የቀድሞ የአዳማ ከንቲባን ሥራቸውን ለተመለከተ፤ የወንዜ ልጅ ብቻ ያስተዳድረኝ የሚል ጥያቄ አያነሳም?

Wednesday, 25 July 2018 13:57

ወ/ሮ አዳነች ሀቤቤ፣ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ ወስደዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ይገኛሉ። በአመራርነት በኦሮሚያ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ኃላፊ፤ የኦሮሚያ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ፤ የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፤ የኦሮሚያ ልማት ማሕበር ዋና ሥራአስኪያጅ፤ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአሁን ሰዓት በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የኦሕዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡

 

ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሹመትን በተመለከተ በማሕበራዊ ሚዲያ እና በአንዳንድ የዜና ማሰራጫዎች የተለያዩ የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየቶች ሲደመጡ ነበር። እንደሚታወቀው፤ የተሻሻለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ለማሻሻል በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ በጸደቀው አዋጅ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በምክትል ከንቲባነት ሾሟል።


የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን ለማሻሻል ሰሞኑን በፓርላማ የጸደቀው አዋጅ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ከምክርቤቱ አባላት መካከል እንደሚመረጥ የደነገገ ሲሆን ምክትል ከንቲባው ግን ከምክርቤቱ አባላት ውስጥ ወይንም ከምክርቤቱ አባላት ውጭ ሊሾም እንደሚችል መደንገጉ ይታወሳል። በዚሁ መሠረት በቀጣይ ዓመት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ኢንጂነር ታከለ የአዲስ አበባ ከተማን በምክትል ከንቲባ ይመራሉ።


በከንቲባው ሹመት ሁለት የክርክር ነጥቦች ተነስተዋል። አንደኛው፣ ከአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት መካከል ሰዎች ጠፍተው ነው፣ ሕጉን አሻሽሎ መሾም የተፈለገው። ሆን ተብሎም ከኦሕዴድ ለመሾም ተፈልጎ ነው። አንዳንዶቹ እንደውም፣ የከንቲባው ቦታ ለኦሮሞ ተመራጭ ብቻ ያደረገው ማነው ሲሉም ጠይቀዋል?


በሌሎች ወገን የተንጸባረቀው፣ አዲስ አበባን ማስተዳደር ያለበት የአዲስ አበባ ተወላጅ ነው። የከንቲባውም ሹመት ለአዲስ አበባ ልጅ መሆን አለበት የሚሉ መከራከሪያዎች ናቸው። ለዚህ ምላሽ ለመስጠት የአዳማ ከተማን ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል።


አዳማ ቢያንስ ከ18 ከንቲባዎች በላይ አስተዳድረዋታል። በአዳማ ከተማ ነዋሪ የነበሩ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) የተሾሙ አስተዳድረዋታል። ኢሕአዴግ ሀገሪቷን ከተቆጣጠረ ጀምሮም የገዢው ፓርቲ አባላት አዳማን አስተዳድረዋል። በሁለቱም መንግስታት የተሾሙት ኃላፊዎች የራሳቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች አሏቸው። ባለፈው መንግስት የኢሠፓ አባል በመሆን፤ በኢሕአዴግ የድርጀት አባል በመሆን ሹመቶች ተሰጥተዋል። አዲስ አበባም ከዚህ በተለየ መልኩ ያስተዳደራት የለም። በሁለቱም መንግስታት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መሆን መስፈርት ነው። በወንዜ ልጅ ምርጫ ሀገር ያስተዳደረ የለም። መስፈርቱ ምን መሆን አለበት የሚለውን ለመመለስ ይረዳን ዘንዳ የቀድሞ የአዳማ ከንቲባ የነበሩትን የወ/ሮ አዳነች ሀቤቤን የሥራ ተሞክሮዎች መውሰድ መልካም ነው።


የአዳማ ከተማ ዋና መገለጫዎች ተደርጎ የሚወሰደው ገዢው ፓርቲ እንደሚለው የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ዋነኛው ነው። በተለይ በአዳማ መሬት ከፍተኛ የኪራይ ሰብሳቢዎች ዋሻ መሆኑ አሻሚ አይደለም። በጣት የሚቆጠሩ የከተማው ባለሃብቶች የሚዘውሩት የመሬት አቅርቦት አሰራር የነገሰበት ከተማ ስለመሆኑ ከዚህ ጸሃፊ በላይ ምስክር የለም። በአዳማ መሬት ሽያጭ በአንዴ ወደ ከፍተኛ የሃብት ማማ ላይ የደረሱ፣ የከተማው ባለሃብቶች አሉ።


