የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በሕግ ይጠየቅልን!

Wednesday, 26 August 2015 13:57

በሰለሞን ሽፈራው

 

የዛሬው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የምትገኝበት አጠቃላይ እውነታ በፈርጀ ብዙ የለውጥ ንቅናቄ ላይ መሆኗን እንደሚያመለክት ድፍን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እየተገነዘበው ስለመምጣቱ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ይህ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ክብሯ የመመለስ ዓላማ ያለው ፈጣን የልማት ንቅናቄ ወይም የህዳሴ ጉዞ እውን ሆኖ ለማየት የበቃንበት መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ፤ መላው የሀገራችን ህዝቦች ለዘመናት የታገሉለትን የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ በማያሻ መልኩ እንደመለሰ የታመነበት ፌዴራላዊ ሕገመንግስት ፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉ ነው።

በግልጽ አማርኛ ለመናገር፤ ከሰማኒያ በላይ የየራሳቸው ቋንቋ፤ እንዲሁም ባህልና ሌላም ስነልቦናዊ እሴት ያላቸው ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሚገኙባት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ ይዞ የቆየውን የማንነት ጥያቄ፤ ለመመለስ ሲባል ተግባራዊ የተደረገው የፌዴራሊዝም ስርዓታችን፤ ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ያስቻለ ጤናማ የአብሮነት መንፈስ ከመፍጠሩ የተነሳ፤ ኢትዮጰያውያን እርስ በርስ ተፈቃቅደን፣ ብሎም ተፈቃቅረን ጭምር የምንኖርባትን የጋራ ቤታችንን (አገራችንን) ለማደስ እጅ ለእጅ ተያይዘን በድህነት ላይ እንዘምት ዘንድ ምክንያት ሆኗል።

ይህን ስል ደግሞ ከተራ የአፍቃሪ ኢህአዴግነት ስሜት በመነጨ ከንቱ ውዳሴ የስርዓቱን በጐ ገፅታዎች ይበልጥ ለማሰማመር ያህል ብቻ አይደለም። ይልቅስ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች በእርግጥም እርስ በርስ ተፈቃቅደንና ተፈቃቅረን ለመኖር የሚያስችል ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ያስቀመጥንበትን ሀገራዊ ቃል ኪዳን ማክበርና ማስከበር ካለብን፣ በትናንቱ የጋራ ታሪካችን የተፈፀሙ ስህተቶች እንዲደገሙ የሚጋብዝ ቸልተኝነትን ማሳየት አይጠበቅብንም የሚል ጽኑ እምነት ስላለኝ እንጂ።

በተለይም ደግሞ “ማታ ጨለማ ውስጥ አድፍጦ የመታህ እንቅፋት ጠዋት ላይም ከደገመህ አንተ ራስህ ከድንጋዩ አልተሻልክም” የሚያሰኝ አላስፈላጊ እንዝላልነት ጐልቶ የሚንፀባረቅበትን ታሪካዊ ስህተት ሲፈጽሙ የሚስተዋሉት፣ ለዚህች አገር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃኘት የሚበጅ ትውለድ እንዲቀርፁ እምነት የተጣለባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሆነው ሲገኙ አደጋው ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እንግዲያውስ እኔም ይህቺን ማስታወሻ ለመፃፍ የተገደድኩበት ዋነኛ ምክንያት፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችንም እጅግ አንጋፋውና ለኢትዮጰያውያን ህዝቦች ሀገራዊ ክብር መረጋገጥ ያለመ ሳይንሳዊ እውቀትን በመቅሰም ረገድ እንደ ፈር ቀዳጅ የሚቆጠረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፈፀመው ስህተት ነው።

