የኢሰፓ ቀይ ደብተር በኢህአዴግ ዘመን እድሳት አገኘ

Wednesday, 19 August 2015 12:56

- ከአኢሴማ ወደ ሴቶች ሊግ ከአኢወማ ወደ ወጣት ሊግ

በዘመኑ ገረመው

 

በአንድ ወቅት ከአንድ የእድሜ ባለጠጋ የቀድሞ ሰራዊት አባል ጋር ቁጭ ብለን እየተወያየን ነው። አዛውንቱ የቀድሞ የሰራዊት አባል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሰፊ ልምድ በአይጠገብ ገለጻቸው እያስኮመኮሙኝ ነው። ከውይይታችን መሀል ለዛሬ ጽሁፍ ይሆነኝ ዘንድ አንድ ነጥብ ላነሳ ወደድኩ።

ነገሩ እንዲህ ነው። ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ (ጊዜያዊ ቢልም ለ17 ዓመታት በስሙ መጠራቱን ቀጥሎበት ነበር። ዳሩ በዚህ ዘመንስ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ በሚል መጠሪያ ስም ጫካ የገቡ ታጋዮችስ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብተውም መች ስማቸውን ቀየሩ? የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ህወሓት) እየተባሉ አሉ አይደል) በስልጣን ዘመኑ መገባደጃ አካባቢ ነገሩ ሁሉ ተበለሻሽቶበት ነበር አሉ። መቼም ነገር ሲበላሽ አይጣል ነው። ሰውየው “አላህ ሲጣላ በትር አይቆርጥም ያደርጋል እንጅ ነገሩ እንዳይጥም” እንዳሉት ማለት ነው። ደርጉ ስልጣኑ ሊገባደድ አካባቢ እንደ አውሬ አድርጎት የነበረ ሲሆን በመንግስታዊ አገልግሎት አካባቢ ደግሞ “እኔ መንገድ እና ህይወት ነኝ፤ ከእኔ በቀር ወደ ስልጣንም ሆነ ወደ ስራ የሚሄድ የለም” ብሎ እርፍ አለ አሉ።

ደርግ ሆዬ ገበሬውን በመሬትና በውትድርና ሲቆጣጠር ከተሜውን ደግሞ በሸማቾች ማህበር፣ በስራ እድል እና በወታደር ምልመላ አሸማቆ ለመቆጣጠር ሙከራ አድርጎ ነበር (መከራ ገብቶ ነበር እንጅ)። በዚህ የተነሳም ከየአቅጣጫው ጫና በዛበት። ጫናው ሲበዛ ደግሞ ጫንቃው እየጎበጠ ሄደ እና በአፉ ሊደፋ ሆነ (በመጨረሻም ተደፋ)። በተለይ በከተማ አካባቢ የወሰደው እርምጃ አላምር ያለው ሁሉንም ነገር በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ስኳር ለመግዛት በኢሰፓ አባልነት፣ ጨው እና ፉርኖ ዱቄት ለመግዛት በኢሰፓ አባልነት፣ ስራ ለመያዝም በኢሰፓ አባልነት በማድረጉ ነበር። (ዳሩ አሁንስ እነ ስኳር፣ ፉርኖ ዱቄት፣ ምስር፣ ዘይትና አጠቃላይ የምግብ እህልስ በኢህአዴግ አባልነት ቢገኙ አይደል) እናም የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል እንዲሉ አበው (እማውም ይተርታሉ) እናቶች ለስኳር፣ ለጨውና ለዱቄት ሲሉ በቀበሌያቸው የአኢሴማ (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር) አባል ሆነው ቀይዋን ደብተር ተቀብለው በኩራት ዱቄትና ጨው ገዙ። ወጣቱ ደግሞ ለእናቱ ስኳር እና ጨው መግዣ ገንዘብ ለማግኘት በአኢወማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር) ተደራጅቶ ቀይዋን ደብተር በመያዝ ቢሮ ገባ።

