“መቶ በመቶ የሚባል የምርጫ ውጤት አስቂኝ ግን ደግሞ አደገኛ ነው”

Wednesday, 21 October 2015 15:23

 

 

ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት

የቀድሞ የአየር ኃይል አዛዥ

አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) (LLB, LLM and PhD Candidate) የህወሓት/ኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ፣ ከ1983-1986 የሰሜን ማዕከላዊ እዝ አዛዥ እና በጡረታ እስከ ተሰናበቱበት 1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ በተሰናበቱበትም ወቅት የሜጀር ጄኔራል ማዕርግ ደርሰው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የሰላም እና ደህንነት ጥናት ተቛም የዶክትሬት ዲግሪ እያጠኑ ይገኛሉ። ሆርን አፌርስ ድረገጽ ላይ ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያሰፈሩት አስተያየት በከፊል አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

1. መግቢያ

በኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት “ሩቅ አስባ ሩቅ ለማደር እየተጋች ያለች አገር” በሚል መሪ ቃል ስር ላሳካዉ አንፃራዊ መረጋጋት እና ተጠቃሽ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡ይሄም ስኬት ኩሩው የኢትዮጵያ ህዝብ ደስተኛ እንዲሆን እና ወጣቱም ተስፈኛ እንዲሆን እያስቻለው ነው፡፡ ባለፈው አስር ዓመት ኢትዮጵያ ከአለማችን ፈጣን ኢኮኖሚዎች በመጀመሪያ ረድፍ የምትጠራ አገር ሆናለች። ይህ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትም ተጨባጭ እና ሊካዱ የማይችሉና እሰየው የሚያስብሉ ልማታዊ እና ማህበራዊ ለውጦችን አስከትሏል። ከሞላ ጎደል የተሳካው የምእት አመቱ የልማት ግቦች፣ እንደ ህዳሴው ግድብ አይነት ታላላቅ ፕሮጀክቶች፣ እየተሳለጡ ያሉ ሰፋፊ የስኳርና የማዳበርያ ፋብሪካዎች ተከላ ሲታይ ይህን እዉን ያደረገዉን መንግስት እና አመራሩን ማመስገን ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያገኙት የSouth-South ሽልማትም የዚህ ጥረት ማሳያ ነው፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እኔም እንኳን ደስ አልዎት ማለት እፈልጋለሁ። የመጀመሪያው የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP 1) አጠቃላይ አገራዊ አፈፃፀም ደረጃዉ አበረታች ነበር ማለት ይቻላል፤ በክልሎች መካከል ሊታረም የሚገባው አለመመጣጠን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። በኢኮኖሚው መስክ አገራችን ኢትዮጵያም ገፅታዋንም በፍጥነት እየቀየረች ትገኛለች። GTP 1 አስፍቶ ማስብን እና አግዝፎ መስራትን ያስተማረ እቅድ ስለነበር እያንዳንዱ ዜጋ ላይ የፈጠረው መነሳሳት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። የተለጠጠ እቅድ ይዘህ እጅግ በጣም ብዙ አልመህ ብዙ ብትሰራ በ ፐርሰንት ሲታይ ትንሽ ቢመስልም ውጤቱ ትንሽ አቅዶ እስዋን ብቻ ከማሳካት ግን ሺ እጥፍ ይሻላልም፣ ይበጃልም። ስለዚህ የተለጠጠ (ambitious) ፕላን መሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል። ከጀርባው ያለው እሳቤም ማደግ ካለብን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ያስፈልገናል፤ ይህ ለማድረግ ደግሞ ተለቅ ያለ ስራ መስራት አለብን ነው። ይሄም በጎ እሳቤ ነው። ትልቅ ነገር ሳያስቡ ትልቅ አገር መገንባት አይቻልም። በአጠቃላይ በትምህርት መስፋፋት (በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቛማት መስፋፋት)፣ በጤና ኬላዎች መዳረስ፣ ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ የሚደረጉ ድጋፎች፣ ስፋፊ የትራስፖርት አውታሮች ያሳካ የኢኮኖሚ እድገት፣ ሃብታም ገበሬዎችን መፍጠር የቻለ ግብርና፣ ብዙ ወጣቶችን የፈጠራ እና የሃብት ባለቤት ማድረግ የቻለ ጉዞ ተገቢ እዉቅና ማግኘት አለበት። የኢንዱስትሪ ክፍሉም በብዙ ችግሮች የተሞላ ቢሆንም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የላቀ መሆኑ ሊደነቅ ይገባል።

አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት በማስፈን እና ሰላም ላጡ ህዝቦች የሰላም ሃይል በመሆን እሚደረገው የዲፕሎማሲ እና የመከላከያ ኃይላችን ጥረትም እጅጉን የሚመሰገን ነው። ኢትዮጵያ ላይ የሰፈነው አንፃራዊ ሠላም እና መረጋጋት ዝቅ ተደርጎ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ እነ ሶርያ እና ሊቢያ ከነሙሉ ሃብታቸው ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉም መርሳት የለብንም። እነ ኬንያ እና ሶማሊያ በአሸባሪዎች ሲታመሱ በሠላም ተኝተን የምናድረው የሰፈነዉን አንፃራዊ ሠላም ተማምነን ነው። ዋናው የሠላማችን ምንጭ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን ቢሆንም የፀጥታ ኃይሎቻችን ልዩ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

በተለይም ትህዴንን (TPDM) ለአዲስ ዓመት ስጦታ በማበርከታቸው አድናቆቴን መግለፅ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚታየው የሶስትዮሽ ስምምነትም የኢትዮጵያ መንግስት አስተዋይነት እና ለብሄራዊ ጥቅሙ ያለው ተቆርቛሪነት ያረጋገጠበት ድርጊት ተደርጎ ሊቆጠር የሚገባው ነው። ተስፋ ሰጪ በሆነው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምክንያት የተፈጠረው አገራዊ የህዳሴ መንፈስም ከምንም ሳይሆን መሬት ላይ ካለው እዉነታ የሚመንጭ አዎንታዊ ቁጭት ስለሆነ ለለዉጥ ጉዞው እጅግ ጠቃሚ ግብአት ነው። ይሁን እንጂ የኑሮ ውድነት እጅግ እየሻቀበ በመሄዱና በሃብታምና ድሃ ያለው ልዩነት በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ አደገኛ ስለሆነ ተገቢ እርምት መወሰድ አለበት እላለሁ፡፡

ልማታዊ ስኬቶቹ የመንግስትን ልማታዊነት ያሳያሉ ማለት ግን ዴሞክራሲያዊነቱን ይገልፃል ማለት አይቻልም። በአጭሩ ሠላማዊ እና ልማታዊ ማለት ዴሞክራሲ ማለት አይደለም። ዴሞክራሲ ድባቡ እየሰፋ ነው ወይስ እየጠበበ ነው? የሚለው ማየት ተገቢ ነው። ይህን ለመመለስ መለኪያ ያስፈለገናል፡፡ መመዘኛችን ህገ-መንግስታችን፤ የመንግሰትና የገዢው ፓርቲ አቋሞች መሰረት አድርገን ብናየው ስርኣቱን በበለጠ ለማየት ያስችለናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ “በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱ ለማረጋገጥ” እና ለሌሎች ተዛማጀ “ዓላማዎችና እምነቶች ማሰርያ” እንዲሆን ህገ መንግስቱ መፅደቁ መግብያው ላይ ሰፍሮ እናገኛለን። ለዚህም ነው ሰላማችንንና ዴሞክራሲያችንን ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ህገ-መንግስቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ነው የምለው።

