“በፈረሰ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ከሚኖር ባልፈረሰ አገር ውስጥ አምባገነንነት ይሻለኛል”

Wednesday, 18 July 2018 15:26

“በፈረሰ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ከሚኖር

ባልፈረሰ አገር ውስጥ አምባገነንነት ይሻለኛል”

አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር

በይርጋ አበበ

አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ የተመረቁ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ማስትሬታቸውን) ደግሞ ከዚሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአፍሪካን ፖለቲካል ጥናት (African Political Studies) ተምረዋል። በደቡብ ሱዳን ግጭት ከዳራው እስከ መፍትሔው ትኩረት ባደረገ መልኩ ጥናታቸውን አካሂደዋል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሲቪክስ ትምህርት በማስተማር ላይ ሲሆኑ በወቅታዊ ጉዳዮችና በኢትዮ ኤርትራ አዲስ ግንኙነት ዙሪያ ለሰንደቅ ጋዜጣ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች አዲስ ግንኙነት ጀምረዋል፤ ለ20 ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የኤርትራ ኤምባሲም በአዲስ አበባ ተከፍቷል። ከዚህ በኋላ በሁለቱ አገራት ሊኖራው የሚችለው ግንኙነት ምን መልክ ይኖረዋል? የሚያገኙት ጥቅምስ ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ ቴዎድሮስ፡-የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሊኖረው የሚችለውን መልክ ከማየታችን በፊት የሁለቱን አገራት ተጠቃሚነት እንመልከት። የኤርትራ መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገልሎ የኖረና በአካባቢው አገራትም ጠብ አጫሪነት ተለይቶ የሚታወቅ ነው። ለኢትዮጵያ መንግስትም የጎን ውጋት መሆኑ ነው የሚነገረው። ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ባለመኖሩም በኢኮኖሚ በጣም እየተጎዳ ያለ መንግስት ነው። ወደቦቹንም ቢሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማንም የሚጠቀምበት ስላልነበረ ኢኮኖሚውን ማሳደግ አልቻለም ነበር።

ከኢትዮጵያ አንጻር የሚሰጠውን ጥቅም ካየነው ደግሞ አንድ አጭር ምሳሌ ብናነሳ ሲሚንቶ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ አጓጉዞ መሸጥ በማርኬቲንግ ስሌት ሲታሰብ ምንጊዜም ኪሳራ ነው። ከኤርትራ ጋር ሰላም ከሆንን መሰቦ ሲሚንቶ ቀጥታ ፋብሪካው ከሚገኝበት መቀሌ እስከ አስመራ 300 ኪሎ ሜትር ነው የሚርቀው። ስለዚህ አስመራን ጨምሮ የኤርትራ ከተሞችን መቆጣጠር የሚስችለውን አቅም ያገኛል ማለት ነው። ከመቀሌ ተነስቶ አዲስ አበባ ለመግባት የሚወስደበት ርቀት ግን አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ነው።

እንደዚህ አይነት የሰላም ግንኙነቶች የሚኖራቸው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም። በምርቶችና ሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚስከፍለው የትራንስፖርት ማጓጓዣ ዋጋው ነው። ከውጭ የሚመጡ እቃዎችን ከጅቡቲ መቀሌ ወይም ከጅቡቲ ወልድያ ኮምቦልቻ ለማጓጓዝ የሚወስደውን ጊዜና የትራንስፖርት ዋጋ ስታስብ በአሰብ በኩል በሚመጣበት ጊዜ የሚኖረውን ቅናሽ ቀላል አለመሆኑን ትረዳለህ። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የባህል፣ የቋንቋ እና ሌሎች ተመሳስሎሾች በኩልም የሚኖረው ግንኙነት ቀላል አይደለም።

