“የሰላም ድርድሩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ላይ አሉታዊ ሚና እንዳይኖረው ጥንቃቄ ያስፈልጋል”

Wednesday, 27 June 2018 13:19

“የሰላም ድርድሩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ላይ

አሉታዊ ሚና እንዳይኖረው ጥንቃቄ ያስፈልጋል”

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ

 

የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻ የተላለፈውን የአልጀርስ ስምምነት አለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር መወሰኑን ይፋ አድርጓል። የኤርትራ መንግስት በበኩሉ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ መቀበሉን አስተውቋል።

ማክሰኞ ከቀኑ አራት ሰዓት የኤርትራ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል አድርገውለታል።

በዚህ አምድ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚተገበረው የአልጀርስ ስምምነት በምን ደረጃ የሚገለጽ ነው? የኤርትራ መንግስት ለሰላም ድርድሩ የሰጠው ምላሽ አንደምታዎች ምን ይመስላሉ? ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስምምነቱን ከመቀበላቸው ጋር አያይዝው ሕወሓትን ለመጎንተል ለምን አስፈለጋቸው? በድርድሩ የሁለቱ ሕዝቦች ተሳትፎ እንዴት ይታያል? እና የመደመር ፖለቲካን በተመለከተ ከፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ጋር፤ ፋኑኤል ክንፉ ቆይታ አድርጓል።

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ በአሁን ሰዓት በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የዓለም አቀፍ የፀጥታና ደህንነት ፕሮፌሰርና መምህር ናቸው። በአፍሪካ ቀንድ የደህንነትና የፀጥታ ተመራማሪ በመሆን ላለፉት ሃያ አመታት ሰርተዋል። በአፍሪካ ሕብረት የደህንነትና ፀጥታ አማካሪና ተመራማሪ በመሆን አገልግለዋል።

 

ሰንደቅ:- የኢትዮጵያና ኤርትራ የአልጀርሱ ስምምነት ለመተግበር ፈቃደኛ መሆናቸውን እየገለጽ ነው። ወደተግባር ይለወጣል የተባለውን ስምምነት እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡-በመጀመሪያ ሁለት ነገሮች በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። ይህም ሲባል፣ ኢሕአዴግ እየተዘጋጀ ያለው ለሁሉም አቀፍ የሰላም ስምምነት ነው? የተቀበለው የአልጀርሱን ሙሉ ስምምነት ነው? ወይንስ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ነው? የአልጀርሱ ስምምነት ከሆነ ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ነው። ለሰላም ቅድሚያ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀደመ የስምምነት ማዕቀፍ ነው። ይህንን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ አለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ከሆነ ያስኬዳል።

የድበር ኮሚሽኑ ውሳኔን ብቻ ከሆነ የስምምነቱ አንዱን አካል ወስዶ መተግበር ነው የሚሆነው። ይሄ ድንበርን ብቻ ስለሚጐላ ብዥታ ይፍጥራል። አነስ የሚል ስምምነት ነው የሚሆነው። ስለዚህም በግልጽ ማስቀመጡ ተገቢነቱ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ:- አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ የተሻለ ተደርጎ የሚወሰደው የትኛው ነው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር የተሻለ ውጤት ያመጣል። ምክንያቱም በዚህ ሙሉ የስምምነት ሰነድ ውስጥ የሰፈሩትን ነጥቦች መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ይኸውም፣ የጦርነቱን መንስኤዎችን ማየት፤ ድንበር ማካለል፤ የካሳና ቅሬታ ጉዳዮችን ዕልባት መስጠት፤ እነዚህ ሁኔታዎች ወደተግባር ገብተው እስከሚጠናቀቁ ድረስ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሰላም አስከባሪና የፀጥታ ቀጠና መመስረት፤ ሁለቱን ሀገሮች እያነጋገሩ ስምምነቶችን መጨረስ ያጠቃልላል።

ስለዚህ የሚደረገው የሰላም ስምምነት ድርድር ነው። ይህም በመሆኑ፣ ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ማንኛውም ዓይነት ድርድር ማዕከሉ ሰላም መሆን አለበት፤ ይገባልም። ሰላም ሲባል በድንበሩ ጉዳይ፤ በሕዝቡ እንቅስቃሴ፤ የንግድ እንቅስቃሴ፤ የፀጥታ ጉዳይ፤ በሁለቱም የፀጥታ ሓይሎች የሚደረግ ትብብር፤ ይህንን ሁሉ ነው የሚያጠቃልለው። ለሰላም ዝግጁነት ከሌለ የአልጀርስን ስምምነት መፈጸም አይቻልም።

