“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህር ዳር ሲገቡ በመከላከያ እና በፖሊስ ኃይሎች አጥረው አስቀመጡን”

Wednesday, 02 May 2018 13:00

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህር ዳር ሲገቡ በመከላከያ እና በፖሊስ ኃይሎች አጥረው አስቀመጡን”

አቶ አበባው ጌትነት

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ

የአማራ ተወላጆች ተወካይ

 

በይርጋ አበበ

 

527 አባውራዎች ከእነ ሙሉ ቤተሰባቸው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ያቀኑ ሲሆን አሁንም ድረስ ጉዳያቸውን መፍትሔ የሚሰጥ እንዳላገኙ ይናገራሉ። በቅርቡ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ከአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተቀበሉት ዶክተር አብይ አህመድ በሹመታቸው ዕለት ለኢትዮጵያ ህዝብ የገቡት ቃል ኪዳን፣ “ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በመረጡት የአገራችን ክፍል ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸው ሊከበር ይገባል፤ ከዚህ በኋላ መፈናቀል አይኖርም” የሚል ነበር። በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በተፈጠረ “የአመራሮች ግጭት” ከመቶዎች በላይ ህዝብ የተፈናቀለ ሲሆን ዶክተር አብይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ ወደ ሶማሌ ክልል መቀመጫ አቅንተው ከክልሉ ባለስልጣናትና “የተመረጡ ታዳሚዎች”ጋር ባካሄዱት ውይይት እንገለፁት “የተፈናቀሉትን የኦሮሚያ ተወላጆች በክልላችን ለማስፈር ሞክረን ነበር። ነገር ግን የሚቻል አልሆነም ምክንያቱም የሰዎቹ ፍላትና ስነ ልቦና ከሶማሌ ክልል ወንድም እና እህቶቹ ጋር በጣም የተዋሀደ በመሆኑ ነው” በማለት የተፈናቀሉት ወደነበሩበት ቀዬ እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ሊከናወን እንደሚገባ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መፈናቀል ይቅር የተፈናቀሉትም በአስቸኳይ ወደ ቀደመ ቀያቸው ይመለሱ” ብለው ማሳሰባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ተመሳሳይ ችግሮች አሉብን ያሉ ከአማራ ክልል ሌላ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች ለሰንደቅ ጋዜጣ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ 20 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ከኖሩበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መሰደዳቸውን ይናገራሉ። ሆኖም በዚያ አካባቢ ለመቆየት የሚያስችል ምንም ነገር ስላነበረ ወደ ባህር ዳር ማቅናታቸውንና በባህር ዳርም በተለምዶ “አባይ ማዶ” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን (ቅዱስ ገብርኤል) ተጠልለው እንደሚኖሩ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ “ጉዳያችንን መንግስት እንዲያይልን ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በአካልም በደብዳቤም አቅርበን ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ይናገራሉ። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉትን ወገኖች ቅሬታን በመወከል ለሰንደቅ ጋዜጣ ያቀረቡት አቶ አበባው ጌትነት የተባሉ የተፈናቃዮች ተወካይ ናቸው። ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ቃለ-ምልልሱን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅላችሁ እንደመጣችሁ ገልጸውልናል። ለመሆኑ ስንት ሰዎች ናችሁ የተፈናቀላችሁት? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛላችሁ?

