You are here:መነሻ ገፅ»poletica»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

“አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ስትፈትሻቸው ከሰፈር ዕድር 

የተሻለ ጥንካሬ የላቸውም”


ዶ/ር ንጋት አስፋው ፖለቲከኛና ምሁር

በይርጋ አበበ

 

ዶክተር ንጋት አስፋው ትውልድ እና እድገታቸው አዲስ አበባ ሲሆን አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያለውን ትምህርታቸውን የተማሩትም እዚሁ አዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የተከታተሉት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ነው። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በምስራቅ እና ምዕራብ አውሮፓ ተከታትለዋል። በተመረቁበት የማናጅመንት ትምህርትም በአውሮፓ የተለያዩ አገራት በስራ ላይ ከቆዩ በኋላ ከ20 ዓመት በፊት ወደ አገራቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ የግል ዩኒቨርስቲዎች የማስትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማርና በአማካሪነት (Advisor ሆነው) እያገለገሉ ይገኛሉ።


በፖለቲካ ህይወታቸውም ቀደም ሲል አንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል እና አመራር ሆነው ሰርተዋል። በቀደመው ስርዓት ደግሞ የደርግን መንግስት በመቃወማቸው ለእስር እና ለግርፋት ተዳርገው እንደነበር ይናገራሉ። አንጋፋው ምሁር እና ፖለቲከኛ ዶክተር ንጋት አስፋው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ በቅርቡ ስለተከበረው የአድዋ ድል ውጤት እና በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በመኖሪያ ቤታቸው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ሰንደቅ፡- የፖለቲካ ተሳትፎ ያለዎት ምሁር ነዎትና ወደ ዋናው ውይይታችን ከመግባታችን በፊት ፖለቲካን መቼ ነው የጀመሩት?


ዶክተር ንጋት፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ነው መሳተፍ የጀመርኩት። ያደኩበት ነው ማለት እችላለሁ። ብዙ ዘመን ባልታሰርም ደርግ በአሰቃቂ ሁኔታ ገርፎኛል። ያ ያረካሁበት የአገሬ ፖለቲካ ብዙ ነገሮችን አሳልፏል። አሁንም በተቃዋሚ ጎራ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ከመፍረሱ በፊት አመራር ነበርኩ። አንድነት እንደማንኛውም ታዳጊ አገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች እሱም የመፍረስ እጣ ገጥሞት ፈርሷል። በሶስተኛው ዓለም አገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አሳሳቢ ነው። መውደቅ፣ መፍረስ እና መነሳት አለ። አንድነትም በውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ፈርሷል። ለምን ፈረሰ እንዴት ፈረሰ የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም። ስለዚህ አንድነት ስለፈረሰ እኔም መፍረስ የለብኝምና አሁን ሁኔታውን እያጠናሁና የፓርቲዎቹን ፕሮግራም፣ ደንብ እና የአገሬን ሁኔታስ ለመፍታት እንቅስቃው ምን ይመስላል? የሚሉትን መርምሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንዱ የተቃዋሚ ጎራ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል ዝግጅት ላይ ነው ያለሁት። ለረጅም ዓመታት ሳራምደው የነበረው አቋሜ ሰላማዊ እና ሰላማዊ ትግል ብቻ የሚል ሲሆን አባል እሆንበታለሁ ብዬ የማስበው ፓርቲም በፕሮግራሙ ሰላማዊ ትግልን ብቻ የሚያራምድ ሊሆን ይገባዋል። እልህ፣ ቂም በቀል እና ነፍጥ ያነገበን ፖለቲካ እልደግፈውምም በዚህ መንገድ የሚመጡትንም በግሌ እዋጋቸዋለሁ።


ሰንደቅ፡- እርስዎ ፈርሷል የሚሉትን አንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ጨምሮ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመውደቅና በመንገዳገድ ላይ ያሳለፉ ናቸው ይባላል። በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ። የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በቁጥር መብዛት ለአገሪቱ ፖለቲካ አስተዋጽኦው ምንድን ነው?


ዶክተር ንጋት፡- እንግዲህ በአገራችን ውስጥ እንዳልከው ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ምንም በለው ምን ግን በፕሮግራም ደረጃ ደግሞ እጅግ የተቀራረበ ሆኖ ነው የምታገኘው። የአገሪቱ ዋናው ስንቅ እዛ ባለው የእነሱ ፕሮግራም ላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ስንቅ አቀረቡለት? በምን በምን መልኩ ህዝቡን ሊያታግሉ ይችላሉ? የኢኮኖሚ ፕሮግራማቸው ምን ይመስላል? የፖለቲካ ፍልስፍናቸውስ ምን ይመስላል? በሌሎች ማህራዊ መስኮችስ ያላቸው ፕሮግራም ምን ይመስላል? እውን የዚህችን አገር ህዝብ እና ታሪክ እንዲሁም ችግሯን መሰረት ያደረገ ነው ወይስ ከውጭ የተኮረጀ ፕሮግራም ነው የቀረጹት? ሁሉንም ችግሮች ሊፈታ የሚችል የፖለቲካ ፕሮግራም ነው የሚያስፈልገው። ይህን በተመለከተ ነው እኔም ጥናት እያደረኩ ያለሁት። መብዛታቸውን በተመለከተ ከመብት አንጻር ይብዛ እንዲያውም ያንሳል። ነገር ግን ከጥንካሬ አኳያ፣ ስርዓቱን ማለትም ገዥውን መደብ ከማየት አኳያ፣ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄና ፍላጎት ከማየት አኳያ ብዙ ነገር ይቀራል። ስለዚህ ተወደደም ተጠላ እነዚህ በፖሮግራም የሚመሳሰሉ ድርጅቶች ወደ አንድ አካባቢ መምጣት አለባቸው። አሁን እየተደረገ ያለውም ይህንን ለማምጣት ነው። ሁሉም ሊብራል ዴሞክራሲ እንከተላለን ይላል፤ በመካላቸው ልዩነት ሳይኖር ትንንሽ ዘውድን በኪስ ይዞ መዞር ማለት ነው።


በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህን የፖለቲካ ድርጅቶች ስፈተሹ በአብዛኛው እርባና የላቸውም። ድርጅታዊ መዋቅራቸውን ከሴል አንስተህ እስከ ከፍተኛ የፖሊት ቢሯቸው ቢታዩ ከአንድ የሰፈር እድር የተሻለ ጥንካሬ የላቸውም። እኔ በእርግጠኝነት ነው የምናገረው። እኔ በዚያ በኩል ነው የመጣሁት። አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እጅግ ግዙፍ ፓርቲ ነበር። እጅግ ከፍተኛ ምሁራንን ያሰባሰበ እና ከሴል አንስቶ አገር አቀፍ ድርጅታዊ መዋቅር ያቀፈ ፓርቲ ነበር። ይህን ስርዓት ለመጣል በሚገባ የተደራጀ ፓርቲ ነበር። ስለዚህ ስርዓቱ (ኢህአዴግን) ለዴሞክራሲ እና ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት የቆመ ስርዓት ባለመሆኑ እዛ ውስጥ (አንድነት ፓርቲን ለማለት ነው) ቅጥረኞች ገብተው ሊያንኮታኩቱት ቻሉ። ይህ እንዲሆን ያደረጉት ደግሞ እላይ ያሉት ሰዎች ናቸው። በእኔ እይታ አንድነት የፈረሰው በምርጫ ቦርድ ነው የሚለውን አልቀበለውም። ምርጫ ቦርድ ሊያፈርስ አይችልምና። የእሱ ስራ ማንኛውንም ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚተዳደሩበት ህግና ደንብ የሚመራ አካል እንጂ ውስጣዊ ድርጅቱን ሊያፈርስ አይችልም። አንድነትን ምርጫ ቦርድ አፈረሰ የሚሉት ስንኩል አስተሳሰብ ነው። ሃቀኛ የሆነ ቢኖር ኖሮ ድርጅቱን መልሶ ተቀብሎ እንደገና ሊያጠናክር ይችል ነበር።


ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ 60 በለው 80 ወይም መቶ ፖለቲካ ፓርቲ በጎሳ ቅርጫት የታጎሩትን ጨምሮ የትም የሚደርሱ አይደሉም። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ሌላ ነው። ጥያቄው ከፖለቲካ ድርጅቶች በላይ ሄዶ ጥያቄውን እና ትግሉን ህዝቡ በባለቤትነት ይዞታል እንጂ ለህዝቡ አለሁልህ የሚልም ሆነ ህዝቡ የእኔ ነው የሚለው ጠንካራ ፓርቲ የለም። አንዳንዶች አለን ለማለት የሚፍጨረጨሩ ሲኖሩ፤ ብዙዎቹ ደግሞ ሽባ ሆነው ከመሽመድመዳቸው የተነሳ ኢህአዴግ ጉያ ውስጥ ተወሽቀው ለራሳቸው የሆነ ስያሜ ሰጥተው ‹‹አለን›› ሲሉ ይታያሉ። እነሱም ሆነ የሚፍጨረጨሩት ሩጫቸው የትም አያደርሳቸውም። በእኔ እይታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሊያዋጣ የሚችለው እነዚያ የተበጣጠሱ ሀይሎች መበጣጠሳቸውን ወደ ጎን ጥለው ወደ አንድነት መምጣት ሲችሉ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ሊያዋጣ የሚችለው መድብለ ፓርቲ ስርዓት ይህ ብቻ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ሁለት አውራ ብቻ መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ቤታችን ስትሆን ህዝቡ ካለበት ችግር እና ካለው ጥያቄ እፎይ ሊል የሚችለው ሊመሰረቱ ይገባቸዋል ብዬ ከማስባቸው ሁለቱ ጠንካራ ፓርቲዎች ላይ ሲንጠለጠል ብቻ ነው።


ሰንደቅ፡- ከገዥው ፓርቲ ጋር በፖሊሲና በፕሮግራም የሚለያዩ ሁለት ወይም ሶስት ጠንካራ ፓርቲዎች ቢኖሩ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ያድጋል የሚሉ ወገኖች አሉ። በምዕራቡ ዓለም የምናየውም ተመሳሳይ ነው። በጎረቤት ኬንያም የጄሞ ኬኒያታ ቤተሰብና የኦጊንጋ ኦዲንጋ ቤተሰብ የሚመሯቸው ሁለት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው ጠንካራ ፍልሚያ የሚያካሂዱት። ይህ ባህል ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ፍላጎት የለውም ሲሉ ምክንያታቸውን ያቀርባሉ። ለአብነትም ቁጥራቸው በርከት ያሉ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲፈርሱ መደረጉን ይገልጻሉ። በእርሰዎ እይታ እውን ፈረሱ የሚባሉት ጠንካራ ፓርቲዎች በሙሉ ከውድቀታቸው ጀርባ ኢህአዴግ አለበት?


