የመደመር ፖለቲካ፤ በጅግጅጋ

Wednesday, 11 April 2018 14:30

 

“የተፈጠረው መፈናቀል፣ ሞት፣ እና ጉዳት በጊዜው ማስቆም ባላመቻላችን በእጅጉ እንፀፀታለን”

አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር

“ሁላችንም ነው የከሰርነው፤ አንዳችንም አላተረፍንም”

አቶ ለማ መገርሳ

“ከአሁን በኋላ በኛ መካከል ጸብ ከተፈጠረ ትራክተር መዋዋስ ላይ፣ ዶዘር መዋዋስ ላይ መሆን አለበት”

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ

በሳምሶን ደሳለኝ

መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራ ከፍተኛ የፈዴራል መንግስት ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት ጉብኝት አድርጓል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር፣ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ፅ/ቤት ሐላፊ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ለማ መገርሳ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖች በጉብኝቱ ተካተዋል። በጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው ገራድ ውልዋል ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ሲደርሱም ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሶማሌ ክልል የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ማድረጋቸው ከሁሉም በላይ ለሰላም የሰጡትን ቦታ አመላካች ነው። እንደሚታወቀው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች በኢትዮጵያ ውስጥ በልማት፣ በደህንነትና በፀጥታ ያላቸው ፋይዳ ምትክ አልባ ነው። ካላቸው የህዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋትም ከወሰድነው፣ በክልሎቹ ውስጥ ሰላም ያለውን ዋጋ ለመገመት ብዙም ከባድ አይደለም።

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ በሁለቱ ክልሎች መካከል በአስከፊነቱ እና በመጥፎነቱ የሚጠቀስ የሕዝብ መፈናቀል እና የዜጎች አሰቃቂ ሕይወት ሕልፈት የተስተናገደበት ከመሆኑ አንፃር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልሎቹን ወደ ሰላም በመመመለስ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ጨዋታ ለማውጣት መወሰናቸው ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው፤ ፋይዳም እንደዚሁ ከፍተኛ ነው።

በዚህ ጽሁፍ የኦሕዴድ እና ሶሕዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ያወጡትን የሰላም አቋም መግለጫ፤ የሶማሌው ክልል ፕሬዚደንት ለእንግዶቻቸው ያቀረቡትን ንግግር ይዘት በተመለከተ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አቅርበነዋል። እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደነት የአቶ ለማ መገርሳን ገዢ ኃሳቦች አስፍረነዋል።  

በዲሴምበር 02 ቀን 2018 የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከኢትዮ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ሶማሌ እንዲመለሱ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

የኢሶህዴፖ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎች በጅግጅጋ ከተማ ባደረጉት የጋራ የምክክር መድረክ መነሻ፣ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በሙሉ ወደ ኢትዮ ሶማሌ እንዲመለሱ የስብሰባው ተሳታፊዎች በሙሉ ድምፅ መወሰናቸው መገለፁም ይታወቃል።

በማዕከላዊ ኮሚቴው የተሰጠው ውሳኔ፣ የተፈናቀሉትን ወገኖች ወደ ቄያቸው የመመለስ ተግባር (መግለጫው በተሰጠብት ጊዜ ለመመለስ ሥራዎች) ሙሉ ኃላፊነቱን የክልሉ መንግስት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት እና የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎች እንደሚወስዱ ተገልፆ ነበር። በተያያዘም፣ በተጨማሪም የሰላም መድረኮችን በመፍጠር በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ችግር የመቅረፍ እና የሁለቱን ክልል ህዝቦች የማቀራረብ ስራ በመስራት   ህገመንግስቱን የማስከበር እና የመጠበቅ ስራ እንደሚሰራ ይፋ አድርገው ነበር።

 

 

 

