የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰፈር እንዴት ሰነበተ?

Wednesday, 11 April 2018 14:22

በይርጋ አበበ

ኢህአዴግ ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ ያለፉትን ሰባት ወራት በከፍተኛ እና ወሳኝ ጉዳዮች ተወጥሮ ያሳለፈበት ጊዜ ነው፡፡ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውንና ፓርላማው አጽድቆት ለአስር ወራት ስራ ላይ የቆየውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ድንገተኛ ስብሰባ ካነሳው በኋላ እንደገና ለስድስት ወራት ተፈጻሚ እንዲሆን ውሳኔ ያሳለፈው በዚሁ ባሳለፍናቸው ሰባት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ባልተለመደ መልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የምክር ቤቱ አባላት በተቃወሙትና ብዙዎቹም በዕለቱ በአዳራሽ ሳይገኙ የቀሩበት ውሳኔ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም የ52 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ራሳቸውን ከኃላፊነት አግልለው በምትካቸው የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ዶክተር አብይ አህመድ ከኦህዴድ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ተረክበዋል፡፡

የኦህዴዱ ሊቀመንበር የኢህአዴግን ሊቀመንበርነትና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን በተረከቡበት ዕለት ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የምንጠራው ተቃዋሚ በማለት ሳይሆን የተሻለ ሃሳብ ይዞ እንደቀረበ ወንድም ነው፡፡ ከእነሱ ጋር ለመስራትም መንግስታችን ዝግጁ ይሆናል›› ብለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የኢህአዴግ ያለፉት ወራት እና ሳምንታት አብይ ተግባራት ሲሆኑ በተቃዋሚው መስመር (እንደ ዶክተር አብይ አጠራር ‹‹ተፎካካሪዎች››) ያለው ሰሞነኛ ጉዳይ ምን ይመስላል? ስንል ደጃቸውን አንኳኩተናል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ሃሳባቸውን ያካፈሉን ፖለቲከኞች ናቸው፡፡

 

 

የፓርቲዎቹ ውስጣዊ ጥንካሬ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ቤት የወጡት መንግስት በቅርቡ ለእሰረኞች ምህረት ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡ ለመሆኑ መንግስት ላቀረበላችሁ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የፓርቲያችሁ ጥንካሬ ምን ይመስላል? ስንል ሊቀመንበሩን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ዶክተር (ረዳት ፕሮፌሰር) መረራ ጉዲና ሲመልሱ፤ ‹‹የህዝብ ድጋፍን በተመለከተ ከሆነ የጠየከኝ ያለን ይመስለኛል ደግሞም በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ከዚያ ፓርቲያችን ደግሞ መንግስት በሃቅ ችግሮችን ለመፍታት እደራደራለሁ ካለ እኛ ለመደራደር ዝግጁ እና ብቁ ነን፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት እንደተደረገው ጊዜ ለመግዛት የሚደረጉ ድርድሮችን አልተቀበልነም ነበር አሁንም እንደዛ የሚሆን ከሆነ አንቀበልም›› ሲሉ የፓርቲያቸውን ጥንካሬ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት ያቀረበውን አብሮ የመስራት ጥሪ ተቀብሎ በመቅረብ በህዝብ አመኔታ የሚሰጠውን ስራ ለመስራት የውስጥ ጥንካሬው ምን ይመስላል?›› ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ፤ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ከቀድሞ አንድነት አባላትና አመራሮች ጋር መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ ንግግር ላይ እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን ከሸንጎ ጋርም አብሮ እየሰራ ነው፡፡ ስለዚህ ያቀረብክልኝን ጥያቄ ለመሸከም እና ለማስተናገድ በቂ ችሎታም እውቀትም የሰው ሃይልም አለው ብለን እናስባለን›› ያሉ ሲሆን፤ ጥሪውን በተመለከተ ‹‹ከፓርቲ በላይ ነው ታስረው ከተፈቱ ሰዎችን እና የግብረ ሰናይ ድርጅት ኃላፊዎችን እና ሌሎችን ያካተተ ንግግር ይሆናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ስለ ግለሰብ እና ስለ ፓርቲ ጥንካሬ ብዙ የምንጨነቅበት አይመስለኝም›› ብለዋል፡፡

አቶ የሽዋስ አያይዘውም ‹‹ኢህአዴግ ማሰሩን ካቆመ የእኛን ጥንካሬ ማምጣቱ ቀላል ነው›› ሲሉ የገለጹ ሲሆን ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹በ2007 ዓ.ም ምርጫ ኢህአዴግ 100 ፐርሰንት አሸነፍኩ ሲል፣ ከ200 በላይ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች እስር ቤት ነበሩ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ያህል ሰዎች ከእስር ቢፈቱና ቢንቀሳቀሱ በቂ አቅም ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተቃራኒው ከኢህአዴግ ውስጥ 200 የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ቢታሰሩ እኮ ኢህአዴግ ራሱ ደካማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ማሰሩንና ማዋከቡን ካቆመ ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችም ለራሷ ቀርቶ ለሌሎች አገሮች የሚተርፍ እውቀት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ በተደጋጋሚ የታየ ነው›› ብለዋል፡፡