በተለይ የአዳማ የኪራይ ሰብሳቢ ሰንሰለት ከአስተዳደሩ፣ ከፍርድ ቤቱ፣ ከፖሊስ ተቋማት እና ከቀበሌ ሹመኞች ጋር በእጅጉ ቁርኝት ያለው በመሆኑ፣ አቅሙ በቀላሉ የሚሽመደመድ አይመስልም። በርካታ የከተማው ከንቲባዎች ይህንን ግዙፉ የኪራይ ሰብሳቢ ሰንሰለት ለመበጠስ የሚችሉትን አድርገዋል። አልሰሩም ባይባሉም፤ ትርጉም ያለው ለውጥ አላመጡም።


በአዳማ የተዘረጋውን የኪራይ ሰብሳቢዎችን ሰንሰለትና ዋሻ ትርጉም ባለው መልኩ የተዋጉት፣ ወ/ሮ አዳነች ሀቤቤ ናቸው። ልብ ልንለው የሚገባው አንድ እውነታ፣ ወ/ሮ አዳነች ተወልደው ያደጉት በአርሲ ዞን፣ አሰኮ ወረዳ፣ ጨፌ ቀበሌ ውስጥ ነው። ከአዳማ ከተማ ጋር ግንኙነታቸው እንደአንድ ኢትዮጵያዊ እንጂ የተለየ ቁርኝት የላቸውም።


ማሳያዎችን በማቅረብ ሥራቸውን እንመልከት። በአዳማ ከኪራይ ሰብሳቢ ኃይል መሬት ነጥቆ መውሰድ የማይታሰብ ነበር። ወይም ከተራራ ጋር መጋፋት ተደርጎ በየመሸታው ቤቶች የሚወራ ተረክ ነበር። ከተማው ኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ነው። ሕገወጥ የመሬት ወረራ ዋናው የገቢ ምንጭ ነው። ዝነኞቹ የከተማው ስጋ ቤቶች በከተማው ባለስልጣኖች፣ ዳኞች፣ ትራፊኮች ፖሊሶች፣ የቀበሌ ሹመኞች እና ደላሎች የሚያጨናንቋት ከተማ ናት። ይህንን የኪራይ ሰብሳቢዎች ሰንሰለትና ዋሻ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ግን ሴትየዋ አላመነቱም።


በእነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች በኢንቨስትመንት በሪል እስቴት ስም ተይዘው የነበረውን 250 ሔክታር መሬት ወደ መንግስት ካዝና እንዲገባ ያደረጉት፤ ወ/ሮ አዳነች ናቸው። ወደ መንግስተ ካዝና የተመለሰው መሬት በፍጥነት ወደ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት ነው የዋለው። ከ250 ሔክታር መሬት ውስጥ፤ 47 ሔክታር ለከተማ ሥራአጥ ወጣቶች፤ 100 ሔክታር ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ተገቢውን ካሳ እና ጥቅማጥቅሞች ሳይከበርላቸው በኪራይ ሰብሳቢዎች ሰንሰለት ከመሬታቸው በነፃ በሚባል ደረጃ እንዲለቁ ለተደረጉ በአዳማ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ነው የተሰጠው፤ 35 ሔክታር ከሶማሌ ክልል በግፍ ለተፈናቀሉ አባዎራዎች እና እማወራዎች ለቤት መስሪያ እና ለንግድ አገልግሎት ነው የዋለው፤ ቀሪው ሔክታር መሬት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት ለመምህራን እና ለአስተማሪዎች የቤትመስሪያ እንዲውል ነው፤ ከንቲባዋ ያደረጉት።


በተጨማሪም በከንቲባዋ አመራር ሰጪነትም፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የተያዙ 350 የቀበሌ ቤቶችን በኤችአይቪ ለተጠቁ እና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ለከተማ ነዋሪዎች እንዲተላለፉ አድርገዋል።