ጥር 29/05/2010 ዓ.ም የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአስር ቀናት በአዳማ ከተማ በነበረው የግምገማ ውይይት ባወጡት መግለጫ፣ “ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት በመመለስ እንደ ወንድማማች ሕዝቦች የባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እንዲመራ ጊዚያዊ ችግሮችን ፈተን ለዘላቂ የጋራ ጥቅሞቻችን በወንድማማችነት መንፈስ እንድንረባረብ የሶማሌም ይሁን ሌሎች ብህሔር ብሔሰቦች በኦሮሞ ባህልና የገዳ ስርዓተ ባስተማረን መልኩ በፍቅርና በአብሮነት እንዲኖሩ ለማስቻል ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ” ማቅረቡ የሚታወቅ ነው።

መግለጫው አያይዞም፣ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ዜጎች ካለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ በማስቻል በፍትህ ስርዓቱና በፖሊሲ ስርዓታችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉ ሁለንተናዊ ሪፎርም ማከናወን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ መደረሱን ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው ላይ ማስፈሩ የሚታወስ ነው።

 

 

የሶማሌ ክልል ፕሬዝደነት አቶ አብዲ መሐሙድ ኡመር፣ “በርግጥም የሰጡን ትኩረት ለህዝቦች ያለዎትን ክብር፣ የጉብኝትዎ ፍጥነት ደግሞ ለሀገራችን አንድነት እና ለህዝቦቿ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለመሥራት የገቡትን ቃል እንደሚተገብሩ ተስፋ አሳድሮብናል” ሲሉ ነበር ተስፋቸውን ያስቀመጡት።

የጠፋው ሰላም በባለቤቶቹ ለመፍታት መታቀዱ ያለውን ልዩነት ሲያስቀምጡ፣ “ጉብኝቱ ቤተሰብ እና ወንድማማች ከሆነው የኦሮሚያ ክልል ጋር ያጋጠመንን አሳዛኝ፣ የሚቆጭና መቼም ቢሆን ማጋጠም የሌለበት፤ እንዲሁም ግጭቱን ለመፍታት ዝግጁ በሆንበት ወቅት ላይ መሆኑ፣ እንዲሁም ችግሩን ተጋግዘን እና ተያይዘን ለመፍታት ሃላፊነት ያለባቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ወንድሜ አቶ ለማ መገርሳ፣ የክልሉ አመራሮች እና የተከበሩ አባ-ገዳዎች ያካተተ በመሆኑ ደግሞ ከተስፋ ባለፈ ችግሩን ለመፍታት ብርታት ይሆነናል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንኳን ደስ አልዎት ያሉበት መንገድ አስገራሚ ነበር፣ “…ምክንያቱም በክቡርነታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ውስጥ የምናየው የሁላችን የሆነችውን ኢትዮጵያችን የዛሬ ስኬት፣ የነገ ብሩህ ተስፋ እና ለሁሉም ልጆቻችን እኩል ክፍት የሆነ ተመሳሰይ እድል መኖሩ ነው። …ትናንት ከትግራይ አድዋ እና ከደቡብ ወላይታ ላደገ ኢትዮጵያዊ ክፍት ሆኖ ያየነው ትልቅ ሀገርና ህዝብ የመምራት እድል፣ እነሆ ዛሬ ደግሞ ከኦሮሚያ አጋሮ በቅሎ በኢህኣዴግ ጉያ ስር ላደገውና ለአመራር የበቃው ኢትዮጵያዊ ልጃችን እዉን ሆኖ በማየታችን ነው።”

ኢትዮጵያንም ከፍ አድርገው ያሳዩበት ዕይት ትኩረት የሰባ ነው፣ “የታየው ሰላማዊና ጨዋ መተካከት ኢትዮጵያችን እና ኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ስልጣኔያችንና የዛሬ ህዳሴያችንን የሚመጥን ማንነት የተላበስን መሆናችን ደግሞ የተመሰከረበት ነው።” ያሉት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን ስኬትና ውድቀት የገዢው ፓርቲና የአጋር ድርጅቶች ስኬትና ውደቀት አድርገው ያቀረቡበት መንገድ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተሰራውን ሴራና የስልጣን ጥምን ያየ፤ በሕዝብ ስልጣን አይጫወትም” የሚያስብል ነው። ፕሬዝደንቱ እንዳስቀመጡት፣ “የእርስዎ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ስኬት የኢህአዴግ ስኬት ነው። የእርሶ ስኬት የእኛ የኢሶህዴፓ ስኬት ነው። የእርሶ ስኬት የኢትዮጵያችን እና የሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ስኬት ነው። ከዚህ በመነጨ ከዛሬዋ እለት አንስተን የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሰላም፣ ልማት፣ ደህንነት፣ እኩልነት ብሎም ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ አንድነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግስት፣ የክልሉ ፓርቲ እና የክልሉ ህዝብ በቁርጠኝነት እንደምንሰራ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ሁለተኛ እድል ድርጅታቸው እንደሌለው አስረግጠው አስቀምጠዋል።

