“ኢህአዴግ የተሰው ጓዶቹ ታሪክ ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለገ የግድ ባህሪውን መለወጥ አለበት”

Wednesday, 28 March 2018 13:01

“ኢህአዴግ የተሰው ጓዶቹ ታሪክ ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለገ የግድ ባህሪውን መለወጥ አለበት”

ዶክተር ፍሰሃ አስፋው

የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር

በይርጋ አበበ


ዶክተር ፍሰሃ አስፋው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በነበረው ስርዓት በኢትዮጵያ ብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት እና በ1987 ዓ.ም በጸደቀው ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባልነት ተሳትፈዋል። ‹‹የኢትዮጵያን ብሔረሰብ የሚገልጽ መጽሃፍ›› እና ‹‹ያለፍኩበት›› የሚሉ ሁለት መጽሃፎችን ከእውቀት ጓዳቸው ቀድተው ለአንባቢያን ያካፈሉ ምሁር ናቸው። በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ እና በመፍትሔው ላይ ያተኮረ ቃለ ምልልስ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር አከናውነዋል። የቃለ ምልልሱ ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች ቀርቧል።


ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?


ዶክተር ፍሰሃ፡- እንግዲህ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በተለይም ባለፉት አራት እና አምስት ወራት ውስጥ በተለየ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው። ታማለች እንዳንል ከታመመች ትንሽ ቆይታለች፤ ጠንቶባታል እንዳንልም ደግሞ የሚካሄደው ሂደት የወደፊቱን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ያመጣል የሚል እምነትም አለኝ። ስለዚህ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሁኔታ ከሁለት አንጻር ነው ማየት የምፈልገው። በአንድ በኩል ወደ በጎ እያመራች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በጎውን መንገድ የሚያደናቅፉ አንዳንድ ጭምጭምታዎች ወይም እይታዎች እየታዩ ነው ያሉት።


ሰንደቅ፡- የሚታየዎት በጎ መንገድ ምንድን ነው? በጎውን የሚያደናቅፈውስ?


ዶክተር ፍሰሃ፡- በጎ ብለን የምንወስደው እንደምናየው አሁን ኢህአዴግ ራሱ ችግር መኖሩን ማመኑ እና መናገሩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢትዮጵያ ችግር አለ የችግሩ መፍትሔ አካል ለመሆን ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ብለዋል። እንዲህ ሲባል ግን እሳቸው ብቻ የችግሩ ዋና መንስዔ ናቸው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን ያደረጉት ነገር የለምና። ግን ከአነጋገራቸው እንደምንረዳው ለችግሩ መፍትሔ ለመሆን እኔ ስልጣን ለቅቄያለሁ ማለታቸው ይህ አንዱ የበጎ መንገድ ጅማሮ ነው። ኢህአዴግ ወልዶ ያሳደጋቸው ልጆቹ አሻፈረኝ ብለው በያለበት አስጨንቀውታል። ወጣቶቹ ያስጨነቁበትን ምክንያትና የጫናውን ግፊት መጠኑን ኢህአዴግ ተገንዝቧል ማለት ነው። ይህን እርምጃ እኔ በበጎ ነው የማየው። ምክንያቱም የለውጥ ሂደት ስለሆነ። ኢህአዴግም ሆኖለት ከተለወጠ ‹እለወጣለሁ› ብሏል።
ክፉ የሚባለው ደግሞ ኢህአዴግ አሁንም የስልጣን ሱሰኛ መሆኑ እና የህዝብን ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ በአገሪቱ የተለያዩ መጥፎ ነገሮች መከሰታቸው ነው። የሰው ህይወት የሞተ ሲሆን ሌላ ቀውስም ተፈጥሯል።


ሰንደቅ፡- አቶ ኃይለማሪያም ስልጣናቸውን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ከገለጹ ከቀናት በኋላ ጥያቄያቸው በፓርቲያው ተቀባይነት ቢያገኝም ይህ ቃለመጠይቅ እስከተዘጋጀበት ትናንት ማክሰኞ ዕለት ጠዋት ድረስ የሚተካው ሰው አልታወቀም። ይህን ጉዳይ ከዴሞክራሲ እና ከዘመኑ ፖለቲካ ጋር እንዴት ያዩታል?


