የአዕምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ወገኖቻችን ትኩረት ሊያገኙ ይገባል!

Wednesday, 16 September 2015 14:10

በዲ/ን ኒቆዲሞስ

 

ከወር በፊት የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር Ethiopian National Association on Intellectual Disabilities “እኛም እንችላለን!” በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ባደረገው ዓመታዊ በዓል ላይ ተገኝቼ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ልጆችና ቤተሰቦቻቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና የጥበብ ሰዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶችም ተገኝተው ነበር።

በዚህ በዛሬው አጠር ያለች ትዝብት አከል ጽሑፌ በዕለቱ የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ አከናውኖት በነበረው ዓመታዊ በዓልና በአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ባለባቸው ወገኖቻችን ዙርያ ጥቂት አሳቦችን ለማንሳት ወደድኹ።

ጽሑፌን ካነሣሁት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ባለው አንድ ገጠመኜ ልጀምር። ከጥቂት ዓመታት በፊት በእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት የጠበል ሥፍራ አንድ ዕድሜው በሠላሳዎች አጋማሽ አካባቢ ከሚገኝ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ካለበት ትሑት ወጣት ጋራ ተዋውቄ ነበር። ታዲያ የዚህ ወጣት የኑሮ ኹናቴ ውስጤ ጥያቄ ፈጠረብኝና ላነጋግረው ወሰንኩ። ምንም እንኳን ይህ ወጣት እምብዛም ለመነጋገር ባይችልም ቤተሰብ እንዳለውና ቤተሰቡም ቦሌ አካባቢ የሚኖሩ ባለጠጋዎች እንደሆኑና ወደዚህ ከመጣም አምስት ዓመታትን ያህል እንዳስቆጠረ እየተኮላተፈ ነገረኝ።

ወጣቱ በጥሩ ምቾት የተያዘ እንደሆነ ተክለ ሰውነቱና ገጹ ይመሰክራል። ቤተሰቦቹ አንድ ሙሉ ግቢ ተከራይተውለት በዛ ባማረ ግቢ ውስጥ ከሚንከባበከበው የአንድ የገጠር ሰው ከሆነ ጎልማሳ ጋራ ነው አብሮ የሚኖረው። ከዚህ ወጣት ጋራ የነበረኝን ጨዋታ ለአፍታ ገታ አድርጌ በቂ ሆነ መረጃ ለማግኘት በማሰብ እንክብካቤ የሚያደርግለትን ጎልማሳ አነጋገርኩት። እርሱም የወጣቱ ቤተሰቦች የቅርብ ዘመድ እንደሆነና ለእርሱም ዘመዱና ወገኑ የሆነውን ይህን ወጣት ለመንከባከብ በደመወዝ የተቀጠረ እንደሆነ አጫወተኝ። ምግብ ከማብሰል ጀምሮ ሁሉንም እንክብካቤ ለዚህ ወጣት የሚያደርግለት ይህ ሰው ነው።

ታዲያ በጨዋታችን መካከል ጎልማሳው ሰውዬ ወዲያውም ስሜቱ ደፈረሰበትና፣ “አያ እንደው ምን ያለ ጉድ፣ ምን ያለ መዓት ነው አምላኬ ያሳየኝ። እንደው ይሄ ሁሉ ዎስፒታል ባለበት ከተማ እንደው ሐኪሞቹ ለዚህ በሽታ አንዳንች መፍትሔ መላ ጠፍቷቸው ነው ይህን የመሰለ ጀግና እንዲህ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች የሆነ ኑሮ የሚኖረው።” ሲል በአግራሞት ተሞልቶ ጠየቀኝ። ኀዘንና ምሬት፣ ቁጭትና ብሶት ባጠላባት ጨዋታችን መካከል ይህን ሰው ቢረዳኝም ባይረዳኝም በሚል ስሜት ውስጥ ሆኜ ቢያንስ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት መዓት ወይም የፈጣሪ ቁጣ እንዳልሆነ ግን ላስረዳው ሞከርኩ። አስከትዬም ለችግሩ የተጋለጡ ሰዎች ተገቢው የሕክምና ድጋፍና ክትትል ከተደረገላቸው፣ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከማኅበረሰቡ ፍቅርና እንክብካቤ ካገኙ በጤናቸው ላይ መሻሻል እንደሚያሳዩ ነገርኩት።

እንግዲህ ልብ በሉ ይህ ሰው ሁሉ የሞላቸው ቤተሰቦች፣ የሥጋ ወንድሞችና እህቶችም ያሉት ወጣት ነው። ግን ቤተሰቦቹ ይህን ልጃቸውን ከራሳቸው ጋራ አድርገው ሊንከባከቡት አልፈለጉም። በትክክል ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ለመገመት ቢያስቸግርም ግና አንድ ነገር ግን ማለት የሚቻል ይመስለኛል። እነዚህ ቤተሰቦች የዚህ ልጃቸውን ችግር በማየት መጨነቅ፣ መሳቀቅና ከግንዛቤ እጥረት ምክንያት ከጎረቤትና ከዘመዶቻቸው የሚመጣባቸውን ሐሜትና ትችት በመፍራት ‹‹ጠበል ቢቀመጥ ይሻለዋል” በሚል ሰበብ ከወንድምና እህቶቹ፣ ከዘመድና ከወገን ለይተው ብቻውን ራቅ ብሎ እንዲኖር ወስኑበት። የሚያሳዝነው ይህ ወጣት ከዓመታት የብቸኝነት ኑሮ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ለመመለስ የቻለው የማይቀረውን የሞት ጽዋ ከተጎነጨና ይህችን ምድር ከተሰናበተ በኋላ ነበር።

