ለወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፡- እንደእነ አቶ ግርማ ያሉት የሐሰት መምህራንና አጥማቂ ነኝ ባዮች ሊጋለጡና ወደ እውነት መንገድ ሊመለሡ ይገባቸዋል!!

Wednesday, 07 October 2015 14:51

 

 

በዲ/ን ኒቆዲሞስ

‹‹… በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተ ክህነቱ ተቋም ዝም ቢልም መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን የማኅበረሰቡን አብሮነትና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚንድ የእነ አቶ ግርማ ዓይነት ያለ አጥማቂ ነን ባዮችን፣ የኢትዮጵያ ቤ/ን የማይወክሉና የማታውቃቸውን ግለሰቦችን እኩይ ሥራን እያየና እየሰማ መታገሥ አለበት ብዬ አላስብም። ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታ እኚህን ሰውና መሰል ግለሰቦችን ሊያስቆም፣ በሕግም ሊጠይቃቸው ይገባዋል ባይ ነኝ …።››

ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል በቤተ ክርስቲያናችን ስላሉ አጥማቂ ነን ባዮች፣ ሐሣይ መሢሕዎች ላይ የጻፈው ጽሑፍ ብዙዎችን እያነጋገረ እንደሆነ ሳንታዘብ እንዳልቀረን እገምታለኹ። በዚህ ጽሑፍህ ላይም በመጦመሪያ መድረኩና በተለይም ደግሞ በሶሻል ሚዲያው የስድብ፣ የውግዘት፣ የርግማን መዓት እንዳስተናገደ ታዝበናል። አንድ ጸሐፊም ይህ የዲ/ን ዳንኤል ጽሑፍህ አጥማቂውን አቶ ግርማን የተመለከተ መሆኑንም ከግንዛቤ በማስገባት የሰጠውን ምላሽ የ‹‹ዘሐበሻ ገጸ-ድር›› አስነብቦናል።

ከኢትዮጵያ እስከ ሰሜንና ደቡብ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካና ካናዳ ድረስ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለጋሽ ግርማ ፍጹምነት፣ ታላቅነት፣ ጻድቅነት፣ የፈውስ ስጦታና  ገቢረ ተኣምራት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ጥብቅናም ቆመዋል፤ ይሄን ያህል ደጋፊና ተከታይ አላቸው ማለት ነው፤ በእውነት አስገራሚ ነው!!

ነገርዬው ከመገረምም አልፎ እጅጉን የሚያሳዝንና ምእመናችን ምን ያህል በክህደትና በስህተት አሠራር ተጠላልፎ የወደቀ፣ ልክ እንደ ነነዌ ሕዝብ ግራና ቀኙ መለየት ያቃተው፣ ምልክትን የሚሻ፣ ተኣምራትን የሚያሳድድ ትውልድ እንደሆነ የሚያሳየን ነው። በመሠረቱ ዳንኤል በእነዚህ አጥማቂ ነን ባዮች የቅዱስ ወንጌል ጠላቶች፣ ሐሰተኞች፣ ከሃዲዎች፣ አጭበርባሪ ነጋዴዎች ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም። በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ የነበሩና አሁንም መልካቸውንና አካሔዳቸውን ቀይረው የተከሰቱ ናቸው።

የእኚህን አጥማቂ ነኝ ባይ የአቶ ግርማን ቪዲዮ በመጀመሪያ ጊዜ ያየኹት ለትምህርት ደቡብ አፍሪካ በነበርኩበት ወቅት ነበር። በዚህ ቪዲዮ እጅጉን ነበር ያዘንኩት። እንዲያ ያን ምስኪን ምእመን ሰብስበው ድራማ ሲሰሩበት ሣይ ልቤ ተነክቷል። እንዴት እንዲህ ዓይነቱ የጥፋት ርኩሰት በቤተ ክርስቲያናችን አውድ ምሕረት ላይ ያለ ምንም ከልካይና ሃይ ባይ ብዙዎችን እያሳተና እያሳሳተ እንደ ይሁዳ የገንዘብ ከረጢታቸውን ሲሞሉ አባቶችና ቅዱስ ሲኖዶስ እንዴት ዝም ይላሉ ብዬም ነበር።