አቶ አበባው፡- ህጻናትንና ሙሉ የቤተሰብ አባላትን ሳይጨምር አባውራዎች ብቻ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለን የመጣነው ሰዎች ቁጥራችን 527 ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። የንብረት ባለቤት የነበርን ትጉህ አርሶ አደሮች ዛሬ የዕለት ምግብ ለማግኘት የሰው እጅ እያየን ነው የምናድረው። በአንድ ግቢ ውስጥ ተሰብስበን ውለን የምናድር ሲሆን በታጣቂ ነው የምንጠበቀው። ከአካባቢው ውጡ ተብለን ብዙ ጊዜ ወከባ ሲደርስብን ቆይቷል። አሁን አንተን ከማናገሬ በፊትም እኔን ጨምሮ ስምንት የተፈናቃዮች ተወካይ አስተባባሪዎችን ባህር ዳር ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አስረውን አድረው ነው የተፈታነው። ለጊዜው የምንገኘው ባህር ዳር አባይ ማዶ ከሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እያደርን ያለነው። ከዚያ እንዳናድርም የባህር ዳር ኮማንድ ፖስት የቤተክርሰቲያኑን አስተዳዳሪዎች ሳይቀር ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ቤተክርስቲያኗ ግን እስካሁን ፊቷን አላጠቆረችብንም።

ሰንደቅ፡- ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሄዳችሁ ሰዎች ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ችግር ይደርስባችሁ እንደነበረ እና ተመሳሳይ መፈናቀል ደርሶባችሁ ነበር ይባላል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ አበባው፡- የተባለው ትክክል ነው። እኔ ለምሳሌ እኖርበት በነበረው ከማሺ ዞን ጅጋፎ ወረዳ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰትና በእኩልነት አለመዳኘት ችግር ይደርስብን ነበር። ለምሳሌ ፍርድ ቤት ሄደህ ርትዕ ፍርድ ማግኘት አይታሰብም፤ በአመራሮች የመበደል እና ሌሎች የመብት ጥሰቶችም ይደርሱብናል። ከዚህ በፊትም በ1995 እና 2003 ዓ.ም ተፈናቅለን ነበር። በ1995 ዓ.ም ስንፈናቀል በኦሮሚያ ክልል ተጠግተን ከቆየን በኋላ ተመልሰን ወደ መኖሪያ ቀያችን ገባን። እንደገና በ2003 ዓ.ም በተፈጠረ ግጭት ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደን ተጠግተን ከቆየን በኋላ ተመለስን። በሁለቱም ጊዜ በደረሰብን መፈናቀል ንብረቶቻችን ሙሉ በሙሉ ወድመውብናል ከውድመት የተረፈውንም ተዘርፈናል። በተለይ በ2003 ዓ.ም በአንድ ወረዳ ይኖር የነበረ 8 ሺህ ህዝብ ነበር የተፈናቀለውና ንብረቱም ቤቱም የወደመበት።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ መፈናቀል ከተፈጠረ በኋላ በሁለቱ ክልል አመራች መካከል ውይይት በማካሄድ መፍትሔ አልተቀመጠም ነበር?

አቶ አበባው፡- በ2003 ዓ.ም በነበረው መፈናቀል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ አያሌው ጎበዜ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዙ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ነብሳቸውን ይማርና አቶ አህመድ ናስር ሁለቱ ኃላፊዎች ተናበቡና ‹‹የተፈናቀሉት ሰዎች በሙሉ ከእኔ ክልል ከሆነ የተፈናቀሉት ማረጋገጫ ካላቸው እንደገና ወደነበሩበት ቀየ ተመልሰው እንዲሰፍሩ አደርጋለሁ›› ሲሉ አቶ አህመድ ናስር ቃል መግባታቸው የሚታወቅ ነው። በዛን ጊዜ የነበሩት አስመላሽ ኮሚቴ አሁን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰማ ጥሩነህ አስተባባሪነት ወደ ቦታው እንድንመለስ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን የአማራ ክልል መንግስት ተመልሰን የሰፈርነውን ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳለን ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልነበረም። ይህን ባለማድረጉ ደግሞ ሁልጊዜም በእኛ ላይ የመብትና የነጻነት ጥቃት የሚፈጽሙብን የአካባቢው ባለስልጣናት ጫና ይበልጥ በረታብን። ያላግባብ እና ያለ ደረሰኝ የመሬት ግብር ክፈሉ እንባላለን፤ እኛም ለመኖር ስንል እንከፍላለን። በአጠቃላይ በአገራችን እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረን ነው ስንኖር የቆየነው።

ሰንደቅ፡- በዚህ ዓመት ደግሞ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ ነው ከአካባቢው የተፈናቀላችሁት። የአሁኑ ችግር መነሻ ምክንያቱ ምን ነበር?