ዶክተር ፍሰሃ፡- ይህ እኮ ህገ መንግስቱን የተከተለ አይደለም። በህገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህይወታቸው ቢያልፍ (ባለፈው አቶ መለስ ሲያልፉ እንደሆነው) ወይም በራሳቸው ፈቃድ ስልጣን ቢለቁ በህገ መንግስቱ መሰረት ተተኪያቸው ሊመረጥ የሚገባው ወዲያውኑ ነው። ይህ አለመሆኑን ስንመለከት ግን ኢህአዴጎች በራሳቸው ውስጥ ወንበሩን ለማግኘት ሽኩቻ መፈጠሩን በግልጽ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመምረጥ በህገ መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት መሄድ ሲችሉ ይህን ያህል ጊዜ መውሰድ አልነበረበትም። በእኔ አመለካከት በህገ መንግስቱ መሰረት ከሄዱ ደግሞ ምናልባት የማይፈልጉት ሰው ሊመረጥባቸው እንደሆነ ሰግተዋል። ስለዚህ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደባቸው እነሱ የሚፈልጉት በተለይ አውራው ፓርቲ ህወሓት የሚፈልገው እንዲሆንለት ነው ማለት ይቻላል።


በመካከላቸው ችግር መፈጠሩን የሚያመለክተው ምን መሰለህ? እነሱ ኢህአዴጎች ራሳቸው መግለጫ ሲሰጡ ‹በስምምነት ውይይቱ እየተካሄደ ነው› ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ። ከዚህ በፊት ስምምነት ካልነበረባቸው ወይም አሁንም ችግር ከሌለባቸው ‹በስምምነት ውይይቱ እየተካሄደ ነው› ማለት ለምን አስፈለጋቸው? ስለዚህ በእኔ እይታ ችግር ስለነበረባቸው ወይም ስምምነት ስላልነበራቸው አሁን ስምምነት እየፈጠሩ ነው ማለት ነው። ይህን ስንመለከት ውዥንብር የሚፈጥር ነው ብዬ አስባለሁ።


ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ተቃውሞ እና ግጭት ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱ የሚታወስ ነው። ግጭቶች በወቅቱ ካልተፈቱ በተለያየ መልኩ ብዝሃነት ያለባት የዚህች አገር እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?


ዶክተር ፍሰሃ፡- እኔ አንድ የማምነው ነገር አለ። የህዝብን ፍላጎት ለጊዜ ትንሽ በሀይል ማስታገስ ይቻላል እንጂ በምንም ተዓምር በሀይል ልታቆመው አትችልም። በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ራሱ ጥሩ ምሳሌ ነው። የትግራይ ነጻ አውጭ እምቢ በማለቱ 17 ዓመት ሙሉ ታግሎ ሌሎችንም ትግል ውስጥ ከቶ ደርግን ጥሏል። አሁንም ቢሆን ኮማንድ ፖስቱ የህዝቡን ፍላጎት ሊገታው አይችልም። በእርግጥ ጊዜያዊ የሆነ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል፤ ለዘለቄታው ግን አስከፊ ነው የሚሆነው። ኢህአዴግ ራሱ የፖለቲካ መድረኩ ሲዘጋበት ጠብመንጃ አንስቶ እንደተዋጋው ሁሉ ወደፊት እንግዲህ ይህ የኮማንድ ፖስት አስተዳደር በዚህ አፈና ከቀጠለ ህዝቡ ያለ ፍላጎቱ ተደራጅቶ መሳሪያ ሊያነሳ ይችላል። ይህ ደግሞ ለአገሪቷ ትልቅ ውድቀት እና ጠንቅ ይሆናል። እንዳልከው በብዙ ነገር በዋናነት በቋንቋ እና በሀይማኖት የተከፋፈልን ነን። በተለይም በኢህአዴግ ዘመን ይህ የቋንቋ ልዩነት ገኖ የወጣበትና ሰውም ‹ለካ እኔ እንዲህ ነኝ› የሚል ስሜት የሚያነሳበት ዘመን ስለሆነ ይህ የትጥቅ ትግል ከመጣ አገሪቱን የባሰውን የከፋ አቅጣጫ ይመራታል ባይ ነኝ። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመረጠ በኋላ የመጀመሪያውና ትልቁ ስራው መሆን ያለበት ኮማንድ ፖስቱን ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም፤ ሲቀጥል በምን አይነት፣ የማይቀጥል ከሆነስ እንዴት በሚለው መፍትሔ መስጠት ይኖርበታል።


ሰንደቅ፡- ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው?


