አድማጭ ጆሮ ያጡ የበርኻ ድምጾች

Wednesday, 06 June 2018 13:39

 

በይርጋ አበበ

 

ቁጥራቸው ከ3200 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተሰብስበው ነገን በተስፋ ይጠብቃሉ፤ ትናንትን ግን ማስታወስ የማይሹ ናቸው። ወጣቶቹ ወደ አፋር ክልል አሚባራ ወረዳ ያቀኑት በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም ነበር። ወደ ቦታው ያቀኑት ደግሞ በኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን አማካኝነት የዛሬ ህይወታቸውን ሊቀይር የሚችል የተስፋ ቃል ተገብቶላቸው ነው። ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ደግሞ መቶ በመቶ ገቢው ከመንግስት የሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን ወላጆቻቸውን ባጡ ህጻናት፣ በለምኖ አዳሪዎችና በጎዳና ተዳዳሪዎች ህይወት ዙሪያ ነው ትኩረት አድርጎ የሚሰራው።

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ወደ አፋር ክልል ወስዶ ከብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር በመተባበር የክህሎትና የሙያ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል። በስልጠና ታግዘው ወደ ስራ የገቡት በሎደር ኦፕሬተርና መካኒክ ሙያዎች መሆኑን የተመለከቱ ሌሎች ወጣቶች ሶስተኛ ዙር ስልጠና መዘጋጀቱን ሲሰሙ የግል ስራቸውን ሳይቀር በመተው ወደ አሚባራው ‹‹አዲስ ራዕይ የስልጠና ማዕከል›› በማቅናት ለአስር ወራት ስልጠናቸውን ተከታትለው ጨረሱ።

በዚህ ስልጠና ግን እንዳሰቡት እንደ ቀደሙት ጓደኞቻቸው ወደሚፈልጉትና በሰለጠኑበት ሙያ ሊሰሩ የሚያስችላቸው ዕድል አልተፈጠረላቸውም። በዚህ የተነሳም ስልጠናውን ከሚሰጠው ኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሴሽንና ከሜቴክ ጋር ተጋጩ። ግጭታቸው በመካረሩም በአካባቢው የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ኦራልና ታንክ ይዞ ወደ ስልጠና ማዕከሉ በመግባት የረበሹ ወጣቶችን እንደገደለ እና በቁጥጥር ስር የዋሉትንም ለአሰቃቂ እስር እንደዳረገ ወጣቶቹ ለሰንደቅ ጋዜጣ ይናገራሉ።

በቅርቡ ደግሞ የኤልሻዳይ ሪሊፍና ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ የማነ ወልደማሪያም ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉን ተከትሎ ወጣቶቹ ወንጀሉን አውግዘው ለመገናኛ ብዙሃን ድምጻቸውን አሰሙ። በዚህ እና አለብን በሚሉት ችግር ዙሪያ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን ከሰጡ ወጣቶች ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ እና የኤልሻዳይ የአፋር ክልል ማዕከል ኃላፊዎች የሰጡትን ምላሽ በማያያዝ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የወጣቶቹ ቅሬታ

ኤፍሬም አበበ ይባላል። ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ነገን የተሻለ ሆኖ ለማየት ከትውልድ ቀየው ርቆ አዲስ አበባ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችን ተዘዋውሮባቸዋል። በአገር ውስጥ ብቻ መንቀሳቀስ ያልበቃው ወጣት ስደትን እንደ አማራጭ በመውሰድም ወደ ኬንያ አቅንቶ ኑሮውን ለመግፋት ሞክሮ ነበር። ሆኖም በጆሞ ኬኒያታዋ አገርም እንዳሰበው ኑሮ ቀላል አልሆነለትም። ወደ አገሩ ተመልሶም በአዲስ አበባ የሴቶች ውበት ቤት ተቀጥሮ ሲሰራ መቆየቱን ለሰንደቅ ጋዜጣ ይናገራል።

