You are here:መነሻ ገፅ»የኔ ሃሳብ
የኔ ሃሳብ

የኔ ሃሳብ (338)

 

ልጅ ዓምደጽዮን ምኒልክ ኢትዮጽያ

 

አርጀንቲናዊው የማርክሲስት አብዮተኛ፣ የነፃነት ታጋይ፣ ሐኪም፣ ደራሲ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት፣ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያና የጦር መሪ … ኧርኔስቶ “ቼ” ጉቬራ (ቼ ጌቫራ - Spanish) የተገደለው ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት (መስከረም 29 ቀን 1960 ዓ.ም/October 9, 1967 G.C) ነበር።


በወጣትነት እድሜው የደቡብ አሜሪካ አገራትን ተዘዋውሮ የተመለከተው “ቼ” ፣ በየሀገራቱ የነበረው ድህነትና ኢ-ፍትሃዊነት የላቲን አሜሪካ ሕዝብ ከተጫነበት የጭቆና ቀንበር እንዲወጣ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት አስገደደው።
ዝነኛው አብዮተኛ “ቼ” አስቦም አልቀረ፤ በጓቴማላ፣ በኩባ፣ በሜክሲኮ፣ በቦሊቪያ … እየተዘዋወረ ከነፃነት ታጋዮች ጎን ተሰልፎ አምባገነኖችን ተፋልሟል።


ከአሜሪካ ምድርም ወጥቶ ወደ አፍሪካ ተሻገረና ከአልጀሪያና ከኮንጎ የነፃነት ተዋጊዎች ጋር ተገናኝቶ እርዳታ እንዳደረገ ታሪኩ ያስረዳል። ወደ ሶቭየት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያና ሌሎች ሀገራትም በመሄድ የዘመኑን ማኅበረ-ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ተመልክቷል።


አብዮተኛው ቼ በህዳር 1959 ዓ.ም ቦሊቪያ ዋና ከተማ ላ ፓዝ ሲደርስ፣ የአምባገነኑ ሬኔ ባሬንቶስ ሐገር የመጨረሻ መዳረሻዬ ትሆናለች ብሎ አላሰበም ነበር። በማርክሲስታዊ ርዕዮተ ዓለም ተከታይነቱና በአብዮተኛነቱ ምክንያት የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ርዕዮተ-ዓለምን ለማጥፋት ላይ ታች ስትል በነበረችው አሜሪካና፣ በድህነትና በጭቆና ቀንበር የሚማቅቀውን ሕዝብ “እያሳመፀብን ነው” ብለው … እንኳን እርምጃው ስሙ ባስፈራቸው የደቡብ አሜሪካ አምባገነኖች በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው “ቼ”፣ (መስከረም 28 ቀን 1960 ዓ.ም/October 8 1967 G.C) ፌሊክስ ሮድሪጌዝ በተባለ ኩባን ከድቶ ለአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ተቋም (CIA) ሲሰራ በነበረና፣ ክሎስ ባርቢ በተባለ የናዚ የጦር ወንጀለኛ ምክርና ጥቆማ “ቼ” በቦሊቪያ ወታደሮች ቆስሎ ተማረከ።


“…1800 የሬኔ ባሬንቶስ ወታደሮች ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ተዋጊዎች ከበው የተኩስ ናዳ ሲያዘንቡባቸው “ቼ” ቆስሎ ስለነበር፣ ከመማረክ ውጭ አማራጭ አልነበረውም” ሲል የአብዮተኛውን የሕይወት ታሪክ የፃፈው ሊ አንደርሰን ጽፏል።


በተያዘበት እለትም ተዋጊ ጓዶቹ የት እንዳሉ ሲጠየቅ ትንፍሽ ሳይል ቀረ። ቦሊቪያንና ሕዝቧን እንዳሻው ሲያሽከረክራቸው የነበረው ፕሬዝደንቱ ሬኔ ባሬንቶስ፣ ጀግናው አብዮተኛ ከታሰረበት ሊያመልጥ ይችላል ብሎ በመስጋቱ “ተዋጊ ጓዶቹ የት እንዳሉ እንደገና ይጠየቅ” ብላ ስትጮህ የነበረችውን አሜሪካን እንኳ አልማሰማም ብሎ በቶሎ እንዲገደል ትዕዛዝ አስተላለፈ። ቀደም ሲል ጓደኞቹ በ”ቼ” ተዋጊዎች የተገደሉበት ማሪዮ ቴራን የተባለ የ27 ዓመት የመጠጥ ሱሰኛና የአምባገነኑ ሬኔ ባሬንቶስ ወታደር “ቼ”ን ለመግደል ጥያቄ አቅርቦ ስለነበር ተፈቀደለት።


ሱሰኛው ማሪዮ ቴራን “ቼ”ን ሊገድለው ወደእርሱ ሲጠጋ “… ልትገድለኝ እንደመጣህ አውቃለሁ፤ ተኩስ! ፈሪ! አንተ መስራት የምትችለው ሰው መግደል ብቻ ነው …” ብሎ ሲሞት እንኳ እንደማይፈራ ነግሮታል። ገዳዩ ቴራንም ዝነኛው አብዮተኛ ላይ ዘጠኝ ጊዜ አከታትሎ ተኮሰበት! አምስት ጥይቶች እግሮቹ ላይ፣ ቀኝ ትከሻው፣ ክንዱ፣ ደረቱና ጉሮሮው ላይ ደግሞ አንድ አንድ ጥይቶች አርከፈከፈበት። የዝነኛው አብዮተኛ ሕይዎትም አ ለ ፈ!


የአብዮተኛው ኧርኔስቶ “ቼ” ጉቬራ የረጅም ጊዜ ወዳጅና የትግል ጓድ የነበሩት የኩባው መሪ ፊደል አሌሃንድሮ ካስትሮ ሩዝ (ፊደል ካስትሮ)፣ እ.አ.አ በ1997 በሳንታ ክላራ ከተማ ለወዳጃቸው የመታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው አድርገዋል።


እ.አ.አ ከ1957 እስከ 1968 ለአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ተቋም (CIA) ሲሰራ የነበረና በኋላ ደግሞ ከድቶ ኩባ የቀረ አንድ የስለላ ሰው “በወቅቱ ሲ.አይ.ኤን በዓለም ላይ እንደ “ቼ” ጉቬራ የሚያስፈራውና የሚያስጨንቀው ሰው አልነበረም፤ ምክንያቱም ሰውየው ማንኛውንም ዓይነት ትግል ለመምራትና በድል ለማጠናቀቅ ያለው ችሎታ ብቻ ሳይሆን ግርማ ሞገሱም ጭምር ያስፈራ ነበር” በማለት አሜሪካ “ቼ”ን ምን ያህል ትፈራው እንደነበር ምስክርነቱን ሰጥቷል።


የዝነኛው አብዮተኛ ስም በእኛም ሀገር ታዋቂ ነው። “ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፣ እንደ ሆ ቺ ሚንህ እንደ ቼ ጉቬራ” ተብሎ እምቢተኝነት ተሰብኮበታል፤ አብዮት ተቀጣጥሎበታል።

 

በቅዱስ መሀል

 

የካናዳው ፍሬዘር ተቋም እና የዓለም የኢኮኖሚ ነጻነት ኔትወርክ በየአመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት ከሰዓታት በፊት ይፋ አድርጓል።  ሪፖርቱ 159 ሃገራትን ያካተተ ሲሆን ኢትዮጵያ በዘንድሮው ሪፖርት አምና ከነበረችበት የ145ኛ ደረጃ ወደታች አንድ ደረጃ ዝቅ በማለት የ146ኛ ደረጃን አግኝታለች።  ሆንግ ኮንግ እንደ ሁሌውም የአንደኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ሲንጋፖር፣ ኒውዚላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ አየርላንድ፣ እንግሊዝ፣ ሞሪሽየስ፣ ጆርጂያ፣ አውስትራሊያ እና ኢስቶኒያ ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን ተቀዳጅተዋል።  የዚህ ዓመት ሪፖርት ልዩ የሚያደርገው የመረጃው ጥንቅር በአንጻራዊነት ከሌሎቹ ዓመታት የተሟላ ሆኖ መገኘቱ እና የጾታ ዕኩልነትን ሴቶች በየሃገሩ ባላቸው የኢኮኖሚ ነጻነት አንጻር ሚዛን ላይ ተቀምጦ ለመለካት መብቃቱ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ መለኪያ ከ1 ነጥብ 0.78 ማግኘት ችላለች።


የኢኮኖሚ ነጻነት እና ብልጽግና ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን በሪፖርቱ ከተካተቱ 159 ሃገራት ውስጥ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት በጨቋኝ ስርዓት ስር የሚገኙ ሃገራት እና በድህነት የሚታወቁት ናቸው። የሪፖርቱን የመጨረሻውን 10ደረጃዎች የያዙት ኢራን፣ ቻድ፣ በርማ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ አርጀንቲና፣ አልጀሪያ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ እና ቬንዙዌላ ናቸው። ሪፖርቱ ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ዝግ የሆኑትን ሰሜን ኮሪያን እና ኩባን ከሃገራቱ በቂ መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ሊያካትት አልቻለም። የዘንድሮው ሪፖርት አሜሪካ እና ካናዳን እኩል በ11ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጥ ሌሎች ግዙፍ የኢኮኖሚ ሞተር ከሚያንቀሳቅሱ ሃገራት ውስጥ ደግሞ ጀርመንን በ23ኛ ደረጃ፣ ጃፓንን በ39ኛ ደረጃ፣ ሕንድን በ95ኛ ደረጃ፣ ሩሲያን በ100ኛ ደረጃ፣ ቻይናን 112ኛ እንዲሁም ብራዚልን 137ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል።


ከፍተኛ የኢኮኖሚ ነጻነት ባለባቸው ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሃብታም፣ የፖለቲካ እና ሲቪክ መብት ነጻነት ባለቤት እንዲሁም  የመኖር ዕድሜያቸውም ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት አንጻር ሲታይ በ25ዓመታት ያህል ልቆ መገኘቱን በጋራ ጥናት ያደረጉት የፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርስቲው ጀምስ ጉዋርቴይ፣ የሳውዘርን ሜቶዲስት ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ሮበርት ላውሰን እና  የዌስት ቨርጂኒያው የምጣኔ ሃብት ጠበብት ጆሹዋ ሆል ግልጥ አድርገዋል። በሪፖርቱ ከፍተኛውን ደረጃ የተቆጣጠሩት ሃገራት ዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ 42,463 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን በሪፖርቱ ማዕከላዊ ደረጃን የተቆናጠጡት ሃገራት ደግሞ 6,036 ዶላር ያህል አማካይ ገቢ ያገኛሉ። ሪፖርቱ የኢኮኖሚ ነጻነት አለባቸው ብሎ ባስቀመጣቸው ሃገራት ከሚገኙት ድሆች ውስጥ የ10በመቶ ያህሉ አማካይ ገቢ ብቻ (11,998 ዶላር) የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት ዜጎች ጠቅላላ የነፍስ ወከፍ ገቢ አንጻር በአማካይ ሁለት እጥፍ ይበልጣል።


የሪፖርቱ መመዘኛዎች በሆኑት አምስት የኢኮኖሚ ነጻነት አውታሮች ውስጥ ኢትዮጵያ በሶስቱ መመዘኛዎች ያሻሻለች ሲሆን በሁለቱ ደግሞ ደረጃዋ አሽቆልቁሏል።  ሪፖርቱ ሚዛን ከ1 እስከ 10 በሚሰጥ በየተለያዩ መመዘኛዎች ነጥብ አማካይ ድምር ውጤት መሰረት የሃገራትን የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ ይዳስሳል። በሪፖርቱ የመጀመሪያ የኢኮኖሚ ነጻነት መመዘኛ መነጽር ሆኖ በቀረበው የቢዝነስ ሕግጋት እና ደምቦችን እንመልከት። ይህ መመዘኛ ለንግድ የሚውል የብድር አገልግሎት እና የወለድ ተመን ቁጥጥር፣ የስራ ቅጥር ውል እና የቅጥር ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ወለል ነጻነት መኖር አለመኖር፣ የቢዝነስ ድርጅት እና ነጋዴዎችን ገዳቢ ሕግ መኖር አለመኖር፣ ለንግድ ምዝገባ የሚወስደው ቀናት እና የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ስፋት፣ የንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ሂደት እና በዚያ ዙሪያ ያሉ ቢሮክራሲዎችን ለማለፍ የሚደረጉ ሕገወጥ የገንዘብ ክፍያዎችን ሁሉ ይዳስሳል። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ አምና ከነበራት የ6.23 ነጥብ ዘንድሮ ወደ 6.05 ዝቅ ብላለች።


ሁለተኛው መለኪያ ሚዛን ኢትዮጵያ ከውጩ ዓለም ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር የሚመለከት ሲሆን ሪፖርቱ ሃገሪቱ አምና ከነበራት የ5.22 ውጤት ወደ 5.23 ከፍ ማለቷን ያሳያል። በዚህኛው የኢኮኖሚ ነጻነት መለኪያ ሚዛን ኢትዮጵያ ወደ ሃገርቤት በሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ የምትጥለው ታሪፍ፣ የንግድ ማነቆ የሆኑ መመሪያዎች እና ደምቦች፣ በጥቁር ገበያ ላይ የሚደረግ የውጭ ገንዘቦች ግብይት ነጻነት እንዲሁም በሃገሪቱ ያለውን የገንዘብ ፍሰት ነጻነት እና የውጭ ኢንቨስትመንት ገደቦች ጥልቀት ይዳስሳል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ  የገበያ ተዋናዮች እና ውድድር ደካማ ከሆኑት የሃገሪቱ ተቋማት በተጨማሪ ግልጽነት እና ነጻነት የሌለበት መሆኑ ሃገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ያላትን ሕልም እስከዛሬ እውን እንዳይሆን ካደረጉት እንቅፋቶች መሃል አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ውጭ በምትልከው ቡና፣ ወርቅ፣ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የቅባት እህሎች እና ሌሎች የግብርና ምርቶች አማካይነት ከዓለም ገበያ ጋር  የተቆራኘ ቢሆንም መንግስት በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት በሃገሪቱ የባንክ ሲስተም፣ የካፒታል ገበያ እና የቢዝነስ ስራዎች ላይ የማያሰራ ከፍተኛ ቁጥጥር መኖር ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ተጠቅማ ወደተሻለ የኢኮኖሚ እና የማህበረስብ ዕድገት ምዕራፍ እንዳትደርስ እንቅፋት ሆኗታል።


የሪፖርቱ ሶስተኛው ሚዛን የገንዘብ ፍሰት መጨመር እና ግሽበትን የሚመለከት ሲሆን በዚህ ዘርፍ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ አምና ከነበረችበት የ 5.47 ነጥብ ወደ 5.42 ነጥብ ዝቅ ማለቷን ያሳያል። አራተኛው የኢኮኖሚ ነጻነት መመዘና መህልቁን የሚጥለው በሕግ ስርዓት እና በንብረት ባለቤትነት መብት ላይ ሲሆን በዚህኛውም ሃገሪቱ አምና ካስመዘገበችው የ4.47 ውጤት ወደ 4.61 ከፍ ብላለች። ይህኛው መመዘኛው የፍትሕ ስርዓቱ እና የዳኞች ገለልተኛነት፣ የሕግ ስርዓቱ ተዓማኒነት፣ የፖሊስ ታማኝነት፣ የወታደራዊ ተቋሙ በሕግ የበላይነት እና በፖለቲካው ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፣ የሕጋዊ ውል ጥንካሬ እና ተፈጻሚነት እንዲሁም ወንጀል በቢዝነስ ላይ ያለውን ተጽእኖ ስፋት እና ልክ በመዳሰስ በተጠቀሱት ዘርፎች ኢትዮጵያ ጥቂት ማሻሻያ እንዳረገች ይጠቁማል።


የኢኮኖሚ ነጻነቱ አምስተኛ መመዘኛ የመንግስት መጠንና ልክን ይዳስሳል። ይሄውም መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ እና የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፣ የመንግስት ገንዘብ አጠቃቀም እና ወጭ እንዲሁም የኩባንያ ግብር ተመንን በመቃኘት ኢትዮጵያ አምና ከነበራት የ6.11 ውጤት ዛሬ በወጣው ሪፖርት ወደ 6.62  መጠነኛ ጭማሪ አሳይታለች። በአጠቃላይ የሪፖርቱ ጥቅል መግለጫ ከአምናው አንድ ደረጃ ዝቅ ያላቸውን ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት ጎራ መድቧታል። ጎረቤት ኬንያ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ነጻነት ያለባት ሃገር ተብላ ስትመደብ በአጠቃላይ ጥቅል መግለጫም ኬንያ ማዕከላዊ የኢኮኖሚ ነጻነት ካለባቸው ሃገራት ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ተመድባለች።


በአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ በሆነችው ሃገር ኢትዮጵያዊያን የሚያገኙት ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከምስራቅ አፍሪካ ዝቅተኛው ነው። በዓለም የመጨረሻ ድሃ በሆነችው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ማሽቆልቆሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘላቂ ምሰሶ ላይ አለመቆሙን ይመሰክራል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የስትራክቸራል ችግር እንዳለበት ዓይኑን የገለጠ ሁሉ ሊያየው በሚችል ደረጃ መግዘፉም አሌ አይባልም። ይሄ የኢኮኖሚ መዛነፍም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የሃገሪቱን የፖለቲካ አምድ ሲነቀንቀው ዓለም እየታዘበ ያለበት ሰውት ነው። የኢኮኖሚ ነጻነት ቁልቁል መውረድ የሕግ የበላይነት እና የፍትህ ተቋማት ነጻነት፣ የሃይማኖት ነጻነት፣ የሰው ሃይል ዕድገት ነጻነት፣ የሞላዊነት እና የማህበረሰብ ብልጽግና ውድቀት አመላካችም ነው።


የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ነጻነት አይኖርም። ነጻነት የሌላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ደግሞ ደካማ ናቸው። በምስራቅ አፍሪካ ደካማ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት የሚገኙትም በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ባሉበት ሃገር ጠንካራ የመንግስት ተቋማት እና የፍትህ አካላት እንደሚኖሩ ከጎረቤት ኬንያ ማየት እንችላለን። በቅርቡ የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓለም ‘ትክክለኛ’ ሲል  የመሰከረለትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ‘ሕገመንግስቱን የተከተለ አይደለም!’ በማለት የምርጫ ውጤቱን ሰርዞ ሌላ ምርጫ እንዲደረግ ማዘዙ ኬንያ ያለችበትን የፍትህ እና የዳኝነት ነጻነት ከማሳየቱም በላይ ለአፍሪካ ተስፋ ፈንጥቆላት አልፏል።

 

በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

(http://www.danielkibret.com)

በእምነት ታሪክ ውስጥ የታሪክ፣ የአርኬዎሎጂ እና የቅርስ ጥናት ሰዎችን ያስጨነቁ ሁለት ጥያቄዎች አሉ። ታቦተ ጽዮን እና ጌታ የተሰቀለበት መስቀል የት ነው ያሉት? የሚሉት ጥያቄዎች። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ አሰሳዎች፣ ቁፋሮዎች፣ መዛግብትን የማመሳከር ሥራዎች፣ አሉ የተባሉ የይዞታ ጥያቄዎችን የመመርመር ፍተሻዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። በጣም የሚገርመው ነገር ግን የዓለም ቅርሶች መናኸርያ የሆነችው ኢትዮጵያ ሁለቱንም በተመለከተ ለዓለም የምትገልጣቸው ነገሮች አሏት።

ሰሞኑን በሀገራችን ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል በመከበር ላይ በመሆኑ «ለመሆኑ ጌታ የተሰቀለበት መስቀል የት ነው ያለው?» የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ያሉ መረጃዎችን እንቃኝ።

