የዜጋውን ውለታ ያልዘነጋ ጠቅላይ ሚኒስትር

Wednesday, 23 May 2018 14:05

-    በሺዎችና በሼሁ ነፃ መውጣት የተገለጸው የዜግነት ክብር

 

“ሼህ አላሙዲንን በተመለከተ ከሳዑዲው ዓረቢያ አልጋ ወራሽ ጋር መቶ በመቶ ተግባብተናል፡፡ እንደሀገር ያለንን ጽኑ አቋም አመላክተናል፡፡ ለእኛ ሃብታምም ድሃም ዜጋ ነው፡፡ ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲንን የማንፈልጋቸው ሰዎች ካለን፤ ሲመጡ እንነግራቸዋለን እንጂ በባይተዋር ሰዎች እጅ ውስጥ እያሉ የሚጨክን ልብ ኢትዮጵያውያን የለንም፡፡

ይህን ጠንካራ አቋማችንን የተረዱት አልጋ ወራሹ፣ እስከ ሌሊቱ አስር ሰዓት ድረስ ባደረግነው ውይይት ተግባብተን፣ ጠዋት ሼሁን ነፃ ለማድረግ ከውሳኔ ላይ ደርሰው ሊሰጡን ከወሰኑ በኋላ፤ በገጠማቸው ከፍተኛ የቤተሰብ ተፅዕኖ፣ ሼሁ አብረውን ሊመለሱ አልቻሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ነግረውናል፡፡

የሼህ አላሙዲን መታሰር፣ በዓለም ያሉ ዲያስፖራዎች ሁሉ አጀንዳ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ፣ አንቺ አንተ ከሆንክ፣ አንድ ኢትዮጵያ ታስራለችና፤ ኢትዮጵያ ስትታሰር ዝም ማለት የሚያስችለው ሌላ ኢትዮጵያ መኖር የለበትም፡፡ የጀመርነውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማስቀጠል፣ ጊዜውን መናገር ብቸገርም፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደሀገራቸው እንደሚመለሱ ርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ባሳለፍነው እሁድ በሚሊኒየም አዳራሽ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በሳዑዲ አረቢያ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተ፣ “ምን ትፈልጋላችሁ ብለው ሲጠይቁን፤ ምንም አንፈልግም፤ ዜጎቻችንን ብቻ ፍቱልን አልናቸው፡፡ ዜጎቻችንን ማክበር ስንጀምር፣ የጠየቅነው ብቻ ሳይሆን ያልጠየቅነውም ተሰጠን”፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዜጎችን ክብር የማስጠበቅ ምግባር፣ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ፤ ባለዕዳ አይቀበለውም” ይሉት የአበው ብሂል ነው፡፡

የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር ዘርዘር አድርገን ስናየው፣ “የአንድ ዜጋም ጉዳይ ግድ ይለናል፤ ለእኛ ዋጋ አለው፡፡ ዜጎቻችንን ስናከብር አብዝተው አከበሩን፡፡ የጠየቅነው ብቻ ሳይሆን ያልጠየቅነውም ተጨመረልን” ማለታቸው ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ በገለጹትና በብዙ ገጽ ሊተነተን በሚችለው በዚሁ ንግግራቸው፣ ከ1ሺ የበለጡ ኢትዮጵያውያን እስረኞች፣ ጉብኝታቸውን ተከትሎ ከእስር ተፈተው ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ አብሥረዋል፡፡ ተስፋ በቆረጡበት ወህኒ ቤት ውስጥ፣ ፈጣሪ የጎበኛቸውን ያህል ደስታቸውን ሲገልጹ፣ በመገናኛ ብዙሃን ተመልክተናል፤ አድምጠናል፡፡