ስህተቱ የፈፀመበት አግባብም በተቋሙ ስር የሚገኘው “የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ” የተሰኘ ክፍል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እያሳተመ ገበያ ላይ ካዋላቸው ታሪክ ቀመስ የአማርኛ ድርሳናት መካከል በተለይም “የሐበሻ ጀብዱ” የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፍ አማካኝነት ሲሆን፤ የስህተቱ አይነትና ይዘት ምን እንደሚመስል ደግሞ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ። ይህ የምላችሁ መጽሐፍ በ1928 የአድዋውን ሽንፈት ለመበቀል ስትል ፋሽስት ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ ያመዘተችውን ወራሪ ሠራዊት ለመመከት የተሰለፈው ኢትዮጵያዊ ታጣቂ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያደረገውን የመከላከል ሙከራና የገጠመውን ሽንፈት በሚያስቃኝ የጦርነት ውሎ ላይ የሚያጠነጥን ነው።

ጉዳዩን አስገራሚ የሚያደርገው ግን ይሄን “የሐበሻ ጀብዱ” የተሰኘ በ1928ቱ የጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ከወደ ኢትዮጵያ የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያወሳ መጽሐፍ የደረሰው አንድ ከምስራቅ አውሮፓ የመጣ የቼክ ሪፐብሊክ ዜጋ እንደሆነ መግለፁ ነው። ምክንያቱም ፀሐፊው ከዚያን ጊዜ በፊትም ይሁን በኋላ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ውስጣዊ ጉዳይ ይህ ነው የሚባል እውቀት የሌለውና የዱቼ ሙሶሎኒ ጣሊያን ሀገራችን ላይ ያወጀችውን ወረራ ሲሰማ ድንገት ብድግ ብሎ በጅቡቲ በኩል እንደገባ የሚናገር ሆኖ ሳለ፤ እንደዚህ ዓይነቱን ጥንቃቄ የሚሻ የውስጥ ጉዳይ አንስቶ ድርሳን መፃፉ የተአማኒነት ጥያቄ ያስከትላል።

በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለው እጅግ አወዛጋቢ የጦርነት ታሪክ ውስጥ የተፈፀሙ መሠረታዊ ስህተቶችን በውል ለይቶ በማውጣት አጥፊውን አካል የማሳወቅ ኃላፊነት መውሰድ ምን ያህል ስፋትና ጥልቀት ያለው የመረጃ ግብዓት ማሰባሰብን የሚጠይቅ ሚዛናዊ አቀራረብን መከተል ግድ የሚል ስራ እንደሚሆን ሲታሰብ፤ ይህ ለአገሩ ባዳ፣ ለሰው እንግዳ ስለመሆኑ ራሱው የሚነግረን ምስራቅ አውሮፓዊ ወታደር በጥቂት ወራት ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ዘምቶ በነበረበት አጋጣሚ የታዘበውን በፃፈበት “የሐበሻ ጀብዱ” ላይ የተስተዋለውን ጉልህ ስህተት መፈፀሙ እምብዛም ላያስገርም ይችላል። ደራሲው ወደ ሀገሩ ተመልሶ ከሄደ በኋላ፤ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየባቸው የወራት እድሜ፣ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግስት ጐን ተሰልፎ የፋሽስት ጣሊያንን ወራሪ ሠራዊት ሲዋጋ የፈፀመውን የጀግንነት ተግባር ቼካውያን ወገኖቹ እንዲያውቁለት ፈልጐ የጦር ሜዳ ውሎውን የሚተርክ ድርሳን በራሱ ቋንቋ መፃፉና ማሳተሙ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ይህን እጅግ አነካኪ ሊባል የሚችል ስህተት የተካተተበትን መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ እንዲታተም ማድረግ ግን ከማስተዛዘብም በላይ ሊያሳስበን ይገባል።

ምክንያቱም መጽሐፉ በዋነኛነት ያነሳው ርዕሰ ጉዳይ የጣሊያን ወረራና በአፄ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ ሥርዓት ትመራ የነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ላለማስደፈር ስትል ከበስተሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ዳር ድንበር ጥሶ የመጣውን አውሮፓዊ የቅኝ ግዛት ሠራዊት፤ ሞፈርቀንበሩን እየሰቀለ በዘመተ አርበኛ አርሶ አደር ለመከላከል በተለይም ትግራይ ውስጥ ያደረገችው ያልተሳካ ሙከራ ምን ዓይነት ገጽታ እንደነበረው ለማስረዳት ያለመ ትረካ ነው። መሰረተ ሀሳብ በሚተረክበት የጦርነት ውሎ ዙርያ የሚያጠነጥን እንደመሆኑ መጠን፤ ደራሲው “ማይጨው ላይ የመጨረሻውን የሽንፈት ጽዋ ለመጐንጨት የተገደድነው የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ (ራያና አዘቦዎች) ከጀርባችን ስለወጉን እንጂ በጣሊያን መንግስት ወታደራዊ ጥቃት ብቻ አይደለም” የሚል ማጠቃለያ የሰጠበት አግባብ እጅግ የተዛባ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።

