የኢሕአዴግ ሥራአስፈፃሚ እና ምክር ቤቱ፤ በጠ/ሚ አብይ ሕዝባዊ ውይይቶች ወደ ተባበረ ድምፅ ይመለስ ይሆን?

Wednesday, 02 May 2018 13:04

 

ላለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሥርዓተ-መንግስቱ፣ ገዢው ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ አስፈሪና ሀገር በታኝ ሥጋቶች ተደቅነውበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው። አሁን ላይ አንፃራዊ ሽግግር የሚመስል መረጋጋት አዝማሚያ ያላቸው አመላካች ነገሮች እየተስተዋሉ ናቸው። ከሁሉም በላይ እነዚህ ሶስት ዓመታት ክቡር የሆነውን የዜጎች ሕይወትን ቀጥፏል። በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የልማት አውታሮች እንደቀላል ነገር በጠራራ ፀሐይ ወድመዋል።

በሀገራችንም ሳያበቃ በምስራቅ አፍሪካና በዓለም ዓቀፉ ሕብርተሰብ ከነበረው ግዙፉ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ችግር አንፃር ኢትዮጵያ የመበተን እድል እንዳላት ሥጋታቸውን ሲያሰሙ ነበር። በተለይ በቀንዱ ሀገሮች ያሉ መንግስታት ጠንካራ የመንግስትነት መሰረት እንደሌላቸው በስፋት ስለሚታመን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው አለመረጋጋት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለመገመት እንኳን አዳጋች ነበር።

ሌላው በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተቀጣጠለው የለውጥ ፍላጎት የተለያየ ትርጉም እየተሰጠው ባለቤቱም በውል ሳይታወቅ ለያዥ ለገናዥ እስከሚያስቸግር ድረስ የተሄደበት ርቀት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን ለመገመት አስቸጋሪ ነበር። በተለይ በማሕበራዊ ሚዲያው ሁሉም ተንታኛ በታኝ ሆኖ የተሰለፈበት መስመር ለፖለቲካ ጡዘቱ የነበረው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ሌላው የኢሕአዴግ ድርጅቶች ሊቀመናብርት በጋራ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰጡት የልዩነትና የአንድነት መግለጫ፤ የገዢው ፓርቲን ውስጣዊ የፖለቲካ ግለትን ልዩነቶች ነፀብራቅ ነበሩ። እንደሕዝብ “ዋስትና” የሚሰጥም መግለጫ አልነበረም። በርግጥም ለግንባሩ ሊቀመንበር ለመምረጥ የነበረውን መተጋገል ለተመለከተ ሰው፣ ውስጣዊ ቀውሳቸው ሕዝቡን እንደረበሸው አውቀው መጠነኛ ማርከሻ ለማስቀመጥ የሰጡት መግለጫ እንደነበር መረዳት ተችሏል።      

የድርጅቱ ሊቀመንበር የተመረጠበትን አግባብ ፕሮፌሰር መድሐኔ ታደሰ እንዳስቀመጡት፣ “የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት መታየት ያለበት፤ እንደከዚህ ቀደሙ በተባበረ ድምፅ፣ በውስጥ ድርጅታዊ ቀመር ወይም በስምምነት ወይም በሹመት ሁሉም ድርጅቶች ያመጡት አመራር አይደለም፤ በውስጥ ትግል የመጡ አመራር ናቸው። በውስጥ ፍልሚያ ላይ የውጭ ተጽዕኖ ተጨምሮበት ነው። ይህም ሲባል ኦሕዴድ የራሱን የኃይል ማዕከልና መሰረት ተጠቅሞ፣ የሕዝቡን ብሶት ተጠቅሞ፣ ግጭቶቹን ተጠቅሞ፣ በድርጅቱ ውስጥ በፖለቲካና በግምገማ የበላይነት ሳይቀዳጅ እንደውም እያቀረቀረ ቆይቶ፤ በምርጫ አሸንፎ ለስልጣን የበቃ ኃይል ነው። ለዚህም ነው በተለየ መንገድ የተገኘ ስልጣን የሚሆነው። የተለያዩ ታክቲኮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጠቅመው ያገኙት ሥልጣን ነው” ብለዋል።

የፕሮፌሰሩ ገለፃ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አሕመድ በቀጥታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነውም ተሹመዋል። ይህም ሲባል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በፓርቲያቸው አብላጫ ድምጽ የተመረጡ እንጂ በሕዝብ በቀጥታ የተመረጡ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደሉም። ምክንያቱም በፓርላሜንታዊ የመንግስት ቅርጽ-ሥርዓተ መንግስት፣ መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ እንጂ፤ ግለሰብ አይደለም። የሚመረጠውም ፓርቲ እንጂ፤ ግለሰብ አይደለም።

ባልተለመደ መልኩም ገዢው ፓርቲ በሕዝብ ጫና ውስጥ የወደቀበትን ነባራዊ ሁኔታዎችንም ተመልክተናል። ከገዢው ውስጣዊ ሕገ ደንብ በላይ የገዘፈ የህዝብ ግፊት አስተውለናል። የድርጅቱ ሊቀመንበር ምርጫም ባልተለመደ መልኩ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ አግኝቷል። ከሁሉም በላይ ገዢው የነበረው እውነታ ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲያቸውን አጥር ወይም አሰራር ሕዝቡ ተሻግሮ ዳግም በአደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መቀበሉን አረጋግጧል።