በርግጥ ጥቅሙ ለማን ያጋድላል? ካልከኝ እርቅ ሲፈጸም እከሌ ተጠቀመ እከሌ ደግሞ በጣም ተጎዳ የሚል ባይገለጽም፤ ከኢትዮጵያ ይልቅ ኤርትራ ያገኘችው የዲፕሎማሲ ድል ከፍተኛ ነው። ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ‹ከመጀመሪያውም ጀምሮ እኛ ትክክል ነበርን፤ ማዕቀብ የተጣለብንም ባልተገባ ሁኔታ ነው እንጂ ለቀጠናው ሰላም መስፈን የምንፈልግ ነን› ሲሉ ራሳቸውን የሚያሳዩበት ይሆናል።

የአሰብን ወደብ ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ተመጣጣኝ ክፍያ ብታስከፍል ራሱ ለኤርትራ የሚገባው ገቢም ቀላል አይሆንም። ጤፍን ጨምሮ እንደ ቡና ያሉ አገር በቀል ምርቶችም ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ በስፋት ስለሚገቡ ለኤርትራዊያን ተጨማሪ ጥቅም ይሆናል።

ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለው ሰላም መፍጠሩ እና በኢኮኖሚ በኩልም ቢሆን ከቅርበቱ አንጻር የአሰብን ወደብ መጠቀም ከቻለች ተጠቃሚ የሚደርጓት መስኮች ናቸው። ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ የነበረው ከኤርትራ የሚነሱ ራሳቸውን የነጻነት ሀይሎች ብለው የሚጠሩ በኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ አሸባሪ ተብለው የሚጠሩ ድርጅቶችን ማስጠጋቷ ነበር። አሁን ሰላም መፈጠሩ ይህን ስጋት ለኢትዮጵያ መንግስት ያስቀርለታል። በእርግጥ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላም ባይፈጠርም አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ከተፈጠረ የነጻነት ሀይሎች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያደርሱበት ጫና ይቀራል። ምክንያቱም መጀመሪያም የነጻነት ሀይሎቹ ኤርትራ የገቡት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ስላልነበረ ነውና።

 

 

ሰንደቅ፡- አቶ ኢሳያስ በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ሲናገሩ ‹‹ያለፈውን ጥላቻ እና የተሰራብንን ሴራ ትተን..›› የሚል ሀረግ ተጠቅመዋል። ከዚህ ንግገራቸው ተነስተን የኢትዮጵያ ህዝብ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ ያለውን እይታ የተላበሰው በኢትዮጵያ መንግስትና ሚዲያዎች በተሴረባቸው ሴራ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ ቴዎድሮስ፡- ይህ እንግዲህ በአፍሪካ አገራት በተለይም አምባገነን የሆኑ መሪዎች ሰብዕናን በመግለጽ በኩል ሚዲያ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በነገራችን ላይ አንድ መንግስት አምባገነን ነው ወይስ ዴሞክራት? የሚለውን ለመለየት ህዝብ መቶ በመቶ ካጨበጨበለት ስርዓቱ አምባገነን ነው ማለት ነው። ያ አምባገነንነት የሚፈጠረው ደግሞ ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ ነው። ለምሳሌ ሳዳም ሁሴን ምርጫ አካሂደው 99 ነጥብ 9 ፐርሰንት አሸንፈው ነበር። በዴሞክራሲ ስርዓት መቶ ፐርሰንት የሚባል ድጋፍም የምርጫ ውጤትም የለም። ሚዲያዎች ደጋግመው ባቀነቀኑ ቁጥር ማንኛውም ህዝብ በጉዳዩ ላይ ጫና ውስጥ መግባቱ አይቀርም። አቶ ኢሳያስ ላይም ሚዲያው የፈጠረብን ተጽኖ መኖሩ አይቀርም። በእርግጥ አቶ ኢሳያስ አምባገነን መሆናቸው አያጠያይቅም። ኤርትራንም ቢሆን ምንም አላሸገሯትም።

