የዜጎች መፈናቀልና የአገሪቱ ፖለቲካ ቀጣይ ጉዞ

Wednesday, 23 May 2018 13:52

 

በይርጋ አበበ

ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንግዳ ካልሆኑት እኩይ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ውስጥ የዜጎች ከመኖሪየ ቀያቸው ‹‹መጤ›› እየተባሉ መፈናቀል አንዱ ነው። በዚህ ድርጊት የተነሳም የአገሪቱ ፖለቲካ እና ዜጎች በክፉ ሲነሱ ቆይተዋል፤ አሁንም እየተነሱ ይገኛሉ። ዜጎችን ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ የማፈናቀሉ ድርጊት ቆየት ያለ ቢሆንም ካፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ መጠኑና ቅርጹን በመቀየር ተባብሶ ቀጥሏል። በዚህ ሁኔታ አገሪቱ እንዴት ትጓዛለች? የአገሪቱ ፖለቲካስ ምን መልክ ይኖረዋል? ተፈናቃዮች እየደረሰባቸው ካለው መጠነ ሰፊ ችግርስ እንዴት ማገገም ይችላሉ? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ለተለያዩ ምሁራን አቅርብንላቸው የሰጡንን ምላሽ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

መፈናቀል እና የኢህአዴግ ፖለቲካ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም ትምህርት አስተማሪው ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን ፌዴራሊዝም ጠንካራ እና ደካማ ጎን ተንትነው መረጃ በመስጠት ይታወቃሉ። እንደምሁሩ እምነት ፌዴራሊዝሙ አካባቢያዊነትን አብዝቶ መስበኩ ለኢትዮጵያ መጥፎ ጎንዮሾችን ይዞ ቀርቧል። በ2010 ዓ.ም ብቻ ከምስራቅ ኢትዮጵያ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ዜጎች መፈናቃቸውን ለአብነት ያስታወሱት ምሁሩ ‹‹መፈናቀል ዛሬ የተጀመረ አይደለም›› ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ይናገራሉ።

ዶክተር ሲሳይ ሃሳባቸውን ሲያጠነክሩትም ‹‹ከ1984/ 85 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ከየአካባው ይፈናቀል ነበር። በተለይ በኦሮሚያ ክል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ይፈናቀሉ እንደነበር ይታወቃል። ይኸው ሂደት ቀጥሎ በደቡብ ክልልም ቤኒሻንጉል ጉሙዝም አማሮች የተፈናቀሉበት ጊዜ አለ። አልፎ አልፎም ትግራዮች የተፈናቀሉበት አጋጣሚ እንደሆነ ይታወቃል። ላለፉት 27 ዓመታት የነበረው አደረጃጀት የነበረው ፖለቲካዊ እሳቤና ስራ ላይ የዋለው አስተዳደራዊ ሁኔታ የበለጠ ለብሔር ብሔረሰብ ትኩረት የመስጠት ለአካባቢ ማንነቶች ከሚገባው በላይ ትልቅ ቦታ እና ግምት የመስጠት አስተሳሰቦች ነበሩ። በተቃራኒው ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለጋራ አብሮነት ለዜጎች መብት ተገቢውን ቦታ አለመሰጠቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሎ ማሰብ ይቻላል›› ሲሉ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን መግዛት ከጀመረበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ተመሳሳይ መፈናቀል እንደነበረ አስረድተዋል።