በ 1994 ዓ.ም የማስታወቂያ ሚኒስቴር “በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች” በሚል ርእስ ባሳተመው ፅሁፍ ‘ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የህልዉና ጥያቄ ነው’ ይላል። ይህ ሰነድ የተሟላ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ የተቀመጠበት በመሆኑ የመመዘኛችን መነሻ እንዲሆን ወድጅያለሁ፡፡ ሰነዱ ዘርዘር አድርጎ የተመለከታቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ብዙ መሆናቸው መገንዘብ ይቻላል። ይሄው የ1994ቱ ሰነድ ምክርቤቶችን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ “ምክር ቤቶች የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እምብርትና የዴሞክራስያዊ አገዛዝ አውራ ተቋሞች ናቸው” ይላቸዋል። ሆኖም መሬት ላይ ያለው እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ይመስላል። ለምን?

በተመሳሳይም በ 1992 ዓ.ም ለውይይት በተዘረጋው የኢህአዴግ ፅሁፍ ላይ ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ የሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን “ትምህርት ቤቶችን ወደ ኢህአዴግ ትምህርት ቤትነትን ለመቀየር የማይቻል ከመሆኑም በላይ ሃቀኛ ዴሞክራሲያዊም አይሆንም። መላዉን ህዝብ /አብዛኛው ክፍል/ ለአመታት አንድ ፓርቲ አመለካከት በማጋለጥ፣ ሌሎችን በመከላከል የሚደረግ አሰራር መከተል በሃሳቦች መካከል ነፃ ዉድድር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። የሃይለስላሴና የደርግ መንግስታት ይህን ማድረጋቸው የሚያመላክተው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያቸዉን ነው።” አሁንም እውነታው ከዚህ የራቀ ይመስላል።ለምን?

ከአምስት ዓመት በኃላ በ 1999 ዓ.ም የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጦ የወጣ ችግር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ከስር መሰረቱ እንፈታዋል ተብሎ ተዝምሮለትም ነበር። ነበር ሆኖ ቀረ!! አሁንም በ 2007 ዓ.ም መጨረሻ ኢህአዴግ መልካም አስተዳደር ዋናው ችግሬ ነው እያለ ነው። ይህ ለምን ሆነ? የዚህ ጽሁፍ አላማም ለምን ይህ ችግር ሳይቀረፍ፣ አለ ከተባለበት ግዜ ምንም መሻሻል ሳያሳይ፣ እንደዉም እየተባባሰ ለምን እንደመጣ ለማሳየት እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመጠቆም ነው።

ኢህአዴግ በኢኮኖሚው መስክ ከሞላ ጎደል ያለመዉን እያሳካ ይታያል፤ ከዴሞክራሲ አኳያ ግን እግሩ ሲጎተት መመልከት የተለመደ ሁነት ከሆነ ሰነባብቷል። በዚህ ዙርያም በዴሞክራሲው መስክ ችግሮች እየታዩ ነው ብሎ ኢህአዴግ በ 1992-93 ዓ.ም ከገመገመበት ወቅት እስከ አሁንዋ ሰዓት ይህ ነው ሊባል የሚችል የሰፋ የዴሞክራሲ ድባብ ሳይፈጠር ካለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

GTP 1 በሚፈለገው መጠን እና ፍጥነት እንዳይሳካ ካደረጉት ምክንያቶች የመልካም አስተዳደር ችግር በዋናነት መጥቀስ ይቻላል። ከአጠቃላይ የዴሞክራሲ ድባብ መጥበብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ የሙስና እና የፍትህ መደል ናቸው፤ የGTP 1ን አፈፃፀም በሚፈለገው ፍጥነት ያላስኬዱት። መልካም/ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ማስፈን ከተበላሸ/ ካልተቻለ GTP 2 አይሳካም ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት አገራችን የሰራቻቸው የሚያፈርስ፣ ሰላማችን እና መረጋጋታችን እንድናጣ የሚያደርግ በመሆኑ እዛ ላይ አተኩሬ ትዝብቴን እገልፃለሁ። ይህ ፅሁፍ በጥልቀት በተሰራ ጥናት እና ምርምር ሳይሆን በአጠቃላይ ቅኝት (General Observation) የተመረኮዘ ሲሆን፤ የማነሳው ጉዳይ ሰፋ እና ዘርዘር ያለ ምርምር እንደሚያስፈልገውም መጠቆም እወዳለሁ። በጥልቅ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ አንዳንድ ሁኔታዎችን በሚገባ ያልገለፅኩት ካለ ወይም በጣም ካጋነንኩት አንባብያንን ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

2. ችግሮቻችን ምንድን ናቸው? መልካም አስተዳደር የወቅቱ ቁልፍ ችግር

2.1 በአሁኑ ግዜ የችግሮቻችን አውራ መልካም አስተዳደር ያለማስፈን ችግር ነው ተብሏል፡፡ ለመሆኑ መልካም/ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ምን ማለት ነው?

የመልካም ወይም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ምንነት በጣም አከራካሪና ሰፋ ያለ ሙግት የሚካሄድበት መስክ እንደሆነ ግንዛቤ ዉስጥ በመክተት ነው፤ በዚህ ንዑስ ርእስ ስር ለዚህ ፅሁፍ ሲባል የተወሰኑ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የመረጥኩት። መስተዳድር ወይም አስተዳደር የሚለው ንድፈ ሃሳብ አዲስ ያልሆነና ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው። እንደ ናንዳ (Nanda, 2006: 271) ገለፃ አስተዳደር የሚለው ሃሳብ የትርጉም እልባት ያላገኝ እና ትርጉሙም ልናሳካ በምንፈልገው አላማ እና በምንከተለው ዘይቤ እንደሚመሰረት ታብራራለች። አስተዳደር የነባራዊው ፖለቲካዊ ስርዓት ነፀብራቅ ሲሆን በመጠነ ስፋቱ እና ተዛማጅ ትርጉሙም ከግዜ ወደ ግዜ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ነገር ነው። በፍፁማዊ የዘዉድ አገዛዝ እና ሌሎች የአምባገነን መንግስታት አስተዳደር ሊያሳካ የሚችለው የመጨረሻው አላማ የአስተዳደር ቢሮክራሲያዊ ገፅታው፤ ማለትም ዉጤታማነት እና ብቁነት (ቅልጥፍና) ነው።