ዶክተር ንጋት፡- አሁን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓቱን ስታየው እጅግ አክራሪ ግራ ዘመም ፖለቲካ ነው። ደርግን ድል አድርጎ የመጣው እኮ ህወሓት ነው። ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እኮ የህወሓት ተጨማሪ ክፍሎች (ዲፓርትመንትስ) ናቸው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው የኢህአዴግ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የተቀዳው እኮ ከዚሁ ግራ ዘመም ባህሪው ነው። ግራ ዘመም ፖለቲካ ደግሞ በምንም መልኩ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲኖር አይፈልግም። ሊያስተናግድም አይችልም። ነገር ግን ምዕራቡን ለመሰልና ግራ ዘመም ላለመባል ‹መድብለ ፓርቲ› የምትለዋ ሃሳብ ህገ መንግስቱ ላይ ሾልካ ገብታለች። ስለዚህ ከገዥው ፓርቲ ባህሪ የተነሳ ሁሉም ፓርቲዎች ሲፈርሱ እናያለን። ለምሳሌ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትና አንጋፋው የፖለቲካ ፓርቲ መኢአድ ሶስት እና አራት ጊዜ ነው የተንኮታኮተው፣ ሰማያዊ አለሁ አለሁ ብሎ ቢታገልም ከሁለት ተከፈለ። አሁን አገሪቱ ላይ ያሉት ሁሉም ህብረ ብሔራዊ ነኝ የሚል ፓርቲ ሁሉ የወጣው ከመኢአድ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ቢባል በፓርቲዎቹ አመራሮች በሚፈጠር ልዩነት አንዱ ተነስቶ የራሱን ድርጅት ይመሰርታል። ከእሱ ጋር የነበረው ደግሞ ነገ ተነስቶ ሌላ ይመሰርታል። በዚህ ሁሉ ውስጥ የስርዓቱ ሚና እንዳለበት ግልጽ ነው። ምክንያቱም ስርዓቱ ለመድብለ ፓርቲ የቆመ ስርዓት አለመሆኑ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩ የጠበበ በመሆኑ ነው።


ፕሮግራምህን ወደ ህዝብ ገብተህ እንድታስተዋውቅ እኮ አይፈቀድልህም። ሁሉንም እንተወው፤ እኔ ባለኝ መረጃ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 117 ቀበሌዎች አሉ። በእነዚህ የቀበሌ አዳራሾች ለተቃዋሚ ድርጅቶች የተሰጠበትን ጊዜ ሰምተህ ታውቃለህ? በእርግጠኝነት ሰምተህ አታውቅም፤ ምክንያቱም ተሰጥቶ አያውቅማ። በራሳችን ገንዘብ የተከራየነውን ቤት እኮ እንዳንሰራበት አከራዮችን አስፈራርተው እንድንወጣ ተደርጓል። ሌላው ደግሞ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የምታደርገው እኮ ህዝብ ወደ ሰልፉ መጥቶ ፕሮግራምህን እንዲያይና እንዲሰማ በሚያመች ቦታ ነው። እኛ እኮ ጃሜዳ ተሰብሰቡ ተብለናል። እግዚአብሔር ያሳይህ ጃንሜዳ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ፣ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ የክብር ዘበኛ ሆስፒታል፣ የጦር አምባ እና ምኒልክ ሆስፒታል ያለበት ነው። እዚያ ሜዳ ውስጥ ማን ሊመለከት ነው ሰላማዊ ሰልፍ የምታደርገው? ስለዚህ ይህ አምባገነን ስርዓት ስለሆነ ለህዝብ የፕሮግራም እና የፖሊሲ አማራጭ የሚያቀርቡ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ሊፈቅድ አይችልም። ምክንያቱም ይህ ሥርዓት መሰረቱ አክራሪ የግራ ዘመም ፖለቲካ ነው።


ቀደም ሲል ያነሳኸው የኬንያ ሁለቱ ፓርቲዎች መሪዎቹ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ እና የፓርቲዎቹን ታሪካዊ እንቅስቃሴ ማንሳቱን ትተን ከምርጫው ማግስት በኋላ በአፍሪካ ታሪክ መጀመሪያ የሆነውን ውሳኔ ፍርድ ቤቱ ከወሰነ በኋላ ምርጫው ተደገመ። ከድጋሚ ምርጫው በኋላ በተፈጠረው ግጭት ብዙ ሰው ቢጎዳም ሁለቱ የፓርቲዎቹ መሪዎች ኡሁሩ ኬኒያታ እና ራኢላ ኦዲንጋ ቆም ብለው አሰቡና የሁለታችን ልዩነትና ውዝግብ ለአገራችንና ለአገራችን ህዝብ አይበጅም፤ ስለዚህ እንወያይ ብለው ተወያዩ። ለአገራቸውም መፍትሔ ለማምጣት ወደ ሰላም መጡ። ይህ የኬንያዎች አካሄድ ትምህርት የሚሆናቸው ከሆነ የእኛ ገዥዎችም ቆም ብለው ለህዝብ አማራጭ ማምጣት የሚችል የፖለቲካ ምህዳር ሊፈጠርለት ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን ደርግ እንዳደረገው ማርክስን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መጫን ውጤት የሌለው ላብራቶሪ ነው የሚሆነው። አንድ እኔን ብቻ እወቅ፣ እኔን ተከተል እና እኔን ስማ የሚል ቆሞ ቀር አስተሳሰብ የተጠናወተው ፖለቲካ በአገራችን ለተፈጠረው ችግርም ምክንያት ሆኗል።


ሰንደቅ፡- ህዝቡ ትግሉን በባለቤትነት ይዞታል ብለዋል። ቀደም ባሉት ቀናትም የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ ‹‹ኢህአዴግ ትግሉን ከፓርቲዎቹ ወደ ህዝቡ አውርዶታል›› ሲሉ ተናግረዋል። ይህን ሃሳብ በተደጋጋሚ ጊዜ ምሁራን ሲናገሩ ይሰማል። ትግሉ ከፓርቲዎቹ ወደ ህዝቡ የወረደው በፓርቲዎች መዳከም ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን?


ዶክተር ንጋት፡- እኔ በመሰረቱ የማምነው ትግሉ ወደ ህዝቡ እንዲወርድ የተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመድከማቸው ሳይሆን ስርዓቱ ፖለቲካ ድርጅቶቹን ስለገደላቸው ነው። ለዚህ ነው ለዚህ ሁሉ ችግር እና ሁከት መነሻው ስርዓቱ ነው የምለው። ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ የፖለቲካ ምህዳሩን ቆልፎ ፓርቲዎቹ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል። በዚህ ምክንያት ፓርቲዎቹ ራሳቸውን አጠናክረው ከህዝብ ጋር በመገናኘት ትግሉን እንዳይመሩ ያደረገው ገዥው ፓርቲ ነው።


ሰንደቅ፡- እርስዎ ከሚሉት በተቃራኒ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን ለማረጋገጥ በአገራችን በተከፈተው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በርካታ ፓርቲዎች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ነው ሲል ኢህአዴግ ይናገራል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ኢህአዴግ ራሱን አውራ ፓርቲ ብሎ ሰይሞ ሌሎች እንዳይንቀሳቀሱ በጥላው ከልሏቸዋል ሲሉ የሚሞግቱ አሉ። በዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ይስጡን እስቲ?


ዶክተር ንጋት፡- በመሰረቱ አውራ ፓርቲ የአንድ የዴሞክራሲ ባህል መገለጫውም አይደለም። አውራ ሆኖ የወጣው ብዙዎቹን ጨፍልቆ ነው። ስርዓቱ እኮ ገዥ መደብ ነው። የአገሪቱን ሀብት በሙሉ የያዘ ፓርቲ ነው። ሚዲያው የእሱ ነው፤ ብሩ የእሱ ነው፤ ንብረቱ በሙሉ የእሱ ነው። ነገርኩህ እኮ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አንድ የቀበሌ አዳራሽ ይጠቀማል እንዴ? የትኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ነው ተሰብስቦ ፕሮግራሙን ለህዝብ እንዲያስተዋውቅ ያደረገው? ይህ ብቻ እኮ አይደለም። የታሰሩት ፖለቲከኞች በዚህ ምክንያት እኮ ነው የታሰሩት። ስርዓቱ ለዚህ የቆመ ስላልሆነ አይፈቅድም። ለዚህ እኮ ነው ችግሮቹ እየተጠራቀሙ ሄደው እዚህ የደረስነውና አገሪቱን መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትወድቅ ያደረጋት።


ስንደቅ፡- በዚህ የተነሳ አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ከሆነችና የችግሩ ስፋትም እየበዛ ነው ካልን መፍትሔው ምንድን ነው?