ወደስልጠና ማዕከሉ የገባበትን ምክንያት ሲናገርም ‹‹ቀደም ሲል በሁለት ዙር ስልጠናዎች የተካፈሉ ወጣቶች ራሳቸውን የሚያስችል ሙያ ሰልጥነው ለአገራቸውና ለቤተሰባቸው ሲተርፉ በማየቴ ነው›› ይላል። ወጣት ኤፍሬም አያይዞም ለአስር ወር የተሰጠውን ስልጠና በሎደር ኦፕሬተር ተከታትሎ መመረቁንና መንጃ ፈቃዱም በእጁ እንደሚገኝ በማሳየት ጭምር ተናግሯል። ‹‹ሆኖም›› ይላል ወጣቱ ስለ ችግሩ ሲናገር ‹‹ስልጠናውን ተከታትለን ልንጨርስ ጥቂት ቀናት ሲቀረን በ15 ቀን እቅድ መጥቶ ወደ ግብርና አግሮ ፕሮሰሲንግ ትገባላችሁ ተብለን በርካታ ወንድሞቻችን ህይወታቸውን አጥተዋል›› ብሏል።

ደረሰብን የሚለውን ችግር በተመለከተም ወጣቶቹን ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ቢያሰባስባቸውም ወጣቶቹን በባለቤትነት ተቀብሎ የሙያ ስልጠናውን የሚሰጠው ሜቴክ ነው። በወጣቶቹ ላይ የችግር አለንጋ መገረፍ የጀመረውም በዚህ ጊዜ እንደሆነ ይናገራል። ሜቴክ በባለቤትነት ተቀብሎ ወጣቶቹን ካሰለጠነ በኋላ መንግስት ለዚህ ሁሉ ወጣት የስራ ዕድል እንደሌለው በመግለጽ ወጣቶቹ ወደ ግብርና አግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲያመሩ (ስለ ግብርና የአንድ ቀን ስልጠና እንኳን አልተሰጣቸውም) ሲነገራቸው ተቃውሞ ያሰማሉ። ይህን ጊዜ ደግሞ የሜቴክ ሰዎች ለመከላከያ በመደወል ችግር እንደተፈጠረ ነግረው አካባቢው በወታደርና በመሳሪያ ይከበባል ይላል ወጣቱ። ከዚያ በኋላም በርካታ ወጣቶች በጥይት ተደብድበው እንደሞቱና ይህን ፈርተው የሸሹ ደግሞ ወንዝ እንደወሰዳቸው ከዚህ የተረፉትም ተይዘው መታሰራቸውን ተናግሯል።

በዚህ ሁሉ መሃል ታዲያ ስለ መብት የሚናገሩትም እየተመረጡ ተይዘው ‹‹ጀርባችሁ ይጠናል፣ የሰላምና የልማት ፀር ናችሁ ወዘተ እየተባለ ስቃይ ይደርስበታል›› ሲል በዝርዝር ይናገራል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ መኳንንት በቀለ የተባለ የአማራ ክልል ተወላጅ ነው። ወጣቱ ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል በተለያዩ የቀን ስራዎችን እየሰራ ኑሮውን ይገፋ እንደነበር ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጾ፤ ኤልሻዳይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና በማንሳት የሙያ ስልጠና እንደሚሰጥ ሲሰማ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሉ እንደገባ ይናገራል። ስልጠናውንም በአግባቡ ተከታትለው ከሰለጠኑ በኋላ ድንገት በተፈጠረ ለውጥ ተስፋቸው ሁሉ መጨለሙን ተናግሯል።