ዶክተር ፍሰሃ፡- አገሪቱ የግድ ጠቅላይ ሚኒስትር ያስፈልጋታል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየትም ይሁን ከየት (ከአራቱ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች ለማለት ነው) ይመረጥ እምብዛም ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም። ነገር ግን ለውጥ ሊመጣ የሚችለው የሚመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር በመጀመሪያ ደረጃ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ መልስ መስጠት ሲችል ነው። የህዝቡ ጥያቄ ደግሞ መንግስት እንደሚለው ስራ አጥነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሙስና ተንሰራፍቷል የሚለው ብቻ አይደለም። ህዝቡ ይህን ጥያቄ ያነሳው ድሮ ነው። የህዝቡ ጥያቄ እና ፍላጎት የስርዓት ለውጥ ነው። ይህን የስርዓት ለውጥ ጥያቄ መመለስ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን ይገባዋል። በአገሪቱ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ መደረግ ያለበት እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሆነው ደግሞ ህዝቡ ተሳታፊ የሆነበት የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የፖለቲካ መድረኩን ማስፋት ነው። የፖለቲካ አደረጃጀቱን እንዳሁኑ በዘር ሳይሆን በፖለቲካ አመለካከት (አይዲኦሎጂ) ላይ መሰረት ያደረገ መሆን አለበት።


ሌላው ለስርዓት ለውጥ ጥያቄ መልስ የሚሆነው ህገ መንግስቱን ራሱን መፈተሸ ያስፈልጋል። ህገ መንግስት ከሰማይ የተሰጠ የሁሉም አገር መተዳደሪያ ህግ አይደለም። ህገ መንግስት የህዝቡን ባህል፣ እምነት እና ሁሉን አቀፍ አስተሳሰብ መሰረት ተደርጎ የሚቀረጽ የህግ ክፍል ነው። እንደ ጊዜውና እንደ ወቅቱ ሁኔታ ሊሻሻል ይገባዋል። ለዚህ እኮ ነው በዓለም ላይ ያሉት አገራት ሁሉ ተመሳሳይ ህገ መንግስት የሌላቸው። ኢህአዴግም ቀደም ብሎ እንደተናገረው ህገ መንግስትን እስከማሻሻል ድረስ እንሰራለን እንዳለው በህገ መንግስቱ አንዳንድ ክፍሎች ላይ ፍተሻ እንዲደረግ መፍቀድና ማወያየት አለበት። እነዚህን ነገሮች ከህዝብ ጋር አብሮ የመስራት ግዴታ አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ካደረገ የህዝቡን ጥያቄ መልስ ሰጠ ማለት ነው። ያ ከሆነ ደግሞ ያለ ኮማንድ ፖስት በአገሪቱ ጸጥታ እና ሰላም ሰፈነ ማለት ነው። አለበለዚያ ግን እንደተለመደው ‹ሙስና ነበረብን፣ ራሳችንን ፈትሸን አጽድተናል፣ የስራ አጥነት ጥያቄውን እንመልሳለን› የሚሉት ንግግሮች መፍትሔ አይሆንም። ኢህአዴግ ራሳችንን ፈትሸናል ሲል ምን ማለቱ ነው? ሰው እንዴት ራሱን ይፈትሻል? ህዝቡ ፈትሾት ትክክል አይደለህም፤ አገዛዝህ ትክክል አይደለም ብሎታል። በፍተሻ ወድቋል እኮ።


ሰንደቅ፡- አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እና የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ኢህአዴግ መፍቀድ አለበት ሲሉ ካለፉት ዘመናት የገዥው ፓርቲ ባህሪ ተነስተው ሲመለከቱት ይህ የሚሆን ይመስለዎታል?


