ተቋም አልባ ለውጥ እና የአገሪቱ ቀጣይ ፈተናዎች

Wednesday, 25 July 2018 13:21

በይርጋ አበበ


ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያ በሚያስብል መልኩ አብዛኛው አገሪቱ ክፍል ድጋፍ ሰጥቷቸዋል። ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፉን ለመስጠት የቻለበትን ምክንያት ሲናገርም ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን በዋናነት ያስቀምጣል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀርበው የድጋፋቸው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብሔርና ከነገድ የተለየ አመለካከትን ይዘው መቅረባቸው ሲሆን በተከታይነት የሚቀርበው ምክንያት ደግሞ እስረኛን ከማስፈታት ጀምሮ በተለያዩ መስኮች የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋ የሚያስችሉ ተግባራትን መፈጸማቸው ነው ሲሉ ይናገራሉ።


ሆኖም ይህ የዶክተር አብይ አህመድ ከአገር ውስጥ እስከ ጎረቤት አገርና ገልፍ ባህረ ሰላጤ ድረስ የዘለቀው ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችና የአገር ውስጥም የህዝብ ድጋፍ ዘላቂነቱን የሚጠራጠሩ ምሁራንና ፖለቲከኞች አሉ። ለዚህ ስጋታቸው የሚቀርቡት ቀዳሚ ምክንያት ደግሞ የዶክተር አብይ አካድ ተቋማዊ መልክ አልተላበሰም በማለት ነው። ተቋዊ መልክ ያተላበሰ ለውጥ ደግሞ ውጤቱ ዘላቂነት አይኖረውም ሲሉ የሚሰጉ ሲሆን አያይዘውም በከፍተኛ አመራች የተካሄደው የለውጥ ጅማሮ ወደታችኛው የስልጣን ተዋረድ አልዘለቀም ሲሉ ያቀርባሉ። የምሁራኑንና የፖለቲከኞችን ሃሳብ ከዚህ በታች እናቀርበዋለን።

 

የለውጥ ጅማሮውና የህዝብ ጥያቄ

 

ከ1997 ዓ.ም ብሔራዊና አገር አቀፍ ምርጫ ማግስት ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ደም የተቃባበት ዘመን ነው ሲሉ ፖለቲከኞቹ ይናገራሉ። በአንጻሩ ኢህአዴግ በአገሪቱ ላይ ተጨባጭ የኢኮኖሚና ማህራዊ ስኬቶችን አስመዝግቤያለሁ ሲል ይናገራል። ለዚህ ስኬቱ ጠቋሚ ውጤቶች ብሎ የሚቀርባቸው ደግሞ እንደ ህዳሴ ግድብ፣ የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ እና የመሳሰሉትን የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ ውጤቶች ነው።


ይህን የልማት ጅማሮና ውጤቶች መቀበል አይከብደንም የሚሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ደግሞ ኢህአዴግ ከዴሞክራሲ ጋር ዐይን እና ናጫ ሆኗል ሲሉ ይወነጅሉታል። ለዚህ መከራከሪያቸው አስተማማኝ አስረጂ አድርገው የሚቀርቧቸው ምስክሮች ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን፣ የጸረ ሽብርተኝነት እና የበጎ አድራጎት አዋጆችን በማንሳት ነው። እነዚህ አዋጆች ህዝብን ለማፈን ተቃውሞን ደግሞ ለማጥፋት የታቀዱ ስልታዊ ማጥቂያዎች ናቸው ብለው ይናገራሉ።


በተለይ በጸረ ሽብርተኝነትና በጋዜጠኝነት ላይ ወጡ አዋጆች በርካቶችን ለእስርና ለስደት የዳረጉ ሲሆን የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መኖራቸውን ደግ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በዚህ በኩል ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲወጡ የወሰዷቸው እርምጃዎች ሁሉም በሚያስብል መልኩ የህዝብ ጥያቄዎች ነበሩ ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች። ዶክተር ተፈሪ ብዙነህ በዚህ ሃሳብ የሚስማ ምሁር ናቸው። እንደ ምሁሩ አረዳድ ‹‹በርካታ ዜጎች ወላቻቸውና ቤተሰባቸው ለእስር ተዳርጎ በመቆየቱ ህዝብ የታሰሩበት ወገኖቹ እንዲፈታ ሲጠይቅ ቆይቷል›› ሲሉ ንግግራቸውን ይጀምራሉ።


በዚህ የተነሳም ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የአመራር ለውጥ ለህዝብ ይዞ ቀረበው ተስፋም ሆነ ጅማሮ ለህዝብ ጥያቄ መልስ የሰጠ መሆኑን የሚምኑት ምሁሩ፤ ለውጡና የተገኘው ምላሽ ግን ከህዝብ ጥያቄ ጋር ሲነጻጸር ገና መሆኑን ይናገራሉ። በተለይም ለውጡ ወደታችኛውና መካከለኛው የገዥው ፓርቲ አመራር ያልወረደ መሆኑ ህዝብ አሁን በስጋት ውስጥ እደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።


አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ የተባሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲቪክስ መምህር በበኩላቸው የአመራር ለውጡ እና የለውጡ ጅማሮ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ቢጋሩትም ስጋት እንዳሏቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የሚያቀርቡት ምክንያት ህዝቡ ለለውጥ የተዘጋጀ እና ነጻነትን ለመሸከም ዝግጁ ሆኖ እንዳላገኙት ይናገራሉ። አሁን አሁን በህዝቡ ላይ የሚዩት የመለያየት ስሜትና በየአቅጣጫው እየፈነዳ ያለው ግጭት ለውጡን በእንጭጩ ለማስቀረት ይችላል ብለው እንደሚምኑ ገልጸዋል። ነገር ግን ህዝቡ መተባበር ካሳየና አንድ ከሆነ ይመጣል ብለው የሚስቡት ስጋት እንደማይደርስ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ለዚያ ስኬት ደግሞ ዶክተር አብይም ሆኑ ካቢኔያቸው በቅድሚያ ሊያከናውኑት የሚገባቸው የቤት ስራዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለውጡ ሊመራ ይገባ ሲሉ ይናገራሉ።


በአሜሪካን አገር የሚኖሩትን አንጋፋው ምሁርና ፖለቲከኛ ዶክተር አክሎግ ቢራራ “ድርጅታዊ ምርመራ” በሚለው መጽሃፋቸው፤ ኢህአዴግ በብድርና በእርዳታ ሰራኋቸው ከሚላቸው የልማት ስኬቶቹ በተጓዳኝ በአገሪቱ ሙስናን እና የዘር ጥላቻን፣ የአንድ ፓርቲና የአንድ ብሔርን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ያጎናጸፈ ነው›› ሲሉ ይገልጹታል። አያይዘውም አሁን በአገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ በኢህአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው የአመራር ለውጥ ጋር የተገናኘ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚወስዱት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የዴሞክራሲ ለውጥ እና የመንግስት ውሳኔ

 

የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም በምህረት እና በይቅርታ መልክ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ ይታወሳል። ሆኖም እስካሁን የተደረገው እስረኛን የመፍታት ስራ ግን በህግ እና በስርዓት መልክ ሳይሆን በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ሲባል በመንግስት መልካምነት የተደረጉ ነበሩ ማለት ይቻላል። ከትናንት በስቲያ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው።


መንግስት ደግሞ በቀጣይ አገሪቱን ወደዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይመራታል ብሎ ያሰበውን ተቋማዊ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ “የምህረት አዋጅ” ማውጣቱን የገለጹት ጠቅላይ አቃቢ ህጉ፤ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም የተፈጸሙ ጥፋቶችን መንግስት ምህረት እንደሚደርግ ጨምረው ተናግረዋል። ምህረት የተደረገላቸው ግለሰቦችና ህጋዊ ሰዎች (የፖለቲካ ድርጅቶች) በምህረት አዋጁ ተጠቅመው ከእስር ይፈታሉ፣ ክሳቸው ይቋረጣል እንዲሁም በውጭ አገር የሚኖሩም ወደ አገራቸው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።


የተቋማዊ ለውጥ ናፍቆት

 

አቶ ቴዎድሮስ መብራቱም ሆኑ የስነ ትምህርት ምሁሩ ዶክተር ተፈሪ ብዙአየሁ የሚናገሩት በአገሪቱ የተፈጠሩ ለውጦች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም ፈጽሞ እንከን አልባ አይደሉም። ለዚህ ደግሞ የመንግስት ውሳኔ በተቋማዊ አደረጃጀትና መዋቅር ሊታገዝ ይገባዋል።


ኢትዮጵያ ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ዶክተር አብይ ድረስ ስትመራ የመሪ ብቃት ችግር የለባትም›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ችግሩ የተቋማት ግንባታ ላይ ስላልተሰራ ለውጦች ቀጣይነት ሳይኖራቸው ይቀርና በእንጭጩ ይቀጫሉ ብለዋል። አሁንም ዶክተር አብይ በአትዮጵያ መሪነት ታሪካቸው ሲወሳ የሚኖረው በፈጠሩት ለውጥ ሳይሆን በሚፈጥሩት ተቋማት ግንባታ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ። ለዚህ ደግሞ የፍትህ ስርዓቱ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሁሉንም የዴሞክራሲ ተቋማት በተጠና መልኩ ሊዋቅሩ ይገባል ብለዋል።


ዶክተር ተፈሪ ብዙአየሁ ደግሞ በተቋማት ግንባታ ላይ ከአቶ ቴዎድሮስ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ቢኖራውም በዋናነት ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡት ተቋማት ግን የደህንነት፣ የመከላከያ እና የፖሊስ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው ሊዋቀሩ ይገባል ይላሉ። አያይዘውም በአገሪቱ የተፈጠሩ ለውጦች መልካም ቢሆኑም ከእስር የተፈቱ እና ሰዎቹን ወደ እስር ቤት የላኩት ሰዎች አሁን በአንድ ሜዳ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በበቀል መልኩ ችግር ሊፈጠር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ላይ በላይኞቹ እርከን በኩል ለውጥ መፈጠሩን አስታውሰው ሆኖም በታችኛውና በመካከለኛው አመራር በኩል ግን የተፈጠረ ለውጥ አለመኖሩን በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል ይላሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1104 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 935 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us