የአገራችንና የክልላችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚመለከት በዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት የተሰጠ መግለጫ

Wednesday, 07 October 2015 14:52

 

የዓረና ትግራይ የሥራ አስፈፃሚ አባል ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባና የማ/ኮሚቴው ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ ከነሃሴ 30/2007 - ጳጉሜን 2/2007 ዓ/ም ያካሄዱ ሲሆን በግንቦት 2007 ዓ/ም የተካሄደው አገራዊ ምርጫና የዓረና እንቅስቃሴ እንዲሁም የክልላችንና የአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታዎች በመገምገም ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ትግልን የበለጠ ተጠናክሮ እንዲካሄድ የሚረዱ ውሳኔዎች አሳልፏል።

የ2007 ዓ/ም  ምርጫ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ከምርጫ በሃላም የዘለቀ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርጫው በእስራት ድብደባና በሞት ታጅቦ መፈፀሙ በምርጫው ህወሓት/ኢህኣዴግ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን የፖሎቲካ ተቃዋሚዎችን ጠላቶቼ ናቸው በገቡበት ገብቼ አንድ ድምፅ እንካን እንዳያገኙ አደርጋለሁ በማለት የመንግስት ሃብትና መዋቅር እንዳለ ለምርጫው ዘመቻ እንዲውል በማድረግ ሰላማዊ ሀይል እንዳልሆነ ያሳየበት፣ የምርጫ ዲሞክራሲ የሚዘጋ ሓይል መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ግዜ እንደነበር አረጋግጧል። ይህ የገዢው ፓርቲና መንግስት ተግባር በአብዛኛው ሕዝብ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት አካባቢ በሰላማዊ የትግል ስልት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ወይ ህወሓት/ኢህኣዴግ የሰላማዊ ትግል መንገድ ሆን ብሎ እየዘጋ ባለበት ሁኔታ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ  መንገድ ለውጥ ይመጣል በሚል ላይ ታች መልፋቱ እውነት ለውጥ ያመጣል ወይ የሚሉ ጥያቄዎች አንስቷል። እነዚህ ጥያቄዎች በዓረና ዓባላትና ደጋፊዎች አካባቢም የተነሱ ጥያቄዎች ስለነበሩ የዓረና ማ/ኮሚቴ በዚህ በተፈጠረው አመለካከት በረጋ መንፈስና ጥልቀት ባለው ውይይት ባለንበት ዓለማዊ ይሁን ሃገራዊ ፖለቲካዊና ተጨባጭ ማዕከላዊ ኢኮኖሚያዊ ስነልቦናዊ ሁኔታ ሌላ የተሻለ የትግል መንገድ እንደሌለ፣ ሰላማዊ የትግል አማራጭ ነፃና ፍትአዊ ምርጫ በሚካሄድበት አገር ብቻ ሳይሆን ነፃና ርትዓዊ ምርጫ በማይካሄድበት እንዲኖር ለማድረግ አፈናን ለማስወገድም የሚካሄድ የትግል ስልት ነው። ስለሆነም በኢትዮጵያ ይህ የትግል አቅጣጫ ቅድሚያ የሚሰጠው የትግል አማራጭ መሆኑ በመተማመን ድምዳሜ ላይ ደርሶዋል።

ገዢው ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በብረት ለመታገል ከመረጡት ይበልጥ አምርሮ የሚጠላውና ከሰላማዊ የትግል መንገዳቸው ተገፍተው በመውጣት ሰላማዊው ወዳልሆነ የትግል ዘዴ እንዲገቡ የሚያደርግ ጭፍን አፈና እየፈፀመባቸው ያለውም የሰላማዊ ትግል ሓያልነት ስለሚያሰጋው መሆኑን በውይይቱ ሂደት አስምሮበት ያለፈ ጉዳይ ነው። አባላትና ደጋፊዎች በመጨፍጨፉ በሰላማዊ ትግል ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ዜጎች የለውጥ ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች በመሆን እንዳይታገሉ ገና ለገና በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ማምጣት አይቻልም በማለት ራሳቸውን ከሰላማዊ መንገድ ተሳትፎ እንዲገደቡ የሚያደርግ አፈና እየፈፀመበት ነው። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ወጣቱ በአገር ውስጥ ከሚደረገው የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አማራጭ በመሸሽ ወደ ትጥቁ ትግል እንዲገፉ ለማድረግ ወይ ተስፋ ቆርጦ ከፖለቲካ ውጭ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የዓፈና ስርዓት ዕድሜ የሚራዘመው ወይ ደግሞ ተደጋግሞ እንደሰማነው የመለስን ራዕይ መመርያ በማድረግ እስከ 50 ዓመት መግዛት የሚቻለው የሰላማዊ ትግል ስልትን የመረጡ ወጣቶች ሰላማዊ ወዳልሆነው የበረሃ የትግል ስልት እንዲገፉ ወይ ከፖለቲካ ውጭ እንዲሆኑ  በማድረግ ስለሆነ ነው።

