“መንግስት በአማራው ህዝብ ላይ እየፈጸመ ላለው የዘር ማጽዳት ወንጀል በህግ ሊጠየቅ ይገባል”

Wednesday, 09 May 2018 13:31

“መንግስት በአማራው ህዝብ ላይ እየፈጸመ ላለው

የዘር ማጽዳት ወንጀል በህግ ሊጠየቅ ይገባል”

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ‹መኢአድ)

በይርጋ አበበ

 

ከ1983 ዓ.ም የስርዓት ለውጥ በኋላ በኢትዮጵያ ከታዩ የአስተዳደር ለውጦች አንዱ እና ቀዳሚው ‹‹ፌዴራላዊ ስርዓት›› መገንባቱ ነው። ይህ ፌዴራላዊ ስርዓት ግን ‹‹ማንነትን በተለይም ብሔርን እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ›› ስለሆነ በዜጎች መካከል አለመተማመንን እና መጠራጠርን አስከትሏል ሲሉ የሚተቹ ወገኖች ትችታቸውን መስጠት የጀመሩት ገና ከስርዓቱ ምስረታ ጀምሮ ነበር። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ‹‹የአገሪቱ የቆዩ ችግሮች አስተማማኝ መልኩ ለመፍታት ትክክለኛ እና አማራጭ የሌለው ስርዓት ይህ ብቻ ነው›› ሲል ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ይሞግታል።

 

 

የመግለጫው ይዘት በአጭሩ

የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ሳይሆን ፌዴራሊዝሙ የተመሰረተበትን ‹‹ቋሚ መሰረት›› አጥብቀው የሚተቹት ወገኖች ከሚቀርቧቸው ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ‹‹ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ የሚለያይ እና ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ውድመት የዳረገ መፈናቀል አስከትሏል›› በማለት ነው። የዚህ ሃሳብ አቀንቃኝ ከሆኑት ወገኖች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት›› ድርጅት ሰሞኑን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ስለተፈናቀሉት የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ስለደረሰው ‹‹መጠነ ሰፊ›› ችግር ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል። መኢአድ በመግለጫው ‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዘር እና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ እና ስርዓት ባጣ የጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት ወዳልተፈለገ የእርስ በእርስ ግጭትና መፈናቀል እያመራች ትገኛለች›› ሲል ይገልጻል።

ፓርቲው አያይዞም ‹‹በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ መጠነ ሰፊ የማፈናቀል የዘር ማጽዳት እና ሀብት ንብረታቸውን የመዝረፍ ተግባር እየተፈጸመ ይገኛል። ዜጎች በክልሉ ሲኖሩ ህጋዊ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እና ግብር ሲከፍሉበት የነበረ ደረሰኝ ያላቸው ናቸው›› ሲል የተፈናቃዮችን የቆየ ኑሮ አስታውሷል።

በቅርቡ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞን የተፈናቀሉ አማራዎች በባህር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው የሚኖሩ ሲሆን የዕለት ቀለብም ሆነ ልብስ የሌላቸው ሲሆን ጎሮሯቸውን የሚዘጉትም ከከተማው ነዋሪ እና አንዳንድ በጎ ፈቃደኛ ድርጅቶች ከሚያደርጉት ድጋፍ ነው። በዚህ በኩል በተለይ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋዎች እና የዳሽን ባንክ ሰራተኞች ያደረጉት ድጋፍ የሚጠቀስ ነው። ክልሉን የሚያስተዳድረው ብአዴን ለተፈናቃዮቹ ያደረገውን ድጋፍ በተመለከተ ‹‹ምንም ነው›› ሲል የገለጸው መኢአድ ‹‹የፌዴራል መንግስቱም ሆነ የአማራውን ብሔር እወክላለሁ የሚለው ብአዴን ችግሩን በቸልተኝነት መመልከቱና አፋጣኝ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ተፈናቃዮችን በማዋከብ፣ በማሰርና በማፈን በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ጉዳት እያደረሰ ይገኛል›› ብሏል።

