የረሃብ ሥጋትን ለመቀነስ መንግሥትም ሆነ ሰብአዊ ርኅራኄ የሚሰማን ዜጎች ሁሉ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል!!

Wednesday, 14 October 2015 13:30

 

ፍል-፩

በዲ/ን ኒቆዲሞስ

 

እኛ ኢትዮጵያውያን ለረሃብ ክሥተት በፍጹም እንግዶች አይደለንም። ጠኔ-ችጋር ደግሞ ደጋግሞ የጎበኘን፣ ረሃብ ስማችንን ያጎደፈብን፣ በሃፍረት አንገታችንን ያስደፋን፣ ቅስማችንን የሰበረን፣ ታሪካችንን ያጠለሸብን፣ የእልቂት፣ የሰቆቃ፣ የደም ምድር- ‹‹አኬል ዳማ›› በሚል የሚያሰቅቅ ስያሜ የተጠራን፣ መላው ዓለም በኀዘን ከንፈሩን የመጠጠልንና እንባ የተራጨልን ምስኪን ሕዝቦች ነን። ከዚህ አገራችን ለዘመናት ከተጎናጸፈችው እጅጉን ከምናፍርበትና ከምንሳቀቅበት ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ጋር በተያያዘ በዛሬው መጣጥፌ ይዋል ይደር ሳንል ጊዜ ሰጥተን እንመካከር ዘንድ ዘንድሮ በዝናም እጥረት በአገራችን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለረሃብ ስለተጋለጡት ሚሊዮኖች ወገኖቻችን እስቲ አብረን ትንሽ እንቆዝም።

በዚህች ቅጽበት ምናልባት አውቀነውም ይሁን ሳናውቅ በብዙ ትርፍና ባላስፈላጊ ወጪ በመዝናናት በጥሩ ምቾትና ድሎት ላይ ያለነውንና በማንኛውም ልኬት ሰዎች ለተባልን ሁሉ ፊታችንን መለስ አርገን ሚሊዮኖች ወገኖቻችን ለረሃብ ስለተጋለጡበትና በየአሥር ዓመቱ ብቅ እያለ ቤተኛው ስላደረገን የረሃብ ጉዳይ ላይ በጋራ እንወያይ ዘንድ ወደድኹ። እንደ መግቢያም ዛሬም ድረስ ሳስታውስው እጅጉን ከሚያሳዝነኝ ከአንድ ገጠመኜ ጹሐፌን ልጀምር።

በደቡብ አፍሪካ የአርትና የባህል ሚ/ር፣ ማንዴላና የትግል ጓዶቻቸው ለ፳፯ ዓመታት በተጋዙበትና በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በተመዘገበው በሮቢን ደሴት የነጻነት ሙዚየምና እና በኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን ትብብርና የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠውን ‹‹የአፍሪካ ቅርስና ቱሪዝም ጥናት የድኅረ ምረቃ/የፖስት ግራጁየት የትምህርት ፕሮግራም›› የስኮላር ሺፕ ዕድል አግኝቼ ትምህርቴን በተከታተልኩባት በኬፕታውን ከተማ በሮቢን ደሴት ሙዚየም የሆነ ገጠመኜ ነው።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን ከመጀመራችን በፊት የትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ የሆነው ናይጄሪያዊው ጎልማሳ ከተለያዩ አገራት የመጣን ተማሪዎችን እርስ በርሳችን እንድንተዋወቅና እንዲሁም ይህን የነጻ የስኮላር ሺፕ ትምህርት ዕድል ለሰጠን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለጥቁር ሕዝብ ነጻነት፣ ለሰው ልጆች መብትና እኩልነት ሲሉ ለበርካታ ዓመታት ቃላት ሊገልጸው የማይችለውን መከራና ግፍ በተቀበሉባት ለሮቢን ደሴት ወኅኒ/ግዞት ቤት ከነጻነት በኋላ ደግሞ ሺህዎች በየዕለቱ የሚጎርፉበት የነጻነት መታሰቢያ ሙዚየም ለመጎብኘትና ምስጋናችንን ለመግለጽ በሚል ነበር በደሴቲቱ የተገኘነው።

የትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ ከጉብኝታችንና ከቀኑ ውሎአችን በኋላ በሮቢን ደሴት በሚገኘው መኖሪያው የእራት ግብዣ አድርጎልን ነበር። ከኬፕታውን ሲ ፓይንት- ከኔልሰን ማንዴላ ጌት በመርከብ ለ፵፭ ደቂቃ ያህል ቀዝቃዛውንና ማዕበል የሚንጠውን የአትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥ፣ ውብ በሆነችው የደቡብ አፍሪካ እናት ከተማ በኬፕታውን ድንቅ ተፈጥሮ እየተደመምን፣ ከአድማሱ ጋራ የተጋጠመ የሚመስለውን ባለ ልዩ ግርማ ተራሮቿን በርቀት እየቃኘን፣ እንዲሁም በዓለማችን የመርከብ ቴክኖሎጂ ታሪክ ተወዳዳሪና አቻ የሌላት የተባለችውን የእንግሊዟን ታይታኒክ መርከብ ከ1800 ተጓዦቿ ጋር ያሰጠመውን በባለ ግርማ ሞገሱን የአትላንቲክ ውቅያኖስ የመርከብ ላይ ጉዞና የዶልፊኖችን የውኃ ላይ አስገራሚ ትእይንትና በሮቢን ደሴት ጉብኝታችን የፈጠረብንን ልዩ ደስታ ስሜታችንን እንዳሞቀው ነበር የትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ በሆነው በሮቢን ደሴት መኖሪያ ቤቱ ለእራት የታደምነው።

ታዲያ እራት ተበልቶ አልቆ የደቡብ አፍሪካውያኑን ወይን እየተጎነጨን ስንጨዋወት በጨዋታችን መካካል በትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ ቤት ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠውን የኔልሰን ማንዴላን የትግል ሕይወት የሚተርከውን መጽሐፍ አንስቼ ሳገላብጥ፣ ማንዴላ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በነበሩበት ጊዜ በወቅቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጣቸውን ፓስፖርት በመጽሐፉ ላይ በአባሪነት መካተቱና የኢትዮጵያ ቆይታቸውን የሚያትተውን አስደናቂ ትረካ በማየቴ እጅጉን ደስ አለኝ።

 በአጠገቤ ለነበረችው ከዩኔስኮ ተወክላ ከሀገረ ናምቢያ ለመጣች የክፍል ጓደኛዬ መጽሐፉን እያሳየኋት ማንዴላ ስለ አገሬ ኢትዮጵያ የሰጡትን ድንቅ ምስክርነት በኩራት ካነብበኩላት በኋላ አገራችን ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ለኔልሰን ማንዴላና በአጠቃላይ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግልና ተጋድሎ ያደረገችውን አስተዋጽኦ ከአንጸባራቂው ከዓድዋው ድል ጋራ በአጭሩ ተረኩላት።

‹‹Oh really! እኔ ይሄን አላውቅም፤ ብዙዎች አፍሪካውያንም ይሄን የሚያውቁ አይመስለኝም። ስለ ኢትዮጵያ አብዛኛው የአገሬ ናምቢያ ሕዝብም ሆነ እኔ የምናውቀው ኹለት ነገሮችን ነው። አንደኛው በርካታ ተከታይ ያላቸውን ንጉሣችሁን ኃይለ ሥላሴን/ራስ ተፈሪውያንን ሲሆን ኹለተኛው ግን Sorry to say this …!ይሄን ስልህ እያዘንኩ ነው፤ በአገራችሁ ተከስቶ በነበረው አስከፊው ድርቅ/ራብ ስላለቁት ወገኖቻችሁን ነው የሰማሁትም፣ የማውቀውም። እውነቴን ነው የምልህ እንዲህ ዓይነት ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነውን ታሪካችሁን፣ ሥልጣኔያችሁንና የአፍሪካ ጫፍ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ድረስ የዘለቀ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ያላችሁ ታላቅ ሕዝቦች መሆናችሁን አላውቅም።››

