ታላቁ መጽሐፍ

Wednesday, 12 August 2015 12:40

በዲ/ን ኒቆዲሞስ

 

‹‹የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቃውንት እንደተረጎሙት በአማርኛ የተገኘ እንደሆነ ቢታተምልኝ ዓይነቱን ዐይቼ በብዙ እንድትልኩልኝ ምላሽ እልክልችኋለሁ። ቀደም ሲል እንደላካችሁልኝ ያሉትን መጻሕፍት ሕዝባችን ይወዳቸዋል፤ ይልቁንም ከአማርኛና ከግዕዝ ጋር ሆነው የታተሙትን ስላለካችሁልኝም በረከት የልቤን ምስጋና ለማመልከት ሁለት የዝሆን ጥርስ ለጉባኤው ሥራ ጥቃሞት ልኬያለሁ። በመንፈሳዊ ሥራችሁ ስላሰባችሁኝ እግዚአብሔር ያኑራቸሁ።›› ጳጉሜ ፪ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ.ም. ዐፄ ምኒልክ ለዓለም መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከአንኮበር ከተማቸው የላኩት የምስጋና ደብዳቤ።

 

በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ይህን ነው ተብሎ ሊገለጽ በማይችል ትልቅ ተጽዕኖንና አሻራን ያሳረፈ፣ የዓለማችንን ፖለቲካ/ሥነ-መንግሥት ሒደት ላይ ጉልህ ድርሻ ያለው፣ በሕግና በፍልስፍና፣ በሕዋ ሳይንስና በሕክምና፣ በኪነ ጥበብና በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጽሑፍና በጥበብ ሥራዎች ላይ ተጽዕኖው እጅግ የገነነ፣ የተደነቀና የተወደደ ዘመናት ያስረጀ አንድ ታላቅ መጽሐፍ አለ። ለዚህ መጽሐፍም ሲሉ በርካታዎች ከአገር ወደ አገር ተሰደዋል፣ ተግዘዋል፣ ተንከራተዋል፤ ክቡር ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል፣ በእሳት ተቃጥለውና ተሠቃይተው ለአሠቃቂ መከራና ሞትም ተዳርገዋል።


ይህ የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ መንገዶች የለወጠና ብዙዎችም ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው እስከመስጠት ድረስ በፍቅር የወደቁለት የትኛው ትንግርተኛ መጽሐፍ ይሆን ብለን ለአፍታ ቆም ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አይቀርም። ይህ በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ደማቅና ጉልሕ የሆነ አሻራውን የተወው ድንቅና ተወዳጅ መጽሐፍ - መጽሐፍ ቅዱስ ነው።


እዚህ ጋር ለእንግሊዝና በሂደትም ለዓለም መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ምሥረታ ምክንያት ስለሆነችው ስለ እንግሊዛዊቷ ወጣት ሜሪ ጆንዝ ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበራትን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጸውን ታሪኳን ማንሳት የሚገባ ይመስለኛል። ታሪኩ የተፈጸመው በ፲፯፻፺፪ዓ.ም. ነው። ሜሪ ጆንዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ካላት ጥልቅ የሆነ ፍቅር የተነሣ ከቤቷ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቅት ላይ ወደሚገኘው የወላጆቿ ወዳጆች ቤት በየዕለቱ እየሄደች ታነብ ነበር። ብላቴናዋ ሜሪ በዚህ ብቻ አላቆመችም፤ የግሏ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት በማሰብም ለስድስት ዓመታት ያህል ገንዘብ አጠራቅማለች።


ሜሪ የግሏ እንዲሆን ለማድረግ ልዩ ናፍቆት ያሳደረባትን መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ደግሞ ፵ ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዛ ነበር። ይሁን ሁሉ ዋጋ ከፍላ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይገኝበታል የተባለበት ቤት በደረሰች ጊዜ የናፈቀችው መጽሐፍ አልነበረም። በዚህ ጊዜ ሜሪ ጆንዝ አንገቷን ደፍታ ተንሰቅስቃ አለቀሰች። አብረዋት የመጡት ካህኑ ኤድዋርድስ በኀዘኔታ ተውጠው፤ ‹‹አሁን ለዚህች ልጅ፣ ለዚህች ብላቴና ምንም መጽሐፍ ቅዱስ የለህም ማለት ነው ሚ/ር ቻርለስ?›› አሉ በመንተባተብና በመለማመጥ።


