በሙስሊም ተከሳሾች ውሳኔ ላይ የተንጸባረቁ አስተያየቶች

Wednesday, 05 August 2015 14:24

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነአቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ የቀረበለትን ክርክር ሲመለከት ቆይቶ ባለፈው ሰኞ ዕለት በ18 ተከሳሾች ላይ ከ7 አስከ 22 ዓመት ፍርድ መስጠቱ ከተሰማ በኋላ ርዕሰ ጉዳዩ በማህበራዊ ድረገጾች ሰፊ የመነጋገሪያ አጀንዳን ፈጥሯል፡፡ ፍርዱን ተከትሎ መንግስትን ከመተቸት ጀምሮ የተወሰደው እርምጃ ትክክል መሆኑን የሚናገሩ ወገኖች ግራና ቀኝ ሆነው ሲከራከሩ ተስተውለዋል፡፡ ጥቂቶቹን ሃሳቦች መርጠን እንደሚከተለው አስፍረነዋል፡፡

 

*** *** ***

 

ኡስታዝ (መምህር) አቡበከር አህመድና ያሲን ኑሩን በመጀመሪያ የማውቃቸው በስብከት ሲዲዎቻቸው ነው። 


እንደኔ እንደኔ፣ የያሲንና የአቡበከር ትምህርታዊ ስብከቶች ከሃይማኖታዊነታቸው ይበልጥ፣ ዩንቨርሳል ቋንቋነታቸው ይበልጥብኛል። ስለ ጊዜ፣ ስለ ስልጣኔ፣ ስለ ወድማማችነት፣ ስለ ፍቅር፣ እንዲሁም ስለ በርካታ ጉዳዬች የሰበኩባቸው ሲዲዎችን አድምጬ ተምሬባቸዋለው።


አዎ! የእነዚህን ሰዎች ቅንነትና በጎነት በቅርበት አውቀዋለው።


ፈፀሙ የተባሉት፣ "እስላማዊ መንግስትን ለመመስረት ማሴር" ከአስተምህሯቸውና እምነታቸው ውጪ ነው። እነኚህ ሰዎች "ከየትኛውም የሀይማኖት ተከታይ ጋር በፍቅርና በወንድማማችነት ተቀላቀሉ" እያሉ በየመስጊዱ እያስተማሩ፣ በአደባባይ ደግሞ ሽብርና ብጥብጥ ሊፈጥሩ አይችሉም።


እነዚህ ግለሰቦች ያለፈቃዳቸው በህዝብ አመኔታ የተመረጡ የህዝቡ ወኪል ናቸው። እነዚህ ሰዎች ግለሰቦች አይደሉም። ይልቁንም፣ እያንዳንዳቸው ህዝብ ናቸው።

 
ህዝብ ላይ እንዴት ይፈረዳል?
ህዝብ እንዴት ይታሰራል?
ህዝቡን ፍቱት!!!
(ቢኒያም ሐብታሙ)

 

*** *** ***

 

በሃይማኖት ሽፋን የሚራመደው አክራሪነት የደቀነው አደጋ፣


እውነቱ ብላታ ደበላ (የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ)


አገራችን የበርካታ ሃይማኖቶች መናሃሪያ አገር ነች፡፡ እጅግ በርካታ የአለማችን


ሃይማኖቶች ከፈለቁበት መካከለኛው ምስራቅ የመነጩ ኃይማኖቶችን በቀደምትነት ተቀብላ ያስተናገደች አገር ነች፡፡ የአይሁድ ኃይማኖት፣ ክርስትናና እስልምና ገና ከጠዋቱ መስፋፋት ሲጀምሩ ተቀብለው ካስተናገዱ የአለማችን አገሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ አገር ናት፡፡ ከነዚህ ጥንታዊ ሀይማኖቶች በተጨማሪ በኋለኞቹ ዘመናት በየትኛውም የዓለም ክፍል እየተፈጠሩ የተስፋፉ እምነቶችን ተቀብላም አስተናግዳለች፡፡ ከእነዚህ በተጓዳኝ አገራዊ መሰረት ያላቸው ሃይማኖታዊና ባህላዊ እምነቶችንም ያስተናገደች አገር ነች፡፡