ዶክተር ሲሳይ አክለውም ‹‹አንድን ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ እንደመጤ እንደወራሪ አድርጎ የመቁጠር፣ ቀደም ሲል የነበረውን ስርዓት ያንድ አካባቢ ወይም ህዝብ ወኪል እንደነበረ አድርጎ የማሰብ፣ ለምሳሌ ስለ አማራ ሲታሰብ ነፍጠኛ ወይም ትምክህተኛ ብሎ የመፈረጅ ይህ በመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ በፓርቲ መሪዎች ጭምር ገኖ በአደባባይ ሲነገር ስለነበረ ያ ደግሞ ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ ፍላጎቱን ለማርካት በተለይም መሬትንና ንብረትን ለመቆጣጠር ሲል እነዚህ ወገኖች ለፍተው ያፈሩትን ሀብት በቀላሉ ለመዝረፍ በጥቂት ሰዎች እና ጥቂት የፖለቲካ ሰዎች ይጀመርና ሌላውም በስሜት የሚቀላቀልበትና ማፈናቀል የሚፈጠርበት አጋጣሚ እንዳለ ማየት ይቻላል›› በማለት የማፈናቀሉን ምክንያት ይገልጹታል።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በአንቀጽ 32 ‹‹ማኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት መብት አለው›› ሲል ይደነግጋል። የአገሪቱ የበላይ ህግ የሆነ ህገ መንግስቱ ይህን ቢልም ዜጎች ግን በተደጋጋሚ ጊዜ ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ እየታየ ነው። የህግ ባለሙያውና የአንቀጽ 39 መጽሃፍ አዘጋጅ አቶ ውብሸት ሙላት በዚህ ጉዳይ ላይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ምላሽ፤ አማራ ከ1983 ጀምሮ ከተለያየ ቦታ ተፈናቅለዋል። ለዚህ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። አንዱ የፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር የተቆራኘ ፖለቲካዊ ሴራ ነው። ከየቦታው ሲፈናቀሉ መፈናቀል ተገቢ እንዳልሆነ እንኳን የሚገልጽ አገር መሪ አልነበረም። እንደውም መፈናቀላቸው ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት ጥረት ይደረግ ነበር። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከጉራፋርዳ አማራዎች ሲፈናቀሉ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር እና አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን የተናገሩትን ማስታወስ ነው። ከዚህ አንጻር ማፈናቀል ተገቢ አለመሆኑን በኦፊሴል አጀንዳ ሆኖ መኮነን የተጀመረው ከጎንደር የትግራይ ተወላጆች ከተፈናቀሉ በኋላ ነው። ከዚያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የኦሮሞ ተወላጆች ሲፈናቀሉ በተወሰነ መልኩ የማፈናቀል ጉዳይ አገራዊ አጀንዳ እየሆነ መጣ። አሳዛኙ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያፈናቀሉ ኃላፊዎችን እንኳን ወደ ፍትሕ ለማምጣት አልተሞከረም፤ ወይም ይሄን ማድረግ የቻለ የፍትሕ ሥርዓት አልዘረጋንም።

ሁለተኛውም ምክንያት ከሕግ ጋር የተያያዘ ነው። የተወሰኑ ብሔሮችን ጨምሮ የአማራ ሕዝብን የሚያገሉ እና ባይታወር የሚያደርጉ በርካታ ሕጎች በተለያዩ ክልሎች ወጥተዋል። እንግዲህ የአማራ ሕዝብ በብዙ ክልሎች ተሰራጭቶ የሚኖር ቢሆንም ከክልሎቹ ሕዝብ አንጻር የሶስት ክልሎችን ሁኔታ እንመለከት›› ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ እና በጋምቤላ ከሚኖሩ ህዝቦች መካከል አማራ አብላጫ ቁጥር እያለው ከፖለቲካ ተሳትፎ መገለሉን ያስረዳሉ። አቶ ውብሸት አምክንዮአቸውን ያቀረቡት ከ1999 ዓ.ም ህዝብና ቤት ቆጠራ ባገኙት ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ውብሸት አምክንዮአቸውን ያቀረቡት ከ1999 ዓ.ም ህዝብና ቤት ቆጠራ ባገኙት ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል። ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር ሲሳይ መንግስቴም ሆኑ አቶ ውብሸት ሙላት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ቆየውን የዜጎች መፈናቀልን ምንጭ ከመጥቀሳቸውም በተጨማሪ መንግስት ለዚህ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ አለመስጠቱን ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። ዶክተር ሲሳይ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ ‹‹አርባ ጉጉ ላይ አማሮቹን የማፈናቀልና የመግደል ብሎም የመዝረፍ ተግባር ሲጀመር እዛ ላይ የፌዴራል መንግስቱ ጠንከር ያለ እርምጃ ባለመስጠቱ ቀጥሎ ጋምቤላ ላይ፣ በደቡብ ክልል፣ ወለጋ ላይ እና በቅርቡ ደግሞ ሶማሌ እና አማራ ክልል ላይ በትግራይ ብሐየር ተወላጆች የደረሱ መፈናቀሎች ተክስተዋል። ይህ ደግሞ መንግስት ህግና ስርዓትን ለማስከበር ቁርጠኛ ባለመሆኑ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ከሶማሌ ክልል ከ700 እና 800 ሺህ ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆች ሲፈናቀሉ ይህ የመጨረሻው ጫፍ የደረሰበት ይመስለኛል›› ብለዋል።