የአእምሮ ዕድገት ውሱንነትም ይሁን በሌላ የአካል ጉዳተኞች በሆኑ ወገኖቻችን ላይ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰባችን ድረስ ያለውን የተዛባውን ግንዛቤ በማስተካከል ረገድ ለውጥ ለማምጣት ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ግልጽ ነው። ዛሬም ድረስ የአካል ጉዳተኝነትን የፈጣሪ ቁጣና መዓት፣ መርገም፣ ኃጢአትና ቅጣት እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች በርካታ ናቸው። ይህን የተዛባ አመለካከት የከፋ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ ሰዎች ይህን የተዛባ አመለካካታቸውን በተጎጂዎችና በተጎጂ ቤተሰዎቻቸው ላይ በማንጸባረቅ በግልና ማኅበራዊ ሕይወታቸው ላይ ጫና በመፍጠር፣ ለሌላ የጤና እክል፣ ለሌላ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ እየዳረጓቸው መሆናቸው ነው።

በዚሁ የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር ዓመታዊ በዓል ላይ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለበት ወላጅ እናት የሆነች እናት ከመድረክ በስተጀርባ ሆና ያቀረበችው፣ ብሶት፣ ኀዘንና ቁጭት ተቀላቀለበት የብዙዎችን ልብ የነካና ያሳዘነን ግጥም አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ገና ማኅበረሰባችን መካከል ያለውን አመለካከት ለመቀየር ብዙ መሥራት እንዳለብን ያለመላከተ ነው። ይህች እናት ልጇን ይዛ በገባችና በወጣች ቁጥር ከጎረቤቶቿ የሚደርስባት ሐሜት ምን ያህል ጀርባውን እንዳጎበጠውና ቅስሟን እየሰበረው እንዳለ የገለጠችበት ግጥሟ የብዙዎችን ልብ የነካ ነበር፡  

ከላይ በጽሑፌ መግቢያ ላይ ያነሣኹት አሳዛኝ ገጠመኜም ሆነ የዚህች እናት ሰቆቃ፣ ምሬትና ብሶት የአእምሮ ዕድገት ውሱንነትም ሆነ በአጠቃላይም በአካል ጉዳተኞች የኅብረተሰባችን ክፍሎች ላይ ላለው የተዛባ አመለካከት አንድ ጥሩ ማሳያ ነው። በየጓዳውና በየቤቱ ተደብቀው ያሉ ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮችን እናንሳ ቢባል በጣም በርካታ ናቸው።

በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ ምሕረት፣ በመዲናችን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ለሥራ በሚዘዋወሩበት ጊዜ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ሕፃናትና ታዳጊ ልጆች በቤተሰቦቻቸውና በማኅብረሰቡ መካከል ከግንዛቤ ማነስ በሚደርስባቸው አድሎና መገለል፣ ወላጆቻቸው ካለባቸው ከከፋ ድህነትና ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ያጋጠሟቸውን አሳዛኝና ልብ የሚነኩ የሥራ ላይ ገጠመኞቻቸውን ኀዘን በተቀላቀለበት ስሜት አንስተውልን ነበር።

ለዓመታት ፀሐይ ብርሃን እንኳን ለማየት ተነፍገው፣ በአልጋ ላይና በግንድ ላይ ታስረው የሚውሉ ከዚህም የተነሣ ደግሞ አካላቸው ልምሾ ሆኖ፣ ቆዳቸው ገርጥቶ፣ የዓይናቸው ብርሃን ፈዞ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ ተገልለው፣ ለሰዎችና ለውጪ ሕይወት እንግዳና ባይተዋር ሆነው የሚኖሩ ልጆች እንዳጋጠሟቸው አንስተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እነዚህ ወገኖቻችን በቤተሰብም ሆነ በማኅበረሳበችን መካከል ተገቢው የሆነ እንክብካቤና ፍቅርን በመነፈጋቸው ምክንያት ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለአስገድዶ መደፈር የተጋለጡ፤ በዚህም ምክንያት ለአላስፈላጊ እርግዝና፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ ኤች አይ ቪን ጨምሮ ለሌሎች የተለያዩ በሽታዎች የተዳረጉ መሆናቸውን በንግግራቸው ወቅት ገልጸው ነበር።

