የዶክተር አብይ ሰሞንኛው የፖለቲካ ውሳኔዎችና አካሄዶች

Wednesday, 16 May 2018 13:30

 

·        ከኦዴግ ጋር ድርድር፤ ከአማራ ብሔር ተወላጆች ጋር ምክክር

በይርጋ አበበ

       ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አስኳሉ ህወሓት የተቀዳበት ምንጭ የማርክሲስት ሌኒንስት ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ርዕዮተ ዓለም ነው። ይህን የተናገረው ደግሞ ራሱ ፓርቲው ሲሆን ገና በትግል ላይ ሳለ ይፋ ያደረገው። በወቅቱ ባወጣው ማንፌስቶውም ማሌሊት (ማርክሲስት፣ ሌኒኒስት ትግራይ) እንደሆነ ሲያስታውቅ በወቅቱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት የህወሓትን ርዕዮተ ዓለም አስመልክቶ ከአንድ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ጋር በ1968 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ህዝቡ ማርክሲስት ሌኒኒስትን ይቀበለው አይቀበለው የማውቀው ነገር የለም። ነገር ግን ከታጋዩ አብዛኛው አባል ይቀበለዋል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

       ይህ ፓርቲ ራሱን በጦር ሜዳ ድል እና ሎጂስቲክ እየጠነከረ ሲሄድ “ታግሎ ያታገላቸው” የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ይህንን ርዕዮተ ዓለም ተቀብለው የተቀላቀሉ ሲሆን የገዥው ፓርቲ ፕሮግራምም የህወሓት የትግል ፕሮግራም ነው እየተባለ ይነገራል። ፓርቲውም ቢሆን የፕሮግራም ለውጥ ማድረጉንም ሆነ አለማድረጉን ያስታወቀው ነገር ባይኖርም አገሪቱን ላለፉት 26 ዓመታት እና ከዚያ በላይ ጊዜያት ሲገዛ የሚከተለው ፕሮግራሙን አለመቀየሩን ያሳብቃሉ። አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሌላው ዓለም በአብዛኛው የሚጠቀስ ርዕዮተ ዓለም አይደለም። ይህን ርዕዮተ ዓለም ዶክተር መረራ ጉዲና ሲገልጹትም “ከምዕራቡና ከምስራቁ የተዳቀለ የራሱ ማንነት የሌለው” በማለት ነው። የምስራቁ ርዕዮተ ዓለም ደግሞ በባህሪው “ወዳጅ” ወይም “ጠላት” ብሎ የመፈረጅ ባህሪ የተላበሰ ሲሆን አገራትን ሲገልጻቸው እንኳን “ወዳጅ አገር ወይም ጠላቶቻችን” በማለት ነው።

         ኢህአዴግም ባለፉት 26 ዓመታት ተኩል ጉዞው በአገር ውስጥ ከሚፎካከሩት ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት ፍረጃን የተከተለ መሆኑን የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው “በህወሓት ሰማይ ስር” በሚለው መጽሃፋቸው አስፍረውታል። በኢህአዴግ በጠላትነት ከተፈረጁ ፓርቲዎች መካከል “አርበኞች ግንቦት ሰባት እና ኦነግ” የተባሉ ድርጅቶች ናቸው። ሁለቱ ድርጅቶች “አሸባሪ” ተብለው “የተፈረጁ” ሲሆን ከእነዚህ ሁለት ድርጅቶች ጋር በግልም ሆነ በድርጅት ግንኙነት መፍጠር በጸረ ሽብር ህጉ ያስጠይቃል። ያ አዋጅ በአቶ መለስ ጊዜ የወጣ ሲሆን አቶ ኃይለማሪያም ወንበሩን ከተረከቡብ በኋላም “የመለስን ሌጋሲ አስቀጥላለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ ሁለቱ ፓርቲዎች ከአሸባሪነት እንደተፈረጁ ቆይተዋል።

       አቶ ኃይለማሪያም በአገሪቱ የተፈጠረው ችግር እንዲበርድ የመፍትሔው አካል ለመሆን “ራሳቸውን” ከስልጣን ካወረዱ በኋላ በቦታቸው የተሰየሙት ዶክተር አብይ አህመድ ግን በበዓለ ሲመታቸው ዕለት በሰጡት ዘለግ ያለ መግለጫቸው “ከአገር ውጭ ሆነው ስለ አገራቸው የሚቆረቆሩ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ወገኖቼ አብረን ለመስራት መንግስታችን ዝግጁ መሆኑን ስገልጽላችሁ በደስታ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ሰሞኑንም በአቶ ሌንጮ ለታ ለሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራክ ግንባር (ኦዴግ) መንግስት ጥሪ አቅርቦለታል። ኦዴግም ጥሪውን በደስታ ተቀብሎታል።

       ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ (ቢበዛ ሶስት ዓመት) የአማራ ብሔርተኝነት እየጎለበተ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቀጣይ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል አሳሳቢ መሆኑን የሚናገሩ አሉ። የአማራ ብሔርተኝነት ጉዳይ ለፖለቲከኞችና ለምሁራን ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለመንግስትም ሌላ የቤት ስራ ሆኖ መቅረቡን ተከትሎ መንግስት ጉዳዩን በምን መልክ መያዝ እንዳለበት ለመምከር ዶክተር አብይ አህመድ ከብሔሩ ተወላጆች ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግስት መክረዋል። ዶክተር አብይ እና መንግስታቸው ሰሞኑን በሁለት የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በቀናት ልዩነት ያካሄዷቸውን ድርጊቶች እንመለከታለን።

 

 

የኦሮሞ ፖለቲካ ከትናንት እሰከ ዛሬ ረፋድ

       ከሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ኦህዴድ፣ ኦፌኮና ኦዴግ ድረስ ያሉ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በብሔሩ ፖለቲካ ላይ የበላይነትን ለመውሰድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። በትግል ወቅት በለስ ቀንቶት ከኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ጋር አራት ኪሎ ገብቶ እስካሁን የቆየው ኦህዴድ ብቻ ይሁን እንጂ ኦነግም የሽግግር መንግስቱ መስራች ነበር። በብዛት ከደርግ የተማረኩ ወታደሮች የመሰረቱት ኦህዴድ ቀስ በቀስ ራሱን እያሳደገ አሁን ካለበት ደረጃ ይድረስ እንጂ በክልሉ ህዝብ እና በብሔሩ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ወቀሳ ሲያስተናግድ መቆየቱ ይታወሳል። ከኦነግ ጋር በነበረው የፕሮግራምና የዓላማ ልዩነት አንደኛው ገዥ ሌላው ተቃዋሚ ሆነው የቆዩት ሁለቱ ወገኖች አሁን ኦነግ የፕሮግራምና የትግል ስልት ለመቀየር ውሳኔ ላይ የደረሱ ፖለቲከኞች ካዋቀሩት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ጋር በጋራ ለመስራት በመንግስት በኩል ጥያቄው ቀርቦ አሜሪካ ላይ የመጀመሪያው ድርድር ተካሂዷል። ድርድሩን በተመለከተ መንግስት ለህዝብ ይፋ ባደረገው መግለጫ እንዳስታወቀው “ይህች አገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ቤት ናት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህችን ምትክ የሌላት ቤቱን ሰላሟን የመጠበቅ እና እንደዜጋም ያለ ገደብ የሚጠቀምበት ሙሉ መብት እንዳለው ይታወቃል” በማለት ነበር።

       ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ የድርድር ሙከራ ተካሂዶ ያለስኬት መጠናቀቃቸውን ያስታወሰው የመንግስስት መግለጫ፤ አሁን የተካሄደውን ድርድር በውጤት የታጀበ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ኦዴግም የመንግስትን ጥሪ ተቀብሎ አብሮ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን የገለጸ ሲሆን መንግስትም የኦዴግን ምላሽ በአድናቆት እንደሚመለከተው በመግለጫው አስታውቋል። “ድርጅቱ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ህገ መንግስቱን በማክበር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል። ይህ የግንባሩ አቋም በመንግስት በኩል በከፍተኛ አድናቆት ጋር ተቀባይነት አግኝቷል” በማለት የኦዴግን ውሳኔ የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣይ ሊካሄዱ ስለሚችሉ ጉዳዮች ሲስታውቅም፤ “ሀገር እና ህዝብን ባስቀደመ እና በሰለጠነ መንገድ የሚደረግን ውይይትና ድርድር መንግስት የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ሰላማዊ በሆነ መስመር መታገልም ውጤታማ ያደርገናል ብለው ከሚያምኑ አካላት ጋር በቀጣይም ውይይትና ድርድር ለማድረግ በጽኑ ይፈልጋል ለተግባራዊነቱም አበክሮ ይሰራል” ሲል ገልጿል።

