሰራ አስቀምጠናል። ይህ የእቅድ ሰነድ ፐብሊክ ዶክመንት ስለሆነ ማየት ይቻላል። በወዳጅ ሀገሮቻችንም ይታወቃል። ከዚህም በላይ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ከሶማሊያላንድ ጋር የበርበራ ወደብ አጠቃቀም ስምምነት አድርገን በበርበራ ወደብ የመብራት ኃይል እቃዎችን ስናስገባ ነበር። የእርዳታ ስንዴም በበርበራ ወደብ ነው የምናስገባው። ስለዚህም ፍላጎታችን ለእድገታችን ያሉንን አማራጮች በመጠቀም ሕዝባችን መጥቀም ነው። የተለየ ፍላጎት የለንም” ብለዋል።


የሶማሊያ ፓርላማ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዴት ነው የምታዩት ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ “የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ ምንም ይሁን ምንም እንደሀገር የሰጡትን ውሳኔ እናከብራለን። ሆኖም መታወቅ ያለበት የሶማሊያ ፓርላማ አብዛኛው ዲያስፖራ ናቸው። ኑሯቸውም በውጭ ሀገራት ነው። በሞቃድሾ መንደር ውስጥ የሚኖሩ አይደሉም። በሞቃድሾ የሚኖረው የሶማሊያ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት አሳምረው ያውቀዋል። በተለይ ከእ.ኤ.አ. 1991 በኋላ ሶማሊያ በገጠማት የመንግስት መፍረስ አደጋ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የተለየ ቦታ እንዳለቸው የሞቃድሾ ነዋሪዎችን መጠየቅ በቂ ነው። ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላም የሕይወት መስዋዕትነት የከፈልን የክፉ ቀናቸው ደራሽ ሕዝብና መንግስት መሆናችንን በአደባባይ የሚመሰክሩት ነው። በግዛታችንም በመቶሺ የሚቆጠሩ የሶማሊያ ዜጎችን አቅፈን፣ ደግፈን እየኖር ነው። የሶማሊያ ዲያስፖራ ሁሉም አይደሉም፣ ቀላል ቁጥር ያልሆኑ በግብፅና በኳታር ፍላጎቶች እንደሚሽከረከሩ እናውቃለን” ብለዋል።


አያይዘውም፤ መሬት ያለውን እውነታ ለማስቀመጥ ከተፈለገም የሶማሊያ ፓርላማ በሶማሊያላንድ ግዛት ውስጥ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የለውም። ምንም አይነት ቁጥጥር የላቸውም፣ የሶስተኛ ወገኖችን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ መግለጫ እያወጡ ነው የሚገኙት። እውነቱ እነሱም አይጠፋቸውም። ሶማሊያላንድ ከሃያ ዓመት በፊት ጀምሮ እራሳቸውን ችለው እያስተዳደሩ ናቸው፤ እውቅና ባያገኙም። ሰላማዊ ምርጫ እያደረጉ የሚያስተዳድራቸውን መንግስት እየመሰረቱ፣ እየኖሩ ናቸው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።


“የሶማሊያ መንግስት በኳታር ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት እንደሆነ እንገነዘባለን። ኳታር ከዩናይትድ ዓረብ ኤሜሬት ጋር የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንዳሉ የሚታወቅ ነው። በተለይ በንግድ ከሚያደርጉት ፉክክርና መጠላለፍ በላይ በሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ላይ ያላቸው አቋም እስከመጠፋፋት የሚያደርሳቸው ነው። ኳታር ከዩናይትድ አረብ በተጨማሪ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከግብፅ ከባሕሪን ጋር ከፍተኛ የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ ትገኛለች። ከዚህ አንፃር ስትመለከተው ጉዳዩ የሶማሊያላንድ ወደብ ከመጠቀም ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ቀውስ በቀንዱ ሀገሮች መካከል እየገባ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው” የበርበራ ወደብ ጉዳይ ለዓረብ ሊግ የቀረበበት መንገድ በግብፅ ግፊት እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ሶማሊያዊያን የዓረብ ነገድ አይደሉም፡፡ ግብፅ በናይል ውሃ ላይ ያላትን ፍላጎት ለማስጠበቅ፣ ሶማሊያን የአረብ ሊግ አባል ማድረጓ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁንም የኢትዮጵያን እድገት ለማደናቀፍ ግብፅ የዘየደችው ሴራ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በርበራ ወደብን ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበው ውድቅ እንደተደረገባቸው የሚታወስ ነው ሲሉም አክለዋል።