ዶክተር ፍሰሃ፡- እንግዲህ ‹ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ ካልሆነ ….› ነውና ነገሩ ኢህአዴግም ለራሱ ሲል ይህን ማድረግ አለበት። ኢህአዴግ እዚህ ከመድረሱ በፊት ለዴሞክራሲ ሲል ባካሄደው ትግል ብዙ ጓደኞቻቸው ሞተው እና ብዙዎቹ ቆስለው ነው የቀሩት ስልጣን ላይ የወጡት። ስለዚህ እነዚህ ስልጣን ላይ ያሉት የኢህአዴግ ባለስልጣናት የሞቱት እና የቆሰሉት ጓደኞቻቸው ታሪካቸው ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለጉ የግድ ባህሪያቸውን መለወጥ አለባቸው። መጥፎ ባህሪያቸውን እና አመራራቸውም ትክክል አለመሆኑን በእነሱ ዘመን ተወልደው ያደጉ ልጆቻቸው ድንጋይ እየወረወሩ መስክረውባቸዋል። ስለዚህ ኢህአዴግ ይህን ባህሪውን መለወጥ አለበት። አልለወጥም ካለ ደግሞ ሁኔታው የግ….ድ ባህሪውን እንዲለውጥ ያስገድደዋል። ያ ደግሞ አስከፊ ነው የሚሆነው። አስከፊነቱ ደግሞ ይበልጥ የሚከፋው የእሱን ታሪክም አበላሽቶ አገሪቱንም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ አስገብቶ እና በአገሪቱ እልቂት አስከትሎ መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ምንም አትሆንም። ግን ከእልቂት፣ ከጥላቻ እና ከቂም በቀል ፖለቲካ መታቀብ የምንችለው ኢህአዴግ ባህሪውን ሲለውጥ ብቻ ነው። የአገሪቱ ችግር ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ኢህአዴግ ብቻውን የሚፈታው አይደለም፤ የችግሩን ስፋት ደግሞ ራሱ ኢህአዴግም ያመነው ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ መድረክ ሊፈጠር ይገባል የምልህ። ህዝብ እና መንግስት በጋራ ተወያይቶ ለችግሩ እልባት የሚሆን መፍትሔ ማምጣት ነው ለአገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚሆነው። ዋናው የመፍትሔ ሃሳብ የሚመጣውም እኮ ከህዝብ ነው። የመንግስት ዓላማውና ኃላፊነቱ ህዝብን ማስተዳደርና በህዝቡ ጥያቄ መምራት ብቻ ነው እንጂ ችግሩን የምፈታልህ እኔ ነኝ ዝም ብለህ የምሰጥህን ተቀበል የሚል አይደለም።


ሰንደቅ፡- ከሁለት ወራት በፊት አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሊቀመንበሮች በሰጡት መግለጫ እስረኞችን እንዲፈቱ ኢህአዴግ የወሰነው በአገሪቱ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሆነ ተናግረው ነበር። አሁን አገሪቱ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ በሰንደቅ ዓላማ ሳይቀር ብሔራዊ መግባባት አልተፈጠረም። ለመሆኑ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር መሰራት ያለበት ምንድን ነው?


ዶክተር ፍሰሃ፡- ብሔራዊ መግባባት ማለት እኔ እንደሚገባኝ ራሱ የፈጠራቸውን ፖለቲካ ፓርቲዎችና የአገር ሽማግሌዎች ሰብስቦ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራሁ ነው ማለት አይደለም። አሁን ያሉትን የአገር ሽማግሌ ነን የሚሉትንም ሆነ የሀይማኖት አባቶችን ህዝቡ የሚቀበላቸው አልሆነም። ምክንያቱም ራሱ አልመረጣቸውም፤ እነሱም ቢሆን ሽማግሌ አይደሉም። እንዲያውም የራሳቸውን ጥቅም የሚፈልጉ እና የሚስከብሩ ናቸው። ትክክለኛ ብሔራዊ መግባባት ማለት ለሁሉም ወገን መድረክ ተከፍቶ ህዝቡ የሚፈልገውን ተናግሮ የሚፈልገውን እና የሚስፈጽምለትን ራሱ መርጦ ሲያቀርብ ነው ብሔራዊ መግባባት ማለት። ለተፈጠረው ችግር ህዝቡን በየቀበሌው እና በየገበሬ ማህበሩ ተሰብስቦ ፍላጎቱ ተጠይቆ ከዚያ መሃል ህዝቡ የሚናገረውን አድምጦ እና የሚስፈጽምለትን መርጦ መግባባት እስከሚደረስ ድረስ ውይይት ማድረግ ሲቻል ነው ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠረው እንጂ አንድ አካል በመረጣቸው ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰብስቦ በሚወሰን ውሳኔ አይደለም። ስለዚህ ለብሔራዊ መግባባት የሚያደርሱ ቅድመ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል። ይህ ሲባል ደግሞ ‹‹የተፈጠረው ጥፋት ይቅርታ ተደርጎ፣ ያለፈው አለፈ አሁን ለአገራችን ሲባል የሞተውም ነብሱን ይማር፣ ስድቡም ሆነ ጥላቸው ገደል ይግባ፣ አሁን ለአገራችን ተፋቅረን አንድ ነገር እንስራ›› ተብሎ ብሔራዊ እርቅ ሲፈጠር ነው። ይህን ለማምጣት ደግሞ መንግስት ሆደ ሰፊ መሆን አለበት የስልጣን ስስት ሊኖረው አይገባም። መጥፎ የስልጣን ስስት ከሌለው ከስልጣን ቢወርድ እንኳን ተመልሶ መምራት የሚያስችለውን ዕድል ሊያገኝ ይችላል። መጥፎ የስልጣን ስስት ካለው ግን ይወድቃል፤ ከወደቀ ደግሞ ይሰበራል።


