“የዶክተር አብይን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ የምገልጸው በረጅም ዋሻ ጫፍ ላይ እንደሚታይ ብርሃን ነው”

Wednesday, 04 April 2018 14:36

“የዶክተር አብይን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ የምገልጸው በረጅም ዋሻ ጫፍ ላይ እንደሚታይ ብርሃን ነው”

ዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ
የህክምና እና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር

በይርጋ አበበ

 

ዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ ምንዳ የህክምና ባለሙያ ሲሆኑ የስነ ልቦና አማካሪ እና የሀይማኖት መምህርም ናቸው። የሁለት ሴት ልጆች አባት የሆኑት እኒህ ዘርፈ ብዙ ምሁር በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂደዋል። ኢትዮጵያ አሁን በፖለቲካውና በማህበራዊ ዘርፍ ቀውስ ውስጥ ገብታለች የሚሉት ምሁሩ፤ የቀውሱን መንስኤ እና መፍትሔ በግልጽ አስቀምጠዋል። ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸውንም ለኢትዮጵያ በአስፈላጊ ወቅት የተዘጋጁ ሰው ሲሉ ይገልጹታል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ከፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ሰንደቅ፡- የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- የነበርንበት ሁኔታ እጅግ በጣም ፈታኝ እና ከባድ እንደነበረ ነው የሚታየኝ። ለኢትዮጵያ በሁለት መንገድ የሚፈጠሩ ግጭቶች ማለትም በሀይማኖት እና በብሔር ልዩነት የሚነሱ ግጭቶች በጣም አደገኛ ናቸው። በእነዚህ ሁለት መንገዶች የሚፈጠሩ ግጭቶች ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆን እናውቃለን። በዚህ የተነሳ ሁላችንም ደንን……በኛ ፍርሃት ውስጥ ነበርን። ፍርሃታችን ደግሞ ለግል ብቻ ሳይሆን የነበረው ረብሻ የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ ነበር። በእኛ አገር ሁኔታ ደግሞ ስታየው አንድ ፋብሪካ ሲቃጠል እንደ አሜሪካኖች በአንድ ወይም በሁለትና በሶስት ወራት የሚተካ አይደለም። እኛጋ በሚፈጠር ግጭት የሚደርስ የንብረት ውድመት መተኪያ አልባ ናቸው። ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ያስከተለው ውድመትም ሆነ የሰብዓዊ ጉዳት በቀላሉ የማይተካና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነበር። ሰዎች ስራ እያቆሙ፣ ቱሪዝሙ እየተጎዳ፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የነበረን ተቀባይነት እየቀነሰ እና በአደገኛ ቁልቁለት ላይ ነበርን። በዚህ የተነሳም የነበረውን ክስተት በግሌ በጣም በሚያስፈራ ሁኔታ ነበርን ብዬ ነው የማምነው።


ሰንደቅ፡- እርስዎ የሚሉትን አሳሳቢ ሁኔታዎች መከሰት ተከትሎም መንግስት መፍትሔ ብሎ የወሰደው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ነው። ይህ አዋጅ አንዳንዶች ችግሩን ለጊዜው ቢያበርደውም ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም ሲሉ፤ መንግስትን ጨምሮ በሌላ ወገን የተሰለፉ ወገኖች ደግሞ የአዋጁን ተገቢነት አስረግጠው ይሞግታሉ። በግልዎ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን እንዴት ያዩታል?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- በግሌ ስለ አዋጁ የማምነው አስፈላጊ መሆኑን ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች አገራት ሲጠቀሙበት አይተናል። አስጨናቂ ወቅት ሲፈጠር ለማረጋጋት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ አስፈላጊ ነው። እንደኔም ሃሳብ አሁን የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይሆን ችግር የሚያመጣው አፈጻጸሙ ነው። አፈጻጸሙ ሲባል ሰዎች በአዋጁ ክፍተት አግኝተው የራሳቸውን ጥቅም ከተጠቀሙበት አደገኛ ነገር ያመጣል። አዋጁ ከታወጀ በኋላ ግን በመንግስት በኩል ሊደረግ የሚገባው አፈጻጸሙ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። በሚወሰደው እርምጃ ላይ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ሰዎች የግላቸውን ቂም ሊወጡበት ይችላሉ፣ የጸጥታ ሀይሉን የደንብ ልብስ ለብሰው የሰዎችን ንብረት ሊዘርፉበት ይችላሉ፣ የተለያየ ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ።