 የተከበርክ ሰላም ፈላጊው የኢትዮጵያ ህዝብ አገራችን ኢትዮጵያ ትሁን ትግራይ በአሁኑ ግዜ የመልካም አስተዳደር ችግር የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ችግር የፍትህ እጦት የስራ እጦት የወጣቶች ስደት ሙስና የሚድያ አፈና የፖለቲከኞች የጋዜጠኞችና ፀሓፊዎች አፈና እስራት ሰፊ አገሪቱን አካባቢ የሚሸፍን የዝናብ እጥረት ድርቅና ርሃብ ተደማምረው የአገራችን ህዝቦች ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ የሆኑበት ሁኔታ ውስጥ ናቸው።

በህወሃት/ኢህአዴግ የነሃሴው ጉባኤዎች የተጠቀሱትን ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ይፈልቃሉ ብለው የጠበቁ ዜጎች ጥቂት አልነበሩም። ሆኖም ግን ችግሮችን እንደምንፈታ ቃል እንገባለን ከሚለው መሃላ ውጭ ሌላ ተጨባጭ ለውጥ አልታየም። የብልሹ አስተዳደር ምንጭ ስንከተለው በቆየነው የተሳሳተ ፖሊሲ ነው ስለ ሆነም ችግሩ ፖሊሲያችንና አጠቃላይ አመለካከታችንን በማስተካከል እንፈተዋለን የሚል በአንድ ዓረፍተ-ነገር የሚገለፅ ውሳኔ እንኩዋን ከጉባኤዎቹ ያለመስማታችን ህወሓት/ኢህአዴግ በቆየበት መንገድ ብቻ ሳይሆን በከፋ አስተዳደራዊ ብልሹነት ለመቀጠል መወሰኑን የሚያሳይ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ ብልሹ አስተዳደር ምንጭ ገዢው ፓርቲ ደጋግሞ እንደገለፀው የአፈፃጸም ችግር የፈጠረው ሳይሆን መንስኤው መሰረታዊ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለምና የፖሊሲ ችግር የፈጠረው ነው።

ዓረና ትግራይ የእነዚህ ስር የሰደዱ የአስተዳደር ብልሹነት መነሻ የገዢው ፓርቲ እየተከተለ ያለው ፖለቲካዊ ብልሹነት መሆኑን በመገንዘብ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበት በአገሪቱ የፖለቲካ ርእዮተዓለምና ፖሊሲ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በማመን የመፍትሄ አቅጣጫዎቹ የአገራችንና የክልላችን ህዝቦች እንዲያውቁዋቸው ለማድረግ እስካሁን ድረስ የተቻለውን ጥረት አድርገዋል። የገዢው ፓርቲ ርእዮተአለም አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአገራችን ሕገ መንግስት በሚፃረር መልኩ ሕብረ ፓርቲያዊ ስርዓት በማፍረስ አውራ ፓርቲ እንዲጠናከር ማድረጉ ነፃ የሲቪክ ማህበራት እንዲያብቡ ማድረግ ሲገባ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በድርጅት አባላት የሚመሩ ማህበራት እንዲያብቡ ማድረግ የህግ ልእልና በማክበር ትልቅ ሚና ያላቸው የፍትህ አካላት ነፃነት ገለልተኝነት እንዲርቃቸው ማድረግ ነፃ ሚድያ በማቆም ሕብረተሰቡ በነፃነት መረጃ የሚያገኝበት ሓሳቡና ፍላጎቱ በነፃነት የሚገልፅባቸው ሚድያዎች እንዲሆኑ ማድረግ ሲገባ ልማታዊ ጋዜጠኛ በሚል የገዢው ፓርቲና መንግስት ሙገሳ የሚያስተጋቡ የህዝብ ትክክለኛ/እውነተኛ ድምፅ የማይሰማባቸው ብቻ ሳይሆኑ የህዝብ ድምፅ የሚያፍኑ እንዲሆኑ መደረጉ ሕ/ሰብ በነፃ እንዳይደራጅ ሓሳቡን ሃሳቡን በነፃነት እንዳይገልፅ የሚሰሩ ለቁጥጥር እንጂ ለነፃነት የማይሰራ አንድ ለአምስት የሚባል አደረጃጀትና የስለላ መረብ በመዘርጋት እስከ ቤተሰብ የሚደርስ መንግስታዊ መዋቅር በመዘርጋት ለነፃነት ብሎ ወደር የሌለው መስዋእት የከፈለ ህዝብ በቀን ተቀን ቁጥጥር ጥበቃ ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገውን ሂደት የሚያርም/የሚያስተካክል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከህወሓት/ኢህአዴግ ሊታይ አልቻለም። የህወሓት/ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የፈጠረው ብልሹ አስተዳደርና ድህነት በጉባኤዎቹ አስወግዳቸዋሎህ በማለት በመፎክር ጠንካራ ግምገማ አካሂዳለሁ በማለት የገባው ቃል ከልብ ያልመነጨ ልፍለፋና ችግሮቹን እንዲፈቱ የሚያደርግ ሳይሆን እንዲባባሱ የሚያደርግ ነው።