የመስቀሉ መጥፋት

በአብያተ ክርስቲያናት ከሚነገረው ትውፊት በስተቀር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎት የነበረው መስቀል እንዴት ሊጠፋ እንደቻለ የተመዘገበ ታሪክ እኔ አላገኘሁም። አብዛኞቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ግን አይሁድ በመስቀሉ ላይ ይደረግ የነበረውን ተአምራት በመቃወም ከክርስቲያኖች ነጥቀው እንደ ቀበሩት ይተርካሉ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ የቆስጠንጢኖስ የሕይወት ታሪክ /Life of Constantine/ በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በክርስቲያኖች ዘንድ ታላቅ ሥፍራ የነበረው የጌታ መቃብር ተደፍኖ በላዩ ላይ የቬነስ ቤተ ጣዖት ተሠርቶ እንደ ነበር ይናገራል። አውሳብዮስ በዝርዝር አይግለጠው እንጂ ይህ የቬነስን ቤተ መቅደስ በጎልጎታ ላይ የመሥራቱ ጉዳይ የሮሙ ንጉሥ ሐድርያን በ135 ዓ.ም ኢየሩሳሌምን Aelia Capitolina አድርጎ እንደ ገና ለመገንባት የነበረው ዕቅድ አካል ነው።

አይሁድ በሮማውያን ላይ እስከ ዐመጹበት እና ኢየሩሳሌም ከክርስትና በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እስከ ጠፋችበት እስከ 70 ዓም ድረስ መስቀሉ በክርስቲያኖች እጅ እንደ ነበር ይታመናል። በኋላ ግን ክርስቲያኖቹ የሮማውያንን እና የአይሁድን ጦርነት በመሸሽ ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ሌሎች ሀገሮች ሲሰደዱ፤ በኋላም በባር ኮባ ዐመፅ ጊዜ /132-135 ዓም/ ኢየሩሳሌም ፈጽማ በሮማውያን ስትደመሰስ የመስቀሉ እና የሌሎችም ክርስቲያናዊ ንዋያት እና ቅርሶች ነገር በዚያው ተረስቶ ቀረ። ንጉሥ ሐድርያንም የኢየሩሳሌም ከተማን ነባር መልክ በሚለውጥ ሁኔታ እንደ ገና ሠራት። ያን ጊዜ ነው እንግዲህ የቬነስ ቤተ መቅደስ በጌታችን መቃብር ላይ የተገነባው። ቆስጠንጢኖስ ለኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ ለአቡነ መቃርዮስ በጻፈው እና ሶቅራጥስ እና አውሳብዮስ መዘግበው ባቆዩን ደብዳቤ ላይ ይህ ታሪክ ተገልጧል።

ቀጣዮቹ 300 ዓመታት ለክርስቲያኖች የመከራ ጊዜያት ነበሩ። የሮም ቄሳሮች ክርስትናን እና ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱባቸው ዓመታት በመሆናቸው መስቀሉን የመፈለግ ጉዳይ በልቡና እንጂ በተግባር ሊታሰብ አይችልም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱም ኢየሩሳሌም እየተዘበራረቀች እና የጥንት መልኳ እየተቀየረ በመሄዱ በጌታ መቃብር ላይም የሮማ አማልክትን ለማክበር ቤተ መቅደስ በመሠራቱ ነገሩ ሁሉ አስቸጋሪ እየሆነ ሄደ።

የመስቀሉ እንደገና መገኘት

ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች መስቀሉን እንደገና ያገኘችው ንግሥት ዕሌኒ መሆንዋን ይናገራሉ። በ380 ዓም አካባቢ የተወለደው ታሪክ ጸሐፊው ሶቅራጥስ Ecclesiastical History በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በምእራፍ 17 መስቀሉ እንዴት እንደ ተገኘ ዝርዝር መረጃ ይሰጠናል። ንግሥት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ በጎልጎታ የጌታ መቃብር ላይ የተሠራውን የቬነስ ቤተ መቅደስ አፈረሰችው፤ ቦታውንም በሚገባ አስጠረገችው። በዚያን ጊዜም የጌታችን እና የሁለቱ ሽፍቶች መስቀሎች ተገኙ። ከመስቀ ሎቹም ጋር ጲላጦስ የጻፈው የራስጌው መግለጫ አብሮ ተገኘ።

ሶቅራጥስ ከሦስቱ መስቀሎች አንዱ የክርስቶስ መሆኑን እንዴት ሊታወቅ እንደቻለ ሲገልጥ እንዲህ ይላል «አቡነ መቃርዮስ በማይድን በሽታ ተይዛ ልትሞት የደረሰችን አንዲት የተከበረች ሴት አመጡ። ሁለቱን መስቀሎችንም አስነኳት፤ ነገር ግን ልትድን አልቻለችም፤ በመጨረሻ ሦስተኛውን መስቀል ስትነካ ድና እና በርትታ ተነሣች። በዚህም የጌታ መስቀል የትኛው እንደሆነ ታወቀ» ይላል። ከዚያም ንግሥት ዕሌኒ በጌታ መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን አሠራች። ከመስቀሉ የተወሰነውን ክፍል ከፍላ ከችንካሮቹ ጋር ወደ ቁስጥንጥንያ ስትወስደው ዋናውን ክፍል በጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን ተወችው።

ይህንን ታሪክ ሄርምያስ ሶዞሜን የተባለው እና በ450 ዓም አካባቢ ያረፈው ታሪክ ጸሐፊም Ecclesiastical History, በተሰኘው ጥንታዊ መጽሐፉ በክፍል ሁለት ምእራፍ አንድ ላይ ይተርከዋል። ዞሲማን እንደሚለው በ325 ዓም የተደረገው ጉባኤ ኒቂያ ሲጠናቀቅ የቆስጠንጢኖስ ትኩረት ወደ ኢየሩሳሌም ዞረ።

ምንም እንኳን ሶዞሜን ባይቀበለውም መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ያመለከተው ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ ይኖር የነበረ አንድ አይሁዳዊ መሆኑን እና እርሱም ይህንን መረጃ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ከነበረ መዝገብ ማግኘቱን እንደ ሰማ ጽፏል። ንግሥት ዕሌኒ ባደረገችው አስቸጋሪ ቁፋሮ መጀመርያ ጌታ የተቀበረበት ዋሻ፤ ቀጥሎም ከእርሱ እልፍ ብሎ ሦስቱ መስቀሎች መገኘታቸውን ሶዞሜን ይተርካል። ከመስቀሎቹም ጋር የጲላጦስ ጽሑፍ አብሮ መገኘቱን እና የጌታ መስቀል ከሌሎች የተለየበትን ሁኔታ ከሶቅራጥስ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ይተርከዋል።

ንግሥት ዕሌኒ በጎልጎታ፣ በቤተልሔም፣ በደብረ ዘይት፣ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርታ እንዳረፈች ሶዞሜን ይተርካል። ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ዕረፍቷን በ328 ዓም አካባቢ መስቀሉ የተገኘ በትንም በ326 ዓም ያደርጉታል። በ457 ዓም አካባቢ ያረፈው ቴዎዶሮት የተባለው ታሪክ ጸሐፊም የመስቀሉን የመገኘት ታሪክ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ያቀርበዋል።

መስቀሉ በኢየሩሳሌም

ንግሥት ዕሌኒ ለበረከት ያህል የተወሰነ ክፍል ወደ ቁስጥንጥንያ ከመውሰዷ በቀር አብዛኛውን የመስቀሉን ክፍል በብር በተሠራ መሸፈኛ አድርጋ በጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀመጥ ለአቡነ መቃርዮስ ሰጥታቸዋለች። ይህ መስቀል በየተወሰነ ጊዜ እየወጣ ለምእመናኑ ይታይ እንደ ነበር አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ። በ380 ዓም ኤገርያ የተባለች ተሳላሚ መነኩሲት ቅዱስ መስቀሉ ወጥቶ በተከበረበት በዓል ላይ ተገኝታ ያየችውን ለመጣችበት ገዳም ጽፋ ነበር። /M.L. McClure and C. L. Feltoe, ed. and trans. The Pilgrimage of Etheria, Society for Promoting Christian Knowledge, London, (1919)/

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመስቀሉ ክፍልፋዮች ወደ ተለያዩ ሀገሮች መወሰድ የጀመሩት በዚህ ጊዜ ነው። በሞሪታንያ ቲክስተር በተባለ ቦታ የተገኘውና በ359 ዓም አካባቢ የተጻፈው መረጃ የመስቀሉ ክፍልፋዮች ቀደም ብለው ወደ ሌሎች ሀገሮች መግባት እንደ ጀመሩ ያሳያል። ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም መስቀሉ ከተገኘ ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ በ348 ዓም በጻፈው አንድ ጽሑፍ ላይ «ዓለሙ በሙሉ በጌታችን መስቀል ክፍልፋዮች ተሞልቷል» በማለት ገልጦ ነበር። ከዚህም ጋር «ዕጸ መስቀሉ እየመሰከረ ነው። እስከ ዘመናችንም ድረስ ይኼው እየታየ ነው። ከዚህ ተነሥቶም በመላው ዓለም እየተሠራጨ ነው። በእምነት ክፍልፋዮቹን እየያዙ በሚሄዱ ሰዎች አማካኝነት» ብሏል።/On the Ten Points of Doctrine, Colossians II. 8./

ዮሐንስ አፈ ወርቅም የመስቀሉን ቅንጣቶች ሰዎች በወርቅ በተሠራ መስቀል ውስጥ በማድረግ ምእመናን በአንገታቸው ላይ ያሥሩት እንደ ነበር ጽፏል። በዛሬዋ አልጄርያ በቁፋሮ የተገኙ ሁለት ጽሑፎች የመስቀሉ ክፍልፋዮች በ4ኛው መክዘ የነበራቸውን ክብር ይናገራሉ። /Duval, Yvette, Loca sanctorum Africae, Rome 1982, p.331-337 and 351-353/። በ455 ዓም በኢየሩሳሌም የነበረው ፓትርያርክ ለሮሙ ፖፕ ለልዮን የመስቀሉን ቁራጭ እንደ ላከለት ተመዝግቧል።

በአውሮፓ ምድር የተዳረሰው አብዛኛው የመስቀሉ ክፍልፋይ የተገኘው ከባዛንታይን ነው። በ1204 ዓም በአራተኛው የመስቀል ጦርነት ጊዜ የዘመቻው ተካፋዮች በዓረቦች ጦር ድል ሲመቱ ፊታቸውን ወደ ቁስጥንጥንያ አዙረው ከተማዋን፣ አድባራቱን እና ገዳማቱን ዘረፏቸው። በዚያ ጊዜ ተዘርፈው ከሄዱት ሀብቶች አንዱ ዕሌኒ ከኢየሩሳሌም ያመጣችው የመስቀሉ ግማድ ነበር። ይህንን ግማድ እንደ ገና በመከፋፈል አብዛኞቹ የአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ሊዳረሱት ችለዋል። የወቅቱን ታሪክ ከመዘገቡት አንዱ ሮበርት ዲ ክላሪ «በቤተ መቅደሱ ውስጥ አያሌ ውድ ንዋያት ይገኙ ነበር። ከእነዚህም መካከል ከጌታ መስቀል የተቆረጡ ሁለት ግማዶች ነበሩ። ውፍረታቸው የሰው እግር ያህላል፤ ቁመታቸውም ስድስት ጫማ ይህል ነበር» ብሏል። /Robert of Clari’s account of the Fourth Crusade, chapter 82: OF THE MARVELS OF CONSTANTINOPLE/

የመስቀሉ ለሁለተኛ ጊዜ መጥፋት

እስከ ስድስተኛው መክዘ ድረስ በኢየሩሳሌም ጎልጎታ የነበረው መስቀል በ614 ዓም በፋርሱ ንጉሥ ክሮስረስ 2ኛ /Chrosroes II/ ተወሰደ። የፋርሱ ንጉስ ኢየሩሳሌምን በወረረ መስቀሉን እና ፓትርያርክ ዘካርያስን ማርኮ ወደ ፋርስ ወሰዳቸው። እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሰው ሕርቃል በ627 ዓም ባደረገው ጦርነት ክሮስረስ ድል ሲሆን ነው። ሕርቃል በመጀመርያ ወደ ቁስጥንጥንያ ካመጣው በኋላ እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቀድሞ ቦታው በጎልጎታ አስቀምጦት ነበር።

እስከ አሥረኛው መክዘ ድረስ በኢየሩሳሌም በቀድሞ ክብሩ ቢቆይም ዐረቦች አካባቢውን እየተቆጣጠሩ ሲመጡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ክርስቲያኖች መስቀሉን በ1009 ዓም አካባቢ ሠወሩት። ለ90 ዓመታት ያህል ያለበት ቦታ ተሠውሮ ከኖረ በኋላ በመጀመርያው የመስቀል ጦርነት ጊዜ በ1099 ዓም ከተሠወረበት ወጥቶ እንደ ቀድሞው መታየት ጀመረ።

ለሦስተኛ ጊዜ መጥፋት

በ1187 ዓም በሐቲን ዐውደ ውጊያ ሳላሕዲን የተባለው የዓረቦች የጦር መሪ የመስቀል ጦረኞችን ድል አድርጎ ኢየሩሳሌምን ሲቆጣጠር በዚያ የነበረውን መስቀል መውሰዱን አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ይገልጣሉ። ከዚያ በኋላ ግን መስቀሉ የት እንዳለ እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም። በወቅቱ የነበሩት የሮም ነገሥታት መስቀሉን ለማግኘት ከሳላሕዲን ጋር ብዙ ድርድር አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

በአብዛኞቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የመስቀሉ ክፍልፋይ እንዳለ ሁሉም ይናገራሉ። አንዳንዶቹ አለ የሚባለው ክፍልፋይ ከመብዛቱ የተነሣ የሚያነሡት ትችት አለ። ጆን ካልቪን «ሁሉም ክፍልፋዮች ከመስቀሉ የወጡ ከሆነ፤ እነዚህን ሁሉ ብናሰባስባቸው አንድ መርከብ የግድ ያስፈልጋቸዋል። ወንጌል ግን ይህንን መስቀል አንድ ሰው እንደ ተሸከመው ይነግረናል» ብሎ ነበር።

ይህንን የካልቪንን ሂስ በተመለከተ መልስ የሰጠው ራውል ዲ ፈሌውሪ /Rohault de Fleury,/ በ1870 ዓም በዓለም ላይ አሉ በሚባሉት የመስቀል ክፍልፋዮች ላይ ጥናት አድርጎ ነበር። ራውል መጀመርያ የት ምን ያህል መጠን እንዳለ ካታሎግ አዘጋጀ፤ ከዚያም መጠናቸውን አንድ ላይ ደመረ። በታሪክ እንደሚነገረው የመስቀሉ ክብደት 75 ኪሎ፣ ጠቅላላ መጠኑም 178 ኪዩቢክ ሜትር ነው። ራውል ያገኛቸውና አሉ የተባሉት ክፍልፋዮች አንድ ላይ ቢደመሩ .004 ኪዩቢክ ሜትር /3.‚942‚000 ኪዩቢክ ሚሊ ሜትር/ ነው። በዚህም መሠረት ቀሪው 174 ኪዩቢክ የሚያህለው ሜትር የመስቀሉ ክፍል ጠፍቷል ማለት ነው ብሏል። /Mémoire sur les instruments de la Passion, 1870/

ግማደ መስቀሉ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መዛግብት እንደሚሉት ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ14ኛው መክዘ በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ነው። በግሼን አምባ የተቀመጠው ደግሞ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ነው።

ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርጉ የነበረውን ጉዞ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት የነበራቸውን ታዋቂነት እና ወደ ሀገረ ናግራን ተጉዘው የሠሩትን ሥራ ስንመለከት ኢትዮጵያ እስከዚያ ዘመን ድረስ ግማደ መስቀሉን ለማግኘት ትዘገያለች ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። በኢየሩሳሌም የሚገኘው የኢትዮጵያ ገዳም መስቀሉ ለወጣበት ቦታ እና ለጎልጎታ ያለውን ቅርበት፤ ዐፄ ካሌብም ከናግራን ዘመቻ በኋላ ዘውዳቸውን ለጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን መላካቸውን ስናይ ይህንን የመሰለ ቅዱስ ንዋይ ኢትዮጵያውያን እስከ 13ኛው መክዘ ድረስ አንዱን ክፋይ ሳያገኙት ቆዩ ለማለት ያስቸግራል። ኤርትራ ውስጥ ግማደ መስቀሉ አለበት የሚባል አንድ ገዳም መኖሩን ሰምቻለሁ።

ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ከሆነ በኋላ ነገሥታቱ በሳንቲሞቻቸው ላይ የመስቀል ምልክት ማድረጋቸው፣ እንደ ንጉሥ አርማሕ ያሉትም በበትረ መንግሥታቸው ላይ መስቀል ማድረጋቸው፤ ከቀደምት ክርስቲያን ነገሥታት አንዱ የሆነው ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ተብሎ መሰየሙን ስናይ የመስቀሉ ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ቀደ ምት ታሪክ ያመለክተናል።

በዛግዌ ሥርወ መንግሥትም ዐፄ ላሊበላ ስመ መንግሥቱ ገብረ መስቀል መባሉን፣ ሚስቱም ንግሥት መስቀል ክብራ መባሏን፣ ከሠራቸው አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያ ናት አንዱ ቤተ ጊዮርጊስ በመስቀል ቅርጽ መሠራቱን ስናይ ኢትዮጵያውያን ከመስቀሉ ጋር ቀድመው መተዋወቃቸውን ያስገምተናል። በመሆኑም በዚህ ረገድ መዛግብትን የማገላበጥ እና የመመርመር ሥራ የሚቀረን ይመስላል።

በዐፄ ዳዊት ዘመን መጥቶ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አማካኝነት በግሼን አምባ የተቀመጠው ግማደ መስቀል በይፋ የታወቀውና በነገሥታቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የመጣው ዋናው እንጂ የመጀመርያው ነው ለማለት ያስቸግራል።

ተክለ ጻድቅ መኩርያ ግብጻዊው ጸሐፊ ማክሪዝ Historia Rerum Isi amiticarumin Abissinia በሚለው መጽሐፉ የገለጠውን መሠረት በማድረግ «የኢትዮጵያ ታሪክ ከይኩኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል» በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚተርኩት አስቀድሞ በሰይፈ አርእድ ዘመን በግብጹ ሡልጣን እና በኢትዮጵያዊው ንጉሥ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። የልዑካን ቡድኑ መሪ የኢየሩሳሌሙ ፓትርያርክ አባ ዮሐንስ ነበሩ።

ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲደርሱ ያገኟቸው ዐፄ ዳዊትን ነበር። በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን ችግር በውይይት እና በስምምነት ፈትተው አስማሟቸው። ዐፄ ዳዊትም ግማደ መስቀሉን እንዲልኩለት የኢየሩሳሌሙን ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስን አደራ አላቸው። እርሳቸውም ከግማደ መስቀሉ ጋር ሌሎች ንዋያትንም ጨምረው ላኩለት። በግብጹ ሡልጣን እና በንጉሥ ዳዊት መካከል የተፈጸመው ስምምነት ለኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች እና ነጋዴዎች ጥበቃ ማድረግን የሚያካትት ስለ ነበር ግማደ መስቀሉን የያዙት የዐፄ ዳዊት መልእክተኞች ያለ ችግር ኢትዮጵያ ገቡ።

አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ዐፄ ዳዊት ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 1404 ዓም በድንገት ሲያርፉ ግማደ መስቀሉ በሱዳን ስናር ነበር ይላሉ። ከስናር ያነሡት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መሆናቸውንም ይተርካሉ። ተክለ ጻደቅ መኩርያ ግን ዐፄ ዳዊት ወደ ኢትዮጵያ አስገብተውት በተጉለት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት እንደ ነበር ይናገራሉ። ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የነገሡት በ1434 ዓም ነው። በእነዚህ ሠላሳ ዓመታትም አያሌ ነገሥታት ተፈራርቀዋል። እነዚህ ነገሥታት ግማደ መስቀሉን ለመውሰድ ያልቻሉበትን ምክንያት ማወቅ አይቻልም። ምናልባት ግን በነበረው የርስ በርስ ሽኩቻ ተጠምደው ይሆናል። ሌሎች መዛግብት እንጂ በኋላ ዘመን /ምናልባትም በዐፄ ልብነ ድንግል/ የተጻፈው የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል የግማደ መስቀሉን ነገር አይነግረንም።