ማህበረ -ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገቶችን እና የዴሞክራሲ ጅማሬን ተከትሎ ግን አስተዳደር የሚለው ሃሳብ መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚሉትን በማካተት መልካም አስተዳደርን የዴሞክራሲ ፀጋ አድርጎ መቁጠር የተዘወተረ ነገር መሆን መጀመሩ መገንዘብ ይቻላል። መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ከዉጤታማነት እና ብቁነት የሰፋ እና የገዘፈ ሃሳብ ሲሆን፤ ለአጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የሚቆምና የዜጎችን ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ መብቶች እና ነፃነቶች የሚያስከብርና ማንኛዉምም ዓይነት አድልዎ የማይቀበል ሂደት ነው። ግልፅነት እና ተጠያቂነትም በሲቪል ሰርቪሱ ብቻ የማይታጠር በፖለቲካ አመራሩ እና ተቛማት ሊተገበር የሚገባው ቁልፍ የመልካም አስተዳደር አካሎች ናቸው።

ገብረቭቢ ‘Democracy, Democratic Institutions and Good Governance in Nigeria’ በተሰኘው ፁሁፉ አልካሊ የተባለ ተመራማሪን ጠቅሶ እንደሚለው አስተዳደር ማለት የፖለቲካ ስልጣንን ህዝባዊ ጉዳዮችን ለማስኬድ ማዋል እንደሆነ ይጠቅስና፤ አስተዳደር የሚዳስሳቸው ጉዳዮች ብሎ የህግ የበላይነትን፣ ተጠያቂነትና ግልፅነትን፣ ልማት ተኮር አመራርን፣ ራስን የመግለፅና የመደራጀት መብትን፣ መልስ ሰጪነትን፣ ኃላፊነት መዉሰድን፣ ወካይነትን፣ ዉጤታማነት እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠትን እንደሚያካትት ይገልፃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መልካም አስተዳደር የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ሻቢር ቼማ እንደሚለው “መልካም አስተዳደር ያለዉን ሃብት ለጋራ ችግሮች እንዴት መዋል እንዳለባቸውና በምን አኳሃን መመራት እንዳለባቸው የሚመለከት እንደሆነ ይጠቅሳል። መገለጫ መርሆቹም አሳታፊነት፣ ግልፅነት፣ ተጠየቂነት፣ የህግ የበላይነት፣ ዉጤታማነት፣ ፍትሃዊነት እና ስትራቴጅያዊ ራዕይ መጨበጥን ያካትታል ይላል።” (2005:33).

አዳምስም በተመሳሳይ ስለ ዴሞክራስያዊ አስተዳደር የሚከተለውን ይላል ዴሞክራስያዊ አስተዳደር የህዝባዊ ተቛማት ግልፀኝነት እና ተጠያቂነት ይፈልጋል። ዜጎችም ስለ መንግስት ፖሊሲ፣ ዉሳኔዎች እና ተግባራት መረጃ የማግኝት መብት ሊኖራቸው ይገባል። በኛ አገር ሁኔታ ይህ እንዳይሆን እንቅፋት ከሆነው አንዱ የመንግስት የመረጃ አያያዝ ደካማነት፣ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው አለመገንዘብ እና በዋናነት ደግሞ ሚስጢራዊ እና ሚስጢራዊ የሆኑ መረጃዋች መለየት አለመቻል ነው፤ ይህ ሁኔታ ካልታረመ መሰረታዊ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ስለሚጋፋ ለዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ የራሱ አስተዋፅኦ ማድረጉ አይቀርም። አዳምስ አያይዞም በኃላፊነት ያሉ ሰዎች ለድርጊታቸው እና ለአፈፃፀም ግብራቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላል። የተጠያቂነት እና ግልጽነት መርህ መንግስት አካባቢ ለሚኖረው ሙስና ለመግታት እና የዜጎች ተሳትፎ ለማበርታት ጠቃሚ ነገሮች ናቸው ይላል። ዜጎች ሃሳብን እና ራስን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት እንዲሁም ማንንም ሳይፈሩ ድርጅት የመመስረት እና የተመቻቸውን ድርጅት የመቀላቀል መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያትታል። ከዚህ መረዳት እምንችለው መልካም/ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሲባል ቁንፅል ፖለቲካዊ ሃሳብ ሳይሆን የዜጎችን ስብአዊ እና ዴሞክራስያዊ መብቶችን በአስተዳደር መዋቅር እና ትግበራ ከግምት ማስገባት ማለት እንደሆነ ነው::

እንደ ተመዱ የኤስያና ፓስፊክ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ኮሚሽን አረዳድ መልካም አስተዳደር ስምንት ዋና ባህርያት አሉት ይላል። እነዚህም አሳታፊነት፣ መግባባት ላይ ያተኮረ (Concensus oriented)፣ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ መልስ ሰጪ (Responsive)፣ ዉጤታማ እና ብቁ (ቅልጥፍና)፣ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቃፊ (equitable and inclusive) እንዲሁም የህግ የበላይነት ናቸው ይላል። መልካም አስተዳደር የህዳጣን (Minorities) እና የሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብ እና ድምፅ በዉሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ግምት ዉስጥ መክተትንም ይጨምራል ይላል። አሁን ላለው እና ወደፊት ለሚመጣው ማህበረሰባዊ ፍላጎትም ጭምር ዝግጁ የሆነና መልስ መስጠት የሚችል አቅም እና መዋቅር መፍጠር ነው መልካም አስተዳደር። ሰለዚህ አንድን ሰርዓት መልካም ነው ወይስ መጥፎ አስተዳደር ነው ያለው የሚለዉን ለመገንዘብ ከነዚህ መለኪያዎች አንፃር ነው ማየት ያለብን።

ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት መንግስታዊ ስልጣን የያዙ ሰዎች ላይ ህጋዊ ገድብ ያስቀምጣል። ስልጣን ለተለያዩ የመንግስት አካላት የሚሰጥበት ምክንያትም በተወሰኑ ተቋማት ወይም ግለሰቦች ብቻ ኃይል እንዳይከማች ከሚል እሳቤ ነው። የተለያዩ የመንግስት አካላት በቂ የሆነ አቅም እና ነፃነት ኑሮዋቸው አንዱ መዋቅር ሌላኛዉን የሚቆጣጠርበት እና ህገ መንግስታዊ ሚዛን የሚጠብቅበት አሰራር ያስፈልገዋል። ወታደራዊ ተቋሙም በሲቪልያን ቁጥጥር ስር ማድረግ መቻል ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በጣም ወሳኝ ነው ይላል ፍራንሲስ አዳምስ። እንደ አዳምስ አነጋገር ወታደራዊ ኃይሉን በበላይነት የማዘዝ ስልጣኑ በምርጫ በሚቋቋመው አገራዊ ፖሊሲዎችን በሚያወጣው እና ያለ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ስራዉን በሚተገብረው ሲቪል አስፋፃሚ መሆን አለበት ይላል።

[የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 74/1 እንደሚለው “… ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው” እንዲሁም በአንቀፅ 87/2 መሰረት “የመከላከያ ሚኒስቴር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል” ይላል።]