ፕሬዝደነት አብዲ መሐመድ ኡመር ኢትዮጵያ በአስማት ዛሬ ላይ አልደረሰችም። ከእኛም ብዙ የሚጠበቁ ሥራዎች አሉ በሚል አንደምታ የትላንትናውን፣ ዛሬ ላይ ለማረም በሚመስል መልኩ እንዲህ ነበር ያስቀመጡት፣ “ሀገራችን ኢትዮጵያ እና እኛ፤ ሉአላዊነታችንና ነፃነታችንን አስከብረን ለዘመናት በመዝለቅ ለዛሬ የበቃነው በአጋጣሚ አይደለም። ለዚህ የበቃነው፣ በዛ ያሉ ተከታታይ ትውልዶች ወረራን መክተው እና አፈናን እምቢ ብለው ባደረጉት ተከታታይ ተጋድሎና ትግል ነው። በዚህ ሂደትም አብሮነታቸውን እና መተማመናቸውን የፈተነ ችግር ሳይጋጥማቸው ቀርቶ አይደለም። ችግሮቻቸውንና ልዩነታቻቸዉን በፍቅር እና በአንድነት ቆመው ማለፍ በመቻል ነው”፣ ያሉት።

ኢትዮጵያዊ የሆነው በምርጫችን ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ፣ “የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ በታሪክ ካሊ ተብሎ በሚታወቀው ቀበሌ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የመረጠበት ቃል-ኪዳን ከገባበት ጊዜ አንስቶ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በመሆን ለሀገሩ ነፃነትና ሉአላዊነት ብሎም ለብሄራዊ መብቱና እኩልነቱ ታግሏል። በህይዎት፣ በአካል እና በሀብት መስዋአትነት ከፍሏል። ይህን ኢትዮጵያዊ እምነቱንም ሆነ ትግሉን ዳረኛ ተደርጎ ሲገፋም ሆነ ኢትዮጵያዊ ታማኝነቱ በገዥዎች ሲጠረጠር አውልቆ አልጣለዉም” ሲሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ የማይናወጥ አቋም በኢትዮጵያ ሶማሌ ትውልዶች ውስጥ እየተሸጋገረ መዝለቁ አስምረውበታል።

 

ከ1983 እስከ 2000 ዓ.ም ከምስራቅ ኢትዮጵያ ወደ መሐል ሀገር ይተም የነበረውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴና የሽብር መረብ በጋራ ጥረት ማምከን መቻሉን ሲገልጹ ፕሬዝደንቱ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “በኢህአዴግ መሪነት እዉን ከሆነው የሽግግር መንግስት አንስቶ እስከ 2000 አ.ም ድረስ የተለያዩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ክልሉን ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያችንም ለማተራመስ ያደረጉትን ሰፊ ሙከራ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ግንባር ቀደም ሆኖ በመሰለፍ ከሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ከከሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጋር በጋራ ተቀናጅቶ ድባቅ መቷል” ሲሉ ከምስራቅ ይመጣ የነበረው የደህንነትና የፀጥታ ሥጋት የተወገደበትን መንገድ ከፍ አድርገው አሳይተዋል። ይህም በመሆኑ አሉ፤ “ሕገ-መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ጠብቋል፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ደህንነትና ሰላም ተረጋግጦ ልማታቸው እንዲፋጥንና ለህዳሴያችን እንዲሰሩ ዘብ ሆኗል፤ ሆነናል” ብለዋል።