‹‹እንደ ቢ.ቢ.ሲ ባሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ያስተላለፉልንና ስለ አገራችሁ የምናውቀው የራብ፣ የጦርነትና የሰቆቃ ምድር መሆናችሁን ነው።›› እንደውም አለችኝ ይህቺ ናምቢያዊት የክፍል ጓደኛዬ፤ ‹‹እንደውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገራችሁ ደርሶ የነበረው ረሃብ ባደረሰባችሁ አሰቃቂ እልቂት ልባቸው ክፉኛ ያዘነባቸው የአገሬ የናምቢያ አዛውንቶች አንዳንድ ሰዎች ምግብ ያለ አግባብ ሲጥሉ ሲያዩ ‹Hey please Think the Starved People in Ethiopia››› እንደሚሉ ስትነግረኝ ያ የነበረው የቀኑ ውሎ ደስታዬና በአገሬ የነጻነት ታሪክ ተጋድሎ ኩራቴ በአፍታ ወደ ኀዘን ተቀየረ። ምነው ይሄን መጽሐፍ ባላነሳሁት-በቀረብኝ በሚል ጥፍሬ ውስጥ የመግባት ያህል ሃፍርትና ውርደት ተሰማኝ። ከዛች ቅጽበት በኋላ ከዚህች ሴት ጋራ ብዙም ማውራት አልቻልኩም።

ሺህ ዘመናትን ካስቆጠረው ታሪካችን፣ ቅርሳችንና ሥልጣኔያችን፣ በእጅጉ ከምንኮራበት የነጻነት ተጋድሎ ታሪካችን፣ ከአምላክ ከተቸረን የተፈጥሮ ጸጋችንና ውበታችን ይልቅ ክፉ ክፉው ታሪካችን እንዲህ ከጫፍ እጫፍ መሰማቱና መናኘቱ፣ መተረቻና መጠቋቆሚያ፣ የረሃብ መዝገበ ቃላት ፍቺ ማድመቂያ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና የእልቂት፣ የደም ምድር ‹‹አኬል ዳማ›› መገለጫ ሕዝቦች መሆናችን ግራ እያጋባኝ ይሄው ዛሬም ድረስ ይሄ ክፉ ትዝታዬ ከእኔ ጋራ ይኖራል።

በእርግጥ ይህ ዓይነቱ ገጠመኝ የእኔ ብቻ ገጠመኝ ነው ብዬ አላስብም። በርካታ ኢትዮጵያውያን በሔዳችሁበት አገርና ምድር ሁሉ ተመሳሳይም ብቻም ሳይሆን እንዳውም ከኔም ገጠመኝ ካልኩትም የከፋ ብዙ አንገታችሁን ያስደፋና ያሳቀቀን ገጠመኝ እንዳለን አውቃለሁ። በዛው በደቡብ አፍሪካ የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝቶ ከሔደ ጓደኛችን መካከል ከሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወፈር ያለና የሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ዓይነት በስፖርትና በምግብ የዳበረ ሰውነት ያለውን ወገናችንን አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት የክፍሉ ተማሪ፣ ‹‹አንተ ረሃብ ከሌለበት የኢትዮጵያ ክፍል የመጣህ መሆን አለብህ …!?›› እንዳለችው በቁጭትና በኀዘን ሆኖ አጫውቶናል።

ከጥቂት ዓመታት በፊትም አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ለትምህርት ወደ ደቡብ ኮሪያ ሄዶ የነበረ ኢትዮጵያዊ ወጣት በዩኒቨርስቲው መምህራንና የክፍል ጓደኞቹ ከረሃብ እልቂትና ጦርነት ተርፎ ለዚህ ዕድል መብቃቱ ኩራት ሊሰማው እንደሚገባው በነጋ ጠባ ሲነግሩትና ሲያስረዱት እርሱም ይሄን ይረዱኝ ይሆን በሚል ስለ አገሩ ያለውን እውነታ ቢነግራቸውም ሊያምኑት ባለመቻላቸው  ባጋጠመው የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ ብቸኝነትና ባይተዋርነት እጅጉን ተማሮ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ትምህርቱን ጥሎ ወደ አገሩ እንደተመለሰ የሚተርክ ጽሑፍ እንዳስነበበን ትዝ ይለኛል፡