የቼክ ሪፐብሊኩ ዜጋ ስለ ራያ ሕዝብ ትክክለኛ ማንነት ቅንጣት ያህል መረጃ እንደሌለውና አብረውት የዘመቱት የንጉሱ ባለሟሎች ሽንፈታቸውን በፀጋ ላለመቀበል ሲሉ የፈጠሩትን ሰበብ አምኖ በመቀበል ብቻ እንደፃፈው መገመት የሚቻለው ደግሞ ግለሰቡ “አረመኔዎቹና በጭካኔያቸው የሚታወቁት ራያና አዘቦዎች” እያለ በተደጋጋሚ አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያዋርድ ፍረጃውን ያቀረበበት ጋጠወጥ ሐተታው ሲነበብ ይመስለኛል።

በአጠቃላይ “የሐበሻ ጀብዱ” የተሰኘውን ታሪክ ቀመስ መጽሐፍ ያነበበ ማንኛውም ሰው ሊፈርድ የሚችለው ሐቅ ቢኖር፤ ራያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ኅብረተሰብ የሚለይበት ባዕድ አምላኪ ባህሪ እንዳለውና ከወራሪው የጣሊያን መንግስት ጋር አብሮ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን በመውጋት ሀገራችን ማይጨው ላይ እንድትሸነፍ ያደረገ ታሪካዊ በደል እንደፈፀመም ጭምር ነው ለመግለጽ የተሞከረበት። ይህ ብቻም ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊ ባህሉንና ማንነቱን ከማንም በተሻለ መልኩ ጠብቆ በመኖር የሚታወቀውን ያን ልበ ኩሩ የኅብረተሰብ ክፍል እንደአረመኔና ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት ሳያስፈልገው አምሳያ ወገኖቹን ለመግደል የሚሽቀዳደም እንደሆነ አድርጎ ያቀረበውም ጭምር ነው መጽሐፉ።

ከዚህ አኳያ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ካስተናገደቻቸው የጦር ሜዳ ሽንፈቶች መካከል አንዱና ምናልባትም ሚዛን የሚደፋው ከጣሊያን ዳግም ወረራ ጋር በተያያዘ የዱቼ ሙሶሎኒ ፋሽስታዊ ሠራዊት፣ በተለይም ማይጨው ላይ በተደረገ ውጊያ ዓለመ አቀፍ ሕግ የሚከለክለውን የ“ናፓል” ቦንብ፤ ወይም የመርዝ ጋዝ ከሰማይ ያዘነበበት እጅግ በጣም አሰቃቂ ጥቃት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ማለት ደግሞ በማይጨው ጦርነት እኛ ኢትዮጵያውያን የሽንፈትን ጽዋ ለመጐንጨት የተገደድነው፤ ሞፈር ቀንበሩን እየሰቀለ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንዲዘምት የተደረገው አርበኛ አርሶ አደር፤ በወቅቱ ዓለም ላይ አለ የሚባለውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የፋሽስት ጣሊያን ስልጡን ሠራዊት ለመመከት የሞከረበት ሁኔታ “የጎልያድና የዳዊት” ከሚባለውም የባሰ ወታደራዊ የኃይል አሰላለፍ አለመመጣጠን የተስተዋለበት ስለነበረ እንጂ በሌላ ተልካሻ ሰበብ አይደለም በሚል ሊጠቃለል ይችላል።