ባልተለመደ መልኩም ኦሕዴድ እና ብአዴን ላይ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው የሕዝባዊ መሰረት ውክልና ጥያቄ በከፍተኛ መጠን ሕዝባዊ መሰረት የያዘበት ሁኔታም ተፈጥሯል። ከዚህ በፊት ከአራቱ እህት ድርጅቶች የማሕበራዊ መሰረት ጥያቄ የማይቀርብበት የነበረ እና ለሌሎቹም ድርጅቶች ዋስትና የነበረው ሕወሓት መሆኑ አሻሚ አይደለም። ዛሬ ላይ ግን ኢሕአዴግ ከመቼውም የበለጠ ማሕበራዊ መሰረት እንዲኖረው ያስቻለ አጋጣሚ አግኝተዋል።

ከላይ ለመነሻ የቀረቡት ሃተታዎች አጠቃላይ ስዕል ባይሰጡም የተወሰነ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ናቸው። በዚህ ጽሁፍም ከፖለቲካ መተጋገል በኋላ ባገኘናቸው ውጤቶች መነሻ፣ በአብላጫ ድምጽ የድርጅቱን ሊቀመንበር የመረጠው ምክር ቤት በተባበረ ድምጽ ወይም ወደቀድሞ የድርጅቱ ባሕሎች በመመለስ ድርጅቱን እና ሊቀመንበሩን ወደ መቀበል እና የተባበረ ድጋፍ ለማቅረብ ያለው እድል ምን ይመስላል? የሚለውን ለመፈተሸ ነው።

አንዱ፤ ምክንያት በልዩነት ውስጥ የሚቀርብ ድጋፍ ወይም ጥርጣሬ ሊያስከትል የሚችለውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ በቅጡ ካልተገነዘቡት፤ ወደ አዲስ የፖለቲካ መተጋገልና ትርምስ ውስጥ ይዟቸው እንደሚገባ ለማወቅ የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አይጠይቅም። የሀገሪቷን የመጨረሻ ስልጣን መቆጣጠር፣ በርግጠኝነት የነበረውን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ይቀይረዋል። የሚቀየረው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ በመተማመንና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ጨዋታው ወደ አዳኝና ታዳኝ መቀየሩ አይቀሬ ነው።

የአዳኝና የታዳኝ ፖለቲካ ጨዋታ ችግሩ በፖለቲካው ፓርቲ ላይ የሚቀር ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ለሕዝብ ዳግም ያለመተማመን እና የመጠራጠር ምንአልባትም፣ እንደሀገር የመቀጠል ስጋት መደቀኑ ሳይታለም የሚፈታ ነው። ገዢው ፓርቲ ወደቀድሞ የተባበረ ድምጽ መመለስ ከቻለና በተለይ የዶክተር አብይ ሕዝባዊ ድጋፍን የልዩነታቸው መፍቻ ቁልፍ አድርገው ከተጠቀሙበት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ ቢደረግ ሁሉም ተገቢነቱን በመቀበል ለውጡን የድርጅቱና የአባላቶቹ አድርጎ ይወስደዋል።

ሁለተኛው፤ ከሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙትን የህዝብ ጥያቄዎች ወደ ፖሊሲ ለመቀየር ገዢው ፓርቲ በተባበረ ድምጽ ውስጥ መገኘት ይጠበቅበታል። ግዙፉ የድርጅትና የመንግስት አጀንዳዎችን ለመቅረጽ ሆነ ለማስፈጸም በልዩነት ውስጥ የተቀመጠ ፓርቲ ሊተገብረው አይችልም። ውጤቱም፣ አብላጫ ድምጽ ያለው ገዢ፤ አናሳ ድምፅ ያለው ተገዢ የሚሆንበት የፖለቲካ መድረክና ቅርጽ ያለው ፓርቲ ይሆናል። በተለይ በውስን የፖለቲካ ፕሮግራሞች የተዋቀረው ኢሕአዴግ ለሁለት የሚሰነጠቅበት እድል ሰፊ ነው የሚሆነው።  