ማን ያውቃል፤ የትላንት እስረኞች የዛሬ ባለተስፋ ዜጎች፣ ወደፊት በሀገራቸው በሚሰማሩበት ዘርፍ ስኬታማና አሸናፊ ሆነው፤ ዜጎችን ማክበር ምን ማለት እንደሆነ ምስክርነታቸውን ለቀጣይ ትውልድ ሲያካፍሉ እናያቸው ይሆናል፡፡ በርግጥም፣ ዜጎችን ማክበር የአንድ ትልቅ ሕብረተሰብ ግንባታ ሒደት ተግባር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በጉብኝታው ያተኮሩበት ሌላው ነጥብ የሼህ መሐመድ አላሙዲን ጉዳይ እንደሆነ፣ በሚሊኒየም አዳራሽ ለተሰበሰበው ታዳሚ አስታውቀዋል፡፡ ሼህ መሐመድ አላሙዲንን፣ “የእኛ ዜጋ” በማለት ነው ያከበሯቸው፡፡ ማንም ሃብታም ይሁን ደሃ፣ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ወይም ማንነቱ የሚያጋጥመው ችግር፣ “የእኛ ጉዳይ” ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዜግነት ክብርን በማያሻማ ሁኔታ አስመርው አቋማቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ሁሉም ነገር ከኢትዮጵያዊ ዜግነትና ማንነት በታች መሆኑን ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ከአንድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚጠበቅ አቀራረብ፣ የዜጐችን ክብር ከፍ አድርገው አሰምተዋል፤ አሳይተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላው አስተማሪ አቀራረባቸው፣ አንድ ሰው ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እያለ በደል ሊፈጸምበት እና ፍትሕ ሊነፈገው እንደማይገባ የጠቆሙበት ሁኔታ ነው፡፡ “ቅድሚያ፤ ዜጐችን ነፃ ማድረግ የእኛ ሥራ መሆን አለበት፤” የሚለው የጠቅላይ ሚንስትሩ አቋም፤ መርሕን የተከተለ አመራር ያሳዩበትና በነፈሰበት የማይነፍስ ሰብዕና ባለቤት እንደሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን የማንፈልጋቸው ሰዎች ካለን፤ ሲመጡ እንነግራቸዋለን እንጂ በባይተዋር ሰዎች እጅ ውስጥ እያሉ የሚጨክን ልብ ኢትዮጵያውያን የለንም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቆሙት፣ ሼሁ እንደማንኛውም ሰው ጠንካራ እና ደካማ ጎን ይኖራቸዋል፡፡ የሚያስመሰግናቸውም የሚያስወቅሳቸውም ሥራ አከናውነው ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ሼሁ ከሁሉ በፊት ሰው መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚህ ማብራሪያ ውስጥ ያለው ቁምነገር፣ ሼሁ አሁን ያሉበትን ሁኔታ በመጠቀም፣ ሒሳብ ለማወራረድ እየሰሩ ያሉ ሰዎችንና ተቋማትን ይመለከታል፡፡ ራሱን ለመከላከል በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ያለን ዜጋ ከመውቀስና ከመክሰስ በፊት፤ ነፃነቱ የተጠበቀ በመሆኑ ላይ ማተኮር እንደሚገባ የተሰጡትን ማሳሰቢያ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ለሚፈጸሙ ማናቸውም አይነት ችግሮች፣ የሀገሪቷን ህግ ብቻ በመጠቀም ለመፍታት መሞከር መሰልጠን መሆኑንም መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ቅሬታዎች ካሉም ከሕግ ተጠያቂነት የሚያመልጥ አካል የለም፡፡ ስለዚህም በሕግና በትዕግስት ነገሮችን መመልከት ተገቢ መሆኑን ከንግግራቸው መረዳት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይይ ሼሁን በተመለከተ ሌሎች ሁለት መሰረታዊ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡ እኒህም፣ “….እንደሀገር ያለንን ጽኑ አቋም አመላክተናል፡፡ …..የጀመርነውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማስቀጠል ጊዜውን መናገር ብቸገርም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደሀገራቸው እንደሚመለሱ ርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ…” ያሉት ናቸው፡፡ የሼሁ ጉዳይ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ በዜግነታዊ ማንነታቸው ሊታይ ቢችልም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን፣ በሼሁ ጉዳይ “እንደሀገር ያለንን ጽኑ አቋም አመላክተናል፤” ብለዋል፡፡