ሰንደቅ፡- የኢህአዴግ ምክር ቤት ሰፋ ላለ ጊዜ በፈጀ ስብሰባ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርና የግንባሩን ሊቀመንበር መርጧል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምርጫ ሂደት እንዴት አዩት?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- በኢህአዴግ የምገረምበትን ልንገርህ። ድርጅቱ በጣም ሚስጢራዊ ድርጅት ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደሚያደርጉት ሁሉ አሁንም ጉዳያቸውን ሲያካሂዱ የነበረው በሚስጢር ነበር። በጣም ጥቂቱን ብቻ ይንገሩን እንጂ እዛ ውስጥ የተፈጠረው ነገር በጣም ከባድ እንደነበር በመግለጫቸው ነግረውናል። እልህ አስጨራሽ ትግል አካሂደናል ብለውናል። እዛ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ሙግትም በለው ትግል ምን እንደነበረ ግን አናውቅም። ለጋዜጠኞችም ለህዝቡም በራቸውን ዘግተው የሚሆኑትን ሁሉ ሆነው ውሳኔያውን ይዘው ይወጣሉ። ይህ ደግሞ የፓርቲው ባህሪ ነው። ልክ ባልና ሚስት የራሳቸውን ጉዳይ በራቸውን ዘግተው ይጨርሱና ሰላማዊ መስለው እንደሚታዩት ማለት ነው። የኢህአዴግ አንዱ የሚያስገርመኝ ባህሪውም ይኸው ሚስጢራዊነቱ ነው። የምርጫ ሂደቱንም እነሱ ከነገሩን ተነስቼ ስነግርህ የራሳቸው የሆነ የውስጥ ዴሞክራሲ እንዳላቸው አሳይተዋል ብዬ አምናለሁ።


ሰንደቅ፡- አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት አገኟቸው? አገሪቱ በርካታ ጥያቄዎች ያሉባቸው ዜጎች አገር እንደመሆኗ ከእሳቸውስ ምን ይጠበቃል?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- አንዳንድ ሰዎች ለአንዳንድ ዘመን ይዘጋጃሉ። ለምሳሌ ፕሬዝዳንት ኦባማን ብንወስድ ሲመረጡ ዓለም ነው የተደሰተው ማለት ይቻላል። የፕሬዝዳንት ኦባማ እናት ነጭ በመሆናቸው እና አባታቸው ጥቁር በመሆናቸው አሜሪካ ውስጥ ነጮችም ጥቁሮችም ተደስተዋል። አፍሪካዊያን ደግሞ የባራክ ኦባማ አባት ከኬንያ በመሆናቸው በኦባማ ምርጫ ተደስተዋል፤ ኤስያዎች በበኩላቸው ባራክ ኦባማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በኢንዶኔዥያ ጃካርታ በመከታተላቸው እነሱም በባራክ ኦባማ መመረጥ ተደስተዋል። በዚህ የባራክ ኦባማ ምርጫ የተገጣጠመ ‹‹ፐዝል›› ነው የምታየው። በዚያ ላይ ግለሰቡም የህግ ባለሙያ በመሆናቸውና የተማሩም በመሆናቸው በዚያ ወቅት ለአሜሪካ የተዘጋጁ ሰው ነበሩ።