2.2. የመልካም/ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ችግሮች ስፋትና ጥልቀት

ባጠቃላይ የሃገራችን ሁኔታ ሲታይ መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ አለመቻል፣ ሙስና፣ እና የፍትህ እጦት ሶስት አደገኛ የስርዓቱ በሽታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በሽታዎች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ሁኔታው ሲቀጭጭ ከቁጥጥር ውጪ የመሆን እድላቸው ይሰፋና ማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች ይሆናል፡፡ እነዚህን ሶስት አደገኛ በሽታዎች ለዘመናት ከኛ ጋር የኖሩ እና አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑን የሚገኙ ስለሆኑ ኢኮኖሚያዊ ከሆኑ መንገዶች በተጨማሪ ሌላ መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ በቀጣይነት ግዝፈታቸው እየጨመሩ መሄዳቸው የማይቀር መሆኑ መገንዘብ አለብን:: በአጭሩ ችግሮቹ አብረውን የነበሩና አሁንም እያኗኗሩን ያሉ በሽታዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ መሰረታዊ የስርዓቱ በሽታ ብሎ የዘረዘራቸው ሙስና፤ መልካም ያልሆነ አስተዳደር እና የፍትህ መጓደል እስካሁኑ የተገኙት ድሎችን መና ሊያስቀር እንደሚችል እውቅና መስጠቱም ይበል የሚያስብል ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያለው የዴሞክራሲ ድባብ ሲታይ ዜጎች የሚስማቸውን ቅሬታ ለመግለጽ አብዛኞቹ መንገዶች የሳሱበት ፣ አማራጭ የመረጃ ምንጮች በከፍተኛ ፍጥነት እየቀጨጩ፣ የማበህራት ነፃነት እየተገፋ፣ የመናገር እና በአጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ መብቶች በሚታዩ እና በማይታዩ ዘዴዎች እየተዳከሙ ያለበት ሁኔታ እታዘባለሁ፡፡ መልካም አስተዳደር ህልም የሆነበት ሙስና የእያንዳንዱ መንግስታዊ መዋቅር እና ሰዎች “የተለመደ ተግባር” የሆነበት፣ ፍትህ ከርትዕ ርቆ የጉልበተኞች መጫወቻ እየሆነ በአጠቃላይ ዜጎች በፍርሃት የተሸበቡበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የፍርሃት ዋና መንስኤ ደግሞ ጤንነቱ የተዛባ የፖለቲካ ሁኔታ ነው።

አካፋን አካፋ ካላልን ግብዝነት ይነግሳል፣ ውሸት ኃይል አግኝቶ እውነትን ይተካል፡፡ በመንግስት በኩል ደግሞ የ “ማን አለብኝነት” ትእቢት እና ተቋማዊ አሰራር መጥፋት እና ሌሎች ተደማምረው የአምባገነንነት ዝንባሌዎች (Dictatorial Tendency) እየታዩ ነው፡፡ 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ችግሮች ብሎ የለያቸው ሰናይ ከላይ የገለፅኩት ምስል ነው የሚያሳየን:: ለምሳሌ መቐለ በተካሄደው በኢህአዴግ 10ኛው ጉባኤ ዋና ዋና ድክመቶች ተብለው በጉባኤው ተቀባይነት ካገኙት ካነሳነው ጉዳይ ተያያዥ የሆኑትን ልጥቀስ፡፡ ምንጮቼ በጉባኤው በታዛቢነት ተሳትፎ አድርጎ የነበረዉ ሪፖርተር ጋዜጣና ያነጋገርኳቸው ተሳታፊዎች ናቸው።

$1·         “ህዝባዊነት በግለኝነት እየተሸራረፈ ነው፡፡ ህዝብ የበላይ ወሳኝና ተቆጣጣሪ መሆኑ እየተዘነጋ የግል ጥቅም እና ምቾት ለማሳካት መንቀሳቀስ በኢህአዴግ ውስጥ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

$1·         ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሙስና እየተስፋፋ ነው፡፡

$1·         መልካም አስተዳደር እየጠፋ ነው፡፡

$1·         የፍትህ ስርአቱ እየተዳከመ ነው፡፡     

$1·         ተጠያቂነት እየጠፋ ነው፡፡

$1·         የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ችግር አለ፡፡

ኢህአዴግ ባጭሩ እያለን ያለው “የሙስና፣ መልካም አስተዳደር የማሰፈን እና የፍትህ ችግሮች እየተባባሱ ነው” ነው፡፡ ይህም በመሰረቱ ትክክል ነው። ህዝብን የሚሰማ እየጠፋ ‘እኔ አውቅልሃለሁ’ ባይ እየበዛ፣ ህዝቡ ችግሩ ሲናገር ከተቃዋሚዎች ጋር እያስተሳሰሩ ማሳደድ፣ ዝም ሲል ደግሞ እንደተመቸው አድርጎ ማሰብ፣ እንደ ፓርላማ የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ግዴታዎችን በበቂ ሁኔታ አለመወጣታቸው የስራ አስፈፃሚውን ጡንቻ እያሳበጠ ሄዶ ሄዶ አሁን ላለንበት ሁኔታ አድርሶናል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው ዴሞክራሲያዊ ሁኔታውን ያጠበበው፣ የዚህ መጥበብ ልጆች ናቸው፤ እነ ፍትህ ማጣት፣ ሙስና እና መልካም ያልሆነ አስተዳደር የሚባሉ በሽታዎች፡፡

3. የችግሮቻችን መሰረታዊ ምንጭ ምንድን ነው?

ለበሽታዎቻችን እንደ የአቅም ማነስ፣ ድርጅታዊ ድክመት፣ ያልዳበረ ህዝባዊ የተሳትፎ ባህል የመሳሰሉት ነገሮች መነሻ ምክንያት ሊሆኑ ቢችሉም ዋናው እና ተጠቃሽ ምክንያት ግን አጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እጥረት ነው፡፡ እንከን የለሽ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር እንደሌለና ኢትዮጵያችንም ጀማሪ ዴሞክራሲ የምታራምድ መሆንዋንም እረዳለሁ፡፡ በዚህ ምክንያትም ነው፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራያዊ ስርዓት ለመገንባትም ለመቀልበስም ሊያግዙ የሚችሉ ነገሮች በብዛት የሚገኙት፤ ለዚህም ነው ጀማሪ ዴሞክራሲያችንን ሊቀለብሱ የሚችሉ ኃይሎች እና ሁኔታዎችን በቅጡ ተገንዝበን እና ለይተን በቁርጠኝነት አረንቋውን ማድረቅ ያለብን፡፡ ለዚህም ነው ቲሊ ዴሞክራታይዜሽን መቼም ሙሉ መሆን የማይችል እና የ ኢ ዴሞክራታይዜሽን አደጋ ሊያጋጥመው የሚችል ተለዋዋጭ ሂደት ነው የሚለው። ኢ ዴሞክራታይዜሽን ማለት ቅልበሳ ማለት ነው። በተለያየ አቅጣጫ ተቀራርበው የሚንቀሳቀሱ ሂደቶች ዴሞክራታይዜሽንን እና ቅልበሳዉን ሊያመጡ ይችላሉ ይላል። “Closely related processes, moving in opposite directions, produce both democratization and de democratization”፡፡ ሙለር እና በርግማን እንደሚሉት ዴሞክራሲ ቀላልም ቀጥ ያለም ያልሆነ ግን ደግሞ ሊሳካ የሚችል ነገር ነው:: በነዚህ እና በሌሎች ምክንያት ነው አገሬ ላይ እዉን ሆኖ ማየት የምፈልገው ዴሞክራሲ ሃሳባዊ የሆነና ምንም እንከን የሌለው ዴሞክራሲ አይደለም የምለው፡፡

