"ዛሬ ጋሞ የሚባል ቀበሌ ሳይኖር የማንነት መግለጫና የራሱ ቋንቋ ያለው ህዝብ ሊሆን አይችልም።"

Wednesday, 19 August 2015 12:52

በአስፋ ሻመና

"ማዶላ፤ አልፋና ኦሜጋ ደሬ፤ የማላ ዶጋላ ሕዝብ ታሪክ" በዎራባ እራሻ ጎተና ቱፋ ታደላ፤ የካቲት 2007፤ በአዲስ አበባ፤ የታተመውን በተቻለ መጠን መጽሐፉን ገዝተን ለማንበብ ሞክረናል። በዚህ መጽሐፍ ምክንያት የተነሳውን አቧራ አይተነዋል። በዚህ ላይ እንደዶርዜ አንዳንድ ነገር ማለት አግባብ በመሆኑ የቀረበ ነው።

ስለመጽሐፉ ትንሽ ለማለት ያክል መጽሐፉ 267 ገጽ ይዞ  ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ባለስልጣናት በተጻፉ ደብዳቤዎች የታጨቀ ነው። ከዚያ ቀደም ብለው ያሉ ገጾች  በተለይም ስለማላና ዶጋላ አመጣጥ አሰፋፈር ከዮዲት ጉዲት ታሪክ ጋር እንደት እንደተገናኘ የሚገልጹ ክፍሎች አሉት። እውነትነት ያለውን የአካባቢው ፖለቲካ አስተዳደር ካኦዎች (ንጉሶች) የት እንደነበሩና እነማን እንደነበሩ በከፊል አሳይተውናል። በአንዳንድ ቦታዎች በተለይም በዶርዜና በተወሰኑ አካባቢዎች ሕዝቡ ከሕዝቡ በተመረጡ ሀላቃ ይተዳደር እንደነበር ገልጸዋል።የጽሁፋቸው መነሻም ሆነ መድረሻውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አገናኝተው ተርከዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህ አካባቢ ማለትም ማላና ዶጋላ ሕዝቦች ደሬ ወይም ሕዝብ የተለየ ሁኔታና ቦታ በከፊል ያሳየ አጋጣሚ ነው።

ስለ"ዎራባ ራሽያ ጎተና" ማእረግ እውቀቱ የለንም እንጂ በጎፋ አካባቢ እንደነበረና የእሳቸው ማእረግ እንደሆነ የገለጹ ቢሆንም እሳቸው ለሚሉት የማዶላ ግዛትን ያጠቃለለ የማዕረግ አሿሿም ነበር የሚል እምነት የለኝም። እሳቸው የጠቀሱት አካባቢዎች የማላና ዶጋላ ውህደት የፈጠረው አካባቢ መሆኑ እውነት ነው። የማላና ዶጋላ አመጣጥ እሳቸው እንዳሉት ነው የሚል እምነት ባይኖረንም እንደ መነሻ ሊያዝ ይችላል።ስለጎፋና ወላይታ እንዲሁም ዳውሮ ታሪክ አግዝፈው ሲገልጹ ስለሌሎች ምስራቃዊ እስከ ሁለቱ ሀይቆች ድረስ ስላለው ሕዝብና መሬት መግለጽ አለመቻላቸው የመጽሐፋቸው ጉድለት አድርገን ወስደናል። ጋሞ የተባለ መሬትም ሕዝብም የለም የሚል አንደምታ ባለው አገላለጽ አልፈውታል። ቦነኬ፣ ባልታ፣ ዘገትሰ፣ ዲታ፣ ወዘተ…ካኦዎችና ሕዝብ መኖሩን ዶርዜ የሚባል ብሔረሰብና በአገራችን የሸማ ስራን የፈጠረና የሸማ ስራን ወደጥበብነት የቀየረ ዝነኛ  ሕዝብ መኖርን ሳያውቁ ቀርተው አይመስለንም። ሙሉ በሙሉ የጎፋ መሬትና ሕዝብ ነውም አላሉም።