ሰንደቅ፡- አቶ ኢሳያስ አገራቸውን በኢኮኖሚ ላለማሳደጋቸው የሚያቀርቡት ምክያት ‹‹ህወሓት ነው ማዕቀብ አስጥሎብኝ›› በማለት ነው። ማዕቀቡ አቶ ኢሳያስ ላይ ተጽዕኖ አላሳደረባቸውም ብሎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ ቴዎድሮስ፡- የፈለገ ማዕቀብ ቢጣልብህ ህገ መንግስት ለማውጣት ምን ይከለክልሃል? ማዕቀብ እኮ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችለው እርዳታ በመቀበልና የንግድ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድር ይሆናል እንጂ ዴሞክራቲክ ላለመሆን ማዕቀብ የሚያሳድረው ሚና የለም። ያለ ህገ መንግስት እና ያለ ምርጫ 27 ዓመት ሙሉ እንዴት አገር ይመራል? ባለስልጣኖቹን ስትመለከታቸው እኮ አብዛኞቹ ከአቶ ኢሳያስ የበለጠ ዕድሜ ያላቸው ናቸው።

በ1955 በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የህገ መንግስት ማሻሻያ እንዲካሄድ የነበረው አስገዳጅ ሁኔታ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን ማዋሃዱ ነው። በዚያ ወቅት ኤርትራ የተሻሉ ህገ መንግስት፣ ህጎች እና ስልጣኔዎች ነበሯት። እነዛ ነገሮች ተጽዕኖ አድርገው ነው ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል ያደረገው። አሁን ደግሞ በተቃራኒው በኢትዮጵያ ያለው ከኤርትራ የተሻለ ነው። ይህንን ደግሞ አቶ ኢሳያስ በተመለከቱት ሁሉ ሲገረሙ ታይተዋል።

አሁን የኤርትራ ህዝብ መንግስታቸውን መጠየቅ ይጀምራሉ። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ እና በዶክተር አብይ በራሳቸውም ላይ የሚመለከቱት ለውጥ ለአቶ ኢሳያስ ትምህርት የሚሆን ነው። በአንጻራዊነት ከኤርትራ የተሻለ የዴሞክራሲ ምልክት በኢትዮጵያ መኖሩንም ኤርትራዊያን ስለሚመለከቱ በመንግስታቸው ላይ ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። ለምሳሌ ተግባራዊ አይደረግ እንጂ ህገ መንግስት በኢትዮጵያ አለ በኤርትራ የለም፤ ምርጫ በኢትዮጵያ አለ በኤርትራ የለም።

 

ሰንደቅ፡- ምርጫንና ህገ መንግስትን በተመለከተ በአንድ ወቅት ከአልጀዚራ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ‹‹ምርጫና ህገ መንግስትስ የምትሉን ወያኔ እንደሚካሂደው አይነት ነው?›› ሲሉ በኢትዮጵያ ያለውን ሂደት ተችተውት ነበር። ይህን እንደ ዴሞክራሲ ማየት ይቻላል ወይ?

አቶ ቴዎድሮስ፡- እንግዲህ አምባገነንነት ሲስተማቲክና የወጣለት አምባገነንነት አለ። በኢትዮጵያ ያለው አምባገነንነት ሲስተማቲክ የሚባለው አይነት ነው። በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይካሄዳል ህገ መንግስትም አይከበርም እንጂ አለ። ሲስተሞቹ ተዘርግተዋል ጥቅም ላይ አልዋሉም እንጂ። እዛ ደግሞ ምንም የለም። ህገ መንግስት ብለህ የምትጠቅሰው ወረቀቱም እንኳን የለም።

የአቶ ኢሳያስም በንግግራቸው ራሳቸውን ከህወሓት ጋር ማወዳደርም የለባቸውም። ይህ ምክንያት አይሆንም። በአጭር ጊዜ እንደ ቦትስዋና እና ሞሪሺየስ በአፍሪካ ተጠቃሽ የሆኑ አርዓያዎች አሉ። ለምን እነዛን ተጠቃሽ አላደረጉም? ህገ መንግስት እንዳይኖርህ ህወሓት እንዴት ምክንያት ይሆናል? ህወሓት “ህገ መንግስት አያከብርም”፤ እሳቸው ደግሞ ማክበር፡ ህወሓት “ምርጫ ያጭበረብራል” እሳቸው ደግሞ አለማጭበርበር እንጂ የህወሓትን ድክመት እያነሱ ማነጻጸሪያ ማቅረብ መፍትሔ ሊሆናቸው አይችልም።