በእነዚህ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ባጋጠማቸውም ሆነ በአጠቃላይም በአካል ጉዳተኞች ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን አካላዊ ጥቃት፣ መገለልና የመብት ጥሰት በተመለከተ መንግሥት ተገቢውን የሕግ ከለላና ጥበቃ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ከቀድሞው ዘመን በተሻለ ኹናቴ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች መመዝገባቸው እውነት ነው። እ.ኤ.አ. በ2006 የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቀበል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት በ፳፻፪ ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት በዐዋጅ አጽድቆታል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር መስሪያ ቤትም The Ethiopian National Plan Action of Persons with Disabilities 2012-2021 በሚል ባቀረበው ሰነድ ላይ እ.ኤ.አ. እስከ 2021 ድረስ በአገራችን ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች መብታቸው ተጠብቆላቸው፣ የትምህርት፣ የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነታቸው ሙሉ በሙሉ ዕውን የሚሆንበትን ሥራ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ድርጅቶችና ተቋማት ጋራ በመሆን፣ በትብብር በመሥራት ላይ እንደሆነ ሰነዱ ይጠቁማል። ከዚህ ጋርም ተያይዞ ወላጆችና ማኅበረሰቡ፣ ፖሊስና የፍትህ አካላትም በአንድነት በመቀናጀት እየሠሩ ያለው ሥራም ነገን የተሻለና ብሩህ እንደሚያደርገው ይታሰባል።

እንደ ትምህርት ሚ/ር ያሉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ላለባቸው ዜጎች የልዩ ድጋፍ ትምህርት/Special Needs በማቋቋም፣ በዚህ ዘርፍም መምህራንን በማሠልጠን የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ትምህርት ሚ/ር እነዚህ ወገኖቻችን የመማር መብታቸው ተጠብቆላቸው፣ ትምህርትና የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን የሚያገኙበትን ዕድል በማመቻቸት ረገድ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን መጥቀስ ያለብኝ ይመስለኛል። በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ የተገኙት የትምህርት ሚ/ር ተወካይም መስሪያ ቤታቸው የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ላለባቸውም ሆነ በአጠቃላይም ለአካል ጉዳተኛ ዜጎች ዙርያ የትምህርት፣ የሙያ ሥልጠና እና ልዩ ድጋፍ የሚያገኙበትን ዕድል ለማመቻቸት በሰፊው እየሠራ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

በመንግሥትም ሆነ በሌሎች የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አበረታች ቢሆኑም ከችግሩ ስፋት ጥልቀት አንፃር ግን አሁንም ለአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ላለባቸው ወገኖቻችን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ረገድ በሰፊው መንቀሳቀስ እንዳለብን ግን የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይመስለኝም። ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብና የመንግሥት አካላት ድረስ ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት መወጣት እንዳለብን ልንዘነጋው አይገባም። እነዚህ ወገኖቻችን አስፈላጊው የሕክምና ድጋፍ፣ ፍቅርና እንክብካቤ ከተደረገላቸው ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን መጥቀም ማይችሉበት መንገድ አይኖርም።

በብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶቹ ዓለምን ያስደመመውና ያስደነቀው አሜሪካዊው ቶማስ ኤዲሰን የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለበት ልጅ መሆኑንና በሕይወት የመቆየት ዕድሉም ብዙ እንዳልሆነ እኮ ሐኪሞች ለወላጆቹ ነግረዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቶማስ ኤዲሰን ካገኘው የሕክምና ክትትል፣ ቤተሰባዊ ፍቅርና እንክብካቤ ችግሩን በመቋቋም በብዙ ግኝቶቹ ዓለምን ያስደነቀ ሰው ለመሆን በቅቷል። በዓለማችን ያሉ ጥቂት ማይባሉ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸውና የአካል ጉዳተኞች እንችላለን በሚል ጽኑ የሆነ ጠንካራ መንፈስ ያሉባቸውን ችግሮች ተቋቁመው ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ለሌሎች የመንፈስ ጽናትና ብርታት ምንጭና ተምሳሌት በመሆን የዓለማችንን ታሪክ መቀየራቸውን መዘንጋት የለብንም።

በብሔራዊ አዳራሽ ዓመታዊ በዓል ላይ ባገኙት ሙያዊ ድጋፍና ሥልጠና በመታገዝ ልዩ ልዩ ተሰጦአቸውን በመድረክ ላይ በማቅረብ ብዙዎቻችንን ያስደመሙንና ያስደነቁን፣ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችንና ምርቶቻቸውን በበዛር መልኩ ያቀረቡልን የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ወገኖቻችን በእርግጥም ፍቅርና እንክብካቤ ካገኙ፣ የትምህርትና የሥልጠና ድጋፍ ከተመቻቸላቸው ራሳቸውንም ሆነ ወገናቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊሰመርበት ይገባል። ስለሆነም ከቤተሰብ ጀምሮ ሁላችንም ማኅበረሰባችንና መንግሥት የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ላለባቸው ወገኖቻችን ተገቢውን ትኩረት፣ ፍቅርና እንክብካቤ እንዲያገኙ የበለጠ መሥራት ይገባናል የመሰናበቻ መልእክቴ ነው።

ሰላም!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
916 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 952 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us