ተያያዥ ደህንነትና የሰላም ውጤቱን ሲያስቀምጡ፣ “ክልሉም ከፖለቲካ ውጥረትና አለመረጋጋት ነፃ በመሆን ሰፊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድ፣ የዉኃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እዉን ማድረግ ችሏል። የክልሉ ተወላጆችም ለክልሉ ልማት እንዲሰሩ እና ለኢትዮጵያችን ጥብቅና እንዲቆሙ ያስቻለ ሰፊ የዲፕሎማሲና የህዝብ ግንኙነት ስኬቶችም ተመዝግበዋል” ብለዋል። ስለዚህም፣ “የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የኢትዮጵያ የደህንነት ሥጋት ከመሆን የደህንነቷና የሰላሟ መከታ ወደ መሆን ሊሸጋገር በቅቷል። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ዘንድ ኢትዮጵያዊነት በክብርና በኩራት ባደባባይ የሚላበሱት ማንነት፣ በልብ ውስጥ የተቀመጠም ጠንካራ እምነት ሊሆን በቅቷል” ሲሉ የክልል ሕዝብ በኢትጵያዊነት ላይ ያለውን የማይናወጥ ፅናት አሳይተዋል።

ፕሬዝደንቱ በተለይ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያለውን ቁርኝት ያሳዩበት መንገድ፣ “ረጅም በሆነ ታሪካዊ፤ ቤተሰባዊ፤ ባህላዊ፤ ሀይማኖታዊ እና ድንበር ተጋሪነት ላይ የቆመው ልዩ ቁርኝት ደግሞ ከኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ወንድምና እህቶቹ ጋራ ያለው ግንኙነት ነው። ይህ ቁርኝት ድርቅና ረሀብ ያላሸነፈው፤ ጭቆና እና አፈና ያልበጠሰው፤ የሥጋና የነብስ ቁርኝት ነው” ያለን ሲሉ ነው የገለጽት።

አያይዘውም፤ ከወራቶች በፊት የተከሰተውንና ይህም በቤተሰብና በእምነት ደረጃ የተገነባ የህዝቦቻችንን ትስስር የፈተነ ያልተፈለገ ግጭት ዳግም በማይመለስበት መልኩ ልንሻገረው ይገባል። ለታሪክም ሆነ የህዝቦቻችንን የማይነጣጠል የሁሉ ቀን ህይወት እና የልጆቻችን መጪ እድል ስንል ልንሻገረው እንሻለን። ይህም እውን እንዲሆን ክልብ በመነጨ ንፅህናና ሆደ ሰፊነት ቂም በቀልን በይቅር ባይነት፤ ወቅታዊ እልህን በአርቆ አሳቢነት ተክተን በአፈጣኝ ለጋራ መፍትሄ አብረን እንደምንቆም በክልሉ መንግስት፣ ህዝብና ፓርቲ ስም ቃል እንገባለን።

ከሁሉ በላይ ለእርቅ ግማሽ መንገድ ዝግጁ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ፣ ለደረሰው ከዚህ በፊት ደጋግመን እንደልነው፤ የተፈጠረው መፈናቀል፣ ሞት፣ እና ጉዳት በጊዜው ማስቆም ባላመቻላችን በእጅጉ እንፀፀታለን። ተቃቅፈን ይቅር ተባብለን ከትናንት በመውጣት የተሻለ ነገ እንገነባ እንላለን” ሲሉ ጸጸታቸውን እና ቀጣይ ተስፋቸውን አስረግጠው ለተሰብሳቢ አስታውቀዋል።፡

ፕሬዝደንቱ፣ ከእርቅ እኩል ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮችም እንዳሉ አሳስበዋል። “ሁለቱን ህዝቦች ለዘላቂ አብሮነትና ሰላም ለመብቃት ዋናው ልማትን ማረጋገጥ ነው። ክልሎቻችን አርብቶ አደር የሚበዛበት ከመሆኑ አንፃር የዉኃ አቅርቦትና ልማት ዋነኛው ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ ውጪ በክልሎቹ የተናጥል አቅም የሚሳካ አይደለም። ከዚህ በተያያዘ በምክትል ጠ/ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራዉን ጥራትና የጋራ ልማት ኮሚቴ በማጠናከር ፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ክቡር ጠ/ሚኒስትራችንን በሁለቱ ህዝቦች ስም በአክብሮት እጠይቃለው” ብለዋል።