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግሼን አምባ ላይ ግማደ መስቀሉን ያስቀመጠበት ሁለት ምክንያቶች ይኖራሉ። የመጀመርያው የአምባው የመስቀለኛ ምልክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አምባው በዘመኑ በልዩ የንጉሠ ነገሥቱ ኃይል ይጠበቅ ስለ ነበር ነው። በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም ቢሆን ሌሎች ሀብቶች ከአምባው ላይ መዘረፋቸውን እንጂ የተቀበረውን ለማውጣት ሙከራ መደረጉን የግራኝን ታሪክ የጻፈው ዐረብ ፋቂህ አያነሣም።

ግማደ መስቀሉን የማውጣት ጥረት ተደረገ የሚባለው በ1851 ዓም ዐፄ ቴዎድሮስ በጣም የሚወዷቸው ባለቤታቸው እቴጌ ምንትዋብ ከሞቱ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው። ንጉሥ ቴዎድሮስ እቴጌ ምንትዋብን እጅግ ይወዷቸው ስለነበር በመስቀሉ አማካኝነት ከሞት ለማስነሣት አስበው ነበር። ይህንንም በወታደሮች ኃይል በማስቆፈር አስጀምረውት ነበር። በመካከል ግን ከጉድጓዱ ኃይለኛ ሽታ እና ጢስ ወጥቶ ከቆፋሪዎቹ የተወሰኑትን በመግደሉ ሃሳባቸውን ሠርዘው ባለቤታቸውን በግሼን አምባ ቀብረው ተመልሰዋል።

 

ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት (መድረክ)

የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ከዛሬ 26 ዓመት በፊት የአምባገነኑ የደርግ መንግስት ሲገረሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረው ተስፋና ምኞት ወደፊት አገራችንን ዘላቂ ሠላምና ሕገመንግስታዊ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንደሚሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንደሚገኝ፣ ሕዝቡ በነፃ ፍላጎቱ የህግ የበላይነት እና በራሱ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ መንግስት በማቋቋም፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን እና የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት በማረጋገጥ አንድነቱ የተጠበቀ ኢትዮጵያን በጋራ ለማየት ነበር።

ዛሬ አገሪቷ በምትተዳደረው ሕገ መንግስት አንቀጽ 32/1 መሠረት “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው”። ሕገመንግስታዊ ድንጋጌውን ለማስከበር ባለመቻሉ እንሆ ዜጎች ከአንዱ ክልል ወጥተው በሌላው ወይም በጎረቤት ክልል ውስጥ ለግድያ እና ለመፈናቀል ይዳረጋሉ።

ይህንን እንድናነሳ ያስገደደን ሰሞኑን እንደታየው በምሥራቁ አገራችን ክፍል፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግስታት መካከል በድንበር ጥያቄ ምክንያት በተነሣው ግጭት ዜጎች ለሞት፣ ከነበሩበት ቀዬ፣ ከቤት ንብረታቸው የመፈናቀል አሰቃቂ በደል ብቻ ሳይሆን የወደፊት አብሮነትን ተፈታታኝ ችግር ገጥሞናል። ማንነታቸው የማይታወቁ፣ የተደራጁና የታጠቁ ልዩ ኃይሎች ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን እየገደሉ የሚያፈናቅሉ ኃይሎች መኖራቸው በሁለቱ መስተዳደር ኃላፊዎች ተገልጿል። ይህ ታጣቂ ኃይል ከማን ትዕዛዝ እንደሚቀበል በውል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ሁለቱም ክልሎች አንዱ በሌላው ላይ ከማሳበብ በስተቀር የእነኝህ ኃይሎች አዛዥ ማን እንደሆነ በግልጽ ያስታወቁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ እነዚህ ልዩ ኃይል ተብየዎች እና ለዜጎች ሰብአዊ ህልውና ደንታ የሌላቸው በፌዴራል መንግስት ዕውቅና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መስተዳደር አደራጅቶ እና አሰልጥኖ እንዳሰማራቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።

መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ በዚህ በድንበር ጥያቄ ሰበብ ለዘመናት አብረው የኖሩ ክፉና ደጉን ያዩ ሕዝቦች “አንተ የዚህ ክልል ዜጋ አይደለህም ውጣ ወደ ክልልህ ሂድ” የሚባልበት ጉዳይ ሊኖር አይገባም። ሕገ መንግሥቱን አክብሮ የሚያስከብር መንግሥት እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጸም የዜጎችን መብትና የአከባቢው ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ያለምንም ጥርጥር የኢህአዴግ መንግሥትና ክልል መስተዳድሮች ነበር። ይህ ሣይሆን ቀርቶ ግን በድንበር ጥያቄ ምክንያት የተነሣ በሁሉም አገራችን ክፍሎች ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ ግጭቶች እየተበራከቱ ነው፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት በከንቱ አልፏል፣ ሕዝቦች በከፍተኛ ደረጃ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩ 55,000 የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቅለው አሁን በምሥራቅ ሐረርጌ ተጠልለው የወገንን ዕርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ ከደረሱን መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል። ግጭቱ የሱማሌ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያዋስነው ከምሥራቅ ሐረርጌ እስከ ደቡብ ክፍል ሞያሌ ድረሰ ተስፋፍቶ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል።

ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት ባለፈው 2009 ዓ.ም ዘመን አገራችን የተለያዩ አስከፊ ክስተቶችን አስተናግዳለች። የሕዝብ ብሶት ከገደብ አልፎ አደባባይ የወጣበትና የደረሰበትን ችግር ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ መንግሥትን የጠየቀው ሕዝብ ተተኩሶበታል። ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቶ በመቶ መርጦኛል በማለት የሀገሪቷን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮቹን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ባለበት ወቅት ሕዝብ በዴሞክራሲ አለመኖር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና በመንሰራፋቱ፣ ለሰብአዊ መብት መረጋገጥና በነፃነት መኖር፣ የሥርኣት ለውጥ ጥያቄ አንስቶ እንዲፈታለት ጠይቋል።

የኢህአዴግ መንግሥት ሕዝብ ያቀረባቸውን የመብት ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸው ተቀብሎ ምላሽ ባለመስጠቱ የተነሣ ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የሚያምንና ኃላፊነቱንም እንደሚወስድ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ አድርገው ይቅርታ ጠይቀዋል። ሕዝቡም ኢህአዴግ ቆራጥ ሆኗል፣ የሕዝብን ጥያቄ ካለምንም ማመንታት በራሱ ወስኖ የቀረቡትን ብሶቶች ያስተካክላል፣ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ይከተላል ብሎ ይጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ ከሕዝብ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ አፋጣኝ መልስ የሚሰጥ መስሎ ራሴን በጥልቅ ተሀድሶ አድርጌያለሁ በማለት ራሱን እንደገና አደራጅቶ የካቢኔ ሹም ሽር ከላይ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ አድርጎ ሕዝቡ የጠየቀውን መልስ እሰጣለሁ በማለት ቀድሞ ይዞት በነበረው ሁኔታ ቀጥሏል። ኢህአዴግ የአቋም ለውጥ ለማድረግ ባለመቻሉና ከሕዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ባለመቻሉ የሕዝብ ቅሬታ ቀጥሎ በአገሪቷ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ አስከትሏል።

እንዲያውም ተፈጥሮ ያስከተላቸው ችግሮች ሳይጨመሩ የሕዝብን ብሶት ከሚያባብሱ እርምጃዎች አንዳንዶቹ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ላይ ታላቁ  የኦሮሞ ባህልና ኃይማኖታዊ የእሬቻ በዓል አከባበር ላይ የብዙ ወገኖች ህይወት ዘግናኝ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ጠፍቷል።

የሕዝብ ቅሬታ ተባብሶ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆነ በማለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ከ20,000 በላይ ዜጎች እስር ቤት የታጎሩበትና ለ10 ወራት ያህል ከሕገ መንግስቱ ድንጋጌ ውጪ የዜጎች መብት በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተገደበበት ጊዜ ነበር።

በአነስተኛ ግብር ከፋዮች ላይ የመክፈል አቅምን ያላገናዘበና ትኩረት ተሰጥቶት ከከፋዩ ህብረተሰብ ጋር በቂ ጥናትና ምክክር ሳይደረግበት የተወሰነው ግብር ቅሬታን ፈጥሯል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥናቱ 40በመቶ ግድፈት ያለበት መሆኑን ገልጸውታል።

በየጊዜው የፍጆታ ዕቃዎችና የሸቀጣ ሸቀጥ መግዣ የዋጋ እየናረ በመምጣቱ ዋጋ ግሽበት ሊጨምር ችሏል። ይህም በሸምቶ አደሩ ኅብረተሰብ ላይ ቀላል የማይባል ችግር እንደፈጠረ ይታወቃል።

የ2009 ዓ.ም ዘመን በዚህ ሁኔታ ቢታለፍም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በአዋሳኝ ድንበሮች አከባቢ በተነሣው ግጭት ሁሉም የአገራችን ክፍሎት በዜጎች ላይ የሚደርሰው ሞት፣ ስደት፣ ከቤት ንብረት መፈናቀል በርክቷል።

አሁን በተያዘው አዲሱ 2010 ዓመት መግቢያ ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረው ግጭት አሁንም እየተካሄደ ነው። መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም አወዳይ ከተማ የ12 ኢትዮጵያዊያን ሱማሌዎች እና የ6 ኦሮሞዎች ሕይወት አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ በተደራጁና በታጠቁ ኃይሎች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ኢትዮጵያ ሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳደር የ12ቱ ሟቾች ቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመበት ጊዜ ወዲያውኑ በክልሉ የ7 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን እንዲሆን አውጀዋል። በግፍ ለተገደሉት ዜጎች የሐዘን ቀን ለምን ታወጀ ሳይሆን ሀዘኑንም ሆነ ደስታውን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ባማከለ መልኩ መሆን ነበረበት። በደቡቡ የአገራችን ክፍል በኦሮሚያና በሲዳማ ብሔረሰቦች መካከል  ተመሳሳይ ግጭት ተነስቶ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። በጉጂ ኦሮሞና በቡርጂ ብሔረሰብ መካከል የተካሄደው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም በተቀሰቀሰው ግጭት ከቡርጂ የአንድ ታዳጊ ሕፃን ጨምሮ 3 ሰዎች ሲሞቱ 5 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ብዙ የእህል ክምር በዚሁ ሰበብ ሊቃጠል ችሏል። ከመስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በገላና አባያና በቡሌ ሆራ ወረዳ በሚኖሩ የጉጂ ኦሮሞ እና በአማሮ ወረዳ ውስጥ በሚኖሩ የኮሬ ብሔረሰብ መካከል በተከሰተው ግጭት በኮሬ በኩል የሰባት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ የ14 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ቆስለዋል። በጉጂ በኩል ደግሞ የ8 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል።  በዚሁ ግጭት እስከ 40,000 የሚደርስ ሕዝብ ከነበረበት ቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም በባሌ ዞን አዳራጋ ወረዳ ቢዩ ቀበሌ 16 ሰዎች በተደራጁና በታጠቁ ልዩ ኃይሎች ግድያ ሲፈጸምባቸው 4 ሰዎች ቆስለው ጊኒር ሆስፒታል በመታከም ላይ እንደሆኑ ታውቋል።

በዚህ በባሌ ዞን ከአንገቶና ሌንሳዎ ወረዳዎች በእነዚህ ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ታጣቂዎች በተነሣው ግጭት 1700 የሚደርሱ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ ከነቤተሰባቸው ጭምር ወደ 5000 የሚደርሱ ሰዎች የመፈናቀል ዕጣ እና ሌሎች ችግሮች የድሃ ዜጎቻችን ሕይወት ወደ አዘቅት ከመወርወሩም በላይ ሠላምን ያደፈርሳል።  

ይህ ከድንበር ጥያቄ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለወደፊት በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ግጭት አይከሰትም የሚል እምነት የለንም። በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መካከል የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ሁለቱ ክልሎችን ሲያወዛግብ እንደቆየ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የሁለቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች ስምምነት ተደርጓል ተብሎ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተገልጿል። ስምምነቱ የሕዝብ ፈቃደኝነት ጭምር ከሆነ ዘላቂ ሠላም የመፍጠሩ ጉዳይ ከተሳካ የመድረክ ምኞቱ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል።

በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች ላይ ላዩን ሲታይ ሕዝቦች በድንበር ጥያቄ ምክንያት የሚነሣ ነው ተብሎ ቢቀርብም እውነታው ግን ሕዝቡ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ ክፉና ደጉን የሚራ ሕዝብ እንጂ በዕለት ሁኔታ ተነሳስቶ በድንበር አሳቦ እስከመጠፋፋት እና ለከፋ አደጋ እንደማይደርስ እናውቃለን። ገዢው ፓርቲና መንግሥት የአስተዳደር መዋቅሩ ከላይ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ጎጥ ድረስ ዘርግቶ ሕዝቡን 1 ለ 5 የስለላ መረቡን ዘርግቶ ባለበት ሁኔታ ከመንግሥት እውቅና ውጭ የሚፈጸም አንዳችም ክፉም ሆነ በጎ ነገር እንደማይኖር እርግጠኞች ነን።

በሁሉም አገሪቷ ክልሎች የገዢው ፓርቲና መንግስት ካቢኔዎችና ካድሬዎች አማካይነት ችግሮቹ እንዲባባሱ እንደሚያደርጉት እንገምታለን። ይህም የሕዝባችን የወደፊት አብሮነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ጣልቃ በመግባት ሁኔታዎችን ወደ ሕዝቦች ዕልቂት እንዳያመራና የበለጠ እንዲባባስ የሚፈልጉ አካላት ያሉ መሆኑን ይጠቁማል። ለመሆኑ ለዘመናት በሠላም አብሮ የኖረው ሕዝብ አሁን ተነሥቶ በድንበር ግጭት ምክንያት ለዚህ ከፍተኛ ዕልቂትና መፈናቀል እንዴት ሊደርስ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ሀገሪቷን የሚያስተዳድረው ፓርቲና መንግሥት ራሱ ባወጣው ሕገ መንግሥት የማይገዛ መንግሥት መሆኑን አስምረንበት እንናገራለን። ይኼውም ሕዝብ ቀደም ሲል ያነሳቸው፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የመብትና የስርዓት ለውጥ ጥያቄዎችን ላለመመለስና የሕዝቡን ሠላማዊ ትግል አቅጣጫ ለማስቀየር የታቀደ ዘዴ ሆኖ አግኝተናል።

ዜጎች ሉአላዊ ሀገርና መንግሥት በጋራ የሚመሰርቱት በግል የሚደርስባቸውን ጥቃት መንግሥት እንዲከላከልላቸው፣ የጋራ ኃይል ለመፍጠር፣ መሠረተ ልማትን እንዲሠራላቸው፣ ደህንነታቸውና ፀጥታን እንዲያስከብርላቸው ወዘተ… ብለው ነው። ነገር ግን የኢህአዴግ መንግሥት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፋት፣ የመሠረተ ልማት ውጥኖች ሁሉ በራሱ ችሮታ ያደረገ እያስመሰለ በየጊዜው በሚቆጣጠረው የብዙኃን መገናኛ መሣሪያ ሕዝብን  ለማሞኘት ይሞክራል። የሕዝብ መንግሥት የገዛ ሕዝቡን ያከብራል፣ ይታዘዛል፣ የሕዝቡ ተቀጣሪ ነው፣ አምባገነን መንግሥት ሕዝብን ይንቃሉ፣ የሚከሰቱ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ያምናሉ፣ ሁሉን ነገር ከሥልጣኑ አንፃር ለማየት ይጥራሉ።

ኢህአዴግ በባሕርዩ በህዝቦች ስቃይ የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል የማይጠቀማቸው ስልት የለም። መድረክ፤ ኢህአዴግ አዘወትሮ የሚጠቀምባቸዉን ስልቶች ጠንቅቆ ያውቃል። አሁን በየቦታው ዳር ድንበርን በማካለል ስልት ሕዝቦችን በካድሬዎች አማካይነት እያጋጨ፣ እያለያየ ለጊዜ ማራዘሚያ የሚጠቀምበት ስልት ነው። ስለዚህ ሁሉም ዜጎች ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ችግሮቻቸውን ከሌላ ጣልቃ ገብነት ውጪ ራሳቸው ተቀራርበው ሊያጋጩዋቸው በሚችሉት ጉዳዮች ላይ በመግባባት ተወያይተው መፍታት እንደሚችሉ ለማስገንዘብ እንወዳለን። ለዚህም አፋጣኝ ጥሪ እናደርጋለን።

አምባገነኖች ሕዝብን ለመከፋፈል ቢሞክሩ እንኳን የአንዱ ብሔር ሕልውና ለሌላው ብሔር ህልውና አስፈላጊ ነው። በኢህአዴግ ጠባብ ፍላጎት የፌዴራል ስርዓቱ በዴሞክራሲያዊ አሰራር ባለመታጀቡም የፌዴራል ስርዓቱ አደረጃጀት ለግጭቶቹ መንስኤ ተደርጎም ሊወሰድ አይገባም።

መድረክ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቷ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ፈርጀ ብዙ ችግሮች ኢህአዴግ በያዘው ሁኔታ መቀጠሉ አደጋ ያለው መሆኑን ከማስገንዘብ የቦዘነበት ጊዜ የለም። እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ለማሳየት የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ኢህአዴግ ላወጣው ሕገመንግሥት ተገዢ እንዲሆን፣ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ውስጥ ወሣኝ መሆናቸው ታውቆ በተለይም የአገራችን ጉዳይ ይገባናል የሚሉ ፓርቲዎች በክብ ጠረጰዛ ተቀራርበው ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ ገለልተኛ በሆኑ ወገኖች ማዕከልነትና በታዛቢዎች አማካይነት የጋራ ድርድር ለማድረግ መድረክ ምንጊዜም ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ የጠቀስናቸው ችግሮች የኢህአዴግ መንግስት መዋቅሩን ከላይ እስከ ታች ድረስ ዘርግቶ በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ጉዳዮች ስለሆኑ ተጠያቂው ራሱ መንግሥት ነው፣ ስለዚህ፡-     

1.በአገሪቷ ውስጥ በድንበር ጥያቄ ምክንያት እና በሕዝቦች መካከል በተከሰቱ ግጭቶች ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መቋቋሚያ እንዲከፈላቸው።

2.በመንግሥት አስተዳደር ድክመት ምክንያት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ባለመቻሉ እንዲያውም የየአካባቢው ካድሬዎችና ካቢኔዎች አባባሽነት ምክንያት ለተፈጠረው የዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ተጠያቂዎች ስለሆኑ መንግሥት በአስቸኳይ ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት ቀዬአቸው ተመልሰው የቀድሞ ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲቀጥሉ እንዲያደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

3.የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በጋራም ሆነ በተናጠል የአካባቢውን ፀጥታ፣ ሠላም የማስከበርና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነትና ሕገመንግስታዊ ግዴታ አለባቸው። በመሆኑም ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂ ኃይሎች በቡድን ተደራጅተው ምንም ትጥቅና የመከላከል ኃይል በሌላው ሕዝብ ላይ ዘምተው ይህን የከፋና ዘግናኝና አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ የንፁሐን ዜጎች ህይወት ሲጠፋና ከነበሩበት ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ሲደረግ ባለሥልጣኖቹ አስቀድመው አያውቁም ማለት አይቻልም። የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እርምጃ መውሰድ ሲገባቸው ይህንኑ ባለማድረጋቸው ለጠፋው የዜጎች ሕይወትና ለደረሰው ውድመት በሕግ እንዲጠየቁ እናሳስባለን።

4.ይህን ኃላፊነት የጎደለውን ሰይጣናዊ ድርጊት ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በሠላም በመኖር ላይ ባለው ሕዝብ መካከል ግጭቶች እንዲባባሱ፣ የዜጎች ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም፣ ሕዝብ እንዲፈናቀል ያደረጉ፣ ለዚህ በቀጥታ አመራር የሰጡ፣ የፈጸሙ፣ የተባበሩ ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ እስከ ታችኛው ቀበሌ አመራር ድረስ እጃቸው ያለበት፣ በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሁሉ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለደረሰው ውድመት ተጠያቂዎች ናቸው። ስለዚህ ጥፋቱን ገለልተኛ የሆነ አካል አጣርቶ ጥፋተኞች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ እናሳስባለን።