አንዷን የአልጀርስ ስምምነት ውሳኔ ብቻ ነጥሎ ወደ ስምምነት ውስጥ ለመግባት መሞከር ውጤት አያመጣም። ምክንያቱም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻው ድንበር አልነበረም። የግጭቱ መንስኤ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፤ የፀጥታ ጉዳይ ነው፤ በአካባቢው ባለው የኃይል አሰላለፍ ጉዳይ ነው፤ ስለዚህም የግጭቱ መሰረት ሰፊ ነበር። ይህንን በሚፈታ መልኩ ነው የሰላም ስምምነቱ መቃኘት ያለበት። የውይይቱ መድረክ በዚህ መልክ ከሆነ፣ ረጀም ርቀት መጓዝ ያስችላል።

ሰንደቅ:- የኤርትራ መንግስት ለቀረበለት የሰላም ድርድር የሰጠውን ምላሽ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርስ ስምምነትን አለቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ያቀረበውን የሰላም ድርድር፣ የኤርትራ መንግስት የተቀበለበትን ሁኔታ አፅንዖት ሰጥቶ መመልከቱ ጥሩ የሚሆን ይመስለኛል። ይህም ሲባል፣ ከኤርትራ መንግስት ይጠበቅ የነበረው ምላሽ እናንተ (የኢትዮጵያ መንግስት) ከተቀበላችሁት ጥሩ፤ በተመረጠ ቦታ፣ ሸምጋዮች በተገኙበት፣ ቅድመ ሁኔታዎች ተነስተው፣ ለመወያየት ዝግጅት እናደርጋለን የሚል ነበር። ይህ ማለት የመቀበል የመጀመሪያው ምላሽ ነበር የሚጠበቅበት። የኤርትራ መንግስት ያደረገው ዘሎ ወደ አዲስ አበባ ልዑክ እንልካለን ነው ያለው።

እዚህ ላይ መታየት ያለበት፣ በየትኛው ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ነው ወደ አዲስ አበባ ልዑክ እልካለሁ የሚል ምላሽ ያቀረበው። ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው የኤርትራ ልዑክ፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ለውይይት ነው? ወይንስ ለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ነው? ወይንስ ለአልጀርሱ ሙሉ ስምምነት ነው? ለዚህም ነው ምላሹ ጥያቄ የሚያጭረው።

ለምን ቢባል፣ የኤርትራ መንግስት በድንበር ግጭቱም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በአካባቢው ፀጥታ ጉዳይ የነበረው አቋም ይታወቃል። ከነበረው አቋም አንፃር የኤርትራ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ሁለቱም ሀገሮች እንደሁለት ሉዑላዊ ስልጣን እንዳላቸው አካሎች ቆጥረው በኢትዮጵያ በኤርትራ ጉዳይ ሰላም ሊያመጣ የሚችል የአልጀርስ ስምምነት መፈተሽና መነጋገር ላይ ነው ማተኮር ያለባቸው። ይህ ጉዳይ በግልፅ መቀመጥ አለበት። ለነገሩ አሁን የመፈታተሽና የመጠናናት ጊዜ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ በኩል ጊዜ ወስዶ ሃሳቦችን ቀምሮ ለመደራደር ትንሽ እርጋታ ያስፈልጋል። አሁን አስፈላጊ የመፈተሻ ጥያቄዎች ከተጠየቁም በቂ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥ ኢሕአዴግ ውስጥ ባሉ እና ከኢሕአዴግ ውጪም ባሉ ኢትዮጵያዊ ኃይሎች ብቻ የመጣ ለውጥ ተደርጎ መሰመር አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣን በጐ ለውጥ የኢትዮጵያውያን ባለቤትነት ብቻ የተረጋገጠበት ሆኖ መውጣት አለበት። ሌሎች የለውጥ አካል ነን ብለው ተደርበው ባይገቡ፣ ይመረጣል። አይጠቅምም። ሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ ይመለከተናል ብለው ለመደራደር ለመነጋገር እንመጣለን ሲሉ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የእራሱን አቋም በግልጽ መያዝና ማስቀመጥ አለበት። ምክንያቱም የትኛውም ድርድር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። በነፃነት የሚካሄድ ድርድር መሆን አለበት። የቅርብ ጊዜ የመጐዳት ታሪካችንም የሚያስተምረው ይሄን ነው።