አቶ አበባው፡- በሁለት ወጣቶች መካከል ግጭት ተፈጠረ። ግጭቱ የተፈጠረው ከአንድ የክልሉ ተወላጅ እና ከአማራ ክልል በሄደ ወጣት መካከል ነበር። በግጭቱም የቤኒሻንጉል ጉሙዙ ተወላጅ ይሞታል። ግጭቱ የተነሳው በተራ ውንብድና ቢሆንም ወደ ጎሰኝነት ቀይረው ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ቀኑን ሙሉ ግጭቱ እና ማሳደዱ በረታ። በዚህ ሂደት ውስጥም 14 ሰዎች ሲሞቱ የዘጠኙ ስርዓተ ቀብር ተፈጽሞላቸዋል፤ የአራቱ ግን አስከሬናቸው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ስለገባ ሊገኙ አልቻሉም ነበር። እኔ ባለኝ መረጃ 139 ቤቶች ሲቃጠሉ ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

እንደምታውቀው ጥቅምት ወር አዝመራ የሚደርስበት ወቅት ቢሆንም ዓመቱን ሙሉ የደከምንበት ሰብል (አኩሪ አትር፣ ሰሊጥ፣ ቦቆሎ…..) ሳይሰበሰብ ሜዳ ላይ ቀርቷል። የነገርኩህ 527 አባውራዎች ከነሙሉ ቤተሰባቸው ምንም ንብረትና ሀብት ሳይዙ ህይወቱን ለማትረፍ ሊፈናቀሉ ችሏል።

ሰንደቅ፡- መፈናቀሉ ከደረሰ በኋላ ወደ አማራ ክልል አምርታችሁ ምን አደረጋችሁ?

አቶ አበባው፡- እንደነገርኩህ ነብሳችንን ለማረፍ ማቄን ጨርቄን ሳንል ከመኖሪያ ቀያችን የተፈናቀልን ሰዎች ወደ አማራ ክልል ሄድን። በአማራ ክልል ምግብ ዋስትና ሜካናይዜሽን ጎንደር ቅርንጫፍ በመሰባሰብ ከመንግስት ተገቢውን እርዳታ እና የሰፈራ ፕሮግራም እንድናገኝ ጠይቀን ነበር። በዋናነት እኛ አስተባባሪዎች የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዷለምን እና ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ያነጋገርናቸው። አቶ ገዱን ስናነጋግራቸው “የእናንተ ጉዳይ የሚፈታውም ሆነ መኖር የምትችሉት ክልል ስድስት (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል) ስለሆነ በድጋሚ ሄዳችሁ እንድትሰፍሩ ነው የሚደረገው” ሲሉ መልስ ሰጡን። እኛም በበኩላችን ወደነበርንበት ክልል ተመልሰን እንደማንሄድ አጥብቀን ተከራከርን። ምክያቱም በተደጋጋሚ መፈናቀልና ግጭት ሲደርስብን ስለቆየ አሁንም ዋስትና በሌለው መልኩ ልንመለስ አይገባም” ብለን ስንነግራቸው እሳቸውም መልሰው፤ “ወደ ነበራችሁበት ክልል የማትሄዱ ከሆነ ወደተወለዳችሁበት ቀየ መሄድ ትችላላችሁ እንጂ ከመንግስት ምንም አይነት እርዳታ ልታገኙ አትችሉም። ምክንያቱም ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይገኛል፡ ይህን ሁሉ ህዝብ ተፈናቅሎ በመጣ ቁጥር አስፍረን ማኖር አንችልም። ስለዚህ ሊሆን የሚገባው ወደነበራችሁበት ክልል ተመልሳችሁ እንድትኖሩ እንጂ እርዳታ ማቅረብም ሆነ ማስፈር አንችልም። ልትጠይቁ የምትችሉትም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን እንጂ እኔን አይደለም ምክንያቱም እናንተን አላውቃችሁም›› አሉን።