የአገራችን የዴሞክራሲ ሁኔታ ለጋ ነው ስል የሚከተለውን የቲሊ አባባል ያስታዉሰኛል፤ በቲሊ አረዳድ “We are not trying to explain yes-no swiches between undemocratic and democratic conditions. We are not trying to explain degrees and changes of democracy” ስለዚህ ስለ አገራችን የዴሞክራሲ ሁኔታ ሳወራ ስለ ሂደት እንጂ ህልመኛ ሆኜ መሆን የማይችለውን እና እስከአሁን አለም ላይ የሌለውን ገነት መሳይ ዴሞክራሲ ፈልጌ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እ.ፋ.አ ከ1789 ጀምሮ ፈረንሳይ በትንሹ አራት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ክፍሎች ስታይ በትንሹ ደግሞ ሶስት የዴሞክራሲ ስርዓት ቅልበሳ ግዝያቶች አሳልፋለች፡፡ ዘመናችን የዴሞክራሲ በመሆኑ እንደዚህ ኣይነት የቅልበሳ የቅንጦት (luxury of de-democratization) አማራጭ ግን የለንም። በኛ ሁኔታ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ዴሞከራሲ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እየተንገራገጨ ቢሆንም ሁሉ ግዜ ወደፊት መዙን ማረጋገጥ ይኖርብናል እንጂ አጠቃላይ ቅልበሳ አገሪቱ ወደ አደገኛ ቀዉስ ይመራታል፡፡

የዲሞክራሲ እጦት የተመረጠ እና ልዩ የመጥፎ አስተዳደር ማዳበሪያ ነው፡፡ የፈለገው ልማት ቢመጣ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ መጥበብ ካሳየ ሶስቱም በሽታዎች አለን!! አለን!! አለን!! ምን አባታቹህ ታመጣላቹህ! እያሉ መፈንጨታቸው አይቀርም:: በሽታዎቹ እንዳይፈነጩብን በመሰረቱ የሚከላከልልንን ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት አለን፡፡ ችግሩ ተግባር ላይ ሲዉል ህገ-መንግስቱ ባስቀመጠው መንፈስ (Sprit of the Constitution) አለመተግበሩ ነው፡፡ ከፍ ያለ ኢ-ህገ-መንግስታዊነት ሲበረታ ሶስቱ በሽታዎች የራሳቸው ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ ‘አሸነፍናቹህ፤ ረታናችሁ’ ይሉናል:: አጠቃላይ የዲሞክራሲ ከባቢው እየጠበበ ሲሄድ ሶስቱም በሽታዎች ተጠናክረው፤ ተበረታተው፤ ተባዝተው እና ተኳኩለው ይፈነጩብናል፡፡ በዴሞክራታይዜሽን እና ኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሂደቶች ሁሌም መሳሳብ እና ዉጥረት ይኖራል። መንግስት እንደ መንግስት ግን የዴሞክራታይዜሽን አጋዥ አልያም የኢ-ዴሞክራታይዜሽን አሳላጭ ነው መሆን እሚችለው፤ መሀል ላይ የሚንገዋለል መንግስታዊና ተቋማዊ አቋም ሊኖር አይችልም። ስለዚ ምርጫው አንድ እና አንድ ነው፤ ለዴሞክራሲ መስራት ወይም የፀረ ዴሞክራሲ ኃይል መሆን።

ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ እና ሶስቱ በሽታዎች በተቃራኒ መንገድ ነው ጉዞአቸው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታው ሲሰፋ በሽታዎቹ መጠጊያ እና መሸሸጊያ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ ምሽግ ፈልገው ወይም ቆፍረው ይደበቃሉ፤ልክ የወባ በሽታ ከህክምና በኃላም ቢሆን በሆነ የሰውነታችን ክፍል እንደምትደበቀው፤ ይሄ ለመደበቅ የምታሳየው ባህሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ ሲጠብ ደግሞ በሽታዎቹ ወደ አደባባይ እየወጡ ህጋዊ ልባስ እየተጎናፀፉ መገናኛ ብዙሀንን ጭምር እየተጠቀሙ ይፈነጫሉ፤ ህዝብንና አገሪትዋንም በኃሊት ማርሽ ወደ አዘቀት ይከቷታል፡፡ ከስር የምታዩት ስእላዊ መግለጫ ይህንን ሃሳብ የበለጠ ለማስረዳት በፀሃፊው የተዘጋጀ ነው::

[ምስል አንድ: የዴሞክራሲ ምህዳር ሲሰፋ በሽታዎቹ ይቀጭጫሉ፤ በተቃራኒው የዴሞክራሲ ምህዳሩ ሲጠብ በሽታዎቹ ጎልተው እና ጠንክረው ይወጣሉ።]

ልማት የዴሞክራሲ አካል መሆኑ ሳንዘነጋ፤ ህገ-መንግስቱን የመተርጎም ችግር አለ ሲባል ከዲሞክራሲ አኳያ የተደነገጉት የሲቭል እና ፖለቲካዊ መብቶች ተፈፃሚ አለማድረግ ማለት ነው:: በተጨማሪም በየጊዜው መንግስትን ለማቋቋም በሚደረገው ምርጫ የፍትሃዊነት እና የህዝባዊ ተቀባይነት (Legitimacy) ችግር ሲኖር ነው ህገ-መንግስቱ በአግባቡ እየተተረጎመ አይደለም የሚባለው፡፡

የ2007 ምርጫ ማሸነፍ ያለበት ፓርቲ አሸነፏል፡፡ በእጅጉ ከፍተኛ ድምጽ መመረጡም ይገባዋል እላለሁ፤ ይችን አገር ከውድቀት አስነስቶ በመግቢያ እንደገለጽኩት ወደ ተስፋ ያላት አገር ወደ መሆን አቅጣጫ እየመራት ነው፡፡ አሸናፊነት አይበዛበትም፡፡ የተቃዋሚዎች ድክመት ተጨምሮበት በእጅጉ ከፍተኛ ድምፅ ቢመረጥ አያስገርምም:: ነገር ግን ለምሳሌ ያህል እኔ በመረጥኩበት የምርጫ ክልል እቤት ድረስ የዘለቀ የነበረው መዋከብ እና በአንዳንድ ምርጫ ክልል አንድ ለአምሰት የነበረው አሉታዊ ተጽእኖ ስሰማ፣ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም የነበረው ከፍተኛ አድልዎ ስገነዘብ ምርጫው እንከን የለሽ ነው ሲባል እስቃለሁ። ህዝቦቻችን መብታቸውን ለማስጠበቅ ባልቻሉበት፣ ህገ-መንግስታዊ እና ዴሞከራሲያዊ ተቋሞቻችን ባልጠነከሩበት ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግር ባለበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ዴሞክራሲያዊ ነው ማለት አይቻልም።

