የኢኮኖሚው እድገት በድርቅ ሲፈተን

Wednesday, 19 August 2015 13:00

በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች ድርቅ ተከስቷል የሚሉ መረጃዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች መለቀቅ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው በስፋት እየሄደበት ይገኛል። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ደግሞ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች በዚሁ ዙሪያ አንዳንድ መረጃዎችን መስጠት ጀምረዋል።  የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ጌታሁን ነሀሴ 2 ቀን 2007 ዓ.ም ለህትመት በበቃው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተናገሩት ሃሳብ ችግሩ መኖሩን በመጠኑም ቢሆን የሚያላክት ነው።  ሃሳባቸውም ቃል በቃል የሚከተለውን ይመስላል።

 

"በአንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ በመዘግየቱና መጠኑም በመቀነሱ ድርቅ የሚመስሉ ምልክቶች ታይተዋል።" በዚሁ ዙሪያም የመንግስትን አቋም ከሰሞኑ ያብራሩት የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት  ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን በኤሊኖ ተፅዕኖ በተከሰተው የአየር ፀባይ ለውጥ በሀገሪቱ ላይ የግብርና ምርት ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ አስቀድሞ የተተነበየ በመሆኑ ችግሩን ለመቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ የቆዩ መሆኑን አመልክተዋል። ብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊዎችም የአየር ለወጡን አሳሳቢነት በግልፅ ቋንቋ ተናግረዋል።

 

ዝናብ መቅረቱ ድርቅ ማስከተሉ አይቀሬ ነው። ይህ ሁኔታ አሁን ባለበት ደረጃ ውጤቱ በግልፅ የሚታይበት ሁኔታ አይኖርም። ገበሬው ያለፈው አመቱን ጥሪቱን እየበላ ጥቂት ቀናትንና ወራትን ሊገፋ ይችላል። የክረምቱ ሁኔታ አሁን ባለበት አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ ከጥቅምትና ከህዳር በኋላ ግን የእርዳታ እገዛ ማስፈለጉ አይቀሬ ነው።

 

ለችግሩ መንስኤ ተደርጎ እየተጠቀሰ ያለው በያዝነው ክረምት የዝናብ እጥረት መከሰቱ ነው። የአየር ንብረት ለውጡ የዝናብ ወቅት መዛባትን የማስከተሉ ጉዳይ ለኢህአዴግ መንግስት ይቅርና፤ ከኃያላኑ መንግስታት አቅምም በላይ ስለሆነ በዚህ በኩል ኢህአዴግ ይወቀሳል የሚል አመለካከት የለኝም።

 

 ድርቅ በአውስትራሊያ በተደጋጋሚ ተከስቷል። በካሊፎርኒያ ለአመታት ዝናብ ባለመዝነቡ የግዛቷ የከርሰ ምድር ውሃ ሳይቀር ተሟጦ የአካባቢው ሁኔታ የቴክኖሎጂ አቅም ከሚመልሰው በላይ ከሆነ ሰነባብቷል። የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ በተከሰተው የሙቀት መጠን መጨመር  በርካታ ህንዳውያንና ፓኪስታናውያን በሙቀት ቃጠሎ እስከወዲያኛው አሸልበዋል። በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የሙቀት መጠን መጨመር በርካታ ሀገራት በጎርፍ እየተጥለቀለቁ ነው። ችግሩ በቀጣይ ከዚህም በባሰ ይቀጥላል።

 

ነገሩን ወደ ሀገራችን ስንመልሰው የአየር ለውጥ ተፅዕኖው በኢትዮጵያ ደግሞ መልኩን ቀየር አድርጎ መጥቷል። ይህም የክረምት ዝናብ ወቅቱን ማዛባት ነው።

 

"ክረምቱ በጥሩ አጀማመረ ገባ፣ መሃል እየሳሳ ሄደ፣ በያዝነው ነሃሴ ወር ደግሞ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ይዘንባል። ከዚያም የተለመደውን የክረምት ጊዜ ሳይጠብቅ በአፋጣኝ ይወጣል።"