ዶክተር ንጋት፡- አሁን የተነሳውን ችግርና እየነደደ ያለውን ጥቁር እሳት ሊበርድ የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ሁሉንም የአገሪቱ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የራሳቸው ፕሮግራም ያላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ትልልቅ ምሁራን እና የፖለቲካ ሰዎች ቁጭ ብሎ መወያየትና መፍትሄ ማምጣት ሲችሉ ነው። ኢህአዴግ እኮ ችግር ሲመጣ ችግሩ የእኔ ነው ይልና መፍትሔውም እኔ ነኝ ዝም ብለህ ስማ የሚል ፓርቲ ነው። እኛ ደግሞ ጉዳዩ ስለሚመለከተን ዝም አንልም ነው የምንለው። ትጥቅ ያነሱት የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ ህዝቡ አልፈልጋችሁም ይበላቸው እንጂ በአገራቸው ጉዳይ ስለሚመለከታቸው እነሱንም ያካተተ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ ውይይት ሊከፈት ይገባል ብዬ አምናለሁ።
የህዝብ ሉአላዊነት ሊከበር የሚችለው በወከላቸው ተወካዮቹ አማካኝነት ብቻ ነው። በማንኛውም አገር የህገ መንግሰቱ የበላይ አካል ህዝብ ነው። ስለዚህ በአትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሁለት ጊዜ ነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው። ከዚህ በፊት ‹‹አይደገምም›› የሚል ጽሁፍ በካናቴራ ተጽፎ ልጆቻችን ያንን ለብሰው ከእስር ወጡ። አሁን ያ ድራሹ ጠፍቷል። ከዚያ በኋላም ጥልቅ ተሃድሶ በለው፣ የካቢኔ ለውጥ በለው፣ ለወርና ከዚያ በላይ የፈጀ ግምገማም ተካሄደ ውጤት አልመጣም። ሰሞኑን ደግሞ በሞያሌ ከተማ በተሳሳተ መረጃ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል ተባለ። አንድ ወታደራዊ ኦፕሬሽን በተሳሳተ መረጃ ይህን ያህል ሰው እንዴት ሊገድል ይችላል? አንዱ ራሱ እኮ ያስጠይቃል፤ እንኳን ያን ያህል ህዝብ አልቆ። የወንጀሉ ፈጻሚዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው መባሉ አይደለም ቁም ነገሩ። ትልቁ ቁም ነገር የእኔ መብት እስከምን ድረስ ነው የሚከበርልኝ? የሚለው ነው። ይህን ተከትሎ ወደ ኬንያ ስደት ቀጥሏል። ችግሩ በሌላ አካባቢ ቢፈጠርም ወደ ሌላ አጎራባች አገር ስደት መስፋፋቱ አይቀርም።


ስለዚህ አሁን ያለው ችግር የኢህአዴግ አጀንዳ መሆን የለበትም። አጀንዳው የህዝቡ መሆን አለበት። ምክንያቱም ህዝብ መፍትሔ ይፈልጋል፤ ከበርካታ ምሁራን ጋር ስንገናኝ የምናደርገው ውይይት ይህ ነው። መንግስትም ይህን ተረድቶ ከህዝብ ጋር ይሁን፤ የውይይት መድረክ ይከፈት። በአገራችን እኮ አኩሪ የሽምግልና እና የውይይት ባህል አለን። የአባ ገዳ እና የአገር ሽማግሌዎች የቆየ አኩሪ ባህል ይህን ችግር ሊያቆም ይችላል እንጂ በጠብመንጃ ችግሩን እና ተቃውሞውን ልታቆመው አትችልም። ሰላምን በጥይት አታስከብረውም። ስለዚህ እኔ የምለው ‹ደም ማፍሰስ ደም ያፈላል› እና የአገራችን ጸጥታ ሀይል በማያስፈልግ ተልእኮ ውስጥ አይግባብን። እሱም ቢሆን ሰላም ይፈልጋል።


ሰንደቅ፡- ለችግሩ ብቸኛው መፍትሔ ሁሉን አቀፍ ውይይት ነው ቢሉም፤ በኢህአዴግ በኩል ያለው አቋም ግን ከዚህ የተለየ ነው። ከእስካሁኑ የኢህአዴግ ባህሪ ተነስተን በእርስዎ ሃሳብ ተስማምቶ ኢህአዴግ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ ያደርጋል ብለው ያስባሉ?


ዶክተር ንጋት፡- ላለፉት ረጅም ዓመታት በኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት ላይ ሳይሆን በልዩነት ላይ ሲሰበክ ቆይቷል። ያ ልዩነት ደግሞ እያበጠ ሄዶ ወዳላስፈላጊ ብሔርተኝነት ሄዷል። ይህ ደግሞ ወደማንወጣው መንገድ እየወሰደን ነው፤ ምልክቶችም እየታዩ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት በረጅም ዘመን አኩሪ የውይይት ባህል እና በሰለጠነ የፖለቲካ እይታችን ማርገብ የሚችለው ቀደም ሲል የጠቀስኩልህ ሀይሎች ብቻ ናቸው። ወደ ኢህአዴግ ባህሪ ስንመጣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መፍትሔ እኔ ብቻ ነኝ፤ ችግሮቹ ከአቅሜ በላይ ቢሆኑ ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እመክተዋለሁ፤ የሚል አቋም ነው ያለው። ያ ደግሞ አያስኬድም፤ የመጠፋፋት ነገር ይመጣል። አገራችን ያለችበት ጂኦፖለቲካል አቀማመጣችን እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያው።


በአካባቢያችን በጅቡቲ፣ በኤርትራ፣ በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ሳይቀር የጦር ሰፈር እየተገነባ ነው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪም ቢሆን ይመለከተናል። እስካሁን ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ቱርክ እና ግብጽ ሳይቀሩ በኤርትራ እና በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ የወታደራዊ መንደር ወደ መገንባት ሄደዋል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ በአካባቢያችን አሸባሪ ቡድኖች እንደ አልሻባብ፣ አልቃኢዳ፣ ቦኮሃራም እና አይሲስን የመሳሰሉት እስላማዊ አክራሪ ቡድኖች ለእኛ ስጋቶች ናቸው። የእነዚህን ሁኔታዎች አሳሳቢነት የተረዱት ሩሲያ እና አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከመንግስት ጋር የተነጋገሩትም ለዚህ ነው። አካባቢው አስፈሪና አሳሳቢ በመሆኑ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በሰላም መፈታት እንዳለበት ያምናሉ። ቀደም ባሉት ዘመናት በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ የገለልተኝነት ሚና እንጫወት ነበር። አሁን ግን ወደንም ሆነ ሳንወድ የግድ ከሁሉም እያጣቀስን ነው የምንኖረው። ይህ ማጣቀሱ ደግሞ ይህን ህዝብ ይጎዳል። ስለዚህ ይህ ስርዓት ረጋ ብሎ ማሰብ አለበት።


በሌላ በኩል በአገራችን የአመራሮች አለመስማማት ያለ ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባሩ ሊቀመንበር በመሆናቸው የፖለቲካ መሪ ናቸው። በተመሳሳይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው። እዚህ ላይ ግን ህዝቡ በትክክል በማያውቀው ነገር ‹ለቅቄያለሁ የተሻለ ሰው ይይዝ› ማለታቸው መልካም ነው። ነገር ግን ከመልቀቂያቸው ውሳኔ ጀርባ ያለ አንድ ሀይል እንዳለ ነው የምረዳው። የዚያን ሀይል ማንነት እና ፍላጎት በግምት የምትናገረው ሳይሆን ወደፊት ታሪክ የሚያወጣው ነው የሚሆነው። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እያካሄደ ባለው ስብሰባ የግንባሩን ሊቀመንበር መርጦ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያቀርብና ለፓርላማ አቅርቦ ያስጸድቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርላው ከማጽደቅ የዘለለ ሚና የለውምና። ነገር ግን ፓርላማው ላይ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉንም ከመቀበል ወጣ ያለ አቋም ሲያራምድ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አየን። ይህ ባህል በግራ ዘመም ፖለቲካ ያልተለመደና ሆኖ የማያውቅ ነው። ይህ የሚያሳየው የሆነ ነገር እንዳለ ነው። ይህም አንዳች የአመራር ፍትጊያ እንዳለ እረዳለሁ። ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ውጤታቸው የከፋ ሊሆን ስለሚችል ይህ ስርዓት ለሰላምና ለአገር ሲባል ከኡሁሩ ኬኒያታ መማር አለበት። በደልም ቢኖር ተቻችሎ መኖር እና የህዝቡን ጥያቄ ረጋ ብሎ አዳምጦ መመለስ እንጂ በምንም መልኩ አንድ ጎሳ ነጥሮ እንዲወጣ ሌላው እንዲታፈን የስልጣን ጥያቄ መሆን የለበትም። ስለዚህ ይህ ስርዓት መያዝ ያለበት አጠቃላይ የ27 ዓመቱ ቀውስ እዚህ ደረጃ ደርሷል። ይህንም ገምግሞታል።