ልክ እንደዚሁ ዶክተር አብይንም ስንመለከት የትምህርት ዝግጅታቸው ሲነገረን በጣም ጥሩ ነው። የግጭት አፈታት ላይ ጥናት እንዳደረጉ አይተናል፤ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ነው። ስለዚህ በስልጣን ዘመናቸው ትምህርታቸውን ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የመጡበት የፖለቲካ ጉዟቸውና ስራቸውም አሁን ለሚረከቡት ስራ አስፈላጊ ነው። ሌላው ቀርቶ የብሔር ስብጥራቸውም ከሁለት ብሔር መፈጠራቸውና ወጣትም መሆናቸው ለዚህ ጊዜ የተዘጋጁ ሰው ይመስሉኛል። ነገር ግን እሳቸው እንደግለሰብ ስልጣን ላይ ከመቀመጣቸው ይልቅ ፓርቲያቸው ኦህዴድ እንደ ፓርቲ ስልጣን በመያዙ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም የኦህዴድ መሪዎች ሲናገሩ እንደሰማነው የረጅም ጊዜ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ውጤት ነው ብለዋልና። የኦሮሞ ህዝብ ትግል ውጤት ደግሞ ይህ ከሆነ እዚህ ቦታ ላይ አሁን ኦሮሞን የሚወክለው ድርጅት ኃላፊነት ላይ መቀመጡ እጅግ በጣም ደስ ይላል። ምክንያቱም ለአንድ ህዝብ እንደ ድል ነው የሚቆጠረው።


ሰንደቅ፡- የዶክተር አብይን ሹመት ከኦሮሞ ህዝብ ትግል ጋር አገናኝተው ተመልክተውታል። ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ድል ነውም ብለዋል። በዚህ አይነት ሌሎች ብሔሮችስ ቅሬታ እና ለስልጣኑ ትግል ላለማድረጋቸው ምን ዋስትና አለን?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት ኦባማን አንስቻለሁ። እሳቸው ወደ ስልጣን የመጡት ተስፋን ሰብከው ነው። እንዲያውም ገና ሴናተር ሆነው እያሉ The Audacity of Hope የሚል መጽሃፍ ጽፈው ተስፋን ሰብከው ነበር። ለአሜሪካ ህዝብ ተስፋን ሰጥተው ነው ወደ ስልጣን የመጡት።


አሁን ኦህዴድም ያደረገው ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኢትዮጵያዊ አንድነት ተስፋን እየሰበኩ ነው የመጡት። አቶ ለማ ኢትዮጵያነትን ሰበኩ፤ ዶክተር አብይም እንዲሁ። እነዚህ ሰዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ የራሳቸውን ብሔር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚወዱ መሆናቸውን እየገለጹ ነው የመጡት። ኢትዮጵያዊነትን ስትሞቀው የምታወልቀው ሲበርድህ የምትለብሰው አይደለም እያሉ በግልጽ ስለ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር እየሰበኩ ነው እዚህ የደረሱት። አሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስፈለገው ተስፋ ሲሆን እነሱም ይዘውልን የመጡት የአንድነት ተስፋን ነው። በአንድነት የመኖር እና ያለመፈራረስን ተስፋ። ኢትዮጵያ እንደ አገር አንድነቷ ተጠብቆ ትኖራለች የሚል ተስፋ አስቀድመው በንግግሮቻቸው ሰበኩ። አሁን ወደ ስልጣን ሲመጡም የራሳቸውን ብሔር ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሚያስጠብቁት የሌሎቹን ብሔሮች ጥቅምና ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጥቅምና አንድነት ያስጠብቁልናል ብለን ተስፋ አደረግን።


ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ በዚህ ከፍተኛው የኃላፊነት መንበር የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይደለም ሲሉ ሃሳብ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ። በእርሰዎ እምነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠብቃቸው የፖለቲካ እና የአስተዳደር ፈተና ምንድን ነው?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- የመጀመሪያው ፈተና ይሆናል ብዬ የማስበው በአንድ በኩል ራሳቸው የሚያምኑበት የራሳቸውን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ መሄድ በሚፈልጉበት መንገድ እንደመሪ ይዘው መሄድ ይፈልጋሉ። ተቃዋሚዎችንም አካተው በዚህ መንገድ መሄድ ይፈልጋሉ። በዚህ በኩል ደግሞ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግ ነው›› ብሎ ኢህአዴግ እቅጩን ነግሮናል። ይህ ምን ማለት ነው ያልን እንደሆነ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የጥምር አስተሳሰብ አመራር ነው ውሳኔ የሚሰጠው ማለት ነው። በኢህአዴግ አሰራር የሚቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትርም የሚያስፈጽመው የኢህአዴግን ፖሊሲ ነው፤ አለቀ። የእነሱን የፖለቲካ ባህላቸውን ግልጽ አድርገው አስቀምጠዋል። ኢህአዴግ ራሱ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርጎ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ማሳተፍ፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ይህ ሁሉ የድርጅቱ ውሳኔ ነው። በኢህአዴግ አሰራር አንድ ግለሰብ መሪ ሆኖ ተቀምጦ ብቻውን የሚያሳልፈው ውሳኔ የለም።