     ይህን ውሳኔ እንዴት እንደሚመለከቱት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የንግድና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ተፈሪ በዛብህ፤ በበኩላቸው ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የእነ አቶ ሌንጮ ለታ ቡድን በህዝብ በተለይም በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ እምብዛም ነው። አጀንዳውን እንደ አገራዊ ጉዳይ ስንመለከተው ለእርቅና ለድርድር በር ከፋች ነው ብዬ አላስብም›› ብለዋል። ዶክተር ተፈሪ አክለውም ‹‹ኦህዴድ ቀደም ሲል በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከሚኖሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብረን እንሰራለን የሚል መግለጫ ሲያወጣ አብሮ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን ቀድሞ ገለጸው ይኸው የእነ አቶ ሌንጮ ቡድን ነበር። ስለዚህ ይህ ቡድን በእኔ ግምት ጥቅም ፈላጊ (ኦፖርቹኒስት) ይመስለኛል። ምክንያቱም ያኔም ምኑም ባልተረጋገጠበትና ባልተረጋጋበት ወቅት ጥሪውን የተቀበለ ቡድን አሁንም ጥሪውን ለመቀበል እንደማይቸገር ታውቃለህና›› ብለዋል። “ለዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ኢህአዴግ ከራሱ ሃሳብ ውጭ የሆኑ አስተሳሰቦችን መቀበል ሲችል ብቻ ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው” ሲሉም ሃሳባቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

የቤተመንግስቱ ግብዣ እና የአማራ ብሔርተኝነት

       ዶክተር አብይ አህመድ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ሽማግሌዎችን፣ ምሁራንን እና ታዋቂ ሰዎችን በኢዮቤልዮ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል። (በወቅቱ የመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ፊልም ቀራጭ ባለሙያ አለመገኘቱን ልብ ይሏል) የእራት ግብዣም ያደረጉላቸው ሲሆን እየጠነከረ ስለመጣው የአማራ ብሔርተኝነትም ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው መምከራቸውን የሰንደቅ ምንጮች ተናግረዋል። በተለይ የብሔሩ ተወላጆች ስለ አማራ ብሔርተኝነት እያደገ መምጣት በሰጡት አስተያየት ‹‹ከ 1983 ዓ.ም ጀምሮ አማራ በታሪኩ እንዳይኮራ፣ በኢኮኖሚ እንዳይጎለብት፣ በፖለቲካው እንዳይሳተፍ እና በማንነቱ እንዲሸማቀቅ ሆን ተብሎ በስፋት ሲሰራበት ቆይቷል። ይህን የመሰለ ብሶት ነው የአማራን ብሔርተኝነት ያመጣው›› በማለት የተናገሩ ሲሆን፤ በሽግግር መንግስቱ እና በህገ መንግስቱ መጽደቅ ወቅት አማራ ተወካይ እንዳልነበረውም በማውሳት ጭምር ብሔሩ ከፖለቲካው ስለተገፋበት መንገድ ተናግረዋል።

       ይህን ሁሉ አድምጠው መልስ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ‹‹ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት ያስፈልገናል። በተጎዳነው ልክ እርምጃ እንውሰድ የምንል ከሆነ አንለወጥም። ስለዚህ የይቅርታ መንፈስ ያስፈልገናል እንኳን እኛ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምም ይቅርታ ጠይቀው በሀገራቸው መኖር ይችላሉ›› ማለታቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል።

         በስብሰባው ላይ ታዳሚ የነበሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ “በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መነጋገራችን ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ያስታወቁ ሲሆን ስለነበረው ድባብ ሲናገሩ ደግሞ “ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ በዚህ መድረክም ስለኢትዮጵያነት፣ ስለመልካም ስነ ምግባር መዳበር አስፈላጊነት፣ ስለ አንድነትና ከልብ ይቅር ስለመባባል መሰረታዊ ጥቅም መሳጭ በሆነ ርትዕ አንደበታቸው መልእክት አስተላፈዋል›› ሲሉ ገልጸዋል። ምሁሩ አያይዘውም ‹‹የአማራ ብሔርተኝነት አስፈሪ እየሆነ ነውና እናንተ ምሁራን ከወዲሁ ልትገሩትና ሰከን ባለ መልኩ እንዲሄድ ልታደርጉት ይገባል ሲሉ ከሚያዝያ 12 እስከ 14 2010 ዓ.ም በባህር ዳር ለተሰበሰብነው የአማራ ምሁራን የተናገሩትን ትናንትም ደግመውታል›› በማለት ተናግረዋል።