ተቃዋሚዎች የሚገባቸውን ቦታ አላገኙም፤ ህዝቡም በአገሩ ጉዳይ በትክክል የሚወያይበት መንገድ አልፈጠርንለትም ሌላው ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ተገልጿል። የመልካም አስተዳደር ችግር ሲባል ደግሞ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እና የሲቪል ሰርቪሱ መዋቅር ማለት ነው። እኔ እንዲያውም የምሰጋው አሁን ያለው ከፍተኛ የሆነ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የሚበላው ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ወረዳ ደረጃ ከወረደ አገር ጠፋ ማለት ነው። አሁን እያየን ያለውም ወደ ወረዳ እየወረደ መምጣቱን አመላካች የሆኑ አስፈሪ አዝማሚያ እያየን ነው። ምክንያቱም ወረዳ ላይ የመሬት ጉዳይ አለ ሌሎች ሰፊ የሀብት ምንጮችም ያሉት ወረዳ ላይ ነው። እዛ ላይ በደንብ አልተሰራም። ስለዚህ አገርን ሊያፈርስ የሚችል ክፉ የሙስና መንገድ ስለሆነ ያንን መዋጋት ያስፈልጋል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ያሉበት መንግስት ሊወስደው የሚገባው እርምጃ በሩን ለውይይት ክፍት ማድረግ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ለራሱም ህልውና ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም።


ሰንደቅ፡- በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝተው ስለ አድዋ ድል ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ነበር። በጥናትዎ ሲገልጹም የአጼ ምኒልክን የክተት አዋጅ ተንተርሰው ሲያቀርቡ የጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ‹‹አገርን የማጥፋት እና ሀይማኖትን የመለወጥ አላማ›› እንዳለው ገልጸዋል። ለዚህ የሚያቀርቡት ማስረጃ ምንድን ነው?


ዶክተር ንጋት፡- በተለያየ ምክንያት ስትበጣጠስ የነበረች አገር እንደገና አንድ የሆነችው በአጼ ምኒልክ ነው። እሳቸው የአገሪቱ ንጉሰ ነገስት መሆናቸውን ካወጁ በኋላ ለሌሎቹ ክፍላተ ሀገራት የአገሬው ተወላጅ እንዲያስተዳድር ሙሉ መብትና ስልጣን ሰጥተዋል። በየግዛቱ ያሉ አስተዳዳሪዎች ግብራቸውን መገበር እንጂ በአስተዳደሩ ውስጥ ንጉሰ ነገስቱ ጣልቃ አይገቡበትም። በዚህ የተነሳም በእሳቸው ዘመን ‹እንዘጭ እምቦጭ› የሚል የግዛት አስተዳዳሪ አልነበረም። ይህ የሆነው በንጉሰ ነገስቱ ብልሃት ሲሆን ለዚህ ደግሞ የእሳቸው አማካሪ የነበሩት የመሳፍንት የዘር ሀረግ ያላቸው ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል አማካኝነት ነው።


ወደ አድዋ ድል ጥያቄህ ስመጣ በበርሊኑ አፍሪካን የመቀራመት ኮንፈረንስ መሰረት አውሮፓዊያን በ1811 በጀመሩት የኢንዱስትሪ አብዮት ለኢኮኖሚያቸው እድገት ጥሬ ሀብት ፍለጋ ላይ ነበሩ። ይህን ደግሞ በአንድ ቀን ተነስተው ያካሄዱት ፕሮጄክት ሳይሆን የ50 እና የመቶ ዓመት እቅድ የተያዘለት ፕሮጄክት ነው። በሀይማኖት፣ በአሳሽነት፣ በፖለቲካ፣ በወታደራዊ ስልጠና፣ በህክምና እና በተለያዩ መንገዶች የአህጉሩን መውጫ መግቢያ አጥንተዋል። ጣሊያንም ኢትዮጵያን ለመያዝ ስትመጣ ከኮንፈረንሱ እንደወጣች ቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ አልመጣችም። ለመቶ ዓመት የአገሪቱን መውጫ መግቢያ ስላጠናች ነበር። የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ለጦርነቱ መነሻ ይሁን እንጂ ውሉ ባይኖርም ጦርነቱ መነሳቱ እንደማይቀር በፖሊሲ ደረጃ የተሰራበት ነበር። አጼ ዮሃንስ ወደ ሱዳን መዝመታቸውን ተከትሎ ምጽዋ የነበረው የጣያን ጦር አስመራን ያዘ። ከዚያ ከ1887 ጀምሮ ከአስመራ ወደ አዲግራት፣ ከዚያም ወደ መቀሌ፣ ከመቀሌ አምባለጌን እየያዘ ግዛቱን አስፋፍቷል። በዚህ ጊዜ አገሪቱ ውስጥ ርሃብ መነሳቱ እና እንስሳቱ ስለተጎዳ ንጉሰ ነገስቱ የወሰዱት እርምጃ አልነበረም። ነገር ግን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስተላለፉት መልዕክት ነበር እሱም የውጫሌን ውል አንቀጽ 17 እንደማይቀበሉትና ጣሊያንም የመስፋፋት ስራውን እንዲያቆም የሚገልጽ ነበር።


የንጉሰ ነገስቱን ጥሪ ስንመለከት ‹‹… በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጥም። አገር የሚያጠፋ፣ ሀይማኖት የሚለውጥ ጠላት መጥቶብሃል፤ ለአገርህ፣ ለሚስትህ እና ለልጅህ ስትል ጉልበት ያለህ በጉልበት ጉልበት የሌለህ በጸሎት እርዳኝ ወስልተህ የቀረህ ግን አልተውህምለዚህ አማላጅ የለኝም ማሪያምን አልምርህም›› ሲሉ የክተት አዋጅ አወጁ። እዚህ ላይ አገር የሚያጠፋ የሚል ሀረግ አለ። ጣሊያን በያዘው የቅኝ ግዛት አስተዳደር በሰራው ካርታ ኤርትራን ከትግራይ ጋር አቀናጅቶ አንድ ግዛት፤ ወሎ፣ ጎንደርና ጎጃምን በአንድ፤ ሸዋን ለብቻ፤ ጅማን ይዘህ ሲዳሞን መላውን እሰከ ወለጋ እና ጉሙዝ በአንድ፤ አርሲ ባሌን ይዘህ እስከ ሀረርጌ ለብቻ፤ የኢትዮጵያን 1/5ኛ የሚሆነውን የኦጋዴንን ግዛት ከሞቃዲሾ ጋር ቀላቅሎ አንድ ግዛት አድርጎ ኢትዮጵያን ከአምስት ከፍሎ ነበር ሊገዛ የነበረው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ እንድትጠፋ አልተደረገም? ዓላማው በትክክል ኢትዮጵያን ለማጥፋት እንደሆነ ግልጽ ነው።


አድዋ ላይ ድል ከሆነ በኋላ በድጋሚ ከ40 ዓመት በኋላ በፋሽሽት አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲጀምር በአንድ ቀን ብቻ ከሶስት ሺህ በላይ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳትን የገደለው ጣሊያን ነው። አቡነ ጴጥሮስን የገደላቸውስ ጣሊያን አይደለም? የኤሊባቡሩን አገረ ስብከት አቡነ ሚካኤልን የገደላቸውም ጣሊያን አይደል እንዴ? ታዲያ እዚህ ላይስ ሀይማኖትን ለማጥፋት አልተነሳም? ለዚህ ነው ንጉሰ ነገስት አጼ ምኒልክ አገር የሚያጠፋ ሀይማኖት የሚለውጥ ጠላት ሲሉ የገለጹት። በአገሩ እና በሀይማኖቱ ድርድር የማያውቀው የአገራችን ህዝብም ለዚህ ነው ከወላይታ አድዋ፣ ከሐረር አድዋ፣ ከሲዳሞ ከከምባታ፣ ከወለጋ፣ ከባሌ ከጎጃም አጠቃላይ ከመላው አገራችን ተነስቶ አድዋ ድረስ በራሱ ስንቅ፣ ትራንስፖርት እና ትጥቅ የዘመተው።


ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት መልኩ እና በቆየ ማንነቷ ተጠብቃ እንድትቆይ የተደረገው በዚያ መልኩ በተካሄደ ትግል በተገኘው የአድዋ ድል ኩራታችን ነው። ይህ ደግሞ የንጉሰ ነገስቱ ጥሪ ትክክለኛ እና የህዝባችን አገር ወዳድነት ያስገኘው ውጤት ነው።

ከመስመር ዝርጋታው በፊት

Wednesday, 14 March 2018 13:21

 

ከተማችን በቅርቡ የፈጣን አውቶቡስ መስመር ባለቤት እንደምትሆን ተገልጿል። የትራንስፖርት ችግሩ የዘወትር ራስ ምታት ለሆነባት ከተማ እንዲህ አይነቱን ዜና መስማት አስደሳችነቱ ምንም ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ስራው በቅርቡ ሊጠናቀቅ እንደሚችልም ተስፋ አለን። እዚህች ላይ ግን ትኩረት ልናደርግበት የሚገባ ነገር አለ። የመጀመሪያ እና ዋናው ከአውቶቡሶቹ ፍጥት ጋር ሊከሰት የሚችለው የትራፊክ አደጋ ጉዳይ ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባዋል። በሀገራችን ፍጥነትን መቆጣጠር አለመቻል ለበርካታ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ዋና ከሚባሉ መንስኤዎች አንዱ ነው። አሁንም ፈጣን አውቶቡሶችን ወደ ስራ ከማሰማራት በፊት ሊከሰት የሚችለውን የትራፊክ አደጋ ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ስራ መስራት ያስፈልጋል።