ስለዚህ ዶክተር አብይ በአንድ በኩል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይፈልጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግን ፖሊሲ ነው የሚያስፈጽሙት። እነዚህ ሁለት ነገሮች ደግሞ ከቀኝ እና ከግራ ወጥረው የሚጎትቷቸው ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ቀላል ፈተና አይደለም።


ነገር ግን ውጭ ያሉትም ሆነ አገር ቤት ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሲናገሩ እንደሰማኋቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ጊዜ እንስጣቸው፣ እንታገሳቸው›› የሚል አዎንታዊ የሆነ ምልከታ አይቻለሁ።


በአጠቃላይ የዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥን የምገልጸው ፈረንጆቹ ‘There is Light the End of the Tunnel’ ወይም በአማርኛ በረጅም ዋሻ ጫፍ ላይ ብርሃን ታይቷል እንደሚሉት ነው የሚታየኝ። ከረጅም ዋሻ ጫፍ ላይ ብርሃን ታየ ማለት ከጨለማው ዋሻ መውጣት እንደሚቻል ተስፋ ያሳያልና።


ሰንደቅ፡- ከፖለቲካ ጉዳዮች ወጣ ባለ መልኩ ወደ ማህበራዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚያደርጉ ጥያቄዎችን አንስተን እንወያይ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የማህበራዊ ዝቅጠት በአገሪቱ ተከስቷል ሲሉ የሚናገሩ ምሁራን በርክተዋል። ለዚህ ሃሳባቸው የሚያቀርቡት አስረጅ ነጥብ ደግሞ የወጣቱን በሱስ በተለይም በጫት ሱስ መጠመድ ነው። በእርሰዎ አረዳድ አገሪቱ ውስጥ የማህበራዊ ቀውስ አለ?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- በዚህ ላይ የተጠኑ ጥናቶች አሉ። ባለፈው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ባቀረበው ጥናት ወጣቱ በሱስ እንዴት እንደተያዘ ያንንም ለመቋቋም ምን አይነት ስትራቴጂ መቀረጽ እንዳለበት ሲነገር ነበር። እውነት ነው፤ አገራችን ውስጥ የማንክደው የማህበራዊ ቀውስ አለ። ለዚህ ደግሞ ምሳሌዎች ልንገርህ፤ በየከተሞች ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ከግቢ ወጥተው የሴተኛ አዳሪነት ስራ ይሰራሉ። ይህ በጣም የሚያሳዝን የማህበራዊ ቀውስ ነው። ድሃ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ወደ ከተማ ልከው ልጆቻቸው ግን በዚህ ስራ ተሰማርተው በግላጭ ፎቷቸው በየሆቴሎቹ ሪሰፕሽን ተቀምጦ ወደ ዚህ ስራ ሲሰማሩ ማየት ማህበራዊ ቀውስ ነው።


የተለያዩ ሱሶች በተለይ ጫት በመላው አገሪቱ ከጥግ እስከ ጥግ ድረስ ይቃማል። ይህ የጫት መቃም ተግባር ደግሞ በእንግሊዝኛው Habituation (የዕለት ተዕለት ተግባር ሊባል ይችላል) በሚባል ደረጃ ነው የሚቃመው። የመጠጡን መጠነ ሰፊነት ትመለከታለህ። የስነ ምግባር መውረድም እንዳለ ትመለከታለህ። ይህም በወጣቱ ተስፋ መቁረጥ፣ በተለይ በስራ ማጣት የተነሳ ነገ የተሻለ ነገር አለማየት የተነሳ ወደዚያ አይነት ሱስ ይገባል። በአጠቃላይ ስናየው ግን ከፍተኛ ሊባል የሚችል የማህበራዊ ቀውስ በአገራችን አለ።