በወቅቱ የትምህርት ቤት ደጃፍ የረገጠም ሆነ የቀለም ቀንድ የሆነ ወጣት በሙሉ የአኢወማ አባል ሳይሆን የመስሪያ ቤት ደጃፍ ሊረግጥ የሚችለው በወታደር ታጅቦ ነበር እሱም “አድሃሪ” ተብሎ ሊረገጥ። እናም ይህን ያዩ ሁሉ ከመሞት መሰንበት ብለው ቀይዋን ደብተር ለማግኘት ተሰለፉ። እናም የኢሰፓ አባል ሆኑ።

በመግቢያዬ ላይ የገለጽኳቸው አባት የነገሩኝ ታሪክም የሚያጠነጥነው በዚህ ላይ ነው። አንድ በግብርና ኑሮን መግፋት የተሳነው ጎልማሳ በአኢገማ (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማህበር) ታቅፎ ቀይዋን ደብተር (የኢሰፓ አባልነት መታወቂያ ካርድ) ይዞ ከተማ ይገባ እና ወታደርነት ተመልምሎ የምድር ጦር እቃ ክፍል ይመደባል። ጎልማሳው አፈር መግፋት የተሳነው ቢሆንም ቀይቷ ደብተር በሰጠችው ነጻነት ተመክቶ የምድር ጦሩ እቃ ክፍል አለቃ ካልሆንኩ አለ። በዚህ የተነሳ ከልካይ በማጣቱ ብዙ ቦታ ገብቶ ከፈተፈተ በኋላ መቼም ከሰው መርጦ ለታቦት ከእንጨት መርጦ ለሹመት ነውና አንድ የኢሰፓ ቀይ ደብተር የሌለው ጎረምሳ ያንን ባለ ጊዜ ዘሎ ጆሮ ግንዱን በጥፊ ይወለውለዋል። ባለጊዜው እንዴት በዘመኔ ተደፈርኩ ብሎ ቡራ ከራዩ ሲል ጎረምሳው “ባለጌን ባለጌ ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል ከፈለክ ና እደግምሃለሁ” ብሎ ለሁለተኛ ዙር ቡጢ ተዘጋጀ። በመሃል ገላጋዮች ገብተው ነገሩን ያበርዱትና ለአንድ ዓመት ያህል የጎሪጥ ሲተያዩ ከርመው በዓመቱ ብሶት የወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርጉን አሽቀንጥሮ መሃይሙን የኢሰፓ አባልም አሰናብቶ ወንበሩን ራሱ ተቆጣጠረው።

ይህ ከሆነ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ደግሞ ሌላ ኢሰፓ ሌላ ባለ ጊዜ መጣ። ብሶት የወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት ራሱ ሌላ ባለጊዜ ሆነ እና ቀይዋን ደብተር ያልያዘ የበሰለ እህልም ሆነ አብስሎ የሚበላ የለም” ሲል በይፋ በአደባባይ አወጀ። እናቶችን በቀበሌ አዳራሽ ሰብስቦ የሴቶች ሊግ አባል ያልሆነ ጾታውን እቀይራለሁ አለ። ሴቶቹ ጾታቸው የሚቀየር መስሏቸው ይሆን ወይም በሌላ ምክንያት (ምናልባት ኢሰፓ ያደረሰባቸውን ግፍ በመፍራት እባብን ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ) ቶሎ ብለው የሴቶች ሊግን ተቀላቀሉ እና ከሊጉ ላለመውረድ ከፍተኛ ትንቅንቅ ማድረግ ጀመሩ።

ትንሽ ቆይቶ ደግሞ በሊግ ያልታቀፈ ወጣት የሴት አንገት ማቀፍ አይችልም አለና አረፈው ማን? ይሄው ብሶት የወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት። በሊጉ ያልታቀፈ ወጣት ሴት ማቀፉ ይቅርብኝ ቢል እንኳ አንዳች ምንዳ እንደማያገኝ ተነገረውና ቶሎ ብሎ በሊጉ ታቅፎ ውድድር ማካሄድ ጀመረ። የአማራ ወጣት ሊግ፣ ከኦሮሚያ ወጣት ሊግ የትግራዩ ወጣት ሊግ ከደቡቡ አቻው እየተወዳደረ በሊጉ አሸናፊ ለመሆን ተፋለመ።