በአጠቃላይ ሲታይ ብዙ ማንነቶች፤ በርካታ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፤ መልስ እንሻለን የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ባሉበት አገር አንድ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋሮቹ 100% መቀመጫውን መቆጣጠር የሚያሳየን ነገር፤ አንድም በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ችግር መኖሩን አልያም የምርጫ ስርዓቱ ችግር እንዳለበት ወይም ተግባራዊነት ላይ ችግር እንደነበረበት ነው፤ 100% የሚባል ውጤት አስቂኝ ግን ደግሞ አደገኛ ነው ፡፡ ይሄ ዉጤት አርቆ ለሚያስብ ሰው የአደጋ እንጂ የድል ምልክት ተደርጎ መቆጠር አይችልም። መሬት ላይ ያለዉን የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ የምክር ቤት ሁኔታ የስጋት እንጂ የኩራት ምንጭ መሆን አይችልም።

የሰፋ ዴሞክራሲያዊ ምህዳር ሲኖር የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በእኩልነት አለን የሚሉትን አማራጭ ለህዝቡ እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል፡፡ ዴሞክራሲ ማለት እኮ የተለያዩ ሃሳቦች በእኩልነት ለዉድድር የሚቀርቡበት ፖለቲካዊ ገበያ ማለት:: ይህ ተጨባጭ ምሳሌ የሚነግረን ነገር አንድ እና አንድ ነው፤ እሱም አጠቃላይ የዲሞክራሲ ምህዳሩ ሲጠብ ሶስቱም በሽታዎች በግላጭ ባንዲራቸውን ለማውለብለብ እንደማይቸገሩ ነው፡፡

ህዝቡ በሶስቱም በሽታዎች ሲጠቃ ለምንድን ነው በሚሰማ ሰላማዊ ሰልፍ፤ ህዝባዊ ስብሰባዎች፤ ተወካዮችን በመሳብ (recall) እና ሌሎች መንገዶች ተጠቅሞ ምሬቱን ማሰማት ያልቻለው? የሚለው በደንብ መጤን አለበት፡፡ ልክ በ10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ እንደተገለፀው ‘ደህና፤ ይስተካከሉ ይሆናል’ ከሚል መነሻ ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች ምክንያቶች ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አለብን፡፡ ለምሳሌ ህዝብ ዝም ያለው መብቶቹን የሚያረጋግጥበት ሁኔታ ስላላገኘ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ መሠረታዊ በሆኑ የመኖር ጉዳይ ላይ እያማረረ እለታዊ እንቅስቃሴውም ጭምር ማከናወን እየተሳነው እያለም በግልጽ ተቃውሞውን ማሰማት ያልቻለው ለምን ይሆን? ወይስ ተቃዉሞ መግለፅ የሚያስከፍለው ዋጋ ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት ነው? ወይስ ተባብሮ የመስራት ችግር (Collective Action Problem) ነው? ወይስ አፋኝ መዋቅሮች አላንቀሳቅስ ብለዉት ነው?

በውሃ፤ መብራት እና ሌሎች አገልግሎቶች በብዛት የሚማረር ህዝብ እንኳን መብቴ ተጣሰ ብሎ ውስጥ ለውስጥ ከማንሾካሾክ አልፎ መብቱን ሲያስከበር አይታይም:: ለምን? የሚለው ጥያቄ በጥልቀት ስንመረምር ነው ብዙ ነገር ሊገባን የሚችለው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ አጠቃላይ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታው እየሰፋ እና አመቺ እየሆነ ካልሄደ ሶስቱም በሽታዎች ህዝብ ላይ መፈንጨታቸው አይቀርም፡፡ ሁኔታዎች እንዲህ ባለ ጠባብ የዲሞክራሲ ምህዳር ሲቀጥል የሚያስከትሉት መዘዝ ዘርፈ ብዙና ብዙ ዋጋ ያስከፈለና ወደፊትም የሚያስከፍል ስለመሆኑ ለመተንበይ ነብይ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ GTP 1 በሚፈለገው መጠን ተግባራዊ እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን GTP 2ንም ጭምር አደጋ ላይ ሊጥለው የሚችለው ይሄው ጠባብ የዲሞክራሲ ምህዳር ነው፡፡

ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የዜጎች ተስፋ እየተሟጠጠ ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ የመሆኑ እድል ይሰፋል፡፡ ይህን መሰል ሁኔታም ከውስጥም ከውጪም ለነሱ ለሚችሉ ፅንፈኛ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር አገሪቷን ወደአላስፈላጊ መንገድ ሊመራ ይችላል፡፡ ፍትህ ተራ ፍርድ የማግኘት ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍትህ የማህበራዊ ተቋም የመጀመርያ ፀጋው ነው ይላል ጆን ራዉልስ፡፡ ሙስናና መልካም ያልሆነ አስተዳደርም ሃገርን ሊበትን የሚችል፤ እየታየ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ገደል የመክተት አቅም ያላቸው ስርዓታዊ በሽታዎች ናቸው፡፡የሶስቱም እናት ደግሞ የጠበበ ወይም የኮሰመነ የዲሞክራሲ ምህዳር ነው፡፡

4. በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩ በማስፋት መልካም አስተዳደርን ለምን አላረጋገጠም?

አሁን ካሉት በርካታ ፓርቲዎች የሃያኛው እና ሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን ቅይጥ አተሳሰብ ያላቸው ናቸው። የ1960ዎቹ ትውልድ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሌላው ዉድቅ ነው” የሚለው አስተሳስብ በትጥቅ ግዜ በነበረው ሁኔታ የድርጅቶች የመጥፋት አጋጣሚ በነበረበት ግዜ የተለያዩ ሃሳቦች እንዳይንሸራሸሩ የማያበረታታ ሁኔታ ሲፈጠር እየጎለበተ ሁኔታዎች ሲረጋጉ እየቀነስ እንደገና ድርጅቶቹ ከዓላማዎቻቸው በላይ ሲሆኑ “ድርጅታችን ልትጠፋ ነው፤ እንዳትጠፋ እናድናት” የሚለው አስተሳሰብ አሁንም በሠላሙ ግዜ ሲንጸባረቅ ይታያል:: ዴሞክራሲ የሚጠይቀው ተጣጣፊነት፣ መቻቻል እና የጋራ መግባባት በተወስኑ አመራር እና ወጣት ክፍል ቢንጸባርቅም አሁን ያለው ገዢ አስተሳሰብ ግን ያለመታረቅ ባህል፣ የመጋፈጥ ፖለቲካ እና መራራቅ (uncompromising militancy, confrontational politics and polarization) ነው።