ይህን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ ውብሸት ሙላት ንግግራቸውን ማሰማት የጀመሩት የፌዴራሊዝሙን አወቃቀርና የክልሎችን ህገመንግስት ለክልሉ ነዋሪዎች የሰጡትን ትርጓሜ በማውሳት ነው። ሃሳባቸውን ሲጀምሩም ‹‹ከፌደራሉ አጠራር ለየት ባለ መልኩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በተመለከተ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕግጋተ መንግሥታት ላይ እናገኛለን። የጋምቤላ ሕገ መንግሥት በክልሉ የሚገኙትን ነባር ብሔር ብሔረሰቦች “መሥራች አባላት” በማለት ሲጠራቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ “የክልሉ ባለቤት ብሔረሰቦች” የሚሉ ሐረጋትን ይጠቀማሉ። ከእነዚህ ሕግጋተ መንግሥታት የምንረዳው መሥራች ያልሆኑና ባለቤት ያልሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ ነው። በግልጽ በጽሑፍ ሁለቱ ክልሎች መሥራችም ይሁን ባልተቤት ይበሉ እንጂ ቀሪዎቹም ክልሎች ቢሆኑ የተከተሉት ይሔንኑ አካሔድ ነው ማለት ይቻላል።

ምክንያቱም የትግራይ ክልል የትግሬ፣ የኢሮብና የኩናማ፣ የአፋር ደግሞ አፋርና አርጎባ እያለ እየዘረዘሩ ይቀጥላሉ። የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መብቶችን እንደቡድን የሚያጎናጽፉት ያው ዞሮ ዞሮ ለነባሮቹ ብቻ ነው›› የህግ ምሁሩ አክለውም ‹‹ማፈናቀል ኢሕገመንግሥታዊ ድርጊት ነው። ሕገ መንግሥትን ይጥሳል። የሰብኣዊ መብትን ይጥሳል። የሰብኣዊ መብት ስምምነቶችን ይተላለፋል። በመሆኑም ሕገ ወጥ ነው። ሕገ ወጥ መሆኑ ደግሞ እንደነገሩ ሁኔታ በወንጀልም በፍትሐ ብሔረም ያስጠይቃል። የማፈናቀል ተግባር ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ሆንብለው ወይም በቸልተኝነት እስከፈጸሙት ድረስ የወንጀል ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል።

በተወሰነ መልኩ ከጉራፋርዳ አማራዎች በመፈናቀላቸው ምክንያት በድረጊቱ ውስጥ የተሳተፉት ሰዎች በወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል። በአጠቃላይ የማፈናቀልን ሁኔታ በምንመለከትብት ጊዜ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች መፈናቀል ደርሶባቸዋል። ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉትን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ዜጎች በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታ እና በመረጡት የሙያ ዘርፍ ተሠማርተው የመኖር ብሎም ሃብትና ንብረት የማፍራት መብተቻው በመፈናቀላቸው ምክንያት ተጥሷል፤ ጉዳትም ደርሶባቸዋል ማለት ነው›› ሲሉ የመፈናቀልን ጥልቀትና ሊያስከትል የሚችለውን ቅጣት በዝርዝር አስረድተዋል።

 

የቤኒሻንጉልና የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ሁኔታ

ባሳለፍናቸው ሁለትና ሶስት ወራት በስፋት ከተደመጡ የመፈናቀል ዜናዎች መካከል ቀዳሚው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በለው ጅጋፎ ወረዳ ስለተፈናቀሉ ከሁለት ሺህ በላይ አማሮች የተሰማው ዜና ነው። 108 ተማሪ ህጻናትን ይዘው ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ በአካባቢው አስተዳዳሪዎች አማካኝነት እንደተባረሩ የተናገሩት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ አማራዎች፤ ስለተደረገላቸው ድጋፍ ሲናገሩ ‹‹ከአማራ ክልል ህዝብ የተደረገልን ድጋፍ በጣም ጥሩ እና ወገን እንዳለን የተረዳንበት ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። ለተፈናቃዮቹ ዜጎች በውጪ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች በኩል የተሰበሰበ ወደ 805 ሺህ ብር የተበረከተላቸው ሲሆን የዳሽን ባንክ ባህርዳር ቅርንጫፍ ሠራተኞች፣ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ወገኖች፣ የወሎ ክፍለሀገር ተወላጆች እና የወልቃይት ማንነት አስተባባሪ ኮሚቴዎች የገንዘብና የሞራል ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል።