ወጣቱ አስተያየት ሰጪ ስለተፈጠረው ሁኔታ በዝርዝር ሲያስቀምጥ ‹‹ስልጠናውን ካጠናቀቅን በኋላ መንጃ ፈቃዱ ተሰጠን። መንጃ ፈቃዱ የመከላከያ ስለሆነ ከስድስት ወር በኋላ መንጃ ፈቃዱን መልሱና የሲቪል መንጃ ፈቃድ ይሰጣችኋል ብለው ተቀበሉን። እስካሁን ግን የተፈጠረ ለውጥ የለም›› ሲል ቅሬታውን ማሰማት ይጀምራል። መኳንንት አስተያየቱን ሲቀጥልም ‹‹በየክልላችሁ ይሰጣችኋል በተባልነው መሰረት ክልሎቹ ሲጠየቁ ኦሮሚያ እና ትግራይ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። አሁን ደቡብ ለክልሉ ተወላጆች መስጠት የጀመረ ሲሆን አማራ ክልልም እሰጣለሁ ብሏል። እኔም ይህን እየጠበኩ ነው›› ብሏል።

‹‹የእኛ ነገር ወደፊት ስትል ወደኋላ ነው›› የሚለው ደግሞ ሀብታሙ ከበደ የተባለ ወጣት ነው። ወጣቱ በማሰልጠኛ ማዕከሉ ትልቅ ተስፋ ሰንቆ እንደነበረ ገልጾ አሁን ግን ‹‹ምናለ በቀረብኝ›› ማለት እንደጀመረ ተናግሯል። ‹‹ምንም አይነት ተስፋ የሚሰጥ ነገር በሌለበት በርኻ አራት ዓመት መቀመጥ ይሰለቻል፤ ተመሳሳይና ተስማሚ ያልሆነ ምግብ በየቀኑ እየተሰጠን መኖር፤ እንዲሁም በማልፈለገው ሙያ እንድሰራ እሱም ያልተጨበጠ ተስፋ ብቻ አምኖ መኖር ሰልችቶኛል። ጎዳና ብወጣ ወይም የጉልበት ስራ ሰርቼ ብኖር ከዚህ የተሻለ ስራ ሰርቼ መኖር እችላለሁ›› ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።

በሁሉም ወጣቶች ቅሬታ ውስጥ ግን አንድ ነገር አለ ‹‹ኤልሻዳይ ለእኛ የነበረውን ተስፋ እና እየሰራ ያለውን ተግባር እናደንቃለን›› ይላሉ። ወጣቶቹ አያይዘውም ‹‹በአቶ የማነ ወልደማሪያም ላይ የደረሰ የግድያ ሙከራ በእኛ ብቻ ሳይሆን በእሱ እርዳታ በሚያድጉ ህጻናት ላይ የተነጣጠረ ነው›› በማለት ድርጊቱን በጋራ ያወግዛሉ።

የገና ዳቦ ሆንኩ የሚለው ኤልሻዳይ

በአፋር ክልል የኤልሻዳይ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ ደስታ እና ምክትላቸው አቶ መለስ ካሳ ከወጣቶቹ የቀረቡትን ቅሬታዎች በሙሉ ትክክል መሆናቸውን ይናገራሉ። ሁለቱ የድርጅቱ አመራሮች ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ መለስ ካሳ በልጆቹ ጉዳይ የድርጅታቸውን ሚና አስመልክቶ ሲናገሩ ‹‹‹‹ልጆቹ ሰልጥነው ከወጡ በኋላ ያሉትን ጊዜያት በሙሉ በኤልሻዳይ ስር ሆነው አያውቁም። ማህበሩ በማህበር ተቋቋመ እንጂ ባለቤት የለውም። በሁለቱ ዙሮች ልጆቹን አሰልጥኖ ስራ ያስያዛቸው ኤልሻዳይ እንጂ ሜቴክ አልነበረም። ስልጠና የሚሰጠው ሜቴክ ነው። ለስልጠና የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችን ብቻ ነው ሜቴክ ለስልጠና የሚቀርበው እንጂ ስራ አያስይዝም። ኤልሻዳይ ከመንግስት ጋር በመተባበር በሜቴክ ፕሮጄክቶች እንዲመደቡ ሲያደርግ ቆይቷል። በሶስተኛው ዙር ግን የተፈጠረው ችግር እነዚህ ከአስር ሺህ በላይ የሆኑ ሰልጣኞች በሰለጠኑበት ሙያ የሚሆን ቦታ የለም ሲል መንግስት ገለጸ። ስለዚህ ኤልሻዳይ ልጆቹ በእርሻ እንዲሰማሩ ፕሮፖዝ አድርጎ መሬቱን አስፈቀደ›› ሲሉ የነበረውን ችግር መነሻ ገልጸዋል።