“ማዶላ” የሚለውንም የህዝብ ስያሜ በራሳቸው እንደሰጡ ገልጸዋል። የስያሜው ታሪካዊ መሰረቱ የሌለውም ቢሆንም ማላና ዶጋላን በማገጣጠም የተገኘ ነው በማለት ገልጸዋል።በቆሞ በዶርዚኛ (ኦሞ) በመጨረሻ ገጽ ላይ ሲዘረዝሩ እሳቸው በሚሉት አካባቢ ያለውን በሙሉ በመግለጽ በሌሎች አካባቢ ያሉትን መግለጽ አለመቻላቸው እጥረት እንዳለባቸው ያሳያል። ዶርዜ ጊዮርጊስ፣ ኤሊ ገብርኤልና ብርብር ማሪያም ታቦቶች ከዮዲት ጉዲት ጋር ከሰሜን እንደመጡ  ይግለጹ እንጂ የአመጣጣቸውን ሁኔታ አላሳዩንም። አንድ ጥሩ ነገር ያየነውና በአካባቢው የሰው ስም አጠራር እንዴት እንደነበር ማሳየታቸው ነው። ደራሲው ታደለ ቱፋ ይባላሉ (በአማርኛ) የአካባቢው አጠራር ግን እሳቸው እንዳስቀመጡት የአባት ስም ቀድሞ ተጠርቶ የልጅ ስም ቀጥሎ መጠራቱ (ቱፋ ታዳላ) ነው። እኝህ ደራሲ ስለግል ታሪካቸው የጻፉት ከመጻሐፉ መጠን ጋር ስነጻጸር የሰፋ ሆኖ ከመገኘቱ በተጨማሪ ለጽሁፍ የማይመጥኑ ነገሮች የታጨቁበት መሆኑን አይተናል። ረጅም ዓመት አገልግሎት ከመስጠታቸው አንጻር ምናልባት ያላቸውን ልምድ ያሉበትንና የተፈጠሩበት አካባቢ አጉልቶ ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር። የሰው ልጅ መሰረት እሳቸው የተፈጠሩበት አካባቢ አድርገው ቀርጸዋል። እዚህ አካባቢ የኖህ መርከብን ጨምረው የገለጹበት ሁኔታ ከአፈታሪክ በስተቀር መሰረት የሌለው እንደሆነ ይታያል። ምናልባትም የሰው ዘር አመጣጥን ሁኔታ ማርክሲዝምን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን መርህ የተከተለም አይደለም። ቢያንስ የማርኪስዝም ንድፈ ሀሳብ በመከተል የሰው ዘር ከእሳት ክብ ከነበረችው ዓለም ለዘመናት እየቀዘቀዘች ስትሄድና ነፍስ ያለው ነገር ለመፈጠር ከተመቸው የምድር ሁኔታ ተነስቶ ሰለሴሎች (cells) ከዚያም እጽዋት እንሰሳት በመቀጠልም ከእንስታት ለሰው መሰረት ከሆነው ዝንጀሮ ከመሰለ እንሰሳ የተገኘው ሰው የተፈጠረውና ወደ ሰው መልክ የተቀየረው እሳቸው የተወለዱበት አካባቢ ነው ማለት አልቻሉም። ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር አዳምና ሄዋን በገነት ከተፈጠሩ በኋላ በዚያ በፈጸሙት ሃጥያት ምክንያት ከገነት ወደ ምድር ሲወረወሩ ያረፉት እሳቸው የተወለዱበት አካባቢ ነውም አላሉም። የሰው ልጅ መፈጠርን ሊገልጹ የቻሉበት ቢያንስ እንደሉሲ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመት ቅሪት (አፋር አካባቢ እንደተገኘው አጽም) በአርኪዎሎጅ የተደገፈ ማስረጃ አላቀረቡልንም። ለሰው ልጅ የመፈጠር ሁኔታ ትተን እንኳን ስለኖህ መርከብ ብንወስድ በመንደራቸው ለመኖሩ ምንድነው ተጨባጭ ማስረጃቸው? 