ከሊግ የተረፈውን ደግሞ በመንግስታዊ መስሪያ ቤት በኩል አላሳልፍ በማለት ደቀ መዝሙሮችን እንዲህ ሲል አዘዛቸው “ሂዱና በመላው አገሪቱ በህወሓት፣ በብአዴን፣ በደኢህዴን፣ በኦህዴድ አንድ ገዥ ስም እያስተማራችሁ አጥምቋቸው። ያመነ የተጠመቀ ይድናል፣ ለቤተሰቡም ይተርፋል። ያላመነ ያልተጠመቀ ግን አይድንም አያድንምም” ብሎ በየአቅጣጫው ላካቸው። በዚህም መሰረት ግማሹን በከፍተኛ ትምህርት ቅጥር ግቢ ውስጥ ቀሪውን ደግሞ በስራ ቅጥር ቦታ እየተከተሉ ማስተማሩንና ማጥመቁን ተያያዙት። እነሆ አገሪቱ በሙሉ አምነው በተጠመቁ ኮሚኒስት ወጣቶች ተሞላች።

ቢጠመቅም ከልቡ ያላመነ ለድጋሚ ትምህርት ሲዳረግ፣ ያላመነ እና ያልተጠመቀ ደግሞ በቅዱሳን ማህበር እድል ፈንታ እንዳይኖረው ጌታ ኢህአዴግ በታላቅ ድምጽ ተናግሯል እንዲህ ሲል “የኢህአዴግን ፖሊሲና ርዕዮተ ዓለም በትክክል ተቀብሎ የሚሰራ ከሆነ የትምህርት ደረጃው አያሳስበኝም። ምክንያቱም ሲቪል ሰርቪስን የመሰለ ዩኒቨርስቲ አለኝ በዚያ አስተምራቸዋለሁ። ሲቪል ሰርቪስ ቢሞላ እንኳ ሌላ እከፍታለሁ” ብሏል።

ለዚህ አባባሌ አስረጅ ሁነት ላቅርብ። ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅት የሚሰራቸውን ስራዎች ለህዝብ ይፋ ለማድረግ የህዝብ ግንኙነት የሚባል የስራ መደብ ያስፈልገዋል። በዚህ የስራ መደብ ተመድቦ በመንግስት መስሪያ ቤት ለመስራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከመግባቱ በፊት የሚቀርብለትን መመዘኛ እንመልከት።

- የስራ መደቡ መጠሪያ፦ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ (ከጀማሪ እሰከ ከፍተኛም ሊሆን ይችላል)

- የትምህርት ደረጃ፦ በማንኛውም የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ድግሪ (ምናልባት እስከ ሶስተኛ ድግሪም ሊደርስ ይችላል እንደ ደመወዙና የስራ ደረጃው ይለያያል)

- የስራ ልምድ፦ ዜሮ ዓመት (ለከፍተኛና ለመካከለኛ ባለሙያዎች መደቡ የሚጠይቀው ልምድ ይቀመጣል)

- ተጨማሪ ስልጠና፦ የህዝብ ግንኙነት ስልጠና የወሰደ።  

እኔን ያላመነ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የወጡ የመንግስት መስሪያ ቤት (የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት እና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ) ያወጣቸውን የቅጥር ማስታወቂያዎች ይመልከት!!

ከላይ ከተቀመጡት መመዘኛዎች መካከል የመጨረሻውን መመዘኛ ያላሟላ ስራ ፈላጊ በመንግስት መስሪያ ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆኖ ለመስራት ክፍት የስራ መደብ ባወጣው መስሪያ ቤት ደጃፍ ድርሽ እንዳይል ተከልክሏል። የኢሰፓ ቀይ ደብተር በኢህአዴግ ሲታደስ ማለት ይህ አይደል!!

ኢህአዴግ ነገረ ስራው አልጥም ያለው ምናልባት ሰውየው “አላህ ሲቆጣ በትር አይቆርጥም፤ ያደርጋል እንጅ ነገሩ እንዳይጥም” ያሉት ደርሶበት ይሆን? ይህስ አይሁን!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1292 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us