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ አውቶቡሶቹ ይዘውት የሚመጡት ዘመናዊ አሰራሮች በሃገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥመው እና በታሰበው መንገድ መተግበር ስለመቻሉ ነው። ብዙ ጊዜ ዘመናዊ አሰራሮችን በተግባር ላይ ለማዋል የሚደረጉ ጥረቶች እክል ሲገጥማቸው ይስተዋላል። ስለዚህ አውቶቡሶቹ ይዘዋቸው የሚመጡትን ዘመናዊ አሰራሮች በተፈለገው መጠን ተግባራዊ ለማድረግ አስቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን ይሄን ያህል ወጪ ከወጣባቸው በኋላ በሰበባ ሰበብ ከስራ ውጪ መሆን ሊከሰት ይችላል።

                ስንታየሁ ታደሰ - ከአዲስ አበባ

ቁጥሮች

Wednesday, 14 March 2018 13:18

7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር            ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ለሚገዙ ዕቃዎች የተመደበ ወጪ፤

100 ሚሊዮን ብር                  ባለፉት ስድስት ወራት ከተወገዱ ንብረቶች የተገኘው ገቢ፤

60 ቢሊዮን ብር በላይ            2003 . ጀምሮ ግዢ የተፈፀመበት ወጪ፤

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ          በእነዚህ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከተወገዱ ንብረቶች የተገኘው ገቢ፤

   ምንጭ- የመንግስት ግዢ ንብረት ማስወገድ አገልግሎት

 

በሠላምና በፀጥታ መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ። በፀጥታ ውስጥ ዝምታ አለ። አለመናገር፣ ምንም አለማለት በራሱ ፀጥታ ነው። ፀጥታ በሠላም ውስጥም ሆነ ከሠላም ውጪም ሊፈጠር ይችላል። ግለሰብም ሆነ ህዝብ በፀጥታ ውስጥ ሲገባ ፀጥታው ከሠላም ያልመነጨ፣ ዝምታው ቅሬታን ያዘለ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ህዝብ ሲናገር ደስታውና ቅሬታውን፣ ፍላጎቱንና ስሜቱን ይገልፃል። የህዝብ ድምፅ ለመንግስት የመንገድ መብራት ነው። ዝም ባለ ህዝብ ውስጥ የሚገኝ መንግስት የጊዜ ጉዳይ እንጂ አቅጣጫውን ስቶ ይወድቃል።

 

የመንግስት ጤንነት በየጊዜው እየተለካ የሚስተካከለው ዝምታ በወለደው የህዝብ ፀጥታ ሳይሆን ከሠላም በሚመነጭ ህዝባዊ አስተያየት ነው። በመሆኑም መንግስት መትጋት ያለበት ፀጥታን ለማስከበር ሳይሆን ሠላምን ለማምጣት ነው። በሠላም ውስጥ ያለው ፀጥታ ሠላማዊ ነው። ከሠላም ውጪ የሚኖር ፀጥታ ግን በውስጡ ቅሬታን ያዘለ በመሆኑ ፍተሻ ያስፈልገዋል። ፀጥታ በራሱ በተረበሸ አካባቢ ውስጥ ጊዜያዊ መደማመጥን ለመፍጠር ያገለግል ይሆናል እንጂ ፍፁማዊ ሠላም መሆን አይችልም።

 

የሠላም ግንባታ (Peace Building) በሂደት የሚገነባ፣ የሚሰራ እንጂ እንደ ፀጥታ በአንድ ጀምበር የሚመጣ አይደለም። በሠላም ውስጥ ፍርሃት፣ ሥጋት፣ ቂም፣ ጥላቻ የለም። ከሠላም ባልመነጨ ፀጥታ ውስጥ ግን ውጥረት፣ ፍርሃትና አለመተማመን አለ። ከሠላም ያልመነጨ ፀጥታ የተኩስ አቁም ያህል የሚፈጠር ጊዜያዊ ሠላም ነው። ፈረንጆቹ ‘Negative Peace’ እያሉ ይጠሩታል። በመሆኑም ሠላምን ለማስፈን በሚደረግ ሂደት የሚፈጠርን ፀጥታ እንደ ዘላቂ ሠላም መቁጠር የተሳሳተ ፖለቲካዊ ቀመር በመሆኑ ያለፉት ስህተቶች መልሰው መደገም የለባቸውም። ዘለቄታዊ ሠላምን ለማስፈን በተፈጠረው ጊዜያዊ ፀጥታ ውስጥ ለሠላሙ መደፍረስ የሆኑ ምክንያቶች ተበጥረው እንዲለዩ በማድረግ መፍትሄ ከማፈላለግ ውጪ በፀጥታ ውስጥ ለመደላደል መሞከር አያዋጣም። 

“ኮሚቴው” ትናንት ተመረቀ

Wednesday, 14 March 2018 13:12

በይርጋ አበበ

አርቲስት ፈቃዱ ከበደ ማሞ ከአስር በላይ ገጸ ባህሪያትን ወክሎ የሚጫወትበት ‹‹ኮሚቴው›› ባለ አንድ ገጸ ባህሪ ቴአትር ትናንት በአዶት ሲኒማ ተመረቀ።


በብርሃን ተስፋዬ ተደርሶ በስንታየሁ ታዬ (ስንታየሁ ፋቡላ) የተዘጋጀው ማህበረ ፖለቲካዊ ኮሜዲ ቴአትር በየሳምንቱ ረቡዕ፣ ሀሙስ እና አርብ ለዕይታ የሚበቃ መሆኑን የምረቃ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው የምሳሌ መልቲ ሚዲያ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ የኋላሸት ዘሪሁን ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግሯል።


ቴአትሩን አዘጋጅቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ መፍጀቱን የገለጸው ጋዜጠኛ የኋላሸት፤ ኮሚቴው በየሳምንቱ ረቡዕ በዓለም ሲኒማ ለዕይታ ሲበቃ፣ ሀሙስ በእምቢልታ ሲኒማ ይታይና አርብ ደግሞ በአዶት ሲኒማ የሚታይ መሆኑን ተናግሯል። ቴአትሩን ፕሮዲዩስ ያደረገው ጂአዲ ፕሮሞሽን ነው። 

የሰዓሊ እያዩ ገነት ‹‹ነቁጥ›› የስዕል አውደ ርዕይ ባሳለፍነው ቅዳሜ ተከፍቷል።

 

ሰዓሊ እያዩ አውደ ርዕዩን እና ስራዎቹን በተመለከተ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጸው ‹‹ነቁጥ›› የሚለው ቃል ከመጽሃፍ ቅዱስ የተወሰደ ነው። ትርጓሜው ዥጉርጉር ማለት ሲሆን በአንድ እንስሳ ቆዳ ላይ ያሉ የተለያዩ ነቁጦች መብዛት እንስሳውን አንድ ከመሆን አያግዱትም፤ ነቁጦቹ በመጠን መስፋና ማነሳቸውም የእንስሳውን ማንነት አያጠፋውም ሲል በዝርዝር አስቀምጧል። ይህም ከኢትዮጵያዊነት ብዝሃነትና አንድነት ጋር እንደሚያዝ አስታውቋል።


ሰዓሊው ሃሳቡን ሲያራራም ‹‹በዚህ አውደ ርዕይ የማነሳው ትልቁ ጉዳይ ሀገር በቀል የሆነውን የነገረ-ኪን አረዳዶችን ከምዕራባዊያኑ ነገረ ኪን ምልከታ ጋር በማጋባት ወይም በማጋጨት ሁለቱ ጉዳዮች በሚፈጥሩት አዲስ ኪነ ጥበባዊ ይትባህል አዲስ ዓለም ማመላከት ነው›› ሲል ተናግሯል።


በቆዳ ላይ የተሳሉትን ሃያ ስዕሎች ለዕይታ የሚያቀርበው ሰዓሊ እያዩ፤ ቆዳ እና የሰው ልጅ ዘመናትን የተሻገረ ቁርኝት እንዳላቸው አስታውቋል። ገና ከፍጥረተ ሰው ጀምሮ አዳም ሃጢያት ከሰራ በኋላ ርቃኑን እንዲሸፍን እግዚአብሔር የቆዳ ልብስ እንደሰጠው ገልጾ፤ በኢትዮጵያም የቆዳ ጠቀሜታ ጥንታዊ መሆኑን ተናግሯል። ቆዳ በሀገራችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስነ ልቦናዊ ፋይዳ ያላቸው እቃዎችን መስሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግሯል። የስዕል አውደ ርዕዩ እስከ መጋቢት መጨረሻው ሳምንት ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

 

                                                                                   

በደረጀ ትዕዛዙ

በተለያዩ ሙያ ውስጥ ሆነው አገራቸውንና ወገናቸውን በመደገፍ በግብራቸው ስማቸውን ያገነኑ ሊቃውንቶቻችን ጥቂት ናቸው። እነዚህ ጥቂቶቹም ቀስ በቀስ በማይመክቱት ተፈጥሯዊ ህግ እየተወሰዱ «ነበሩ» እንድንል ተገደናል። ባላቸው ሳይንሳዊ ዕወቀትና ምጥቀት ለአገር፤ ብሎም ለዓለም ባበረከቱት አስተዋጽኦ የሎሬትነት ማዕረግን የተቀዳጁት እንደነ ፀጋዬ ገብረ መድህን እና አፈወርቅ ተክሌን የመሳሰሉት የጥበብ ሰዎች ህልፈታቸው ምን ያህል ልባችንን እንደሰበረው እንረዳለን።