 

 

ሰንደቅ፡- አቶ ኢሳያስ ልጃቸውን ለስልጣን እያጩት እንደሆነ ይነገራል። ከሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በኋላ ከስራቸው እንዳይጠፋ አድርገውታል ይባላል። በቅርቡም ዶክተር አብይ አህመድ የአቶ ኢሳያስን ቤት ሲጎበኙ ልጃቸው በአባቱ ቤት ታይቷል። ቀጣዩ የኤርትራ መሪ ከኢሳያስ ቤት የሚወጣ ይመስለዎታል?

አቶ ቴዎድሮስ፡- አሁን ባለው ሁኔታ ህገ መንግስት እና የምርጫ ስርዓት ከሌለ ልጃቸውን የማይተኩበት ምክንያት አይኖርም። ስልጣን እንዴት እንደሚተላለፍ የሚገልጽ ነገር የለም። ግን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በኤርትራ ለውጥ እንደሚኖር ነው ልጃቸው ስልጣን ያዘም ሌላ ሰው ተረከበው። ለምሳሌ በኩባ ፊደል ካስትሮ ሲደክሙ ስልጣኑን ወንድማቸው ራውል ካስትሮ ሲረከቡ ከአሜሪካ ጋር የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ለማስተካከል ሞክረዋል። የሰሜን ኮሪያም በተመሳሳይ ነው ያደረጉት።

እኔ ተስፋ የማደርገውም አቶ ኢሳያስና ካቢኔያቸው ይህን ዘመን ነበር የሚናፍቁት። ስለዚህም ስልጣናቸውን ለሌላ አሳልፈው ይሰጣሉ ብዬ ነው የምጠብቀው።

 

ሰንደቅ፡- ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወዳጅነታቸውን በአዲስ መልክ ቢጀምሩም በጦርነቱ ወቅት በሁለቱም ወገን የወታደር ምርኮ ነበር። እስካሁን በምርኮኛ መመለስ ዙሪያ የተነገረ ነገር የለምና ወደፊት ምርኮኛን በመመላለስ ዙሪያ የሚኖር ለውጥ ይኖር ይሆን?

አቶ ቴዎድሮስ፡- ከቀናት በፊት ጽንፈኛ አክቲቪስቶች ይናገሩ የነበሩት እስካሁን የተካሄደው እርምጃ ምን ጠቀመ? በተለይ አቶ ኢሳያስ አማርኛን እና አማራን ይጠላሉ የሚሉ ነገሮች ነበሩ። በቀደም በሚሊኒየም አዳራሽ የተደረገው ነገር ቀደም ሲል በጽፈኞች የተነገረውን ‹‹ፉርሽ›› ነው ያደረገው። ምርኮኛንና አስረኛን በመመላለስ ዙሪያ በስምምነታቸው ስድስት ነጥቦች ላይ ብዙም አልተጠቀሰም። ትልልቅ ቁም ነገሮች ስለተፈቱ እንደዚህ አይነት ነገሮችን መፍታት ቀላል ነው ብዬ ነው የማስበው። የታሰሩትም ሆነ የተማረኩት ሰዎች በህይወት ካሉ ወይም ደግሞ በመጥፎ ሁኔታ ስር ታስረው ከሆነም በቅድሚያ አዕምሯቸውን መመለስ ይኖርባቸው ይሆናል። ምክንያቱም በዚህ ሰዓት ቢለቀቁና የደረሰባቸውን ሁሉ ቢናገሩ ግንኙነቱ ላይ ሌላ ጥላ የሚያጠላ ይመስለኛል።

እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ሰዎቹ ጠላት ተብሎ በተለየ ቡድን ውስጥ የተማረኩ በመሆናቸውና ሁለቱም መንግስታት የጉሬላ ተዋጊ ባህሪ ስላላቸው በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ብዙ ትችት የሚቀርብባቸው መንግስታት ናቸው። የራሳቸውን ዜጋ የሚያሰቃዩ መንግስታት ስለሆኑ የጠላታቸውን ወታደርም በአሰቃቂ ሁኔታ የማይዙበት ምክንያት አይኖርም ብሎ መገመት ይቻላል። ስለዚህ እስረኞቹና ምርኮኞቹም ላይ እንደዚህ አይነት አሰቃቂ አያያዝ ተደርጎባቸው ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ኮሎኔል በዛብህ ሁለትና ሶስት ጊዜ ነው የኤርትራን መንግስት በጀት የደበደቧቸው።

 

ሰንደቅ፡- ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንመለስ። ዶክተር አብይ እየሄዱበት ያለውን መንገድ በኢህአዴግ ውስጥ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል ይባላል። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ የነጻትንና የዴሞክራሲን ዋጋ አልተረዳም የሚሉ አስተያየቶች አሉ። እነዚህ ሁለት አካሄዶች ወዴት ያመሩናል?

አቶ ቴዎድሮስ፡- በመጀመሪያ ከውስጣቸው የገጠማቸውን ተቃውሞ እንመለክት። አብዮት በሚካሄድባቸው ሁሉም አገራት አደናቃፊዎች መኖራቸው አያጠያይቅም ከዚህህ በፊትም ነበሩ ወደፊትም ይኖራሉ። የተሳኩ አብዮቶች የመኖራቸውን ያህል የተቀለበሱ አብዮቶችም አሉ ምክንያቱም አደናቃፊዎች ስላሉ። ለምሳሌ ደርግ ስልጣን ሲይዝ ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው ሀሳብ የሁሉም ሃሳብ ቢሆንም መሬታቸው የተቀማባቸው ሰዎች የአብዮቱ አደናቃፊዎች ነበሩ።

እኩልነት ይስፈን፣ ዶላር በጓሮ በኩል የሚወጣው ይቁም፣ ኮንትሮባንድ ይቅር የሚሉ በዶክተር አብይ የሚነገሩ ነገሮች አሉ። እነዚህ ሃሳቦች ትክክኛ ናቸው። ነገር ግን ኮንትሮባንድ ሲነግዱ የነበሩ የመንግስትን ውሳኔ መቃወማቸው አይቀርም ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ነው። ይህን ጊዜ ነው የመንግስት ብልህነትም የሚያስፈለገው። ቀድሞ ይህኛውን ነገር ማክሸፍ ነው የሚያስፈልገው እንጂ ከአብዮቱ ጋር አደናቃፊ መነሳቱ በኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠረ አድርጎ መውሰድ አይቻልም።

የህዝቡን ስሜት በተመለከተ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ከአሁኑ ስለትልቋ አገር እየተናገሩ አሁንም ከጎጥ አስተሳሰብ ያልወጣ እና የጎሳ አክቲቪስት የሚነዳው ማህበረሰብ አለ። ይህ ነገር ውጤቱ የዶክተር አብይን እቅድ በዜሮ እንዳያባዘው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ዴሞክራሲን ተጠቅመው የራሳቸውን እኩይ አስተሳሰብ ህብረተሰቡ ላይ የሚያሰርጹበት እድል ከተፈጠረ በጣም አደገኛ ነው። ምክያቱም አካሄዳቸው አገር ያፈርሳልና። እኔ በግሌ በፈረሰ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ከሚኖር ባልፈረሰ አገር ውስጥ አምባገነንነት ይሻለኛል። ይህን ማንም እንዲያውቀውና እንዲሰመር እፈልጋለሁ። ዶክተር አብይም እየፈረሰች ባለች አገር ውስጥ ዴሞክራት መሪ ከሚሆኑ ባልፈረሰችና አንድነቷ በተጠበቀች አገር ውስጥ አምባገነን መሪ ቢሆኑ እመርጣለሁ። ከምንም በላይ የአገር አንድነት ይቀድማልና ነው። አስተሳሰባቸውን ይዘው ዴሞክራሲን ተጠቅመው እንደዚህ አይነት አገር አፍራሽና ተገንጣይ የሆኑ አስተሳሰቦች ህዝብ ውስጥ የሚሰረስሩት እና የሚረጩት ነገር አለ።