ሰንደቅ:- ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ድርድሩን መቀበላቸው ባሳወቁበት ንግግራቸው፣ የሕወሓት ጉዳይ ያበቃለት ጨዋታ ነው ሲሉ የሰላም ጥሪውን ለመቀበል እንደአንድ ምክንያት አስቀምጠዋል። ይህ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ መግባት ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆን?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ባለቤቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ኢትዮጵያዊያን የጣልቃ ገብ ፖለቲካ ፈጽሞ መፍቀድ የለባቸውም። የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው ጥሪ የአልጀርስ ስምምነቱን ዓለምን ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ የኤርትራ መንግስት መፈትፈት የሚጠበቅበት አይመስለኝም። በኢትዮጵያም በኩል እንዲሁ። በተመሳሳይ ሁኔታም፣ በኤርትራ የውስጥ ፖለቲካም ማን ስልጣን ያዘ፣ ማን ወረደ፣ ቀጣይ የኤርትራ ፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚሉት ጉዳዮች ለኤርትራውያን መተው ብቻ ነው። በኤርትራ ጉዳይ ሶስተኛ ወገን ገብቶ ቢፈትፈት ተገቢ አይደለም።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ የፖለቲካ ጨዋታው አልቋል ማለታቸው ቢያንስ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታ መኖሩን አምነዋል። በአስመራ ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታ ፈጽሞ የሚታስብ አይደለም። ስለዚህ በአሉታዊ መልኩ የፖለቲካ ጨዋታ የሚለውን አስቀመጡት እንጂ ፕሬዝደንት ኢሳያስ፣ ለፖለቲካ የሚሆን ከባቢያዊ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ማመናቸውን መውሰዱ ጠቃሚ ነው። በኤርትራ ውስጥ፣ የምጣኔ ሃብት ደረጃውም የዜጎችም ነፃነት መፈናፈኛ በሌለበት የመጨረሻው ደረጃ ይዘው ነው የሚገኙት። የዜጎች መፍለስ እንደሕዝብ ኤርትራን ሊያጠፋት ከጫፍ ደርሷል። ሕገመንግስት የሌለበት ሀገር ነው። በአንፃራዊነት ከወሰድነው በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሽግግር ቢያንስ እንደ ሂደት የተሻለ ነው።

ስለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፖለቲካ ላይ ተንተርሶ ከኢትዮጵያ ጋር እንነጋገራለን፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ አዝቅት እንዳትገባ የድርሻችን እንወጣለን ተብሎ በአንድ ሉዐላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ለመግባት መሞከር፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሽግግርን ያበላሸዋል። ዴሞክራሲውን ያበላሸዋል። ከኤርትራ ጋር የሚደረገውን ድርድር ሙሉ ለመሉ ያበላሸዋል። ከመጀመሪያው ነገሮቹን ለያይቶ ማየት የግድ ነው።

ሰንደቅ:- ፕሬዝደንት ኢሳያስ የሕወሓት የፖለቲካ ጨዋታ አብቅቷል የሚለው አገላለፃቸው፤ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጀመር ምክንያቶች ጋር እንዴት ነው የሚታየው? ወይም ዝምድናው ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ጦርነቱ በኤርትራ በኩል እንደተጀመረ የካሳ ኮሚሽኑም አረጋግጧል። ከታሪክም ከፖለቲካም አንፃር ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም። እንዳውም በኤርትራ ጉዳይ ሕወሓት የተወቀሰው፣ ሕዝባዊ ግንባር ሐርነት ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለገ እንዲፈነጭ አድርጓል በሚል ክስ ነው። ይኸውም፣ ለኤርትራ ነፃነት ድጋፍ ሰጥቷል፤ ተሽቀዳድሞ ዕውቅን ሰጥቷል፤ ከስሜት አንፃር ለኤርትራ ያዘነብላል የሚሉ ክሶች ናቸው ሲቀርቡበት የነበረው። ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ከፍተኛ ክሶች ይቀርቡበት ነበር።