ቅዱስ ሲኖዶስ ዘግይቶም ቢሆን እኚህ ሰው እንዳያጠምቁ ትእዛዝ ቢያስተላልፍም ልባቸውና ዓይናቸው በገንዘብ የታወረ የአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ገቢያችንን ይጨምሩልናል፣ ምእመናኑን ይስቡልናል በሚል እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና አድባራት እየተዘዋወሩ እያጠመቁ ነው። የእኚህ አጥማቂ ነኝ ባይ ይህ አገልግሎታቸውም ከኢትዮጵያ ምድር አልፎ ወደ ባሕር ማዶም ተሻግሮ በርካታ የዋህ ምእመናን እያሳሳተና ወደ ክህደት መንገድ እየመራ ነው።

መቼም በቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነቱ ርኩሰትና ዓመፃ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ እንደሆነ ትስተዋለህ ብዬ አልገምትም። የግብጽን ጥበብ- አስማትን፣ ሟርትንና ድግምትን ከአብነት ትምህርቱ ጋራ ጎን ለጎን ተምረው አጋንትን የሚጎትቱና ሙታንን የሚስቡ፣ ከዓውደ ነገሥት እስከ መርበበተ ሰለሞንና መልከአ ሳጥናኤልን የሚደግሙና በዚህ ሥራቸውም እጅግ የሚፈሩና አንቱታንና ከበሬታን ያተረፉ ደባትራን እንደነበሩ  ታሪካችን ይነግረናል። ድማሙ ብዕረኛ መንግሥቱ ለማ ‹‹ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ›› በሚል በተዉልን የአባታቸው ማስታወሻ ላይ አንድ የተከበሩ መምህር ይህን የሰይጣንን ጥበብ የተማሩ ተማሪዎች በላኩባቸው አይጥ መንጋ በቁማቸው ተበልተው መሞታቸውን መጽሐፋቸው ያትታል።

እንደውም አለቃ ለማ እነዚህን ይህን ክፋት የሚማሩ ተማሪዎችና ደባትራንን እንዳይቀርቧቸው በግልጽ ይቃወሟቸው እንደነበር ይህ መጽሐፍ ያትታል። አስገራሚው ነገር ይህን የአጋንትን ሥራ የሚሠሩ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሚሳተፉ፣ ማሕሌቱን የሚያደምቁ፣ የሚከበሩና የሚፈሩ መሆናቸው ነው አሳዛኙ እውነታ።

ዳኒ እንደ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይነትህና ተቆርቋሪነትህ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ትንሽ አልዘገየኹም ብለህ አታስብም? ስንቱ ነው እናጠምቃችኋለን፣ ለበሽታችሁና ለችግራችሁ ፍቱን መፍትሔ አለን በሚሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ጥላ መከታ አድርገው የስንቱን ቤት ያፈረሱትን፣ ትዳር የበተኑትን፣ አእምሮአቸውን ያሳጡትን፣ ብኩንና እብድ አድርገው ያስቀሯቸውን ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠራቸው።

አሳዛኙ ነገር ይህን የአጋንንት ሥራ ከመማርና ከመለማመድ አልፈው በሌሎች ላይ የሚሞክሩ፣ ይህን የክፋት ሥራ የሚያስፋፉ በጵጵስና ደረጃ ላይ ሣይቀሩ ያሉ አባቶች መኖራቸው ደግሞ ልብን በኀዘን የሚሰብር ነገር ነው። ይህ ትውልድ እንዲህ ዓይነቱን አጋንታዊ አሠራር ሊቃወመው ይገባዋል። ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውቀት የሌላቸው፣ ቁጭ ብለው ከመማር ይልቅ በዙረት ዕድሜያቸውን የፈጁ፣ ትዳራቸውን የፈቱ፣ ኑሮ ያልተሳካላቸው፣ ወታደሮችና ጨዋዎች ኹሉ ከመርካቶ ቆብና ቀሚስ እየገዙ በመልበስ የዋህ ምእመናኑን እንዲህ መጫወቻ ሲያደርጉት ዝም ማለት አለብን እንዴ … አይመስለኝም … ?!