የእነዚህ ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች ተከታይ የሆኑ ህዝቦቻችን እጅግ አብዛኛውን ጊዜ በመቻቻልና በመተሳሰብ አገራቸውን ገንብተዋል፡፡ ከውጭ ጥቃትም ተከላክለዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገራችን የቆዩት መንግስታት ለዘመናት በተከተሉት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ምክንያት አንዱን ሃይማኖት ከሌላው እያስበለጡ በህዝቦች መካከል በሃይማኖት እኩልነት ላይ ያልተመሰረተ ግንኙነት እንዲሰፍን አድርገው ኖረዋል፡፡


ይህን የመሰለ ግልፅ ጭቆናና በደል ከዘውዳዊው ስርአት ጀምሮ እስከ ደርግ መንግስት ውድቀት ከቀጠለ በኋላ አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሃይማኖት እኩልነትን በህግና በተግባር ለማስከበር ችሏል፡፡


አገራችን በዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት የምትመራ ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ ከሁሉ በፊት ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል እውቅና ተሰጥቷቸው ተከብረዋል፡፡ በህገ መንግስታችን መሰረት የሃይማኖት የበላይ ወይም የበታች የለም፡፡


ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል ናቸው፡፡ ሃይማኖትና መንግስት ተነጣጥለዋል፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግስት አስተዳደር ጉዳይ እጁን አያስገባም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሃይማኖትና ትምህርት እንዲነጣጠሉ ተደርጓል፡፡ ዜጐች የመረጡትን ሃይማኖት ያለአንዳች ውጫዊ ተፅዕኖና ግዳጅ የመከተልና የማክበር መብትን ተጐናፅፈዋል፡፡ በተግባርም ሁሉም ሃይማኖቶች በነፃነት የሚገለፁ፤ የሚሰበኩና የሚከበሩበት ሁኔታ ተረጋግጧል፡፡


መንግስት ሁሉም ሃይማኖቶች በቂና ተገቢ የእምነት ማድረሻ ስፍራዎች እንዲያገኙ፣ ለሁሉም ሃይማኖቶች በቂ የቀብር ቦታዎች እንዲመቻቹ፣ ሃይማኖታዊ በዓላት እኩል መንግስታዊ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲከበሩ ተደርጓል፡፡


በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ የማበላለጥ ስራ እንዳይኖር፣ የመንግስት አገልግሎት ለሁሉም ዜጐች ከሃይማኖት ልዩነት ባሻገር በእኩልነት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በእነዚህ ሁሉ መስኮች የሚፈፀሙ ስህተቶች ካሉም በህግ የሚያስጠይቁ እንደሆኑ ተደርጓል፡፡


ከዚህ አኳያ ሲታይ በአገራችን የሃይማኖት እኩልነት በህግና በተግባር የተከበረ ሆኗል፡፡ ይህም በመሆኑ ከአሉባልታና መሰረተ ቢስ ስሜት ቀስቃሽ ውንጀላዎች በስተቀር ሃይማኖታዊ አድሎ እንዲፈፀም የሚያደርግ ህግ አለ ብሎ በማስረጃ የተደገፈ ወቀሳና ትችት ለማቅረብ አንዳችም ተጨባጭ መሰረት የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡


እነዚህ እንደተጠበቁ ሆኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አክራሪነት በአገራችን በመገንባት ላይ ያለውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚፈታተን ሆኗል፡፡


የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነቶችን ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱት ፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተደጋገሙና አልፎ አልፎም የግጭት መልክ እየያዙ ሲሄዱ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ በክርስትናና እስልምና እምነቶች ሽፋን የሚራመዱ ፅንፈኛ ተቃውሞዎችን ስንመረምር የምናገኛቸው እውነታዎች በሃይማኖት ሽፋን ለመነገድ የሚሞክሩት ወገኖች ምን ያህል መሰረተ ቢስ በሆነ አጀንዳ ሁከትና ትርምስ ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ለመገንዘብ እንችላለን፡፡

 

*** *** ***

 

የፍትህ ጓንት የለበሰ ፍትህ አልባ መዳፍ !!


 (አሌክስ አብርሃም)


ትላንት ….