መላው የዓለም ማኅበረሰብ ስለዚያ አሳዛኝ የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነትና ስላስከተለው ፈርጀ ብዙ ጉዳት የሚያውቀው ታሪካዊ አቅም፤ የአድዋውን ቂም ለመበቀል ያለመ ሰፊ ዝግጅት አድርጎ የመጣው የወራሪው ሠራዊት የአፄ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ ስርዓት በእውር ድንብር አግበስብሶ ከዛተው ተራ ባላገር ጋር ፈጽሞ ለንጽጽር የማይቀርብ ወታደራዊ የበላይነት ስለነበረው እንደሆነ እንጂ፤ የራያና አዘቦ ሕዝብ የሀገሩን ሰዎች ክዶ ከበስተጀርባ ስለወጋቸው መሆኑን የሚያወሳ አይመስለኝም። ሌላው በዚህ አጋጣሚ መነሳሳት ይኖርበታል የምለው መሰረታዊ ጉዳይ ግን፤ ያኔ የጣሊያንን ተስፋፊነት የወለደው ዳግም ወረራ ለመከላከል ከመሀል አገር ወደ ትግራይ ምድር እንዲዘምት የተደረገው የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግስት ሠራዊት፤ በተለይም ራያ ቆቦ ላይ ለጥቂት ቀናት ያህል ሲቆይ የፈፀመው የግፍ ተግባር የአካባቢውን ህዝብ ክፉኛ ያስቆጣበት ሁኔታ እንደነበር የሚያመለክቱ የታሪክ መዛግብት መኖራቸው ሲሆን ፍሬነገሩም እንዲህ የሚል ነው…

በወቅቱ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመሩት የመሀል አገር ዘማች ወታደር ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ የሚወስደውን አውራ ጐዳና ወይም ዋናውን የጉዞ መስመር ተከትሎ ይሄድ ስለነበር፤ ራያ ቆቦ በመባል የሚታወቀውን አካባቢ ሲያልፍ አንድ ታጣቂ ድንገት ሞቶ ተገኘና ጠመንጃውን ለመውሰድ የፈለጉ ሁለት የአካባቢው ወጣት ወንዶች ሳይገድሉት እንዳልቀሩ የሚጠቁም መረጃ ተገኘ። እናም ይህ ጉዳይ የተነገራቸው የዘመቻው የበላይ አዛዥ የነበሩት ራስ ሙሉጌታ ይገዙ፤ እያንዳንዱ የሠራዊታቸው አባል የአካባቢውን ወንዶች ሁሉ በጅምላ እያሳደደ እንዲገድል ጥብቅ መመሪያ አስተላለፉ። በዚህ ምክንያትም ጦሩ ከቆቦ ከተማ እስከ አላማጣ ድረስ ያሉትን የራያ መንደሮች ያቋረጠው በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሐን ሰዎችን ተኩሶ እየገደለና እንዲሁም ለዘመቻው ያስፈልገኛል የሚለውን የህዝብ ሀብት ንብረት እንዳሻው እየመዘበረ ነበር።

ሠራዊቱ ስለ ጉዳዩ ምንም የሚያውቁት ነገር በሌላቸው ከሁለት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደዚያ ዓይነቱን የግፍ እርምጃ ሊወስድ የቻለው፤ የንጉሰ-ነገስቱ የጦር ሚኒስቴር የነበሩት ራስ ሙሉጌታ ይገዙ በሰጡት ትዕዛዝ እንደሆነ ሲሰማ በድፍን የራያ ራዩማ ሕዝብ ዘንድ (አዘቦና ቆቦ እንደማለት ነው) ከፈተኛ የመጠቃት ስሜት እንደተንፀባረቀና ለበቀል የተገፋፉ አንዳንድ ወጣቶችም መስተዋላቸውን የሚያወሱ የአካባቢው አዛውንቶች አሉ። ከዚህ የተነሳም የማይጨው ጦርነት በጣሊያን አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደመጣበት መመለስ የጀመረው የመሀል አገሩ ዘማች ወታደር የራያን መሬት አቋርጦ እንዳያልፍ ለማድረግ ባለመ የቁጣ ስሜት ተነሳስተው መንገድ ለመዝጋት የሞከሩ አንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች እንደታዩ ነው የሚታመነው።