 

 ይህ የኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኤጀንሲ ባለፈው ማክሰኞ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ትንበያው ይሄንን ሲመስል፤አንገብጋቢ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ የሚሆነው በቀጣይ ምን ውጤት ይከተላል የሚለውን በተመለከተ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ተከሰተ፤ ይህም ዝናብ እጥረትና መዛባትን አስከተለ፤ ከዚያም ሁኔታ ድርቅን ማስከተሉ እየተነገረ ነው። መንግስት በድርቅ የተጠቃውን ህዝብ በችግሩ ስፋት መጠን መታደግ ካልቻለ ድርቁ ወደ ርሀብ ተቀይሮ ሊያደርስ የሚችለው ሰብአዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

 

 ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የአየር ንብረት ለውጥም ሆነ እሱን ተከትለው የሚመጡ የጎርፍ መጥለቅለቆች፣ የድርቅ አደጋ፣ በፀሀይ ነበልባል መቃጠልና የመሳሰሉት ክስተቶች ከሰውና ከመንግስታት አቅም በላይ በመሆናቸው በውጤቱ ማንም ሊወቀስ አይችልም። ቢወቀሱ እንኳን በኢንዱስትሪዎቻቸው ከፍተኛ የአየር ብክለት እያደረሱ ተፈጥሮ እንዲዛባ እያደረጉ ያሉት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ናቸው።

 

ሆኖም ወቀሳው የሚመጣው ችገሩ ከተከሰተ በኋላ መንግስታቱ በዜጎቻቸው ላይ አደጋው የከፋ  እንዳይሆን የወሰዷቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ነው። እንደዚሁም ችግሩን በመረዳት የአየር ንብረቱ ለውጥ ሊያስከትለው የሚችለውን አሉታዊ ለውጥ ተገንዝበው ባደረጓቸው ቅድመ ዝግጅቶች ደረጃ ላይ ነው።

 

 ህንድ በአንድ ወቅት ሃምሳ ሚሊዮን የሚሆን ህዝቧ ለድርቅ የተጋለጠበት ሁኔታ ነበር። በህንድ ድርቅ በመከሰቱ የህንድ ህዝብ መንግስቱን አልወቀሰም። መንግስት የማንንም የውጭ እርዳታ ሰጪ እጅ ሳያይ ለድርቅ የተጋለጠው ህዝብም ድምፁ ሳይሰማ እነዚያን የመከራ አመታት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያልፍ ማድረግ ግን ችሏል።  የህንድ መንግስት በወቅቱ ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ በድርቅ የተጠቁ ዜጎቹ ከአካባቢያቸው ሳይፈናቀሉ እዚያው ባሉበት በቂ ቀለብ እንዲያኙ ማድረግ ችሏል። ይህ የህንድን የኢኮኖሚ አቅም የሚያሳይ ነበር።

 

የሌሎች ሀገራትም እውነታ ይህ ነው። ድርቅን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይችሉም ህዝባቸው ድርቅ በሚያስከትለው አደጋ ለጉዳት እንዳይጋለጥ የማድረግ አቅምን ግን አስተማማኝ በሆነ መልኩ መፍጠር ችለዋል።

 

የኢህአዴግ መራሹ መንግስት የኢኮኖሚ እድገት የሚፈተነውም እዚህ ላይ ነው።  ኢኮኖሚው ላለፉት አስር ተከታታይ አመታት በሁለት አሃዝ እያደገ መሆኑ በትክክል የሚፈተነው ከዚህ በኋላ ባሉት ጊዜያት ፤በተለይም በቀጣዮቹ ወራት ነው።