የዶክተር አብይ ጥሪ እና የፓርቲዎቹ ዝግጅት

ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲገልጹ አብሮ ለመስራት የሚችሉበትን መንገድ ፓርቲያቸው እንደሚዘጋጅ ገልጸው ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ ፓርቲያችሁ እንዴት ያየዋል ስንል ለአቶ የሽዋስ ጥያቄ አቅርበንላቸው የሚከተለውን መልሰዋል፡፡ ‹‹ፓርቲያችን ጥሪውን የተቀበለው በጥሩ መንፈስ ነው፡፡ በእርግጥ ጥሪው የተደረገው በአደባባይ (ፐብሊክ) ነው ልክ ለኤርትራ መንግስት እና ለውጭ አገር ኢትዮጵያዊያን እንደተደረገው ነው ለፓርቲዎችም ጥሪ የተደረገው፡፡ ግን በዚህ ጉዳይ ለመወያየት ከዚህ በላይ ሰፊ እና ግልጽ የሆነ (ውይይቱና ድርድሩ የሚካሄድበት ጊዜ፣ ቀን፣ አወያይ እና የመሳሰሉት) ማብራሪያ እንጠብቃለን፡፡ ይህ በግልጽ ተቀምጦ ጥሪው ከቀረበልን ለመደራደርና ለመወያየት ያዘጋጀናቸው ግልጽ የሆኑ ነጥቦች አሉን እነሱንም በስራ አስፈጻሚም ሆነ በብሔራዊ ምክር ቤት ተወያይተንበታል›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን በዚህች አገር እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ መደረግ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያወሱት አቶ የሽዋስ፤ ‹‹አገሪቱ የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ለገዥው ፓርቲ ያደሩ በመሆናቸው ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው እንደገና እንዲዋቀሩ መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ አገር ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ለውጥም ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንዴት ይመጣል ለሚለው እንደፓርቲ ያዘጋጀናቸው ነጥቦች አሉ እሱን ይዘን መቅረብ እንችላለን›› ሲሉ ሀሳባቸውን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

የመድረኩ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ‹‹ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ከዚህ በፊት በጽሁፍ፣ በቃል እና በመገናኛ ብዙሃን በኩል ስንጠይቅ ቆይተናል፡፡ ስለዚህ በኢህአዴግ በኩል ጥሪ ከተደረገልን በእኛ በኩል ለመደራደር ችግር የለብንም›› ያሉ ሲሆን ‹‹ነገር ግን ጥሪው መንግስት በሃቅ ለመደራደር እና የዚህችን አገር መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት እስከተዘጋጁ እና እስከፈለጉ ድረስ እኛ በሃቅ ለመደራደር የማንፈልግበት ምክንያት የለም›› በማለት የፓርቲያቸውን አቋም ግል አድርገዋል፡፡

ከዚህ በፊት ኢህአዴግ በአገር ቤት ለሚገኙ ሰላማዊ የትግል መንገድ ለሚከተሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ ጥሪውን የተቀበሉ ፓርቲዎች መካከልም ሰማያዊ እና መድረክ ለድርድር ከተቀመጡ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ከድርድሩ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላስ እንዳለፈው ጊዜ አቋርጣችሁ ላለመውጣት ምን ማረጋገጫ አለ? ለሚለው የሰንደቅ ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ የሽዋስ ‹‹አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በብዙ መስዋዕትነት ከዚህ እንደተደረሰ ዶክተር አብይ ያውቃሉና እንዳለፈው ዓመት ተመሳሳይ ቀልድ ውስጥ ይገባሉ የሚል እምነት የለንም፡፡ ነገሮችን ለመለወጥ ከእውነት ንግግር ያደርጋሉ የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ዋናው ነገር ገና ሂደቱን ሳናየው ከወዲሁ መፍረድ አይቻልም፡፡ በእኛ እምነት ግን እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ዶክተር አብይ ድልድይ ሆነው በግልጽ ለመነጋገር ዝግጁ ይሆናሉ ብለን እናስባለን፡፡ ተግባራቸውን አይተን የምንወስነው ይኖራል›› ብለዋል፡፡ ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ፓርቲያቸው እውነተኛ እና ሃቀኛ ድርድር ከቀረበለት ለጥሪው ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን እንዳለፈው ጊዜ ያለ ከሆነ ግን አሁንም ጥሪውን ላለመቀበል እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
386 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 896 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us