 አቶ ቱፋ ይህንን መጽሐፍ ለምንድነው የጻፉት? ስለማላና ዶጋላ ህዝብ የአካባቢው መሰረታዊነት ለማስረዳት ነው? ስለራሳቸው ለአካባቢው ያደረጉትን ጥረት ለመግለጽ ነው? የማዶላ ሕዝብነው ያሉት አንድ መሆኑን ለማሳየት ነው? የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርስ በመዋለድ በመካከላቸው ምንም አይነት ልዩነት የለም፣ የአንድ ዘር ሀረጎች ነን ለማለት ነው? ጋሞ የሚባል ሕዝብና ምድር የለም ለማለት ፈልገው ሌላውን በሽፋን መልክ ለመግለጽ የታለመ ነው? ጎፋን ከዞንነት ለማውጣት ያደረጉትን ተደጋገሚ ጥረት በሌላ መንገድ ለማሳካት ይሆን  የሚሉ ጥያቀዎችን በሰው አስተሳሰብ ላይ ጥያቄ የሚያጭሩ ናቸው። በዚህ ምክንያት መጽሐፉ ምንን ለማስተማር እንደቀረበ ግልጽ አይደለም። ሆኖም ግን በውሰጡ ሊወሰዱ የሚችሉ ጠቃሚ ነገሮች እንዳሰፈሩ መካድ አይቻልም።

 አንድ ቡድን በራሱ አምኖና ተግባብቶ "እኔ ወይም እኛ እንደዚህ ነኝ ወይም ነን" ካለ እራሳቸውን ለፈለጉት ማንነት መሰረትም ይኑረው፣ አይኑረው ሌላው አካል መቀበል የግድ ነው። በጋሞ ብሔረሰብ ላይ የሰነዘሩት አስተያየት ላይ እንደ ዶርዜ ብሔረሰብነትና እንደ የአገሪቱ ሕገ መንግስት እንደሰጠው መብት በእኛ በኩል አቀራረቡና አገላለጹ ስህተት እንዳለው ተገንዝበናል። ጋሞ ነን የሚሉት ጥቂቶች ግን ይህን እንደ አንድ ሰው አስተሳሰብና እንደ ንድፈ ሀሳብ አቀራረባቸውን በሚያከሽፍ ሌላ ንድፈ ሀሳብ ማለትም ጋሞ የሚለው ቃል ከደርግ በፊት ነበር ወይ? ማነው ይህንን ስያሜ የሰጠው? "ጋሞ" ጠበቅ ብሎ ነው ወይስ ላላ ተብሎ የሚነበበው? ቦታው የትኛውን አካባቢ ያጠቃልላል? (ጋሞነት የዶርዜ ብሔረሰብን የማይመለከት ሆኖ) በፊትስ የነበረው ስያሜ ምን ነበር? "ገሙ ጎፋስ" ሲባል "ገሙ" የሚለው ቃል ጋሞ ለማለት ነውን? ጋሞን አንድ የሚያደርጉ እሴቶቹ ምንድ ናቸው? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ መልስ በማዘጋጀትና በማሰራጨት መከላከል እንጂ ተነካሁ ብሎ ሆ!! ብሎ መነሳት መፍትሄ አይደለም። ወይም መጽሐፉን የደረሱትን ደራሲ ለምን ይህንን በጽሁፋቸው እንዳሰፈሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቅም አግብብ ይሆናል፡ በዚያ ሽፋን ጋሞ ነን ባዮች የነበረን ቁርሾ በመቀስቀስ ጎፋዎች በዞኑ የያዙትን የስልጣን ቦታ በማስለቀቅ ለመያዝ የታለመ ይመስላል።

ማንም ሰው የሌላን ሰው ወይም ቡድን መብት በፈለገው መንገድ መንካት ክልክል ወይም ወንጀል እንደሆነ እኝህ  የህግ አዋቂ ሳይገነዘቡት ቀርተው አይመስለንም፡ አንድ ግን ሊወስዱ የፈለጉት ሪስክ ወይም ለመክፈል የፈለጉት መስዋእትነት እንዳለ ያስታውቃል። ከእሳቸው ጀርባም ሌሎች ሰዎች እንዳሉ እንገነዘባለን።