እንዲህ አይነት ሰዎች የማንነታችን ማሳያ፣ የክብራችን መገለጫዎችም ጭምር ናቸው። ነበሩ። ማንነታቸው ሲነገር፣ እንዲኖር የሚያስገድድ ተግባር ፈጽመው አልፈዋልና ተከታታዩ ትውልድ ምንግዜም ሲያስባቸው ይኖራል።

ባለፈው ዓመት ልክ በዛሬው ዕለት በሥጋ ሞት ያጣናቸውን ምሁር (ኤሚሪተስ ፕሮፌሰር) ዮሐንስ ክንፉን ዛሬ በዚህች አጭር ጽሑፍ ልናስባቸው ወደድን። እናም ማንነታቸውን፣ የነበራቸውን ሙያዊ አበርክቶና ስብዕናቸውን እንዲህ ጥቂቱን ጨልፈን እንደሚከተለው አሰፈርነው።

ከአንጥረኛው ባለጸጋ ደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔ እና ከወ/ሮ ዋጋዬ ገ/ሚካኤል ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም ከወደ ትግራይ አክሱም ውስጥ ተወለዱ። ታሪክ አክባሪ፣ ባህል ጠባቂ፣ ወግ አጥባቂ (Conservative) ከሆኑ ቤተሰብ ውስጥ ያለ ችግር ሲያድጉም፤ ከቤተሰቡ ውስጥ በልዩ ትኩረት ትምህርትን አጥብቀው እንዲይዙ በበጎ ተጽዕኖ ውስጥ ሆነው ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ውስጣቸው እየሰረጸ የሄደው ትምህርት ኋላ ላይ ማደጊያቸው፣ መከበሪያቸው፣ አገራቸውንም ማስጠሪያ ጭምር ሆነ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በኤርትራ አስመራ ከተማ ኮምቦኒ ት/ቤት፤ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሱዳን ካርቱም ኮምቦኒ ት/ቤት ሲማሩ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ት/ቤት ነው የተከታተሉት።

እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው ባገኙት ስኮላርሺፕ ዕድል በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1963 በአካውንቲንግ ዘርፍ ከአሜሪካው ኡታህ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለው ወደ አገራቸው ተመለሱ። በመቀጠልም እ.ኤ.አ. በ1970 ዓ.ም. በዚያው በአሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ከሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር ዘርፍ የዶክትሬት (DBA) ዲግሪያቸውን ይዘው ተመለሱ።

ከዚህ በኋላ የበቁ ምሁር ሆነው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኋላም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈረንጆች ብቻ ያስተምሩት የነበረውን የአካውንቲንግና ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶችን ተረክበው በቋሚነት ማስተማር፣ መምራት ቀጠሉ።

ፕሮፌሰር በዩኒቨርሲቲው በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ በማስተማር የሙያ ጉዞአቸውን «ሀ» ብለው የጀመሩት እ.ኤ.አ. በ1963 ዓ.ም። እ.ኤ.አ. በ1970 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ ሲሆን፣ በ1974 የተባባሪ ፕሮፌሰርነት እንዲሁም በ1995 ዓ.ም. በአካውንቲንግ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ተቀብለዋል። በመደበኛ አስተማሪነትና ተመራማሪነት እንዲሁም የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በማማከር በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ከ47 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ኃላፊነትን በትጋት የመወጣት አቅማቸውና ትጋታቸው ስለሚታወቅ በዩኒቨርሲቲው ከማስተማሩ ጎን ለጎን በየዘመናቱ የተጣለባቸውን የአመራር ኃላፊነት ተወጥተውታል። በዚህም መሰረት ከ1963-66 ዓ.ም. የቢዝነስ አስተዳደር ኮሌጅ ዲን፣ ከ1970-74 ዓ.ም ደግሞ የአካውንቲንግ ዲፓርትመንት ሊቀመንበር፣ ከ1970-74 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት በምክትል ፕሬዝዳትነት ባላደራ በመሆን አገልግለዋል።

በሙያቸው ያላቸው ቀና አገልግሎት ቀጥሎም እ.ኤ.አ. ከ1991-1995 ዓ.ም. የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሊቲ ዲን በመቀጠልም ከ1995 እስከ 1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገር የልማት መካነ ጥናት ተቋምን በዳይሬክተርነት መርተዋል።

ፕሮፌሰር ዮሐንስ በሙያቸው ላይ ተጨማሪ ምርምር ለማካሄድ እ.ኤ.አ. ከ1985-86 የዳላስ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ ልማት ማዕከል የፉል ብራይት ስኮላርሽፕ የሰጣቸው ሲሆን፤ በጀርመን ሀገርም ክያል ዩኒቨርሲቲ የፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን የከፍተኛ ደረጃ ተመራማሪ ተሸላሚ (የሲኒየር ሪሰርች ፌሎሽፕም) በመሆን ምርምራቸውን አካሂደዋል።

እኚህ ጎምቱ ምሁር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጡረታ ቢወጡም የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ከማማከር እራሳቸውን አላቀቡም። የአዛውንትነት ዕድሜያቸው ስራን አልገፋም። ከሐምሌ 1988 ዓ.ም ጀምሮ ሚድሮክ ኢትዮጵያን በሰው ኃይል ሥልጠናና ልማት ዳይሬክተርነት እስከ ህልፈተ-ህይወታቸው አገልግለዋል። ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያ ብቻም ሳይሆን የሀገራችን ኢትዮጵያ ብሎም የአህጉራችን የአፍሪካ ባለውለታ ነበሩ።

በተለይም ለሚድሮክ ኢትዮጵያና ለእህት ኩባንያዎቹ አመራርና ሠራተኞችን ለሃያ ዓመታት ሙያዊ ብልፅግና እንዲያድግና እንዲጎለብት ስልጠና በመስጠት እንዲሁም በአማካሪነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ አድናቆት ሲቸራቸው እንደኖረ ይነገርላቸዋል።

ወደ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀለውን የሚድሮክ ኢትጵያን የትምህርትና ሥልጠና ተቋምንም ያቋቋሙት ፕሮፌሰሩ፤ የተለያዩ ካምፓኒያዎችን በማማከር፣ ግዙፍ ለሆኑ የመንግስትና የግል ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ሙያዊ ማህበራትን በመደገፍ እንዲሁም የቦርድ አባልና ሰብሳቢም ጭምር በመሆን አገልግለዋል።

ባካበቱት የዳበረ የሙያ ዕውቀትና ክህሎት መነሻነት፤ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ከአስር የማያንሱ ሀገራዊ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሙያዊ ማኅበራት አባል ነበሩ።

በልዩ ልዩ የምርምር እና በጎ አድራጎት ማኅበራት በመሥራችነትና በአባልነት እንዲሁም አመራር በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ኢትዮጵያውያን ማኅበር ከመሥራቾቹ አንዱ በመሆንና የማህበሩ ፕሬዝዳንትም ሆነው አገልግለዋል። በኢትዮጰያ በትምህርትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሀሳብ አፍላቂ ማህበር (Ethiopian Think Tank on Education and Society) ከመሥራቾች አንዱ ነበሩ፤ የመጀመሪያውም ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ የአካውንቲንግና የኦዲቲንግ ሙያተኞች ማህበር ከመሥራች ኮሚቴ አባላት አንዱ ነበሩ። ይህንን ማህበርም በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። የአንበሳ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበርም በመሆን ዉያዊ አሻራቸውን አኑረዋል።

የአካውንቲንግ መማሪያ መጽሐፍትን እንዲሁም ሙያቸውን የተመለከቱ ከ54 በላይ የምርምር ጽሑፎችን በጆርናሎች ያሳተሙና በኮንፈረንሶች ላይ ያቀረቡም ምሁር ነበሩ‐ ፕሮፌሰር ዮሐንስ።

በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አገራዊና ዓለም-አቀፋዊ ሽልማቶችን ሲቀበሉ ኖረዋል። የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሽልማት፣ የፓን አፍሪካን የኮርፖሬት ገቨርናንስ ሽልማት፣ ከኢትዮጵያ አካውንቲንግ ማህበር ከፍተኛ ደረጃ የክብር ሽልማት አንዱ ነው።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገልግሎት ዘመናቸውን፣ ትጋታቸውን፣ ችሎታቸውን እና ለዚህች አገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ከሽልማት ጋር «የአካውንቲንግ አባት» የሚል የክብር ስያሜ ሰጥቷቸዋል።

በፈረንጆቹ 2013 ሞሪሺየስ ላይ በተካሄደው የአፍሪካና የህንድ ትብብር በስራ አመራር ጉባኤ ላይ የኤሚሪተስ ፕሮፌሰር ማዕረግ (Emeritus professor award) ተሸልመዋል። ይህ ከፍተኛውን የእውቀት ደረጃ ለያዘ የሚሰጠው የእድሜ ልክ መጠሪያ ነው። ከዚያ ሌላ ማዕረግ የለም። በኢትዮጵያም ይህን ማዕረግ የተቀዳጁት እርሳቸው ብቻ ናቸው።

ኤሜሬተስ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ብዙ ናቸው። በኢትዮጵያ የአካውንቲንግ ትምህርት ፈር ቀዳጅ (pioneer) ናቸው። የዚህም ሙያ ጠርዝ የነኩ ብቸኛ ሰው። በሙያቸው ከ47 ዓመታት በላይ ሲያገለግሉ በርካታ ሊቃውንትን አፍርተዋል። ዛሬ በትላልቅ ካምፓኒዎች፣ ኢንሹራንሶች፣ ባንኮች፣ ከፍተኛ የመንግስትና የግል ተቋማት በኃላፊነት ላይ ያሉ ምሁራን አብዛኞቹ የእርሳቸው ተማሪዎች ናቸው።