ይሁን እንጂ “የሐበሻ ጀብዱ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተተረጐመው መጽሐፍ ላይ ያኔ የራያ ሕዝብ ለምን እንዳኮረፈና የመሀል አገሩን ወታደር ለመተናኮል እንደተገፋፋ እንኳን አልተጠቀሰም። ይህ የጐላ ስህተት የሚያረጋግጥልን ጉዳይ ደግሞ፤ ፀጉረ ልውጡ የውጭ ዜጋ፤ ምንም ነገር ሳያውቅ ድርሳን ለመፃፍ መነሳቱንና በተለይም ንጉሰ-ነገስቱ ሽንፈታቸውን በፈረደበት የራያ ህዝብ ላይ ለማሳበብ ፈልገው የተናገሩትን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ስለሰማ ብቻ እውነት ሳየመስለው እንዳልቀረ ነው።

እስቲ ለማንኛውም አዶልፍ ፓርለሳክ የተባለ ከምስራቅ አውሮፓዊቷ ሀገር ከቼክሪፐብሊክ የመጣ ፈረንጅ ጽፎት፤ ተጫነ ጀብሬ መኮንን ወደ አማርኛ በተረጐመው “የሐበሻ ጀብዱ” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ የራያ ህዝብ በከሃዲነት የተፈረጀበት አግባብ ምን እንደሚመስል አንባቢያን ልብ ትሉልኝ ዘንድ ቀንጭቤ ላቅርብና ከዚያም ወደየማጠቃለያ ሀሳቤ አልፋለሁ። ስለሆነም በመጽሐፉ ገጽ 294 የተተረከውን አንድ አንቀጽ ቃል በቃል እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁና አብረን እንመልከት።

“… በዚያች ቅጽበት ደግሞ ዓድዋ ሊደግም የሰዓታት ልዩነት ሲቀረው ከእነዚያ ከሃዲዎች ራያዎችና አዘቦዎች ድልን በእጁ ሊያስገባ የተቃረበውን የገዛ ወንድማቸውን ከጀርባ ገብተው ጨፈጨፉት። ድልን በእጁ ሊጨብጥ ወደፊት የገሰገሰውን የእናታቸውን ልጅ ድል ነሱት። አዎን ዛሬ እነዚያ ከሃዲዎች ጦርነቱን ወስነውታል። ታሪክም ሰርተዋል። ታሪኩ ግን የክህደት ታሪክ ነው። ለሰላሳ ሽልንግና ለአዲስ የጣሊያን መሳሪያ ባንዳነት አድረው የገዛ ወንድሞቻቸውን ከድተዋል” እያለ የፈረደበትን ሕዝብ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጐ ይሰድበዋል።

እንግዲያውስ እኔም እንደ አንድ ከዚያ ሕዝብ የተከፈለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይህ ሆነ ተብሎ ራያዎችን ጥላሸት ለመቀባት ሲባል በአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ባለሟሎች ደባ የተቀነባበረ እንጂ ፈጽሞ እኛን የሚገልፀን ታሪክ አይደለምና አምርረን ልንቃወመው ይገባል ነው የምለው። ስለሆነም ከቀዳማዊ ወያነ የአመጽ ንቅናቄ ጀምሮ የንጉሱን ዘውዳዊ አገዛዝ በመቃወምና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን በመጠየቅ ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች የፀረ ጭቆና ትግል ፈር እንደቀደደ ታሪክ የመስከረለትን ኅብረተሰባችንን፤ በዚህን ያህል አስነዋሪ ውንጀላ ከሃዲ አድርጐ የሚፈርጅ ያሳተመው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ሕግ ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅልን የአካባቢው ተወላጆች በአንድነት ድምፃችንን ማሰማት ይጠበቅብናል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

ግልባጭ

ለደቡብ ትግራይ ዞን መስተዳደር፣ ማይጨው፤

ለራያ አዘቦ ወረዳ አስተዳደር፣ መኸኒ፤

ለራያ አላማጣ ወረዳ አስተዳደር፣ አላማጣ፤

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1412 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us