ሰንደቅ፡- በዚህ ሃሳብ የሚስማሙ ሰዎች ለዚህ አይነት ማህበራዊ ቀውስ መፈጠር የሚያቀርቡት የፖለቲካው አለመረጋጋትና ጤናማ አለመሆን ኢኮኖሚውን ጎዳው። እነዚህ ተመጋጋቢ ምክንያቶች ወደ ማህበራዊ ቀውስ እንድናመራ አድርጎናል፤ እንደዚህ አይነት የማህበራዊ ቀውስ ሲያጋጥም መድሃኒት የነበሩት የሃይማኖት ተቋማት ነበሩ። አሁን ግን እነሱም ራሳቸው በዚህ አይነት አዙሪት ገብተዋል፤ የሚጠበቅባቸውን የቤት ስራ አልሰሩም ሲሉ ይናገራሉ። እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- የሃይማኖት ተቋማት ስራቸውን አለመስራታቸው በጣም ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሀይማኖተኛ ነው። ወይ ሙስሊም ነው አለዚያ ደግሞ ክርስቲያን (ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ) ነው። አብዛኛው ከዚህ አይወጣም። ስለዚህ እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም እረኝነት የሚባለውን የቤት ስራውን ቢሰራ ኖሮ እንደዚህ አይነት የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ባልገባን ነበር። እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን እና መስጊድ በስሩ ያሉ ምዕመናንን በስም እና በአድራሻ ማወቅ አለባቸው። ይህን የእረኝነት ተግባር መፈጸም ደግሞ ግዴታቸው ቢሆንም የሚከናወነው ግን የተለመደው ሃይማኖታዊ ተግባር (ስብከት፣ ፀሎት ወይም ስግደት) ከተፈጸመ በኋላ የሃይማኖቱ ተከታዮች የት እንደሚውሉ፣ ምን እንደሚበሉ፣ ምን እንደሚሰሩ ክትትል አይደረግም። ይህን አለማድረግ ደግሞ የእረኝነትን ተግባር አለመወጣት ወይም መዘንጋት ነው። በዚህ የተነሳም ምዕመኑ እረኛ እንደሌለው በግ ይሆናል ማለት ነው።


ሰንደቅ፡- በማህበራዊም ሆነ በፖለቲካው መስክ አንደ አገር ቀውስ ውስጥ ነን ከተባለ እና መንስኤውንም ካስቀመጡ ከዚህ ችግር ለመውጣት መፍትሔ ነው የሚሉት ምንድን ነው?


ዶክተር ወዳጄነህ፡- ሁለት ነገሮች መናገር እፈልጋለሁ። አገርን መውደድ ማለትም ፈረንጆቹ Nationalism ወይም schism የሚሉትን ሳይሆን patriotism በሚባለው መልኩ ነው አገር መውደድ ሊገለጽ የሚገባው። ሁለቱ ቃላት ሌሎችን አግላይና ለራስ የተለየ ግምት የሚሰጡ በመሆኑ እኔ አልወዳቸውም። እኔ በዚህ ሰዓት የምፈልገውም አገርን የመውደድ ስሜት በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ እንዲነድ እፈልጋለሁ። ለዚህ አንድ ምሳሌ ልስጥህ። አሜሪካዊያን አገራቸውን እንደሚወዱ ይነግሩሃል። ለምንድን ነው አገራችሁን የምትወዱ ብለህ ስትጠይቃቸው የሚመልሱልህ መልስ በጣም ይገርምሃል። ምን ይላሉ መሰለህ ‹‹አሜሪካ እኮ የተመሰረተችው በነጻነት ዲክላሬሽን ላይ ነው። ሁሉም ሰው እኩል ተፈጥሯል ብለን ነው የምናምነው፤ አሜሪካ የነጻነት እና የእኩልነት ምድር ነች። ስለዚህ አገሬን እወዳለሁ ይሉሃል። ስለዚህ አሜሪካዊያን አገራቸውን የሚወዱት አሜሪካ የቆመችበትን መሰረት ነው።


