የናይል ትብብርና የምሁራን ዕይታ

Wednesday, 16 May 2018 13:34

 

በግብፅ አሌክሳንደሪያ ከተማ ከሜይ 8 እስከ ሜይ 11 2018 በምስራቅ አፍሪካ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች ውስጥ ለሚገኙ ጋዜጠኞች የሚዲያ ስልጠና ተሰጥቶ ነበር። ስልጠናውን ያዘጋጁት የሲውድን ዓለም ዓቀፍ የውሃ ኢንስቲትዩት (SIWI) እና በዩኔስኮ ሥር የሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የውኃ ትብብር ማዕከል (ICWC) ከናይል ተፋሰስ የአቅም ግንባታ ኔትዎርክ (NBCBN)ጋር በመተባበር ነው።

የስልጠናው ዓላማ፣ ጋዜጠኞች በናይል ተፋሰስ ሀገሮች የሚገኘውን የውሃ ሃብት ተያይዞ ለሕብረተሰቡ የሚያቀርቡት ዘገባ ከአድልዖ ከወገንተኝነት የፀዳ እና በሳይንስ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አቅማቸውን በመገንባት ማገዝ ነው። እንዲሁም፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ለምሳሌ ከውሃ ከአካባቢ ለውጥ ጋር በተያያዘ በምስራቅ አፍሪካ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ በጋዜጠኞች ግንኙነትና ትብብር እንዲኖራቸው ማመቻቸት ነው። በተጨማሪም፣ በተፋሰሱ ዙሪያ በሳይንስ የተደገፈ መረጃ ስለአካባቢ ስለአየር ንብረት ለውጥ፣ ስለውሃ ለጋዜጠኞች ማቅረብ ነው። በተፋሰሱ ሀገሮች ውስጥ ያሉ የመስኖ ሥራዎችን በመጎብኘት መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

ስልጠናው አንድ ቀን ሙሉ ፋዩም በተባለ ሥፍራ የሚገኙ የመስኖ ሥራዎችን መጎብኘትን ያካተተ ነበር። የተቀሩትን ጊዜያት አሌክሳንደሪያ በሚገኘው በሲውዲን ኢንስቲትዩት ውስጥ የተከናወነ ነው። በርከት ያሉ የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ውይይቶች ተደርጎባቸዋል። ጋዜጠኞችም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስቻለ ስልጠና ነበር።

ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶች መካከል፤ ከሲውዲን ዓለም ዓቀፍ የውሃ ኢንስቲትዩት ከመጡት ባለሙያዎች ወ/ሮ ማሪያ ቪንክ “Introduction to the role of media in fostering regional/transboundary cooperation”፤ ዶክተር ፊሊያ ሬሰቲያኒ “Water cooperation and benefit sharing in a regional context”፤ ሚስተር ማትስ ኤሪክሰን “A global outlook on water for development and examples on hydroclimatic hazards in Asia” ያቀረቡ ሲሆን እነዚህን የጥናት ሰነዶችን የተለያዩ አብነቶችን በማቅረብ በጥሩ ሁኔታ አቅርበዋል።

ሌላው በዶክተር ኬቨን ዊለር፤ “The immediate implications of the GERD and the need for upstream-downstream cooperation.” “The long-term costs and benefits of infrastructure to mitigate hydro-climatic risks.” በሚል ርዕስ የቀረቡ የጥናት ውጤቶች ናቸው። የዶክተሩ ሳይንሳዊ መረጃዎች በጣም የጠለቁና ገለልተኛ በመሆናቸው የስልጠናው ማሰሪያ ተደርጎ የተወሰደ ነው።

ሌላው፣ በርካታ ጠቃሚ መረጃ የተገኘበት እንዲሁም መረጃ አልባ አወዛጋቢ ትንተና ያቀረቡት የግብፅ ዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ ናቸው። ያቀረቧቸው የጥናት ወረቀቶች፣ “Climate change and expected impact on water resources in the Nile from hydro climatic hazards (Floods, droughts, etc) Hydro climatic hazards”
& “
Water for agriculture – a basin wide perspective on agriculture-based economy and basis for livelihoods in the eastern Nile basin countries “ & “Impact on life and livelihoods in the basin including forced migration.” የሚሉ ናቸው። በስልጠናው የተለየ አቀራረብ እና አተያያት የነበረው በአቶ ወንድወሰን ሰዒድ የቀረበው ፣“ Emotion, the Nile and the Media.” የሚለው የጥናት ወረቀት ነው።

 

በዚህ ጽሁፍ ሁሉንም የስልጠና የምርምር ሰነዶች ማቅረብ አይቻልም። ከቀረቡት ጥናቶች መካከል በተለይ የዶክተር ኬቨን ዊለር እና የዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ በወፍ በረር ለመመልከት እንሞክራለን።

ዶክተር ኬቨን ዊለር በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪና መምህር ናቸው። ለዶክትሬት ዲግሪያቸው የማሟያ የጥናት ሥራቸውን ያደረጉት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ ላይ ነበር፤ ጨርሰውም ተመርቀዋል።