ሰሜን ኦሞ እየተባለ በሚጠራበት ጊዜ ወላይታዎች ከዞኑ ወጥተው የራሳቸውን ዞን ለመመስረት የተጠቀሙትን ስልት ቀደም ብለው የነበሩና አሁንም ያሉ የጋሞ ብሔረሰብ አባል ነኝ የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ዞር ብለው ሊያስታውሱት ይገባል። ጎፋ ዞን ሆነ በጋሞ ጎፋ ዞን በአንድነት ኖረ ለሕዝቡ የሚፈጥረው የተለየ ነገር የለም። እንዲሁም ተለያይተው በሁለት ዞን መኖራቸው እስካሁን ይታይ የነበረውንና ለሁለቱም አካባቢዎች ማነቆ የሆነውን እርስ በርስ መሳሳብና መገፋፋት ሁኔታና በዚህም የተነሳ በአካባቢው እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሆኖ የቆየውን በተለይም አርባምንጭ ከተማን ይቀይራል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም ከላይ የጠቀስነው ጎፋ ዞን ሆኖ መውጣት ከተሳካ አቶ ታደለን በሕግ ከመጠየቅ ያለፈ ነገር አይኖርም ብቻ ሳይሆን ለጎፋ ዞንነት ራሳቸውን ጭዳ ያደረጉ ወይም መስዋእት የሆኑ የእነሱ ጀግና ይሆናሉ።

የጎፋ ሕዝብ እንደ ዶርዜ ሕዝብ ቀደም ብሎ ወላይታና ዳውሮ እንደዞን ተነጥለው ሲወጡ በወቅቱ አብረው መውጣት ይችሉ የነበረው አጋጣሚ ቀርቶባቸውና ተዘናግተው ዛሬ ለዞናቸው መፈጠር ከፍተኛ መስዋዕትነት ለመክፈል ተገደዋል። ይህም መጽሐፍ የዚህ ትግሉ አጋር አንዱ አካል ይመስለናል። ይህ ሁኔታቸው ከዶርዜ ሁኔታ ጋር ያመሳስላቸዋል። ቀደም ባለው ጊዜ እነግድቾ፣ ኦይዳ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ዘይሰ ብሐረሰባዊ ማንነታቸውን "እኛ እራሳችን የቻልን ብሔረሰብ ነን" ብለው ማንነታቸውን አስከብረዋል። በወቅቱ ዶርዜ ግን በዚያ የማንነት ሻሞ ጊዜ በመዘናጋቱና ከሌሎች አሁን ከላይ ከተጠቀሱት ብሔረሰቦች ይበልጥ ዘመን ተሻጋሪ፣ በ1976 ዓ.ም፣ በ1987 ዓ.ም የህዝብና ቤቶችን ቆጠራ በኮድ 73 የታወቀና ብሔራሰባዊ ማንነቱ በሕግና በሕግ የተረጋገጠለት ብሔረሰብ እንደነበር፤ በምኒልክ፣ በንጉሱ ከዚያም በደርግ ዘመን ይታወቅ የነበረው ብሔረሰብ ዛሬም ሕገመንግስት የፈቀደለት መብቱ ተጨፍልቆና አጥቶ በክልልና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እየተንገላታ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። ስለሆነም የአቶ ታደለ ጽሁፍ ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎችን በሙሉ ለመመለስ የተዘጋጀ መጽሐፍ ሳይሆን ጎፋን በዞንነት ለማውጣትና ጋሞዎችን አበሳጭቶ ከጋራ አንድነት ወይም ከዞኑ እንዲገፉ ለማድረግ የታለመ ይመስላል። እቅዳቸው እየተሳካ ያለም ይመስላል። ባይሳካም እንኳን እንደበፊቱ አብሮ መኖር ሳያስቸግር አይቀርም። ይህም በሐምሌ 11 በአካባቢው የተፈጠረው ትርምሶች መጽሐፉ ያለመውን ግብ ለመምታት መንደርደሪያ ሁኔታ እንደሆነ ያሳየናል። ከዚያም በሳምንቱ ሰኞ ሐምሌ 20 በተደረገው ኮንፍረንስ ላይም ጎልቶ የተንጸባረቀበት ጎፋን የመግፋት ሁኔታ መታየት ነው።