መሬቱ ከተፈቀደ በኋላም ቢሆን ችግሩ አለመቀረፉን የሚናገሩት አቶ መለስ የችግሩን ምንነት ሲገልጹም ‹‹መሬቱ ከተፈቀደ በኋላ ሜቴክ ይምራው ተብሎ በሜቴክ ስር አንድ ዓመት ቆየ። ሜቴክ አለመቻሉን የተመለከተው መንግስት ደግሞ ኃላፊነቱን ከሜቴክ አንስቶ ለግብርና ሚኒስቴር አስተላልፎ ሰጠው›› ሲሉ ወጣቶቹ እያነሱት ላለው ችግር ምንጩን ገልጸዋል። ሆኖም ኤልሻዳይ እስካሁን ድረስ ለልጆቹ ምግብና ልብስን በማቅረብ እንዲሁም 40 ሚሊዮን ብር በማውጣት በየወሩ 1400 ብር የኪስ ገንዘብ እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል። ምግቡ የሚገኘው ከመንግስ የእርዳታ እህል ሲሆን ልብሱ ደግሞ ከጉምሩክ በተወረሰ ኮንትባንድ እንደሆነ ገልጸዋል።

ግብርና ሚኒስቴር (እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በሚባልበት ወቅት) ድርጅቱን ከሜቴክ ተቀብሎ ለማስተዳደር ቢሞክርም እስካሁንም ጠብ የሚል ለውጥ እንዳልፈጠረ አቶ መለስ ካሳ ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በሚመራ ስትሪም ኮሚቴ ክትትል የሚደረግበት መሆኑን የገለጹት ምክትል ስራ አስኪያጁ፤ መሬቱን ለልጆቹ ለማስረከብ ኤልሻዳይ 900 ሺህ ብር የሊዝ ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ለግብርና ስራ የተፈቀደው መሬት ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ ሰፊ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል። ለውሃ ዝርጋታ ብቻ ለኦሮሚያ ውሃ ስራዎች የውሃ መስመር ዘርግቶ እንዲያስረክብ 50 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመ አቶ መለስ የተረናገሩ ሲሆን ነገር ግን ከዓመት በላይ ቢሆነውም እስካሁን መስመሩ አለመዘርጋቱን ገልጸዋል።

አቶ መለስ በማብራሪያቸው መደምደሚያ ላይ ሲናገሩ ልጆቹ የሚያነሱት ችግር ትክክል መሆኑን ገልጸው ሆኖም በኤልሻዳይ በኩል የተፈጠረ ክፍተት አለመኖሩን ተናግረዋል። በተለይም ወጣቶቹ የቀበሌ መታቀወቂያ እንኳ እንዲያገኙ የመንግስት አሰራር እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል። እነዚህ ዜጎች የዚህች አገር ዜጎች ሆነው ሳለ የዜግነት መታወቂያ ካርድ እንዲሰጣቸው ስንጠይቅ የመኖሪያ አድራሻ የላቸውም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠን። ኤልሻዳይ ዋስ እንደሚሆናቸው ቢናገርም የሚሰጠው ምላሽ ግን ያሳዝናል›› በማለት ካምፕ ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች ሁሉም የዜግነት መታወቂያ ከመንግስት እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።  