መኢአድ ለተፈናቃዮች መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያስቀመጠውን ሲገልጽም ‹‹ብሔር ተኮር ማናቀልና ግድያ እንዲቆም ችግሩን ለመፍታት ይቻል ዘንድም አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉ ከሁለት ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆች አፈናቃዩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካሳ እንዲከፍል›› የሚሉት ይገኙበታል። ፓርቲው በዚህ ጉዳይ ላይ ጨምሮ በሰጠው የመፍትሔ ሃሳብ ላይ ‹‹ተፈናቅለው በባህር ዳር ቅዱስ ጊዮርስ ቤተ ክርስቲያን ለተጠለሉት ዜጎች የአማራ ክልል መንግስት ህጋዊ ከለላ በመስጠት ጊዜያዊ መጠለያ፣ ምግብ እና አልባሳት እነዲያቀርብ። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጋር በመነጋገር መፍትሔና ዘላቂ ዋስትና እንዲሰጣቸው መነጋገር›› ሲል አስታውቀዋል።

 

 

ትምህርት እና ተፈናቃዮች

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የተሰደዱት ኢትዮጵያዊያን የአማራ ብሔር ተወላጆች ቁጥራቸው ከ500 በላይ ቢሆንም እስካሁንም ድረስ ተገቢው ከለላ እና መፍትሔ ያልተሰጣቸው መሆኑን በሳምንት እትማችን መዘገባችን ይታወሳል። ከዘገባው በኋላ የተስተካከለ ነገር ካለ ስንል የተፈናቃይ ተወካዮችን አነጋግረን ነበር። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ከመንግስት በኩል የተደረገላቸው ድጋፍ አለመኖሩን ገልጸው ሆኖም የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል። በዚህ በኩል የዳሽን ባንክ ባህር ዳር ቅርንጫፍ ሰራተኞች እና የጎንደሩ ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ያደረጉትን ድጋፍ በአብነት አንስተዋል።

ለተፈናቃዮች አሁን ነገሮች እየከበዱ ቢሆንም ይበልጥ አሳሳቢ የሆነባቸው ግን የልጆቻቸው ‹‹ነገ›› ነው። ከተፈናቃይ ቤተሰብ የተወለዱ 108 ህጻናት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ይህ ደግሞ ድሮውንም አሳሳቢ በነበረው የአገሪቱ የትምህርት ጥራት መጓደል ላይ የህጻናቱ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው በበሰብአዊ መብታቸው ላይ የተቃጣ ድርጊት ሲሉ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡ ምሁራን ተናግረዋል።

ምሁራኑ አያይዘውም ‹‹ክልሉ በትምህርት ጥራት ውራ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከዓመት በፊት ባወጣው ዘገባ በክልሉ የትምህርት ሽፋን መልካም የሚባል ቢሆንም የትምህርት ተቋማቱ ደረጃ እና ትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል›› ያ ሲሆን፤ አክለውም ይህ በሆነበት ክልል እና ህዝብ ላይ ተጨማሪ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ መደረጉ ደግሞ የችግሩን ጥልቀት ይባስ ያባብሰዋል›› ብለዋል።

 

 

የተፈናቃዮች ሁኔታ

የአማራ ብሔር ተወላጆች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞን ሲፈናቀሉ ቁጥራቸው በአባወራ ደረጃ 527 ሲሆኑ ከእነ ልጆቻቸው ሲቆጠሩ ከሁለት ሺህ በላይ ደርሷል። ይህን ያህል ህዝብ በተፈናቀለበት ጊዜ 13 ሰዎች ሲሞቱ 49 ሰዎች ቆስለዋል። 149 ቤቶች ደግሞ መቃጠላቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡ የተፈናቃይ ተወካዮች ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጠው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፓርቲ በበኩሉ ‹‹መንግስት በአማራው ህዝብ ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል እየፈጸመ በመሆኑ በህግ ሊጠየቅ ይገባል›› ብሏል። ፓርቲው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ሲያስቀምጥም ከዚህ ቀደም ባሉት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመናት በአማራ ብሔር ተወላች ላይ ደረሰ ያለውን መፈናቀል እና መሳደድ በዋቢነት በማንሳት ነው። ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በ2004 ዓ.ም በደቡብ ክልል ጉራ ፋርዳ ወረዳ፣ ቀደም ሲል ደግ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባዎች መፈናቀልና መሳደድ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ መድረሱን አስታውሶ ‹‹ይህ በብሔሩ ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል ነው›› ብሎታል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
672 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 949 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us