እንዴት ሰው በሰለጠነ አውሮፓና አሜሪካ ባሉ ዓለማት ነገሮችን ኹሉ በሎጂክና በምክንያት በሚቀበል ራሽናል በሚባል ማኅበረሰብ መካከል እየኖረ ቢያንስ እምነት እንኳን ቢጎድለው እንዴት እንደ ባለ አእምሮ እንዲህ ዓይነቱን የለየለት ማታለል፣ ድራማና ማጭበርበር መለየት ይሣነዋል። በቅርቡ ያየኹት የእኚህ ሰው-የአቶ ግርማ ቪዲዮ ላይ አንድ የናሳ ሳይንቲስት ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ወንድማችን በእርሳቸው ጥምቀት ሲናዘዝ አይቼ እጅጉን አዘንኩ። ይህ ሰው እንኳን የናሳ ሳይንቲስት ሊሆን ቀርቶ በዚህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ በር ማለፉን እንኳን ያጠራጥራል።

ለዚህ ሰው አጥማቂ ነኝ ባዩ አቶ ግርማ ባደረጉለት ኢንተርቪው ላይ ክፉ መንፈስ ለምን አበሾች ላይ ብቻ ትበረታህ ተብሎ ሲጠየቅ፡- ‹‹አይ አንተ ደግሞ ፈረንጆቹ እኮ ኹሌም የእኛ ናቸው የት ያመልጡናል ብለህ ነው?! ደግሞ ፈረንጆቹ ምንም አያውቁም አልጫ ነገር ናቸው …።›› ይህን ነው የናሳው ሳይንቲስት ነኝ ባይ ተጠማቂ ቃል በቃል የተናገረው… የሚገርመው በቪዲዮው ላይ ተደጋግሞ ይህ ሰው የናሳ ሳይንቲስት መሆኑ ነበር ሲነገር፣ ሲሰበክ የነበረው። ይህ ደግሞ ለምን እንደሆነ የታወቀ ነው። ምእመናን የእኚህ ሰው ገቢ ተኣምራታቸው ወደተከበረው ተቋም ወደ ናሳ የጠፈር ምርምር ማእከል እንኳን ድረስ ሣይቀር ዘልቆ የገባ ነው የሚል የጭንቅላት ጨዋታ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

ዳኒ ብትችል ቤተ ክርስቲያናችንን ተጠግተው ይህን የዋህ ምእመናን በማታለል ላይ ያሉትን አቶ ግርማንና ሌሎች እርሳቸው መሰሎችን ነጋዴዎችንና አጭበርባሪዎችን በማጋለጥ ተከታታይ ጽሑፎችን ብታስነብበን በእውነት ነው የምልህ ይህን ምእመናን ከሐሰተኞች መምህራንና ሐሣይ መሢሕዎች ትታደጋለህ። ከማንም ይልቅ አንተ በዚህ ጉዳይ መጻፍህ ብዙዎችን እንደሚያንቀሳቅስና እንዲሚያነቃቃ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን ደግሞ በሰሞኑ ጽሑፍህ እንደተገነዘብከው ተስፋ አድርጋለኹ።

መጽሐፍ፡- ‹‹በሰው ልማድ ምንም እንኳን የምንመላለስ ብንሆን እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፣ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው። የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ኹሉ እናፈርሳለን፣ ለክርስቶስ ለመታዘዝ አእምሮን ኹሉ እንማርካለን፣ መታዘዛችሁ በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ደግሞ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።›› እንዲል። (፪ቆሮ. ፲፣፫-፮)

እንግዲህ ዳኒ እንደ መጽሐፉ ቃል ይህን የአጋንትንንና የሰው ልጅ ጥልቅ አእምሮ የፈጠረውን አሳብና የክፋት አካሔድ/ክፉ የጨለማ ሥራ ማፍረስና እነዚህን ሰዎችንም ወደ ክርስቶስ መንግሥት መማረክ፣ አለመታዘዝን ደግሞ ለመበቀል የመንፈስ ሰይፍ የኾነው ቃለ እግዚአብሔር በእጃችን እንዳለ የሚያስረዳን ኃይለ ቃል ነው። እናም ዳኒ በዚህ በጀመርከው የጨለማውን አጋንንታዊውንና የሰው ልጅን አእምሮ የክፋት ሥራ ማፍረስና ማጋለጥ እንድትቀጥልበት ታናሽ ወንድምህ አደራ እልኻለሁ።