የኦሮምያ ክልል ፕ/ት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ከፕሬዝደንቱ እና ከተሳታፊዎች ያለውን የሰላም ቁርጠኝነት ከተቀበሉ በኋላ ከኦሮሚያ ክልል ስለተፈናቀሉ የሶማሌ ክልል ተወላጆች የሰጡት የሰላም ዋስትና እና ተነሳሽነት የብዙዎችን ተሳታፊዎች ያረጋጋና ቀልብ የገዛ ነበር፤ እንዲህም ነበር ያሉት፣ "ከኦሮምያ ክልል የተፈናቀሉ ወንድም ሶማሌዎችን አብዲ መሃመድ እንኳን ጣልቃ ሳይገባ በራሴና በግሌ ኃላፊነት ወስጄ ወደ ቀድሞ ቦታቸውና ቤታቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን" የሚል ቁርጠኛ አቋም ነበር።

አቶ ለማ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ችግሮቹን ነቅሰውም አስቀምጠዋል፣ “ብዙ የተሰሩ ስህተቶች፣ የተፈጸሙ ጥፋቶች በመካከላችን አሉ፡፡ በግለሰቦች የተፈጸሙ ስህተቶች አሉ፡፡ እነዚህን ስህተቶች አርመን አብሮነታችን ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡ በዚህ ችግር ኦሮሞና ሶማሌ ብቻ ሳይሆን ሀገራችንም ነው የተከዳችው እንጂ ማንም የተጠቀመ የለም፡፡ አንድ ሳንቲም የተጠቀመ የለም፡፡ ሁላችንም ነው የከሰርነው፡፡ በታሪካችን ማየት መስማት የማንፈልገው ነገር ነው በመካከላችን ጥቁር ጠባሳ የጣለብን፡፡”

ስለሆነም አሉ አቶ ለማ፣ “እኔን ዛሬ ካለነው አመራሮች በላይ ኦሮሞና ሶማሌ በሚገባ ይተዋወቃል፡፡ ባሕላዊ ተቋማት አላቸው፡፡ ችግሮቻቸውን የሚነጋገሩባቸው ቋንቋዎች አሏቸው፡፡ ከመንግስት በበላይ የሆኑ አባ ገዳዎች አሉ፡፡ ወርቅ ባሕል፤ ችግሮች የሚፈቱ፣ በሶማሌ ሕዝቦች ኡጋዞች፣ ሱልጣኖች አሉ፡፡ ችግር እንዴት እንደሚፈታ በሚገባ የሚያውቁ፡፡ ስለዚህ ይህ ለመንግስት የሚተው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ከአብዲና ከለማ በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔና አብዲ የኮንትራት አገልግሎት ነው የምንሰጠው፡፡ መንግስትም ቢሆን የኮንትራት አገልግሎት ነው የሚሰጠው፣ ዘላለም የሚኖር መንግስት የለም፡፡ ዘላለም የሚኖር ካለ የኦሮሞና የሶማሌ ወንድም ህዝቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ በአንድ ሰሞን የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ዘላለም ዘላቂ የሕዝቦቻችን አንድነት አብሮነት ወንድማማችነት ሊበላሽ አይገባም፡፡”