       ሆኖም የግላቸውን አቋም ሲያስታውቁ ‹‹እውነት እላችኋለሁ የአማራ ብሔርተኝነት ለማንም ስጋት ሊሆን አይችልም›› ያሉ ሲሆን ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹ህወሓት ስትነሳ ጠላት በመፍጠር ነበር አማራ ጠላቴ ነው በማለት። የአማራ ብሔርተኝነት ግን የተነሳው ጠላት በመፍጠር አይደለም›› ብለዋል። ንቅናቄውን በጥርጣሬና በፍራቻ ከማየት ይልቅ የአማራ ብሔርተኝነት የተነሳበትን ምክንያት ማስታወሱን የመረጡት ዶክተር ሲሳይ ‹‹አማራ ባለፉት 27 ዓመታት ከሚገባው በላይ ሲገፋ፣ ሲሳደድ፣ ሲገደልና በአደባባይ ንብረቱ ሲዘረፍ ከጎኑ ቆሞ አይዞህ ያለው መንግስታዊም ሆነ ፖለቲካዊ አካል አልነበረም። የኢትዮጵያ አንድነት ሲፈርስ ‹ኢትዮጵያዊነትም አደጋ ላይ ወደቀ› ባለ ‹ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ› ወዘተ ተብሎ ተፈረጀ። አማራ እየተባለ በስሙ በሚጠራው ክልል ውስጥ የሚኖረው ህዝብ እንኳን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ በሁሉም የኢኮኖሚያና የማህበራዊ እንቅስቃሴ ወደኋላ ሲቀር እና በኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትና ወሊድ ቁጥጥርን በማስፋት ከሀገሪቱ አንደኛ እንዲሆን ተዳርጓል›› ሲሉ ገልጸዋል።

         ዶክተር ሲሳይ በወቅቱ ካነሱት ሃሳብ ላይ ሲጨምሩ ደግሞ ‹‹በአጠቃላይ ባለፉት 27 ዓመታት የአማራ ህዝብ ክብር፣ ሞራልና ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ፣ ታሪኩ እንዲዛባ የሚያደርጉ ስራዎች ነበሩ። ይህም ሊሆን የቻለው ባለፉት 43 ዓመታት ህወሓት በ1968 ዓ.ም አውጥቶ በስራ ላይ ባዋለው ማኒፌስቶ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው የትግራይን ሪፐብሊክ ለመመስረት ሲበል የአማራን ህዝብ በጠላትነት በመፈረጅ አበክሮ ይሰራበት ስለነበረ ነው። ይባስ ብሎ የህይወትና የጉልበት መስዋዕትነት ከፍሎ በገነባት አገሩ እየኖረ ባለፉት 27 ዓመታት የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈረደበት›› በማለት የአማራ ብሔርተኝነት የተነሳበትን ምክንያት አስቀምጠዋል።

     በአዲሱ የአማራ ብሔርተኝነት መነሳት ዙሪያ ባር ዳር ላይ ውይይት ያደረገው የብአዴን አመራርም ቢሆን የችግሩን መነሻ አምኖ መቀበሉን በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን “ለዴሞክራሲያዊ የአማራ ብሔርተኝነት መጎልበት ድርጅታችን ብአዴን ይሰራል” ሲል ይፋ አድርጓል።

       ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ፖለቲከኛ “የአማራ ብሔርተኝነትም ሆነ የኦዴግና የኢህአዴግ ግንኙነት ወደሰመረ መስመር እንዲመጣ ሁሉም ወገን በተለይም የጨዋታውን ሜዳ እና ኳስ በእጁ የያዘው ኢህአዴግ ወሳኝ ሚና ሊጫወት ይገባል” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

     የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እና የመኢአዱ ፕሬዝዳንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ በበኩላቸው ‹‹በዚህች አገር ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ ሁሉም ወገኖች እንዲነጋገሩ ዶክተር አብይ ቃል በገቡት መሰረት ጥሪውን ማድረግ አለባቸው። ጥሪው ሲቀርብ ደግሞ በቅድመ ሁኔታ በተገደበ መልኩ ሳይሆን ሃሳብ አለኝ የሚል ሁሉ ያለ ቅድመ ሁኔታ ተጠርቶ ሊነጋገር ይገባል እንጂ እንዳለፉት ጊዜያት በቅድመ ሁኔታ በታጠረ መንገድ ከሆነ ከችግሩ አልተማርንም ማለት ነው›› ሲሉ ለሰንደቅ ገልፀዋል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1549 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 983 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us