የመደመር ሃሳብ ሲነሳ ቀመር ውስጥ እንድንገባ ሳይሆን ነገሮችን በቅንነት እንድንረዳ ነው እየተላለፈ ያለው መልእክት። ዞረም መጣም የተለያየ ብሔረሰብ ብንሆንም አንድ ህዝብ ነን የሚባለው ነገር የሚጠቅመን ሃሳብ ነው እንጂ በባንዲራ ነገር መነታረክ፤ ትልቁ የኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ እያለ ስለ ሁለት አርቲስቶች እያነሳን የምንነታረክበት ነገር በጣም አሳዛኝ ነው።

ዘረኝነቱ የትም ቦታ ገብቷል። ስለዚህ ይህን በጥበብ ማለፍ ካልቻልን አንድ ሰው ብቻውን ሊያመጣ የሚችለው ነገር አይኖርም። ለውጡን እንደግፍ ሲባል እኮ ሰልፍ እንውጣ ማለት አይደለም። ሃሳቡን መደገፍ ማለትም ከዘረኝነት እንውጣ ማለት ነው። እንደመር ሲባል እንደስካሁኑ በብሔር ከማሰብ ይልቅ ኢትዮጵያ እንበል ለማለት ነው። አንድ ኢትዮጵያ ሲባል ደግሞ እንደቀድሞው ዘመን አንድ ሀይማኖትና አንድ ቋንቋ ማለት አይደለም። በእርግጥ ይህም በጊዜው ትክክል ነበር። በዚህ ሃሳብ ተመርተው የተገነቡ አገራት አሉ። ለምሳሌ አሜሪካኖች ሬድ ኢንዲያኖችን አጥፍተው ነው የተገነቡት፤ እንግሊዝም አንግሎ ሳክሶችን አጥፍተው ነው አገር የሆኑት። ፈረንሳይ፣ ጃፓን ሌሎችም እንዲሁ። ያ ግን በድሮ ዘመን ይሰራበት የነበረ ነው ትክክል ነው ብሎ ያሰበውን ሰርቶ አልፏል። አሁን ያንን እያነሱ እገሌ ለምን ተነሳ? እገሌ ለምን ተረሳ? እያሉ ማላዘን ቆሞ ቀርነት ነው እንጂ ሌላ ምንም አትለውም። ያለፈን ነገር ብታነሳውም ብትጥለውም ምንም ልታደርገው አትችልም። መፍትሔው በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠርንበት፣ በምንኖርበትና በምንሰራበት አገር እንዴት እንኑርና እንለውጥ ነው።

ከዚህ በኋላም ቋንቋን መሰረት አድርጎ በዘር ምክንያት መድሎ የሚያደርግብንን እና የመሳሰሉትን አሰራሮች ለመሸከም ማንም የሚፈቅድ የለም። ነጻነት ሲመጣ ዴሞክራሲ ሲመጣ እያንዳንዱ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በህገ መንግስቱ መሰረት በምርጫ በኩል የሚፈቱባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው። ለምሳሌ የቋንቋ ጉዳይን እንመልከት። ከዚህ በኋላ ፋብሪካ ማቃጠል፣ መንገድ መዝጋት፣ ሕዝብ ማፈናቀል፣ እከሌ የሚባል ቋንቋ የፌዴራል የስራ ቋንቋ አደርጋለሁ የሚል ተደራጅቶ ይምጣና ተመርጦ ይህን ሃሳቡን ያራምድ። እስካሁን እኮ ዴሞክራሲ ስላልነበረ ነው ነገሮችን በአመጽ መንገድ እንዲፈቱ ይደረግ የነበረው እንጂ አሁን ነጻነት በመጣበት ጊዜ ህዝብን እንዴት ታስፈርድበታለህ? ከዚህ በኋላ መንገድ በመዝጋት፣ ፋብሪካ በማቃጠል በብሔር እየተደራጁ እና ስም እየሰጡ ጥቃት መፈጸም አገር ያፈርሳል እንጂ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።¾

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
317 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 73 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us