ትግራይ ይሁን ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የነዚህ ችግሮች ቁስለኛ ሆኖ እንዲቀጥል ተፈርዶበታል። በ40ኛው የህወሓት ምስረታ በአል ከአጠቃላይ ታራሹ መሬት ግማሹ በመስኖ እየለማ ነው እንዳልተባለ በትግራይ ክልልና በብዙዎች ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተጋርጦ ያለው የድርቅ ችግር መንግስት ችግሩ ለማሳነስና ለመደበቅ እየሞከረ ቢሆንም ችግሩ ተገቢውን አትኩሮት እንዲሰጠው የድርቁ ተጠቂዎች በረሃብ እየተጠቁ ሰለሆኑ ከብቶቻቹሁን ሽጡ ከማለት ከብቶቻቸውን የሚያድኑበት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግ የእንስሶቹ ምግብ እንዲቀርብላቸው በትግራይ ህዝብ ደም የተገኘው የትእምት ሃብትም ግዜ ሳይጠፋ የህዝቡን ችግር በመፍታት የራሱን ሚና በወቅቱ እንዲጫወት ዓረና ትግራይ ጥሪውን ያቀርባል።

ችግሮቻችን አገራዊና የጋራ ስለሆኑ ጥምር አገራዊ የለውጥ አቅም መፍጠር የግድ እያለ ነው።ይህ የለውጥ ሓይል እውን እንዲሆን ደግሞ ዓረና ጀምሮት የቆየውን አንድ ጠንካራ አገራዊ ፓርቲ እውን እንዲሆን የማድረግ ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ ማ/ኮሚቴው ዳግም ወስነዋል።ይህ የውህደት አጀንዳ የጥላቻ ፖለቲካ በሚያስወግድ አገራዊ አንድነትና ብዙሃነት በሚያከብር ተቃኝቶ ስለሚፈፀም የአገራችን ውስጣዊና ዓለማዊ ቁመና በሚያደምቅ መንገድ የሚፈፀም ይሆናል።

የተከበራቹህ ለውጥና ርትዕ ፈላጊ ወገኖች

1.  ዓረና ትግራይ በህወሓት/ኢህአዴግ የደነደነው ብልሹ አስተዳደር የሚያስተካክል አመለካከትና ፖሊሲ ይዞ ቀርቦ ድርጅት በመሆኑ ፍትህና ርትዕ የሰፈነበት አገርና ክልል እንዲፈጠር ለውጥ ፈላጊው ወጣቱ ሓይል በዚህ በአገሩና ክልሉ የለውጥ ሂደት መሳተፍ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ቁልፍ ሚና እንዳለው የሚያምን ፓርቲ ስለሆነ ወጣቶች የስደት የስራ አጥነት የአድልዎና ፖለቲካዊ መገለልን መፍትሄ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል መሆኑን የሚያምነውን ዓረናን በመደገፍና የትግሉ ባለቤት በመሆን እንዲንቀሳቀሱ፣

2.  ዓረና ከጥላቻና የዘር ፖለቲካ የፀዳች በአንድነትና በብዙህነትዋ የተዋበች የኮራች አትዮጵያን መፍጠር ራዕይ አድርጎ እየገሰገሰ ያለ ፓርቲ ስለሆነ የመላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲሰጠው፣

3.  የዓረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የክልሉ ህዝባችን ገዢው ፓርቲ በሚያደርሰው ወከባና አፈና እስራት ተስፋ ባለመቁረጥ በሰላማዊውና ዴሞክራሲያዊው የትግል መንገድ በመፅናት የሰላማዊ ለውጥ ተምሳሌት ሁነን እንድንሰራ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት ጥሪውን ያቀርባል።

መልካም የትግል ዘመን ይሁንልን¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1214 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us