እነዚህን ኪራይ ሰብሳቢዎች ለመዋጋት ድፍረት ባለው መልኩ፣ ተራ የከተማ ሴት መስለው መስሪያቤቶችን ፈትሸዋል። አዳማ ውስጥ በሚገኝ በአንድ መስሪያቤት መዝገብ ለመክፈት እስከ 500 ብር ክፍያ እንዲከፍሉ ተጠይቀው፤ ክፍያ ፈጽመዋል። ክፍያ ከተከናወነ በኋላ በመስሪያቤቱ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገዋል። ኪራይ ሰብሳቢውን ተግባር እራሳቸው ኃላፊነት ወስደው አጋልጠዋል።


ከንቲባዋ በከተማ ውስጥ በዘረጉት የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢ ዘመቻ ፍተሻ ባለቤት አልባ የኪራይ ሰብሳቢዎች ፎቆች ተገኝተዋል። ይህም በመሆኑ፣ በመንግስት ንብረትነት እንዲወረሱ አድርገዋል። አሁን ላይ ከተወረሱት ፎቆች መካከል አንዱ የከተማው ኮሙንኬሽን ቢሮ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።


ይህ ብቻ አይደለም። አዳማ ከተማ የኖረ የክረምት ጎርፍ ምን እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። ለዘመናት ሲንከባለል የነበረ ችግር ነው። በክረምት ነዋሪዎች ቤታቸውን እስከመልቀቅ ይደርሳሉ። ይህንን የነዋሪዎች የዘመናት ችግርን ለመቅረፍ የአዳማ ነዋሪ መሆን አላስፈለጋቸውም። የከተማውን ሕብረተሰብ ነጋዴውን በማንቀሳቀስ ፕራይቬት ፕብሊክ ፓርትነርሺፕ በማቋቋም በአንድ ገቢ ማሰባሰቢያ 110 ሚሊዮን ብር እንዲሰበሰብ ከፍተኛውን የአመራር ሚና ተጫውተዋል። የከተማው ጎርፍ ወደአንድ አቅጣጫ እንዲፈስ ተደርጎ ሰው ሰራሽ ሃይቅ እንዲፈጠር እና ችግሩ ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲቀረፍ አስችለዋል።


ከንቲባዋ በዚህም ሳያበቁ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን በመጠየቅ በ500 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ የገንዘብ መጠን በአዳማ አባገዳ ሥር በሚገኘው ተራራ ዙሪያ ሰው ሰራሽ ሃይቁ እንዲያርፍ አድርገዋል። በቀጣይ በሚዘረጉ መሰረተ ልማቶች ከአካባቢው የሚነሳ ጎርፉ ወደዚህ ሰው ሰራሽ ሐይቅ እንዲፈስ በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ችግሩ ይቀረፋል። እንዲሁም ወደሀረር መውጫ አማራጭ መንገድ በአባገዳ ተራራ አቅራቢያ 22 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 50 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ እንዲገነባ አድርገዋል።


በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀስላቸው ሌላው ሥራቸው፤ የአዳማ ከተማ ለአስር ዓመታት የሚሆን መዋቅራዊ የማስተር ፕላን እቅድ በበላይነት አመራር በመስጠት ውጤታማ አድርገው ፈጽመዋል። ማስተር ፕላኑ ለማዘጋጀት 53 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ይህን ገንዘብ ከሕብረተሰቡ፣ ከነጋዴዎች እና ከመንግስት ተቋማት ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ ጥምረት በመፍጠር ተግባራዊ ያደረጉት፤ ከንቲባ አዳነች ሀቤቤ ናቸው።


ከአዳማ ከተማ ከንቲባነት ውጪ ያላቸውን የስራ አፈፃጸምም ከተመለከትን የሹመት መመዘኛው ችሎታ ብቻ መሆኑ ለመስማማት አንቸገርም። ይኸውም፣ የኦሮሚያ ልማት ማሕበር ከተመሰረተ ከሰላሳ ዓመት በላይ እድሜ ቢኖረውም የሕብረተሰቡን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያው ችግሮችን ትርጉም ባለው ሁኔታ መፍታት የጀመረው፣ አለማጋነን በወ/ሮ አዳነች አመራር ሰጪነት ስራ ከጀመረ በኋላ ነው። ቁጥሮችን በማሳያነት ማስቀመጥ እንችላለን፤ በኦሮሚያ ውስጥ በእሳቸው አመራር ሰጪነት ከ500 የማያንሱ አንደኛ ትምህርት ቤቶች፣ 30 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 3 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፤ 103 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ልዩ ትምህርት ቤቶች፤ በኦሮሚያ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ውጤትና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከዘጠነኛ ክፍል በላይ ተማሪዎች የሚማሩበት በአዳማና በሙገር፤ እንዲገነቡና አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋል።