በሄዱበትና በተሰደዱበት አገር በነጋ ጠባ ስለ ኢትዮጵያ የሚወራው የረሃብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና የእልቂት ታሪክ ቅስማቸውን ሰብሮት በባእድ ምድር ቀና ብለው መራመድ እያቃታቸው በኀዘን፣ ሰቀቀንና በቁጭት አንጀታቸው እያረረ፣ እግዚኦ የኢትዮጵያ አምላክ ሆይ መቼ ነው ስማችንና ታሪካችንን የምትለውጠው!? በሚል ተማኅጽኖ እንባቸውን እያፈሰሱ ከአምላካቸው ጋራ የሚሟገቱ በርካታ ወገኖች ዛሬም ድረስ አሉን። ስለ አገራቸው፣ ስለ ወገኖቻቸው በቁጭት የሚንገበገቡ።

ይህን ለዘመናት አንገታችንን ያስደፋንን የረሃብ፣ የእርስ በርስ ጦርነት የውርደት ታሪካችንን ለማደስ ጉልበቴ በርታ በርታ እያልንበት ባለንበት ዘመን ረሃብ በራችንን ዳግመኛ ማንኳኳቱና በተከታታይ ምልክቱ ቢታይም በተለየ ግን በዘንድሮው ወርኀ ክረምት በዝናም እጥረት ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ለረሃብ ለተጋለጠው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝባችንን ከረሃብ፣ ከችጋር እልቂት ይታደጉልን ዘንድ መንግሥታችን ለጋሽ አገራትንና ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችን እየተማጸነ ነው።

ከእንግዲህ ወዲህ የሚሠሩ ወርቅ እጆችን ይዘን ስንዴ ልመና እንዴት ይታሰባል፣ ሕልማችን ሕዝባችንን በቀን ሦስት ጊዜ ማብላት ነው፣ ረሃብን ታሪክ እናደርገዋለን፣ በምግብ እህል ራሳችንን እየቻልን ነው … ዕድገታችንን የኢኮኖሚ ግሥጋሤያችን ዓለም ሁሉ እጁን በአፉ ላይ እንዲጭን እያደረግነው ነው … ወዘተ እንዳልተባልን፣ እንዳላስባልን ዛሬ ግን ይኸው ዓይናችንን በጨው አጥበን በምዕራባውያኑ ደጃፍ ምግብ ልመና አኩፋዳችንን ይዘን መሰለፋችን እጅጉን ያሸማቅቃል፣ ያሳፍራልም።

መንግሥት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ባለፈው ወርኻ ክረምት የዝናም ስርጭቱ ዝቅተኛና የተጠበቀውያን ያህል ባለመሆኑ የተነሣ ከ፬.፭ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለረሃብ እንደተጋለጠና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አሳውቆአል። ለረሃብ የተጋለጡትን ወገኖቻችንን ቁጥር በተመለከተ መንግሥት ይፋ ያደረገው ቁጥር የተዛባ መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየገለጹ ነው። እነዚሁ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዕርዳታ ድርጅቶች ለረሃብ የተጋለጠው ሕዝባችን ቁጥር ወደ ፯ ሚሊዮን እንደሚጠጋና ይህ ቁጥርም ወደፊት ሊያሻቅብ እንደሚችል እየተናገሩና እያስጠነቀቁ መሆናቸው ሌላኛው በፊታችን የተጋረጠብን ክፉ ዜና/መርዶ መሆኑ ማወቅ ሁላችንም ግድ ይለናል።

ሰላም!  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
569 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us