ወዳጄ ካህን ኤድዋርድ ‹‹አንድም የለኝም።›› አሉ ሚ/ር ቻርልስ ቀጥለውም ‹‹በእርግጥ ለሌላ ሰው ለመስጠት ያሰብኳቸው ሁለት ወይም ሦስት መጽሐፍ ቅዱሶች በመደርደሪያው ላይ አሉ፤ ትርፍ ግን የለኝም።›› ሜሪ ጆሮዋን ማመን አልቻለችም፤ ዳግም ስሜትዋን መግታት ተስኗት ተንሰቅስቃ አለቀሰች፣ ከተቀመጠችበት ወንበር ላይም ዘፍ ብላ ወደቀች። ይህን ልብ የሚነካ ትዕይንት የታዘቡት ሚ/ር ቻርለስ ድንገት ተነሥተው እጃቸውን ሜሪ ላይ ጫኑ። ‹‹ልጄ ሆይ መጽሐፍ ቅዱስሽን ማግኘት አለብሽ፣ የፈለገው ቢሆን ባዶ እጅሽን አልሸኝሽም፤ አይዞሽ ልጄ ዝም በይ።›› አሉ።


ወደ መጽሐፍት መደርደሪያቸውም ሄደው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ወደ ሜሪ ተመለሡ። ‹‹ሜሪ ውሰጂ›› ብለው አቀበሏት። ሜሪ መጽሐፍ ቅዱሱን ተቀብላ ወደ ደረቷ አስጠግታ በማቀፍ ዐይኖቿ በዕንባ እንደረጠቡ ሚ/ር ቻርለሰን ቀና ብላ ዐየቻቸው፤ ፊቷ ላይ የብርሃን ተስፋ ያበራ ነበር። ‹‹በእውነት የኔ ነው አለች?!›› ‹‹የአንቺ ነው ልጄ›› አሉ ሚ/ር ቻርለስ። ሜሪ እንደገና በደስታ አነባች፣ ሚ/ር ቻርለስን በብዙ አመስግናም በሐሤት ተሞልታ መጽሐፍ ቅዱሳን ይዛ ወደ ቤቷ ተመለሰች።


ከሜሪ ጆንዝ አስደማሚ ታሪክ ስንመለስ በቀደመው ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ልብ የማግኘቱ ጉዳይ እጅጉን አስቸጋሪና ብዙ ልፋትንና ድካምን አንዳንዴም ሕይወትን እስከማጣት ድረስ የሚዘልቅ መሥዋዕትነትን የሚያስከፍል እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ።


እንደ ጆን ዊክሊፍ ያሉ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በጥንታዊው የላቲን ቋንቋ ብቻ የተጻፈውንና በጥቂት የሮማ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና አገልጋዮች እጅ ብቻ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስን ተራው ሕዝብ በሚያውቀውና በሚረዳው የእንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎም ለሕዝብ በሰፊው ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት ሕይወታቸውን ጭምር አስከፍሏቸው ነበር።


ጆን ዊክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስን ተራው ሕዝብ በሚረዳው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፎ በማሰራጨቱ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራው እንዲታገድ የተደረገ ሲሆን፣ አፅሙም ከመቃብር ወጥቶ በእሳት እንዲቃጠል ተፈርዶበት ነበር። እንዲሁም በፕራግ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረውና የጆን ዊክሊፍ ደጋፊ የነበረው ጆን ሔስ ፲፫፻፺፫ ዓ.ም. መጽሐፍ ቅዱስን በማሰራጨቱ በቁሙ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተፈርዶበታል። በኋላም ፲፮ኛው ክ/ዘ የሥነ መለኮት ምሁር የነበረው ዊሊያም ቲንደል ከአገሩ እንግሊዝ ተሰዶ ጀርመን በስደት በነበረበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን አሳትሞ ለሕዝብ በማሰራጨቱ ተይዞ ከተሰቀለ በኋላ አስክሬኑ እንዲቃጠል ተደርጓል። ብዙዎችም መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡና ሲያሰራጩ የተገኙ ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስ በአንገታቸው ላይ ታስሮ በእሳት እንዲቃጠሉ ተፈርዶባቸዋል።