በመጨረሻ ሕዝባችን ለወደፊቱ በዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት የተነሳ በወገኖቻችን ላይ ለተፈጸመው የሞት አደጋ ጥልቅ የሆነ ሀዘናችንን እየገለጽን እንደዚህ ዓይነት የጥቃት እርምጃዎች እንዳይጋለጥ አብሮነትን የሚሸረሽሩ ወቅቱን እየጠበቀ የሚከሰተውን ግጭት ሕዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ነቅቶ በመጠበቅ ስርዓት በተሞላበት እና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ አንድነቱን አጠናክሮ አስፈላጊውን የዕርምት እርምጃ እንዲወስድ መድረክ አበክሮ ያሳስባል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2010 ዓ.ም

 

ኢዴፓ

 

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በ2008 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ሃገራችን ገጥሟት የነበረው አደጋ ከፍተኛ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። ፓርቲያችን በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋነኛው የችግሩ ምንጭ ግን የኢህአዴግ ቋንቋንና ብሄረሰባዊ ማንነትን ያማከለ የፌደራል ስርዓት ነው የሚል እምነት አለው። ቋንቋንና ብሄረሰባዊ ማንነትን ዋነኛ መስፈርቱ ያደረገው የፌደራል ስርዓት ኢዴፓ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው ከአንድነት፣ ከመቻቻልና ከመከባበር ይልቅ የጎሪጥ ለመተያየትና ለኔ ብቻ የሚል የጠባብነት ስሜትን የሚፈጥር ለልዩነት በር የሚከፍት ስርዓት እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል። ነገር ግን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠቱ ምክንያት ችግሮች ከመፈታት ይልቅ በየጊዜው እየተባባሱ ለመሄድ ተገደዋል። መንግስት በፌደራሉ ስርዓት ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ግዜያዊ መፍትሄ ላይ ያተኮረ እርምጃ መውሰድ ላይ በማተኮሩ ውጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሃገራችንን ህልውና የሚፈታተን ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው።


ሰሞኑን በኦሮሚያ ህዝብ ክልልና በኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ክልል አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ተከስቶ ወደ ከተሞች በዘለቀው ግጭት ምክንያት ዘግናኝ አደጋ ተከስቷል። የብዙ ዜጎች ህይወት አልፏል፣ ሃብት ንብረታቸው ወድሟል፣ ዜጎች ለዘመናት በአብሮነት፣ በመቻቻል ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው ለከፍተኛ የስነ-ልቦና፣ የሞራል ውድቀትና እንግልት ተጋልጠዋል። እንዲህ አይነቱ የጎሳ ግጭት አርብቶ አደር በሆኑ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከእንሰሳት የግጦሽና የውሃ እጥረት ጋር ተያይዞ ይከሰት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን መልኩን እየቀየረ በመምጣት ህዝባችንን ለከፍተኛ ግጭት ከማጋለጡም በላይ ለሃገራችን ህልውና ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል። ባለፉት ቀናት በጭናክሰን፣ በባቢሌ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በበደኖና በሌሎች አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትና አዛውንቶች ከፍተኛ እንግልት ላይ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ግጭቱ አድማሱን እያሰፋ እንዳይሄድ ኢዴፓ ከፍተኛ ስጋት አለው።


እንዲህ አይነቱ ሃገራዊ ስጋትና አደጋ ተባብሶ ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ከሁሉም በላይ መንግስት ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ያለውን መንግስታዊ መዋቅርና አደረጃጀት፣ የፖሊስ፣ የመከላከያና የጸጥታ ሃይሉን ተጠቅሞ ህዝቡን ከአደጋ የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። ሆኖም አስቀድሞ የፌደራል መንግስቱና የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ግጭቱን ለመከላከልና ጉዳቱን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረትም ሆነ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ የተሰጠው ምላሽ አዝጋሚ መሆን ጉዳቱን ከፍተኛ እንዳደረገውና ፓርቲያችን ተገንዝቧል። በመሆኑም


1ኛ- መንግስት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ አሁን ያለውን የፌደራል ስርዓት የህዝቦችን አንድነትና መከባበር ያረጋገጠ ነው ከሚል ደረቅ ፕሮፖጋንዳ ተላቆ ለግጭት መነሻ እየሆነ ያለውን የፌደራል ስርዓቱን አወቃቀር ከቋንቋና ከብሄረሰባዊ ማንነት በተጨማሪ ሌሎች ለመከባበርና ለመቻቻል እንዲሁም ለጠንካራ ሃገራዊ አንድነት መሰረት የሚጥሉ መስፈርቶችን ያካተተ በማድረግ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፣
2ኛ- መንግስትና የሁለቱም ክልሎች ባለስልጣናት ችግሩን አለባብሰውና የጥቂት ግለሰቦች ድርጊት አድረገው ነገሩን ከማቃለል ተቆጥበው በዘላቂነት ችግሩ የሚፈታበትን የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲከተሉ፣


3ኛ- የክልሉ መንግስት እና የፌደራል መንግሰት የጸጥታ ሃይሎች ችግሩን ለመፍታት በሚል እየወሰዱ ያሉትን የጅምላ እስርና የሃይል እርምጃ በአስቸኳይ በማቆም ችግሩን በግዜያዊነት ለማስቆም ከሚያከናውኑት የእሳት ማጥፋት ስራ ጎን ለጎን ከዚህ ግጭት በስተጀርባ ያለውን ማንኛውንም የጥፋት እጅ አድነው መያዝ ይኖርባቸዋል፣


4ኛ- በግጭቱ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እርዳታ እና ወደ ቀድሞ ህይወታቸው የሚመለሱበት ድጋፍ መንግስት በአስቸኳይ እንዲያርግላቸው፣
5ኛ- በግጭቱ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ አካል እንዲቋቋም እዴፓ እየተጠየቀ ከባለፉት ሁለት አመታት ወዲህ እዛም እዚሀም በተለያዩ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችና ተቃውሞዎች መስመራቸውን ስተው እንደ ሀገርና ህዝብ ዋጋ እንዳያስከፍሉን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጉዳዩ ጋር ግንኑኙት ያለን አካላት በተለይም መንግስት፣ ህዝቡ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ሃይሎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ፣ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች፣ በውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የእምነት ተቋማት፣ ሙሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላችሁን ግዴታ እንድትወጡ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።


የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 

ጋዜጣዊ መግለጫ

በግብር ጭማሪው ላይ ቅሬታና ተቃውሞ ለሚያሰሙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የሚሰጠው መንግሥታዊ ምላሽና የጉዳዩ አያያዝ ሰብዓዊና የዜግነት መብቶቻቸውን የጠበቀ ሊሆን ይገባል፤

 

በክልሎች መካከል ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች በአስቸኳይ እልባት ይሰጣቸው

 

1.  በንግድ ማህበረሰቡ ላይ የገቢ ግምትና የግብር አተማመንን ተከትሎ በነጋዴዎች የተነሱ ቅሬታዎችና ተቃውሞ

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 41/1 ማንኛውም ዜጋ በመረጠው የስራ ዘርፍ የመሰማራት መብት እንዳለው ይደነግጋል። ይህንን የዜጎችን መብት የማሟላት ግንባር ቀደም ኃላፊነት የተጣለው በመንግስት ላይ ነው። መንግስት የሚያወጣቸው ሕጎችና መመሪያዎች እንዲሁም የሚወስዳቸው እርምጃዎች የዜጎችን ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ያገናዘቡና የሚያሻሽሉ፣ የዜጎችን ጥቅም በማስጠበቅ ላይ ያተኮሩ ሊሆኑ ይገባቸዋል፤ በተጨማሪም በነዚህ ሂደቶች ውስጥ ከህዝብ ጋር በቂ ምክክርና ውይይት አስቀድሞ መደረግና በተቻለ መጠንም መግባባት ላይ መደረስ ይኖርበታል፣ ይህ ሳይደረግ ቀርቶ ሕጎችን፣ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በቀጥታ በሕዝብ ላይ መጫን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሰመጉ ያምናል።

 

በቅርቡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን “አማካይ የቀን ገቢ ግምት” በማለት በንግድ ማህበረሰቡ ላይ የጣለውን የግብር መጠን አሳውቋል። ይህንንም ተከትሎ ከንግድ ማህበረሰቡ የገቢ ግምትና የግብር አወሳሰኑ የቀን ገቢያችንን ያገናዘበ አይደለም፣ እጅግ የተጋነነ ነው በማለት ከፍተኛ ቅሬታ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞችና አካባቢዎች ተሰምቷል፤ ይህ የንግዱ ማህበረሰብ ቅሬታና አቤቱታ የነጋዴዎችን የዜግነትና ሰብዓዊ መብቶችን በአከበረ ሁኔታ ባለመያዙና ባለመፈታቱ፣ ይህ መግለጫ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ፣ የንግድ ሱቆችን መዝጋትና የሥራ ማቆም አድማ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ በርካታ መልኮች ያሉት ከፍተኛ ተቃውሞና አቤቱታ በንግዱ ማህበረሰብ በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰማቱ እንደቀጠለ ነው።

 

በአንዳንድ አካባቢዎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የሚያነሱትን ቅሬታ እና አቤቱታ ከቅሬታ አቅራቢው የፖለቲካ አመለካከት ጋር በማያያዝ አድሎ እየተፈፀመ እንደሚገኝ አንዳንድ ነጋዴዎች በምሬት ያነሳሉ። እንዲሁም ከ20 እስከ 30 ዓመታት በንግድ ስራ ተሰማርተው ግብር እየገበሩ የቆዩ ነጋዴዎችም፣ አዲሱ የግብር ጭማሪ ላይ ቅሬታቸውን በማሰማታቸው ብቻ፣ “ለንግድ ስራችሁ መነሻ የሆናችሁን ገንዘብ ከየት አመጣችሁ?” በማለት እንግልትና መጉላላት እንደተፈጸመባቸው ለሰመጉ ገልጸዋል። የመንግስት አካላት የንግዱን ማህበረሰብ ቅሬታና አቤቱታ፣ የዜግነትና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በጠበቀ አግባብና በትግሥት ከማስተናገድና ከመፍታት ይልቅ አቤቱታ በሚያቀርቡ ነጋዴዎች ላይ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ማንገላታት፣ የንግድ ሱቅ ማሸግ፣ የተሽከርካሪ ሠሌዳ መፍታት እና ሕገወጥ እስር መፈጸማቸው ሕገመንግሥቱን የሚጻረር መሆኑን ሰመጉ ያምናል።

 

የነጋዴው ማህበረሰብ ተቃውሞውን ለመግለጽ የሚወስዳቸው ሰላማዊ እርምጃዎችም ሆኑ መንግሥት ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ በሚያሰሙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚወስዳቸው ኢ-ሕገመንግሥታዊ እርምጃዎች የመጨረሻ ውጤታቸው ምንም ቢሆን፣ በአጭር ጊዜ ግን የንግዱን ማህበረሰብ ግለሰብ አባላትና በአጠቃላይ የንግዱንም እንቅስቃሴ እንዲሁም መንግሥትን በልዩ ልዩ መልኩ እንደሚጎዳው ግልጽ ነው። በተለይም በመብት ጠያቂው የንግዱ ማኅበረሰብ እና መብቶችን የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታን በተሸከመው መንግሠት መካከል የሚወሰዱት ሕጋዊና ሕገወጥ እርምጃዎች ዞሮ ዞሮ እጅግ በሚበዛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ቀድሞም የነበረውን የሸቀጦችና የአገልግሎቶች እጥረት፣ የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነትና የመሳሰሉትን ጫናዎች እያባባሰና የሚያባብስ መሆኑም ሌላው ትኩረት የሚሻ አሳሳቢ ችግር ነው። ይህም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የዜጎችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ መብቶች የሚጎዳ ስለሆነ መንግሥት ሳይውል ሳይድር ዘላቂና ዕውነተኛ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል።

 

የንግዱን ማህበረሰብ እጅግ ያስደነገጠውና ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረበት “አማካይ የቀን ገቢ ግምት” ይፋ ከተደረገበት ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ሲያሰባስብና ቅሬታ ያላቸውን የንግዱን ማህበረሰብ አባላት አቤቱታ ሲቀበል ቆይቷል። ሰመጉ ዝርዝሩን ከተጨማሪ ጥናት በኋላ ወደፊት ይፋ የሚያደርገው ይሆናል። ለአሁኑ ግን የጉዳዩን አሳሳቢነት፣ እንዲሁም አፋጣኝ ትኩረትና ዕውነተኛ መፍትሄም የሚሻ መሆኑን ለማሳየት እንዲረዳ ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ያነሷቸው ቅሬታዎችና ይህንንም ተከትሎ የተወሰዱባቸው እርምጃዎች ከዚህ በታች በአጭሩና በጥቅሉ ቀርበዋል።

 

1.1.አዲስ አበባ

·              አዲስ ከተማ ክ/ከተማ (መርካቶ) ሰመጉ ያነጋገራቸው በርካታ ባለሱቆች ሐምሌ 2009 ዓ.ም ይፋ በተደረገው የቀን ገቢ ግብር ትመና ላይ ያላቸውን ቅሬታና ተቃውሞ ለማንጸባረቅ ሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ሱቃቸውን ዘግተው እንደነበርና የዘጉትን ሱቅ እንዲከፍቱ ማስጠንቀቂያ እንደተለጠፈባቸው ከዚያም ሱቆቻቸውን ለመክፈት እንደተገደዱ ለሰመጉ ገልጸዋል። መንግስት በሚያከራያቸው የንግድ ቤቶች ውስጥ የሚነግዱ ነጋዴዎች ለደቂቃም ቢሆን ሱቆቻቸውን ለተቃውሞ ቢዘጉ የተከራዩትን የንግድ ቤት ለቀው እንዲወጡ እንደሚደረጉ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

 

·              ቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ሲሳይ ሜዳ ገበያ ማዕከል፤ በዚሁ የገበያ ማዕከል ከጀበና ቡና (ቡና ጠጡ) እስከ የችርቻሮ ጥራጥሬ ንግድ የሚሰሩ ነጋዴዎች የዕለት ሽያጭ ግምት ከብር 300-1700 እንደተገመተባቸውና ይህም ማለት “በቀን ከምንሸጠው በ10 እጅ ተባዝቶ ነው የተገመተብን” በማለት ከፍተኛ ቅሬታቸውን ያሰማሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ ቂርቆስ የገበያ ማዕከል የሚሰሩ ነጋዴዎች፣ “ተመኑ ገቢያችንን በትክክል ያገናዘበ አይደለም” በሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም “ይጨመርባችኋል” በማለት የወረዳው የገቢዎች ኃላፊ እንደስፈራራቸው በምሬት ይገልጻሉ።

 

·              በዚሁ ወረዳ ውስጥ በአንድ የእንጨት ስራ ነጋዴ ላይ በቀን ገቢ ብር 40,000.00 /አርባ ሺህ ብር/ ታስገባለህ ተብሎ ተተምኖበታል።

 

·              ለአጠቃላይ ቀውሱ ተጨማሪ ማሳያ የሚሆነው በአንዳንድ አካባቢዎች የነጋዴዎች ገቢና የተተመነው ግብር ፈጽሞ ተመጣጣኝ አለመሆኑ፣ በተመሳሳይ ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች መካከል በጣም የተራራቀ የግብር ተመን መወሰኑና አነስተኛ የንግድ አንቅስቃሴና ገቢ ያላቸው ነጋዴዎች ከፍ ያለ የንግድ እንቅስቃሴና ገበያ ካላቸው ነጋዴዎች እኩል የግብር ተመን የተጣለባቸው መሆኑ ነው።

 

1.2.   ልዩ ልዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች፡የግብር ይስተካከልን ጥያቄያቸውን ጎላ ባለ መልኩ ነገር ግን በሰላማዊ መንገድ ከጠየቁት መካከል የሚከተሉት አካባቢዎች ነጋዴዎች ይገኙበታል፤

·         አማራ ክልል፡ ባህርዳር፣ ደብረታቦር፣ ወልድያ፣ ደሴ፣ ሸዋሮቢት፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ደንበጫ፣ ፍኖተሰላም፣ ሞጣ እና በተለያዩ ከተሞች፣

·         ኦሮሚያ ክልል፡ አምቦ፣ ጀልዱ፣ ጊንጪ፣ ግንደበረት፣ ሆለታ፣ ባኮ፣ ጉደር፣ ጃጄ፣ ደንቢ ዶሎ፣ ጊምቢ፣ መንዲ እና ነቀምት፣

·         ደቡብ ክልል፡ ሐዋሳ፣ ወላይታ ዞን ገሱባ ከተማ፣ አርባ ምንጭ፣ ጎፋ፣ ሳውላና አካባቢው፣

·         ምስራቅ ኢትዮጵያ፡ አዲሱን የግብር ተመን በተመለከተ ቅሬታ በስፋት ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል ደደር፣ ጨለለንቆ፣ አሰበ ተፈሪ፣ ጭሮ፣ በዲሳ፣ ገለምሶ፣ መቻራ፣ ቆቦ፣ ሐረር፣ ሀሮምያ፣ አወዳይ፣ ጂግጂጋ፣ ድሬደዋ፤

·         አዲስ አበባ ከተማ፡ ቂርቆስ ክ/ከተማ፣ ሽሮሜዳ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ፣ መርካቶ፣ ሃያሁለት፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ አራዳ ክ/ከተማና በሌሎችም ክ/ከተሞች ቅሬታዎች ቀርበዋል።

 

ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በተወሰደው “አማካይ የቀን ገቢ ግምት” መነሻነት የእለት ገቢያቸውን ያላገናዘበ ግብር የተጣለባቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ድርጅታቸውን በመዝጋትም ሆነ ሳይዘጉ በሰላማዊ መንገድ እንዲስተካከልላቸው ጥያቄና አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ቅሬታውና አቤቱታው በአጠቃላይ በሀገሪቱ በሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ዘንድ ታይቷል። የነጋዴው ማህበረሰብ ቅሬታዎችም በተለያዩ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደቀረቡና በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “40 በመቶ የሚሆነው የግብር ግምት ስህተት ነበር” በማለት በመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወቃል።

 

በአሁኑ ጊዜ የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ለአንዳንድ ተመልካቾች መልስ ያገኙ ቢመስሉም እንዲሁም መንግሥት ለአብዛኞቹ ቅሬታዎች በቅሬታ መስማት ሥርዓት መፍትሄ ሰጥቻለሁ ብልም፣ ሰመጉ ያሉት መረጃዎች የሚያመለክቱት ግን ጉዳዩ ገና እልባት አለማግኘቱን ነው። በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በተጣለባቸው ወይም ተሻሽሎላቸዋል በተባለው የግብር ተመን ላይ አሁንም ቅሬታ ስላላቸው ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆኑም። አንዳንዶች አቤቱታችን በየደረጃው በሚገኙ የመስተዳድር እርከኖች ምላሽ አላገኘም በሚል ወደ ፍርድ ቤት እየሄዱ ነው። ሌሎች ጥቂት የማይባሉ ደግሞ የቀራቸው አማራጭ የንግድ ፈቃዳቸውን መመለስ ብቻ መሆኑን እየገለጹ ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የንግዱ ማህበረሰብ ችግር ገና ያልተፈታ መሆኑንና ጥያቄውን ኃለፊነትና አስተዋይነት በተሞላበት መንገድ አሁንም ሳይረፍድ መፍታት እንደሚገባ ነው።

 