ከህዝቡ ይህን የመሰለ ድጋፍ ቢደረግላቸውም በክልሉ መንግስት በኩል ‹‹ምንም›› አይነት ድጋፍ ስላልተደረገላቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ‹‹የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት እኛ ካረፍንበት (የባህር ዳሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን) ከ600 ሜትር የማይበልጥ ሆኖ ሳለ አቶ ገዱም ሆኑ ሌላ የእሳቸው ተወካይ መጥተው ለማናገርም ሆነ ችግራችንን ተመልክተው መፍትሔም ሆነ ድጋፍ ሊሰጡን አልቻሉም›› ሲሉ ቅሬታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አስተማሪው ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ‹‹የተፈናቃዮቹ ፍላጎት ዘላቂ መፍትሔ ብለው ያሰቡት በቋሚነት ኑሯቸውን ለመምራት ወደ ነበርንበት ቦታ መመለስ የደህንነት ዋስትና የለንም። ስለዚህ በዚያው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በመተከል ዞን እንድንኖር የሁለቱ ክልል መንግስታት መክረው ውሳኔ ያሳልፉልን የሚል ሃሳብ ማቅረባቸው ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ምክንያቱም የክልሉ መንግስት ያቀረበላቸው መፍትሔ ወደነበሩበት ቦታ ሄደው እንዲሰፍሩ ወይም በወላጆቸው አካባቢ እንዲሰፍሩ የሚል ነው። እነዚህ ሁለት መንገዶች ደግሞ ለተፈናቃዮቹ የሚስማሙ አማራጮች አይደሉም›› ብለዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ እና መፍትሔ ለመስጠት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ከአማራ ክልል መንግስታት ተወካዮችን የያዘ ልዑክ ለቀናት በባህር ዳር ሲመክር ቆይቶ ሰሞኑን ደግሞ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማቅናቱንም ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

ሌላው የመፈናቀል ዜና ደግሞ ሰሞኑን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ኦጂላ እና አዋዲ ቀበሌዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች የመፈናቀል ዜና ነበር። ተፈናቅለናል ያሉ የአማራ ብሄር ተወላጆች ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት ለዓመታት ከኖርንበት ቀዬ እና ግብር ከምንከፍልበት መሬት ላይ በግዳጅ እንድንነሳ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን በተመለከተ የክልሉን መንግስት አቋም በግል የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት የኦሮሚያ ክልል የገጠር ፖለቲካ ቢሮ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ የሚከተለውን ብለዋል። ‹‹ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አጂላ እና አዋዲ ጉሉፋ በተባሉ ቀበሌዎች የአማራ ተወላጅ ወንድሞቻችን እንደተፈናቀሉና የመብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ተደርጎ ሲዘገብ ቆይቷል። እነዚህ አባወራ አርሶ አደሮች ከኦሮሞ በወንድማችነት በፍቅር አብረው የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ዜጎቻችን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰርቶ የመኖር መብታቸው ይከበር ዘንድ በቀበሌዎቹ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የወረዳው መስተዳድር ለእያዳንዳቸው በአባውራ ሁለት ሄክታር መሬት ይዞታ እንዲያገኙ አድርጓል›› ካሉ በኋላ አሁን ተነሳ የተባለው ችግር የጠፈጠረው መሬትን አስፋፍተው ለመያዝ በህገ ወጥ መንገድ የሞከሩ ሰዎች ከወረዳው አስተዳዳሪዎች ጋር ባለመግባባት ከድርጊታቸው እንዲያቆሙ ሲነገራቸው በተሳሳተ መረጃ ሌሎቹን በጉዳዩ የሌሉበትንም በማስተባበር በማነት ላይ የተፈጠረ ድርጊት አስመስለው ያቀረቡት እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ የተነሳም ተፈናቀሉ የተባሉትን ሰዎች የኦሮሚያ ክልል መንግስት ወደነበሩበት ቀዬ ተመልሰው የተለመደ ኑሯቸውን እንዲኖሩ ማድረጉን አቶ አዲሱ ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ትናንት ከቀትር በኋላ መግለጫ ያወጣው ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹በማንነት ላይ የሚደረግ ማፈናቀል ይቁም›› ሲል አስታውቋል።

 

 

የፖለቲካ ዥዋዥዌ

ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በመፈናቀል አገሪቱም ሆነች ዜጎቿ የሚደርስባቸውን ችግር አስመልክተው ሲናገሩ ‹‹መፈናቀል የመጀመሪያ ጉዳት የሚደርሰው በህጻናት ላይ ነው። ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ይገለላሉ፣ በመፈናቀሉ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ሴቶችም ከፍተኛ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ከሁሉም በላይ ለበርካታ ዓመታት ለፍተው ያፈሩትን ሀብት ሲቃጠል፣ በቀላሉ ጥለውት ሲሄዱ ወይም በወሮበላ ሲዘረፍ የሚስከትለው የስነ ልቦና ጫና ከፍተኛ ነው። የወደፊት ህይወታቸው ላይም ተስፋ ማስቆረጥ የሚያሳድርባቸው ሲሆን ከዚህም የከፋው ደግሞ በመፈናቀል የሰው ህይወት የጠፋበት አጋጣሚም አለ›› ሲሉ በመፈናቀል ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ጠቅሰዋል።