አሁን ይህንን ገልብጠው፤ የኤርትራ መንግስት ሕወሓት በሌለበት ነው ብሔራዊ ጥቅማችን የምናስከብረው ማለታቸው አስገራሚ ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ እንደፈለግን መንቀሳቀስ የምንችለው ‘የሕወሓት ተፅዕኖ በቀነሰበት ወቅት’ ነው ማለታቸው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ዓይነት መልዕክት እንደሚሰጥ ግልፅ ነው። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻም ምን እንደነበረ በግልጽ ያሳያል። የጦርነቱ መነሻ፣ አለከልካይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ የመሳተፍ ስትራቴጂ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ አንጋሽና አውራጅ መሆን። ይሄ ምኞት ተቀይሯል አሁን? መረጋገጥ አለበት። የኤርትራ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተመሰረተው፣ በቀንዱ ሀገሮች ባሉ ኃያላን ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የኤርትራን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተንቀሳቅሶ የሀገራቱን ዝምድና መቀየር ነው። ይህ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በየመን፣ በኢትዮጵያም ተሰርቶበታል። ለቀጠናው መረበሽ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበረውም፤ ይኸው የኤርትራ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የነደፉት ፖሊሲያቸው ነው።

በዚህ ፖሊሲያው መነሻ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። ምንም ሰላም ምንም ጦርነት የሌለበት ቀጠና ፈጥረው ተቀምጠዋል። ለሁለቱም ሕዝቦች የማይበጅ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ይህንን ወደሰላም እናምጣው ስንል፣ የጦርነቱ ምንጭ ምን ነበር? የመሬት ጉዳይ ጦርነቱ እንዲነሳ በትክክል አስተዋፅዖ ነበረው ወይ? የጦርነቱን መነሻ ረስተን ችግሩን ሳንፈታ ኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ እንችላለን ወይ? ብለን ወደኋላ መመለስና ማየት አለብን። ይህንን የምናደርገው፣ ለመካሰስና አንዱ አጥፊ ሌላው ተበዳይ የሚል ዳኝነት ለመስጠት አይደለም፤ ወይም ቂም ቁርሾ ለመተው አይደለም። የፈለግነውን ሰላምም ለማበላሸት አይደለም። በትክክል ችግራችን ምንድን ነው ብለን ለመወያየት ከስሩ ለመፍታት እንዲያግዘን ነው።

የጦርነቱ መነሻ ለጊዜው የሰላም መዝሙር ሲባል ገሸሽ ማድረጉ ጠቃሚ ቢሆንም፣ እውነተኛ የሰላም ድርድር ውስጥ ሲገባ እነዚያ የጦርነት መነሻው የነበሩ ምክንያቶች ናቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ መፃዒ እድሎችን አቅጣጫ የሚወስኑት። ጥያቄዎችን ከጦርነት ይልቅ በሰላም እንዴት እንፍታቸው ነው? ተሳስተን በጦርነት የፈታናቸው ለጦርነቱ መነሻ የነበሩ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የአካባቢው ፀጥታ እና የኃይል አሰላለፍ የበላይነት ጉዳዮችን በሰላም በንግግር እንዴት እንፍታቸው ነው? ይህም ሲባል እንደ ሁለት ልዑላዊ ሀገሮች ማለት ነው። ወደዚህ ነው መምጣት ያለብን።

አሁን በኤርትራ በኩል ያለው ዕሳቤ በሰላሙ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እደራደራለሁ ግን የተወሰነ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ኃይሎች ስለተዳከሙ ይህንን እድል ልጠቀምበት እችላለሁ፣ ይህንን አጋጣሚ መጠቀም አለብኝ፣ ከሚል መነሻ ከሆነ በግልፅ ጉዳዩን አውጥቶ እንደማይሰራ፣ ሁለቱን ሕዝቦችንም እንደማይጠቅም ማስመር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሰላምም አያመጣም፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል።

ሰንደቅ:- በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ያሉትን ሕዝቦች ማሳተፉስ እንዴት ነው ታሳቢ የሚደረገው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በሁለቱ ሀገሮች መተግበር ከተቻለ ምላሽ አለው። በነገራችን ላይ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጣ መንገድ የሚያልፈው በጎንደርና በትግራይ ነው። የሰላሙም መስመር የሚያንጸባርቀው ይሄንኑ ነው። እንደው ዘለህ በአውሮፕላን ከሚኒልክ ቤተመንግስት ጋር በተሳሰሩ ጉዳዮች ላይ ብቻ ተመስርተህ ሰላሙን አመጣዋለሁ ማለት ሰላሙን ከማበላሸቱ ውጪ የሚፈይደው ነገር አይኖርም።