ዶክተር ኬቨን የጥናት ወረቀታቸውን ሲያቀርቡ የአካዳሚ ጥናት መለያ ባሕሪዎችን አስቀምጠው ነው። ይኸውም፣ በራሱ ሀሳብ የሚመራ፤ ነፃ ትንተና ምርመር (independent analysis)፤ በጣም ተባባሪ (highly collaborative)፤ ለሌሎች አስቻይ አማራጮችን ከግምት እንዲወስዱ የሚያቀርብ (provide possible approaches for others to consider (consultants, ministries, TNC) ነው ሲሉ አስምረው ነበር የጀመሩት።

ዶክተር ኬቨን በሰጡት ሙያዊ ትንተናዎች በተለይ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ጋር በተያያዘ በሳይንሳዊ ቀመር ከማስደገፋቸው በላይ በጉዳዩ ላይ ያላቸው በራስ መተማመን የሁላችንም ቀልብ የሳበ ነበር። በተለይ በግብፅ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል በሚደረጉ ድርድሮች ከመግባባት መድረስ አልቻሉም ከሚባለው ጉዳይ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚሞላበት አግባብ መሆኑ በስፋት ተዘግቧል።

ዶክተር ኬቨን በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናታቸውን ተመስርተው እንዳስቀመጡት፣ በመጀመሪያ ዓመት በጣም ትንሽ የውሃ መጠን በግድቡ በመያዝ ወደ ሥራ ለመግባት እያለቁ ያሉትን ተርባይን 9 እና 10 ለመሞከር ይውላል። በሁለተኛው አመት በግድቡ በሚያዘው ውሃ ሁሉንም ተርባይኖች ለመሞከር በሚያስችል መጠን ውሃ በግድቡ እንዲገባና እንዲያዝ ይደረጋል። በተቀረው አመታት 640 ሜትር ከፍታ ያለውን የህዳሴውን ግድብ ለመሙላት ይውላል ብለዋል። እንደዶክተሩ ገለፃ ግድቡን ለመሙላት ቢያንስ አምስት ዓመት ያስፈልጋል። ይህ የሚወሰነው እንደዝናብ መጠኑ ነው ብለዋል።

ዶክተር ኬቨን ለሰልጣኞች ቁልፍ ነጥቦች ብለው አስቀምጠዋል። ዶክተሩ ጥናታቸውን በአሰረጂነት አቅርበው፣ ኢትዮጵያ ተጋፊ (aggressively) በሆነ መልኩ ግድቡን የመሙላት እቅድ የላትም፤ ኢትዮጵያ እንደዝናቡ መጠን ለመሙላት ፈቃደኛ ናት፤ ሁሉም ነገሮች አሁን በድርድር ላይ ናቸው ብለዋል።

“የህዳሴው ግድብ ውሃ ሲሞላ አደጋ አይኖረውም?” ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶክተር ኬቨን የሰጡት ምላሽ፣ “አደጋ ይኖራል። ነገር ግን አደጋው መቶ በመቶ በተቀናጀ ኦፕሬሽን ሊስተካከል የሚችል ነው (risk exist, but are 100% manageable with coordinated operation)” ብለዋል። አያይዘውም፣ በተፋሰሱ ሀገሮች በተለይ በሱዳን በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል በሚያደርጉት ድርድር ከስምምነት ላይ መድረስ ከቻሉ አደጋ የሚባል ሊከሰት አይችልም። ዋናው ጉዳይ በትብብር መስራት ነው።

ሌላው በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል አወዛጋቢ እና ለስምምነት መድረስ እንቅፋት ተደርጎ የሚወሰደው “ጉዳት” እና “ጉልህ ጉዳት” በሚሉ ሀረጎች መካከል ያለው አረዳድ ነው። በስልጠናው ወቅትም ለዶክተር ኬቨን ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄዎች ማከከል አንዱ “ከረጅም ጊዜ ተፅዕኖ አንፃር በተለይ የናይል ውሃ መጠንን መጠቀምና መከፋፈል ጋር በተያያዘ ጉልህ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ነው።” ነበር። ዶክተር ኬቨን ግብፅን በምሳሌ በመውሰድ ሁሉንም በተፋሰሱ ሀገሮች መከከል በተለይ በኢትዮጵያ በሱዳን እና በግብፅ የሚገኙ በውሃ የተሞሉ ግድቦችን ለኃይል ማመንጫ በሚቻለው ደረጃ በተቀናጀ መልኩ በመጠቀም ውጤታማ መሆን ይቻላል። ይህም ሲሆን ምንም አይነት ጉልህ ጉዳት አይደርስም (cause no significant harm) ሲሉ የጥናት ሰነዶችን በጥልቅ በመተንተን አስረድተዋል።

