የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት

Wednesday, 14 October 2015 13:35

 

 

 

·        ከሁሉ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና የብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል!!

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ

 

የኢህአዴግ መንግስት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እተገብረዋለሁ በሚለው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት እንደፈለገ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፈልን ደብዳቤ ገልጾልናል። ይህ ሁኔታ መልካም ቢሆንም ቅሉ እንደ መንግሥት የሚነድፋቸው ዕቅዶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አምነውበትና የኔ ብለው በሙሉ ልብ ሲቀበሉት እና ሙሉ ተሳትፎ ሲያደርጉበት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

ይሁን እንጂ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በተበጣጠሰ ሁኔታ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ትስስሯ ፈፅሞ በላላበት ሁኔታ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረው ችግር ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለያይቶና አራርቆ በጠላትነት እንዲተያይ አድርጎታል። ይህ በመሆኑም የጉልበት (Labor) እና የካፒታል (Capital) ዝውውር ተገትቶ ባለበት ሁኔታ እና ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይሰሩና ሀብት ንብረት እንዳያፈሩ ተገትተው እና ተገድበው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የዚህን አካሄድ አስከፊነት የሚያመለክተን በየዩኒቨርስቲው የሚገኙ ተማሪዎች በአንድ ስሜትና በወንድማማችነት ለምርምርና ለፈጠራ ከመነሳት ይልቅ የጎሳ ጎራ ለይተው እየተቆራቆሱ መገኘታቸው ለሀገሪቱ በሚጠቅም ጎዳና ላይ አለመሆናቸውን ያመለክታል።

ኢህአዴግ የፈጠረውና ያጠናከረው ወገን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሞኖፖል ይህ ሌላውና የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ያልሆነው ክፍል ደግሞ ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል። ይህም የሚያሳየው እንደፖለቲካው ሁሉ ፍትሃዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል አለመኖሩን ነው።

ዜጎች ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ በሚናገሩበትና በሚጽፉበት ወቅት ሽብርተኛ እየተባሉ ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ ወደ እስር ቤት ይወረወራሉ። ፍትህም በወቅቱ አይሰጣቸውም። ለብዙ ጊዜ በዚያው ሲማቅቁ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ያለፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ከእስር ቤት እንዲለቀቁ ይደረጋል። ይህ ሁኔታም ሠላምን ሳይሆን ጥላቻን፣ የሀገር መረጋጋትን ሳይሆን ብጥብጥን የሚፈጥር መሆኑን ገዢው ፓርቲም ቢሆን ቁልጭ አድርጎ የሚያውቀው ይመስለናል።

የኢህአዴግን መንግሥት እንደነዚህ ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ሕዝባችንን በሀብታም እና ድሃ፣ የኢህአዴግ ደጋፊና ጠላት በሚል ስለከፋፈለው፤ እርሱ የፈጠራቸው ሀብታሞች የሀገሪቱን ሀብት፣ በሞኖፖል እንዲይዙ ሲደረግ ቀሪውና እውነትን በመፈለግ እርሱን ሲታገል የነበረው ሕዝብ ደግሞ ከሥራው ይፈናቀላል። ከንግድ ሥራው ከስሮ እንዲወጣ ይደረጋል፤ አርሶ አደር ከሆነም ከመሬቱ ይፈናቀላል። ይህ አካሄድም አንድነትን ሳይሆን መለያየትን፣ ወንድማማችነትን ሳይሆን ጠላትነትን፣ መደጋገፍን ሳይሆን መጠላለፍን የሚፈጥር መሆኑን በድጋሚ ለኢህአዴግ ለማሳሰብ እንወዳለን።

ከላይ እንደተጠቀሰው የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በጥቂቶች ቁጥጥር ስር ስለዋለና ፍትሃዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል ስለጠፋ ከሕዝባችን 80 በመቶ የሚሆነው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ውድቆ ይገኛል። የኢህአዴግ መንግሥትም ይህን የተጎዳ ክፍል ሕዝብ ዞር ብሎ ከማየትና ከመደገፍ ይልቅ የራሱን ፖለቲካ ማጠናከርና ሁኔታዎችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይታያል።

የኢህአዴግን መንግሥት ከመምከርና ለማሳሰብ የምንወደው በሀገሪቱ ውስጥ፡-

1.  የልማት፣ የእድገትና ብልጽግና መሠረቱ ዲሞክራሲና የዜጎች መብት መጠበቅና መከበር ሆኖ ሳለ ዜጎች አባላትም በዚህ አመለካከታቸው የተነሳ እየተሰደዱ፣ እየተዋከቡና ንብረታቸውን እየተነጠቁ በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣

2.  ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሕዝባችን ተጋብቶ፣ ተዋልዶና ሀብት አፍርቶ በሠላም ከሚኖርባቸው የተለያዩ አካባቢዎች “ክልልህ አይደለም፣ ከክልላችን ውጣ” እየተባለ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ሀብታቸው እየተነጠቀ፣ እየተቃጠለ፣ እየተቀማ፣ እነርሱም እየተደበደቡና እየታሰሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ከነቤተሰባቸው እየተባረሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ዜጎች በወጣው ዕቅድ ላይ በሙሉ ልብ ሊሳተፉ ይችላሉ በማለት ያስቸግራል።

3.  እንደዚህ ያለውን ግዙፍ ብሔራዊ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነትና የእኔ ባይነት መሳተፍና ለተግባራዊነቱም በትጋት ይነሱ ዘንድ ከላይ የተጠቀሱት ከፍተኛ የሆኑ ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን።

እንደዚህ ባሉ ማነቆዎች እና ችግሮች ላይ እርምት ሳይደረግ የወጣውን ዕቅድ ሕዝባችን በአንድ ልብ ደግፎ በመረባረብ ከዳር ያደርሰዋል ብሎ ማሰቡ ብዙ እርምጃ ያስኬዳል የሚል እምነቱ የለንም። ስለዚህ የኢህአዴግ መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሀገሪቱ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከፈለገ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው የሚል ምክራችንን ልንለግስ እንወዳለን።

በአጠቃላይ የኢህአዴግ መንግሥት በዚህ ዕቅድ ላይ ሕዝባችንን ለውይይት ከመጥራቱ በፊት መቅደም ያለባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች እንዳሉና በቅድሚያ መፈፀም እንዳለባቸው እያሳሰብን ሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያካተተ ስብሰባ ተደርጎ ብሔራዊ ውይይት፣ እርቅና መግባባት የሚደረስበት ስብሰባ ኢህአዴግ መጥራት እንዳለበት እናሳስባለን።

                              አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

                                ጥቅምት 01 ቀን 2008 ዓ.ምn       

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
644 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 114 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us