ሰንደቅ፡- በአገሪቱ እንደዚህ አይነት ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ምሁራን ከፖለቲካው መስክ ይሸሻሉ የመፍትሔ አካል ለመሆን ዝግጁ አይሆኑም ይባላል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶች ይቀርባሉ። በአንድ በኩል ከምቾት ቀጠናቸው መውጣት ስለማይፈልጉ ነው ሲባል በሌላ በኩል ደግሞ ምሁራንን ኢህአዴግ ሆን ብሎ ገፍቷቸዋል ይባላል። በዚህ ላይ ያለዎት አረዳድ ምንድን ነው?


ዶክተር ፍሰሃ፡- ምሁር ሲባል የተማረ ሰው ማለት ነው ሌላ ትርጉም የለውም። የተማረ ሰው ደግሞ ለመናገር አይቸኩልም፣ አንድ ነገር ለማድረግ ማጥናት አለበት፣ ግራ ቀኙን መመልከት አለበት፣ ይጎዳል አይጎዳም ብሎ ማጤን አለበት። ትክክል ነው አይደለም የሚለውን የሚያመዛዝን ነው እንጂ አንድ ነገር ተፈጠረ ብሎ አፉ እንዳመጣለት ወይም ለጊዜው ያሰበውን የሚተነፍስ አይደለም። ስለዚህ ምሁራኑ አሁን ለአገራቸው እያሰቡ ነው፤ ምን ይደረግ ሲሉ እየመከሩ ነው። ቀስ እያሉ ነው የሚናገሩትም ሆነ የሚጽፉት። ስለዚህ ዋናው ነገር አንድን ሰው ምሁር የሚያሰኘው አስቦ፣ አውጥቶና አውርዶ፣ ግራ ቀኙን አይቶ መናገር መቻሉ ነው። አሁን ለምሳሌ አንዳንድ በፖለቲካው ውስጥ ምሁራን ነን የሚሉ አሉ። በቅርቡ በአንድ የውጭ ሬዲዮ ስሰማ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ‹የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለምንድን ነው እኔን ሳያናግረኝ የሄደው? የአገሪቱን ችግር የማውቀው እኔ ነኝ እኔን ማነጋገር ነበረበት። ይህን ባለማድረጉ ደግሞ ስህተት መሆኑን ለአሜሪካ ኤምባሲ ደብዳቤ ጽፌያለሁ› ብለው ሲናገሩ ሰማሁ። እኔ ለፕሮፌሰር በየነ የነበረኝ ግምት ላቅ ያለ ነበር። ይህን ስሰማ ግን ትንሽ የተለየ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎብኛል።


አንድ ምሁር ታውቃለህ እስቲ ተናገር ሲባል ሲናገር እንጂ እኔ አውቃለሁ እኔን ጠይቁኝ እኔን ካልጠየቃችሁኝ … ብሎ በአደባባይ ሲናገር የሰማሁት ምሁር የለም፤ በፖለቲካም ሆነ በሙያው መስክ። ለኢትዮጵያም ሆነ ለፕሮፌሰር በየነ ጥያቄ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይደሉም መልስ የሚሰጡትም ሆነ ችግሩንም የሚፈቱት።


ሰንደቅ፡- ምሁራን ሃሳባቸውን እንዲሰጡ የግድ ወደ እነሱ ካልተሄደ ሃሳባቸውን ማግኘት አይቻልም ማለት ነው? በተናጠል የሚያስቡትንስ በአንድ ጥላ ስር ሆነው ለህዝቡ የሚያደርሱበት አማራጭስ አይኖርም እንዴ?