ዶክተር ኬቨን አያይዘውም፣ በሀገሮች መካከል ያለውን አለመተማመን ለመቅረፍ ብቸኛ አማራጭ በሳይንስ የተደገፈ መረጃ መጠቀም ነው። ጥናት ላይ መሰረት ያላደረጉ መከራከሪያዎች ለመተማመን አያስችሉም። ሱዳን ግብፅና ኢትዮጵያ ፈጥነው ከስምምነት መድረስ ከቻሉ በአጭር እና በረጅም ጊዜ በተቀናጀ መልኩ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው። ሳይረፍድ መስማማቱ አዋጪ ነው ብለዋል።

የአሌክሳንደሪያው ስልጠና አዲስ ነገር ይዞ የመጣው በግብፅ በኩል አዲስ ትርክት በዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ ““Impact on life and livelihoods in the basin including forced migration.” በሚል የቀረበው “ጥናታዊ” ወረቀት ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ አስገዳጅ የገበሬዎች ፍልሰት ይፈጠራል የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀርበው ነበር። እንደዶክተር አሊ ገለፃ፣ ከሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ “2 ሚሊዮን የግብፅ ገበሬ” ይፈናቀላል ብለዋል።

በዚህ ነጠብ ላይ ሞቅ ያለ ክርክር ተደርጓል። ለዶክተር አሊ የቀረበላቸው ጥያቄ በጣም ቀላል ነበር። ይኸውም፣ “2 ሚሊዮን ገበሬ ይፈናቀላል የሚለው ድምዳሜ ከየት የጥናት ሰነድ የተገኘ ነው? እርስዎ ያጠኑት ከሆነ አቅርበው ቢያስረዱን ወይም በሶስተኛ ወገን የተጠና የጥናት ሰነድ ካለ ያቅርቡትና እንወያይ?” የሚል ነበር። በዚህ መልኩ ጥያቄ አይቀርብም በሚል የተዘናጉት ዶክተር አሊ አንድም ያቀረቡት የጥናት ሰነድ የለም። በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሽ የላቸውም፤ ተራ ፕሮፖጋንዳ ግን አልነበረም።

ምክንያቱም ዶክተር አሊ ኤል-ባሕራዊ የዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው። በምንም መልኩ አለመረጃ ያወራሉ ተብሎ አይታሰብም። ዶክተሩ በአንድም በሌላ ምክንያት አምነው ያቀረቡት የመከራከሪያ ነጥብ አይደለም ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከዓላማ ውጪ የቀረበ ጉዳይ ተደርጎ ግን አይወሰድም።

የዶክተሩና የላካቸው አካል ፍላጎት በቀላል አቀራረብ የህዳሴውን ግድብ ውሃ መሙላት ተከትሎ ሊቀንስ በሚችለው የውሃ መጠን “2 ሚሊዮን የግብፅ ገበሬ ለስደት ይዳረጋል” የሚል አዲስ የፍርሃት ፖለቲካ በአውሮፓ ሀገሮች ለመርጨት የታለመ ነው። ይህም ሲባል፣ በሶሪያ ስደተኞች የተጥለቀለው የአውሮፓ ማሕበረሰብ ስለስደተኞች መስማት አይፈልጉም፤ ተሰላችተዋልም። ይህንን የተረዱት ዶክተር አሊና የላኳቸው አካላት፣ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚፈናቀለው የግብፅ ገበሬ መዳረሻው አውሮፓ ነው፣ የሚል የፍርሃት ፖለቲካ ማስተጋባት ፈልገው የዘየዱት ስለመሆኑ ለማወቅ የሮኬት ሳይንስ አይጠይቅም።

በግብፅ የገበሬዎች ፍልስት የፍርሃት ፖለቲካ በአውሮፓ ማሕበረሰብ ላይ በመርጨት ዶክተር አሊና የላካቸው አካል ምን ይጠቀማሉ ብሎ መጠየቅ አግባብነቱ ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም፣ ግብፅ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ ዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ በመውሰድ አጀንዳ ለማድረግ የማትፈነቅለው ድጋይ የለም። ከሙከራዎቹ አንዱ፣ የዶክተር አሊ መረጃና ጥናት አልባው በሕዳሴው ግድብ ምክንያት “ 2 ሚሊዮን የግብፅ ገበሬዎች ወደ አውሮፓ ይፈልሳሉ” የሚለው አዲሱ የፕሮፓጋዳ ትርከት ነው። ቀላል የሚመስል ሆኖም ግን አደገኛ የፕሮፖጋዳ ዝግጅት የተደረገበት ፈጽሞ ለተጀመረው የመተባበር መንፈስ አጋዥ ያልሆነ አቀራረብ ነው።

በስልጠናውም ላይ ዶክተር አሊ አንዳችም መረጃ ይሁን የጥናት መከራከሪያ ነጥብ ሳያቀርቡ ነበር፤ ስልጠናው የተጠናቀቀው። በተረፈ በሌሎች ባለሙያዎች የቀረቡት የጥናት ወረቀቶች በርካታ ቁምነገሮች ያገኘንባቸው ናቸው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1477 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1051 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us