በዚህ ንግግራቸው በጣም ነው የተከፋነው። ምክንያቱም ኑሯችን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይሁን እንጂ ባለንበት ክልል ሰርተን ከምናፈራው ሀብት ላይ በተቋቋመ ኮሚቴና ጽ/ቤት በኩል ለአልማ (አማራ አቀፍ ልማት ማህበር) እና ለብአዴን (ለብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) በየዓመቱ ገንዘብ ስናዋጣ የኖርን ሰዎች ነን። ይህ ለእኛ የደህንነት ዋስትና ሊሆን አይገባም ወይ? ብለን ጥያቄም አቅርበንላቸው የነበረ ቢሆንም መልስም ሳይሰጡንና ንግግራችንንም በወጉ ሳያዳምጡን ‹‹ስብሰባ አለብኝ›› ብለውን ትተውን ገቡ።

ሰንደቅ፡- በእሳቸው ንግግር መሰረት ወደ ወላጆቻችሁ ቀየ ሄዳችሁ ለመኖር አልሞከራችሁም? ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንመለስም ያላችሁበት ምክንያትስ ምንድን ነው?

አቶ አበባው፡- አቶ ገዱ መልስ በኋላ ወደ ነበርንበት ሰፈር ሄደን ከባህር ዳር ህዝብ ጋር ተቀላቅለን በተቀመጥንበት በኮማንድ ፖስት የታገዘ ሀይል ወዳለንበት ቦታ በመምጣት ‹‹ከአቶ ገዱ መልስ ተሰጥቷችኋል፤ ስለዚህ ወይ ወደነበራችሁበት ክልል ሂዱ ወይም ደግሞ ወደ ወላጆቻችሁ ቀየ ተበተኑ›› ነበር ያሉን። ለምሳሌ እኔ ትውልድ ቀየዬን ለቅቄ ከወጣሁ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖኛል። ሌሎቹም ከእኔ በላይ ለሆነ ጊዜ ከትውልድ ቀያቸው ተለይተው የኖሩ ናቸው። ታዲያ እንዴት አድርገን ነው ወደማናውቀው የወላጆቻችን አገር ሄደን የምንሰፍረው? የአካባቢው አስተዳዳሪዎች አያውቁን፤ ለመኖሪያ የሚሆን መሬት በሌለበት ሁኔታ ምን ሰርተን ልንኖር ነው የምንሄደው? ብለን መልስ ሰጠናቸው። በነገራችን ላይ አንዳንዶቻችን ቤተሰቦቻችን እንኳን አያውቁንም።

የኮማንድ ፖስቱ እና የክልሉ ጸጥታ ሀይሎች በሰጠናቸው ምላሽ ተበሳጭተው “በፈቃዳችሁ የማትሄዱ ከሆነ ተገዳችሁ እንድትሄዱ ትደረጋላችሁ” ብለው ለማስፈራራት ሞከሩ። እኛም የፈለጋችሁትን አምጡ እንጂ ለጥያቄያችን መልስ ሳናገኝ ከዚህ ወደየትም አንሄድም ብለን በአቋማችን ጸናን። በዚህ ጊዜ የተፈናቃዮቹን ስምንት አስተባባሪዎች ጠርተው “የምግብ ዋስትና ኃላፊ በምግብ ጉዳይ ሊያነጋግራችሁ ይፈልጋል” ብለው ጠሩንና አፍነው ወስደው ባህር ዳር ከተማ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አሰሩን። ለአንድ ቀን ካሰሩን በኋላ አስፈራርተውና አስፈርመው ፈቱን። ነገር ግን ከተፈታን በኋላ የባህር ዳር አካባቢ ኮማንድ ፖስት አዛዥ አቶ ገደፋው መጥተው ከሰፈርንበት አካባቢ (ምግብ ዋስትና ጎንደር ቅርንጫፍ ግቢ) እንድንነሳ አደረጉን። ከዚያም ማደሪያ ስናጣ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሄደን የደብሩን አስተዳዳሪ ጠይቀን እዚያ እንድናድር ፈቅደውልን አደርን። ነገር ግን አሁንም ቤተ የክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እኛን ከደብሩ ለተጨማሪ ጊዜ እንዳያሳድሩ ጫና እና ትዕዛዝ ሰጥተዋቸው ስለነበር ለተጨማሪ ቀን እንዳናድር ተደረገ። ከዚያም ወደ ምግብ ዋስትና ግቢ ሄደን ስንሰፍር በፓትሮል መኪና የተጫኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እያመጡ ሲያስፈራሩን ለቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ግቢው ውስጥ እንድናድር እንዲፈቅዱልን ልመና አቅርበን ፈቃደኛ ስለሆኑልን እዛው ነው ያለነው።