ይህ መፈናቀል የሚመጣውን የፖለቲካ ቀውስ በተመለከተ ሲናገሩም ‹‹በዚህ አይነት በደል ውስጥ ሆነው በአገራቸው እየኖሩ ባይተዋር ሲሆኑ ከሁሉም የከፋው ነገር ነው። በሰው አገር ሆነህ እንደዚህ አይነት ነገር ቢፈጸምብህ አገር አለኝ ብለህ ወደአገርህ ትመለሳለህ። አገርህ ላይ ሆነህ ግን እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል የልብ ስብራትንም ይፈጥራል። በዚህ የተነሳ ደግሞ እኔ ማነኝ ብለው እንዲጠይቁ ሁሉ ያደርጋቸዋል። እየኖርኩ ያለሁት በአገሬ አይደለም እንዴ ብለው እንዲጠይቁ የሚደርጋቸው ሲሆን አሁን ያለው መንግስት እኔን አይወክልም ወደሚል አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታም ምኔም አይደለም የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ያደርጋቸዋል›› ብለዋል።

እንደ ዶክተር ሲሳይ እምነት በማፈናቀል ወቅት ተፈናቃዩን ብቻ ሳይሆን አፈናቃዩንም የስነ ልቦና ተጠቂ ያደርገዋል። ‹‹አፈናቃዩን በተመለከተ ስነ ልቦናውን ስትመለከት በራ ወገን እና አገር ላይ ሌሎቹን አፈናቅሎ ንብረታቸውን ቀምቶ የሚገኘው ጥቅም ዘለቄታ እንደሌለው ነገ ከነገ ወዲያ ሁኔታውን ሲረዳ ራሱን እንደሚወቅስ ማሰብ ይቻላል›› በማለት ተናግረዋል።

አቶ ውብሸት በበኩላቸው በዚህ ሃሳብ ይስማሙና ስጋት ብለው የሚስቀምጡትንም ሲገልጹ በርካታ የአማራ ብሔር ህዝብ በሚኖርባቸው የአገራችን ክልሎች የብሔሩ ተወላጆች ከፖለቲካ ወሳኔ መገለላቸውን በማውሳት መናገር ይጀምራሉ። ሃሳባቸውን በዝርዝር ሲያስቀምጡም ‹‹የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የከተሞች ማዕከላትን ለማቋቋምና ሥልጣናቸውን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ለከተማ ምክር ቤት በሚደረደግ ምርጫ ከምክር ቤቱ መቀመጫ ውስጥ 55 በመቶው ለክልሉ ነባር ሕዝቦች የተተወ ነው። ተመሳሳይ ስያሜ በተሰጠው አዋጅ የኦሮሚያ ክልል ቢሆን 50 በመቶ ለከተማው ኦሮሞ፣ 20 በመቶ በገጠር ቀበሌዎች ለሚኖሩ ኦሮሞዎች ብቻ ተለይቶ ተቀምጧል። ያውም ይህ የሆነው ቀድሞ 30 በመቶ ለከተማው አምስት በመቶ ለገጠር ገንዳዎች የነበረውን በመጨመር ነው።

በደቡብ ክልል ደግሞ በልዩ ወረዳና ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ ከተሞች ለነባር ሕዝቦቹ 30 በመቶ ተቀምጧል። እነዚህ የሚወዳደሩበትን ምክር ቤት የሥራ ቋንቋ ማወቅ አለማወቅ እንኳን እንደ መስፈርት አልወሰዱትም። የፌደሬሽን ምክር ቤት በአንድ ወቅት የወሰነው ግን የሚወዳደርበትን ምክር ቤት ቋንቋ የሚችል ማንም ሰው የመወዳደር መብት አለው በማለት ነው። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ክልሎች የምርጫ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ቀድሞውንስ አላቸው ወይ? የሚለውን። በሌላ አገላለጽ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51(15) መሠረት የፌደራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር አይደለም ወይ? እንደማለት ነው። በዚህ አንቀጽ መሠረት የምርጫና የፖለቲካ መብቶችን የሚመለከቱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው የፌደራሉ መንግሥት ነው›› ሲሉ ይተነትናሉ።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2371 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 130 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us