የሼሁ ነፃ መሆን “እንደሀገር” ጉዳይ የመታየቱን አግባብነት ለማሳየት፤ በ2009 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዓመታዊ በዓል ሲከበር፣ ሼክ አሊ አል-አሙዲ በራሳቸው አንደበት ይፋ እንዳደረጉት፣ “ከ110ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር” ችለዋል፡፡ እንዲሁም በሼኩ ባለቤትነት እና የቅርብ ክትትል የሚተዳደሩ፣ ከ77 በላይ ኩባንያዎች ባለቤት ናቸው፡፡ በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ካላቸው አሻራ በተጨማሪ፣ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት ሰብዓዊ ድጋፍ በመንግስትም በሕዝብም እውቅና የተሰጠው መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡

ከሁሉም በላይ የሚገዝፈው ውለታቸው ግና፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ቁመና አስተማማኝ ባልነበረበትና የኢትዮጵያ መንግስት ቅቡልነቱ መሰረት ባልያዘበት በ80ዎቹ ታሪካዊ ወቅት፣ ግንባር ቀደሙ ኢንቨስተር ሆነው ሃብታቸውን በማፍሰስ በሀገራቸው እና በሕዝባቸው ላይ ያላቸውን ጠንካራ እምነት፤ ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ ማሳየት የቻሉ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸው ነው፡፡ ሼሁ በራሳቸውና በሀገራቸው ላይ ያሳደሩትን መተማመን በመመልከትም፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በሀገራችን እድገት ላይ ተሳታፊ ለመሆን በቅተዋል፤ ለደረስንበት እድገትም አስተዋፅዖ ማድረግ ችለዋል፡፡

የሼሁን ጉዳይ ሀገራዊ የሚያደርገው ሌላው ትሩፋታቸው፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ጋር የተያያዘው አስተዋፅኦዋቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ግንባታን ይፋ ሲያደርጉ ለሕዝብ የቀረበውን የቦንድ ሽያጭ በከፍተኛ ዋጋ በመግዛት ሼሁን የቀደማቸው አልነበርም፡፡ ሼሁ፣ የአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ቦንድ ግዢ በመፈጸም፣ ዳግም ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት ያረጋገጡበትን ታሪካዊ ወቅት የሚዘነጋ ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡ የሼሁ የቦንድ ግዢ፣ ለእኛ ኢትዮጵያውያን የፈጠረልንን ደስታ ያህል የሚረብሻቸው ሶስተኛ ወገኖችም አይጠፉም፡፡

እንደሚታወቀው ግብፅ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሊውል የሚችል የገንዘብ ብድር፣ ከዓለም ዓቀፍ አበዳሪ ተቋማት እንዳይፈቀድ ማድረግ የቻለች ሀገር ናት፡፡ እንዲሁም ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ በተለይ አሁን ያላቸውን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከግምት ከወሰድነው፣ የሼሁ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ተሳታፊ መሆንን እንዴት እንደሚረዱት ለማወቅ የሮኬት ሳይንስ ዐዋቂነትን አይጠይቅም፡፡ እንዲሁም ሼሁ አሁን ላሉበት ሁኔታ የግብፅ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችልም መገመት ከባድ አይሆንም፡፡

ከላይ ካሰፈርነው ፍሬ ነገር አንፃር ሼሁ፣ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተር እንደመሆናቸው የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ መገኘቱ ሊያስከፍላቸው የሚችለው ዋጋ መኖሩን ቢገነዘቡም፣ ዳግም ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩበት ተግባራቸው መሆኑን፣ የህዳሴው ግድብ ምስክር ነው፡፡

ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመጠቀም ጭምር ሼሁን ነፃ ለማውጣትና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት ተገቢ ነው፤ ሼሁም ይገባቸዋል፡፡ ሼሁ፣ በችግራችና በእድገታችን ጉዞ ወቅት ያልተለዩን፣ ታምነው የተገኙልን፣ በመካከለኛው ምስራቅ ከሚነፍሰው ነፋስ ጋር አብረው የማይነፍሱ የብሔራዊ ጥቅማችን ደጀን ናቸውና፡፡

እኛም፣ ከዚህ በፊት ከዶክተር ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ጋር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢገኙ ከጎናቸው እንቆማለን፤ ያልነው፤ በግልብ ወይም በማይቆጠሩ እውነታዎች ላይ ቆመን አልነበረም፡፡ የሼሁ ጉዳይ የአንድ ዜጋ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ ሳይሆን፤ የብሔራዊ ጥቅማችንም ጉዳይ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

ሼሁ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ለሀገራቸው በሰላም እንዲበቁ እንመኛለን፡፡

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ

“በኢትዮጵያ ደሴ ከተማ ተወልደው ልጅነታቸውን በወልዲያ አሳልፈዋ፡፡ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ አህጉር ላይ ደማቅ አሻራ ጥሏል፡፡ እርስዎ በአፍሪካ ያልተቆጠበ ኢንቨስትመንት ያስፋፋ ባለራዕይ የቢዝነስ ሰውነዎት፡፡ ለአፍሪካ ዕድገት ያልዎት ቁርጠኛነት በየትኛውም ቢዝነስ ማሕበረሰብ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በተለይ ለትምህርት የሚያሣዩት ተነሣሽነት ሌሎችን ያነቃቃ ነው፡፡ በጠቃላይ በበጎ አድርጋት ሥራ ላይ አዲስ ደመለኪያ ፈጥረዋል፡፡ ከዚህ ተግባርዎ ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ የአፍሪካ አንድነት እና የአፍሪካ ሕብረት ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ የኛ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ጨምሮ ለሥነጥበብና ጥበበኞች ያለተገደበ እገዛ አድርገዋል

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ

ለሼህ መሐመድ አላሙዲን የክቡር ዶክተሬት ዲግሪ ሲያበረክቱ

የሰጡት የምስክርነት ቃል

“ይችን ጥቂት አስተዋፅዖ ለክሊንተን የኤች.አይ.ቪ ኢኒሼቲቭ ሳደርግ፣ ለትውልድ ሀገሬ የጤና መሻሻል የማደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማሣያ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ይህን ድርጅት በመደገፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥራቱ የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲደርስ እንደሚያደርግ ምኞቴ ነው”

 

ኢትዮጵያ ለእኔ ብዙ ነገሬ ነች፡፡ ባልንጀሮቼ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰኔ ይገርማቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ በልቤ ውስጥ ስለእናት ሀገሬ የሚሰማኝ ስሜት ነው፡፡ በተቀረው ዓለም የእኔ የኢንቨስትመት ውሳኔ መሰረት የሚያደርገው በተሰላ ኪሳራና ትርፍ ነው፡፡

 

ኢትዮጵያ የእኛ እስትንፋስ እና የመኖራችን መሰረት ናት፡፡ እናት ሀገራችንን ከውጭ የሚመጡ ኃይሎች የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያመጡና ወደ ብልፅግና ጓዳና እንዲያደርሷት መጠበቅ የለብንም፡፡ ይህንን ማድረግ የእኛ ብሔራዊ ግዴታና ኃላፊነት ነው፡፡ የሃገራችን እድገት ለማምጣት ቁርጠኛ በመሆን ሕዝባችን ተጠፍሮ ካያዘው ድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነፃ ማውጣት አለብን፡፡

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
2672 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 121 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us