ለመሆኑ ይህ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ይህን ያህል ክብርንና ታላቅ ሥፍራን ያገኘ፣ ሕይወትን ጭምር ሣይቀር ያስከፈለ የዘመን ድልድይን ተሻግሮ አሁንም ድረስ እንደተወደደና እንደተከበረ የዘለቀ፣ ትንግርተኛ መጽሐፍ ይህን ሁሉ መከራ አልፎ ዛሬ በእጃችን ሊገኝ የቻለበት ምክንያቱ ምን ይሆን ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ለጥያቄያችን ምላሽ ይሆነን ዘንድ በጣም ጥቂት እውነታዎችን እናንሳ።


መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጽሐፍት የሚለይበት ዋንኛው ምክንያት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሪነት በመጻፉ ነው፤ ስለሆነም ልዩ የሆነ ኃይል፣ ምሥጢርና ጉልበት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅሩን፣ አሳቡን፣ ዘላለማዊ ተስፋውንና ጽኑ የሆነ ቃል ኪዳኑን የተገለጸበት መጽሐፍ በመሆኑ ከኹሉም መጽሐፍት በእጅጉ የተለየ ነው።


ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከቅጂ ቅጂ፣ ከቋንቋ፣ በእጅ እየተገለበጠ፣ በታሪክና በዘመናት የሚከሰቱ በርካታ መከራዎችንና አደጋዎችን እንዲሁም ቃሉን ለማጥፋት በየዘመናቱ የተነሡ የተቃዋሚዎችን አደጋና ጥቃት፣ የመናፍቃንን ማጥላላትና ውግዘት በማለፍ ለዘመናችን ደርሷል። መጽሐፍ ቅዱስ በየሀገሩና በየዘመኑ የተነሡትን የበርካታ ምሁራንና ኢአማንያንን ትችትና ነቀፋ አሸንፎም ዛሬም ሕያው ሆኖ በየትኛውም ኑሮና ሥልጣኔ ደረጃ የሚገኙ በቢሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች በፍቅርና በደስታ የሚቀበሉት፣ የሚያነቡት ልዩ፣ ተወዳጅና ተናፋቂ መጽሐፍ ሊሆን በቅቷል።


በአንድ ወቅት አንድ አፍሪካዊ ልዑል በታላቋ ብሪታንያ ንግሥት በሆኑት በንግሥት ቪክቶሪያ ጋባዥነት አገረ እንግሊዝን ለመጎብኘት ዕድሉን አግኝቶ ነበር። ይህ አፍሪካዊ ልዑል ለአንድ ሳምንት ያህል እንግሊዝን ከጎበኘ በኋላ ወደ አገሩ ሲመለስ ሣለ ንግሥት ቪክቶሪያ በቤተ መንግሥታቸው የራት ግብዣ አድርገውለት ነበር። በዚህ የመሸኛ የራት ግብዣ ላይም አፍሪካዊው ልዑል ስለ ቆይታውና በጉብኝቱ ስለተሰማው ስሜት ንግግር እንዲያደርግ ንግሥት ቪክቶሪያ በክብር ጋበዙት።


አፍሪካዊው ልዑል ንግሥት ቪክቶሪያ፣ እንግሊዛውያን ሉዓላውያን ቤተሰቦችና በርከት ያሉ የክብር እንግዶች በተሰበሰቡበት በቤኪንግሃም ቤተ መንግሥት እንዲህ ሲል ተናገረ። ‹‹ንግሥት ሆይ በእውነት እንደ ኢትዮጵያዊቷ ገናና ንግሥተ ሳባ በሩቅ፣ በዝና የሰማችውን የንጉሥ ሰለሞንን ጥበብና ማስተዋል በዓይኗ አይታ ያረጋገጠችበት፣ የተደመመችበት፣ የተደነቀችበት ዓይነት ልዩ የሆነ ስሜት ነው የተሰማኝ። ንግሥት ሆይ በአገርዎ ገናና ታሪክ፣ ግዙፍ ሥልጣኔ፣ በመንግሥትዎና አስተዳዳር ብልሃትና ጥበብ፣ በሕዝብዎ ጨዋነትና ታታሪነት በእጅጉ ተደንቄያለሁ።››


በነገራችን ላይ የኛው የቋራው አንበሳ፣ አባ ታጠቅ ካሣ፣ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስም ለአገራቸው ኢትዮጵያ የእንግሊዝን ዓይነት ሥልጣኔና ዕድገት ዕውን በማድረግ ከዓለም በፊት ቀድማ ነቅታ ከጥበብ ተፋታና ርቃ በኋላ ቀርነት ጥልቅ እንቅልፍ፣ ድብታ ውስጥ የገባች ውድ አገራቸውን የቀደመ ክብሯንና ዝናዋን ለመመለስ ሲሉ ከእንግሊዞች ኃያልነትና ታላቅነት፣ ጥበብና ሥልጣኔና ጋር በፍቅር ወድቀው ያን ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የተመኙለትን ሥልጣኔ ዕውን ለማድረግ ከእንግሊዞች ጋር በብዙ እንደተሟገቱ፣ በብዙ እንደደከሙ፣ እንደማሰኑ ነበር ራእያቸውን ዕውን ሳያደርጉ ያለፉት።