መንግሥት ይህን ከፍተኛ የግብር ጭማሪ በነጋዴው ላይ የጣለው፣ ምናልባት ወጪውን ለመሸፈን የሚረዳ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንደሆነ አድርጎ መረዳት ይቻላል። በሌላም በኩል የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የንግዱ ህብረተሰብ ፍትሐዊ፣ ለአድሎ ነጻ የሆነ፣ አቅምን ያገናዘበ እንዲሁም በመተማመንና በተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግብር መክፈል እንዳለበት እምነቱ ነው። ከዚህ በላይ የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ነገር ግን መንግስት የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄ በሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ መስጠት ይገባዋል። የንግድ ድርጅቶችን በማሸግ፣ ነጋዴዎችን በማስፈራራትና ያለአግባብ በማሰር እየወሰደ ያለውን ሕገወጥ ድርጊት እንደገና በፍጥነት ሊያጤንና ሊያርምም ይገባል። ከእልህና ጥድፊያ ይልቅ በትዕግሥትና በእውነተኛነት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመወያየት ፍትሐዊና አቅምን ያገናዘበ እንዲሁም ነጋዴውንም ሆነ መላ ሕዝቡን ዋና ተጠቃሚ የሚያደርግ ግብር እንዲጥልና እንዲሰበስብ እንዲሁም ሁሉንም የንግድ ማህበረተሰብ አባላት ያለአድልዎ በእኩልነት እንዲያስተናግድ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም መብታቸውን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸው ምክንያት የታሰሩ ነጋዴዎች እንዲፈቱ፣ የታሸጉባቸው ሱቆች እንዲከፈቱና ማስፈራራትና ማዋከቡም እንዲቆም ሰመጉ ይጠይቃል።

 

2.  በድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ሰበብ የከፉ ግጭቶች ከመቀስቀሳቸው በፊት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመመካከር አስቸኳይ መፍትሄ ይስጥ

 

ሰመጉ በሰበሰባቸው የተለያዩ መረጃዎች መሰረት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አካባቢዎች ከማንነት፣ ከአስተዳደርና ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ግጭት እየቀሰቀሰ ነው፣ ወይም ውሎ አድሮ ሊቀሰቀስ ይችላል። ከእነዚህም ግጭቶች አንዳንዶቹ ቀድሞውንም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውሶች አስከትለዋል፤ በጊዜ ካልተፈቱም ስፋቱንና መዳረሻውን ለመተንበይ የሚያስቸግር የከፋ የሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም የሰላም መረጋጋትና የባሱ የአንድነት ቀውሶችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሰመጉ ስጋት ነው።

 

2.1.  የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የድንበር ማካለል፡ እነዚህ ሁለት ክልሎች የድንበር ስምምነት ሰነድ የተፈራረሙ ቢሆኑም በአንድ ክልል ውስጥ ይተዳደሩ የነበሩ ቀበሌዎች ወደ ሌላኛው እንዲተዳደሩ በመወሰኑ በሁለቱም ማህበረሰቦች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፣ እስካሁንም አልተፈታም። በመሆኑም ሊነሳ የሚችለውን ግጭት ሊያስቀር አልቻለም። በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም አጋማሽና መጨረሻ እንዲሁም ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚዘጋጀበት ወቅትም በተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ባሉት የክልሎቹ ድንበር ግጭቶች ምክንያት ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሕይወት እየጠፋ ነው፣ በርካታ ዜጎች ቆስለዋል፣ በልዩ ልዩ መልክ እየተጎዱም ነው። በተለይም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሚኤሶ ወረዳ እንዲሁም የባሌና የብረና አዋሳኝ በሆነው የምሥራቅ ሐረርጌ ባቢሌ እና ፊቅ ወረዳዎች፣ በሀዊ ጉደና ወረዳ ግጭት እየተካሄደ ነው። በተጨማሪም የግጭት አደጋ ካንዣበበባቸው አካባቢዎች መካከል የጉርሰም ወረዳ፣ ቦርደዴ (ሀርደም ቀበሌ) እና ቦረና ወረዳዎች ይገኙበታል።

 

2.2.  በቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች፡ በድንበር ውዝግብ ምክንያት ሰርቦ፣ አባያና ደንቢ በሚባሉ አካባቢዎች በሚኖሩ የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል፤ በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ በመፈናቀል ላይ እንደሚገኙ ሰመጉ ለመረዳት ችሏል።

 

2.3.  በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ኦሮሞ ብሄረሰብ በሚኖርበት ገላና፣ አባያና የቡሌ ሆራ ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎችና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የኮሬ ብሔረሰብ በሚኖርበት በአማሮ ወረዳ ድንበሮቹን እንደ አዲስ ለመለየትና ለማካለል በተደረገው እንቅስቃሴ በሁለቱ ወንድማማች ማህበረሰቦች መካከል ግጭት ተደጋጋሚ ግጭት ተቀስቅሶ የብዙ ዜጎች ህይወት ጠፍታል፣ ከፍተኛ ንብረትም ወድሟል።

 

2.4.በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መስተዳድር ውስጥ፡ በሲዳማ ዞን በቦረቻ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የሲዳማ ብሔረሰብ አባላትና በወላይታ ዞን በምዕራብ አባያ ሁንቦ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የወላይታ ብሔረሰብ አባላት መካከል የተሞከረውን የድንበር ማካለል ሂደት ተከትሎ የሚታየው የድንበር ይገባኛል ውጥረት አስከፊ መዘዝና የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ሰመጉ ያምናል።

 

3.  ማሳሰቢያ

 

 

አስደንጋጭ የሆነውና በበቂ ሁኔታና ሙያ ያልተጠናው የግብር አወሳሰን በርካታ የንግዱን ማህበረሰብ አባላት ቅር ያሰኘና በአንዳንድ አካባቢዎች ቁጣን የቀሰቀሰም ሆኗል። ይህም የሆነበት ምክንያት ግብሩ በተጠናና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ባለመተመኑና በበቂ ሁኔታ ከህብረተሰቡ ጋር ምክክር ባለመደረጉም ነው። ስለዚህ መንግስት ቅሬታ ያነሱ ነጋዴዎችን አቤቱታ በመስማት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥና የግብር አወሳሰኑም በድጋሚ እንዲያጤን ሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።

 

ከማንነት፣ ከአስተዳደርና ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን፣ እየተቀሰቀሰ መሆኑን ወይም ሊቀሰቀስ እንደሚችል ሰመጉ የሰበሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ። በተመሳሳይ አካባቢዎች ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸው ይታወቃል። ስለሆነም የተፈሩት ግጭቶች በድጋሚ ተቀስቅሰው የሰው ህይወትና ንብረት ከመጥፋቱና በቀላሉ የማይሽር ጠባሳም ከመፈጠሩ በፊት መንግስት የፖሊሲዎቹን፣ የሕግና የአሰራሮቹን እንዲሁም የአፈጻጸሞቹን ትክክለኛነትና አዋጭነት እንደገና መርምሮ፣ ከሚመለከታቸው ማህበረሰቦችም ጋር በግልጽ፣ በቅንነትና የጋራ ጥቅምንና ደህንነትን ማዕከል ባደረገ መንፈስ በመወያየት በአስቸኳይ ዘላቂና የማያዳግም መፍትሄ እንዲሰጥ ሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።  

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዓ /ጳጉሜ 04 ቀን 2009 ዓ.ም/

                 

 

ጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ሁለት የሥራ ኃላፊዎች “የወወክማ ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊ መሆኑን የሚገልፅ ሰነድ በእጃችን ይገኛል” ሲሉ ለቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ የሰጡትን ምላሽ አንብበነዋል ስለ ሕጋዊነቱ ማረጋገጫ ነው የተባለውን የቃለ ጉባዔውን ሠነድንም ተመልክተነዋል።

የኤጀንሲው የክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብዛየን ገ/እግዚአብሔር እና የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ኤጀንሲው የጠቅላላ ጉባዔውን ሕጋዊነት ሊያረጋግጥበት ስለቻለበት ሁኔታ በቃለ መጠይቁ የሰጡት አመክንዮና ትንታኔ በፍሬ ነገር፣ በሕግና በደንብ ላይ ተመስርቶ ተቋማዊ ይዘቱን በጠበቀ ሁኔታ ሳይሆን በግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ፤ በሰሚ ሰሚ ላይ የተመረኮዘ (ጆሮ ጠገብ) በመሆኑ ኤጀንሲውን  ለማቋቋም በወጣው በአዋጅ ቁ. 621/2001 አንቀጽ 84 መሠረት ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት የኤጀንሲው አቋም ነው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል።

እንደ ብቁ ማስረጃ ተቆጥሮ የቀረበው ቃለ ጉባዔም በሚገባ ሳይመረመር ከነጉልህ ግድፈቶቹ በገሃድ ሊወጣ ስለቻለ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም ለተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማሕበር (ወወክማ) /YMCA/ 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ፤ ለጉባዔው አባላት ጥሪው የተላለፈበት ሁኔታ፣ በስብሰባው የተካፈሉ ሰዎችን ማንነት፣ የተደረገውም የቦርድ አባላት ምርጫ፣ ሕግንና የማሕበሩን ደንብ ያልተከተለ ስለሆነ ጉባዔው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ተሰርዘው ሌላ ጠቅላላ ጉባዔ መጠራት ይገባዋል ሲሉ የጠቅላላ ጉባኤና የማሕበሩ አባላት ለበጎ አድራጎት ደርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ “በተባበረ ድምጽ” (Petition) ያቀረቡት የተቃውሞ አቤቱታ እና ነሐሴ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ሁለት ግለሰቦች በጋዜጣው ላይ የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል ሲሉ ያሰፈሯቸው አስተያየቶች ትክክል መሆናቸውን ከማስረገጥ ባሻገር በእጃችን ይገኛል ያሉት ማስረጃ የጉባዔውን ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ ሆኖ አልተገኘም።

የኤጀንሲው ክትልልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት፣ በቀረበው ቅሬታ ላይ በቂ ክትትል ሳያደርግ፣ ሕግንና በኤጀንሲው ጸድቆ በሥራ ላይ ባለው የወወክማ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ የሠፈሩትን ድንጋጌዎችን እና ሠነዶችን ሳይመረምር እንዲሁም የሥራ ጊዜውን የፈፀመውን የቦርድ አባላትን ጨምሮ አዲሶቹን “ተመራጮች” እና ተቃውሞ ያቀረቡ አባላትንና ሌሎች በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ የሆኑ የማሕበሩን አባላት አገናኝቶ ሳያነጋግር የደረሰበት ድምዳሜ ሕጋዊና ፍትሃዊ ያለመሆኑን እንደሚከተለው ለመግለጽ ወደድን።

1.  የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ እስከ ተቋቋመበት 2001 ዓ.ም ድረስ ሲሰራበት በቆየው የወወክማ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የብሔራዊው ወወክማ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የነበሩት ከየቅርንጫፍ ማህበሩ የሚወከሉ አምስት አምስት አባላት ነሩ።

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን እየሠራ ባለው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ግን በውክልና የጠቅላላ ጉባዔን የመመሥረት ድንጋጌ አልሰፈረም።

ስለሆነም በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 13 በተደነገገው መሠረት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የሚሆኑት በደንቡ አንቀጽ ስምንት በፊደል (ለ) መሠረት የመምረጥና የመመረጥ መብት ያላቸው በሁሉም ቅርንጫፎች የተመዘገቡ የወወክማ አባላት ይሆናሉ ማለት ነው።

ሚያዚያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ በቀረበ ሪፖርት ማህበሩ አስራ ዘጠኝ ሺህ አባላት እንዳሉት ተገልጿል። ስለሆነም ለሁሉም አባላት መተዳደሪያ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት በደብዳቤና በብዙሃን መገናኛ የስብሰባ ጥሪ መተላለፍ ይገባዋል። ከክልልም ቢሆን መብት መጠበቅ ይገባል። በዚህ ረገድ ምልዐተ ጉባዔውን በቀላሉ ለሟሟላት ባይቻል እንኳን በአዋጁ አንቀጽ 84 መሠረት ድጋሚ ጥሩ በማስተላለፍ በተገኘው አባል ስብሰባውን ማድረግ ይቻል ነበር። በሺህዎች የሚቆጠሩ አባላትን ለማሰባሰብ የሚቸግር ከሆነ ብቸኛው መፍትሄ ደንቡን አሻሽሎ እንደቀድሞው በውክልና አሰራር መጠቀም ነው። ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ የአባላትን ህጋዊመብት ወደ ጎን ትቶ ጥቂት አባላት ተጠራርተው ቢሰበሰቡ ህገዊ ሊሆን አይችልም። የኤጀንሲው ኃላፊዎችም በደንቡ ላይ ከተገለፀው ውጪ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ቁጥር 20 ነው 24 ነው በማለት የሚከራከረው ከየት አምጥቶ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

2.  ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጉባዔው በቅርንጫፎች ውክልና ይመሰረታል ቢባል እንኳን፤ የወወክማ ጠቅላላ ጉባዔ ከየቅርንጫፉ በሚወክሉ ሁለት ሁለት አባላት የተዋቀረና  ማህበሩ 12 ቅርንጫፎች እንዳሉት በተገለፀው መሠረት 24 የጉባኤ አባላት እንዳሉት እየታወቀ የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያስረዳልኛል ብለው ባቀረቡት የሰነድ ዝርዝር ላይ ባይታይም 10 ቅርንጫፎች እና 20 የጉባዔ አባላት እንዳሉ ገልጸዋል።

በቅርንጫፎች ብዛት በኩል በኤጀንሲውና በማህበሩ መካከል የመረጃ ክፍተት ስላለ ነው በተጠቀሰው የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ኤጀንሲው ከማህበሩ መረጃ አሰባስቧል ወይ ብለን ለመጠየቅ የተገደድነው።

3.  ተደረገ በተባለው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ 54 የጉባዔ አባላት እንደተሳተፉበት የሚያሳይ የስም ዝርዝር የያዘ የመጽሐፍ መረጃ ቀርቧል።

ይሁን እንጂ፤

ሀ. ከተራ ቁ 1 እስከ 8 በስም የተዘረዘሩት ሰዎች (ሁለቱ ቁ. 4 እና 5) አልፈረሙም። የፈረሙትም ቢሆን የአገልግሎት ጊዜያቸውን የፈፀሙ የቦርድ አባላት ሲሆኑ በማህበሩ ደንብ መሠረት በተከታታይ ለ3ኛ ጊዜ ለምርጫ ሊቀርቡ የማይችሉ እንዲሁም በዚህ ጉባዔ ላይም በአባልነት እንዲሳተፉ ከየትኛውም ቅርንጫፍ ስላልተወከሉ በጉባዔው ላይ የሥራ ሪፖርት በማቅረብ ሥልጣናቸውን ከማስረከብና በታዛቢነት ከመገኘት በዘለለ ሌላ ሚና የሌላቸው ስለሆነ፤ እንደ ጉባኤ አባል ሊቆጠሩ አይችሉም። በተጨማሪም በተራ ቁጥር 2 ስር ስማቸው የተመዘገበውና እንደገና ተመርጠው የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል የተባሉትም ግለሰብ የመቀሌ ወወክማ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ይርጋ ገ/እግዚአብሔር እኛን አይወክሉንም በማለት በኢሜል ለብሔራዊ ቦርዱ በላኩት ሰነድ ያረጋገጡ መሆኑ እየታወቀና ከሌላም ቅርንጫፍ ውክልና የሌላቸው በመሆናቸው ምርጫው ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው።

ለ. ከተራ ቁ. 10 እስከ 20 እንዲሁም በተራ ቁ 24፣27፣28፣30፣33፣38፣44፣ 48፣ 52 የተዘረዘሩት በጠቅላላው 19 ሰዎች የማህበሩ ተቀጣሪ ሠራተኞች ናቸው። በጉባዔ አባላት መመዝገቢያ ሰነድ ላይ ሊመዘገቡ የማይገባና ግፋ ቢል እንደ አስረጂ ወይም እንደ ታዛቢ የሚቆጠሩ ስለሆነና በተራ ቁ. 27 ላይ የተመዘገቡት የአዲስ ከተማና የዑራኤል ወወክማ ከላይ እንደተገለፁት ቅጥር ሠራተኛ የነበሩና ከሥራም ከተሰናበቱ በኋላ የየትኛውም ቅርንጫፍ ማሕበርተኛ ሆነው ያላገለገሉ የአመራር ቦርድ አባል ያልነበሩ በመሆኑ በመተዳደሪያው ደንብ መሰረት ይህንን ያላሟላ ግለሰብ መምረጥም መመረጥም አይችልም። ስለዚህም ምክትል ሰብሳቢው ሆነው የተመረጡትበት አግባብ ሕገወጥ መሆኑ አሻሚ አይደለም።

ሐ. በተራ ቁ 29 ስማቸው የሰፈረውና በኤጀንሲው ዳይሬክተር የአራት ኪሎ ወወክማን ወክለው በጉባዔው ተሳትፈዋል የተባሉት አቶ ይልማ ሃብተማርያም በሌላ ባልቀረበ የፊርማ ማሰባሰቢያ ላይ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ስማቸውን በእጅ ጽሁፋቸው ጽፈው የፈረሙ ቢሆንም ማስረጃ ነው ተብሎ በቀረበው ሠነድ ላይ ግን አልፈረሙም። በተጨማሪም ከአራት ኪሎ ወወክማ የጠቅላላ ጉባዔ አባል በመሆን ቀደም ሲል የተወከሉት አቶ አስናቀ ደምሴ በጉባዔው ላይ ተገኝተው የፈረሙና በዕለቱም ስብሰባው በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የተጠራ አይደለም ሲሉ የልዩነት ሃሳባቸውን አስመዝግበው እና ስብሰባውን አቋርጠው የወጡ ቢሆንም በስም ዝርዝሩ ማስረጃ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ያልወጣ በመሆኑ በጋዜጣው ላይ ያውም በእጅ የተፃፈውን በመተው በኮምፒዩተር የተተየበ ሌላ ሠነድ መቅረቡ የሰነዱን ትክክለኛነት የማያረጋግጥ መሆኑን ያሳያል። በተራ ቁ. 42 የተመዘገቡትም ስለመገኘታቸው አልፈረሙም።

መ. አንድ የቅርንጫፍ ማህበር በጉባዔው የመሣተፍ መብቱ በሁለት ተወካዮች ብቻ የተገደበ መሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልጽ ያልሰፈረ ቢሆንም የኤጀንሲው ኃላፊዎች ባረጋገጡት መሠረት፡-

-    አዲስ ከተማ 3 ተወካዮችን

-    ዐድዋ 4 ተወካዮችን

-    አዳማ 3 ተወካዮችን

በድምሩ 4 ተወካዮን ከኮታ በላይ እንዲሳተፉ መደረጉ ብቻውን ጉባኤውን ሕገ ወጥ ያስብለዋል።

ሠ. አቶ አሸናፊ መንግስቱ የተባሉ ግለሰብ በተራ ቁጥር 18 ላይ የአዲስ ከተማ ወወክማ ማሠልጠኛ  ማዕከልን በተራ ቁጥር 24 ላይ ደግሞ የዑራኤል ወወክማን በመወከል (ያውም በአንዲት ገጽ ላይ) ሁለት ጊዜ ፈርመው እንደ ሁለት ሰው ሆነው ተቆጥረው ተሳትፈዋል። (ያሰፈሯቸው ፊርማዎች ተመሳሳይ ስለሆኑ ከተካደ በፎርንሲክ ሊጣራ ይችላል) እኝህ ግለሰብ የዋናው ወወክማ ቋሚ ሠራተኛ ከመሆናቸው አንጻር የጠቅላላ ጉባዔ አባል እንደሆኑ በማስመሰል ያውም በሁለት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ስም ፈርመው መገኘታቸው የተፈፀመውን የሕግ ጥሰት ኤጀንሲው እየተረዳ ጉባዔው ሕጋዊ ነው ብሎ አይኑን ጨፍኖ መከራከሩ እና የጉባኤውን ውጤት ማጽደቁ ተገቢም ሕጋዊም አይደለም። በዚህ መልኩ ሠነዱን እንዲዘጋጅ ያደረገው አካል፣ ግለሰቡና የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች ጭምር በተናጠልና በጋራ ከመጠየቅ አይድኑም።

ረ. እንደ ኤጀንሲው ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማረጋገጫ የኢትዮጵያ ወወክማ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ቁጥር 20 ሆኖ ሳለ እና በአንደኝነት የተመረጡት ያገኙት ድምጽ 22 መሆኑ ሲታይ ምርጫው በምን ሥርዓት እንደተከናወነ ወይም ዋጋ የሌላቸው ድምፆች ሁሉ ተቆጥረዋል ማለት እንደ ስህተት ሊቆጠር አይችልም።