 

ግብፅ በሶማሊያላንድ


እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 05 እስከ 08 ቀን 2016 አስራ አራት አባላት ያለው የግብፅ ልዑካን ቡድን በሶማሊያላንድ ጉብኝት ማድረጉ የሚታወስ ነው። በልዑካኑ ውስጥ ተካተው የነበሩት፣ የባህር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የወታደራዊ ደህንነት እና የመረጃ ተቋም ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲሆኑ በወቅቱ ልዑካን የመሩት በኢትዮጵያ የቀድሞ የግብፅ አምባሳደር የነበሩት ሞሃመድ እንድሪስ ናቸው። በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስቴር በመሆን እያገለገሉ ነበር።


የግብፅ ልዑካን በሶማሊያላንድ ዋና ከተማ በሐርጌሳ ከሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ጋር ስብሰባም አድርገዋል። የግብፅ ልዑካን ቡድን በአጀንዳነት በርካታ ጉዳዮች አቅርቦ ተወያይቷል። ከቀረቡት የውይይት አጀንዳዎች መካከል፤ በንግድና በትምህርት ትብብር ማጠናከር፤ ግብፅ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመቀናጀት በየመን ላይ ለከፈቱት ወታደራዊ ዘመቻ የበርበራ ኤርፖርትን ለግብፅ አየር ኃይል የስምሪት ማዕከል እንዲሆን መፍቀድ፤ ለስምሪቱ ማዕከል የሚሆን የመሬት አቅርቦት እንዲመቻች ፈቃድ ማግኘት ናቸው።


እንዲሁም የበርበራ የኤርፖርት አጠቃቀም ውልና ፈቃድ እንዲዘጋጅና እንዲሁም በግብፅ መንግስት ድጋፍ እና ባለሙያዎች እገዛ የበርበራ ወደብን ለማስፋፋትና ለማደስ፤ በበርበራ ወደብ ለግብፅ አየር ኃይል ማዕከል ማዘጋጀት የሚሉ ነጥቦች በውይይቱ ተነስተዋል። በበተጨማሪም የቱርክ መንግስት የተዋሃደች ሶማሊያን ለመመስረት የያዘውን የአደራዳሪነት ሚና ግብፅ እንድትረከበው ድጋፍ ጠይቀዋል።


ሌላው በወቅቱ ትልቅ አጀንዳ ተደርጎ የቀረበው፣ በሶማሊያ ውስጥ “ህቡዕ አጀንዳ” ካላቸው እንደኢትዮጵያ ከመሳሰሉ ሀገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነቶችና ትብብሮችን ሶማሊ-ላንድ እንድታጤነው የሚጠይቅ ነበር። ከላይ በሰፈሩት አጀንዳዎች ሶማሊያላንድ የምትስማማ ከሆነ በግብፅ በኩል የቀረበው በሁሉም ዘርፍ ሶማሊያላንድን ለመደገፍ እና የውጭ የትምህርት ዕድል ማቅረብ፣ በተለያዩ የሶማሊያላንድ አካባቢዎች የሕክምና ዶክተሮችን ለአገልግሎት እንዲሰማሩ መፍቀድን ያካትታል።


በወቅቱ በነበሩት የሶማሊያላንድ ፕሬዝደንት የተሰጡት ምላሾች በግብፅ ልዑካን የተጠበቁ አልነበሩም። ይህም ሲባል ፕሬዝደንቱ፤ በግብፅ በኩል ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል ሕዝባዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መኖራቸውን በውይይቱ ላይ በማያወላዳ መንገድ አስቀምጠዋል። እነሱም፣ የግብፅ አየር ኃይል እና ባህር ኃይል በበርበራ ወደብ ላይ የስምሪት ማዕከል እንዲኖራቸው መፍቀድን በተመለከተ ወደቡ የህዝብ ሃብት በመሆኑ እሳቸው ብቻቸውን የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። በሌሎች አጀንዳዎች በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፎች ለመተባበር በቀረቡት ላይ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፈቃደኝነት አስታውቀዋል። ከሶማሊያ መንግስት ጋር ለማዋሃድ ያቀረቡትን ጥያቄ እንደማይቀበሉት፣ ፕሬዝደንቱ አቋማችውን ግልፅ አድርገውላቸዋል።