በዘመናቸውም አፄ ቴዎድሮስ ለሕዝባቸው፣ ለወታደሮቻቸውና ካህናቱ መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት እንዲያገኙና እንዲያስተምሩበት በማሰብ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን እንግሊዛዊውን ሚሲዮናዊ ማርቲን ፍላድን በመማጸን መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት እንዲሰራጭ ማድረጋቸውን የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ። በዐፄ ቴዎድሮስ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ከገቡም በኋላ ሕዝባቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጸሐፍት ዘግበዋል። እ.ኤ.አ በ1864 10000 አዲስ ኪዳን የአማርኛ መጻሕፍት በሀገር ውስጥ እንደተሰራጩና በወቅቱም ሌሎች 14000 ግልባጮች ታትመው እንደነበር የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፡- The Foundation of Education, Printing, Newspaper, Book Production, Libraries and Literacy in Ethiopia በሚል ጥናታዊ ጹሑፋቸው ጠቅሰውታል።


ወደ አፍሪካዊው ልዑል ስንመለስም በንግግሩ ፍጻሜ መጨረሻ ልዑሉ እንዲህ አለ። ‹‹ለመሆኑ ንግሥት ሆይ እንዲህ በዓለም ኹሉ ለናኘው ለአገርዎ ታላቅነት፣ ለሕዝብዎ ሥልጣኔ፣ ለመንግሥትዎ ገናናነትና ክብር ምስጢሩ ምን እንደሆነ ሊነገሩኝ ይችላሉ።›› ሲል ጥያቄውን በትሕትና አቀረበ።


ንግሥት ቪክቶሪያም ለአፍሪካዊው ልዑል በሐር ጨርቅ የተሸፈነ መጽሐፍ ቅዱስ በስጦታ ካበረከቱለት በኋላ እንዲህ አሉት፡- ‹‹ወዳጄ የታላቋ ብሪታንያ የመውደቅና የመነሣት ታሪክ፣ የታላቅነት ምስጢር፣ የመንግሥቴና የሕዝቤ ገናናነት ሥልጣኔ ምንጭ፣ የእኔም ጥበብና ማስተዋል ምስጢሩ አሁን በሰጠኹ ታላቅ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛልና በማስተዋል አንብበው፣ ለሕዝብህም አስተምረው አሉት።››


በዓለም ታሪክ በጥንታዊነታቸው፣ የተለየ ተወዳጅነትንና ዝናን በማትረፋቸው ዘመናትን ተሻግረው አሁንም ድረስ ትልቅ አድናቆትንና ከበሬታን በማትረፍ በብዙዎች ዘንድ ልዩ የክብር ስፍራን የተቀዳጁና የሕትመት ብርሃንን ደግመው ደጋግመው ለማየት የቻሉ ጥቂት መጻሕፍት አሉ።


ከእነዚህ በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ከበሬታንና ተወዳጅነትን ካተረፉና ደጋግመው የሕትመት ብርሃንን ለማየት ዕድል ካገኙ ጥቂት መጻሕፍት መካከል ‹‹ታላቁ መጽሐፍ›› በሚል ቅፅል የሚጠራውን መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዳደር መጽሐፍ የለም። በሕትመት ብዛትም ሆነ በሥርጭት አኳያ መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዳደር መጽሐፍ እስካሁን አልተገኘም። ወደፊትም የሚገኝ አይመስልም።


መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን ድረስ ከ፭ ቢሊዮን በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ የተሰራጨ ሲሆን በየዓመቱም ከመቶ ሚሊዮን በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ በመላው ዓለም ታትሞ ይሰራጫል። በዚህን ያህል ሕትመት ሥርጭትና ብዛት ለመድረስ አይደለም ለመቅረብ የሚችል መጽሐፍ ቅዱስን ሊወዳደር የቻለ አንድም መጽሐፍ አልተገኘም፣ የለምም። ይህ መጽሐፍ በዓለማችን ታላላቅ ሰዎች፣ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ፈላስፋዎች፣ ጠቢባንና በአጠቃላይም በሰው ልጆች ሕይወት ላይ በጎና አዎንታዊ የሆነ ታላቅ ተፅዕኖን ያሳደረ በብዙዎች ዘንድ ድንቅ፣ የተመረጠ፣ የተወደደ ልዩ መጽሐፍ ነው።