ለጡረተኛ ወታደሮች የስራ ዕድል መፍጠር

ወጣቶቹ ከሚናገሯቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል ቀዳሚው የአስተዳደር ችግር ሲሆን በተለይም የሚመሯቸው በሙያው የተማሩ ምሁራን ሳይሆኑ ከመከላከያ ጡረታ የወጡ ኮሎኔሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህን ደግሞ አቶ መለስም ይጋሩታል። ልጆቹ በኃላፊዎች ይባረራሉ የሚባለው አቤቱታ በሜቴክ ጡረተኛ ወታደሮች እንደሆነ ተናግረዋል። ልጆቹ የሚያነሱትን የመብት ጥያቄም ቢሆን በእምቢታ የሚመክቱትና እርምጃ የሚወስዱት እነዚሁ ጡረተኛ ኮሎኔሎች መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ‹‹እኛ ለስሙ ስራ አስኪያጅ መደብን እንጂ የመወሰን ሙሉ ስልጣን ያላቸው ጡረተኞቹ መኮንኖች ናቸው›› ብለዋል።

መንግስት ከወዴት ነው?

የወጣቶቹ በርካታ ጥያቄዎች ሄደው ማረፊያቸው በአገሪቱ መንግስት የማስተዳደር ብቃት ላይ ይወድቃል። ‹‹ተራራ መግፋት የሚችል ወጣት ለአራት ዓመት ሙሉ ጡረተኛ ሆኖ በበርኻ መሰቃየት የለበትም›› ሲሉ በምሬት ይናገራሉ። በመጨረሻም የችግሮቻቸውን ሰፊ ቅሬታዎች በዚህ አጭር ጽሁፍ አዘጋጅቶ ለማቅረብ ባይቻልም የችግራቸው ሁሉ ቁልፍ ያለው መንግስት ኪስ ውስጥ መሆኑን ግን ለመታዘብ ሞክረናል። ልጆቹም ሆኑ የኤልሻይ የስራ ኃላፊዎች የሚናገሩትም ይህንኑ ነው። ከ3200 በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ባስተላፉት የመጨረሻ መልዕክት ‹‹መንግስት ሆይ ከወዴት ነህ? በርኻ ላይ ቆመው የሚጠሩህን ልጆችህን ድምጽ ትሰማ ዘንድ በዚህ ጽሁፍ በኩል ይድረስህ›› ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

ስማቸውን መግለጽ የማይይልጉ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ መንግስት ሲጀመር ልጆቹን መንከባለብና የስራ ዕድል መፍጠር ያለበት በራሱ መንገድ ነበር። ይህ ማድረግ ካቻለ ደግሞ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያወጣ በሶስተኛ ወገን በኩል ስራውን ማሰራቱ የአስተዳደር ድክመቱን ያመላክታል። ይህን ደግሞ በፖለቲካው መስመር የተሰለፉ ሰዎችም ሲነግሩት ቆይተዋል።

‹‹አሁንም›› ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ‹‹ይህን ያህል ወጣት በአንድ ካምፕ ውስጥ አፍኖ በሙቀትና በርሃብ ከማሰቃየት የችግሩ ምንጭ የት ላይ እንዳለ አጥንቶና አስጠንቶ እርምጃ መውሰድና የልጆቹን ጥያቄም ሳይውል ሳያድር መመለስ ይኖርበታል›› ሲሉ አጥብቀው ይናገራሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ‹‹ኤልሻዳይ የማስተዳደር ብቃት ከሌለውም ተጠያቂ ማድረግ፤ ጡረተኛ ወታደሮችም ቢሆኑ በዚህ ስራ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ መፍቀድ አግባብነት ስለሌለው በቀጥታ ለሚመለከተው ክፍል ልጆቹንና ፕሮጄክቱን ማስተላፍ አስፈላጊ ነው›› ብለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1353 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 822 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us