መንግስት በድርቅ የተጎዳውን ህዝብ የሌላ ወገን እገዛን ሳይጠይቅ በሀገሪቱ አቅም መወጣት ከቻለ፤ በእርግጥም ኢህአዴግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን የገነባ መሆኑን ማስመስከሪያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስተር ሀይለ ማርያም ደሳለኝ ከሰሞኑ በተካሄደው የዲያሰፖራ ቀን ማጠቃለያ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ድርቅ ሲከሰት ፈጥነው የእርዳታ እህል ያቀርቡ የነበሩ የረደኤት ድርጅቶች የመንግስትን ችግሩን የመወጣት አቅም ለመመልከት ዳር ቆመው መመልከትን የመረጡ መሆናቸውን አመልክተዋል። መንግስትም በዚህ ረገድ በራሱ አቅም ችግሩን ለመወጣት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ጭምር ነው ያመለከቱት።

 

 በንጉሱ ዘመን ድርቅ ሲከሰት ሀገሪቱ ዜጎቿን መመገብ ካለመቻሏም ባለፈ ወሬው ሳይቀር እንዳይሰማ አፈና መደረጉ በውጤቱ በርካታ ሰበአዊ እልቂት እንዲፈጠር አደረገ። ይሄው ሰበአዊ ቀውስም ለቀሪው አለም መድረሱ ኢትዮጵያና ረሀብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው እንዲቆራኙ አደረገ። የሰባ ሰባቱ ድርቅም ውጤት ርሀብን ያስከተለ ነበር። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን በተለያዩ ጊዜያት የተከሰተው ድርቅ መንግስት የረደኤት ድርጅቶችን የምፅዋት እጅ እንዲያይ አድርጎታል።

 

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ አጋማሽ በኋላ ግን የአየሩ ሁኔታ የተስተካከለ ስለነበር የክረምቱ እንደዚሁም የበልጉ የዝናብ በድርቅ በኩል የሚሰሙ ወሬዎች አልነበሩም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእርዳታ ፕሮግራሞች ተቀይረው ገበሬው በሴፍቲኔት ፕሮግራም በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ በስፋት ሲሰራ ቆይቷል።

 

አሁን ባልተጠበቀ ሁኔታ ዝናብ ቀረ። የኢህአዴግ ፖሊሲዎች ብሎም የኢኮኖሚው እድገት ተመዝኖ የብቃት ማረጋገጫውን የሚያገኘው ልክ እንደሌሎች መንግስታት ሁሉ የሀገሩን ድርቅ በሀገሩ በሬ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ከቻለ ነው። "ክረምት ካልገባ ሁሉም ቤት፤ እንግዳ ካልመጣ ሁሉም ሴት ነው" የሚለው አባባል ነገሮች ብቃታቸው በፈተና እንደሚመዘኑ ማሳያዎች ናቸው። የዘንድሮው ክረምት አደጋ ላይ የመውደቁ ጉዳይ ኢህአዴግ እንደ መንግስት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም እንደሀገር የምትፈተንበት ነው። ግብርና መር በሆነው ኢኮኖሚ ገበሬው ቢያንስ የአንድ አመት ጥሪት ቋጥሮ አስቀምጧል ተብሎ ይገመታል።

 

 በመሆኑም "ዝናብ ቀረ እህል የለም" በሚል ገበሬው በወራት ጊዜያት ውስጥ እርዳታ ፈላጊ ከሆነ የግብርናው እድገት ጥያቄ ውስጥ የሚገባው ያኔ ነው።  ገበሬው የዚህን አመት የግብርና ምርት በተገቢው መጠን ባይሰበስብም ባለፈው ዓመት ጥሪቱ ጥቂት ከተንገታገተ በኋላ ችግሩ ከከፋ መንግስት ሊደርስለት ይችላል።

 