ሶስተኛው፤ ተራማጅ እና በእድሜ የገፉ ኃይሎች የሚመስል በአንዳንድ መድረኮች ሲንፀባረቁ ተሰምተዋል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም በሃምሳዎቹ እድሜ ስልጣን መልቀቅ ሲወደስ፣ የእድሜ ባለጸጎቹ አሁንም በፓርቲው ውስጥ “አልወጣም” ብለዋል በሚል የመድረክ ሽንቆጣ ተደቁሰዋል። ይህ አቀራረብ ከሕዝባዊ ውይይቱ ድጋፍና ሳቅ ተችሮታል። በውስጠ ፓርቲ መተጋገል ውስጥ ሊያስከትል የሚችለው የፖለቲካ ዋጋ በቅጡ ተጢኖ መድረኩ ላይ የተሰነዘረ አይመስልም። ወይም በቀላል አማርኛ ውስጣዊ የፖለቲካ መተጋገሉ “በተራማጅ” እና “በተቸነከሩ” ኃይሎች መካከል አድርጎ የማቅረብ የመድረክ ፖለቲካ ይመስላል። ይህ በራሱ ገዢው ፓርቲ የቀድሞ የፖለቲካ አመራሮችን ከፖለቲካው ውስጣዊ መተጋገል ጋር ብቻ አያይዞ ለማቅረብ መሞከሩ፣ ትርጉሙ ከባድ ነው። ምናልባትም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያምን አስተዋፅዖ ለመግለጽ የነባሩን አመራር አስተዋፅዖ ለማሳነስ መሞከር አደገኛ አካሄድ ነው። አቶ ኃ/ማሪያም በፍላጎታቸው ስልጣናቸውን ስለመልቀቃቸውም ከሚናገሩት ግለሰቦች ውጪ፤ መረጃ የለም። እንዴት እንደለቀቁም “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉ።

አራተኛው፤ የፕሮፌሰር መድሃኔን ገልፃ ማቅረቡ ተመራጭ ነው። ይህም ሲባል ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፣ “የድሮዎቹ አቶ መለስ የነደፏቸው የኢሕአዴግ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አቋሞች በርግጠኝነት እንደነበሩት ይቀጥላሉ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ምክንያቱም በመለስ ውርስና በኢሕአዴግ የሃሳብ አንድነት ላይ ልዩነቶች አሉ። ይኸውም፣ ከብሔር ጥያቄ ይነሳል፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይመጣል፣ ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ሊመጣ ነው? ምን ዓይነት ሥርዓተ መንግስት ሊመጣ ነው? ምን ዓይነት የውጭ ዝምድና ሊመጣ ነው? ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊመጣ ነው? የሚሉትን ስንመለከታቸው፤ አንድ አይነት የሃሳብ አንድነትና ስምምነት እንደድሮ ይቀጥላል ማለት አይቻልም። የዶ/ር አብይ ተስፈንጥሮ መውጣት ኢህአዴግን ለድርጅት ማንነት ቀውስ ዳርጐታል። የግድ ማንነቱን ማስተካከል ሊኖርበት ነው።” ብለዋል።

እነዚህ ሥርነቀል የፓርቲ ይዘትና ቅርጽ የሚቀይሩ ጥያቄዎችን በአብላጫ ድምጽ በማግኘት ብቻ የሚታለፉ ተደርገው የሚወሰዱ አይደለም። ምክንያቱም፣ የአፈፃጸም ጥያቄዎች ሳይሆኑ የአራቱም ፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍና ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። የመንግስት ቅርጽን ጭምር የሚቀይሩ ናቸው። ከግንባሩ የመውጣት ውሳኔዎችም ሊያስመዝዙ የሚችሉ ጥያቄዎች ናቸው። በምንም መመዘኛ በተባበረ ድምጽ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ናቸው። ስለዚህም፣ አደጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ ማግኘት የሚገባው ነው።

ስለዚህም “በአጠቃላይ ሲታይ አዲስ ያልረጋ ጅማሮ ነው የሚመስለኝ። አሁንም የሃሳብ አንድነት፣ የድጋፍ አንድነት ስለሌለ ሁሉም ነገር በቀላሉ ይራመዳል ማለት አይደለም። የተለያዩ የኃይልና የአስተሳሰብ ማዕከላት መኖራቸው አይቀርም። የኃይል ማዕከላት ብዝሃነት እየተፈጠረ ነው። በመንግስት ስልጣን ውስጥም የአመለካከትና የኃይል አሰላለፉ ማዕከሎች መኖራቸው አይቀርም። አሁን ያለው ሽግግር ጅማሮ ነው እንጂ በደንብ ድጋፍ ያገኘ መሰረቱ የጠነከረ ለውጥ ነውም ማለት አይቻልም። በመገዳደር የመጣ የለውጥ ጅማሮ ነው ካልን፣ ለውጡ ሊዘልቅ የሚችለው በትግል (Political Contestation) ነው ማለት ነው። ለውጡን ተከትሎ ያለው የኃይል ዝምድና የተለያዩ የኃይል ማዕከላት እርስ በእርሳቸው የሚገዳደሩበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። እንደቀድሞ ከላይ እስከታች በቁጥጥር ስርዓትና አመለካከት ጥራት፣ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ ድርጅቱን ቀጥ አድርገህ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እያየህ የሚጓዙበት ሁኔታ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አይኖርም” ሲሉ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ በፖለቲካ ትንተናቸው አስቀምጠውታል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ እና ምክር ቤቱ፣ ለድርጅታቸውና ለመንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ሕዝቡ ከሰጣቸው ቅቡልነት አንፃር ቀጣይ ጉዟቸውን ፈጥነው ወደ ተባበረ ድምጽ ገብተው ፓርቲውን ለማዳን ካልሰሩ፣ ከሆነው ያልሆነው ይበልጣል ብለው የሚሰጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በጣም ብዙ ናቸው። አበው እንደሚሉት፣ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ…።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1415 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1020 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us