ሰ. ድምጽ በተመዘገበበት ሰነድ ላይ እንዲወዳደሩ ከተደረጉት ዕጩዎች መካከል በማህበሩ 70ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በሙያቸው ብቻ የበጎ ፈቃድ የነፃ አገልግሎት በማበርከት ላይ የነበሩትን ጨምሮ በጠቅላላ ጉባዔ የተሳታፊዎች የስም ዝርዝር ላይ ያልተመዘገቡና የማህበሩ አባል ያልሆኑ 10 ሰዎች ለምርጫ እንዲወዳደሩ መደረጉና ከመካከላቸውም አራቱ የተመረጡበት ሁኔታ መኖሩ ህገ ወጥ ምርጫ መከናወኑን በግልጽ ያሳያል።

ሸ. በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ቀድሞ በተከናወነ ስብሰባ ጉባዔውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ በተመረጡት በፕሮፌሰር አለማየሁ ያልተጠራ ጉባኤ መሆኑ እንደተገለጸ ጥሪው ተላልፏል ቢባል እንኳን በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 16 (5) ስር እንደተገለፀው መደበኛ ስብሰባ ከ15 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ የስብሰባውን ዝርዝር ጉዳይ፣ ቦታውናና ቀኑን በመግለጽ አባላት እንዲያውቁት እንደሚደረግ የሚያዝ መሆኑን የኤጀንሲው ኃላፊዎች እያወቁ  በ17 ቀናት ውስጥ ጥሪው ተላልፏል ማለታቸው ሕዝብን ከማደናገር በዘለለ የጉዳዩን ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ አይደለም።

ቀ. ዶ/ር ፀጋዬ በርሄ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚያሳየው የቀድሞ የቦርድ አመራር ቅሬታ ለኤጀንሲው ደብዳቤ ጽፈን እንዲያጣራ ጠይቀን እያለን ይህን ወደ ጎን በማት እውቅና መስጠቱ ሕጋዊ አይደለም የሚል እና ግለሰቦቹ ግን እናንተ ብትከሱንም ምንም አላመጣችሁም ማለታቸውን በመጥቀስ እንዲሁም በስብሰባው ላይ ተነስቶ አነጋጋሪ ሆኖ የነበረው አቶ ይርጋ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነህ ከመቀሌ እየተመላለስክ ትራንስፖርት እና አበል እየተከፈለህ ወወክማን ልታስተዳድረው አትችልም የሚል የነበረ ቢሆንም፣ የኤጀንሲው ኃላፊዎች ይህን ወደ ጎን በማለት ያልተጠየቁትን እና የመረጡትን ብቻ ቀንጭበው በመውሰድ የሰጡት መግለጫ እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ በነባሩ ቦርድ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያልፈለጉ መሆኑን ከተሰጠው መግለጫ ለመረዳት ይቻላል።

በ. በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 7 (9) ስር አዲሶቹ ተመራጮች 30 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በአስመራጭ ኮሚቴው አረካካቢነት ስራቸውን ተረክበው እንደሚቀጥሉ ተደንግጎ እያለ የኤጀንሲው የስራ ኃላፊ ንብረቱም ሆነ ጽ/ቤቱ በሥራ አስኪያጁ እጅ የሚገኝ በመሆኑ የሚረካከቡት አንዳችም ነገር የለም ርክክብም አያስፈልግም ሲሉ የሰጡት መግለጫ ስራቸውን በሕግ ሳይሆን እንደሁኔታው የሚመሩ መሆኑን ያሳያል።

ሌላው የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በጉባዔው ላይ እንዳልተገኙ እየገለፁ በሌላ በኩል ደግሞ እንደተገኙ ወይም ሕጋዊ ሠነድ ተሟልቶ እንደቀረበላቸው በማስመሰል የሰጡት መግለጫ ሕጋዊ መሠረት የለውም።

ከዑራኤል ወወክማ ታግደዋል የተባሉት አቶ ስብሃት የአራት ኪሎ ወወክማ አባል እንደነበሩ በግልፅ የሚታወቅ ሲሆን በህገ ማህበሩ መሰረት የትኛው ጠቅላላ ጉባኤ እንዳገዳቸው መረጃ አልቀረበም። በአንጻሩ ግን ግለሰቡ ለ70ኛ ዓመት የወወክመ ክብረ በዓል ዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴ አባልና የቴክኒክ ኮሚቴ ጸሐፊ በመሆን የአራት ኪሎ ወወክማን ወክለው እንዲሰሩ በብሔራዊ ማህበሩ የተጻፉ ደብዳቤዎችን አቅርበው ተመልክተናል። ይህንንም ሕጋዊ ሰነድ ለጋዜጣ ዝግጅት ክፍሉ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርገው አቅርበናል።

በተጨማሪም የኤጀንሲው ኃላፊ የአቶ ስብሐትን የዑራኤል ተወካይ አለመሆን በመግለጽ “በእኛ እጅ በሚገኘው ሰነድ ላይ ለዑራኤል የተወከሉት አቶ ኤፍሬም ለማ ናቸው” በማለት ለማረጋገጥ የሞከሩ ቢሆንም ቀደም ሲል ለደብረ ማርቆስ ያቀረቧቸው ዕጩ አቶ አሰፋ ከበደ ከዕጩነት ወጥተው በአቶ ኤፍሬም ለማ እንዲተኩላቸው ባቀረቡት መሠረት ተተክተዋል በሚል የተሰጠ ድምጽ ለማሳየት በተቀመጠው የጋዜጣው ሠንጠረዥ ላይ አረጋግጠው ይታያል። ታዲያ እውነቱ የቱ ነው ብሎ መቀበል ይቻላል? ይህንን ለሕዝብ ፍርደ ትተነዋል።

ሌላው በሕገ መንግስቱ ከወንጀለኛ መቅጫና ከንግድ ሕጉ በስተቀር ሌሎች ሕጎች ተሽረዋል በማለት የቀረበውንም በተመለከተ የሀገሪቷ የፍትሐ ብሔር ሕግና ሌሎች ነባር ሕጎች የላትም እንደማለት የሚያስቆጥር ስለሆነ አባባሉን በመታዘብ ፍርዱን ለሕዝብ የምንተወው ይሆናል።

-    በመጨረሻም በቃለ መጠይቁ ላይ የኤጀንሲውን የሥራ ኃላፊ አንድ በዕድሜ የበለፀጉ የማህበሩ የቀድሞ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩ አካዳሚሺያን ዶ/ር ግለሰብን አንተ እያሉ መጥራት ከአንድ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊ የሚጠበቅ ነውን?

-    በአዋጁ አንቀጽ 60 (2) ላይ ማንኛውም የማህበር አባል ማለትም አንድ አባል እንኳን ቢሆን ቅሬታውን ለኤጀንሲው ለማቅረብ መብት እንዳለው በግልጽ ደንግጎ እያለ ከ20 በላይ አባላት ተፈራርመው ያቀረቡትን አቤቱታ ለማደናገር ሲባል የጠቅላላ ጉባዔ አባላት አይደሉም በሚል በማጣጣል መገለፁ ተገቢም ህጋዊም አይደለም።

-    እንዲሁም የኤጀንሲው ክትትል ዳይሬክቶሬት የቡድን መሪ በማጠቃለያቸው ላይ ስህተት ካለ ለማረም የሚያስችል ሌላ ጉባኤ ሊጠራ እንደሚችል በመጥቀስ የተሻለ ምላሻቸውን ያቀረቡ ቢሆንም የድጋፍና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ግን በተቃራኒው የሰጡት ምላሽ አስተማሪነት የሌለው፣ እልህ የተቀላቀለበት እና ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ሆኖ አግኝተነዋል።

በመሆኑም በአዋጁ መሠረት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ከዚያም ካለፈ የኤጀንሲው ቦርድ ለተነሳው ውዝግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕጋዊና ተገቢ ምላሽ በመስጠት የወወክማን ህልውና እንዲታደጉልን በአክብሮት እየጠየቅን ለተጨማሪ ማብራሪያና ካስፈለገም በተጠራን ጊዜ ለውይይት ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን።

         ቅሬታ አቅራቢ የወወክማ አባላት   

 

-    የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል

ኢብሳ ነመራ

የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ  ግጭት  ሊቀሰቅስ ይችላል  ብሎ  የገመተውን  ማንኛውንም  ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ሲወረውር ቆይቷል። የእርስ  በርስ  ግጭት  በመቀስቀስ ሃገሪቱን  የማተራመስ ህልሙ ዛሬ፣  ዘንድሮ … በወረወረው አጀንዳ ባይሳካ ነገ፣ ከረሞ  ሌላ የግጭት  አጀንዳ  ከመፈለግ  እንደማይቦዝን  የእስከዛሬ ባህሪው በግልጽ አሳይቶናል። በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራው የኤርትራ መንግስት እስካለ ደረስ ይህ ይቀጥላል። እስሩ የተሸሸጉት የትምክህትና የጠባብነት ህልማቸው ካልተሳካ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ቡድኖችም የዓለማችንን ብቸኛዋ ህገመንግስት አልቦና ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ለሆነ ጊዜ አንድም ምርጫ ተካሂዶባት የማታውቀው የኤርትራ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ያተራምሳል ብሎ ያመነበትን  አጀንዳ ሲሰጧቸው ተቀብለው ወደ ሃገር ቤት ለማስረግ ከመፍጨርጨር እንዳይቦዝኑም ግልጽ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን የማተራመስ ተልዕኳቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙት ማህበራዊ ሚዲያዎችን  ነው።

በቁጥር ከአስር በላይ የሚሆኑት በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራው የኤርትራ መንግስት የከፈታቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ያተራምሳል በሚል ስሌት  ተዘጋጅቶ  የሚሰጣቸውን  ማንኛውንም አጀንዳ ሳይሰለቹ በተደጋጋሚ፤   ምናልባትም በየሰአቱ የተለያየ አደናጋሪ ገጽታ እየሰጡ ያሰራጫሉ። የኤርትራ  መንግስት ኢትዮጵያን የማተራመስ  ጥረት ባለፉት ሁለት  አስርት ዓመታት  ሲካሄድ  የቆየ ቢሆንም፣ በተለይ በኢትዮጵያ የማህበራዊ  ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር  እጅግ  በጨመረባቸው ያለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት እጅግ  ተጋግሏል።

ሰሞኑን  የኤርትራ መንግስት ማህበራዊ  ሚዲያዎች አንድ የግጭት አጀንዳ ሙጭጭ ብለው ይዘዋል። ይህም አንድ የኢትዮጵያን ክልላዊ መንግስታት አወቃቀር  የሚያመለክት  ካርታ ነው። ይህ ካርታ  የትግራይ ክልል፣ በምዕራብ የሃገሪቱ አቅጣጫ  የሱዳንን  ድንበር  ይዞ የምዕራብ  አማራን፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝን፣ የምዕራብ  ኦሮሚያንና የጋምቤላን ክልሎች አካቶ እስከደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች   ክልል  ድረስ ይዘልቃል።  ከደቡብ ህዝቦች አንድም መሬት አልነካም።  የትግራይ ክልል የተባለው የደቡብ  ብ..  ክልል በስተሰሜን ምእራብ ጫፍ  የሚዛን  ተፈሪ፣  በበቃ ለም መሬቶችን  ሳይነካ  ቆሟል። ከላይ  ያሉትን  መሬቶች  በሙሉ ጨረጋግዶ እዚያ  ጋር  ለምን  እንደቆመ  ካርታውን  የሰሩት ሰዎች  ብቻ ናቸው የሚያውቁት፤ ይህ  ካርታ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ  ኮርፖሬሽን  የቴሌቪዥን  ዜና  ሽፋን  ሆኖ  ቀርቧል የሚል ወሬ  ሰምቻለሁ። ካርታውን ሽፋን አድርጎ የቀረበውን ዜና  ሰምቼዋለሁ፤ ኢትዮጵያ በትግራይ  ክልል በተከናወነው  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለዓለም አቀፍ  ሽልማት ታጨች  የሚል ዜና ነው። የቀረበውን ካርታ ግን ልብ ብዬ አልተመለከትኩትም። እርግጥ ብመለከተውም ብዙ ዋጋ አልሰጠውም። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የሚያክል የሃገሪቱ አንጋፋ የቴሌቪዥን ጣቢያ በህገመንግስት ከተረጋገጠው የኢፌዴሪ ክልላዊ መንግስታት ካርታ የተለየ ካርታ ለተመልካች ማቅረቡ ግን ያስቆጣል። የዚህ አይነቱን ዝርክርክ አሰራር እንደቀላል ስህተት መቀበል ትንሽ ይከብዳል። ቴሌቪዥን ጣቢያው በስህተት ለቀረበው የኢትዮጵያ ካርታ ይቅርታ መጠየቁን ሰምቻለሁ፤ ይቅርታው መቼ በምን አይነት አኳኋን እንደቀረበ ግን አላውቅም፤ እኔ አልሰማሁትም። ያም ሆነ ይህ፤ ኢቢሲ በቴሌቪዥን ስርጭቱ ሀሰተኛውን የኢትዮጵያ ካርታ አቅርቧል፤ ለዚህም ይቅርታ ጠይቋል ብለን እንውሰድ።

አንድ መገናኛ ብዙሃን ባስተላለፈው መረጃ ላይ ስህተት ሲገኝ ለስህተቱ በይፋ ይቅርታ መጠየቁ ተገቢ ነው። እናም የኢቢሲ ቴሌቪዥን ይቅርታ ሊደረግለት ይገባ ይሆናል። ቴሌቪዥን ጣቢያው ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ስህተት ፈጽሞ የነበረ በመሆኑ አሁንም ላለመድገሙ ግን ዋስትና የለንም። ምናልባት ቴሌቪዥን ጣቢያው የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ሰርጎ ገብ ዘልቆት እንዳይሆን ያሰጋናል። ከኢቢሲ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ጀምሮ፣ በየደረጃው ያሉ አዘጋጆች ለኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ  አጀንዳ አስፈፃሚ ላለመሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ጥፋት እየደገሙ፣ ሁሌም በይቅርታ እየታለፉ መዝለቅ የሚችሉ አይመስለኝም። የፈጸሙት ስህተት ሊያስከትል በሚችለው ስጋት ልክ ሊጠየቁ ይገባል። በሃሰተኛ መረጃ ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት የተከለከለው ለግል መገናኛ ብዙሃን ብቻ አይደለምና፤ ይህ የትግራይን ክልል በምእራብ አቅጣጫ በቀጭኑ እስከ  ደቡብ ክልል ስቦ የለጠጠ ካርታ በህገመንግስት ተቀባይነት ያገኘውን የኢፌዴሪ የክልሎች የወሰን አከላለል  አይወክልም። የትግራይ ክልላዊ መንግስትም ይህን ካርታ ካርታዬ ብሎ አያውቅም። ተጠቅሞበትም አያውቅም። ይህን ካርታ የሰራ አካል የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በርስ ለማተራመስ ያስችላል ያለውን ማንኛውንም ጉዳይ፣ ብስል ከጥሬ ሳይለይ እየለቃቀመ የሚያሰራጭ አካል ከመሆን የተለየ ሊሆን አይችልም። ይህ ካልሆነ ደግሞ እብድ ነው።

ይህ ካርታ በድረ ገጾች ላይ ተለጥፎ ሊሆን ይችላል። በድረ ገጾች ላይ መለጠፉ፣ የለጠፉትን አካላት ማንነት አይለውጠውም። ድረ ገጽ ላይ መለጠፉ ብቻም ተቀባይነት እንዲኖረው አያደርገውም። ማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾችን ጨምሮ ማንም የፈለገውን የሚያወራበትና እስካሁን ባለው አሰራር ከተጠያቂነት ስርአት ያፈነገጠ ሚዲያ ነው። ማንም የፈለገውን ጉዳይ ለፈለገው ዓላማ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሊለጥፍ ይችላል። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚቀርበውን ዝባዝንኬ አጣርቶ ትክክለኛውን መወሰድ የተጠቃሚው አካል ኃላፊነት ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፈን በሙሉ የሚያጋብስ ግለሰብ እንደማህበራዊ ሚዲያው የተዘባረቀ ከመሆን አያመልጥም።

ሰሞኑን የኤርትራ መንግስት ማህበራዊ ሚዲያዎች  የትግራይ ክልል መሬታችሁን ሊወስድ ነው ብለው ያስተላለፉትና እያስተላለፉት የሚገኙት ካርታ በእርግጠኝነት በኤርትራ መንግስት እና/ወይም በባለሟሎቹ የተሰራ ነው። ዓላማውም የትግራይን ህዝብ ከተቀሩት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ማጋጨት ነው። የተቀሩት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲነሱ የመቀሰቀስ እኩይ ዓላማ ያዘለ ነው።

ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት የምትከተል ሃገር ነች። የፌደራል መንግስቱ በብሄራዊ ማንነትና በህዝብ አሰፋፈር ላይ ተመስርቶ የተዋቀሩ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ዘጠኝ ክልሎች አሉት። እነዚህ በኢፌዴሪ ህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩት ክልሎች -   አፋር፤ አማራ፤ አሮሚያ፤ ሶማሌ (በኋላ በክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ  ሶማሌ ተብሏል)፤ ቤኒሻንጉል/ጉምዝ፤ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የጋምቤላ ህዝቦችና የሃራሪ ህዝብ ክልሎች ናቸው።

ክልሎቹ የተዋቀሩት፣ በመልከአምድር አይደለም፤ በዘፈቀደም አይደለም፤  በአንድ አካል ፍላጎትም አይደለም። ከዚህ ይልቅ በህገመንግስቱ አንቀጽ 46  ንኡስ አንቀጽ አንድ መሰረት ነው። ይህ አንቀጽ ክልሎች የተዋቀሩት በህዝብ አሰፋፋር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍቃድ ላይ በመመስረት ነው ይላል። እናም ማንም ተነስቶ የፌደራል መንግስቱም ጭምር የክልሎችን ወሰን ሊቀይር አይችልም። የፌደራሉ መንግስት ህገመንግስት (የኢፌዴሪ ህገመንግስት) የፌደራሉን ክልሎች ማንነት የሚገልጽ ቢሆንም፣ የየትኛው ክልል ወሰን የት ድረስ እንደሚዘልቅ፣ የትኛው በየትኛው አቅጣጫ ከማን ጋር እንደሚዋሰን የሚገልጸው ነገር የለም። ይህ የክልሎች ጉዳይ ነው። ድንበራቸውን የወሰኑት ክልሎች ናቸው። የፌደራል መንግስቱ በክለሎች ነው የተመሰረተው። የፌደራል መንግስቱ ስልጣን በሙሉ ከክልሎች የመነጨ ነው።

በህገመንግስቱ አንቀጽ 50 መሰረት የፌደራል መንግስትና ክልሎች የየራሳቸው የህግ አውጪነት፣ የህግ አስፈፃሚነትና የዳኝነት ስልጣን አላቸው። የክልል ከፍተኛ የስልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለሚወክለው ክልል ህዝብ ነው። የክልል ምክር ቤት የክልሉ የህግ አውጪ አካል ነው። የኤፌዴሪን ህገመንግስት መሰረት በማድረግ የክልል ህገመንግስት ያዘጋጃል፣ ያጸድቃል፤ ያሻሽላል። የክለሎች ድንበርና አወሳኞች የሚገለጹት በክልል ህገመንግስት ላይ ነው። እናም የትግራይም፣ የአማራም፣ የቤኒሻንጉልም፣ የኦሮሚያም፣ የጋምቤላም፣ የደቡብ ብ.ብ.ህ.ም ክልላዊ መንግስታት ህገመንግስት ወሰን የኤርትራ መንግስት ሰሞኑን ያሰራጨውን ካርታ የሚመለከት ወሰን የላቸውም።