 በዚህ ሂደትም ቀጣዩ በልግ ከዚያም ክረምቱ ሊገባ ይችላል። ከዚህ ውጪ በሆነ ሁኔታ ገበሬው ከወዲሁ የሚፈታ መንግስትም እጁን ለምፅዋት ተሯሩጦ የሚዘረጋ ከሆነ ግብርና መር እድገቱም ሆነ የፖሊሲዎቹ በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲወድቁ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። ያለፉት ተከታታይ አመታት የኢኮኖሚ እድገት ድርቅ ሲመጣ እጃችንን ለምፅዋት እንዳንዘረጋ የማያደርገን ከሆነ ከቀደሙት የኢኮኖሚ ሂደቶች በምን እንደሚለይ ለማስረዳትም ሆነ ለመረዳት ይከብዳል።

 

 ኢህአዴግን በአየር ንብረት ለውጡ አንኮንነውም። ኢህአዴግን በተከሰተው ድርቅም አንወቅሰውም። ኢህአዴግ የሚመሰገነውም ሆነ የሚወቀሰው ከድርቅ በኋላ በሚታዩት ቀጣይ ውጤቶች ነው። በድርቅ የተጠቁት ወገኖቻችን በያዙት የቀደመ ጥሪት ጥቂት ሊንገታገቱ ቢችሉም ምርትን ለማግኘት ክረምት አልፎ ሌላ ክረምት መጠበቅ ግድ ይሆንባቸዋል። በዚህ ወቅት ቀለባቸው የሚቆረጠው ከመንግስት ካዝና በሚወጣ እህልና ዘይት ነው ማለት ነው። ከዚህም ባለፈ የውሃና ከብቶች መኖ ጉዳይም ሌላው የመንግስትና የሀገሪቱ ፈተናዎች ናቸው።

 

መንግስት ከዚህም ባለፈ ድርቁ በከተማ ነዋሪዎች ላይ የኖሮ ውድነት ጫናን እንዳይፈጥር ሊሰራቸው የሚገቡ በርካታ ስራዎች እንዳሉ እሙን ነው። ፈተናው ይህ ብቻም አይደለም። የሀገሪቱ የእድገት መሰረት ግብርናው እንደመሆኑ መጠን የግብርናው ምርታማነት መውረድ በአጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ጫናንም እንዳያሳድር ማድረግ መቻልም ሌላኛው የኢህአዴግ መንግስት ፈተና ነው። የመንግስት ኤክሰፖርትና ኢምፖርት ገቢ ልዩነት የሰፋ እንደሆነ የታወቀ ነው። መንግስት የቁም እንስሳትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጪ በመላክ ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሬን እንደሚያገኝ ይታወቃል። ድርቁ በግብርና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ተፅዕኖን የሚያሳድር ከሆነ የመንግስትም የውጪ ምንዛሬ ገቢንም በዚያው መጠን መጉዳቱ አይቀርም። ከወጪ አንፃርም ካየነው መንግስት “የውጪ እርዳታ አቅራቢዎችን እገዛ ሳልጠይቅ በድርቅ ለተጠቁ ወገኖች እህል ገዝቼ አቀርባለሁ” ካለ ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሪን የሚጠይቀው ይሆናል። ይህም በአንድ መልኩ መንግስት ያለበትን የገቢና ወጪ ንግድ ልዩነት እንዳያሰፋው ስጋትን የሚያሳድር ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የተወሰኑ የልማት ፕሮግራሞቹንም ለማጠፍ የሚገደድበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል።

 

 እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ቀጣይ የኢህአዴግ የቤት ስራዎች ይሆናሉ። የኢትዮጵያ የተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እነዚህን ሁሉ ድርቅ አመጣሽ ውስብስብ  የኢኮኖሚ ተፅዕኖዎች መቋቋም ይጠበቅበታል። ፈተናው አሁን ነው። ከሜዳው ውጪ ቆመው የኢትዮጵያንና የመንግስቷን ፈተና ለማየት ያሰፈሰፉ በርካቶች ናቸው።  እርግጥ ነው፤ የኢትዮጵያ ተከታታይ የባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በተፈጥሮ ፊት ለመፈተን ተቀምጧል።

                                                 መልካም ፈተና

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1176 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us