በማጠቃለያነት  ጋሞ እንደብሔረሰብ በመንግስት ታውቆና በተወካዮች ምክር ቤት ሆነ በብሔሰቦች ምክር ቤት ወንበር ተሰጥቶት የመንግስታዊ መዋቅር አካል ሆኖ መኖሩ እየታወቀ መንግስት ራሱ አይደላችሁም ባላለበት ሁኔታ ግለሰብ ገጽ167 "…ጋሞ ለተባሉት የተለየ አገርና ህዝብ የላቸውም" ባለና በዚሁ መጽሐፍ 168  ገጽ ላይ "…ጋሞ ማለት ኋላቀር ወይም ዝም ብሎ የሚጓዝና የራሱን አሳልፎ የሚሰጥ በጊዜው በተከሰተው ሁኔታ የተለየ አገር ያላቸው ሕዝብ ተደርገው ስያሜ ተሰጣቸው እንጂ አገር የላቸውም።" በማለት ገልጸዋል።ይህንንም መነሻ በማድረግ በዞን ደረጃ ትርምስ መፈጠሩ አግባብነት የለውም ብቻ ሳይሆን ከእኛ በላይ ማንም የለም ከማለት የተለየ አይደለም። አሁን በጥቂቶች የተጀመረው እንቅስቃሴ ለጋሞ ብሔረሰባዊ የሥነልቦና አንድነት ከመፍጠር አኳያ ፋይዳ ይኖረው ይሆን? ታዲያ የቦንኬ ባለስልጣን ለቦንኬ እና ለተነሳበት አካባቢ እንጂ ጋሞነትን መሰረት አድርጎ ዶኮን ወይም ሌላውን ለጥቅም ማስጠጋት የመጣውን የመንግስት ድጋፍ ወደራሳቸው ቤትና ሰፈር ከመጎተት የሚያድን አይደለም። ዶኮውም ዛዳውም ጥቂት ባለስልጣን ነኝ የሚባሉት እንዲሁ። ስለሆነም የጥቂቶች መነሳሳት የመንደርተኝነት አባዜ ፈውስ ሊሆን አይችልም። ዶርዜ መብቱ በመረገጡና በመጨፍለቁ ያላደረገውን "የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ" እንደተባለው የአማርኛ ተረት እነዚህ ትምክህተኞች  ሕዝቡን በማነሳሳት ትርምሱን የፈጠሩት ጋሞ ነን ባይ ጥቂት ግለሰቦች መጽሐፉን ከፃፈው ግለሰብ ባልተናነሰ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል እንላለን። እነዚህ ግለሰቦች ዶርዜን ብሔረሰብ አይደለም በሚል የሚያወግዙና ለማውገዣነት በተዘጋጁ የየዞኑ መድረኮች የሚፎክሩና የሚያቅራሩ፤ የዶርዜን ባህልና ስርዓት ለራሳቸው ለብሔረሰባቸው ለማድረግ የተነሱ፤ በከፊል በሌብነትና ከመንግስታዊ መዋቅሩ ጋር በመመሳጠር ጥቂት ስልጣንና ገንዘብ አለን የሚሉ፤ መንግስት ለሁሉም እኩል እንዲዳረስ የዘረጋውን የመልካም አስተዳደር ስርዓት ለራሳቸው ቤተሰቦችና ጎሳዎች የሚያደርጉ፤ ነገ ዶርዜ እሰከመጨረሻው ታግሎ መብቱን በሚያገኝበት ጊዜም በተመሳሳይ በሰሩትና በተናገሩት ወንጀል የሚጠየቁ እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። ማንነት ሲነካ ምን ያህል እንደሚቆጭና እንደሚያንገበግብ ማየታቸው ጥሩ ነው። ጊዜ ያልፋል። ምንም ነገር እንደነበረ አይቆይም። ዘመንና ጊዜ ለውጥን ያመጣሉ። ዶርዜም አንድ ቀን ብሔረሰባዊ ማንነት መብቱን እንደማንኛውም ሌላው ብሔረሰብ በትግሉ ይጎናጸፋል።

****                  *****                  ****

ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ፤ የጸሐፊውን አቋም ብቻ የሚያሳይ ሲሆን ጹሑፉ በአወዛጋቢው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ውይይት ይጋብዛል በሚል የቀረበ ነው። በቀጣይ በተቃውሞም በድጋፍ የሚነሱ ሃሳቦችን የምናስተናግድ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1975 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us