ሰንደቅ:- ያለፈው አልፏል፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ አዲስ ምዕራፍ መጀመር አለባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ያለፈው አልፏል ማለት እኔ እስከሚገባኝ፣ በጦርነትና በግጭት አንቀጥልም እንጂ ምንም ስላለፈው ነገር አይነሳ ማለት አይመስለኝም። ያለፈውን ሳናነሳ እንዴት መደራደር እንችላለን? አዲሱ ምዕራፍ የሚሆነው፣ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነቶች ምን መምስል አለባቸው? በድንበር ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች እንዴት ይንቀሳቀሱ? ነፃ እንቅስቃሴ እንዴት ይሁን? የኢኮኖሚ ግንኙነቶች እንዴት ይሁኑ? የስልጣኔና የባህል ሽርክናችን እንዴት ነው የምናበለፅገው? መዳበር ያለበት በአካባቢው ፀጥታ ላይ በትብብር እንዴት ነው የምንሰራው? እነዚህን የመሳሳሉ ጥያቄዎችን አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በመነሳት ምላሽ መስጠት ነው።

ሰንደቅ:- የመደመር ፖለቲካ መርህን እንዴት አገኙት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- መደመር የሚባለው አስተሳሰብ እኔ የሚገባኝ፤ ሰፋ ያለ ሀገራዊ መግባባት ቅርጽ አድርጌ ነው የምወስደው። ይህ ማለት፣ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያዊያን ተመሳይይ አቋም እንድንይዝ እንዲኖረን ማድረግ ነው። የክፍፍል፣ የጥላቻ፣ የቂም፣ የመጠላለፍ፣ የመጠላላት በተለይ በዘር በሃይማኖት በፖለቲካ አቋም ሊሆን ይችላል፤ ይህንን አስወግደን እንደአንድ ሀገር ማሰብ አለብን ነው።

ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሳነሳው የነበረው፣ ከብሔር ይልቅ ወደ ዜግነት ማድላት አለብን። ምክንያቱም ሁሉም ዜጋ ሲሆን፤ ይደመራል። የዜግነት መብትና ግዴታችን ሁላችንም ላይ በአንድ ዓይነት መፈጸም አለበት። ይህንን አስተሳሰብ ማስረጽ ይገባል። አንድ ሀገር ነው ያለን፤ ስለዚህም ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ማተኮር አለብን። መደመር ማለት በዚህ መልኩ ነው የሚገባኝ።

ከዚህ ውጪ ግን በምንወስዳቸው ርዕዮተዓለምና የፖለቲካ አቋሞች ላይ፤ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መደመር አለባቸው ማለት አይደለም። ምክንያቱም የፖለቲካ ብዝሃነት ይቀንሳል። ዴሞክራሲያዊ ሂደቶችንም ይደፈጥጣል። ከገዢው ፓርቲ በተቃራኒ የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን የመቀነስ፣ የማግለል ሁኔታዎች እንዳይፈጠር በጥንቃቄ መያዙ ጠቃሚ ነው። መደመሩ ሌሎችን እንዳይቀንስ ማስተዋል ይጠይቃል። በመደመር ፖለቲካ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በዜግነታቸው የሚመስላቸውን የፖለቲካ አቋም አደረጃጀት ይዘው፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ልዑላዊነትን በሚያስከብር መልኩ በሕገመንግስታዊ ሥርዓት በሕግ የበላይነት ላይ አንድ ዓይነት ጥላ ሥር ይሰባሰባሉ ነው። ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ኢትዮጵያዊ ነው፤ እንደማለት ነው።

ዋናው መደመር ማለት የተለያየ አቋምና ዳራ ያለው የአንድ አገር ዜጋ በአንድ የረዥም ጊዜ የብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ጥላ ስር ሲቀመጥ ነው።