አያይዘውም፣ በታሪካችን ኦሮሞና ሶማሌ በውሃና በግጦሽ አልፈ አልፎ ይጋጭ ነበር፡፡ ሲጋጩም ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ይታረቁ ነበር፡፡ ኑሯቸውንም ይቀጥሉ ነበር፡፡ ዛሬ በደረስንበት ደረጃ እውነት መተሳሰቡ ቢኖር ለአርብቶ አደሮቻችን የምንኖርባት መሬት አላጠረችም፡፡ መተሳሰቡ ቢኖር የሶማሌ ወድማችን ሕዝብ ኦሮሚያ ውሃ መጠጣት ይችላል፡፡ ስንቱን ተጠቅመንበት ነው ዛሬ መሬት የምንጋፋው፡፡ መሬት አጠረ? ያለንን መሬት ተጠቅመንበት ነው.. ያለንን አልሰራንበትም፡፡ ባልሰራንበት መሬት ክብር የሆነው የሰው ሕይወት ለማጥፋት፣ ለማድማት ንብረት ለማውደም ምክንያት መሆን የማይገባቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህንን ያህል ጥፋት ሲያደርስ፣ ለእኛ ውርደት ነው፡፡ የተፈጠሩት ችግሮች አሳዝነውናል፣ ጎድተውናል፡፡ የማስተካከሉ አቅሙና ብቃቱ ስላለን የተፈጸመውን ጥፋት ማስተካል አለብን፡፡ የእኔ መልክት ይህ ነው” ሲሊ ቀጣይ የሰላም አማራጭ ብቻ እንዳለ አመላክተዋል፡፡

ጠ/ሚ ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው፣ "...ኦሮሞን እንደምትወዱ ኦሮሞም እንደሚወዳችሁ ታሪካችን በሙሉ ይናገራል። ያንን ፍቅራችን አድሰን በመሃል የገጠሙንን ችግሮች ፈተን ወደ ፊት እንደምንራመድ በኔ በኩል ከፍተኛ እምነት ነዉ ያለኝ” ሲሉ የተሰብሳቢውን የሰላም ፍላጎት በመደገፍ አብሮ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

አያይዘውም ጠ/ሚ፣ “የሁለቱ ክልል የሰላም ኮንፈረንስ መጀመር አለበት ላላችሁት ክቡር አቶ ለማ እንዳሉት በአስቸኳይ መጀመር አለበት። ከአሁን በኋላ በኛ መካከል ጸብ ከተፈጠረ ትራክተር መዋዋስ ላይ፣ ዶዘር መዋዋስ ላይ መሆን አለበት። በልተን ሳንጠግብ ለትራክተር ማዋል ያለብንን ጉልበትና ገንዘብ ለጥይት ማዋል ተገቢ ስላልሆነ ያለን ሀብት፣ ያለን ጉልበት ሁሉ ወደ ልማት፣ ወደ ሰላም እንዲመለስ ኮንፈረንሱም ያስፈልጋል፤ ከኮንፈረንሱ በላይ ክቡር አቶ ለማ እንዳሉት በመካከላችን የኛን ችግር ለመፍታትና መንገድ ማሳየት የሚችሉ ትላልቅ ሰዎች ስላሉ እነዚህ አካላት በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት ህዝቦችን ለማቀራረብ፣ አንድ የማድረግ እና ሁሉ ሀሳባችን ልማትና ሰላም እንዲሆን በኮንፈረንሱም ሆነ ከኮንፈረንሱ ዉጪም እንደሚሰሩ ያለኝን እምነት ልገልጽላችሁ እወዳለሁ" ብለዋል።

በመጨረሻ መጠቀስ ያለበት በሁለቱ ሕዝቦች መቀራረብ ሰላም የነሳቸው ኃይሎች ፕሮፖጋንዳ የደረሰበትን ደረጃ ያመላከቱን እና እምነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተሰማቸው አንድ የሶማሌ ሽማግሌ ያሉትን ማስፈር ተገቢነቱ ከፍ ያለ ነው፤ "ልጄ ፈጣሪ ይህን ያብዛልህ። ጠላቶች የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆነ የሶማሌ ሕዝብ አለቀለት እያሉ ሲያሟርቱ፣ አንተ ግን የመጀመሪያውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ክልላችን አደረከው። የሶማሌ ሕዝብ አብሮህ የሚቆሞ መሆኑን እናረጋግጣለን።" ሲሉ ስጋታቸው በሰላም አጋር ጠቅላይ ሚኒስትር መቋጨቱን አስረግጠው ለተሰብሳቢ ልብ በሚነካ አገላለጽ አስቀምጠውታል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
491 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 959 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us