እኛ ኢትዮጵያዊያንም መሰረት አለን፤ አትንኩኝ ባይነታችን፣ ነጻነታችን መደፈር አለመፈለጋችን፣ ሉአላዊነታችን እነዚህ በደንብ ተቀምጠው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የተመሰረተችበት መርህ መሆናቸው መነገርና መቀመጥ አለባቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያን እንወዳለን ስንል ኢትዮጵያ የተመሰረተችበትን መርህ መውደድ ማለት ነው።


ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ኡቡንቱ የሚባል አፍሪካዊ ፍልስፍና አለ። ኡቡንቱ የሚያምነው በእርስ በእርስ መደጋገፍ (Interdependence) አንዱ በአንዱ ላይ መደገፍ አለበት ብሎ ነው። እኔ ላንተ አስፈልግሃለሁ ወይም አንተ ለእኔ ታስፈልገኛህ ማለት ነው። ያንተ መኖር ለእኔ ስኬት አስፈላጊ ነው። የእኔ መኖርም ላንተ ስኬት እንዲሁ። እኔ በመኖሬ ለአንተ ወይም አንተ በመኖርህ ለእኔ ጠላት አለመሆንህን የሚገልጽ አስተሳሰብ ነው። እኔ የዚህ ፍልስፍና ሰባኪ ነኝ። ስለዚህ በኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ የአማራው ህዝብ ለኦሮሞው ህዝብ ያስፈልገዋል፤ ኦሮሞውም ለአማራው ያስፈልገዋል። ትግሬው ለአማራው ያስፈልገዋል፤ አማራውም ለትግሬው እንዲሁ። አፋሩ ለኦሮሞው ኦሮሞው ለሶማሌው በአጠቃላይ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች አንዱ ለአንዱ ያስፈልጉታል። ስለዚህ የአንዱ ህዝብ ወይም የአንዱ ብሔር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት መሆን ያለበት ታስፈልገኛለህ በሚል መያያዝ አለበት። አንዳንዶቻችን የብሔር ማንነታችን ግራ የሚጋባን ሰዎች ነን። ለአብነት ያህል እኔ የተወለድኩት ሐረር ሲሆን አባቴ ጅጅጋ የተወለዱ ሲሆን እናቴ ደግሞ ድሬዳዋ ነው የተወለዱት። አሁን የእኔን አስተዳደግ ስታይ አባቴ ፊታውራሪ መሐረነ ምንዳ ሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነው። እኔን አስበኝ ልጅ ሆኜ ቤታችን ውስጥ ሶማሊኛ ይነገራል፤ ኦሮምኛም ይነገራል፤ አማርኛም እንዲሁ። በዚህ ሁሉ መሃል እኔ የየትኛው ብሔር ወይም ከየትኛው ዘር ነኝ ብዬ አልጠየኩም ነበር። ልክ መንግስት ሲቀየር የብሔር ወሬ ሲመጣ ነው አድጌ ዘመድ ጠይቄ አባቴ ከየትኛው ነገድ፣ እናቴም ከየትኛው እንደሆኑ ያወኩት። ተገድጄ ነው ብሔሬን ያወኩት። አሁንም ቢሆን የብሔር ማንነት ወይም አይደንቲቲ አይሰማኝም፤ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው የሚሰማኝ።


ስለዚህ ሁላችንም በየብሔር ማንነት ፍለጋ ከመግባታችን በፊት ሁሉም ለሁሉም አስፈላጊ መሆናችንን አይተን ያለፈው ንጉስ እንዲህ ነበር፤ እንዲህ አድርጓል የሚለውን ቂም በመተው ወደ ፊት መሄድ፤ መከባበር እና መፈላለግ ያስፈልገናል። ያኔ ችግሮቻችን መፍትሔ ያገኛሉ ብዬ አምናለሁ።

 

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
316 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 147 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us