ሰንደቅ:- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የለውጥ እርምጃ ፍጥነት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን አጀንዳ ጨርሶ ወስዶታል፤ በገዢው ፓርቲ ውስጥም መንገራገጭ ፈጥሯል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ነጥብ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ከዚህ በፊት የተቃዋሚ ጎራውን የፖለቲካ ካርድና አጀንዳ ጠቅልሎ የመወስድ እድላቸው ሰፊ መሆኑን አንስቼዋለሁ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍጥነት ተቃዋሚ ጎራውን ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ ውስጥ ይኸው ፍጥነት የፓርቲውን ባሕሪ በሚቀይር መልኩ እየተጓዘ ይመስለኛል። በኢሕአዴግ ውስጥም፣ በተቃዋሚው ጎራም መደናበር መፈጠሩ አይቀርም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በያዙት ፍጥነት ሲታይ፣ በአንድም በሌላ መልኩ ተቃዋሚ ኃይሎች አብረዋቸው እንዲሰሩ እድል የሚፈጠር ነው። ይህ ማለት አጀንዳው እየተወሰደ በሄደ ቁጥር የተወሰነው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልል ውስጥ መግባት ሀገራዊ ፓርቲ ክልል ውስጥም መግባት የምናይበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። አዲስ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ የሚፈጥር ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሯል። አዲስ የፖለቲካ ካርታም (political trajectory) ተፈጥሯል። የኃይል አሰላለፉ ጠርቶ መልክ እስኪይዝ ድረስ፣ እንዲሁም የመደመር ፖለቲካ ተጨምሮበት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች እነማን ናቸው? እራሳቸውን ችለው የቆሙ ጠንካራ፣ ደካማ የምትላቸው መልኩ መለየት በሚያስቸግር መልኩ ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል። አጠቃላይ በሀገር ደረጃ ግን የኃይል አሰላለፉን እየቀረው ነው።

ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ፍጥነት የፖለቲካ መነቃቃቱን እንዲጨምር አድርጓል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ኃይሎች በተለያየ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ እድል ፈጥሯል። በአንድ መልኩ ለዴሞክራሲው ማበብ ጠቃሚ ነው። ሁሉም ዜጋ ፖለቲካ ያገባኛል የፖለቲካ መድረኩን ተጠቅሜ ድምፅን ማሰማት እችላለሁ የሚል እምነት እንዲይዙ አስችሏል። በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለመያዝ እድሉ አለ የሚል ተስፋም እንዲያጭር አድርጓል። ይሄ በጣም በጐ ነገር ነው።

ከኢህአዴግ አንፃር ከወሰድነው፣ ከደረስንበት የማንነት ቀውስ ጋር በተያያዘ መልኩ አዲስ የኃይል አሰላለፍ የመፈጠር እድሉ እየጨመረ ነው። አንዱ ትልቁ ለውጥ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሙሉ ለሙሉ መዳከም ነው ያመጣው። ቀደም ባሉት ጊዜ በአንድ ጉዳይ ላይ አራቱም ፓርቲዎች ተወያይተው አንድ አቋም ይዘው በተባበረ ድምጽ ይሰሩ ነበር። አሁን ግን በአንድ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ ተቃውሟቸውን ማሰማት መጀመራውን ነው። ቅሬታው የሚገለጸው በውስጣዊ የድርጅቱ መስመር ቢሆን አንድ ነገር ነው። ቅሬታዎቹ እየቀረቡ ያሉት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ነው። ሙሉ ለሙሉ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሌለበት መልኩ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ይህ ማለት ዴምክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሲዳከም ለአዲስ ግልጽ የወጡ የፖለቲካ ሹኩቻዎች በር ይከፍታል። በአራቱ ድርጅቶች ጭምር። የፖለቲካ ልጓም የሚይዘው ነገር የለም። ከዚህ አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍጥነት ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ፍጥነት እኩል አይሆንም። ፍጥነቱ በጨመረ ቁጥር ልዩነቶቹ እየሰፋ ነው የሚሄዱት። ኢሕአዴግ ከማንነት ቀወስ ወደ መሰንጠቅ መሸጋገሩ አይቀርም። ከዛ ወደ አዳዲስ ስብስቦች ሊሸጋገር ይችላል። ለምሳሌ የተወሰኑት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከሌሎች የብሔር ድርጅቶች ጋር መቀናጀትና መተባበር በሚያስችል መልኩ አዳዲስ ጥምረቶች እየተሰሩ የሚፈርሱበት ሂደት ሊፈጠር ይችላል። ዶ/ር አብይና ዋነኛው የኢህአዴግ ክፋይም ተቃዋሚዎችን በተወሰነ ደረጃ ባካተተ መልኩ አንድ ጣምራ አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመፍጠር ሊገደድ ይችል ይሆናል። የገዢ ፓርቲና የተቃውሞው ጐራ መደባለቅና ፍጥነቱን ስትረዳ አዳዲስ የልሂቅ ድርድሮችና ውሎች (Elite Bargain & Elite Pact) የሚመጣበት እድልም ሰፊ ነው። ለዚህ ሁሉ ዋናው ተቋማዊ የሆነና አሳታፊ በሚባል መልኩ ሂደቱን ማስኬድ ነው።¾

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
710 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1035 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us