ስለ ፕሮፌሰር ምስክርነት የሚሰጡ ሁሉ እውቀትን ፈትፍተው ሲያጎርሱ ስስትን አያውቁም። ቀለል ባሉ ምሳሌዎች ትላልቁን የተውሰበሰበ የአካውንቲንግ ትምህርት በተማሪዎቻቸው ውስጥ ያስቀራሉ። በልዩ የማስተማር ጥበባቸው በተማሪዎቻቸው የሚወደዱት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፤ የትምህርት ክፍለ ጊዚያቸው በተማሪዎቻቸው እንደሚናፈቅ ሁሉ፤ እርሳቸውም ለተማሪዎቻቸው ባላቸው አክብሮት ሰዓት አያዛንፉም። አይቀሩም። ሳይዘጋጁ ጠመኔያቸውን ከጥቁር ሰሌዳው አያዋድዱም። ተማሪዎቻቸው ለውጤት ሳይሆን ለእውቀት እንዲተጉ ሲመክሯቸው፤ ከድህነቷና ከጉስቁልናዋ በማገገም ላይ ያለችውን አገር ለማሳደግ ትልቅ ተስፋ እንደሆኑም ጭምር በመንገር ነው።

ዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከፕሮፌሰሩ ጋር ባለው ቅርበት ስለ እርሳቸው ያለው አስተውሎት ከወስጡ የሚጠፋ አልሆነም። ርሁሩህ ናቸው። አልፎ አልፎ ብልጭ የምትል ንዴት ቢጤ አለችባቸው። በአለባበሳቸው ሁሌም ዜንጠኛ ናቸው። ትህትናቸው ይገዛል። መጽሐፍትና የተለያዩ የማስተማሪያ መርጂያዎችን የሚያጭቁበት ትልቅ የእጅ ቦርሳ (ሳምሶናይት) ምንግዜም አይለያቸውም።

መንፈሳዊ ሕይወታቸው የጠነከሩ ናቸው። በውሃ ዋና እና ዮጋ ስፖርት ጤንነታቸውን የሚጠብቁ ሸንቃጣም ነበሩ። በአነጋገር፣ በአረማመድ፣ በአመጋገብና በአቀማመጥ ጭምር ጠንቃቃ መሆናቸው የሚታወቅላቸው ፕሮፌሰር፤ ከስራና ከማህበራዊ ኑሮ ጋር በተያያዘ ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነትም በዚያው መጠን ፍፁም የሆነ ስርአትን የጠበቀ ነው። ለጊዜ የሚሰጡት ዋጋ ከፍተኛ ነው። የቀጠሮን ሰዓት ሰከንድ መታገስ አይችሉም። ስራን አያሳድሩም። ሁሉንም ነገር የሚመሩት ባወጡት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነው። በእንዲህ ሁኔታ በራሳቸው የኑሮ ዘይቤ ሲመሩ፤ ብቸኝነትን በአንድ በኩል፤ ነጻንትን በሌላ በኩል በእኩሌታ ይዘው በመጓዝ ነው።

አገራቸውን ይወዳሉ። ከውጪ ዜጋ ባለቤታቸው የወለዷቸውን ሁለት ልጆች እና ባለቤታቸውን ተለይተው ወደ አገራቸው በመመለስ በሙያዊ አበርክቷቸው የጸኑትም ለዚሁ ነበር።

ከሦስት ዓመት በፊት ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልሰ «አሁን ባለሁበት ዕድሜዬ ላይ እየሰራሁ ገንዘብ ማካበት ቀርቷል፤ አይቻልም። ዋናው ለዚህ ደረጃ መድረሴ ተመስገን ያስብለኛል፤ ከዚህ በኋላ ምን ልሰራ እንደምችል እያሰብኩ፣ በተቻለኝ መጠን ያሰብኩትን እየፈጸምኩ በሠላም መኖር ነው። ዕድሜዬ እስከፈቀደ ልሰራ ያሰብኩትን እሰራለሁ። ጤነኛ ነኝ፤ የነቃ አዕምሮ አለኝ ብዬ አስባለሁ። በኢትዮጵያ ፋይናንስና አካውንቲንግ እንዴት ሊያድግ እንደሚችል የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ …»ብለው ነበር። ይህ ህልማቸውና ምኞታቸውን ብዙም ሳያሳኩ ግን ህልፈታቸው ተሰማ።

አዎ! እኚህን ጎምቱ ምሁር የዛሬ ዓመት ልክ በዛሬው ቀን ነው፣ በድንገተኛ አደጋ በ81 ዓመታቸው ያረፉት። ነፍስ ይማር።

• ገዳሙ እንዲታደስ የእስራኤል መንግሥት ቃል ቢገባም፣ ኮፕቶቹ ዕንቅፋት ኾነዋል
• “ልቀቁና በራሳችን እናድሰው” ያሉትን መንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ተቃውመዋል
• ፖፑ፥ “ጠቅላላ ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” ብለው ለኢትዮጵያ አቻቸው ጻፉ
• “ኢትዮጵያውያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብታችን ነው፤ አያገባችሁም፤” /ፓትርያርኩ/
• በኢትዮጵያ ቅርስነቱ መንግሥት እንዲጠብቀው፣ ፓትርያርኩ ጠየቁ

በክርስትና አስተምህሮና ሥርዐት ባላቸው አንድነት፣ የ“ኦርየንታል ኦርቶዶክስ” ቤተሰብ የሚባሉት የኢትዮጵያ እና የግብጽ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት፣ በጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም ከሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም እድሳት ጋራ በተያያዘ እየተበላሸ መኾኑን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የካቲት 24 ቀን ከተከበረው አምስተኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሢመታቸው ጋራ በተያያዘ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በከፋ እርጅና እየፈራረሰ የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳምና የመነኰሳቱ ማረፊያ ቤት እንዳይታደስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንቅፋት በመፍጠሯና ከዚያም አልፋ ጠቅላላ ይዞታውን ለመንጠቅ እየቃጣች በመኾኑ፣ የሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እየተበላሸ ነው፤ ብለዋል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ገዳሙን ለማደስ ቃል መግባታቸውንና ይህንንም በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የእስራኤል ጉብኝት ወቅት ቢያረጋግጡላቸውም፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን፣ “መንግሥት የሚላችሁን ትታችሁ እኛ እናድስላችሁ፤ በገንዘባችን፣ በመሐንዲሶቻችን በራሳችን እኛ እናድሰው፤” እያለች እንደኾነ ፓትርያርኩ ተናግረዋል፡፡


በጉዳዩ ላይ፣ “ዴር ሡልጣንን ለመጎብኘት ሔደን በኢትዮጵያውን መነኰሳት ተከልክለን ተባረርን፤” ካሉ ሁለት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ መጥተው ስሞታ እንዳቀረቡላቸው የጠቀሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “በእኛ ሥር ኹነው እንዲቀመጡ ንገሩልን፤ ንገሯቸውና መቆያ ቦታም እንሰጣችኋለን፤ ገዳሙን ልቀቁልንና እኛ እናድሰው፤” በማለት እንደጠየቋቸው አመልክተዋል፡፡


በፓትርያርኩ በኩል፣ “ያለፈው ይበቃችኋል” የተባሉት ሁለቱ ግብጻውያን ጳጳሳት፣ “ሳንመካከር፣ ሳንወያይበት እድሳት የሚባል ነገር እንዳይደረግ” በሚል ሊያስጠነቀቁ ቢሞክሩም ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ፖፕ አባ ታዎድሮስ ማሳወቃቸውንና ፖፑም፣ የጳጳሳቱን አቋም በማጠናከር እድሳቱን ከመከልከላቸውም በላይ “ጠቅላላው ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” የሚል ደብዳቤ እንደጻፉ አቡነ ማትያስ በቃለ ምልልሱ አውስተዋል፡፡


ዴር ሡልጣን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብት እንደኾነ በመጥቀስ ለፖፑ ደብዳቤ ምላሽ የሰጠችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እድሳት ከባለቤትነት ጋራ የሚያያዝ እስከኾነ ድረስ በቱሪስትነት እንጅ በባለቤትነት ታሪክ የማያውቃት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በእድሳቱም ጉዳይ የሚያገባት ነገር እንደሌለ መግለጿን አቡነ ማትያስ አስታውቀዋል፤ “ምንም ጸጸትና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፤” በማለት ግብጾቹን ክፉኛ የወቀሱት ፓትርያርኩ፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ቅርስነቱ ጥበቃ እንዲያደርግ በቃለ ምልልሳቸው ጠይቀዋል፡፡


ፓትርያርኩ ከሁለት ዓመት በፊት እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት፣ “ምንም ቢሆን መነጋገር የማይፈታው ነገር የለምና እንነጋገርበታለን፤ ጉዳዩን እንፈታዋለን፤” የሚል ተስፋ ከሀገሪቷ ፕሬዝዳንት የተሰጣቸው ሲሆን፤ አምባሳደሩ አቶ ህላዌ ዮሴፍ ደግሞ፣ በኤምባሲው ዓመታዊ ዕቅድ ውስጥ የዴር ሡልጣን ጉዳይ ከዋነኛ ተግባራት አንዱ ኾኖ ተቀምጦ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱም ክትትል እንደሚያደርግበት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