የትግራይ ክልላዊ ህገመንግስት፣ ክልሉ በሰሜን ከኤርትራ፣ በምስራቅ ከአፋር፣ በደቡብና ደቡብ ምእራብ ከአማራ፣ በምእራብ ከሱዳን እንደሚዋሰን ነው የሚገልጸው። የአማራ ክልላዊ ህገመንግስት ደግሞ በስተሰሜን ከትግራይ፣ በምስራቅ ከአፋር፣ በደቡብ ከኦሮሚያ፣ በምእራብ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ሱዳን ጋር እንደሚዋሰን ነው የሚገልጸው። እውነታው ይህ ከሆነ የአማራ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የኦሮሚያ፣ የጋምቤላ ክልሎች በስተምእራብ የሚዋሰኑት፣ የደቡብ ብ.ብ.ህ. ክልል ደግሞ በሰሜን ምስራቅ ጫፉ የሚዋሰነው የትግራይ ወሰን ከየት የመጣ ነው? ይህ በካርታው ውስጥ የተካተቱ ክልሎች በህገመንግስታቸው ላይ ያላሰፈሩት ካርታ በኤርትራ መንግስት የተሳለ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ይህ የትግራይ ህዝብና የክልሉ መንግስት የማያውቁት፣ በህገመንግስታቸውም ላይ ያላሰፈሩት፣ የፌደራል መንግስቱ አካል ሲሆኑም ያላሳወቁት ካርታ በኤርትራ መንግስት ተዘጋጅቶ የተሰራጨበት ዓላማ ግልጽ ነው። የትግራይን ህዝብ ነጥሎ ከሌሎች ጋር ማጋጨት፤ በቃ፤ የማጋጨት ሴራ መጠንሰሱና ግጭት ለመቀስቀስ መሞከሩ ግን በዚህ አያበቃም። በአማራና በኦሮሚያ፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአፋርና በኦሮሚያ፣ በአፋርና የኢትዮ ሶማሌ ወዘተ. መካከልም ይቀጥላል። እናም እዚሁ ላይ በቃህ ሊባል ይገባል።

የኤርትራ መንግስት ብቻውን ኢትዮጵያን  የማተራመስ ዓላማውን የመስፈጸም አቅም የለውም። ይህን ለማድረግ መሞከርም አይችልም። የማተራመስ ሙከራውን የሚያደርገው በስሩ ባደሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለአማራ፣ ለኦሮሞ … ህዝብ ተቆርቋሪ መስለው የሚቀርቡ የበግ ለምድ የለበሱ ቀበሮ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን አማካኝነት ነው። የተጠቀሰውን የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ይጠቅም ይሆናል በሚል ስሌት የሳለውን ካርታ እየለጠፉ ግጭት ለመቀስቀስ የሚንፈራገጡት መረጃ ዶት ኮም፣ ዘሃበሻ፣ ኢትዮጵያን ዲጄ የተሰኙት ማህበራዊ ሚዲያዎች በቀጥታ በኤርትራ መንግስት ትእዛዝ የሚሰሩ ናቸው።

በሌላ በኩል የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች  ኢትዮጵያውያንን እርስ  በርስ የማጋጨት ሴራ ሊሳካ የሚችለው ኢትዮጵያውያን  በኤርትራ ማህበራዊ ሚዲያዎች  የሚሰራጨውን የፈጠራ  ወሬ እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ ነው። የወሬው ዓላማ የእርስ በርስ ግጭት  በመፍጠር ሃገሪቱን ዳግም ሃገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ ማፍረስ መሆኑን ማወቅ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ነው። የገዛ ቤቱን በእጁ የሚያፈርስ ሞኝ ላለመሆን መጠንቀቅ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ነው። በተለይ በኢፌዴሪ ህገመንግስት ላይ፣ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት ላይ እንዲሁም በክልሎች ስልጣንና አሰራር ላይ ግንዛቤ የሌላቸው ወጣቶች የውዥንብሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ማንቃት ከሁሉም ነፍስ ያወቀ ዜጋ ይጠበቃል። በአጠቃላይ፤ ሰሞኑን በኤርትራ ማህበራዊ ሚያዎች እየተሰራጨ ያለው ካርታ በኤርትራ መንግስት የተዘጋጀ ኢትዮጵያውያንን የማተራመስ ዓላማ ያለው መሆኑ መታወቅ አለበት፤ ንቁ፤

 

 

ሲሳይ መንግስቴ

 

ስለጎንደርና አካባቢው ሲነሳ በርካታ ታሪካዊ ሁኔታዎች አብረው መታወሳቸው አይቀርም፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛውና ዋነኛው ጉዳይ ጎንደር የቋረኛው ካሳ (የኋለኛው አጼ ቴውድሮስ አገር መሆኑ ሲሆን፣ የፋሲል ግንብ፣ የአጼ ዮሓንስ በመተማ ዮሓንስ ከድርቡሾች ጋር በቆራጥነት ሲዋጉ መስዋዕት መሆን እና የመሳሰሉት ታሪካዊ ክስተቶችም ግምት ውስጥ መግባተቸው የግድ ነው። ከዛም አልፎ የደጃች ውቤና የራስ አሊ ፍጥጫ በመጨረሻም የደጃች ካሳ (አጼ ቴውድሮስ) አሸናፊነትን ተከትሎ ጃን አሞራ ውስጥ በምትገኘው ደረስጌ ማሪያም ዘውድ ደፍተው የመንገሳቸው ሁኔታ ትውስ ማለቱ አይቀርም።


ለመንደርደሪያ ይህን ያህል ካልሁ በኋላ በርዕሱ ላይ ወደ ተጠቀሰው ወቅታዊ ጉዳይ ልመለስና የተወሰኑ ሀሳቦችን አንስቼ ያገኘሁትን መረጃ ለተደራሲያን ላካፍል፣ ምክንያቱም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአጠቃላይና ለአካባቢው ቅርበት እንዳለው ሰው በተለይ ጉዳዩ እኔንም ያገባኛል ብየ ስለማምን ምንድነው ነገሩ በማለት የጎንደርና አከካባቢውን ሰው ለመጠየቅ ሞክሬ ነበርና ነው።


የቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሀገር የአሁኖቹ የደቡብና የሰሜን ጎንደር አስተዳደር አካባቢዎች በቀደመው ዘመን ማለትም ከአንድ መቶ አምሳ አመታት በፊት ከአጼ ቴዎድሮስ ወደ ስልጣን መምጣት ቀደም ብሎ በዘመነ መሳፍንት መሆኑ ነው በሶስት የአስተዳደር አካባቢዎች የተከፋፈለ እንደነበር ይታወቃል። እነዚህም ደንንያና አካባቢው በደጃች ማሩ ይገዛ ነበር፣ ቤጌምድር በመባል የሚታወቀውና በአሁኑ ወቅት በዋነኛነት ደቡብ ጎንደር ተብሎ የሚጠራው በራስ አሊ ይተዳደር ነበር።


እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ሽሬና አካባቢውን ጨምሮ የሰሜን አውራጃ (አሁን ላይ በአዲሱ አደረጃጀት ሰሜን ጎንደር የተባለው) በደጃች ውቤ ይተዳደር እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። የኋላ ኋላ ደግሞ አጼ ኃይለ ስላሴ የተወሰኑ አውጃዎችን ወደ አንድ ማዕከል አሰበስበው ጠቅላይ ግዛት ሲያቋቁሙ ከላይ የተጠቀሱት አካበቢዎች የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት በሚል ሰያሜ አንድ ላይ ሆኑ። ደርግ ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት መጀመሪያ ላይ ስያሜውን በመቀየር የጎንደር ክፍለ ሀገር ከማለቱም በላይ በመጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ባወጣው የኢህዴሪ ህገ-መንግስት የጎንደር ክፍለ ሀገርን ሰሜንና ደቡብ ብሎ ለሁለት የከፈለው ሲሆን ብአዴን/ኢህአዴግም ይህንን አደረጃጀት ላለፉት 25 አመታት ባለበት ሁኔታ አስቀጥሎት ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራ ክልል መንግስትና ገዥው ፓርቲ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት በእጅጉ ስላሳሰበው ይመስላል ለሶስት ከፋፍሎ ለማስተዳደር ጥናት ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሰኔ ወር የመጨረሻ ውሳኔውን በማስተላለፍ የሰው ሀይል ምደባውን በይፋ ሲያሳውቅ የድጋፍና የተቃውሞ ድምጾች እዚህም እዚያም መሰማት ጀመሩ።


እኔም ታዲያ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርሁት ከአካባቢው ህዝብ ጋር ካለኝ ጥብቅ የሆነ ትስስር የተነሳና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የአካባቢው ለሶስት መከፈል ዋነኛ ምክንያት ምን ይሆን? የዚህ የሀሳብ ፍጭት መንስኤስ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጥም ይኸ ውሳኔ በክልሉ መንግስት ከመወሰኑ በፊት የህዝቡ ሀሳብ ግምት ውስጥ ገብቶ ነበርን? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ሀሳቦች አንስቼ ያለኝን ቅርበት በመጠቀም ጭምር ከተለያዩ አካላት መረጃ ለማሰባሰብ ሞከርሁ፣ በዚህም መሰረት ያረጋገጥሁት ነገር ቢኖር የሚከተለውው እውነት ነው፡


1. የሰሜን ጎንደር አስተዳደር አካባቢ በህዝብ ብዛትም ሆነ በቆዳ ስፋት ከክልሉ ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ትልቁ ዞን በመሆኑ (ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ የሚኖርበት ስለሆነና ቋራና መተማ ወረዳዎች ብቻ ስፋታቸው የአንድ መለስተኛ ዞንን ስለሚያክል)፣


2. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካባቢው ባለው የተፈጥሮ ጸጋ ምክንያት የክልሉ ብቻ ሳይሆን የፌዴራሉ መንግስት የስበት ማዕከል እየሆነ በመምጣቱ (በተለይም በግብርናው መስክ ሰፊና ድንግል መሬት ያለው መሆኑና ለእንስሳት እርባታም ሆነ ለደን ልማት በእጅጉ የተመቼ አካባቢ ስለሆነ)፣


3. አካባቢው በአምስት አግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች የሚከፈልና ለተለያዩ ሰብሎች (ለገበያም ይሁን ለምግብ የሚሆኑ) በእጅጉ የተመቼ ቢሆንም በመንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት ባለመልማቱ ምክንያት፣


4. አካባቢው ከሱዳን ጋር በቀጥታ ከመዋሰኑ ጋር ተያይዞ የንግድና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነቱ ከመቸውም ጊዜ በላይ እያደገ የመጣበት ሁኔታ መፈጠሩ (ለሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ የደረቅ ወደብ አገልግሎት እንዲኖር የማድረግ አስፈላጊነት የግድ የሚልበት ሁኔታ መከሰቱ)፣


5. አካባቢው ከሱዳን ጋር በቀጥታ መዋሰኑ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ በቅርብ ርቀት ላይ ስለሚገኝ (ክልሎች በ1984 ዓ.ም እንደ አዲስ ከመዋቀራቸው በፊት አካባቢው ከኤርትራ ጋር በቀጥታ ይዋሰን እንደነበር ይታወቃል) የጸጥታ ችግሩም ያን የህል የከፋ በመሆኑ የክልሉን ከፍተኛ አመራር የቅርብ ድጋፍና ክትትል ማግኘት ስለሚገባው እና


6. የበርካታ ወረዳዎች ከጎንደር ከተማ በእጅጉ ርቀው መገኘታቸው (ለምሳሌ ቋራ፣ መተማ፣ አዲአርቃይ፣ በየዳ፣ ጃን አሞራ ወዘተ) ነዋሪዎች ፍትህ በመሻትም ሆነ በዞን ደረጃ ሊያገኟቸው የሚገቧቸውን አገልግሎቶች ለማግኘት በአማካይ ከሁለት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ የግድ ስለሚላቸው ከፍተኛ እንግልትና ወጭ ያስከትልባቸው የነበረ በመሆኑ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ በማስቀረት በቅርቡ አገልግሎቱን ለማሟለት የግድ ስለሚል ነው አካባቢው ለሶስት እንዲከፈል የተደረገው የሚሉት ምክንያቶች በማብራሪያነት መቅረባቸውን አስተውያለሁ።


ታዲያ ይህ ሲሆን የህዝቡ፣ በየደረጃው የሚገኙት የአመራር አካላትና የመንግስት ሰራተኞች ተሳትፎስ ምን ይመስል ነበር? እና ሀሳባቸውስ በምን መልኩ ተስተናገደ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመረጃ ሰጭዎቼ አንስቼላቸው የሰጡት መልስ ሲጨመቅ ደግሞ የሚከተለውን የሚመስል ሆኖ አገኘሁት፣ በዚህም መሰረት፡


ሀ. በዞኑ ውስጥ ከሚገኙት ከ520 በላይ የቀበሌ ነዋሪዎችን ለማወያየት ሲሞከር አላፋና ጣቁሳ አካባቢ የሚገኙ 7 ቀበሌዎች ብቻ የተለየ ሀሳብ አንስተው የነበረ ከመሆኑ ውጭ ሌሎቹ ግን እንዳውም ጉዳዩ የዘገየ ከመሆኑ ውጭ ሀሳቡን እንደግፈለን በሚል መልኩ በመስማማታቸው፣


ለ. ከ500 በላይ እንደሆነ ከሚገመተው የወረዳና የዞን አመራር ውስጥ ከተወሰኑት አባላት በስተቀር አሁንም አብዛኛው አመራር ሀሳቡን የደገፈውና ለተግባራዊነቱም በግንባር ቀደምነት ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን በማረጋገጡ፣


ሐ. የዞኑ የመንግስት ሰራተኛ በተወያየበት ወቅት የተወሰኑ ግለሰቦች ይኸ ውሳኔ በቅርቡ የተከሰተውንና አሁንም ድረስ ብቅ ጥልቅ በማለት የክልሉን መንግስት ረፍት የነሳውን የህዝብ ተቃውሞ ለማዳከምና የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅጣጫ ለማስቀየር ስለተፈለገ ነው የሚል ሀሳብ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም አብዛኛው ግን የስምምነት ሀሳቡን በመግለጹ እና


መ. የሁሉም ወረዳ ምክር ቤቶች በመደበኛ ስብሰባቸው ላይ ጉዳዩን በአጀንዳነት ይዘው ከተወያዩ በኋላ በአብላጫ ድምጽ ሀሳቡን ደግፈው መወሰናቸው በመረጋገጡ ምክንያት የክልሉ መንግስት አስተዳደር ምክር ቤት የሰሜን ጎንደር አካባቢ ከሶስት ተከፍሎ እንዲደራጅ ወስኖ ካለፈው ሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአዳዲሶቹ ዞኖች የሰው ሀይል እንዲመደብ አድርጓል። እንግዲህ እውነታው እንደዚህ ከሆነ የሰሞኑ ክርክር ጉንጭ አልፋ ብቻ ሳይሆን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ መሆኑ ነው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የቅማንት የማንነትና የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄና የክልሉ መንግስት ምላሽ ነው። ቅማነቶች የተለየ ማንነት እንዳላቸውና ይህም የተለየ ማንነታቸው ህጋዊ እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት ከ1984/5 ዓ.ም ጀምሮ እንደነበር አስታውሳለሁ።


ይህም ሆኖ ጉዳዩ የአብዛኛውን የቅማንት ህዝብ ብቻ ሳይሆን የልሂቃኑን ጠንካራ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ጥያቄው ለበርካታ አመታት ሲነሳና ሲወድቅ ለመቆየት ተገዷል። ሆኖም በ1999 ዓ.ም በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን አማካኝነት በተካሄው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሔረሰቦች ዝርዝር ውስጥ የቅማንት ብሔረሰብ እንዲወጣ ተደርጎ በመቅረቡ ሳቢያ የብሔረሰቡን ምሁራን በእጅጉ አስቆጥቶ በተደራጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ አደረጋቸውና የአማራ ክልል አመራርን እረፍት አሳጥቶ ሰነበተ።


ከዛም አልፎ የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት ሰሜን ጎንደር ውስጥ በሚኖሩ አማሮችና ቅማንቶች መካከል ዘመናትን ያስቆጠረው መልካም ማህበረ-ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት በአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ ሻክሮ በሒደትም ወደ ግጭት አመራና የበርካታ ሰው ህይወት ከማጥፋቱም በላይ በአካባቢው ለተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል።


በመጨረሻም የክልሉ አመራር በእጅጉ ተገፍቶና ተላልጦም ጭምር በሒደት የቅማንትን ማንነት እውቅና ከመስጠት አልፎ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያደርግ አዋጅ እንዲያጸድቅ መገደዱ አልቀረም፣ ስለሆነም የቅማንት የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከሰሜን ጎንደር በሶስት መከፈል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው ቢሆንም በአካባቢው ለተፈጠረው አለመረጋጋት ግን የራሱን አስተዋጽኦ ማበረከቱ አልቀረም።


ተጠቃሎ ሲታይ የሰሜን ጎንደር አስተዳደር አካባቢ ለሶስት በመከፈሉ ምክንያት የጎንደርን ህዝብ አንድነት ሆን ብሎ ለማዳከም ነው የሚለው ሀሳብ ያን ያህል ውሀ የሚያነሳ የመከራከሪያ ነው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል፣ ምክንያቴ ደግሞ ከላይ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ ለማንሳት እንደሞከርሁት የጎንደር አካባቢ ቀደም ሲል ጀምሮ በተለያየ አደረጃጀት ሲከፈልና ሲጠቃለል የነበረ ቢሆንም ጎንደሬነትን ሸርሽሮ በፍጹም ሲያዳክመው አልታየምና ነው። በሌላ በኩል አሁን የተፈጠረውን የህዝብ ተቃውሞ ለማዳከምና አቅጣጫ ለማስቀየር ነው የሚለው ክርክርም ብዙ ርቀት የሚያስኬድ ሆኖ አላገኘሁትም።


ይህን ለማለቴም በቂ ምክንያት አለኝ፣ የህዝቡ ተቃውሞ መነሻም ሆነ መድረሻ የፍትህ እጦት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሙስና መስፋፋት እና የእኩል ተጠቃሚነት አለመኖር የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፣ እነዚህ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ደግሞ የአስተዳደር ድንበር በማካለል ብቻ የሚፈቱና የሚደፈቁ ባለመሆናቸው ምክንያት በየትኛውም የአስተዳደር አካባቢ የሚገኘው ህዝብ በአንድ ላይ ተቃውሞውን የመግለጽና እስከመጨረሻው የመግፋት ዕድሉ ሰፊ ነው፣ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ባለፈው አመት ጎንደር ላይ የተነሳው ተቃውሞ ሳይውል ሳያደር ጎጃም ውስጥ ገብቶ ምድር አንቀጥቅጥ የሆነ ሰልፍን መጋበዙ ነው።

 

·         በሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበ ፅሁፍ የተሰጠ ማስተባበያ

መልአከ ሰላም አባ ነአኩቶ ለአብ አያሌው

ሰንደቅ ጋዜጣ 13ኛ ዓመት ቁጥር 625 ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2009 ዓ.ም በገጽ 1 “ከሰማይ ወረደ በሚል ተደጋጋሚ የማታለል በደል የፈፀሙት የደብር አስተዳደሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ታገዱ” የሚለውና ዝርዝር ሃተታው በገጽ 12 ታትሞ ለንባብ የበቃው /የዋለው/ ጽሁፍ በመቃወም ማስተባበያ ማቅረብ።

የህትመቱ ዝርዝር ሁኔታ ሲታይ በስም የተጠቀስኩትን የቤተክርስቲያን አገልጋይ ስብእና እና ክብር ያጎደፈ እና የቤተክርስቲያኗንም ማንነት ሉአላዊነት ዝቅ ያደረገ የእምነቱ ተከታዮንም በአባቶቻቸው ላይ ያላቸውን አባታዊ እምነት እንዲያጡ በህግ በአግባብነት ተጣርቶ እኔም ባለጉዳዩ በአካል ቀርቤ በቃልም ሆነ በጽሁፍ መልስ ሰጥቼበት የእምነት ክህደት በሌለበት ጉዳይ በግል እኔን በሚጠሉ ተባብረው ሙሉ ዘመኔን ከኖርኩበት ከእናት ቤተክርስቲያኔ ስልጣናቸውን ተጠቅመውና መከታ አድርገው ከስራና ከደመወዝ ያፈናቀሉኝ ጥቂት ግለሰቦች /ቡድኖች/ ያቀረቡትን የሀሰት ጽሁፍ ተቀብሎ አየር ላይ እንዲውል እና ለንባብ እንዲበቃ መደረጉ እጅግ አሳዝኖኛል።