ፈጣሪ ለኢህአዴግ ብቻ ልዩ ስጦታ እንደሰጠ በሚያስመስሉ ሁሉ “ከኢህአዴግ መንገድ ውጪ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው” የሚል አስተሳሰብ ህዝቦቻችን አማራጭ ሓሳቦችን ተዘርዝረው እና ተደራጅተው በዚህ መሠረት በፈለጉት ጉዳይ ላይ ይህን አማራጭ መሰረት አድርገው እንዲወስኑ ዕድል አይሰጣቸዉም። 1992-1993 በኢህአዴግ ዉስጥ የነበረው የዉስጥ ቀዉስ (Intra-party crisis) አፈታት የሚያሳየንም ይህንኑ ነው። “አንጃዎች” የተባሉት ከሌላኛው የፓርቲው ወገን የነበራቸው ልዩነት ለህዝቡ ለማቅረብ የመንግስት ሚዲያ እድል ነፈጋቸው። ያሸነፈው “አንጃ” ግን የመንግስት ሚድያ ልክ የኢህአዴግ ሚዲያ እንደሆነ በማድረግ እንደፈለገ ሲጠቀምበት ያለ ምንም ሃፍረት ነበር። ይህ አስተሳሰብ እስካልተወገደ ድረስ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት አጠራጣሪ ነው። ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን በሁሉም መልኩ እየኮሰመነ እንዲሄድና ህገ-መንግስቱም በታለመለት መንፈስ እንዳይተገበር እያደረገ ያለ ይመስለኛል፡፡ በመቐለ ከተማ በግላጭ በአደባባይ ተቋዋሚዎች “ኳኺቶ” (አደገኛ እሾህ) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው መወገድ እንዳለባቸው አረም ተቆጠረው መቅረባቸው አሳፋሪ እና ፀረ ህገ-መንግስታዊ የሆነ ድርጊት ነው፡፡

ዴሞክራሲ በአለም ዋና አጀንዳ በሆነበት ሁኔታ በኛ ሃገርም ተደጋግሞ ይዘመራል። በ 1992 ዓ.ም እና 1994 ዓ.ም በኢህአዴግ እና በመንግስት የቀረቡት ጹሁፎች በቀዉስ ማግስት የተፃፉ ናቸው። ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በተነፃፃሪ ስለ ዴሞክራሲና ተቋሞቹ ጥርት ያለ ሃሳብ አለው። እነዚህ ዶክመንቶች ቀዉሱ ካለቀ በኃላ፤ ማለት መረጋጋት ከተረጋገጠ በኃላ፤ ሳይተገበሩ ሲቀሩ ሼልፍ ማሳመርያ ይሆን እንዴ የተፃፉት? እንድል ያደርገኛል። ዋናው ችግሩ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ከአፋ በላይ ሄዶ ሊዋሃደን አለመቻሉ ነው። Internalize አልተደረገም።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል የነበረዉን አደረጃጀት እና አስተሳሰብ በመሰረቱ ሳይቀይር ነው መንግስትነትን የቀጠለው። እዚህ ጋ መሰመር ያለበት ጉዳይ የትጥቅ ትግል task እና መንግስት ከሆነ ወዲህ የሚኖሩት tasks በአጠቃላይ በተለይ ከዴሞክራሲ ስርኣት በመሰረቱ የተለያዩ መሆናቸው ነው። በትጥቅ ትግል ወቀት አንድን ህዝብ ወይ አካባቢ በብቸኝነት እንድትቆጣጠር የሚያስገድድ ህዝቡን በዋናነት ደርግን ለመድምስስ ሞቢሊዝ ማድረግ ሲሆን በኢፊዴሪ ሕገ-መንግሰት ግን ሕብረ-ፓርቲ ስርኣት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ኢህአዴግ ለሕብረ-ፓርቲ ስርኣት በተሟላ ሁኔታ አልተዘጋጀም፡፡

ከድህነትና ከስላም ማጣት የባሰ የህዝብ ጠላት የለምና፤ በፀረ-ድህነት ትግሉ በስላም ማረጋግጥ አመርቂ ወጤት እየተመዝገበ በመሆኑ ህዝባዊነትና የዓላማ ፅናት የሚያሳይ ቢሆንም በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዙሩያ እየታዩ ያሉት መሰረታዊ ችግሮች ህዝባዊነቱ እየተሸረሽሩ ድርጅቱ በመንታ መንገድ እየተጓዘ ይገኛል:: በቀጣይነት የሚማር ተማሪ የሆነ ድርጅት (learning organization) መሆኑ እያቋረጠ በመምጣቱ አቅሙ እያሟጠጠ ምናልባትም ከ GTP2 በኋላ ወገቤን የሚል ደርጅት እንዳይሆን ያስጋል፡፡ ሁኔታው መሰረታዊ ለውጥን ይጠይቃል፡፡ የትውልድ እና አስተሳሰብ መተካካት የሚጠይቅ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ እያየን ያለነው መድረኩ የሚፈልገው መተካካት ሳይሆን መሸጋሸግ ነው። ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ እና ብቃት ያለው መጪዉን ለመምራት የሚችል በአንፃራዊነት ሲታይ በዴሞክራቲክ ሁኔታ ያደገ ወጣት ሆኖ ህዝባዊ ተቆርቋሪነቱ የላቀ ሙሁር ወደ ስልጣን ከማምጣት እርስ በርሱ ይህ ይሻላል፣ ያኛው ብዙ ዓመት ስርተዋል ይተካ፣ አይነት አባካኝ የሰዎች ዝውወር ነው እየተመለከትን ነው፡፡ ግዜው ቀጣይነት ያለው የአስተሳሰብ ለወጥ ሲጠይቅ ይህን የሚያቀላጥፍ ሂደት አልተደራጀም፤ በእኔ አረዳድ ወጣት ሆኖ ህዝባዊ ተቆርቋሪነቱ የላቀ ሙሁርና ኢህአዴግ ገና አልተቀራረቡም። ኢህአዴግ ያለማውን ሙሁር ወጣት መጠቀም የማይችል ድርጅት ይመስለኛል፡፡

በመንግስት መስርያ ቤቶች ያለው አመዳደብ በብቃት ሳይሆን ከገዢው ፓርቲ ባለው ቅርርብ በመሆኑ ጥቅመኛ (Opportunist) እንዲነግስ ያደርጋል። በማይገባው ቦታ የተመደበ ብቃት የሌለው ሰው ዋናው መሳሪያው ኢ-ዴሞክራስያዊ አካሄድ ነው። ይህ የሚሆነው በራሱ ስለማይተማመን ነው። ተቋማት ማእከል ተደርጎ የተሰራ ስራ በጣም ደካማ በመሆኑ የተሻለ አስተሳሰብ እና ብቃት ያላቸው እየደገፉ ወሳኝ ቦታዎችን እንዲይዙ ማድረግ አልተቻለም። እላይ የተጠቀሰው አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ ዴሞክራሲ ሊስፋፋ አይችልም። አዲስ አስተሳሰብና ብቃት ባለው አዲስ ትውልድ ሲተካ ነው ዴሞክራሲ የሚያብበው። ይህ ለማድረግ 24 ዓመታት እጅግ ብዙ ነው ባይባልም ትርጉም ያለው ለውጥ ሊመጣ ይችል ነበር፡፡