 

በይርጋ አበበ

ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረው የጉዞ አድዋ ቡድን በዚህ ዓመት አምስተኛ ጉዞውን አድርጓል። ለ45 ቀናት የፈጀውን ጉዞ ያካሄዱት የጉዞ አድዋ ተጓዦች በዚህ ዓመት ካለፉት ጉዞዎች በተለየ መልኩ አንድ የጉዞ አባል ጨምረዋል። የአጼ ምኒልክ የትውልድ ሰፈር አንጎለላ ሲደርሱ የጉዞ አባላቱን በራሷ ፈቃድ የተቀላቀለች አንዲት እንስት ውሻ ከተጓዦቹ ጋር አስቸጋሪውን ውጣ ውረድ የበዛበት ጉዞ አካሂዳ አዲስ አበባ ገብታለች። ተጓዥ ውሻዋን ጨምሮ ሁሉም የጉዞ አባለት ከትናንት በስቲያ በጣይቱ ሆቴል የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ዛሬ በመዝናኛ አምዳችን ላይ የምንመለከተው በጉዞ አድዋ ዙሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ጉዞውንና በጉዞው የነበሩ ክንውኖችን እንዲሁም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ክስተቶችን የዳሰሰ ነው። ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የጉዞ አድዋ አስተባባሪው ያሬድ ሹመቴ በብሎጉ ያሰፈረውን በዋቢነት ተጠቅመናል።

የጉዞ አድዋ ፭ አብይ ክስተቶች በጨረፍታ

ጉዞ አድዋ የተዘጋጀው በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ሲሆን ዓላማውም ኢትዮጵያን ለመውረር ባህር አቋርጦ የመጣውን ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመመከት ወደ ጦር ሜዳው የተጓዙ አባቶችንና እናቶችን ለማሰብ ነው። ጉዞውም ከአዲስ አበባ ተጀምሮ አድዋ ወረዳ በሚገኘው ሶሎዳ ተራራ ድረስ በእግር የሚከናወን ጉዞ ነው።

ጉዞውን የአድዋ ተወላጁ ባለጸጋው አቶ ዳዊት ገብረእግዚአብሔር የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉለት ሲሆን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ደግሞ የጉዞው አካል የሆኑበት ነው። (በጉዞው የመጨረሻ ቀን ላይ ተሳታፊ ነበሩ) አሸኛኘቱ በካሌብ ሆቴል የተከናወነ ሲሆን አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮም) በሽኝቱ ላይ ተገኝቶ ‹‹ሰላም ግቡ›› ብሎ አሸኛኘት አድርጎላቸዋል። በዚህ መልኩ የተጀመረው አምስተኛው ዙር ጉዞ አድዋ ከ45 ቀናት በኋላ ከታሪካዊቷ አድዋ ከተማ ደርሰዋል። በዚህ ጉዞ ውስጥም ከአንጎለላ ጀምሯ የጉዞ አባሉን የተቀላቀለችው ውሻ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ሆና ጉዞውን ጨርሳ ተመልሳለች።

የጉዞ አድዋ ፊታውራሪው የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ የጉዞውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በግል ብሎጉ ሲከትብ እንደተመለከትነውም ደብረ ብርሃን ሲደርሱ የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ማህበረሰብ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ በኋላም በወልድያ ዩኒቨርስቲ የመጽሃፍ ማንበብ እና ስለ አድዋ ድል ትምህርት የሰጡበት እንደሆነም ገልጿል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ ተጓዦቹን በሽለላ እና በፉከራ በደማቅ ስነ ስርዓት የተቀበሏቸው ሲሆን በእግራቸው ሲጓዙ የዋሉትን ተጓዦች እግር አጥበው መስሪያ አቅርበውላዋል። በዚህ የእራት ግብዣ ድግስ ላይ 26ኛዋ ተጓዥ ቡቺ ታዳሚ ነበረች እግሯን አልታጠበችም እንጂ።

ከዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪም ሌሎች አካላት አቀባበል እንዳደረጉላቸው የገለጸው የፊልም ባለሙያው፤ ከእነዚህ መካከል በአላማጣ የኢትዮጵያ ቡና ደጋዎች ያደረጉላቸው አቀባበል አንዱ ነው። ቡናማዎቹ ከሰሜኑ ተወካይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር የነበረባቸውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አካሂደው ሲመለሱ ነበር ለጉዞ አድዋ ፭ አባላት አቀባበል ያደረጉላቸው።

ጉዞው እየተካሄደ ባለበት ወቅትም የካቲት 4 ቀን በመድረሱ ማይጨው ላይ አንድ ትልቅ ተግባር ተከናውኗል። ይህም እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ያረፉበት ዕለት በመሆኑም አራቱ የጉዞው ሴት አባላት ጉዞውን በመሪነት አስጀምረው ያስጨረሱ ሲሆን በማይጨው ከተማም የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት አከናውነዋል። ማይጨው ከመድረሳቸው በፊት ደግሞ ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል በተፈረመበት ይስማ ንጉስ የሚባው ቦታ ላይ አጼ ምኒልክን የሚዘክርና ለክብራቸው የሚመጥን ዜማ አዘጋጅተው ዘምረዋል። ሌላው የዚህ ጉዞ ትልቁ ገጠመኝ ከአዲስ አበባ ከወጡ በኋላ አማላጣ እስከሚደርሱ ድረስ ኢንተርኔት የሌለ መሆኑ ነው።

ተጓዦቹ ግዳጃቸውን ጨርሰው 25 ሆነው ወጥተው 26 ሆነው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ከትናንት በስቲያ ሰኞ አመሻሽ ላይ በጣይቱ ሆቴል የአድዋ ድል በዓል የመዝጊያ ዝግጅት እና ተጓዦቹን የማመስገን ስነ ስርዓት ተከናውኗል። በዕለቱ የተገኙት የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ‹‹ታሪክ ሻንጣ አይደለም የትም ጥለኸው ሄደህ ስትፈልግ የምታነሳው›› ሲሉ ተናግረዋል። ታሪክን ለማስተማር ላደረጉት ጥረትም የጉዞ አድዋ አባላትን አመስግነዋል። ለጎዙ አድዋ አባላትም የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

 

መደምደሚያ

‹‹አርቲስት ወይም የኪነ ጥበብ ሰው ለአገር እና ለትውልድ ረብ ያለው ስራ ሰርቶ ማለፍ ሙያዊ ግዴታው ነው። የጉዞ አድዋ ተጓዦችም ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት በፈለጉ የኪነ ጥበብ ሰዎች አስተባባሪነት የተሰናዳ ፕሮግራም ሲሆን ይህን በማድረጋቸውም ምስጋና ይገባቸዋል›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ የሰጡ ሰዎች ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ቦታው ለአዲስ አበባ ሩቅ ቢሆንምና የመንገዱ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ቡቺን ጨምሮ 26ቱ የጉዞ አድዋ ተጓዦች የማይቻል የሚመስለውን ሰርተው በብቃት ተወጥወተው አሳይተዋልና ክብር ልንሰጣቸው ተገድደናል።

የጉዞው ፊታውራሪ የፊልም ባለሙያ ያሬድ ሹመቴ የጉዟቸውን ማጠቃለያ አስመልክቶ በብሎጉ ‹‹የዳግማዊ ምኒልክን ስም በጉልህ ለማወደስ ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልን በድል ተመልሰናል ደስም ብሎናል›› ሲል ጽፏል። የዛሬ ዓመት በፊት በተከበረው የአድዋ ድል በዓል የጉዞ አድዋ አባላትን ወክሎ በበዓሉ ፕሮግራም ላይ ንግግር እንዲያደርግ ሲጋበዝ ‹‹ለድሉ መገኘት ብስለትና ጥበብ የተሞላበት አመራር የሰጡትን አጼ ምኒልክን ልናመሰግን ይገባል›› ብሎ ንግግር ሲያደርግ ከመድረክ መሪዎቹ ወከባ ደርሶበት ሃሳቡን ሳይቋጭ ከመድረክ እንዲወርድ ተደርጎ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ከዚያ በተሻለ የድሉን መሪ እውቅና እንዲያገኙ ስለተደረገ የሰጠው አስተያየት ነበር።

መጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ.ም፤ ከመካነ ሠላም ተነስቶ ወደ ደሴ ሲጓዝ የነበረ ኮድ 3 አማ 12405 የሆነ አገር አቋራጭ አውቶቡስ በለጋምቦ ወረዳ ከገነቴ ከተማ በቅርብ ርቀት አቧራ ጥግ የሚባለውን ጠመዝማዛ መንገድ እንደጨረሰ መንገዱን ስቶ በመውደቁ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የከፋና አሰቃቂ አደጋ መድረሱ ተሰማ።

 

አውቶቡሱ ከመካነ ሰላም፣ ከወግዲ፣ ከሳይንትና ከለጋምቦ ወረዳዎች ከመጫን አቅሙ በላይ ተሳፋሪዎችን ጭኖ እንደነበርና የመኪናው መገልበጥ መንስኤ ይኽው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።


አብዛኞቹ ተሳፋሪዎችም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ነበሩ ተብሏል። ከተሳፋሪዎች መካከል 28 ወንድና 10 ሴት በድምሩ 38 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ቀሪዎቹ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በአቀስታ ከተማ ህዳር 11 ሆስፒታል እና ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ወዲያውኑ መወሰዳቸው የለጋምቦ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘገባ ያስረዳል።

Page 1 of 205

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us