ወደ ሁለተኛው ጥያቄህ ልምጣልህና ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመመለስ የማንፈልግበት ምክንያት አንደኛ ነጻነታችን ሁልጊዜም እየተረገጠ ነው የምንኖረው፤ ከዚያም አልፎ የንብረት ውድመት ስለደረሰብን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በሞት ያጣን ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ። እንደዚህ እየሆንን በዚያ ቦታ መኖር አንችልም ምክንያቱም የክልላችን መንግስት (የአማራ ክልል ማለታቸው ነው) ለእኛ ደህንነት ሊከራከርልንና መብታችንን ሊያስጠብቅልን አልቻለም። ለዚህ ነው ወደዛ አንሄድም ብለን አቋም የወሰድነው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት በእናንተ ላይ ‹‹ደን ይመነጥራሉ፣ ጦረኛ ናቸው እና በአካባቢው ተወላጅ ላይ ስድብ ይሰነዝራሉ›› የሚል የሚቀርብባችሁ ውንጀላ ነበር። ለመሆኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስትኖሩ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ያላችሁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ አበባው፡- አንተ ያልከውን ውንጀላ አውቀዋለሁ፣ እንዳልከው ከዚህ በፊት የተነገረ ነው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ሀሰትና በሬ ወለደ ወሬ ነው። ይህን የሚሉት ለክስ እና ለአንዳንድ ነገር ማጭበርበሪያ እንዲመቻቸው ነው። በእርግጥ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ስንኖር በተለያየ መንገድ ተከባብረን የምንኖር ሰዎች ነበርን። ጫና የሚደረግብን ከአመራሩ ነው። አሁንም ይህ ችግር የደረሰብን የወረዳው አመራር እስከ ታች ድረስ ያለው ካቢኔ ህዝቡን በመቀስቀስ ነው እርምጃ እንዲወሰድብን ያደረጉት። ስለዚህ እኛ እንኳን ስድብ ልንሳደብ ይቅርና ከመጥረቢያ፣ ማጭድና የመሳሰሉት የእርሻ መሳሪያዎች በስተቀር ማንኛውንም ነገር (ዱላም ሆነ የጦር መሳሪያ) ይዘን መንቀሳቀስ አንችልም። በመንግስት የስራ ኃላፊነት በኩልም ካየን ከእኛ ከአማራውም ሆነ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች እና ከሌሎቹ ብሔረሰብ የተወለደ ሰው ስልጣን ላይ የለም። ሁሉንም የመንግስት ኃላፊነት የያዙት የክልሉ ተወላጆች ብቻ ናቸው።