ዶክተር ፍሰሃ፡- የምሁራን ድርጅትም ሆነ ማህበር የለም። የመምህራን ድርጅት ከሆነ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ምሁራን ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ መንግስት አሰባስቦ እንደዚህ አይነት ችግር አለ ምክራችሁን ወዲህ በሉ በተማራችሁት መነጽር መፍትሔው ምን ይመስላችኋል? ብሎ ከጠየቀ ምሁራን ይሰባሰባሉ እንጂ ምሁራን ለአገር ጉዳይ እስቲ ተሰባሰቡ የሚል የለምም ሊኖርም አይችልምም።


ሰንደቅ፡- እርስ በእርስ በግል ተጠራርቶ በመገናኘት አንድ የውይይት መድረክ መፍጠርም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት በመመስረት ሃሳብን ለማካፈል ምሁራኑ ምን ያህል ዝግጁዎች ናችሁ?


ዶክተር ፍሰሃ፡- እንደዚህ አይነት ነገር አይታወቅም። እኔ እስከማውቀው ድረስ በሌላውም አገር የለም። ነገር ግን ምሁራን የሚሰባሰቡት መንግስት ሲጠራቸው ወይም ድርጅቶች ጠርተው ለችግሩ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ ሲቀርብላቸው እንጂ ምሁራን ተሰብስበው ፖለቲካ ፓርቲ መመስረትማ ፖለቲካ ሆነ እኮ። እንደዚህ አይነት ነገር ሊኖር አይችልም፤ አይኖርምም ባይ ነኝ። ፖለቲካን በተመለከተ ምሁር ዘሎ እጁን አያስገባም። ሲጠየቅ ብቻ ነው መልስ የሚሰጠው። ምሁርንና ፖለቲከኛን የሚለየውም ይህ ነው። ለዚህ ነው በየዩኒቨርስቲው ብዙ ዶክተር እገሌ የተባለ ምሁር እያለ ዝም የሚለው። ሲጠየቁ ወይም ፎረም ኖሮ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ሲያቀርቡ ያን ጊዜ ሃሳባቸውን ማግኘትና መውሰድ ይቻላል።


ሰንደቅ፡- በመጨረሻም በግልዎ የሚሰጡት ምክረ ሃሳብ ካለ እንስማዎ?


ዶክተር ፍሰሃ፡- እኔ መቼም እንግዲህ በእውነት ለኢትዮጵያ የማስበው ህዝቡም በተለይ ወጣቱ ተነስቷል። ይህን የወጣቶች አካሄድ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚመራ መሪ ያስፈልገዋል። በኢህአዴግም በኩል ደግሞ ወጣቶቹ መድረክ እንዲሰጣቸው ማድረግ ያስፈልገዋል። ከህዝቡም በኩል ‹ገትጋታነትን› ትቶ ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ፣ ወጣቱም ድንጋይ ከመወርወር ሃሳቡን የሚወያይበት መድረክ እንዲፈጠር ያስፈልጋል። አሁን እንደማየው አውራ እንደሌለው ንብ በየሄደበት የሚናደፍ ተቃውሞ እና ጩኸት ነው። ስለዚህ ወጣቱ ተርቧል ተጠምቷል ነጻነት ይፈልጋል እንዲሁም ስርዓቱንም በቃኝ ብሏል ግን በቃኝ የሚለውን ስርዓት ለመለወጥ ምን አይነት መንገድ ነው የሚበጀው የሚለውን ለመለየት መሪ መፍጠር አለበት።


ኢህአዴግ ደግሞ ስርዓትህ በቃን አንገሽግሾናል ተብሏል። በተለይ በእሱ ዘመን ተወልደው ያደጉ ወጣቶች ስርዓቱ እንዳንገሸገሻቸው በግልጽ ነግረውታል። ስለዚህ ይህን ጥያቄ ሰምቶ መልስ ለመስጠት ቁርጠኛ እና ፈቃደኛ መሆን አለበት። ይህን ካደረገ ለሞቱት እና ለቆሰሉት ጓዶቹ ሃውልት አቆመላቸው ማለት ነው፤ ይህን ማድረግ ካልፈለገ ግን ሃውልት ማቆም ሳይሆን መቃብሩን እየቆፈረ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
946 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1017 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us