ወንድማችን ብትችል የእኚህን ሰው ተከታታይ ቪዲዮቻቸውን እየመረመርህ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ጋራ በማነጻጸር ትንታኔ በመስጠት ብትተቸው መልካም ይሆናል። ልክ ባለፈው ጽሑፍህ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አልወጣ ያለ አጋንንት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም መውጣቱን ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ አንጻር ይህ መናፍቅነት/ክህደት መሆኑን እንደለጽከው ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ከእውቀትና ከእውነት የጎደሉ ሰዎች ናቸው ምእመኑን እያሳቱት ያለው።

ትዝ የሚለኝ ባህታዊ ገ/መስቀል ዝናቸው በገነነበት ዘመን ልጅ ሆነን አንድ ጊዜ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምሩ ‹‹ጂሆቫ ማለት ጅብ ማለት ነው።›› እነዚህ የሖዋ ምስክሮች/ጂሆቫዎች የስማቸው ትርጉም ጅብ ነው የሚለውን ትምህርታቸውን በኋላ ነፍስ አውቄ ‹‹ጂሆቫም ሆነ ይሖዋ›› እስራኤላውያን እጅግ የሚያከብሩትና በዘመኑ የነበሩ አይሁዳውያን ጸሐፍትም ይህን የአምላካቸው ስም ሲጽፉ በታላቅ ፍርሃት በመንቀጥቀጥና በመቆም በልዩ ወርቃማ ቀለም እንደሚጽፉት ከእውነተኛ መምህራን በተረዳሁ ጊዜ አለማወቅ፣ ማይምነት ምን ያህል ሕዝባችንና ሳይማሩ እናስተምራለን በማለት የተነሡ ወገኖቻችንን ከእውነት መንገድና ሕይወት እንዳጎደላቸው ሳውቅ ከልቤ ማዘኔን አስታውሳለኹ።

ወንድሜ ዳንኤል እባክህ ይህን ጽሑፍህን ቀጥልበት፣ ከኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ፣ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ ሣይቀር ዘልቆ ምእመኑን እውነትና ሕይወት ከሆነው ከቤተ ክርስቲያናችን መንገድና አስተምህሮ እያወጣ ያለውን የሐሰት ትምህርትና ሐሳይ መሢሕዎችን አጋልጥልን። አቶ ግርማ ያለ ምንም ቅድመ ኹናቴ ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እያደረጉት ያለውን የክህደት አስተምህሮአቸውን፣ ልምዳዳቸውንና የለየለት ንግዳቸውንና ዝርፊያቸውን ትተው ወደ እውነተኛይቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ እንዲመለሱ ሊነገራቸውና ሊገሠጹ ይገባቸዋል።

በተጨማሪም እኚህ ሰው አጠምቃችዋለኹ የሚሏቸውን ሰዎች ኹሉ እከሌና እከሊት፣ ዘመድህ፣ ጓደኛህና የትዳር አጋርህ አስደግሞብሻል፣ አስደግሞብኻል፣ አስመትቶብሻል፣ አስመትቶብኻል በሚል በኅብረተሰባችን መካከል ለዘመናት የቆየው ማኅበራዊ መስተጋብር፣ አብሮነት፣ መተማማመንና መተዛዝን በማኅበረሰባችን መካከል እንዲዳከምና እንዲጠፋ እያደረጉ እያሉ መሆናቸው ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባዋል። እናም የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁራንና ማኅበረሰቡ ይህን እርስ በርሳችን ያለንን ፍቅር፣ መተማመንና መተሳሰብ እየሸረሸረ ያለውንና እርስ በርስ በጠላትነት እንድንተያይ እደረገ ያለውን የአደባባይ ሸፍጥ፣ የማኅበረሰባችንን አንድነት ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውንና እየተናደ ያለውን መልካም እሴታችንን ለመጠበቅ በጋራ መነሣት ያስፈልገናል ብዬ አስባለሁ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተክህነቱ ተቋም ዝም ቢልም መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን የማኅበረሰቡን አብሮነትና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚንድ የእነ አቶ ግርማ ዓይነት ያለ የኢትዮጵያ ቤ/ን የማይወክሉና የማታውቃቸውን ግለሰቦችን እኩይ ሥራን እያየና እየሰማ መታገሥ አለበት ብዬ አላስብም። ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታ እኚህን ሰውና መሰል ግለሰቦችን ሊያስቆም፣ በሕግም ሊጠይቃቸው ይገባዋል ባይ ነኝ።

አበቃሁ!! ሰላም!!¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1417 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us