ደን ጨፈጨፉ ለሚለው ጥያቄህ ስመልስልህ፤ ደኑን የሚጨፈጭፉት የዚያው የክልሉ ተወላጆች ናቸው። መሬቱ በእነሱ እጅ እንጂ እኛ የምናርሰውን መሬት ሙሉ በሙሉ የምናገኘው ከእነሱ በኪራይ እና በአበል እየተኮናተርን ነው። ስለዚህ የመሬት ባለቤት ባለመሆናችን በዚህ ጉዳይ ልንወቀስ አይገባንም።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትነት ስልጣን ሲወጡ “ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው በመረጡት አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመስራትና የመኖር መብታቸው ሊከበር ይገባል፤ መፈናቀልም ይቁም” ሲሉ ተናግረው ነበር። እናንተ አሁን ካላችሁበት ሁኔታ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለችግራችሁ መፍትሔ አመላካች አይሆንም ይላሉ? ንግግሩንስ እንዴት አዩት?

አቶ አበባው፡- እኔ ይህንን ንግግር የተመለከትኩት ለመድረክ የፕሮፓጋዳ ፍጆታ እንጂ ይፈጸማል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ዶክተር አብይ ባህር ዳር በመጡ ሰዓት እኛ እዚያው ነበርን። ከእሳቸው ጋር እንዳንነጋገር ሆን ተብሎ ገና ሊመጡ አንድ ቀን ሲቀራቸው ጀምሮ የምንኖርበት አካባቢ በፖሊስና በመከላከያ ታጥሮ ከእሳቸው ጋር እንዳንገናኝ መብታችን ተነፍጎ ነበር። ከባህር ዳሩ ጉዞ ውጭም እኔ የተፈናቃዮቹን ጉዳይ ይዤ ጽ/ቤታቸው ድረስ በመሄድ በዝርዝር ጽፌ አስገብቼ ነበር። ስደውል የሚሰጠኝ ምላሽ ግን እስካሁን አልታየም ሲያዩት መልሱን ደውለን እናሰውቅሃለን የሚል ነው። እና እሳቸው የተናገሩት ነገር ተግባራዊ የሚሆን ቢሆን ኖሮ ይህ የእኛ ጉዳይ እስካሁን ሳይዘገይ ታይቶ መልስ ይሰጠን ነበር። ለዚህ ነው ተግባራዊ ይሆናል ብዬ እምነት ያልጣልኩበት።

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እኔ አላውቃችሁም ብለውናል ሲሉ ነግረውናል። እናንተ ደግሞ ከክልላችን ውጭ ብንኖርም የአማራ ክልልን መንግስት ልማት በመደገፍ በኩል የድርሻችንን ስንወጣ ቆይተናል ብላችኋል። ስለዚህ እናንተ ከስርዓቱ ጋር ችግር የለባችሁም ማለት ይቻላል?

አቶ ጌትነት፡- ከመንግስት ጋር የፖለቲካ ችግርም ሆነ ልዩነት የለንም። እኛ ትግላችን ከድህነት እና ከርሃብ ጋር እንጂ ከመንግስት ጋር በፖለቲካ ጉዳይ አንነካካም። ምክንያቱም የኢህአዴግ መንግስት ደጋፊ እና የብአዴን አባል ነን። ከአምስት እና ስድስት ዓመታት በላይ ለብአዴን የገበርንበት ደረሰኝ አለን። ለአልማ ገንዘብ እናዋጣለን። ብአዴን ለሚሰራቸው የክልሉ ልማቶች የማናዋጣው ገንዘብ የለም። ስለዚህ ይህን ሁሉ ስራ የምንሰራው ከብአዴን ጋር ሆኖ ሳለ የፖለቲካ ልዩነትና ችግር አለባችሁ የሚለውን አልቀበለውም። የመብት ጥሰትና ችግራችንን አድምጦ መፍትሔ የሚሰጠን አጣን ነው እያልን ያለነው። ይህን ችግራችንን ደግሞ ብአዴንም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አይተው መፍትሔ እንዲሰጡን ነው የምንጠይቀው። የባህር ዳር እና አካባቢው ህዝብም ለዕለት ችግራችን የሚችለውን እንዲያደርግልን በአጽኦት እጠይቃሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
663 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1025 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us