በተለይ ከውጤት አንፃር ጥሩ ማሳያ የሚሆነው፤ በኦሮሚያ ልማት ሥር በሚገኘው በአዳማ ልዩ ትምህርት ቤት ከአሠራ ሁለተኛ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት 314 ተማሪዎች መካከል፤ 310 ተማሪዎች አራት ነጥብ በማምጣት ወደ ከፍተኛ ትምህርት እንዲገቡ እገዛ አድርገዋል። ሌሎቹም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብተዋል።


በተጨማሪም ለልማት ማሕበሩ ገቢ ማስገኛ እንዲሆን፣ በአዲስ አበባ ኦዳ ታዎር፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ፣ እንዲሁም በአዳማ የገበያ ማዕከል ተገንብቶ ወደስራ ገብቷል። 15ሺ ሼዶች ሥራ ጀምረዋል።


በዚህ ጹሁፍ የከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በአዳማ ከንቲባ በነበሩ ጊዜ የሥራ ተሞክሮዎችን ማሳየት የተፈለገው ከአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት ጋር በተያያዘ ለተነሱ ክርክሮች የተወሰነ ምላሽ ይሰጣል በሚል ነው። ይኸውም፣ ከላይ እንደሰፈረው ወ/ሮ አዳነች ተወልደው ያደጉት በአርሲ ዞን፣ አሰኮ ወረዳ፣ ጨፌ ቀበሌ ውስጥ ነው። ከአዳማ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ከአዳማ ውጪ እንዳሉ ዜጎች ነው። አዳማን ግን ለማገልገል የግድ ተወላጅ መሆን አላስፈለጋቸውም።


ሁለተኛ፣ ወ/ሮ አዳነች የኦሕዴድ አባል ናቸው። አዲስ አበባ ከተማን ከወሰድን ከአቶ ተፈራ ዋልዋ ከአቶ አርከበ የዕቁባይ እና ከአቶ ብርሃነ ደሬሳ ውጪ የኦሕዴድ አባሎች ናቸው ያስተዳደሩት። ኦሕዴድ አባሎች አዲስ አበባን ያስተዳድሩት እንጂ የኦሮሞ አርሶ አደር ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከመፈናቀል አላዳኑትም። በሽርፍራፊ ክፍያዎች አርሶ አደሮች ከቀያቸው እንዲነሱ ነው የተደረገው። ይህንን መከላከል ያልቻሉት የፍላጎትና የአቅም ችግር ብቻ ስለነበራቸው ሳይሆን፣ የገዢው ፓርቲ ፖሊሲ በመሆኑም ጭምር ነበር። ስለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የኦሮሞ ልጅ ተመራጭ በመሆኑ የኦሮሚያ አርሶ አደሮች የተለየ ተጠቃሚ አያደርጋቸውም። ተጠቃሚነት ከፖሊሲ የሚመነጭ እንጂ፣ በግለሰብ ችሮታ የሚለገስ አይደለም።


ስለዚህም የአዳማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አዳማን በተገቢው ሁኔታ ያስተዳደሩት፤ የአዳማ ልጅ ስለሆኑ አይደለም። የድርጅት ተሿሚ በመሆናቸው ብቻ የተለየ አገልግሎት ለአዳማ ሕዝብ አላቀረቡም። በዚህ ፀሐፊ እምነት ለሕዝብ መቅረብ ስላለበት አገልግሎት ጠንቅቀው በመረዳታቸውና ለመስጠት የተዘጋጁ በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም፤ በተገቢ ሁኔታ የትምህርት ዝግጅት ቀደም ብለው በማድርጋቸው ነው።


ለማጠቃለል፤ ሕዝብን ለማገልገል ቁርጠኛና አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ ከሆነ እንዲሁም የትምህርት ዝግጅቱ ከፍተኛ የሆነ ማንኛውም ዜጋ የትም ቦታ ቢመደብ ውጤታማ ይሆናል። ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ ከንቲባን ሹመትን መመልከት እንጂ፤ በብሔር፣ በተወላጅነትና በድርጅት አባልነት መዝኖ ትንታኔ ማቅረብ ሁላችንንም አትራፊ አያደርገንም።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
943 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 813 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us