እስቲ ስለዚህ መጽሐፍ የቀደመ ታሪክና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ጥቂት ነገሮችን ብቻ በማንሳት በታላቁ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ ለዛሬ ያነሣሁትን አሳቤን ልደምድም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደአሁኑ ለአያያዝና ለማንበብ እንዲመች ተደርጎ ከመዘጋጀቱ በፊት በሸክላ፣ በድንጋዮች፣ በፓፒረስ፣ በብራና በመሳሰሉ ነገሮች ላይ ነው ሲጻፍ የነበረው። እስከ ፲፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስም መጽሐፍ ቅዱስ በተለዩና እጅግ ጥንታዊ በሆኑ ቅዱሳን መካናት፣ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በጥቂት ታላላቅ ሰዎችና ሊቃውንት እጅ ብቻ የሚገኝ መጽሐፍ ነበር።


የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት ፲፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀርመናዊው ጉንተበርግ የማተሚያ መኪናን በመፍጠር መጽሐፍ ቅዱስ የሕትመት ብርሃን እንዲያገኝ ከማደረጉ በፊት በዓለማችን ታሪክ በጥንታዊነቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ ቅዱስ በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በእጅ የተጻፈውና በአሁን ሰዓት በቫቲካን ላይብረሪ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ይጠቁማሉ።


ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ ደግሞ በቅርቡ በሰሜን የአገራችን ክፍል በ፮ኛው መቶ ክ/ዘመን በብራና ላይ የተጻፈ ጥንታዊ የሆነ ወንጌል በአርኪዮሎጂና በታሪክ ምሁራን አማካኝነት በትግራይ በአባ ገሪማ ገዳም መገኘቱን እንደ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው መዘገባቸውን ይታወሳል። አገራችን ኢትዮጵያ ለሺ ዘመናት የዘለቀ የረጅም ዘመን ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች አገር፤ እንዲሁም በዓለምም ሆነ በአፍሪካ የራሳቸው የሆነ ቋንቋና ፊደል ካላቸው አገራት ተርታ በቀደምትነት የምትመደብ አገር እንደሆነች በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረና የተረጋገጠ ነው።


ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከሥነ ጽሑፍና ጥበብ ጋርም ተያይዞም የብዙ ዘመን ታሪክ አላቸው። በጥበብ ፍቅር ወድቃ፣ ልቧ መንኖባት ዙፋኗን ትታ ጥበብን ፍለጋ፣ ጥበብን አሰሳ ከአገሯ ተነሥታ በብዙ ገጸ በረከትና ስጦታ ወደ ኢየሩሳሌም ከተጓዘቸው ከንግሥተ ሳባ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ድረስ ኢትዮጵያውያን ለመጽሐፍት፣ ለጥበብ ልዩ ፍቅር ያላቸው ሕዝቦች ነበሩ። ይህ እውነትም ከታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ እስከ ቅዱስ ቁርአን፣ ከግሪካውያን የጥበብና የፍልስፍና ሥራዎች እስከ ጥንታዊዎቹ የታሪክ ተመራማሪ፣ አሳሾችና ጸሐፍት ድርሳናት ውስጥ በሚገባ ተመዝግቦ ይገኛል።


ኢትዮጵያውያን ነገሥታት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና አባቶች ይህን ታላቅ ቅዱስ መጽሐፍ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች እያዘጋጁና እየገለበጡ ለሕዝብ እንዲዳረስ በብዙ ደክመዋል፣ ለፍተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በአገራችን በኢትዮጵያ ያለውን የረጅም ዘመናት ታሪክና እንዲሁም ከጥንት ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያኑ ነገሥታት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና አባቶች ለዚህ ታላቅ መጽሐፍ የነበራቸውን የተለየ ፍቅርና ይህ ቅዱስ መጽሐፍም ለወገኖቻቸው እንዲዳረስ ያሳዩትን ትጋት፣ የከፈሉትን መሥዋዕትነት በሌላ ጊዜ በሰፊው የምመለስበት ይሆናል።


ሰላም!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1173 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us