በመሰረቱ የመንግስትም ሆነ የግል ማንኛውም ሚዲያ እውነትን መሠረት በማድረግ የሀገሪቱን እና የህዝቦቿን ማህበራዊ እሴቶችን ልማት እና እድገት ሌሎችም እውነታ ያላቸው ጉዳዮች የሚገለጽበት እንጂ በህግ እና በእውነት ያልተረጋገጠ የአንድ ዜጋ ስብእና መልካም ስል የሚጎድፍበትን ሀሳብ ከአንድ ወገን ብቻ ተቀብሎ ማስተናገዱ የአንድ ህጋዊ ፈቃድ ያለው ጋዜጣ ስነምግባር መርህ ሊሆን አይገባውም።

ይሁን እና ከላይ በተገለጸው ገፆች ጋዜጣው የዘረዘራቸውን በመቃወም ማስተባበያ እንድሰጥባቸው የምፈልገው በዋናነት የማቀርባቸው ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

 

·         ታቦት ከሰማይ ወረደ በሚል እና በተደጋጋሚ አታለዋል አገላለጽ በተመለከተ

እኔ የተናገርኩት ለመሆኑ ማረጋገጫ ባይኖርም የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ስርዓት እንደሚደነግገው የታቦቱ ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን እና በሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ከሰማይ የወረደውን ታቦት ከእግዚአብሔር እጅ እንደተቀበለ በቅዱሰ መጽሐፍ የተመዘገበ ሲሆን በቤተክርስቲያን አስራር መሠረት

ሀ. ለስሜ መጉደፍ ምክንያት የተገለጸው ታቦት ወረደ የሚለው ጉዳይ በራሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሆህተ ጥበብ ጋዜጣ እና የሀገረ ስብከቱ ብሎግ ወይም ድረገጽ በጊዜ ሚዲያው ትክክለኝቱን ያረጋገጠ መሆኑን ማስረጃ በእጄ የሚገኝ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ማስገንዘብ እፈልጋለሁ።

ለ. በጊዜው በኃላፊነት የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳትም የታቦቱን መገኘት በመስማት፣ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ በመመስከር እና በማስተማር እንዳረጋገጡ በድምጽም ሆነ በምስል ማስረጃው በእጄ ያለው ማስረጃ ያስረዳል። ምክንያቱም ጉዳዩ ምስጢረ ቤተክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን በቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ በቤተክርስቲያን ተገቢውን ገለፃ ለህዝበ ክርስቲያኑ ከማድረግ በስተቀር ሌሎቹ እንዳሉት የተፈጸመ ስህተት የለም። እኔ እራሴ አምኜበት ህዝቡም እንዲያምንበት ስለ ታቦት የማስተምረው ሀዋርያ ሆኜ ሳለ ታቦቱን ለገንዘብ መሰብሰቢያ እንዳዋልኩት ቤተ ክርስቲያን እና ሀይማኖትን እንዳስነቀፍኩበት ምዕመናንን የሚያርቅ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ስነምግባር በተደጋጋሚ እንደፈጽምኩበት በአጣሪ ኮሚቴ የተረጋገጠ መስሎ የቀረበው ሀሳብ በእውነት ሚዛን ሲለካ ለአንድ ወገን እና ለግል ጥቅም የቆሙ ግለሰቦች ያደረጉት እንጂ የማገለግለው ህዝበ ክርስቲያን እንደሚያውቀው ሁሉ አንድም ቀን ከቤተክርስቲያን ተለይቼ የማላድር ኑሮዬም ስራዬም በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ጊቢ ውስጥ መሆኑን እና በከተማ ቤት ተከራይቼ የማልኖር በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ስለ ቤተክርስቲያኗ እና ስለ ሀይማኖቴ ራሴን ለእውነት የማስቀድም መሆኑን እኔን የሚወዱኝ ማህበረ ካህናት እና ምእመናን ህያው ምስክሮቼ ስለሆኑ ከላይ የተጻፈው አባባል ፍጹም ሀሰት ነው።

 

·         በበአለ ንግስ ጊዜ ታቦትን ለቢዝነስ እና ለገንዘብ መሰብሰቢያነት ተጠቅመዋል የሚለውን በተመለከተ

በየትኛውም አውደ ምህረት ለንግስ የተሰበሰበው ህዝበ ክርስቲያን በሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል እና በሚተላለፍለት መንፈሳዊ መልእክት በተጨባጭ ሰርተን ያሳየነውን ልማት በአይኑ አይቶ እና ተመልክቶ ለእምነቱ በትሩፋት ገንዘቡን አውጥቶ በፈቃደኝነት ከሚለግስ በስተቀር እንደ ጋዜጣው አባባል ይህንን ክቡር እና አዋቂ ህዝብ በማታለል ከኪሱ የወሰድኩት ገንዘብ የለም። ይልቁንስ በቤተክርስቲን ውስጥ የሚፈፀመውን ግፍና በደል ካህናቱ ቀርቶ ከህዝበ ክርስቲያኑ የተሰወረ አይደለም። መንግስት እና ሚዲያው በዚህ ከፍተኛ ችግር ላይ ቢደርስልን ሌባው እና አታላዩ  ማን እንደሆነ ሊደርሰበት እንደሚችል ጥሪዬን አቀርባለሁ።

 

·         ባቋቋሙት የሽልማት ኮሚቴ ስጦታዎችን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል በሚል የተገለፀውን በተመለከተ፡-

1.  ለራሴ የሽልማት ኮሚቴ ያቋቋምኩት ነገር የለም፣

2.  ተሸለመ ለተባለውም ሽልማት ጉዳይ የአንገት አይከን፣ በህይወት በምኖርበት ዘመን ምዕመናንን የምባርክበት የእጅ መስቀል፣ በኋላም ከዚህ ዓለም በሞት ስለይ ለቤተክርስቲያን የማወርሰው እንጂ እንደሌሎች የቅንጦት መኪና እና ቤት አልተሸለምኩም።

3.  “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንዲሉ አበው ያለ እረፍት ሌት እና ቀን ለልማት ስተጋ፣ ለወንጌል አገልግሎት መስፋፋት ስተጋ ቤተክስቲያንን የይዞታ ቦታ ለማስከበር ከሚመለከተው መንግስታዊ አካል ጋር በመነጋገር ያደረኩትን አስተዋጽኦ እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖትን ክብር እና መብት ሳስከበር ለቤተ ክርስቲያኗ ሁለንተናዊ ልማት እና እድገት ያበረከትኩትን ከፍተኛ የስራ ፍሬ ውጤት በመመልከት የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት፤ ካህናት እና ምዕናን በራሳቸው ተነሳሽነት እና ፈቃደኝነት ከየግላቸው ባዋጡት ገንዘብ የቤተ ክርስቲያኗን አገልጋይነቴን እና የጀመርኩትን የልማት ስራ አጠናክሬ እንድቀጥል ለማበረታታት ሲሉ ለማንኛውም የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እንደሚደረገው ሁሉ የቤተክርስቲን ሰበካ ጉባኤ አባላት ምዕመናንና ማህበረ ካህናት ባሉበት በአውደ ምህረት በግልጽ የተፈጸመ እንጂ ሰውን አስጨንቄ እና አስገድጄ ለራሴ ከሚቴ አቋቁሜ በስውር ያገኘሁት ስጦታ እንደሌለ ማንኛውም ዜጋ እና ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው ይገባል። ለዚህም በእጄ ያሉት ልዩ ልዩ የጽሑፍም ሆነ የድምጽ ወይም የምስል ማስረጃዎች እውነታውን ያረጋግጣሉ።

 

·          ባስተዳደርኩባቸው ሶስት አድባራት ችግር ፈጥረዋል የተባለውን በተመለከተ

1.  ሳገለግል በነበርኩበት ሶስቱም አድባራት ላይ ጥፋት ፈፅመሀል ተብዬ በተገልጋዩ ምዕመናን በወቅቱ የቀረበብኝ ክስ የለም።

2.  ባገለገልኩባቸው ቦታዎች ከመወቀስ ይልቅ ተመስግኜ ለምን ይዛወሩብናል በሚል ምዕመኑ ዝውውሩን ከመቃወማቸውም በላይ የቤተክስቲያኒቷ ልሳን በሆነው በኖህተ ጥበብ መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር 3 ላይ በምሳሌነት ለሌሎቹ አስተዳደሪዎች የኔን ፈለግ እንዲከተሉ ተመዝግቦ በሰፊው ይገኛል።

3.  በሶስቱም አድባራት ስዛወር ጥፋት ፈጽመሀል ተብዬ ሳይሆን የተለመደውን መንፈሳዊና የልማት ስራ እንድሰራ የሚል መሆኑን በቅዱስ ፓትርያርኩ ተፈርሞ የደረሰኝ የዝውውር ደብደቤ ያስረዳል።

·         ፀበል ቤት ለጋራዥ አከራይተዋል የተባለውን በተመለከተ

1.  በጋዜጣም ላይ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያኗን መሬት አሳልፎ ለመስጠት የተፈጸመ ሳይሆን በደብሩ ሰበካ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት የተሻለና ለምዕመኑ ምቹ የሆነ የፀበል ቦታ ለማዘጋጀት የተፈፀመ ነው። ምክንያቱም በተፈጥሮ የፈለቀው ፀበል የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደረገ እንጂ የነበረው ጸበል አልተዘጋም። ይህንንም በቦታው በመገኘት ማረጋገጥ ይቻላል።

·         የኪራዩን ውል የቤተክርስቲያኗን መብት በሚጎዳ ተዋውለዋል የሚለውን በተመለከተ

እኔ የብሔረጽጌ ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ከመሆኔ በፊት የነበረው የጋራዥ ኪራይ ዋጋ በወር ብር 3,000.00 ሲሆን እኔ ግን ከተመደብኩ በኋላ ሁሉንም በመመልከት የቤተክርስቲያኗን ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ስላገኘሁት ጉዳዩን ለሰበካ ጉባኤ አቅርቤአለሁ። ጉባኤውም ተወያይቶ አነስተኛ ዋጋ የተከራየ መሆኑን በማመን የወር ኪራይ ዋጋ ብር 35,000.00 እንዲሆን በውሳኔ ተደርጓል። ይህንንም ከእኔ በፊት የነበረውንና ከእኔ በኋላ ያለውን የኪራይ ውል በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል። ሱቆቹንም በተመለከተ ማረጋገጥ ይቻላል። ሱቆቹንም በተመለከተ እኔ የደብሩ አስተዳዳሪ ከመሆኔ በፊት በየወሩ ለዘመናት ከብር 3,000.00 – 6,000.00 ድረስ ሲከራይ የነበረውን እና ለ3ኛ ወገን ያከራይ ተከራይ በሚል ያለ አግባብ ሲጠቀሙበት የነበረውን በሰበካ ጉባኤ በማስወሰን በወር አንዱን ሱቅ በብር 1400.00 እንዲከራይ በማድረግ የቤተክርስቲኗን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ አስጠበቅኩ እንጂ እንደተባለው ቤተክርስቲያኗን የሚጎዳ ድርጊት አልፈፀምኩም።

 

·         አሁን የፍ/ቤት ውሳኔ እንዳይፈጠም አድርገዋል የሚለውን በተመለከተ

በመሰረቱ ሊፈፀም የሚችል የፍ/ቤት ውሳኔ ሳይሆን በሰበር ችሎት በክርክር ላይ የነበረውን ጉዳይ በደብሩ ሰበካ ጉባኤና በልማት ኮሚቴው ውሳኔ ግለሰቡ ያቀረበውን ይቅርታ መነሻ በማድረግ ከላይ በተገፀው መሰረት የኪራይ ውሉን በወር ከ3,000.00  ወደ 35,000.00 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል። ተከራዩ የተከራይ አከራይ በሚል ለ3ኛ ወገን አከራይተው ይጠቀም የነበረውን በቀጥታ ከቤተክርስቲያኗ ጋር ውል እንዲፈርሙ በማድረግ ብር 24,000.00 በወር እንዲከፈል ተደርጓል። በመሆኑም እኔ የፈፀምኩት አንድ ግለሰብ ግቢውን ተከራይቶ በወር ብር 3,000.00 ሲከፍል የነበረውን አግባብ እንዳልሆነ ተረድቼ በወር ብር 59,000.00 ቤተክርስቲያኗ ገቢ እንድታገኝ ማድረጌ ጉዳት ከሆነ ለፈራጅ ህሊና ትቼዋሁ።

·         አሁን የፍ/ቤት ውሳኔ እንዳይፈጸም አድርገዋል የሚለውን በተመለከተ

ዝውውር መፈፀም የእኔ የስራ ድርሻ አይደለም። በመሆኑም የፈፀምኩት ዝውውር የለም። ዝውውር የመፈፀም ስልጣንና ኃላፊነት የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ድርሻ ነው።

 

·         አገልጋይን በዘረኝነት ለያይተዋል፣ ከፋፍለዋል የተባለውን በተመለከተ

በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዘርን፣ ኃይማኖትን ሳይለይ ተከባብሮ በሚኖርበት ዘመን እንዲህ ዓይነት አስጸያፊና አስነዋሪ ቃል ከአንድ ኃይማኖታዊ አባት ተነግሯል ተብሎ መገለፁ አሳዛኝ ነው። እኔ መከባበርና መቻቻልን፣ አንድነትን፣ በኃይማኖት መጽናትን የምሰብክ እንጂ እንደተባለው እንዲህ አይነት አስጸያፊ ተግባር እንደማልፈጽም የሚያውቁኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክር ነው። ምናልባትም ይህ አገላለጽ የተሰጠኝ በራሳቸው ውስጥ ያለውን ስሜት እንደሆነ እገነዘባለሁ። በጋዜጣው አምድ ላይ ያወጣው ጋዜጠኛም ቢሆን ይህንን አደገኛና አስጸያፊ ተግባር መፈጸሜን ሳያረጋግጥ አየር ላይ ማዋሉ ከሞያ ስነ ምግባር ውጪ ነው።

 

·         በሀሰት ራሳቸውን ጥይት በመተኮስ መብረቅ ወረደና ከመብረቁ ጋር ታቦት ከሰማይ ጋር ወረደ በማለት የማታለል ተግባር ፈጽመዋል የተባለውን በተመለከተ

1.  በመሰረቱ ሰላም በሰፈነበት በአዲስ አበባ ከተማ አንድ የኃይማኖት አባት በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ይተኩሳል የሚለው አባባል ፈፅሞ ከእውነት የራቀ እና ሊታመን የሚችል አይደለም። እኔ ከመስቀል ባሻገር ጥይትም ሆነ መሳሪያ ለመሸከም ህሊናዬም ሆነ ኃይማኖቴ አይፈቅድም። ምናልባትም ይህንን ኃጢአት የሚያሸክሙኝ ግለሰቦች ጥይቱንና መሳሪያውን ሊሸከሙ የሚችሉ ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ እገምታለሁ።

2.  እውነታው ግን በኮልፌ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ፅላት ተገኝቷል መገኘቱንም በወቅቱ ለነበሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አሳውቄ በልደታ ጋዜጣ ላይ መግለጫ ሰጥቻለሁ። ሊቀ ጳጳሱም በቦታው ተገኝተው ባርከዋል። የሀገረ ስብከቱ የህትመትና ስርጭት ክፍል ኃላፊዎችም በቦታው ተገኝተው አረጋግጠዋል። ታቦተ ህጉም በአሁኑ ሰዓት በቦታው ላይ እየከበረ ይገኛል።

·         በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል የሚለውን በተመለከተ

1.  በመሠረቱ በተደጋጋሚ የተሰጠኝ ማስጠንቀቂያ ሳይሆን ስለመኖሩም ለጋዜጠኛው ሳይቀርብለትና ሳያረጋግጥ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ማለቱ ከስነ ምግባር ውጪ ነው።

2.  ተሰጠ የተባለውን ማስጠንቀቂያ በ1999 ዓ.ም የዛሬ 10 ዓመት የተፃፈ ሲሆን ለእገዳና ለስንብት ምክንያት የሆነውን እንደ አዲስ የተጠቀሰው በዚሁ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ተሰጠ የተባለው ማስጠንቀቂያ ላይ የተጠቀሰና በወቅቱ በ1999 ዓ.ም መፍትሄ ያገኘ ጉዳይ ነው። ምክንያቶቹ እውነትነት የሌላቸው ከግል ጥላቻ የመነጩ ናቸው።

ስለሆነም ሀሳቤን ለማጠቃለል የጋዜጣው ባለቤትም ሆነ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ማስገንዘብ የምፈልገው እኔ የታገድኩት እና ለዚህ ሁሉ ችግር /እንግልት እንድበቃ የተደረገኩበት ዋናው ምክንያት፡-

1.  በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን እያስተዳደርኩ ባለሁበት ወቅት የሀይማኖት እጸጽ እንዳለባቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸው መሆኑን እና ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ የጠየቁ ሁለት አገልጋዮችን በማህበረ ካህናቱ እና፣ በሰበካ ጉባኤው ውሳኔ የታገዱትን ወደ ስራ መልስ በሚል የአምባገነን አስተዳደር አስገዳጅ ትዕዛዝ ለምን አልፈጸምክም በሚል፤

2.  ለቤተ ክርስቲያኗ ልማታዊ እድገት የደብሩ ማህበር ካህናት እና ምዕመናንን በማስተባበር የተሰራውን ልማት ለማደናቀፍ በማሰብ፣

3.  ከላይ እስከ እታች ድረስ በግል እና በቡድን የተደራጁ ግለሰቦች የሚፈጽሙትን ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር እና ሙስና እንዲሁም ያለ አግባብ ጥቅም መፈለግን በጽኑ ስለምቃወም፤

4.  ደብሩ ክፍት ቦታ እና በጀት ሳይኖረው ሰበካ ጉባኤው ጥያቄ ሳይቀርብ የተለያዩ ግለሰቦችን ለመጥቀም ሲባል ብቻ ደመወዝ በመጨመር፣ ሠራተኛ በመቅጠር፣ እንድንቀበል በየጊዜው የሚጻፍብኝን ትዕዛዝ በመቃወም፣

5.  ወጥቼ ወርጄ ራሴ ካለማሁት እና ገቢውን ካሳደኩት እንዲሁም በካህናት እና ምዕመናን ዘንድ ተወዳጅነት ካተረፍኩበት ደብረ ያለ ምንም በቂ ምክንያት በማንሳት ወርሃዊ ደመወዝ ወደማይከፈልበት እና ምንም አይነት የልማት እንቅስቃሴ ወደሌለበት ቦታ መዛወሬን ያየ እና የተመለከተ ሁሉ ጉድ እስከሚል ድረስ የተሰራውን ወይም የተፈጸመውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራር መቃወሜ እና በሚመለከተው አካል ጩኸት በማሰማቴ የተደረገ እገዳ እንጂ ለመታገዴ እና ይህ ሁሉ ግፍ እና በደል እንዲደርስብኝ የተደረገ ተግባር እንጂ ይህ ነው የሚባል አንድም በማስረጃ የተደገፈ ጥፋት የሌለ ከመሆኑም ባሻገር እንዲያውም መናፍቃንን ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሰርገው እንዳይገቡ ለመከላከል እና እንደ ብረት አጥር በመቆሜ ልሸለም ሲገባኝ መልካም ስሜንና አርአያ ክህነቴን እንዲሁም ከኦርቶዶክሳዊት ኃዋርያዊት ጥንታዊት ታሪካዊት ቤተክርስቲያንን ክብርን ልዕልና ያዋረደውን ጋዜጣው ፍትሃዊነት የጎደለው አኳኋን የአንድን ወገን ብቻ ተቀብሎ ለህዝብ ለንባብ ያበቃውን ጽሁፍ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያስተባብል ስል እጠይቃለሁ። በተጨማሪም የሃይማኖት ህጸጽ በተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸውን ሠራተኞች አስተዳደራዊ እርምጃ ወስደው ለሚመለከተው አካል ማሳወቁ የኃይማኖት ህፀፅአለበት የሚያስብል ከሆነ ፍርዱን ለአንባቢ ሰጥቼዋለሁ። እንዲሁም የስነ ምግባርና አሉ የተባሉ ችግሮች በሙሉ እኔን የማይወክሉ መሆናቸውንና ማስረጃ የሌላቸው መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ።

Page 1 of 25

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us