በእርግጥ ሁሉም አገዛዝ በዘመኑ የሚያነሳውንም የሚጥለውንም “ልክ ነው” ማለቱ የተለመደ ነው!! ለምሳሌ ደርግ ስልሳ ሚንስትሮችን በጅምላ ረሸነና “ለአገር ደህንነት ሲባል” አለ ደርግም እንዳቅሚቲ ደርጉን እንደጓንት ተጠቅሞ ጓንቱ ውስጥ ግን የራሱን ደም የጠማው መዳፍ አስቀምጦ ኢትዮጲያ መቸም የማትተካቸውን ድንቅ ልጆቿን እያነቀ ገደለ ! ከዛ “የፍየል ወጠጤን” በሬዲዮ አዘመረ …እንግዲህ “አገር ማለት ህዝቡ ነውና” በድርጊቱ ህዝቡ ደህንነት ስሜት ሳይሆን በነብሰበላው ደርግ ተሸማቀቀ …ያም ብቻ አይደለም አገር ራሷ በእነዚያ ታላላቅ ሰዎች ሞት …እሳት እንደነካው ፌስታል ተጨማደደች …እስካሁንም እንደግመል ሽንት ወደኋላ የሚስባት ታሪክ ….አስከትላ ትናውዛለች!!


ዛሬ የዞን ናይን ጦማሪያንን ጓፎ እስር ቤት ያጎረ “መዳፍ” እየገፋ ያስገባቸውን እየገፈተረ አስወጣ …ለምን ተባለ መልስ የለም !! ይሄን ሰምተን ገና ከግርምታችን ሳንወጣ …የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት ሰሚት ምድብ በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የተጠቀሱ 18 ተከሳሾችን ዛሬ ከ7 አመት እስከ 22 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጥቷቸዋል። ሂደቱን ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ሲከታተለው ነበርና ዝርዝሩን ማውራት ከንቱ ነው ….ግን ያ ጅምላዊነታችን ዛሬም አገርሽቶ ዛሬም ፍትህ ጓንት ውስጥ የተቀመጠ ፍትህ አልባ መዳፍ መራር ድርጊቱን ደገመ …ይሄን ከሞት የሚለየው ታሳሪዎቹን ሳይሆን መላው ዜጋ ለፍትህ ያለውን ተስፋ በጅምላ ማነቁ መረሸኑ ላይ ነው ! ከዛ … “በአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” በብሔራዊ ቴሌቪዥናችን ‹የፍየል ወጠጤን ያዘምራል!!


የፍትህ ጓንት... ውስጡ ለተቀመጠው መዳፍ ታዛዥ መሆኑን ለማረጋገጥ ሩቅም መመልከት አያስፈልግም … ትላንት ጋዜጠኞቹን እና ጦማሪያኑን ፍትህን ገፍትሮ ጣልቃ በመግባት ፍትህ አልባው መዳፍ ሲፈታቸው አይተናልና ! ዛሬም ጅምላዊነታችን አገርሽቶ እነሆ አስራ ስምንት ወጣቶች ላይ ‹‹ጓንቱ ሳይሆን መዳፉ›› ያሻውን ፈረደ !! እኔ በበኩሌ መንግስትን አላምነውም ….ምክንያቱም የታሰሩትን ለምን ፈታችሁ ሲባል በአደባባይ መመለስ ያቃተው ጠቅላይ ሚንስተር “የሚመራው” መንግስት …ለምን እንዳሰረ የመናገር የሞራል ብቃቱም ሆነ በፍትህ ስርአቱ ጣልቃ አለመግባቱን ማረጋገጥ የሚችልበት ወኔ ሊኖረው ይችላል ብዬ ስለማላምን ነው!!


ስለዚህ አገራችን ላይ ፍትህ በመንግስት መዳፍ ላይ የሚጠለቅ ሲያሻውም የሚያወልቀው ጓንት እየሆነች ነው! ለማንኛውም … መንግስት በሽብር ያሰራችሁ እናንተ ኢትዮጲያዊያን ወንድሞቻችን … እንደአንድ ኢትዮጲያዊ እኔ አሸባሪ ናችሁ ብዬ አላምንም! በእናንተ ጥያቄ ለተሸበሩትም ሃቅ ላይ የተመሰረተ … ፍትሃዊነትና የጋራ አገራዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ የማይሸበር ልቦና ይስጣቸው!  እግዚአብሔር ከምንም በላይ በበረታ ክንዱ ነፃ ያወጣችሁ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1007 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us