 

ግብፅ በሞቃድሾ-ሶማሊያ


የግብፅ ልዑካን ቡድን ከቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሀሙድ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። የግብፅ ልዑካን በሞቃድሾ ባደረገው ውይይት ለየት ያለ አጀንዳ ያቀረበው፣ የኢትዮጵያ መንግስት በናይል ወንዝ ላይ ያልተመጣጠነ የውሃ አጠቃቀም እየተከተለ ነው፣ በሚል መነሻ ውይይቱ መጋበዙ ነበር።


የኢትዮጵያ መንግስት ያልተመጣጠነ የናይል ውሃ አጠቃቀምን ለመግታት በግብፅ ልዑካን የቀረበ ምክረ ሃሳብ ነበር። ይኸውም፣ የሶማሊያና የግብፅ ብሔራዊ ጥቅሞችን በጋራ በማስተሳሰር የሶማሊያ የፀጥታ ተቋማትን የመከላከያ እና የፖሊስ ኃይሎችን በማጠናከር አቅማቸውን ማብቃት፤ የተቋማቱን የማሰልጠኛ አካዳሚዎችን ማደስ፣ ማስፋፋት እና በሚሰጡ ስልጠናዎች የግብፅ ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት እንዲሳተፉ ማድረግ፤ እንዲሁም ግብፅ ለምታቀርበው ድጋፍ መነሻ የሚሆን በተቋሞቹ ዙሪያ የቅድመ ጥናትና ዳሰሳ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከግብፅ እንደሚመጡ ገልጸው ነበር።


ሌላው በተመሳሳይ መልኩ ለሶማሊያላንድ ያቀረቡትን ጥያቄ ለሶማሊያም አቅርበው ነበር። ይኸውም፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራውን በመየን ሕዝቦች ላይ የተከፈተውን ጦርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የግብፅ አየር ኃይል የሶማሊያ አየር ኃይል ዋና ማዕከል የነበረውን የበለዶግሌ ኤርፖርት በመጠቀም ጥቃት እንዲፈጽም ለውይይት አቅርበዋል። አጠቃቀሙን በተመለከተም የበለዶግሌ ኤርፖርትን በማደስ እና በኪራይ በሚሰጥ ውል ለመጠቀም የልዑካኑ ቡድን በስብሰባው ላይ ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ለተቋማቱ የሚያስፈልጉ ወታደራዊ አልበሳት፣ የቴክኒክ እና የጦር መሳሪያዎችን በግብፅ በኩል ለማቅረብ ለሶማሊያው ፕሬዚደንት እንዳነሱላቸው በወቅቱ ተገልጧል።


የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሀሙድ የግብፅ ልዑካን ፍላጎቶችን ካደመጡ በኋላ፤ ያልተጠበቀ ምላሽ በጉዳዩ ላይ መስጠታቸው የሚታወስ ነው። ይኸውም፣ የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝደንት በግብፅ ልዑካን የቀረበውን የወታደራዊ፣ የአየር ኃይልና የፖሊስ ተቋማትን የአቅም ግንባታ፣ የማሰልጠኛ ተቋማት እድሳት፣ የወታደራዊ ባለሙያዎች ጉብኝትና የቅድመ ዳሰሳ ጥናት፤ ለግብፅ አየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ የሚሆን የጦር ሰፈር ውል ጥያቄዎችን በተመለከተ እንደማይቀበሉ እና ፈቃደኛ አለመሆናቸውን፤ ለልዑካኑ መግለፃቸውን በወቅቱ ይፋ አድርገዋል። አያይዘውም፣ ከወታደራዊ ጉዳዮች በመለስ ባሉ የተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን በወቅቱ የሶማሊያ ቤተመንግስት የመረጃ ማዕከል መግለጽ የሚታወስ ነው።


የበርበራ ወደብን ለማልማት 442 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚደረግ ሲታወቅ፣ የሶማሊያላንድ መንግሥትም ለ30 ዓመታት የሚቆይ ውል መፈራረሙም ይታወቃል። በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ምዕራፍ የግንባታ ሒደት ስምምነቱ ከተደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚጀመር፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም እንደሚጠናቀቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1552 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 147 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us