5. የመፍትሄ ሀሳቦች

ብዙ ጊዜ ኃላፊነትን ወደታችኛው እርከን ማሻገር በተለመደበት አህጉር ኢህአዴግ በድፍረት ዋናው ተጠያቂ የበላይ አመራር ነው ብሎ ማለቱ ምስጋና እንድቸረው ያደርገኛል፡፡ በሽታውን እና ምልክቶቹን እውቅና ሰጥቶ ኃላፊነት መውሰድ ለለውጥ ሂደቱ እንደ መጀመሪያ እርምጃ መቆጠር አለበት፡፡ ከባዱ ስራ ግን ቀጥሎ መከሰት ያለበት እርምጃ ላይ ነው፤ ከባድ እና ውስብስብ የሚሆነብት ምክንያትም ትግሉ ከሞላ ጎደል ግልፅ ከሆነ ዉጫዊ ኃይል ወይም ተቋም ጋር ሳይሆን ከገዢው ፓርቲና መንግስታዊ መዋቅር ይዘው ከሚገኙ አመራር እና የነሱ ተባባሪዎች ጋር መሆኑ ነው። ባጭሩ ኃላፊነት የወሰደው የበላይ አመራር ከሆነ ትግሉም እዛ ጋር ስለሚሆን ፈታኝ እና ውስብስብ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ የኢህአዴግ 10ኛው ጉባኤም ያስተጋባውም ወደፊት ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው፡፡

ከፍተኛ አመራሩ (በደፈናውም ቢሆን) አደገኛ ሆነው ለተገኙት በሽታዎች ዋና ኃላፊነት ወሳጆች እኛው ነን ብለዋል። በርግጥ ስልጣን ኃላፊነትን ጭምር ተሸክሞ ስለሚመጣ በዴሞክራሲ በበለጸጉ አገራት ይህ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ እንደ ምልአት ህዝቡና የአህአዴግ አመራር ግንዛቤ በግዜ ተፈትኖ ስራውን በአግባቡ ማከናወን ሲገባው ድክመት ያሳያው አመራሩ ነው ማለቱ ባጭር ግዜ ሲታይ ህዝባዊ ተቀባይነት እና እምነት ሊጣልበት ቢችልም (ሃቅን በመቀበላቸው ምክንያት) ተከትሎ ሊመጣ የሚገባው ቀጣይ እርምጃ ካልታከለበት ግን ኃላፊነት ወስደናል የሚለው ውሳኔ ትርጉም አልባ ከመሆን አልፎ ተመልሶ ከፍተኛ አመራሩን ጥርስ ውስጥ የሚያስገባ ነገር መሆኑ አይቀርም፡፡

ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቼ ስቃኝው መንግስት ከሁለት እና ሶስት አመት በኃላ ‘እንዲህ ብለን ነበረ’ እያለ ችግሮቹ ሳይፈታ ሸፋፍኖ የመሄድ እድል አይኖረውም ማለት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ኃላፊነት ወስጃለሁ ሲል ከሙስና፣ መልካም ካልሆነ አስተዳደር እና የፍትህ መጓደል አኳያ እንዴት ነው በዝርዝር መታየት ያለበት? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው:: ኃላፊነት የምንወስደው እኛ የበላይ አመራር ነን የሚለው ውሳኔ በሆነ አይነት ህጋዊ፣ አስተዳደራዊ ወይም ፖለቲካዊ እርምጃ ካልታጀበ ትርጉሙ ምንድ ነው?

መፍትሄው ህዝብን ማእከል ያደረገ እንቅስቃሴ መሆን እንዳለበት የኢህአዴግ 10ኛው ጉባኤ ጭምር አመላክቷል፡፡ ሆኖም የመፍትሄው እንቅስቃሴ (ንቅናቄ) ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መሰረት ያደረገ ካልሆነ ዘላቂነት ባለው መንገድ የሚፈለገው ውጤት አይገኝም፡፡ እነዚህ ተቋማት ለዴሞክራሲ ንቅናቄው ዋስትና መሆን እንደሚችሉት ሁሉ፣ እየጎለበተ ላለው ፀረ ዴሞክራሲ ዝንባሌም መሳርያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራያዊ ተቋማት ስል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ስራ አስፈፃሚው ህግ ተርጓሚ በየእርከኑ ያሉትን ኮሚሽኖች እና ባለስልጣን መስርያ ቤቶች የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሲቪል ማህበረሰቡን የሚያካትት ሰፊ ሃሳብ ነው፡፡

ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ብቻ ለማየት መርጭያለሁ፣ ምክንያቱም ሁሉንም ተቋማት ማየት የማይቻልና የተመረጡበት መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ ለነዚህ ሶስት ተቋማት የሚደረግ መሠረታዊ ለውጥ ለአጠቃላይ የዴሞክራሲ ንቅናቄው እንደ መነሻ ከመጥቀም አልፎ የንቅናቄውን ቀጣይነትም ስለማያረጋግጥ ጭምር ነው፡፡ ይህ ሠላማዊ ንቅናቄ ካለ ስራ አስፈፃሚው ቅን እይታ ተሳትፎና አመራር ሊሳካ እንደማይቻል እምነቴ ነው፡፡ ሆኖም መደረግ ላለበት የዴሞክራሲ ንቅናቄ የጎላ ተቃውሞ የሚመጣዉም ከስራ አስፈፃሚው እንደሚሆን ይገባኛል፡፡ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ስራ አስፈፃሚ አካል ብዙ ስልጣኖች፣ አለም አቀፍ ትስስሮች፣ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም፣ አደረጃጀት፣ ታንክ ያሉትና የደህንነት ተቋማት የሚያንቀሳቅስ አካል በመሆኑ የዚህ ክፍል ተቃውሞ ክብደቱ እጅግ የጎላ ያደርገዋል፡፡

ላሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዕውቅና መስጠት እና ተያይዞ የመጣው የአመራሩ ኃላፊነቱ የኛ ነው የሚል ድምዳሜ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም የችግሮቹ መሠረታዊ መንስኤዎች እና ሊወሰዱ ስለሚገባቸው መፍትሄዎች ግን በጥልቀት የታየ አይመስለኝም። በተለይ ከ 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ማግስት በአንድ በኩል የመቀዛቀዝ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች ቢኖሩም ብዙ የሚያስጨንቁ አይደሉም የማለት እና የማጣጣል አዝማምያዎች እየታዩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክርቤቶችን አስመልክተው፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀም ሚዲያን አስመልክተው የተናገሩት ነገር ገንቢ እና አበረታች ቢሆንም ሌሎች የመንግስት አካላት ግን ችግሩ ቀለል አድርገው ሲመለከቱ እያየን ነው። ይሄ ተቃርኖም የራሱ ተፅእኖ ሊያሳድር ስለሚችል ሊታሰብለት ይገባል። አሉ ለተባሉት ችግሮቻችን ተቋማዊ መልክ ያለው የዴሞክራሲ ተቋሞች ግንባታ ነው መሰረታዊው መፍትሄ። እነዚህ ተቋማት ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት ተገቢ ስራቸዉን በአግባቡ ማከናወን ሲችሉ ነው።

ከአዘጋጁ፡- (የዚህን ጹሑፍ ሙሉውን ቅጂ ማግኘት ለምትፈልጉ የሚከተለውን ድረገፅ መጎብኘት ትችላላችሁ፡፡ (www.hornaffairs.com)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
912 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us